ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, May 3, 2023

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን አንዳንዶች ለማጣጣል በምትሞክሩት ደረጃ ዕውን ሀገር አጥፍቷል? እናንተ ጠቅላይ ሚንስትር ብትሆኑ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች እንዴት ነበር የምትፈቷቸው?==========
ጉዳያችን ምጥን
==========

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ለኢትዮጵያ በመስራት፣በማሰብ እና አዳዲስ ሀሳቦችን በማፍለቅ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የሔደችባቸው መንገዶች የፈተና እና የችግር ብቻ እንዳይሆኑ ትልቅ ድርሻ ተወጥተዋል። ይህንን ዕውነታ መጋረድ ምን ያህል አሳዛኝ እና ኢፍትሃዊነት እንደሆነ አይገባኝም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገና ለፓርላማ ንግግር ሳያደርጉ ጀምሮ ከኋላ ታሪካቸው በመነሳት በከፍተኛ ተስፋ ከደገፉት ውስጥ ነኝ። ጠቅላይ ሚኒስትሩን በዓይን ፊት ለፊት ያየኋቸው በኦስሎ የኖቤል ሽልማት ለመቀበል በተገኙበት የኦስሎ ማዘጋጃቤት አዳራሽ ተገኝቼ ሽልማታቸውን ሲቀበሉም ሆነ ታሪካዊ ንግግራቸውን ሲያደርጉ በዝግጅቱ ለመታደም በገጠመኝ ዕድል ጊዜ ነው። ከእዚህ ውጪ የማያቸውም የምሰማቸውም በመገናኛ ብዙኃን ነው። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደማንም ሰው ከስህተት ነጻ እንደማይሆኑ አምናለሁ። በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሆነውን ሁሉ ለእኔ አዎን! ለእኔ መለኪያዬ እርሳቸው  በዘር እና በጎሳ ፖለቲካ እንዲሁም ለ27 ዓመታት በነቀዘ አስተዳደር የተጎሳቆለች ኢትዮጵያን መረከባቸው እና እርሳቸው ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ይህች በተቋማቷ ብቻ ሳይሆን በአካቢያችን እና በአፍሪካ ደረጃ የተጎሳቆለ ጥግ ላይ የቆመች ሃገር እንዴት ከግራ እና ከቀኝ የነበረውን መጓተት  አንዴ ወደ አንዱ ሌላ ጊዜ ወደሌላው እየተጎተተ ሃገር ሲንገላታ እርሳቸው ያንንም ያንንም ለመያያዝ እየደከሙ የሄዱበት አስቸጋሪ መንገድ ሁሉ ሲታሰብ በእርሳቸው ቦታ ብንሆን ምን ነበር የምናደርገው? የሚለው ከማሰብ በመነሳት ነው።

አዎን! ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግ ማስከበር ላይ ችግሮች እስኪያድጉ የመጠበቅ እና አንዳንድ ጉዳዮች ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሲኖዶስ የመክፈል ሙከራ ላይ መጀመርያ የያዙበት አያያዝ እና ሌሎች ላይ የፈጠሩት ክፍተት በደንብ ይገባኛል። ለእኔ አልገባህ ያለኝ አንዳንዶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆን ብለው ሀገር የማፍረስ ዓላማ ያላቸው አድርገው የሚያቀርቡት ብቻ ሳይሆን መንገዳቸው የጎሳ ፖለቲካ አዋጪ ነው ብለው የሚያምኑ አድርገው የሚያቀርቡት ኢተአማኔ የሆነው ጉዳይ ነው። የጻፏቸው የመደመር መጽሐፍ ላይ የጎሳ ፖለቲካ እንደማያዋጣ ብቻ ሳይሆን መደመር ብቻ አማራጭ እንደሆነ በሚገባ ተንትነው ገልጸው ጽፈውታል። አንድ ሰው ያላመነበትን በእዚህን ያህል የተብራራ እና ከውስጥ ፈንቅሎ በወጣ ስሜት ስለ መደመር እንዴት ይጽፋል?

ለኢትዮጵያ አንድነት ቤተመንግስቱ ትቶ ዘመቻ ለሔደ፣ የኢትዮጵያን ቤተመንግስት ለማደስ ለሰራ ብቻ ሳይሆን የቀደሙትን ነገስታት ሙዜም ላስቀመጠ፣ በጦርነት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ካቆመ ብሎ ለሰላም ደም ከተቃባቸው ጋር በሰላም አብሮ ገበታ ለተቀመጠ፣ የዓባይ ግድብ ብቻ ሳይሆን መከላከያ፣አየር ኃይል፣የትምሕርት ፖሊሲን፣የወደቀውን የልማት ባንክ፣ የተዳከመው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና ሌሎችን የኢትዮጵያ ተቋማት መልሶ ለማቆም ሥራዎችን በመስራት ዓይነተኛ ለውጥ ላመጣ መሪ የምንሰጠው የማጥላላት ደረጃ ዕውን ሰውየውን የሚመጥን ነው? ዐቢይ ዕውን ማኅበራዊ ሚድያው ብቻ ሳይሆን አንዳንድ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ሃሳባቸውን የሚሰጡ ፖለቲከኞች እንደሚሉት ነው? ነው ወይንስ ለእኔ የማይታየኝ ለሌላው የሚታየው ሌላ ዓለም አለ? 

እዚህ ላይ አሁንም እደግመዋለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሸኔ አንጻር እና የሸኔ ጽንፈኛ በኦሮምያ የስልጣን መዋቅር ውስጥ ገብተው እንደፈለጉ ሲሆን ወሳኝ እርምጃ አለመውሰዳቸው በተመለከተ አሁንም የእኔም ቅሬታ ነው። ይህም ሆኖ ግን ይህንን በዓላማ እና በተንኮል ኢትዮጵያን ለመጉዳት ብለው ነው ብዬ ሳይሆን እሳቸው ችግር ይፈታል የሚሉበት የራሳቸው ዓለም ውስጥ የገቡ ሆኖ ይሰማኛል።በእዚህ ሁሉ ሂደት ላይ ከወለጋ በተፈናቀሉት አንጻር እና አሁንም የኦሮምያ ክልል በአዲስ አበባ ዙርያ እና በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ እያደረሰ ያለው ግፍ ዙርያ የወሰዱት እርምጃ አለመኖሩ ሌላው ተጠቃሽ የመንግስታቸው ተአማኒነት ብቻ ሳይሆን ብዙ ሕዝብ ተስፋ እንዲቆርጥ ያደረገው ነው። 

