ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, August 30, 2019

በሁለት ትውልዶች ውስጥ ለመስዋዕትነት የተዘጋጀ የዘመናችን ምሳሌ - አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የአሁኑ ቅዳሜ በኦስሎ፣ኖርዌይ የምስጋና ዝግጅት ላይ ይገኛሉ።ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተጋብዘዋል።

በ1960ዎቹ  መጨረሻ እና የ1970ዎቹ የፖለቲካ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፈዋል።በ1984 ዓም በተፈጠረው የመንግስት ለውጥ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለውጡን ለማስተካከል ከዳር ሆኖ ከመመልከት ከውስጥ ሆኖ መስራት ይገባል በማለት ለመስራት ሞከሩ።ለውጡ በለየለት የጎሳ ፖለቲካ ውስጥ እየተዘፈቀ በመምጣቱ  መቀጠል አልቻሉም።በ1997 ዓም ምርጫውን ተከትሎ የቅንጅት መሪዎች ሲታሰሩ የማስፈታቱን ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ካስተባበሩት ውስጥ ነበሩ። በመቀጠል የግንቦት 7 በኃላም የአርበኞች ግንቦት 7 ዋና ፀሐፊ በመሆን ከየመን እስከተጠለፉበት ጊዜ ድረስ በኤርትራ በረሃ ወርደው የትጥቅ ትግል አስተባብረዋል።በቅርቡ ለአርት ቴሌቭዥን በሰጡት ቃለ መጠይቅ የትጥቅ ትግል ኢትዮጵያን እንደ ሶርያ እና ሊብያ ሊከፋፍል እንደሚችል ከየመን ከመጠለፋቸው በፊትም ድምዳሜ ላይ እንደደረሱ አስታውቀዋል።

አቶ አንዳርጋቸው የተሰማቸውን በግልጥ በመናገር ይታወቃሉ።በ1984 ዓም ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ በወቅቱ የነበረው የዲያስፖራ ስብስብ ለምን? በሚል ሞግቷቸው ነበር።ሆኖም ግን ለኢትዮጵያ እስከጠቀመ ከሩቅ ሆነን ከምናበላሽ ገብተን ሊስተካከል የሚችለውን መስራቱ ይሻላል ብለው ሞግተዋል። በኃላም የግንቦት 7 ንቅናቄ ወደ ኤርትራ ሲገባ እንዲሁ ቀላል ያልተባለ ሙግት ቀርቦባቸው ይህንንም ተጋፍተው በማስረዳት እስከለውጡ ድረስ ገፍተውበታል። አቶ አንዳርጋቸው በሁለቱም ትውልድ ውስጥ ሆነው ሲታገሉ ያመኑበትን በግልጥ በመናገር የሚታወቁ ናቸው።

እኝህ ሰው በአሁኑ ቅዳሜ ጳጉሜን 2/2011 ዓም  (ሴፕቴምበር 7/2019 ዓም) በኦስሎ፣ ኖርዌይ የምስጋና ዝግጅት ላይ ይገኛሉ።ከህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን ይመልሳሉ።በዝግጅቱ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተጋብዘዋል። ቦታው ''አንቲራስስት ሰንተር'' ፣ አድራሻ Storgata 25, 0184 Oslo ነው።

አንዳርጋቸው ማለት አንተ ከቤትህ የሞቀ አልጋ ላይ ሆነህ ለኢትዮጵያ እና ላንተ ሊሞትልህ በረሃ የገባ ጀግና ባለውለታህ ነው።ቢያንስ በዝግጅቱ ላይ አለመገኘት ውለታ ቢስነት ነው። ኢትዮጵያውያን ባለውለታዎቻንንን ስናጥላላ ወደር የለንም። አፄ ኃይለሥላሴን በመግደል የተመፃደቅን፣የራሳችን የሆኑትን ጀግኖች አንዳንድ ሳር እየመዘዝን ክምር የሆነውን ታላላቅ ስራዎቻቸውን እየሸሸግን በማዋረድ እና ኢትዮጵያ ነገ ሌላ ጀግና እንዳይወጣላት በእዚህ እኩይ ስራችን አዲሱን ትውልድ ስሜት ለመግደል ቀን ከሌት የምንሰራ አሳዛኝ ሕዝብ መሆናችን እንቆቅልሻችን ነው። 


አንዳርጋቸው ለመሞት ለተዘጋጀለት የመፃፍ መብት ተጠቅሞ የመሰለውን  ፅፏል፣ወደፊትም ይፅፋል።ይህ ማለት ባቀረባቸው ነጥቦች ላይ ትከራከራለህ እንጂ የሰራቸውን መልካም ስራዎች 100 % አውርዶ ማጣጣል ግን የተለመደው አዙሪት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? 



አቶ አንዳርጋቸው በአዲስ  ስታድዮም ያደረጉት ንግግር 



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

አንድ መቶ ዘጠኝ ፓርቲ የደረስነው ስለማንደማመጥ ነው። በርካታ ቁምነገሮችን የያዘው የሙ/ጥ/ዲ/ን ዳንኤል ክብረት የዛሬ አዲስ ንግግር

ቪድዮ ምንጭ = አንዳፍታ  
ነሐሴ 24/2011 ዓም  (ኦገስት 30/2019 ዓም)


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Wednesday, August 28, 2019

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ የከፈቱ ማንነት እየቆየ እየለየ ነው።የመቀሌው ጉባኤ የድሕረ ስም ማጥፋት ዘመቻው አካል ነበር።ዛሬም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከለውጥ ኃይሉ ጎን በፅናት መቆም ወሳኝ ነው!

ጉዳያችን / Gudayachn
ነሐሴ 23/2011 ዓም (ኦገስት 29/2019 ዓም 


ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ 

ኢትዮጵያ በዘገምተኛ ለውጥ ውስጥ ከምር መግባት ከጀመረች አንድ ዓመት አልፏታል።ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያ ፈፅማ ወደ አደገኛ መንገድ ውስጥ ከመግባት ድና የተሻለ የመፃፍ፣የመናገር እና የመደራጀት መብት እንዲሁም ሁሉም የተቃዋሚ ኃይሎች ወደ አገር ቤት የመግባት እና የመስራት ዕድል አግኝተዋል።ከእዚህ በተጨማሪ በህወሓት መራሹ ኢህአዴግ የነቀዙ ፕሮጀክቶች ለምሳሌ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ሜቴክ እና የ70 ቢልዮን ብር በላይ የአገር ሀብት የበላው የስኳር ፕሮጀክት ጨምሮ የማከም እና ፕሮጀክቶቹን በተሻለ ደረጃ ለማንቀሳቀስ በተደረጉ ጥረቶች ፕሮጀክቶቹ በተሻለ መንገድ እንዲቀጥሉ የማድረግ ሥራ በጥሩ ሁኔታ ላይ  መገኘቱ የአንድ ዓመት ተኩል የለውጡ ሂደት ውጤት ነው።

የለውጥ ሂደቱ በትምህርት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት፣የሕግ ማሻሻያዎችን ለምሳሌ ከመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መመርያ፣ የሲቪል ሰርቪስ እና ሌሎች ሕጎች ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል።ከእዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ከጎረቤት ሀገሮች እስከ መካከለኛው ምስራቅ፣ከአውሮፓ እስከ ሩቅ ምስራቅ  ያላት የዲፕሎማሲ ግንኙነት መሻሻል ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ እየተከበረች እና የመደመጥ አቅሟን ያሳደጉ ስራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተከናወኑት የመንግስት መልካም ስራዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እያለ የለውጡን ሂደት ለማደናቀፍ ያለሙ ኃይሎች በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ላይ ያነጣጠረ መሰረት የለሽ የስም ማጥፋት ስራዎች  በሰፊው ሲሰሩ  ሰንብተዋል።የስም ማጥፋት ዘመቻዎቹ ከከተማ እስከ ገጠር  የተዘረጉ እና በቀድሞ የህወሓት-መር የደህንነት መዋቅር ስር የተሰራ ተራ አሉባልታ ሁሉ ያጠቃለለ ነው። አብዛኞቹ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች  ቀድመው የቀድሞው ስርዓት አድናቂ ነገር ግን በተቃዋሚነት የሚታወቁ ሁሉ በጭንቅ ሰዓት በአምስተኛ ረድፈኝነት በተቃዋሚ ካባ፣ ነገር ግን በጎሳ ስም ተለብደው በተቃዋሚነት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንዲያደርጉ በተሰጣቸው የቤት ሥራ መሰረት በማኅበራዊ ሚድያ እና ሰው ለሰው በመሄድ የስም ማጥፋት ዘመቻቸውን ስያጧጡፉ ሰንብተዋል።

ይህ ሁሉ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከጦርነት በፊት እንደተከፈተ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተልዕኮውን እንደተወጣ የስም አጥፊ ቡድኖቹ አባላት ያስባሉ። እዚህ ላይ ተገቢ ወቀሳ ወይንም ሃሳብ መስጠትተገቢ ሆኖ ሳለ፣ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከፋሺሽቶች ጋር እያመሳሰሉ የሚዋሹንን ግን ለምን በእዚህ ደረጃ ስም ለማጥፋት ተነሱ? ብሎ አለመጠየቅ እና አሰላለፋቸውን አለመረዳት በራሱ የሞኝነት የመጨረሻው ደረጃ ነው።

አሁን ላይ ላይ ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተከፈተው የስም ማጥፋት ዘመቻ የእነማን ዕቅድ እንደሆነ በግልጥ እየታየ ነው።መቀሌ ላይ ነሐሴ 21 እና 22/2011 ዓም በሕገ መንግስት እና ፌድራላዊ አስተዳደር ስም የተደረገው ስብሰባ ለውጡን ተፃሮ ያወጣው መግለጫ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ሲደረጉ የነበሩ ዘመቻዎች ዓላማ ያለፈው ስርዓት ወደ ፊት እንዲመጣ የሚደረግ ስልታዊ ሥራ አካል እንደሆነ በትክክል አሳይቷል። ለውጡ እንደመጣ ሕዝብ እንዲፈናቀል፣የኑሮ ውድነቱ እንዲንር፣አለመረጋጋት እንዲኖር የሰሩ፣የግድያ ሙከራ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ላይ የሞከሩት ሁሉ አለማዋጣቱን የተመለከቱ ኃይሎች ሙሉ ኃይላቸውን ወደ ስም ማጥፋት ካዞሩ በኃላ በመጨረሻ የመንግስትን ህልውና በምንድ መልኩ መግለጫ በማውጣት ጉባኤውን ጨርሰናል ሲሉ ተደምጠዋል።

ኢትዮጵያ በታሪክ ካገኘቻቸው ከአብዮት እና ጦርነት ውጭ በሆነ መልካም የጀመረቸው ለውጥ ፈፅሞ ሊደናቀፍ አይችልም።አሁን ብዙው ነገር ግልጥ ሆኗል።ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የለውጡ ኃይል የጀመረውን የለውጥ ሂደት በኢትዮጵያዊነት መንፈስ መቀጠል፣ሕዝቡ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሚደረጉ የስም ማጥፋት ስራዎችን መቃወም እና ምክንያታዊ የሆኑ ጨዋ አገላለጦችን ብቻ ማበረታታት ብቻ ሳይሆን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመቆም የለውጡን ሂደት ለማደናቀፍ የሚጥሩትን መቃወም አለበት።ኢትዮጵያ በያዘችው የለውጥ ሂደት መቀጠል አለባት።ስትቀጥል ደግሞ ላለፈው አንድ  ዓመት ከተሄድበት ሂደት ወንጀል የሰሩትን ከፅንፈኛ የኦሮሞ አክትቪስቶች እስከ ህወሓት ተፈላጊ ሙሰኞች፣ ከአድር ባይ ድርጎ ለቃሚዎች እስከ የባዕዳንን እጅ የሚማፀኑ ላይ ሁሉ የተጠያቂነት አጀንዳ በመክፈት መሆን አለበት።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ የከፈቱት በረጅም ጊዜ ውትወታ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በበጎ የሚያነሳ ሁሉ ለማሸማቀቅ ደጋግመው ሰፊ ዘመቻ ከፍተው ሰንብተዋል።ባስ ሲል የለውጡ አራማጆች ፎቶ ሲመለክቱ አጋንንት የመላዕክትን ስዕል ሲያይ እንደሚያንቀጠቅጠው ሁሉ የጥላቻ አይናቸው ተጎልጉሎ ሲወጣ ይታያል። አዎን! በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ የከፈቱ ማንነት እየቆየ እየለየ ነው።የመቀሌው ጉባኤ የድሕረ ስም ማጥፋት ዘመቻው አካል ነበር።ሕዝብ በእንዲህ አይነቱ እኩይ አካሄድ  ላይ በጊዜው እርምጃ መውሰድ ካልቻለ ውጤቱ የከፋ ይሆናል።ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከለውጥ ኃይሉ ጎን ዛሬም እንቆማለን!



ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Tuesday, August 20, 2019

''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች በኢሳት ቴሌቭዥን እንዲህ ተቀናብሯል (ቪድዮ)

''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች  በሚል በጉዳያችን ገፅ ላይ የወጣው ፅሁፍ በኢሳት ቴሌቭዥን  እንዲህ ተቀናብሯል።ፅሁፉን ለማንበብ ይህንን ይጫኑ።ቅንብሩን ለመመልከት ቪድዮውን ይጫኑ።



ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Saturday, August 17, 2019

በአረብ ሀገር የሚኖሩ ወጣት እህቶቻችን የፆም እና ጸሎት ሕይወት (ቪድዮ)

ምንጭ = የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት 


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Saturday, August 10, 2019

የኢትዮጵያ ወቅታዊ እና የቅርብ መጪው ተገዳዳሪ ጉዳዮች እና መፍትሄዎች ዙርያ የጉዳያችን ምጥን።

Above Photo  is obtained from Sunset in Ethiopia by Steve Mccurry (sevemccurry.files.wordpress.com
''Gudayachn's'' this particular article written
 in Amharic do not have any interpretation to the above picture. 

ጉዳያችን/ Gudayachn
ነሐሴ 4/2011 ዓም (ኦገስት 10/2019 ዓም) 

ጉዳያችን ገፅ ከ2003 ዓም ጀምሮ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከ900 በላይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የራሷን ዕይታ እና መጉላት የሚገባቸው ዘገባዎችን አቅርባለች።አሁን ያለንበት ወቅትም ብዙዎች ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች እንደሆነ ለመተንበይ የማይታወቅበት ነው የሚል አስተያየት የሚሰጡ አሉ።ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካታ ብጥስጣሽ አጀንዳዎች የኢትዮጵያን ፖለቲካ ''እንደ ገበቴ ውኃ'' ምሁሩንም ሆነ ሕዝቡን እያዋለለው አንድ ዓይነት ቅርፅ  እና አስተያየት ለመያዝ የሚቸገሩ አሉ።ስለሆነም ከስር ባሉት ንዑስ ርዕሶች ስር እጅግ ምጥን በሆነ መልክ የተወሰኑ ነጥቦች ለማስቀመጥ እሞክራለሁ።የሚፃፈው ትክክል ለመሆኑ ጊዜ የሚፈታው ነው።ከእዚህ በፊት ጉዳያችን ላይ ተፅፈው አሁን የሆነውንም መልሶ ማየት ሌላው አማራጭ ነው።ምጥን ሃሳቦች በዝርዝር መፃፍ የሚገባቸው ቢሆኑም ለጊዜው ከብዙ ምክንያቶች አንፃር ዝርዝር ውስጥ መግባት አልፈልግም።ከእዚህ በታች የተነሱት ምጥን ሃሳቦች በሚከተሉት ርዕሶች ስር የገቡ ናቸው።


* የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ምን ይመስላል?

* የፅንፈኛ ኃይሎች መጪ ዕቅድ ምንድነው?
* የዓማራ፣የኦሮሞ እና የትግራይ ፖለቲካ አሁን ያለው እና ወደፊት የሚጠበቅበት?
* ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በፅንፈኛ ኃይሎች አንፃር ባለፈው አንድ ዓመት እርምጃ አልወሰዱም? ወደፊትስ ቀዳሚ ትኩረታቸው መሆን ያለበት ምንድነው?
* የአዲስ አበባ ጉዳይ እንዴት ይያዝ? በውጭ ያለው ዲያስፖራ፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እና የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ኃላፊነት ምን መሆን አለበት?
* ማጠቃለያ
*************************
የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ምን ይመስላል? 

- የውጭ ኃይሎች የራሳቸውን ጥቅም የሚያስጠብቅ መንግስት ለማቆም የሚሮጡበት፣

- ለእዚህም የተለያዩ ቅራኔዎችን በተናጥል እያጠኑ የቱን እንደሚደግፉ መንገድ የሚፈልጉበት፣
- በኦሮሞ ድርጅቶች መሐል ፅንፈኛ ብሔርተኞች፣ለዘብተኛ የሆነውን እና ከሁሉም ኢትዮጵያ ጋር በኢትዮጵያዊነት ለመቀጠል ከሚያስበው ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ለመዋጥ ቢሮክራሲያዊ እና ወታደራዊ አካባቢውን ለመቆጣጠር ጥረት ላይ ያሉበት፣
- ኦዴፓ በሌላ በኩል ከፅንፈኛ ኦነግ ወለድ ብሔርተኞች እና ፅንፈኛ የእስልምና አራማጆች ጋር ጣምራ ፍልምያ ላይ ያለበት ነው፣
- በዓማራ አካባቢ እነኝህን ፅንፈኛ ኃይሎች በስጋት እየተመለከተ ያለበት ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ አለ።ይህም በዓማራ  ውስጥ በራሱ ፅንፍ የያዙ ብሔርተኞች የተፈጠሩበት ሁኔታ ያለበት፣ይህም በራሱ ሌላ አደገኛ ሁኔታ የመፍጠር አቅም ያለው ነው።
- ትግራይ በተመለከተ ህወሓት በክልሉ ውስጥ ስልጣኑን ለማስጠበቅ ያልቻለበት እና እየተንገዳገደ ያለበት፣በቅርቡም ከፍተኛ የተቃውሞ ማዕበል የሚያሰጋው ደረጃ ላይ ነው።

የፅንፈኛ ኃይሎች መጪ ዕቅድ ምንድነው? 

- በኢትዮጵያ  በአሁኑ ጊዜ ሁነት አይነት ፅንፈኛ ኃይሎች አሉ አንዱ የብሔርተኛ ፅንፍ ሲሆን ሌላው አክራሪ እስልምና ነው።

- በኦሮሞ ማኅበረሰብ ስም በአክቲቪስትነት እና ''በሜጫ'' ስም የሚንቀሳቀሱ መጪ ዕቅዳቸው ከብሔር ፅንፍ ዘለው ቀድሞም ወደተነሱበት እን ድብቅ አጀንዳቸው ማለትም ሰላማዊውን የሙስሊም ማኅበረሰብ ''ስስ ጉዳዮች'' እየፈለጉ በማራገብ ሥራ ላይ ከሰሞኑ የሚሰማሩበት ዕቅድ ነው።

የዓማራ፣የኦሮሞ እና የትግራይ ፖለቲካ አሁን ያለው እና ወደፊት የሚጠበቅበት? 


- የዓማራ፣የኦሮሞ እና የትግራይ ፖለቲካ አሁን ያለው በብሔርተኞች እጅ ነው። ወደፊት የሚጠበቅበት ከብሔርተኛ አመራሮች መውጣት አለበት፣

- ለእዚህም መውጫ መንገዱ ሁለት ነው። አንዱ አሁን ያሉት አመራሮች ፈፅመው ከብሔር ፖለቲካ ወጥተው ማንነትን ያከበረ ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ማራመድ እና መተግበር  ነው።ለእዚህም የተከፈተላቸውን ''የወንድ በር'' ማለትም የኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶችን ይዞ ወደ ውህደት የመምጣት ሃሳብ ገፍቶ መሄድ ሲሆን፣
- ሌላው አምራጭ የብሔር ፖለቲካ በምያራምዱ ጨካኝ ኃይሎች እጅ ፖለቲካውን አጋልጠው ሀገርንም እራሳቸው ላይ የሞት ፍርድ መፍረድ ነው።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በፅንፈኛ ኃይሎች አንፃር ባለፈው አንድ ዓመት እርምጃ አልወሰዱም? ወደፊትስ ቀዳሚ ትኩረታቸው መሆን ያለበት ምንድነው?

- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ላለፈው አንድ ዓመት በፅንፈኞች አንፃር ምንም አይነት እርምጃ እንዳልወሰዱ የሚያስቡ ተሳስተዋል፣

- በወለጋ የተነሳው ጦርነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አገላለጥ ''በሶስት ቀን መንግስት እንሆናለን'' ብሎ የፎከረ ኃይል ነበር። በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይህንን ኃይል ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን ገልጠዋል፣ በእርግጥ አሁንም በቢቢሲ ሽፋን እያገኙ አንዳንድ ሽፍታ መኖሩ ቢታወቅም።በቅርቡ በቪኦኤ የተገልጠው በአንድ ቀን ከአምስት መቶ በላይ በዝርፍያ ላይ እና ፀረ ሕዝብ ሥራ ላይ የተሰማሩ የተባሉ ከአምቦ ብቻ መታሰራቸውን እራሱ የኦነግ አንጃ መግለጡ ይታወሳል፣
- በሲዳሞ የክልል ጥያቄ አስታኮ በዜጎች ላይ ወንጀል የሰራው የፅንፍ እንቅስቃሴ አመራሮች መታሰራቸው እና  በሱማሌ ክልል የመገንጠል አጀንዳ የያዘ የአብዲ ኤሊ ቡድን ያንበረከኩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አስተዳደራቸው ነው። እነኝህ ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ግልፅ  አካሄድ የሚያሳዩ ናቸው።
- ወደፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መቼም የማይተኙ እና የቅን ዕሳቤ ድህነት የያዛቸው ፅንፈኛ ብሄርተኞችን እና የፅንፍ እስልምና አራማጆችን በቅድምያ ከኦዴፓ ውስጥ በፍጥነት መመንጠር ካልቻሉ እነኝህ የጥፋት ኃይሎች  በሌላ ቅርፅ በጦር ሰራዊቱ ወይንም ዙርያቸውን ባለ ሌላ መልክ በጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የምደቅኑት አደጋ ይኖራል። ስለሆነም የማያወላውል ውሳኔ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አመራሩ እንዲሁም ከጦሩ ይጠበቃል።

የአዲስ አበባ ጉዳይ እንዴት ይያዝ? 

- የአዲስ አበባ ጉዳይ እና አጀንዳ የነበረው ከታሪክ ዳራው ይልቅ ገበሬዎችን አታፈናቅል የሚለው ትልቁ አጀንዳ ነው።ይህንን አጀንዳ የፅንፍ ኃይሎች ከመብት እና ለሕዝቡ ከመቆርቆር አንፃር ሳይሆን ለአጀንዳ ፍለጋ ብቻ የተተቀሙበት ነው።አሁን ያለው የአዲስ አበባ አስተዳደር በተለይ ከካሳ አንፃር  እና ገበሬዎች ከተማን እንደ አስጊ እንዳይመለከቱ በማድረግ አንፃር ጥያቄውን ለመመለስ እየጣረ ነው።ከእዚህ ውስጥ ገበሬዎች ብቻ ሳይሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪም ካለ በቂ ካሳ እንደማይነሳ፣የካሳ ጉዳዩም በልዩ ሁኔታ ከማየት ባለፈ ገበሬዎች  ቦታውን አለማለሁ ካሉ እንደሚችሉ እየሄደበት ያለው መንገድ ሁሉ አጀንዳ ፈጣሪዎችን ''ጨረቃ ላይ የጣለ'' ጉዳይ ሆኗል፣


- የአዲስ አበባ መስተዳድር በተመለከተ ግን ከተማዋን የሚመጥን አቅም ያለው እና የዲሞክራሲያዊ አካሄድን  የሚያሳይ የኢትዮጵያ ''ሞዴል'' በሚሆን የምርጫ ሂደት ህዝቡ አስተዳደሩን እንዲመርጥ ማድረግ የግድ የግድ አስፈላጊ ነው፣
- ምክንያቱም የአዲስ አበባ ሕዝብ በብዙ መልኩ ስለ ዲሞክራሲ፣ሕግ ማክበር እና ውሁድ ኢትዮጵያዊ ፖለቲካ ስልጡን ከሚባሉ የሀገራችን ክፍል አንዱ ነው፣
- ስለሆነም የአዲስ አበባን ጉዳይ በዙርያዋ ካሉ ኢትዮጵያውያን ገበሬ ነዋሪዎች ጋር ማኅበራዊ ትስስሩን አጎልብቶ ህዝቡ  የራሱን አስተዳደር እንዲመርጥ መብቱ ሊሰጠው ይገባል።ለእዚህም መንግስት በቀን የተቀመጠ የምርጫ ሰሌዳ ከአሁኑ ቢያስቀምጥ መልካም ነው።


በውጭ ያለው ዲያስፖራ ምን ያድርግ፣


- በውጭ ያለው ዲያስፖራ ኮሚኒቲውን ያጠናክር፣የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችን አቅም ያጠናክር ፣ የቱሪዝም ፍሰት እንዲጨምር ያለበትን ሀገሮች ዜጎች ይገፋፋ፣ ሃገሩን ያስተዋውቅ፣

-  በውጭ ያለው ዲያስፖራ ሃገራዊ የሆኑ በርካታ ውይይቶችን እያዘጋጀ አጠገቡ ያሉትን ምሁራን እየጠራ ይሞግት፣
- በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ማኅበራዊ አንድነቱን አጠናክሮ በምጣኔ ሀብት ዘርፍ የሚሰራውን ሥራ መቀጠል አለበት።
- በውጭ ያለው ዲያስፖራ አጉራ ዘለል እና የእርስ በርስ የብሔር እና የሃይማኖት ልዩነት ለማስፋት የሚሰሩትን  ይሞግት፣
- በውጭ ያለው ዲያስፖራ አጠገቡ ያሉ መልካም ሰዎችን ተስፋ ለማስቆረጥ የሚሞክሩትን ተከላክሎ ይሸልም፣
- በውጭ ያለው ዲያስፖራ ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅቶችን ለመመስረት ሃሳቦችን ያመንጭ ይንቀሳቀስ፣
- በውጭ ያለው ዲያስፖራ አዲስ የመጣውን ትውልድ ተስፋ በማያስቆርጥ መልኩ ስለሀገሩ ይንገር፣ይህንን ትውልድ በሁሉም መልክ የተደራጀ እንዲሆን ይርዳ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እና የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ኃላፊነት ምን መሆን አለበት?

- ኢትዮጵያ ቢያንስ ከ80% በላይ ህዝቧ በሃይማኖት ውስጥ ያለ ነው፣

- ይህ ሆኖ ግን የሃይማኖት አካላት አደረጃጀት እና ታማኝ የሆነ አወቃቀር ተጎሳቁሏል፣
- በውስጣቸው ግን የተገፉ እና የማገልገል እድሉን በሌቦች እና የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች የተነጠቁ፣አቅሙ፣ችሎታው፣ ፍላጎቱ እና መንፈሳዊነቱ ያላቸው በርካታ ሰዎች ይዘዋል፣
- ስለሆነም የሃይማኖት አካላት እነኝህ መልካም ሰዎች ወደፊት እና ወደ መምራት እንዲመጡ መንገዱ በመንግስትም ሆነ በሕዝብ የግድ መከፈት አለበት፣
- ይህ ካልሆነ የሃይማኖት አካላት ውድቀት ኢትዮጵያን በእጅጉ የሚጎዳ ትልቅ የታሪክ ጠባሳ ይሆናል።

ማጠቃለያ 

ወደ መደምደምያ ነጥቦች ከመምጣቴ በፊት፣የመነሻ ርዕሱ ስጋት እና ዕድል ስለሚል ዕድል የተባሉት የት አሉ? ብሎ ለሚጠይቅ  ከላይ የተነሱት ውስጥ መከናወን አለባቸው የምላቸው ነጥቦች ከተፈፀሙ የኢትዮጵያ እድሎች እንደሆኑ እንዲወሰድ እፈልጋለሁ።እየሆኑ ያሉት እና የምታቀዱት መጥፎ ዕቅዶች ደግሞ የዛሬም ሆነ የነገ ስጋቶች ናቸው።

ለማጠቃለል ይህንን በዝርዝር ያልተፃፈ ነገር ግን በምጥን የቀረበ የኢትዮጵያ ወቅታዊ እና መጪው ስጋት፣ዕድሎች በተመለከተ የቀረቡትን ነጥቦች በሚከተሉት ነጥቦች እደመድማለሁ።



  • ኢትዮጵያ አሁን በፅንፈኛ የብሔር ኃይሎች አሁን ያለውን የለውጥ ኃይል ለመፈታተን የሚደረጉ ሙከራዎች ከኦነግ ፅንፈኛ ኃይል፣ከዓማራ ፅንፍ የያዘ ብሔርተኛ ቅስቀሳ እና ከህወሓት አመራሮች አሉ። ወደፊትም መልካቸውን ቀይረው ይኖራሉ።
  • የኦሮሞ ብሔርተኛ የፅንፍ አስተሳሰብ አራማጆች ለኦደፓ እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ቀዳሚ አደጋዎች ናቸው።
  • የኦሮሞ የፅንፍ ብሔር አራማጁ በአክትቪስት እና ''ሜጫ'' የሚመራው ቡድን አጀንዳውን ወደ ፅንፍ የሙስሊም  እንቅስቃሴ ለመቀየር እና ከጀርባ ሆኖ ለመዘወር እንቅስቃሴ ላይ ነው።
  • ለእዚህ ጥፋት የብሔር ፖለቲካ እንደመጋቢነት እየጠቀመው ስለሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አስተዳደርም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍጥነት ይህንን ጉዳይ ለመግታት መንቀሳቀስ አለባቸው። ለእዚህም ሃገራዊ አንድነት ማጠናከር እና መተማመን እንዲሰፍን ማድረግ ያስፈልጋል።
  • በቅርቡ የሚነሳው የትግራይ የውስጥ የለውጥ አስተዳደር እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ሕዝብ መደገፍ እና ከብሔር  ፖለቲካ የራቁ ኃይሎች ህወሃትን እንዲተኩ ማገዝ ያስፈልጋል።
  • የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ ላይ እጃቸውን ሊከቱ የሚፈልጉ አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ አረብ ሀገራት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስደንጋጭ እርምጃ ከመንግስት ያስፈልጋል።
  • በኢትዮጵያ ያለውን ድህነት ለመቀነስ እውቀቱ፣የገንዘብ አቅሙ እና ልምዱ ያላችሁ ሁሉ መንግስትን ለማገዝ መነሻው ጊዜ አሁን ነው።
  • የድህነቱ መቃለል እና ከፍተኛ የስራ ዕድል ወጣቱ እንዲኖረው በማድረግ ውስጣዊ ውጥረት ማርገብ እና የፅንፍ ኃይሎች ወጣቱን መጠቀምያ እንዳያደርጉ ዋነኛው እና ቁልፉ ጉዳይ ነው።
  • አሁንም የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ መንግስታዊ አሰራር ማጠንከር፣መርዳት ማለት የብሔርም ሆነ የእስልምና ፅንፈኛ ኃይሎች እንዳይገዳደሩት እና ኢትዮጵያ አደጋ ላይ እንዳትወድቅ የመስራት ዋነኛው የትኩረት ቦታ መሆኑን መለየት እጅግ አስፈላጊ ነው።
========================/////=====================


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Monday, August 5, 2019

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ከ70 በላይ በሚሆኑ ምሁራን በ16 መስኮች ላይ ያተኮረ የመጀመሪያ ደረጃ ረቂቅ ፖሊሲዎች አዘጋጀ።

የኢዜማ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት 

ጉዳያችን/ Gudayachn
ሐምሌ 30/2011 ዓም (ኦገስት 6/2019 ዓም)
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ከ70 በላይ በሚሆኑ ምሁራን በ16 መስኮች ላይ ያተኮረ የመጀመሪያ ደረጃ ረቂቅ ፖሊሲዎች ማዘጋጀቱን ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ሐምሌ 27 እና 28/2011 ዓም በአዲስ አበባ ሆልዴይ ሆቴል ባዘጋጀው የፖሊሲ መወያያ መድረክ አስታወቀ።የኢዜማ የፓሊሲ ጥናት እና ምርምር ኃላፊ አምሐ ዳኘው የውይይቱ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ጥናቶቹ ለኢትዮጵያ ተጨባጭ ችግሮች መፍትሄ መሆን የሚችሉ የፖሊሲ አማራጮችን ለመቅረፅ ዋነኛ ግብዓት እንደሚሆኑ ገልፀዋል። በሌላ በኩል የፓርቲው መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)  አሁን ካለንበት በጭንቀት እና በተሰፋ የሚዋልል ሀገራዊ ሁኔታ ወጥተን ወደተረጋጋ ሥርዓት የምንሄደው በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ ውይይቶች ብቻ መሆኑን ገልፀዋል። 

በውይይቱ ላይ እንደተገለጠው የፖሊሲ ጥናቶቹ በትምህርት፥ቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራ፣ ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ዋስትና፣ ባሕል፥ ቱሪዝምና ኢኮ ሲስተም፣ የፊስካል፥ የገንዘብ እና መዋለ ነዋይ እንዲሁም የውጭ ኢኮኖሚ እና ዲያስፖራ ፖሊሲ  እና ሌሎች  መስኮች  ላይ የተጠኑ የፖሊሲ ጥናቶች ከተጠኑት ፖሊሲዎች ውስጥ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል። በሌላ በኩል ዜግነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት እና ማኅበራዊ ፍትህን መሠረት አድርገው የተሠሩት እነኝህ የፖሊሲ ጥናቶች የኢዜማ አባል የሆኑ እና ገለልተኛ ባለሙያዎች በጋራ ያጠኗቸው ናቸው። በቀጣይ ጊዜ ለውይይት የቀረበው ረቂቅ ፖሊሲው በፓርቲው አመራሮች እና በአዘጋጅ ምሁራን በዝርዝር ከተመከረበት በኋላ፤ በፓርቲው የተለያዩ መዋቅሮች ደረጃ ውይይት እንደሚካሄድበትም በውይይቱ ወቅት ተወስቷል።በመቀጠለም ከፓርቲው አባላት ጋር ከሚደረግ ውይይ በኋላ ረቂቅ ፖሊስው ስልጣን ባለው የፓርቲው አካል ፀደቆ የኢዜማ የፖሊሲ ሰነድ እንደሚሆንም ተነግሯል።

ይህ በእንዲህ እያለ ፋና እንደዘገበው የኢዜማ መሪ ፕሮፌስር ብርሃኑ የፖለሲ ዝግጅቱ የፓርቲው የምርጫ ዝግጅት አካል ይሆን ወይ? ተብለው ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፥ ምርጫው በየትኛውም ጊዜ ይካሄድ ፓርቲው ፖሊሲዎችን የማዘገጃት ግዴታው መሆኑን መናገራቸውን እና ሰለቀጠዩ ምርጫም በሰነዘሩት ሃሳብም የምርጫው ማከናወኛ ወቅት ከጊዜ ይልቅ በሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ቢወሰን የተሻለ ነው ካሉ በኃላ በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እና መረጋጋት መስፈኑ፣ ፓርቲዎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በነፃነት ለመንቀሳቀስ የሚችሉበት አውድ መኖር እና ምርጫ ቦርድ ትክክልኛ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ማረጋገጫ መስጠቱ፤ የምርጫውን መከወኛ ጊዜን የመወሰን አቅም እንዳላቸው  መግለጣቸውን ፋና ዘግቧል።
ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Friday, August 2, 2019

የዓማራ ክልል መስተዳድር እና ሕዝብ በሶስት አካላት ውክብያ ውስጥ ገብቷል።

ጉዳያችን/ Gudayachn
ሐምሌ 27/2011 ዓም (ኦገስት 3/2019 ዓም)

የፖለቲካ ለውጥ ግንዛቤ እና የማኅበረሰብ የአስተሳሰብ ለውጥ በሂደት ልኬት ሲመዘኑ ልዩነት አላቸው።የፖለቲካ ለውጥን በአብዮት ወይንም የነበረ መንግስትን በአንድ ጀንበር ገልብጠህ የምትፈልገውን የፖለቲካ ለውጥ ልታመጣ ትችላለህ። የነበረ የማኅበረሰብ አስተሳሰብን ግን በአንድ ጀንበር አትቀይረውም።በረጅም ጊዜ በብዙ ውጫዊ እና ውስጣዊ ሁኔታዎች እየዳበረ የመጣ የማኅበረሰብ አስተሳሰብ ቤተ መንግስት ውስጥ ስለገባህ ብቻ አትቀይረውም።አስተሳሰቡ በራሱ የብዙ መስተጋብሮች ውጤት ስለሆነ በቀላሉ አይነቀልም።ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንዶች ያልተገነዘቡት ነገር አንዱ ይህንን የጠለቀ ማኅበረሰባዊ ትስስርን በአንድ ጀንበር በፈለጉት መንገድ ለመምራት የመሞከር ስህተት ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ኢትዮጵያዊ እና አገራዊ ስሜትን ከልጅ ልጆቹ እያወራረሰ ከኖሩት ማኅበረሰብ ውስጥ ልክ እንደ ኦሮሞው፣ትግራይ፣ቤንሻንጉል፣ሱማሌው፣አፋሩና ሌላው ሁሉ የዓማራ ማኅበረስብም አንዱ ነው።ይህ ማኅበረሰብ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት በሕወሓት መራሹ የኢህአዴግ ስርዓት ውስጥ ነፍጠኛ፣ትምክህተኛ እና ሌላም ስም በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ እና በብሔራዊ ራድዮ እና ቴሌቭዥን ጭምር ፈፅሞ የማያውቃቸው የቀደሙ መሪዎች እየተጠሩ ሲወቀስ ከርሟል።ይህ የማጥላላት ስውር እና ግልጥ ዘመቻ ደግሞ በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ በውሸት ታሪኮች እየተከሸነ ለታዳጊ ወጣቶች ሳይቀር ስለተዘራ ዛሬ ዛሬ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነ ለፍቶ አዳሪ ሁሉ ነፍጠኛ የሚመስለው የዋህ ትውልድ ሁሉ እንዲፈጠር ከመደረጉ አልፎ ብዙዎች ከኖሩበት ቦታ በውሸት እና የቂም ታሪክ አደግ የአካባቢ ባለስልጣናት ተገፍቶ ከቀየው እስከ መባረር ደርሷል።ለእዚህም ማስረጃ ከጉርዳፈርዳ እስከ ቤንሻጉል የተፈፀሙትን ግፎች መመልከት ይበቃል። 

የዓማራ ክልል መስተዳድር እና ሕዝብ በሶስት አካላት ውክብያ ውስጥ ገብቷል።

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በፈጣን የማኅበረሰብ የለውጥ ንቅናቄ ውስጥ ነች።የለውጥ ንቅናቄው የተለያዩ አስተሳሰብ ያላቸውን አካላት በረጋ መንፈስ እና በቅንነት ያለፈ ታሪክ ንትርክ አቁመው መጪውን ያለመ አጀንዳ ላይ ተወያይተው ወደፊት ይሄዳሉ? ወይንስ ልዩነቶችን በሰለጠነ መልክ መፈታት ትተው በተለመደው የኃይል መስመር በሌላ ዙር ግጭት ሀገሪቱን ወደ ባሰ መቀመቅ ይከቷታል ወይ? የሚለው የወቅቱ ጥያቄ ነው።ይህ በእንዲህ እያለ እንደ ማኅበርሰብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የተለያየ አጀንዳ ያላቸው ኃይሎች ሁሉ ትኩረታቸው የዓማራው  ማኅበርሰብ ላይ በሚፈፀም ውክብያ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ሁኔታ ማናጋት ይቻላል።በእዚህም አጀንዳችንን ማስፈፀም እንችላለን በሚል ዕሳቤ የዓማራ ክልል እና ሕዝብ ላይ ውክብያ መፈፀም ስራዬ ተብሎ ተይዟል። 

በዓማራ ክልል እና ሕዝብ ላይ ውክብያ በመፈፀም ላይ የሚገኙት ሶስቱ አካላት

1) የዓማራ ክልል ተወላጅ እንደሆኑ የሚናገሩ የማኅበራዊ ሚድያ ''አርበኞች'' 

በእዚህ ስር የሚገኙ በትክክል የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ጥበብ-አልባ አክትቪስቶች፣ ከማኅበራዊ ሳይንስ፣ከታሪክ እና ከፖለቲካ ዕውቀት ውጪ የሆነ የትምህርት ዕውቀት ያላቸው ምሁራን ይገኙበታል።እነኝህ አካላት ለዓማራ ሕዝብ ምን ቢደረግ ወይንም የፖለቲካ ትግሉ ግብ ምን ለማግኘት እንደሆነ የጠራ ዓላማ ማስቀመጥ ያቃታቸው ግን አንድ ጊዜ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሌላ ጊዜ ኦዴፓ ቆይተው ደግሞ በዓማራ ማኅበረሰብ ስም የተደራጁ ግለሰቦችን አሁንም ሌላ ጊዜ ደግሞ የዜግነት ፖለቲካ የሚይራምዱትን ሁሉ እየወቀሱ እና ''የዓማራ ጠላቶች'' በሚል ፍረጃ ቀን ከሌሊት ሕዝቡን ከሁሉም አካላት ጋር የማጋጨት እና የማስደንበር ሥራ ላይ ብቻ ተወጥረው የሚውሉ ናቸው። 

የእነኝህ አካላት አካሄድ በተለይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የዓማራው  ማኅበረሰብ መጫወት ያለበትን ጉልህ እና ገንቢ መንገድ ለማመላከት የተነሱ ምሁራንን ሁሉ የማሸማቀቅ ሥራ እየሰሩ  የዓማራን ማኅበረሰብ ሽማግሌ እና ዓዋቂ የሌለበት፣ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር  በፍቅር የመኖሩን የረጅም ጊዜ ጥበብ ሁሉ ገደል የከተቱ ናቸው።ለምሳሌ ሰኔ 15/2011 ዓም በባህርዳር እና በአዲስ አበባ የተፈፀሙ የአዴፓ ከፍተኛ አመራሮች እና የኢታማጆር  ሹም ግዳይ ላይ ሟችንም ገዳይንም ሲወቅሱ ቆይተው በኃላ ከግድያው በኃላ ሁለቱንም ስያሞግሱ የተሰሙ ናቸው።

2) የፅንፈኛ ኦነግ አፍቃሪዎች እና ከፍተኛ የህወሓት ባለስልጣኖች 

በተራ ቁጥር አንድ ላይ ከተጠቀሱት አካላት በተለየ እና በከፋ መልኩ የዓማራ ክልል እና ሕዝብ በማወክ ተግባር ላይ የተሰማሩ የፅንፈኛ ኦነግ አፍቅሪዎች እና የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ናቸው።ሁለቱም አካላት ላለፉት አርባ ዓመታት ''የሞኝ ዘፈን ሁሌ አበባዬ'' እንዲሉ ከወጣትነታቸው እስከ እርግናቸው ድረስ ዓማራ፣ነፍጠኛ፣ትምክህተኛ በሚሉ ቃላት ሲሰክሩ ያደጉ ናቸው።ከእነርሱ ውስጥ አንዳንዶቹ ወደ መሃል ሀገር መጥተው ዓማራ የተባለው ማኅበረሰብ ከሁሉ በከፋ ድህነት እና በበዛ ትህትና ሌላው ወገኑ ኢትዮጵያዊ እንደሚያከብር ሲመለከቱ የአለቆቻቸው የተሳሳተ አስተሳሰብ ተረድተው አመለካከታቸውን አስተካክለዋል።የቀሩት ግን አሁንም ሁለት ፀጉር አውጥተው በስራቸው ያሉትን ወጣቶች በቂም እና በጥላቻ እንዲያድጉ ለማድረግ ሲባዝኑ ይታያሉ። 

የፅንፈኛ ኦነግ አፍቃሪዎች እና የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ባለፈ የቂም ትርክታቸውን በዓማራው ማኅበረሰብ ላይ በመንዛት ብቻ አልተወሰኑም። ይልቁንም በ21ኛው ክ/ዘመን ላይ ተቀምጠው ዛሬም የፖለቲካ አሰላለፍ ቅኝታቸውን በዘመናዊ ዕሳቤ ላይ ከመመስረት እና ኢትዮጵያን አንድ እርምጃ ወደፊት ከመውሰድ ይልቅ ዛሬም መለኪያቸው የዓማራውን ማኅበረሰብ ከመግፋት እና ሴራ ከማሴር አንፃር ብቻ መቀመራቸው አሳዛኙ ሁኔታ ነው።እነኝህ አካላት መጪውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ አደጋ የሚሉት ኢትዮጵያዊነትን እና የህዝብ ለሕዝብ አንድነትን ሲሆን ስኬት የሚሉት ድግሞ የጎሳ ፖለቲካ አብቦ እና አፍርቶ መታየቱን ነው።ስለሆነም የፖለቲካ ድርጅቶችን የሚያቀርቡትም ሆነ የሚያርቁት ምንም በያውቀው በምስኪኑ የዓማራ ማህበረሰብ ላይ  የፖለቲካ ድርጅቶቹ በሚሰሩት የሴራ ፖለቲካ ልክ እየሆነ መምጣቱ አደገኛው የችግሩ ገፅታ ነው።በእዚህም ዙርያ ምሁራኖቻቸውን ወደ መንግስት መዋቅር በማስገባት ርካሽ ዓላማቸውን ለማስፈፀም ሲሞክሩ ይስተዋላሉ። 

በእዚህ ተራ ቁጥር ሁለት ምድብ ውስጥ ያሉት የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የዓማራ ክልል እና ህዝብን በማወክ ተግባር ላይ የተሰማሩት በቀጥታ ሳይሆን በተራ ቁጥር አንድ ላይ ከተጠቀሱት የማኅበራዊ ሚድያ ''አርበኞች'' ጋር ተቀላቅለው እና እራሳቸውን በአክትቪስት ስም ሰይመው መሆኑ ነገሩን አስቂኝም ያደርገዋል።ከአንድ ዓመት በፊት የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናቶችን የግፍ ተግባር ሲያሞካሹ የነበሩ ዛሬ ስልት ቀይረው የዓማራ ማኅበረሰብ የሚቆረቆሩ ሆነው መስለው ግን ሕዝቡን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጋር ስያጣሉት መመልከት የተለመደ ሆኗል።ስለሆነም የማወክ ተግባሩ በረቀቀ መልክ እየተፈፀመ ለመሆኑ አንዱ አመላካች ነጥብ ነው። 

