ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, November 3, 2018

የኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ለአንድ መቶ ዓመታት የተሰሩ ስህተቶች እንዳይደግም ጥንቃቄ ይደረግ።ችግራችን የትምህርት ጥራት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊውን ዕውቀት የመግፋት ችግርም ነው።

ጉዳያችን/Gudayachn
ጥቅምት 24/2011 ዓም (ኖቬምበር 3/2018 ዓም)

ኢትዮጵያ በሌላ ወሳኝ የሽግግር ወቅት ላይ ትገኛለች።ሽግግሩ የፖለቲካ አስተሳሰብ ስርዓትን ብቻ ሳይሆን አዲስ የመጣው ትውልድ አዲስ ዘመናዊ አስተሳሰብን ሁሉ ያካተተ ነው።ለአንድ ትውልድ አዲስ አስተሳሰብ ማምጣት አንዱ እና ወሳኙ ጉዳይ የትምህርት ፖሊሲው ትውልዱን የቀርፀበት መንገድ ነው።ኢትዮጵያ ላለፉት 100 ዓመታት ያሳለፈችው የትምህርት ሂደት ባብዛኛው ሀገራዊ እና ለዘመናት በእራሷ የመንግስት ስሪት እና ማኅበራዊ መስተጋብር ይዛ እንድትሻገር ያደረጋትን ዕውቀት ሙሉ በሙሉ ያገለለ የትምህርት ፖሊሲ ትውልዱ እውቀት ከውጭ የሚመጣ ብቻ አድርጎ የምደመድም መምህር እና ተማሪ አፍርቶ መኖሩ በእጅጉ ጎድቶናል።

በእዚህም ሳብያ በሀገር ውስጥ ያሉብንን መሰርታዊ ችግሮች ላይ ተመራምሮ መፍትሄ ሰጪ ትውልድ ሳይሆን ኢትዮጵያ የሌላትን የገበያ ስሪት ለምሳሌ  ስለ የውጭ ገበያ (''ስቶክ ኤክስቼንጅ'') የሚተነትን የምጣኔ ሀብት አዋቂ አፈራን እንጂ የጉልት ንግድን እንዴት ወደ ትልቅ ገበያ የሚያሳድግ ሊቅ አላፈረናም።ስለ አውሮፓ፣ሩስያ  እና አሜሪካ ሰፋፊ የእርሻ ምርት የሚተርክ እንጂ የኢትዮጵያን የመሬት አጠቃቀም፣ የእርሻ አስተራረስ ወደ ዘመናዊ መልክ ስለማሸጋገር የሚሰራ ምሁር አላፈራንም።ለእዚህ ነው ኢትዮጵያ ከብዙ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ከአንዳንድ የሩቅ ምስራቅ ሀገሮች ሳይቀር ቀድማ፣የካቢኔ ሚኒስትር መስርያቤቶች (ከመቶ ዓመት በፊት በአፄ ምንሊክ ዘመን)፣የፓርላማ ስርዓት (በ1923 ዓም ጣልያን ሳይገባ) እና ዘመናዊ ጋዜጣ እና ኮሌጅ (አዲስ ዘመን በ1935 ዓም፣ የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ከአዲስ አበባይ ዩንቨርስቲ ምስረታ በፊት) ቢኖሯትም ኢትዮጵያን በሚፈለገው ደረጃ ያሸጋገሩ ሳይሆኑ ለምዕራቡ ዓለም መጋቢ ምሁራንን አፍራን እንጂ ኢትዮጵያን ወድሚገባው ደረጃ አላሸጋገርናትም።

በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተጀመረው አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ባለድርሻ አካላትን እያሳተፈ እና  ውይይት እየተደረገበት ነው።በትናንትናው እለትም አዳማ ላይ የወላጆች ሀገር አቀፍ ኮሚቴ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ 55 አባላት ያሉት ኮሚቴ እና 11 ሥራ አስፈፃሚዎች መርጧል። ፍኖተ ካርታው ወላጆችን ማሳተፉ በጎ ተግባር ቢሆንም ዋናው የኢትዮጵያ ትምህርት ችግር ሃገራዊ እሴቶችን አለመጠቀሙ እና ማግለሉ አንዱ እና አይነተኛው የዘመናት ችግራችን በመሆኑ ይህንን ችግር በአንቀጽ እና ሃገራዊ ምሁራንን የማሳተፉ እና በትምህርት ሂደቱ ማለትም ከመምህራን ስልጠና ጀምሮ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።

ከእዚህ በታች ሁለት ጠቃሚ ቪድዮዎች ተለጥፈዋል። አንዱ በሸገር ራድዮ ላይ የቀረበ የኢትዮጵያ ያለፉ የትምህርት ስርዓቶች የነበሩባቸውን የመነሻ ችግር የሚያብራራ የምሁራን ውይይት ሲሆን፣ ሁለተኛው ቪድዮ በቅርቡ የኢትዮጵያን የትምህርት ፍኖተ ካርታ ሲያስጀምሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ያደጉት ንግግር ነው።

ቪድዮ አንድ 
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት በተመለከተ በሸገር የተደረገ ከምሁራን ጋር የተደረገ ውይይት 


ቪድዮ 2 
 ''ላለፉት 20 ዓመታት በተግባር ላይ ያለው  የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ ያስገኘው ጥቅም እንዳለ ሆኖ በአብዛኛው ፍሬያማ አልነበረም '' ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የትምህርት  ፍኖተ ካርታ የተመለከተ ጉባኤ ሲከፍቱ የተናገሩት 


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

No comments: