ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, November 5, 2018

ማንም ጦር እንዲሰብቅ ሊፈቀድለት አይገባም! የኢትዮጵያ ሕዝብ በጦርነት ደጋሹ ላይ ተቃውሞ ማሰማት አለበት።

ጉዳያችን/Gudayachn
ጥቅምት 28/2011 ዓም (ኖቬምበር 6/2018 ዓም)

 በትግራይ እና በአማራ አዋሳኝ አካባቢዎች በተለይ በወልቃይት እና  በራያ የሚኖረው ሕዝብ ክፉውንም ደጉንም ጊዜ  ለዘመናት አብረው አሳልፈዋል።ሆኖም ግን ላለፉት ሀያ ስምንት ዓመታት ህወሓት የወልቃይት እና የራያ ነዋሪዎችን ወደ ትግራይ ክልል ለመከለል በሄደበት የኃይል ተግባር ሳብያ በክፉም ሆነ በደግ አብረው ለዘመናት ተደጋግፈው የኖሩትን ሕዝብ እንዲጋጩ ምክንያት ሆኗል።ግጭቶቹ አሁንም ሕዝብ ለሕዝብ ነው ለማለት አይቻልም።ሕዝብ እርስ በርሱ ተመካክሮ ለችግሮች መፍትሄ እንዲሰጥ ዕድል የሰጠው የለም።ይልቁንም አዛውንቶችን እና አሮጊቶችን ሳይቀር ጠብመንጃ እያሸከሙ ሰልፍ እያስወጡ በቴሌቭዥን እንዲፎክሩ በማድረግ የእርስ በርስ ጦርነት የሚያውጅ ተግባር በህወሓት በኩል ከሶስት ዓመት በፊት ጀምሮ ሲስተጋባ ነበር።

አሁን በትግራይ እና በአማራ መካከል ምንም አይነት ግጭት ቢፈጠር የግጭቱ ታሪካዊ ሂደት በግልጥ የታወቀ ነው።በወልቃይት ጉዳይ የወልቃይት ኮሚቴ የሄዱበት ሰላማዊ ሂደት በድምፅም ሆነ በፅሁፍ ሰነድ የተመዘገበ ነው።ለተነሱት ሰላማዊ ጥያቄዎችም የተሰጠው የኃይል ምላሽ እንዲሁ የተመዘገበ ነው።የግጭቶቹ መነሻ የሆኑት የወልቃይትም ሆነ የራያ አካባቢ ሕዝብ ምን እንደጠየቀ እና ከህወሓት ምን አይነት ምላሽ እንደተሰጠው ይታወቃል። ይህ ማለት አሁን ለሚፈጠረው ግጭት መንስዔውም አሻሚ አይደለም።የወልቃይትን ጉዳይ በተመለከተ በቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ወቅት የትግራይ ገዢ እና ከትግራይ ባላባት የሚወለዱት ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ከተናገሩት በላይ እማኝ አያስፈልግም።ልዑል ራስ መንግሻ ስዩም ወልቃይት እኔ ሳስተዳድረውም የማውቀው ቀደም ብሎም በጎንደር ግዛት እንደሆነ እንደሚያውቁ ተናግረዋል። በመሰረቱ በአንድ ሀገር ውስጥ እየኖሩ ህዝብን በክልል ወዲህ እና ወዲያ እያሉ ማንገላታት ተገቢ አልነበረም።

ባጠቃላይ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መሐከል ማንም ጦር እንዲሰብቅ ሊፈቀድለት አይገባም።ኢትዮጵያ ከበቂ ጊዜ በላይ የጦርነት ዓመታት አሳልፋለች። ሕዝብ በካድሬዎች የተንኮል መረብ እየገባ በጎሳ ግጭት ልጆቹን ገብሯል። አሁንም ይህ ጥቁር ታሪክ ሊደገም አይገባም።ለእዚህ መፍትሄው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነት አንፈልግም ብሎ መነሳት አለበት።ህወሓት የመጨረሻ አማራጩ በሚፈጠር ግጭት ትርፍ ለማግኘት መሞከር መሆኑ የታወቀ ነው።''በትግራይ ኦን ላይን'' በእንግሊዝኛ በቅርቡ የተለቀቁ መጣጥፎች ርዕሶች ብቻ በመጥቀስ ምን አይነት የጠብ ጫሪነት እየተፈፀመ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ከመጣጥፎቹ ርዕሶች አንዱ ''የወልቃይት እና ጠገዴ ነዋሪዎች ትግራይን ከአማራ ወራሪዎች ለመከላከል ዝግጁነታቸውን ገለጡ'' ሲል ከእዚህ ፅሁፍ ቀደም ብሎ የወጣው የእንግሊዝኛ ፅሁፍ ርዕስ ''የራያን ጉዳይ ማንሳት በትግራይ ላይ ጦርነት ማወጅ ነው'' ይላል። ይህ ሁሉ የጀብደኝነት አካሄድ አደገኛ መንገድ ነው።ከግጭቱ ማንም ምንም አያተርፍም።የኢትዮጵያ ሕዝብ በጦርነት ደጋሹ ላይ ተቃውሞ ማሰማት አለበት።ከእዚህ በተለየ በሁሉም ወገን የፉከራ እና የቀረርቶ ድምፅ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም።አንዳንድ በውጭ የሚኖሩ አፍቃሪ ህወሓትም ሆኑ በአማራ ስም የሚንቀሳቀሱ ጦርነት እንዲነሳ ከሚቀሰቅሱ ንግግሮች እራሳቸውን መቆጠብ አለባቸው።

''ላንተም አለ  በጋ '' በድምፃዊ  ዳዊት ፅጌ   



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments: