ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, August 10, 2019

የኢትዮጵያ ወቅታዊ እና የቅርብ መጪው ተገዳዳሪ ጉዳዮች እና መፍትሄዎች ዙርያ የጉዳያችን ምጥን።

Above Photo  is obtained from Sunset in Ethiopia by Steve Mccurry (sevemccurry.files.wordpress.com
''Gudayachn's'' this particular article written
 in Amharic do not have any interpretation to the above picture. 

ጉዳያችን/ Gudayachn
ነሐሴ 4/2011 ዓም (ኦገስት 10/2019 ዓም) 

ጉዳያችን ገፅ ከ2003 ዓም ጀምሮ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከ900 በላይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የራሷን ዕይታ እና መጉላት የሚገባቸው ዘገባዎችን አቅርባለች።አሁን ያለንበት ወቅትም ብዙዎች ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች እንደሆነ ለመተንበይ የማይታወቅበት ነው የሚል አስተያየት የሚሰጡ አሉ።ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካታ ብጥስጣሽ አጀንዳዎች የኢትዮጵያን ፖለቲካ ''እንደ ገበቴ ውኃ'' ምሁሩንም ሆነ ሕዝቡን እያዋለለው አንድ ዓይነት ቅርፅ  እና አስተያየት ለመያዝ የሚቸገሩ አሉ።ስለሆነም ከስር ባሉት ንዑስ ርዕሶች ስር እጅግ ምጥን በሆነ መልክ የተወሰኑ ነጥቦች ለማስቀመጥ እሞክራለሁ።የሚፃፈው ትክክል ለመሆኑ ጊዜ የሚፈታው ነው።ከእዚህ በፊት ጉዳያችን ላይ ተፅፈው አሁን የሆነውንም መልሶ ማየት ሌላው አማራጭ ነው።ምጥን ሃሳቦች በዝርዝር መፃፍ የሚገባቸው ቢሆኑም ለጊዜው ከብዙ ምክንያቶች አንፃር ዝርዝር ውስጥ መግባት አልፈልግም።ከእዚህ በታች የተነሱት ምጥን ሃሳቦች በሚከተሉት ርዕሶች ስር የገቡ ናቸው።


* የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ምን ይመስላል?

* የፅንፈኛ ኃይሎች መጪ ዕቅድ ምንድነው?
* የዓማራ፣የኦሮሞ እና የትግራይ ፖለቲካ አሁን ያለው እና ወደፊት የሚጠበቅበት?
* ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በፅንፈኛ ኃይሎች አንፃር ባለፈው አንድ ዓመት እርምጃ አልወሰዱም? ወደፊትስ ቀዳሚ ትኩረታቸው መሆን ያለበት ምንድነው?
* የአዲስ አበባ ጉዳይ እንዴት ይያዝ? በውጭ ያለው ዲያስፖራ፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እና የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ኃላፊነት ምን መሆን አለበት?
* ማጠቃለያ
*************************
የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ምን ይመስላል? 

- የውጭ ኃይሎች የራሳቸውን ጥቅም የሚያስጠብቅ መንግስት ለማቆም የሚሮጡበት፣

- ለእዚህም የተለያዩ ቅራኔዎችን በተናጥል እያጠኑ የቱን እንደሚደግፉ መንገድ የሚፈልጉበት፣
- በኦሮሞ ድርጅቶች መሐል ፅንፈኛ ብሔርተኞች፣ለዘብተኛ የሆነውን እና ከሁሉም ኢትዮጵያ ጋር በኢትዮጵያዊነት ለመቀጠል ከሚያስበው ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ለመዋጥ ቢሮክራሲያዊ እና ወታደራዊ አካባቢውን ለመቆጣጠር ጥረት ላይ ያሉበት፣
- ኦዴፓ በሌላ በኩል ከፅንፈኛ ኦነግ ወለድ ብሔርተኞች እና ፅንፈኛ የእስልምና አራማጆች ጋር ጣምራ ፍልምያ ላይ ያለበት ነው፣
- በዓማራ አካባቢ እነኝህን ፅንፈኛ ኃይሎች በስጋት እየተመለከተ ያለበት ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ አለ።ይህም በዓማራ  ውስጥ በራሱ ፅንፍ የያዙ ብሔርተኞች የተፈጠሩበት ሁኔታ ያለበት፣ይህም በራሱ ሌላ አደገኛ ሁኔታ የመፍጠር አቅም ያለው ነው።
- ትግራይ በተመለከተ ህወሓት በክልሉ ውስጥ ስልጣኑን ለማስጠበቅ ያልቻለበት እና እየተንገዳገደ ያለበት፣በቅርቡም ከፍተኛ የተቃውሞ ማዕበል የሚያሰጋው ደረጃ ላይ ነው።

የፅንፈኛ ኃይሎች መጪ ዕቅድ ምንድነው? 

- በኢትዮጵያ  በአሁኑ ጊዜ ሁነት አይነት ፅንፈኛ ኃይሎች አሉ አንዱ የብሔርተኛ ፅንፍ ሲሆን ሌላው አክራሪ እስልምና ነው።

- በኦሮሞ ማኅበረሰብ ስም በአክቲቪስትነት እና ''በሜጫ'' ስም የሚንቀሳቀሱ መጪ ዕቅዳቸው ከብሔር ፅንፍ ዘለው ቀድሞም ወደተነሱበት እን ድብቅ አጀንዳቸው ማለትም ሰላማዊውን የሙስሊም ማኅበረሰብ ''ስስ ጉዳዮች'' እየፈለጉ በማራገብ ሥራ ላይ ከሰሞኑ የሚሰማሩበት ዕቅድ ነው።

የዓማራ፣የኦሮሞ እና የትግራይ ፖለቲካ አሁን ያለው እና ወደፊት የሚጠበቅበት? 


- የዓማራ፣የኦሮሞ እና የትግራይ ፖለቲካ አሁን ያለው በብሔርተኞች እጅ ነው። ወደፊት የሚጠበቅበት ከብሔርተኛ አመራሮች መውጣት አለበት፣

- ለእዚህም መውጫ መንገዱ ሁለት ነው። አንዱ አሁን ያሉት አመራሮች ፈፅመው ከብሔር ፖለቲካ ወጥተው ማንነትን ያከበረ ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ማራመድ እና መተግበር  ነው።ለእዚህም የተከፈተላቸውን ''የወንድ በር'' ማለትም የኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶችን ይዞ ወደ ውህደት የመምጣት ሃሳብ ገፍቶ መሄድ ሲሆን፣
- ሌላው አምራጭ የብሔር ፖለቲካ በምያራምዱ ጨካኝ ኃይሎች እጅ ፖለቲካውን አጋልጠው ሀገርንም እራሳቸው ላይ የሞት ፍርድ መፍረድ ነው።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በፅንፈኛ ኃይሎች አንፃር ባለፈው አንድ ዓመት እርምጃ አልወሰዱም? ወደፊትስ ቀዳሚ ትኩረታቸው መሆን ያለበት ምንድነው?

- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ላለፈው አንድ ዓመት በፅንፈኞች አንፃር ምንም አይነት እርምጃ እንዳልወሰዱ የሚያስቡ ተሳስተዋል፣

- በወለጋ የተነሳው ጦርነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አገላለጥ ''በሶስት ቀን መንግስት እንሆናለን'' ብሎ የፎከረ ኃይል ነበር። በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይህንን ኃይል ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን ገልጠዋል፣ በእርግጥ አሁንም በቢቢሲ ሽፋን እያገኙ አንዳንድ ሽፍታ መኖሩ ቢታወቅም።በቅርቡ በቪኦኤ የተገልጠው በአንድ ቀን ከአምስት መቶ በላይ በዝርፍያ ላይ እና ፀረ ሕዝብ ሥራ ላይ የተሰማሩ የተባሉ ከአምቦ ብቻ መታሰራቸውን እራሱ የኦነግ አንጃ መግለጡ ይታወሳል፣
- በሲዳሞ የክልል ጥያቄ አስታኮ በዜጎች ላይ ወንጀል የሰራው የፅንፍ እንቅስቃሴ አመራሮች መታሰራቸው እና  በሱማሌ ክልል የመገንጠል አጀንዳ የያዘ የአብዲ ኤሊ ቡድን ያንበረከኩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አስተዳደራቸው ነው። እነኝህ ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ግልፅ  አካሄድ የሚያሳዩ ናቸው።
- ወደፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መቼም የማይተኙ እና የቅን ዕሳቤ ድህነት የያዛቸው ፅንፈኛ ብሄርተኞችን እና የፅንፍ እስልምና አራማጆችን በቅድምያ ከኦዴፓ ውስጥ በፍጥነት መመንጠር ካልቻሉ እነኝህ የጥፋት ኃይሎች  በሌላ ቅርፅ በጦር ሰራዊቱ ወይንም ዙርያቸውን ባለ ሌላ መልክ በጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የምደቅኑት አደጋ ይኖራል። ስለሆነም የማያወላውል ውሳኔ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አመራሩ እንዲሁም ከጦሩ ይጠበቃል።

የአዲስ አበባ ጉዳይ እንዴት ይያዝ? 

- የአዲስ አበባ ጉዳይ እና አጀንዳ የነበረው ከታሪክ ዳራው ይልቅ ገበሬዎችን አታፈናቅል የሚለው ትልቁ አጀንዳ ነው።ይህንን አጀንዳ የፅንፍ ኃይሎች ከመብት እና ለሕዝቡ ከመቆርቆር አንፃር ሳይሆን ለአጀንዳ ፍለጋ ብቻ የተተቀሙበት ነው።አሁን ያለው የአዲስ አበባ አስተዳደር በተለይ ከካሳ አንፃር  እና ገበሬዎች ከተማን እንደ አስጊ እንዳይመለከቱ በማድረግ አንፃር ጥያቄውን ለመመለስ እየጣረ ነው።ከእዚህ ውስጥ ገበሬዎች ብቻ ሳይሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪም ካለ በቂ ካሳ እንደማይነሳ፣የካሳ ጉዳዩም በልዩ ሁኔታ ከማየት ባለፈ ገበሬዎች  ቦታውን አለማለሁ ካሉ እንደሚችሉ እየሄደበት ያለው መንገድ ሁሉ አጀንዳ ፈጣሪዎችን ''ጨረቃ ላይ የጣለ'' ጉዳይ ሆኗል፣


- የአዲስ አበባ መስተዳድር በተመለከተ ግን ከተማዋን የሚመጥን አቅም ያለው እና የዲሞክራሲያዊ አካሄድን  የሚያሳይ የኢትዮጵያ ''ሞዴል'' በሚሆን የምርጫ ሂደት ህዝቡ አስተዳደሩን እንዲመርጥ ማድረግ የግድ የግድ አስፈላጊ ነው፣
- ምክንያቱም የአዲስ አበባ ሕዝብ በብዙ መልኩ ስለ ዲሞክራሲ፣ሕግ ማክበር እና ውሁድ ኢትዮጵያዊ ፖለቲካ ስልጡን ከሚባሉ የሀገራችን ክፍል አንዱ ነው፣
- ስለሆነም የአዲስ አበባን ጉዳይ በዙርያዋ ካሉ ኢትዮጵያውያን ገበሬ ነዋሪዎች ጋር ማኅበራዊ ትስስሩን አጎልብቶ ህዝቡ  የራሱን አስተዳደር እንዲመርጥ መብቱ ሊሰጠው ይገባል።ለእዚህም መንግስት በቀን የተቀመጠ የምርጫ ሰሌዳ ከአሁኑ ቢያስቀምጥ መልካም ነው።


በውጭ ያለው ዲያስፖራ ምን ያድርግ፣


- በውጭ ያለው ዲያስፖራ ኮሚኒቲውን ያጠናክር፣የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችን አቅም ያጠናክር ፣ የቱሪዝም ፍሰት እንዲጨምር ያለበትን ሀገሮች ዜጎች ይገፋፋ፣ ሃገሩን ያስተዋውቅ፣

-  በውጭ ያለው ዲያስፖራ ሃገራዊ የሆኑ በርካታ ውይይቶችን እያዘጋጀ አጠገቡ ያሉትን ምሁራን እየጠራ ይሞግት፣
- በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ማኅበራዊ አንድነቱን አጠናክሮ በምጣኔ ሀብት ዘርፍ የሚሰራውን ሥራ መቀጠል አለበት።
- በውጭ ያለው ዲያስፖራ አጉራ ዘለል እና የእርስ በርስ የብሔር እና የሃይማኖት ልዩነት ለማስፋት የሚሰሩትን  ይሞግት፣
- በውጭ ያለው ዲያስፖራ አጠገቡ ያሉ መልካም ሰዎችን ተስፋ ለማስቆረጥ የሚሞክሩትን ተከላክሎ ይሸልም፣
- በውጭ ያለው ዲያስፖራ ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅቶችን ለመመስረት ሃሳቦችን ያመንጭ ይንቀሳቀስ፣
- በውጭ ያለው ዲያስፖራ አዲስ የመጣውን ትውልድ ተስፋ በማያስቆርጥ መልኩ ስለሀገሩ ይንገር፣ይህንን ትውልድ በሁሉም መልክ የተደራጀ እንዲሆን ይርዳ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እና የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ኃላፊነት ምን መሆን አለበት?

