ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, February 28, 2017

የዓድዋ ድል እና የቤተክርስቲያን ሚና



ከመንግሥቱ ጎበዜ
ሉንድ ዩንቨርስቲ፣ ስዊድን

  • አፄ ምኒልክ አዋጅን ካስነገሩ በኋላ በአዲስ አበባ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተገኝተው የተሳሉት ስዕለት “አምላከ ቅ/ጊዮርጊስ ድሉን ቢሰጠኝ ይህን የቅ/ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሣር ክዳኑን ለውጨ ባማረ ሕንፃ አሠራዋለሁ ” የሚል ነበር፡፡ 
  • ይህንም ስእለታቸውን ከድል በኋላ ፈጽመውታል፡፡
  • ሊቀጳጳሱ አቡነ ማቴዎስና በእጨጌ ወልደ ጊዮርጊስ በመላ ሀገሪቱ ጸሎት፣ ኀዘንና ምህላ አውጀው ነበር።
  • ቤተክርስቲያን  የአዝማች  ኮሚቴ አቋቁማ ነበር፣ 
  • ከዘመቻው በፊት ዘማች  አብያተክርስቲያናትም  ተለይተዋል፣  
  • በዘመቻውም ታቦት፣መስቀል፣ ንዋያተ ቅድሳት ቃጭል፣ጥላዎች እና ድባቦች ይዘው ሊቃውንቱ እና ካህናት ዘምተዋል።
                                                          
የአድዋ ጦርነት የምዕራባውያን ቅኝ ገዥዎች የመስፋፋትና አፍሪካን የመቀራመት ህልማቸው ውጤት ነው፡፡ እነዚሁ ምዕራባውያን አፍሪካን የመቀራመት ሩጫቸው ወደ ፀብ ሲያመራቸው ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት በርሊን ላይ ከ1977-1978 ዓ.ም ለረጅም ጊዜ ስብሰባ ተቀመጡ::የበርሊኑን ጉባኤ ተከትሎ ምዕራባውያኑ መጀመሪያ አፍሪካ ላይ የያዙት ቦታ መጀመሪያ ስለማያዛቸውና የነሱ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል ማስረጃ ፍለጋ ጀመሩ፡፡በዚህም የተነሳ አፍሪካ ውስጥ ብዙ የተጨበረበሩና የማታለያ  ስምምነቶችን አድርገዋል፡፡ በ1881 ዓ.ም በኢጣሊያዊ ተወካይ አንቶሎኒና በአፄ ምኒልክ መካከል የተደረገው ስምምነት ለዚህ ዋነኛው ማሳያ ነው፡፡ 

ለውጫሌ  ስምምነት ሃያ  አንቀጾች ያሉትና በሁለት ቋንቋዎች የተጻፈ ሲሆን የግጭቱ መንስኤ የሆነው በኢጣሊያንኛ ቋንቋ የተጻፈው 17ኛው አንቀጽ ነበር፡፡ የአማርኛው ውል ፡-የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የውጭ ግንኙነቱን  በኢጣሊያ አጋዥነት  ማድረግ ይቻላቸዋል በማለት ምርጫው የአፄ ምኒልክ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን  የጣሊያንኛው ትርጉም ደግሞ  አፄ ምኒልክ የውጭ ግንኙነቱን  በሙሉ በኢጣሊያ በኩል ማድረግ ይገባዋል በማለት ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ጥገኛ ያደርጋታል፡፡  በዚህም የተነሳ 17ኛውን አንቀጽ አዛብተው በመተርጐም ኢትዮጵያ በኢጣሊያ የሞግዚትነት አስተዳዳር ሥር ሆናለች ብለው ለዓለም መንግሥታት  ማሳወቅ ጀመሩ:: ከሩስያ በስተቀር መላው የወቅቱ ሃያላን መንግሥታት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የውጫሌ ውል ሰጥቶኛል የምትለውን ሥልጣን እውቅና ለመስጠት ዝግጁ ነበሩ፡፡ የሆነ ሁኖ ግን የውጫሌ ውል የተጭበረበረ መሆኑ ከታወቀ በኋላ በእነ አፄ ምኒልክ ተቀባይነት በማጣቱና ውሉን በማፍረሳቸው የአድዋ ጦርነት ሊመጣ ግድ ሆኗል፡፡

የመጀመያው ውጊያ አምባላጌ ላይ  በኅዳር 29 ቀን 1888 ዓ.ም ተደረጎ በራስ መኰንንና  በፊታውራሪ ገበየሁ የጦር መሪነት በድል ተጠናቀቀ፡፡ ሁለተኛው የጠላት ጦር መቀሌ መሽጐ ነበርና በእቴጌ ጣይቱ ዘዴ ውኃ የሚያገኝበት ምንጭ ስለተዘጋ  ለቆ እንዲወጣ ተገደደ፡፡ ዋናው የአድዋው ጦርነት የካቲት 23 ቀን በዕለተ ሰንበት በ6 ሰዓት ውስጥ በኢትዮጵያ የበላይነትና ድል አድራጊነት ተጠናቀቀ፡፡ በብዙ የታሪከ ጸሐፊዎች  ዘንድ የኢጣሊያን ጦር  ለሽንፈት ዳርገውታል ተብለው የሚወሰዱት  ዓበይት ምክንያቶች  የተሳሳተ የንባብ ካርታ፣ የመንገድ መሳሳት ፣ በሁሉም መስክ (በዘመናዊ መሳሪያና ትጥቅ ፣በሰለጠነ ሰራዊትና በመሳሰሉት) የበላይነት ስለነበራቸው ለኢትዮጵያውያን የሰጡት አነስተኛ ግምት በመኖሩ ፣ ኢትዮጵያውያን በሰንበትና በድርብ በዓል ጦርነት አይገጥሙም ብለው ሂሳብ መስራታቸው የሚሉት ናቸው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የኢትዮጵያን ሠራዊት ድል እንዲቀዳጅ የረዱት ነገሮች ጥልቅ የአገር ፍቅር ስሜት፣ ጦርነቱ ለአገርና ለሃይማኖት ጭምር  መሆኑን ሠራዊቱ ማመኑ፣ የላቀ የጦር ስልትና አመራር መኖሩ፣ ጠንካራ የሠራዊት ሞራልና የስነ ልቦና ዝግጅት፣ ሕዝብን የማንቀሳቀስና የመምራት ብቃት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የአድዋ ድል  በአገራችን  ከተካሄዱት በርካታ የጦርነት ድሎች ልዩ የሚያደርጉት ባህርያት አሉት፡፡ የመጀመሪያውና ዋነኛው በአራቱም አቅጣጫ የሚገኙ መላ ኢትዮጵያውያን የተሳተፋበት የጦርነት ድል መሆኑ ነው፡፡ የአድዋ ድል የዘር፣  የብሔር፣ የቋንቋ፣ የፆታ፣ የሐይማኖት ወዘተ  ልዩነት ሳይኖር  በድፍን ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት የተገኘ ውጤት ነው፡፡ ሁለተኛው አስደናቂ የአድዋ ድል ልዩ ገጽታ ደግሞ እስከ አፍንጫው ድረስ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀንና የሠለጠነውን  የኢጣልያን ሠራዊት እጅግ ኋላቀር በሆነ መንገድና መሣሪያ ያልሰለጠነው የኢትዮጵያ ጦር ማሸነፍ መቻሉ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ አድዋ በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁሮች ነጮችን ያሸነፉበት ዓብይ ወታደራዊ ድልም ነው፡፡ በተጨማሪም የአድዋ ጦርነት የድል ውጤት የኢትዮጵያን ነፃነት ከማረጋገጥ አልፎ ዓለምአቀፋዊ እንቅስቃሴን የፈጠረ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ 