የችግሩ ተከታይ ችግር  

ከላይ የተጠቀሱት የሶስቱ አካላት የዓማራ ክልልንም ሆነ ሕዝብ የማወክ ተግባር ተከታይ ችግር ይዞ መምጣቱ አይቀርም። ይሄውም የዓማራን ክልል ሕዝብ ወደ የጦዘ እና አደገኛ የመጠቃት ስሜት እንዲነሳ ያደርገዋል። አንዳንዶች ይህንን የጦዘ የመጠቃት ስሜት እንደ አዎንታዊ የፖለቲካ ዕድል ቆጥረው የክልሉን ሕዝብ ለማነሳሳት  እና ለርካሽ የፖለቲካ ግብ መጠቀምያ ሊያስቡት ይችላሉ። አሁን ባለችውም ሆነ በመጪዋ ኢትዮጵያ የጦዘ የመጠቃት ስሜትን ቀስቅሶ ወደ ስልጣን ለመውጣት የሚደረግ ሙከራ ሁሉ መጨረሻው የእርስ በርስ እልቂት ነው።ይህ ማለት ማንም ተነስቶ ሌላውን ገፍቶ ለመኖር ሲፈልግ ይፈቀድለት ማለት አይደለም።ይህንን የተሳሳተ አስተሳሰብ ተከትለው ወደ ስልጣን የተጠጉትም ዘለቄታዊ የሆነ የፖለቲካ መፍትሄ አጥተው ግራ እንደተጋቡ ማሰቡ ብቻ መንገዱ በራሱ ስህተት መሆኑን መረዳቱ በራሱ ሂደቱ ችግር እንዳለበት ለማወቅ ይረዳል።

 ስለሆነም የችግሩ ተከታይ በራሱ ሌላ ችግር ነው።በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱት ሶስት አካሎች የዓማራ ክልል እና ህዝብን የማዋከብ ተግባራቸውን ማቆም አለባቸው።ይህንን ለማቆም ደግሞ በመጀመርያ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት አለባቸው። ይህ የአስተሳሰብ ለውጥ በሰለጠነ እና በሰከነ መንገድ ከማሰብ ይጀምራል። ይህ ካልሆነ ግን ሕዝቡን ወደ ጦዘ የመጠቃት ስሜት እየገፉት መሆኑ መታወቅ አለበት። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ወደ አደጋ የሚያመራት ነው።

መፍትሄው 

ከእዚህ በፊትም ለመግለጥ እንደሞከርኩት የኢትዮጵያ ችግር የመፍትሄው ስርም ሆነ መፍትሄው ፖለቲካ ብቻ የተንጠላጠለ አይደለም።ከፖለቲካ ውጭ ያሉ ወሳኝ ጉዳዮች አሉ (ጉዳዮቹን አስመልክቶ ከእዚህ በፊት በጉዳያችን  ''ለኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት አደገኛው ፖለቲካዊው ተግዳሮት ብቻ አይደለም። (ጉዳያችን ልዩ ትኩረት)''  በሚል ርዕስ የወጣውን ይመልከቱ)። ስለሆንም የዓማራ ክልል እና ሕዝብ ላይ የሚደረገውን ውክብያ ለማስቆም እና ጉዳይ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን የሚከተሉት መፍትሄዎች መወሰድ አለባቸው።እነርሱም : - 

  • ምንም ዓይነት ድብብቆሽ እና ማድበስበስ የሌለበት ግልጥ ውይይት በተለይ በዓማራ ክልል እና ሕዝብ ላይ የሚደረጉት ውክብያ በሚፈፅሙት የክልሉ ተወላጅ የፈስቡክ ''አርበኞች'' ተግባር የክልሉ ተወላጅ ምሁራን እና የሀገር ሽማግሌዎች መከላከል እንዲችሉ መርዳት፣
  • ማንኛውም ዓይነት የትንኮሳ ንግግሮች፣የቢሮክራሲ የሴራ ተግባራት እና የታሪክ ሽምያዎችን ማጋለጥ እና በፈፀሙት ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ፣
  • የአርባ ዓመቱን የጎሳ ፖለቲካ እና በተለይ የዓማራ ማኅበረሰብ ላይ ያነጣጠሩ ፀብ ጫሪ ንግግሮች በይፋ መታረማቸው እንዲገልጥ ይህንን ያደረጉም በይፋ ይቅርታ  እንዲጠይቁ ማድረግ እና ለወደፊት የሚያስተጋቡ ካሉ በሕግ መቅጣት፣
  • መንግስት ጥንቁቅ የሆነ የምጣኔ ሀብት ክፍፍል፣የበጀት አደላደል እና የመንግስት ምስረታ ስርዓት ሂደት እንዲከተል ማድረግ፣
  • የእነኝህ ሁሉ ችግር አንዱ  መነሻ የሕገ መንግስቱ ፀብ አባባሽ አንቀፆች በመሆናቸው ህገ መንግስቱን የማሻሻል ሂደት ከምርጫው በፊት ማከናወን እና 
  • ሰፊ፣ጥልቅ እና ሁሉን ያሳተፈ   አገራዊ እና ማኅበራዊ ዕሴት (Social Capital) በእጅጉ የሚያሳድግ እንቅስቃሴ ማድረግ እና ለሐያ ሰባት ዓመታት የተዘሩ እና ከእዛ በፊት የተዘሩ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን የማከም ሥራ መስራት የሚሉት ይጠቀሳሉ።
በመጨረሻም በኢትዮጵያ የሚከሰቱት ፖለቲካዊም ሆነ ማኅበራዊ ክስተቶች ለምን ሆኑ ብሎ ለረጅም ጊዜ የማጥናት እና መፍትሄ አምጦ የመውለድ ልማድ ስለሌለ የፊት የፊት ብቻ እያዩ መሄድ ልማድ ሆኖ ነው እንጂ ለችግሮቻችን መፍትሄ የመፈለጉ ሥራ ላይ ሁሉም እኩል ቢሰራ የማይፈታ ችግር የለም።ለምሳሌ ሰኔ 15/2011 ዓም በባህር ዳር እና አዲስ አበባ የተፈፀሙት ግድያዎች ዙርያ የሚወሳው ፖለቲካዊ  ሁነቱ እንጂ የችግሩ መነሻ እና ማኅበራዊ ስሜቱ እንዴት ተፈጠረ የሚለውን ክፍል የሚያጠናው እና የችግሩ ስር ወደ ሚወስደው ጫፍ ሄዶ የመፍትሄ ቁልፉን ለማግኘት እና መንግስት ለማማከር የሚተጋ የለም።ከእዚህ ይልቅ  በማያልቅ የቃላት ውርወራ ላይ መግባት ፋሽን ሆኖ ተይዟል።ጥናቱ ቢደረግ ግን የጦዘ  የተጠቂነት ስሜት ከላይ በተጠቀሱት ሶስት አካላት ውክብያ ዙርያ በተፈጠሩ ስነ ልቦናዊ ስሜቶች ምክንያት ላለመሆኑ ማረጋገጫ የለም። አሁንም ጊዜው አልረፈደም።ወደ ሌላ የጥፋት ምዕራፍ ሳይገባ ለችግሮቹ መፍትሄ የሚሆን ሀገር አረጋጊ፣የህዝብን ስነ ልቦና አካሚ እና በሁሉም ወገን መሐል የመተማመን ስሜት ፈጣሪ አገራዊ ንቅናቄ ከመንግስትም ሆነ ከአገር ወዳድ ምሁራን ሁሉ ይጠበቃል።
=========================/////==========
ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን በአዲስ አበባ ሚሊንየም አዳራሽ ካቀረበው ዜማ (ቪድዮ) 



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...