ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, November 26, 2018

ግጥም በጠብ-መንጃ (ቪድዮ)

ግጥም በጠብ-መንጃ በአርቲስት ፍቃዱ ከበደ


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Tuesday, November 20, 2018

የዘገየ አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ለውጥ እንደቀረ ይቆጠራል።የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ይመለከታል።

ጉዳያችን GUDAYACHN
ሕዳር 12/2011 ዓም (ኖቬምበር 21/2018 ዓም)

በእዚህ ፅሁፍ ስር የሚገኙ ሁለት ገዢ  ነጥቦች 



  • ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመታደግ በፍጥነት መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ምን ምንድናቸው?
  •  የጎጥ እና የዘረፋ ኃይሉ በታሪክ ያልታየ ግጭት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊፈጥር ይችላል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትባላለች።ከሁለት ሺህ ዓመታት በዓይ ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ፣ማኅበራዊ እና ታሪካዊ ሂደት ጋር ስትወጣ እና ስትወርድ የኖረች ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትሰኛለች።የሶርያ ኦርቶዶክስ የሶርያ ቤተ ክርስቲያን እንደምትባል፣ "ቤተ ክርስቲያኒቱ ሀገር ማለት ነች" እንዳሉት ዶ/ር ዓብይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሰኘቷ በብዙ ዕይታ ጥያቄ ውስጥ አይገባም።

ይህች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሁለት ሺህ ዓመታት ታሪክ ውስጥ ከደረሰባት ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፉት 27 ዓመታት የደረሰባት በቡድን የተደራጁ ዘራፊዎች እና ጎጠኞች ያደረሱባት መቦርቦር እና መጎሳቆል እጅግ ከምንገምተው በላይ የከፋ ነው።የቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረት ከቤተ ክህነት እስከ አጥብያ ድረስ የግለሰቦች መጠቀምያ ሆኗል፣ዝርፍያው እንዳይደናቀፍባቸው ዘራፊ የጨለማ ቡድ አባላት  ከጳጳሳት ማስደብደብ፣እስከ አጥብያ አስተዳዳሪ በመኪና ለማስገጨት እስከመሞከር፣ከሀገር ማሰደድ እስከ እስርቤት መወርወር ድረስ በአገልጋይ ካህናት እና ምዕመናን ላይ ፈፅመዋል።ይህ ብቻ አይደለም የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ዘመናዊ መልክ ይዞ ለዝርፍያ እንዳይመች ሆኖ ይዋቀር ብለው በከፍተኛ አማካሪዎች ታግዘው ያቀረቡት የማሻሻያ መዋቅር የአዲስ አበባ አድባራት አስተዳዳሪዎች ከ90% በላይ የደገፉት ቢሆንም አሁንም የዘራፊው እና የጎጥ ቡድን አባላት የማሻሻያ ሃሳብ ባቀረቡት ላይ ከማስፈራራት ጀምሮ እስከ ስም ማጥፋት በፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ጭምር ተደግፈው ፈፅመዋል።

ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመታደግ በፍጥነት መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ምን ምንድናቸው?


አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱ  የተፈፀመባትን ግፍ የመዘርዘርያ ጊዜ አይደለም።በደረሰባት ግፍ መጠን የግፉ እና የዘረፋውን አካላት የመቁረጫ ጊዜ ግን ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የሚከተሉት ተግባራት በቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት እና በመንግስት መወሰድ አለበት። እነርሱም : -
  • ምእመናንን፣የቤተ ክርስቲያናትን የአገልግሎት አካላት በየደረጃው  እና መንግስትን የሚያነቃ ለተግብራዊነቱ ፍጥነት የሚያሳስብ የማኅበራዊ ሚድያ ዘመቻ እና የቃል ለቃል እንዲሁም ቤት ለቤት የሚሄድ ቅስቀሳ ማድረግ። ቅስቀሳው ሌቦችን፣ዘራፊዎችን እና በጎጥ ብቻ ተጠራርተው የተሿሹሙትን በሙሉ መንጥሮ ለማውጣት ዘመቻ ስለሚጀመር የስነ ልቦና ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን በየደረጃው የመጠበቅ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለሁሉም ማሳሰብንም ይጨምራል።
  • የቤተ ክርስቲያኒቱን የለውጥ ሂደት (አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ለውጥ) የሚያስተባብር ልዩ ግብረ ኃይል ከቅዱስ ሲኖዶስ፣ከምእመናን እና የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታይ ከሆኑ ከመንግስት አካላት እንዲመሰረት ማድረግ።
  • ግብረ ኃይሉ በመንግስት ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያለውን ምዝበራ እና ዝርፍያ የሚያጣራ እና በአጭር ጊዜ ዘራፊዎቹ ከስራ እንዲታገዱ የሚያስደርግ እና ለሕግ (ቤተ ክርስቲያን በፍትሕ መንፈሳውም ልታየው የምትችልበት ልዩ የፍትሕ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ልትዳኘው ወይንም በመደበኛ ፍርድ ቤት መቅረብ ያለባቸው ለሕግ እንዲቀርቡ የማመቻቸት እና አስፈላጊ ከሆነም ከሕግ አካላት ጋር በመሆን ከምእመናን የሚመጡ ጥያቄዎችን በሕግ አግባብ እንዲፈቱ ወደ ፍርድ ቤት የሚወስድ መሆን ይገባዋል።
  • የቤተ ክርስቲያኒቱ ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀስ ንብረት በሙሉ የማጣራት ተግባር እስኪጠናቀቅ ድረስ ከስራ ማስኬጃ እና የካህናት ደሞዝ በቀር በዝግ ሂሳብ መያዝ።ይህም በግርግር በርካታ ንብረት እንዳይሸሽ ይረዳል።
  • በቀጣይ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር እና የገንዘብ አስተዳደር በዘመናዊ የአሰራር አግባብ እና የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና እና ዶግማ ባላፋለሰ መልክ ማደራጀት።
  • የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ተግባራዊነት መከታተል ፣ ወንጀለኞችን በፍትህ መንፈሳዊም ሆነ  በተደረሰበት ስምምነት መሰረት መቅጣት።
  • የማሻሻያውን ሂደት በሙሉ ምእመናን እና የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ የሚገዳቸው ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንዲከታተሉት ልዩ የሚድያ አገልግሎት መስጠት የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
የማሻሻያ ለውጡ በፍጥነት ካልተጀመረ የሚከተለው አደጋ 

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተንሰራፋውን የጎጥ እና የዘረፋ ቡድን በቶሎ እጅግ በፍጥነት የማምከን ሥራ ካልተሰራ አደጋ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ደረጃም ሊከሰት ይችላል።እርሱም : -

 የጎጥ እና የዘረፋ ኃይሉ በታሪክ ያልታየ ግጭት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊፈጥር ይችላል።

አሁን በኢትዮጵያ ያለው የለውጥ ንፋስ ያልተስማማቸው የቀድሞው አረመኔያዊ ዘመን እንዲመለስ የሚመኙ አካላት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ጊዜ እና ወቅት እየጠበቁ ነው።እነኝህ በውሸት ምንኩስና እና ቅስና ተሸፍነው በስለላ እና በዘረፋ በቡድን የሚንቀሳቀሱ አካላት ለተኮላሸው የጎጥ ስርዓት የመጨረሻ ምሽግ እና ታማኝነታቸውን ለመግለጥ እና የለውጥ አሰራሩ እነርሱ ላይ እንደሚያነጣጥር ስለሚረዱ  በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አዲስ ግጭት ለማቀናበር እና ትኩረቱ ሁሉ ወደዚሁ ግጭት እንዲሆን አይሰሩም ብሎ ማሰብ አይቻልም።ይህ ደግሞ አደጋው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይሆን ከሃምሳ ሚልዮን በላይ ምዕመን ለያዘችው ሀገርም ጭምር ነው። የተሸነፈው የጎጥ ቡድን የዶ/ር አብይ የለውጥ ኃይል ወደ ስልጣን ከመጣ ከመጋቢት 24/2010 ዓም ጀምሮ ለውጡን ለመገዳደር የተጠቀመበት መንገድ ህዝብን በጎሳ ማፋጀት ነበር።ይህ ጉዳይ አለማዋጣቱ እየታየ ስለመጣ ቀጣዩ የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ይህንን ከቤተ ክህነት እስከ አጥብያ የተዘረጋውን የጎጥ እና የዘራፍ ቡድን ለግጭት ያለፈው ስርዓት አይጠቀምበትም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።ለእዚህ ነው እጅግ በፈጠነ መልክ ቡድኑን እና አሰራሩን ማምከን እና ቤተ ክርስቲያኒቱን በዘመናዊ አሰራር እና መዋቅር ሃያ አንደኛውን ክ/ዘመን ማሻገር ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ማሻገር መሆኑን መረዳት የሚገባው።

ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዶግማዊ እና ቀኖናዊ ሳይሆን አስተዳደራዊ እና መዋቅራዊ ለውጥ ለማድረግ በቅድምያ በውስጧ የተሰገሰጉትን የዘራፊ እና የጎጥ ቡድን ነጥሎ ለሕግ ተገዥ ማድረግ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ የነበራትን የሞራል ልዕልና ለአዲሱ ትውልድ የምታሳይ አድርጎ ማዘጋጀት እጅግ አስፈላጊ ነው።
ለጎጥ እና ዘራፊው የጨለማ ቡድን ቀናት አይደለም ሰዓታት መስጠት እጅግ ውድ ዋጋ ይስከፍላል።

ቤተ ክርስቲያንን አንተውም ከቶ (ኦድዮ መዝሙር)







ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Wednesday, November 14, 2018

በሜቴክ ውስጥ በተፈፀሙ የዝርፍያ ወንጀሎችና የምርመራ ሂደቱ ላይ ያተኮረ አዲስ ዶኩመንተሪ

የሜቴክ ኃላፊ ክንፈ ዳኘው እስር በኃላ የቀረበ  ዶኩመንተሪ ፊልም።
ማሳሰቢያ - ይህ ዶኩመንተሪ ፊልም በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ህዳር 4 እና 5/2011 ዓም ምሽት የቀረበ ነው።
 ።

ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Tuesday, November 13, 2018

ሊደመጥ የሚገባው የወቅቱ ዜማ

ጉዳያችን/ Gudayachn
የአቃቢ ሕግን ጋዜጣዊ መግለጫ ሙሉ ቪድዮ ለመመልከት ይህንን ይጫኑ ።
ድምፃዊ ኃይልዬ ታደሰ



ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Monday, November 12, 2018

ሰበር ዜና - በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በከፍተኛ የሀገር ዘረፋ የተሳተፉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ። የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ የሰጡት መግለጫ ሙሉ ቪድዮ ይመልከቱ

ከእዚህ በታች የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ  ዛሬ ህዳር 3/2011 ዓም የሰጡትን  መግለጫ  ቪድዮ 


ጉዳያችን / GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Wednesday, November 7, 2018

ኢቢሲ ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ በእዚህ ሳምንት አየር ላይ ውሏል።(ቪድዮ)

ፕሮፌስር ብርሃኑ ነጋ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣብያ (ኢቢሲ) ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገዋል።የመጀመርያ ክፍል እነሆ: -
Ethiopian opposition political organisation, founded in 2008, Patriot Ginbot 7 chairman Professor Birhanu Nega interview with state tv-EBC
ጥቅምት 29/2011 ዓም  



ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Monday, November 5, 2018

ማንም ጦር እንዲሰብቅ ሊፈቀድለት አይገባም! የኢትዮጵያ ሕዝብ በጦርነት ደጋሹ ላይ ተቃውሞ ማሰማት አለበት።

ጉዳያችን/Gudayachn
ጥቅምት 28/2011 ዓም (ኖቬምበር 6/2018 ዓም)

 በትግራይ እና በአማራ አዋሳኝ አካባቢዎች በተለይ በወልቃይት እና  በራያ የሚኖረው ሕዝብ ክፉውንም ደጉንም ጊዜ  ለዘመናት አብረው አሳልፈዋል።ሆኖም ግን ላለፉት ሀያ ስምንት ዓመታት ህወሓት የወልቃይት እና የራያ ነዋሪዎችን ወደ ትግራይ ክልል ለመከለል በሄደበት የኃይል ተግባር ሳብያ በክፉም ሆነ በደግ አብረው ለዘመናት ተደጋግፈው የኖሩትን ሕዝብ እንዲጋጩ ምክንያት ሆኗል።ግጭቶቹ አሁንም ሕዝብ ለሕዝብ ነው ለማለት አይቻልም።ሕዝብ እርስ በርሱ ተመካክሮ ለችግሮች መፍትሄ እንዲሰጥ ዕድል የሰጠው የለም።ይልቁንም አዛውንቶችን እና አሮጊቶችን ሳይቀር ጠብመንጃ እያሸከሙ ሰልፍ እያስወጡ በቴሌቭዥን እንዲፎክሩ በማድረግ የእርስ በርስ ጦርነት የሚያውጅ ተግባር በህወሓት በኩል ከሶስት ዓመት በፊት ጀምሮ ሲስተጋባ ነበር።

አሁን በትግራይ እና በአማራ መካከል ምንም አይነት ግጭት ቢፈጠር የግጭቱ ታሪካዊ ሂደት በግልጥ የታወቀ ነው።በወልቃይት ጉዳይ የወልቃይት ኮሚቴ የሄዱበት ሰላማዊ ሂደት በድምፅም ሆነ በፅሁፍ ሰነድ የተመዘገበ ነው።ለተነሱት ሰላማዊ ጥያቄዎችም የተሰጠው የኃይል ምላሽ እንዲሁ የተመዘገበ ነው።የግጭቶቹ መነሻ የሆኑት የወልቃይትም ሆነ የራያ አካባቢ ሕዝብ ምን እንደጠየቀ እና ከህወሓት ምን አይነት ምላሽ እንደተሰጠው ይታወቃል። ይህ ማለት አሁን ለሚፈጠረው ግጭት መንስዔውም አሻሚ አይደለም።የወልቃይትን ጉዳይ በተመለከተ በቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ወቅት የትግራይ ገዢ እና ከትግራይ ባላባት የሚወለዱት ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ከተናገሩት በላይ እማኝ አያስፈልግም።ልዑል ራስ መንግሻ ስዩም ወልቃይት እኔ ሳስተዳድረውም የማውቀው ቀደም ብሎም በጎንደር ግዛት እንደሆነ እንደሚያውቁ ተናግረዋል። በመሰረቱ በአንድ ሀገር ውስጥ እየኖሩ ህዝብን በክልል ወዲህ እና ወዲያ እያሉ ማንገላታት ተገቢ አልነበረም።

ባጠቃላይ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መሐከል ማንም ጦር እንዲሰብቅ ሊፈቀድለት አይገባም።ኢትዮጵያ ከበቂ ጊዜ በላይ የጦርነት ዓመታት አሳልፋለች። ሕዝብ በካድሬዎች የተንኮል መረብ እየገባ በጎሳ ግጭት ልጆቹን ገብሯል። አሁንም ይህ ጥቁር ታሪክ ሊደገም አይገባም።ለእዚህ መፍትሄው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነት አንፈልግም ብሎ መነሳት አለበት።ህወሓት የመጨረሻ አማራጩ በሚፈጠር ግጭት ትርፍ ለማግኘት መሞከር መሆኑ የታወቀ ነው።''በትግራይ ኦን ላይን'' በእንግሊዝኛ በቅርቡ የተለቀቁ መጣጥፎች ርዕሶች ብቻ በመጥቀስ ምን አይነት የጠብ ጫሪነት እየተፈፀመ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ከመጣጥፎቹ ርዕሶች አንዱ ''የወልቃይት እና ጠገዴ ነዋሪዎች ትግራይን ከአማራ ወራሪዎች ለመከላከል ዝግጁነታቸውን ገለጡ'' ሲል ከእዚህ ፅሁፍ ቀደም ብሎ የወጣው የእንግሊዝኛ ፅሁፍ ርዕስ ''የራያን ጉዳይ ማንሳት በትግራይ ላይ ጦርነት ማወጅ ነው'' ይላል። ይህ ሁሉ የጀብደኝነት አካሄድ አደገኛ መንገድ ነው።ከግጭቱ ማንም ምንም አያተርፍም።የኢትዮጵያ ሕዝብ በጦርነት ደጋሹ ላይ ተቃውሞ ማሰማት አለበት።ከእዚህ በተለየ በሁሉም ወገን የፉከራ እና የቀረርቶ ድምፅ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም።አንዳንድ በውጭ የሚኖሩ አፍቃሪ ህወሓትም ሆኑ በአማራ ስም የሚንቀሳቀሱ ጦርነት እንዲነሳ ከሚቀሰቅሱ ንግግሮች እራሳቸውን መቆጠብ አለባቸው።

''ላንተም አለ  በጋ '' በድምፃዊ  ዳዊት ፅጌ   



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Saturday, November 3, 2018

የኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ለአንድ መቶ ዓመታት የተሰሩ ስህተቶች እንዳይደግም ጥንቃቄ ይደረግ።ችግራችን የትምህርት ጥራት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊውን ዕውቀት የመግፋት ችግርም ነው።

ጉዳያችን/Gudayachn
ጥቅምት 24/2011 ዓም (ኖቬምበር 3/2018 ዓም)

ኢትዮጵያ በሌላ ወሳኝ የሽግግር ወቅት ላይ ትገኛለች።ሽግግሩ የፖለቲካ አስተሳሰብ ስርዓትን ብቻ ሳይሆን አዲስ የመጣው ትውልድ አዲስ ዘመናዊ አስተሳሰብን ሁሉ ያካተተ ነው።ለአንድ ትውልድ አዲስ አስተሳሰብ ማምጣት አንዱ እና ወሳኙ ጉዳይ የትምህርት ፖሊሲው ትውልዱን የቀርፀበት መንገድ ነው።ኢትዮጵያ ላለፉት 100 ዓመታት ያሳለፈችው የትምህርት ሂደት ባብዛኛው ሀገራዊ እና ለዘመናት በእራሷ የመንግስት ስሪት እና ማኅበራዊ መስተጋብር ይዛ እንድትሻገር ያደረጋትን ዕውቀት ሙሉ በሙሉ ያገለለ የትምህርት ፖሊሲ ትውልዱ እውቀት ከውጭ የሚመጣ ብቻ አድርጎ የምደመድም መምህር እና ተማሪ አፍርቶ መኖሩ በእጅጉ ጎድቶናል።

በእዚህም ሳብያ በሀገር ውስጥ ያሉብንን መሰርታዊ ችግሮች ላይ ተመራምሮ መፍትሄ ሰጪ ትውልድ ሳይሆን ኢትዮጵያ የሌላትን የገበያ ስሪት ለምሳሌ  ስለ የውጭ ገበያ (''ስቶክ ኤክስቼንጅ'') የሚተነትን የምጣኔ ሀብት አዋቂ አፈራን እንጂ የጉልት ንግድን እንዴት ወደ ትልቅ ገበያ የሚያሳድግ ሊቅ አላፈረናም።ስለ አውሮፓ፣ሩስያ  እና አሜሪካ ሰፋፊ የእርሻ ምርት የሚተርክ እንጂ የኢትዮጵያን የመሬት አጠቃቀም፣ የእርሻ አስተራረስ ወደ ዘመናዊ መልክ ስለማሸጋገር የሚሰራ ምሁር አላፈራንም።ለእዚህ ነው ኢትዮጵያ ከብዙ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ከአንዳንድ የሩቅ ምስራቅ ሀገሮች ሳይቀር ቀድማ፣የካቢኔ ሚኒስትር መስርያቤቶች (ከመቶ ዓመት በፊት በአፄ ምንሊክ ዘመን)፣የፓርላማ ስርዓት (በ1923 ዓም ጣልያን ሳይገባ) እና ዘመናዊ ጋዜጣ እና ኮሌጅ (አዲስ ዘመን በ1935 ዓም፣ የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ከአዲስ አበባይ ዩንቨርስቲ ምስረታ በፊት) ቢኖሯትም ኢትዮጵያን በሚፈለገው ደረጃ ያሸጋገሩ ሳይሆኑ ለምዕራቡ ዓለም መጋቢ ምሁራንን አፍራን እንጂ ኢትዮጵያን ወድሚገባው ደረጃ አላሸጋገርናትም።

በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተጀመረው አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ባለድርሻ አካላትን እያሳተፈ እና  ውይይት እየተደረገበት ነው።በትናንትናው እለትም አዳማ ላይ የወላጆች ሀገር አቀፍ ኮሚቴ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ 55 አባላት ያሉት ኮሚቴ እና 11 ሥራ አስፈፃሚዎች መርጧል። ፍኖተ ካርታው ወላጆችን ማሳተፉ በጎ ተግባር ቢሆንም ዋናው የኢትዮጵያ ትምህርት ችግር ሃገራዊ እሴቶችን አለመጠቀሙ እና ማግለሉ አንዱ እና አይነተኛው የዘመናት ችግራችን በመሆኑ ይህንን ችግር በአንቀጽ እና ሃገራዊ ምሁራንን የማሳተፉ እና በትምህርት ሂደቱ ማለትም ከመምህራን ስልጠና ጀምሮ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።

ከእዚህ በታች ሁለት ጠቃሚ ቪድዮዎች ተለጥፈዋል። አንዱ በሸገር ራድዮ ላይ የቀረበ የኢትዮጵያ ያለፉ የትምህርት ስርዓቶች የነበሩባቸውን የመነሻ ችግር የሚያብራራ የምሁራን ውይይት ሲሆን፣ ሁለተኛው ቪድዮ በቅርቡ የኢትዮጵያን የትምህርት ፍኖተ ካርታ ሲያስጀምሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ያደጉት ንግግር ነው።

ቪድዮ አንድ 
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት በተመለከተ በሸገር የተደረገ ከምሁራን ጋር የተደረገ ውይይት 


ቪድዮ 2 
 ''ላለፉት 20 ዓመታት በተግባር ላይ ያለው  የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ ያስገኘው ጥቅም እንዳለ ሆኖ በአብዛኛው ፍሬያማ አልነበረም '' ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የትምህርት  ፍኖተ ካርታ የተመለከተ ጉባኤ ሲከፍቱ የተናገሩት 


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Thursday, November 1, 2018

በቴፒ አዳዲስ የመከላከያ የደንብ ልብሶች በግለሰብ ቤት ተደብቆ ተገኝቷል። የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል በነዋሪዎች ላይ ግፍ እየፈፀመ ነው።ትምህርት ቤቶች እስካሁን አልተከፈቱም።የፌድራል ሰራዊት ካልገባ አዲስ ግጭት ሊያገረሽ ነው።

ጉዳያችን/Gudayacn Exclusive
ጥቅምት 23/2011 ዓም (ኖቬምበር 2/2018 ዓም)
(ከዜናው መጨረሻ የተለጠፈው የጃኖ ባንድ አዲስ ኢትዮጵያ የጥቁር አልማዝ የሚለው ሙዚቃ ቪድዮ ከዜናው ጋር ግንኙነት የለውም)
========================================
በደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ቡና አምራች ክፍል በቴፒ  ከተማ አዲስ ውጥረት አለ።ለጉዳያችን በተለይ በደረሰ መረጃ መሰረት ላለፉት 28 ዓመታት በህወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት ከተማዋን ማዕከል አድርጎ የተፈጠረው የእርስ በርስ የጎሳዎች የማቃቃር ሥራ እስከአሁን ድረስ ቴፒን አለቀቃትም።የህወሓት ኢህአዴግ ስርዓት ደጋፊዎች ሸክቾ ጎሳ አባላት በብቸኛነት በከተማዋ የስልጣን እርከን እንዲይዝ መደረጉ የሚታወቅነው።
ሌሎችብሔረሰቦች ኦሮሞ፣ከፋ፣ሸኮ፣መጀንግር።ዳውሮ።ወላይታ፣ጉራጌ፣ስልጤ፣ትግራይ፣ዓማራ፣ሲዳማ፣ሱማሌ፣ቤንች፣ሜኒት፣ዲዙ እና ሌሎች ነዋሪዎች በሙሉ ግን መብታቸው ተደፍጥጦ በተለያዩ ጊዚያት ግጭቶች እየተፈጠሩ የሰው ሕይወት ሲጠፋ ኖሯል።

ከአንድ ወር በፊት ወ/ሮ ሙፈርያ ከማል (የአሁኗ የሰላም ሚኒስትር ) ቴፒ ከተማ ተገኝተው እርቅ ለመፍጠር በጠሩት ስብሰባ ላይ አፍቃሪ ህወሓት - ኢህአዴግ ባለስልጣናት የሚፈልጉትን ሰው ብቻ መርጠው አዳራሽ እንዲገኝ አድርገው ህዝቡ ብሶቱን ለወ/ሮ ሙፈርያ እንዳያሰማ ስብሰባውን  እንደጠለፉት ተሰምቶ ነበር።ይህ ስብሰባ በኢትዮጵያ ቴሌቭዝንም ተዘግቦ ነበር።ጉዳዩን ተከትሎም የመከላከያ ኃይል ወደ ከተማዋ ገብቶ ከቆየ በኃላ  ወ/ሮ ሙፈርያ ከአዳራሽ ስብሰባውን ትተው እንደሄዱ የመከላከያ ኃይል ለቆ ሲወጣ የደቡብ ልዩ ኃይል ከተማዋን ተቆጣጠረ።


የደቡብ ልዩ ኃይል ግን ለቴፒ ከተማ አዲስ መከራ ይዞ መጣ።አፍቃሪ ኢህአዴግ የሸክቾ ተወላጆች የደቡብ ልዩ ኃይል ካላይ የተጠቀሱትን ውሁዳን እና ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች ወጣቶች በግፍ እንዲደበደቡ በገንዘብ እና በጥቅማ ጥቅም እንደያዟቸው እና ሕዝቡን እየመረጠ ልዩ ኃይሉ እየደበደበ በመሆኑ  ከፍተኛ ቁጣ በከታማዋ ውስጥ ፈጥሯል።ህዝቡ አቤቱታውን ለማዕከላዊ መንግስት እንዲደርስለት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም እስካሁን በደቡብ ክልል ባለስልጣናት መታፈኑ እና አሁን ጉዳዩ እጅግ አደገኛ ደረጃ ደርሶ የደቡብ ልዩ ኃይልን ጨምሮ በኃይል ሕዝብ ለማስወጣት ቀናት ሳይሆን ሰዓታት የቀሩት መሆኑን የሚመጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።


ይህ በእንዲህ እያለ አፍቃሪ ህወሓቱ የሸክቾ ተወካይ ነን የሚሉ ባለስልጣናት በግለሰብ መኖርያ ቤት ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ ደብቀው ማስቀመጣቸው እና አንድ ሌሊት የደንብ ልብሱን ለብሰው የመከላከያ ሰራዊት ገባ ብለው የሌላውን ብሔር ተወላጆች ሊያጠቁ ዝግጅት ላይ እንደነበሩ በጥቆማ ይሰማል።ሕዝብ ቤቱ ይፈተሽ ብሎ አቤት ይላል።ሰሚ ያጣል።በመሀከል የመከላከያ ሰራዊት መጥቶ እንዲፈትሽ ሲደረግ በርካታ የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ ይገኛል። ይህ ሁኔታ በርካታ ጥያቄዎች አስነስቷል። የደንብ ልብሱ ከጦር ሰራዊቱ ውስጥ ካልተገኘ ከየት መጣ? በሌሎች አካባቢ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዘመን በክልሎች ውስጥ የሰራዊቱን ደንብ የለበሱ ነገር ግን የሰራዊቱ አባል ያልሆኑ ግለሰቦች መንግስት ለማስጠላት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አሉ ወይ? የሚሉት እና ሌሎች ጥያቄዎች አስነስቷል።

ለማጠቃለል በቴፒ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ውጥረት አለ።የጥቅምት ወር ሊጠናቀቅ ቀናት ቢቀሩትም ትምህርት ገና አልተጀመረም።የደቡብ ልዩ ኃይል ሰላም ለመፍጠር ሕዝቡን ሲያግባቡ የነበሩ ወጣቶች ጀርባቸው በሚዘገንን ደረጃ ተገርፈዋል፣ ግድያም ተፈፅሟል።በአሰቃቂ ደረጃ ጀርባቸው የተላጠ ወጣቶች ፎቶ ግራፍ ለጉዳያችን ደርሷል።ሕዝብ የደቡብ ልዩ ኃይል ይውጣልን መከላከያ ይግባ! ከተማዋ በራሷ ነዋሪዎች ትተዳደር የሚሉ ድምፆች አሁንም ሰሚ አላገኙም።አሁን ሕዝብ የመጨረሻ ጠርዝ ላይ ደርሷል።  በድንገት ተንስቶ ግፈኞቹ የደቡብ ልዩ ኃይል ሰራዊት ለመፋለም ሰዓታት  እየቆጠረ ነው።ይህ ደግሞ ከፍተኛ እልቂት ያስከትላል።ነዋሪው በሩን ዘግቶ ተቀምጧል።የደቡብ ልዩ ኃይል ቤቶች እየመረጠ በጭካኔ ነዋሪው ላይ ጥቃት እየፈፀመ ነው።ነዋሪው እራሱን ለመከላከል በህብረት ለመውጣት ዝግጅት ላይ ነው።የሰላም ሚኒስቴር አደጋ ከመድረሱ በፊት ይህንን እልቂት ሊከላከል ስለሚገባ ለጉዳዩ እጅግ አፋጣኝ እልባት መስጠት ይገባል።

የጥቁር አልማዝ ኢትዮጵያ እማማ የተሰኘው የጃኖ ባንድ አዲስ ሙዚቃ(ቪድዮ) 

ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...