የአድዋ ድል ለዘመናት ተከብሮ የኖረውን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ሀገርነትና ነፃነትን ከማረጋገጡም በላይ ለሀገራችን ዓለምአቀፍ ዝናን አጐናጽፏታል፡፡ የአድዋ ድል የቅኝ ገዥዎችን ቅስም በመስበር  ፖሊሲያቸውንም እንደገና እንዲመረምሩ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያን ለመቀራመት በጎረቤት አገሮች አሰፍስፈው የነበሩት ቅኝ ገዥዎች ከኢትዮጵያ ጋር በአቻነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ግንኙነት ለመመሥረት ተገደዋል፣ በቅኝ ግዛቶቻቸውና በኢትዮጵያ መካከል  የድንበር መካለል እንዲደረግ ወስነዋል፣ ኤምባሲዎችን በአዲስ አበባ በመከፍት የዲኘሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ጀምረዋል፡፡ የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን የትብብር፣ የአንድነት፣ የኩራትና የክብር ምንጭ ከመሆኑ ባሻገር  የድሉ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ለጥቁሮች ነፃነትና የክብር ፋና ለመሆን በቅታለች፡፡ የአድዋ ድል ምሳሌነት አፍሪካውያን በቅኝ ገዥዎቻቸው ላይ አንዲነሱ ምክንያት ሆኗል፣ ለፓን አፍሪካን እንቅስቃሴ መፋፋምም ጉልህ አስተዋጽኦ አበርከቷል፡፡ ከዚህ አልፎ የአድዋ ድል  ከነጮች ተፅዕኖ ነፃ የሆነ የጥቁሮች የሃይማኖት እንቅስቃሴ እንዲጀመር ምክንያት እስከ መሆን ደርሷል፡፡  ለአብነትም ኢትዮጵያኒዝም እየተባለ ይጠራ የነበረውና  በተለይ በአሜሪካና በደቡብ አፍሪካ  የነበረውን እንቅስቃሴ መጥቀስ ይቻላል፡፡ 

ለአድዋ ድል መገኘት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሚና እጅግ የላቀ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይህች ጥንታዊ ቤተክርስቲያን  በአድዋ ጦርነት ወቅት ከመነሻው እስከመጨረሻው፣ ከዘመቻው እስከ ድሉ፣ ከዋዜማው እስከጦርነቱ በመሪነትና በተሳታፊነት ነበረች፡፡ ቤተክርስቲያኗ ሕዝቡን በመቀስቀስ፣ አመራር በመስጠት፣  አብራ በመዝመት፣ የስነ ልቦና ዝግጅት እንዲኖር በማድረግ፣ በጦርነቱ በመሳተፍ፣ መረጃ በመስጠትና በማስቀመጥ ባደረገችው አስተዋጽዖ ተወዳዳሪ አልነበራትም፡፡  ለረጅም  ዘመናት ይዛ በቆየችው ልዩ ልዩ አገራዊ ሓላፊነትና ሚናዋ ምክንያት፣ አገር ያለ ሃይማኖት ሃይማኖት ያለ አገር የለም በሚለው እሳቤ፣በቀደሙት የጦርነት ታሪኮች ከሁሉም  በላይ ጥቃት   የደረሰባት  እርሷ በመሆኗ ( ለአብነት ያክል የአህመድ ግራኝን ጥፋት፣የመቅደላን የቅርስ ዝርፊያ ፣ የደርቡሾች ጥቃት መጥቀስ ይቻላል) እና በተለይ ደግሞ የወራሪው መንገድ ጠራጊዎች አባ ማስያስን የመሳሰሉ ሚሲዮናውያን በመሆናቸው ቤተክርስቲንዋ በጦርነቱ የነበራትን ጉልህ ተሳትፎ ምክንያታዊ ያደርገዋል፡፡   

በአደዋ ጦርነት ወቅት ቤተክርስቲያኗ  የነበራትን  የላቀ  ሚና ለመረዳት  የአፄ  ምኒልክን የክተት ዐዋጅ ብቻ መመልከት በቂ ነው፡፡ አዋጁ ጦርነቱ ከቤተክርስቲያን፣ ከእግዚአብሔር እና ከወላዲት አምላክ ጠላት ጋር እንደሆነና የመጣው ጠላት አገር የሚያፈርስ ብቻ ሳየሆን ሃይማኖት የሚለውጥ ጭምር መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በመሆኑም የጦርነቱ አዋጅ ሐይማኖታዊ ቅርጽ ነበረው፡፡ አዋጁ እንደሚከተለው ነበር፡፡

 ስማ፣ ስማ፣ተሰማ የማይሰማ የእግዚአብሔር እና የወላዲት አምላክ ጠላት ነው፡፡ ስማ፣ ስማ      
ተሰማማ፣የማይሰማ የእግዚአብሔርና የቤተክርስቲያን ጠላት ነው፡፡ ስማ፣ስማ ተስማማ፣ የማይሰማ የእግዚአብሔርን የንጉሡ ጠላት ነው፡፡እግዚአብሔር ወሰን እንዲሆን የሰጠንን ባሕር አልፎ ሃይማኖት የሚለውጥና ሀገር የሚያጠፋ ጠላት መጥቶአል፡፡ እኔ ምኒልክ በእግዚአብሔር ርዳታ ሀገሬን ለጠላት አሳልፌ አልሰጥም፡፡ ያገሬ ሰው! ከአሁን ቀደመ የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ርዳኝ፣ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ለሚስትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በኅዘን ርዳኝ፡፡ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፣ አልተውልህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዬም በጥቅምት ነው፡፡ 