- ኢትዮጵያ ቢያንስ ከ80% በላይ ህዝቧ በሃይማኖት ውስጥ ያለ ነው፣

- ይህ ሆኖ ግን የሃይማኖት አካላት አደረጃጀት እና ታማኝ የሆነ አወቃቀር ተጎሳቁሏል፣
- በውስጣቸው ግን የተገፉ እና የማገልገል እድሉን በሌቦች እና የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች የተነጠቁ፣አቅሙ፣ችሎታው፣ ፍላጎቱ እና መንፈሳዊነቱ ያላቸው በርካታ ሰዎች ይዘዋል፣
- ስለሆነም የሃይማኖት አካላት እነኝህ መልካም ሰዎች ወደፊት እና ወደ መምራት እንዲመጡ መንገዱ በመንግስትም ሆነ በሕዝብ የግድ መከፈት አለበት፣
- ይህ ካልሆነ የሃይማኖት አካላት ውድቀት ኢትዮጵያን በእጅጉ የሚጎዳ ትልቅ የታሪክ ጠባሳ ይሆናል።

ማጠቃለያ 

ወደ መደምደምያ ነጥቦች ከመምጣቴ በፊት፣የመነሻ ርዕሱ ስጋት እና ዕድል ስለሚል ዕድል የተባሉት የት አሉ? ብሎ ለሚጠይቅ  ከላይ የተነሱት ውስጥ መከናወን አለባቸው የምላቸው ነጥቦች ከተፈፀሙ የኢትዮጵያ እድሎች እንደሆኑ እንዲወሰድ እፈልጋለሁ።እየሆኑ ያሉት እና የምታቀዱት መጥፎ ዕቅዶች ደግሞ የዛሬም ሆነ የነገ ስጋቶች ናቸው።

ለማጠቃለል ይህንን በዝርዝር ያልተፃፈ ነገር ግን በምጥን የቀረበ የኢትዮጵያ ወቅታዊ እና መጪው ስጋት፣ዕድሎች በተመለከተ የቀረቡትን ነጥቦች በሚከተሉት ነጥቦች እደመድማለሁ።



  • ኢትዮጵያ አሁን በፅንፈኛ የብሔር ኃይሎች አሁን ያለውን የለውጥ ኃይል ለመፈታተን የሚደረጉ ሙከራዎች ከኦነግ ፅንፈኛ ኃይል፣ከዓማራ ፅንፍ የያዘ ብሔርተኛ ቅስቀሳ እና ከህወሓት አመራሮች አሉ። ወደፊትም መልካቸውን ቀይረው ይኖራሉ።
  • የኦሮሞ ብሔርተኛ የፅንፍ አስተሳሰብ አራማጆች ለኦደፓ እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ቀዳሚ አደጋዎች ናቸው።
  • የኦሮሞ የፅንፍ ብሔር አራማጁ በአክትቪስት እና ''ሜጫ'' የሚመራው ቡድን አጀንዳውን ወደ ፅንፍ የሙስሊም  እንቅስቃሴ ለመቀየር እና ከጀርባ ሆኖ ለመዘወር እንቅስቃሴ ላይ ነው።
  • ለእዚህ ጥፋት የብሔር ፖለቲካ እንደመጋቢነት እየጠቀመው ስለሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አስተዳደርም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍጥነት ይህንን ጉዳይ ለመግታት መንቀሳቀስ አለባቸው። ለእዚህም ሃገራዊ አንድነት ማጠናከር እና መተማመን እንዲሰፍን ማድረግ ያስፈልጋል።
  • በቅርቡ የሚነሳው የትግራይ የውስጥ የለውጥ አስተዳደር እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ሕዝብ መደገፍ እና ከብሔር  ፖለቲካ የራቁ ኃይሎች ህወሃትን እንዲተኩ ማገዝ ያስፈልጋል።
  • የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ ላይ እጃቸውን ሊከቱ የሚፈልጉ አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ አረብ ሀገራት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስደንጋጭ እርምጃ ከመንግስት ያስፈልጋል።
  • በኢትዮጵያ ያለውን ድህነት ለመቀነስ እውቀቱ፣የገንዘብ አቅሙ እና ልምዱ ያላችሁ ሁሉ መንግስትን ለማገዝ መነሻው ጊዜ አሁን ነው።
  • የድህነቱ መቃለል እና ከፍተኛ የስራ ዕድል ወጣቱ እንዲኖረው በማድረግ ውስጣዊ ውጥረት ማርገብ እና የፅንፍ ኃይሎች ወጣቱን መጠቀምያ እንዳያደርጉ ዋነኛው እና ቁልፉ ጉዳይ ነው።
  • አሁንም የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ መንግስታዊ አሰራር ማጠንከር፣መርዳት ማለት የብሔርም ሆነ የእስልምና ፅንፈኛ ኃይሎች እንዳይገዳደሩት እና ኢትዮጵያ አደጋ ላይ እንዳትወድቅ የመስራት ዋነኛው የትኩረት ቦታ መሆኑን መለየት እጅግ አስፈላጊ ነው።
========================/////=====================


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።