ይህ በእንዲህ እያለ፣
  • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን ባይመጡ ኖሮ ወደኋላ አምስት ዓመት እንሂድ እና በኦሮምያ እና በአማራ መካከል የነበረው የዚያን ጊዜ ውጥረት ወዴት ይደርስ ነበር? እዚህ ላይ የዛሬ አምስት ዓመት የነበረውን የለውጡ ሂደት ሲጀመር የነበረውን አውዳሚ አካሄዶች ሁሉ እናስታውስ።
  •  እርሳቸው በሔዱበት ደረጃ በደረጃ ስልጣን የመረከብ አካሄድ ባይኬድበት ኖሮ ህወሓት ስልጣኑን ይለቅ ነበር?
  • የዓባይ ግድብ በተዝረከረከበት ሁኔታ አሁን ያለበት ደረጃ ይደርስ ነበር?
  • ተዳክመው የነበሩት የኢትዮጵያ ቁልፍ ተቋማት መከላከያ፣አየር ኃይል፣የልማት ባንክ፣የትምሕርት ፖሊሲ፣ የክክሎች የፌድራል መንግስት አካል መሆን፣ የሱማሌ የአብዲኤሊ የመገንጠል ሙከራ አደጋ፣ ከኤርትራ ጋር የተሻሻለው ግንኙነት፣የህወሃት የዙር ጦርነት እና የሃገር ህልውና አደጋው፣ቆይቶም ወደ እርቁ ለመምጣት የተሄደበት ሂደት ሁሉ የመሪው የነገሮችን አጠቃላይ ሁኔታ የመረዳት አቅም ውጤት አይደለም?
በመጨረሻ ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች ሁሉ እኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ብንሆን የቱን አስቀድመን የቱን እናስከትል ነበር? እስኪ እራሳችንን እንጠይቅ። ፈተናዎች ነበሩ። አዎን! እጅግ የሚያሳዝኑ ፈተናዎች አልፈናል። እነኝህ ፈተናዎች ግን እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ባይመጡም የሚቀሩ ፈተናዎች አይደሉም።ይልቁንም ክልሎች አሁን ከምናየው በላይ የተመሳቀለ አደጋዎች ውስጥ እንገባ እንደ ነበር ነው የሚገባኝ። በትንሹ የሱማሌን የአብዲ ዔሊ የመገንጠል ሙከራ በራሱ ለኢትዮጵያ ትልቅ አደጋ ይዞ ይመጣል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአቅም፣በርዕይ እና በአፈጻጸም ፍጥነት እና ጥራት እንዲሁም ክትትል የሚታማ መሪ አይደለም። ሰውየው አንድ ነው። አስር አይደለም። በብዙ ችግር በታጠረች እና ሀገሪቱን ለማጥፋት የ24 ሰዓት ጊዜ ወስደው በሚሰሩ የውጭ እና የአካባቢ ሀገሮች ውስብስብ መንገድ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውስጥ ሆነን የሚሰራውን ብቻ ሳይሆን ሲያነጥስ ሁሉ ተንኮል አለበት እያልን ነገር በመጎንጎን የማናሰራው ሁሉ ተደምረን እና እነኝህን ሁሉ ተቋቁሞ መስራት በራሱ አንድ እራሱን የቻለ ፕሮጀክት ነው። እስኪ ከመተቸት እና ከማብጠልጠል በላይ ይህ የኢትዮጵያ የጋራ ጉዳያችን ነው ብለን ያገዝነው ሥራ ምንድን ነው? በህልውናው ዘመቻ የነበረውን ተሳትፎ ሳንጨምር ማለት ነው። በህልውና ዘመቻ የብዙዎች ርብርብ ስለነበር።

አሁንም በአዕምሮዬ ያለው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን አንዳንዶች በእዚህ ደረጃ ለማጣጣል የምትሞክሩትን ያህል ሀገር አጥፍቷል? እናንተ ጠቅላይ ሚንስትር ብትሆኑ እነኝህን ችግሮች እንዴት ነበር የምትፈቱት? የሚለው ነው።
አንዳንዴ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ወጥ ሲጨልፍ ስናየው፣መንገድ ሲጠርግ ስንመለከት ሌላው ቀርቶ በመሪ ደረጃ ዝናብ ሲመጣ ዣንጥላ ሳያስይዝ እራሱ ይዞ እና ዝቅ ብሎ ስናየው እንደፈለግን ለመተቸት ተመቸን መሰለኝ። ስንወቅስ እና ስንተችም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የሚባል ነገር አንርሳ እንጂ! የሰፈራችንን የዕድር ሊቀመንበር የምናከብርበትን ክብር ሰጥተን ከእዝያ የሚሰማንን መውቀስ የወግ ነው። ሰውየው ግን በማኅበራዊ ሚድያ በሚሉት ደረጃ የሀገር አጥፊ ነው ብሎ ማመን ከቀላል አመክንዮ የመራቅ ችግር ብቻ ነው።ለሁሉም ጊዜ እና ታሪክ ያሳየናል። ይህም ሁላችንም ዕድሜ ካደለን ነው።ባጭሩ የአንዳንዶቻችን አወቃቀስ መሰረተ ቢስነቱ ቢብስብኝ ነው ይህንን ለማለት የተገደድኩት።
=========================////===========

No comments:

ለፕሮፌሰር መራር፣ልደቱ፣ጀዋርና ኢንጅነር ይልቃል ዘፈን ይህችን ዜማ እንምረጥላቸው።

በቅድምያ ስለ አራቱም የመግቢያ ማስታወሻና ወቅታዊ ሁኔታቸው። አራቱም ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም ብለው ኢትዮጵያን ለእርስ በርስ ጦርነት ሊነክሯት ሞክረዋል።ዝርዝሩን፣ከእነማን ጋር መክረው እንደነበር፣ለኢትዮጵያ ደግሰው...