አፄ ምኒልክ አዋጅን ካስነገሩ በኋላ በአዲስ አበባ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ጸሎት ማድረሳቸውና ብፅዓት ማድረጋቸው ወይም ስዕለት መሳላቸው የጦርነቱ መንፈሳዊ ዝግጅት አካልና ለቤተክርስቲያኗ ልዩ መልእክት የነበረው ነው፡፡ ስዕለታቸውም “አምላከ ቅ/ጊዮርጊስ ድሉን ቢሰጠኝ ይህን የቅ/ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሣር ክዳኑን ለውጨ ባማረ ሕንፃ አሠራዋለሁ ” የሚል ነበር፡፡ ይህንም ስእለታቸውን ከድል በኋላ ፈጽመውታል፡፡ የክተት አዋጁን  ተከትሎም  በሊቀጳጳሱ አቡነ ማቴዎስና በእጨጌ ወልደ ጊዮርጊስ በመላ ሀገሪቱ ጸሎት፣ ኀዘንና ምህላ ታወጀ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቤተክርስቲያን አስተምህሮው ተጠናከሮ ቀጠለ፡፡ አገር ከሌለ ሃይማኖት የለም፣ ሃይማኖትና ነፃነትን ማጣት ሽንፈት ነው፣ ወደ ፈጣሪ ለአገርና ለሃይማኖት ታግሎ መሔድ ሰማዕትነት ነው፣ ኢትዮጵያን  ያህል አገር ማጣት እግዚአብሔርን ከሚያህል ጌታ መለየት ሞት ነው፣ ስለ አገር፣ ሃይማኖትና ነፃነት መሞት ክብር ነው ወዘተ የሚሉት የአስተምህሮው አንኳር ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ከዚያም በቤተክርስቲያን  የአዝማች  ኮሚቴ ተቋቋመ፣ ዘማች  አብያተክርስቲያናትም  ተለይተው ታወቁ፡፡ በዘመቻውም ታቦት፣መስቀል፣ ንዋያተ ቅድሳት ቃጭል፣ጥላዎች እና ድባቦች ይዘው ከሊቃውንቱና ካህናቱ ጋር እንዲዘምቱ ተወሰነ፡፡ 

ከአዲስ አበባ እስከ አድዋ በነበረው የዘመቻ ጉዞ  ቤተክርስቲያኗ ግምባር ቀደም ሆና  ሕዝቡን ከጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ጋር  በአንድነት በመምራት በአስተምህሮዋ፣ የዘማቹን ወኔ በመገንባት፣ ስለአገር ፍቅር በመሰበክ፣ በጾምና በጸሎት  ወደፊት ትገሰግስ ነበር፡፡  በጉዞው ወቅት በሊቀጳጳሱ አቡነ ማቴዎስና በእጨጌ ወ/ጊዮርጊስ አስተባባሪት መንፈሳዊ አገልግሎቱ በመዓልትና በሌሊት በሰዓታት፣ በማኅሌት፣ በቅዳሴ በነግህና በሰርክ ጸሎት ሳይቋረጥ ይከናወን ነበር፡፡ ዘማቾቹም  በሰንበት ቀን አለመጓዝ፣ ዓበይት በዓላትን ማከበር፣ለድኃው መመጽወት እና የመሳሰሉትን ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን ያከናውኑ ነበር፡፡ የጦር መሪዎቹ ሳይቀር  በጸሎታቸው የተጉ የመንፈሳዊ  ልእልና ያላቸው ነበሩ፡፡ ልዑል ራስ መኰነን አምባላጌን  ለማስለቀቅ በነበራቸው ምኞት በጦርነቱ ኃይልና ድል እንዲሰጣቸው ለአምላከ ቅ/ጊዮርጊስ ጸሎታቸውን አቀርበዋል፡፡ በመጨረሻም በአንገታቸው ላይ ባለው የወርቅ መስቀል አማትበው ጦርነቱን ለመግጠም እንደወሰኑና ድል አደረገው አምባላጌን ነፃ እንደአወጡ  ይነገራል፡፡ እቴጌ ጣይቱ በመቀሌ የመሸገውን ጠላት የውኃ ምንጩ እንዲያዝ ዘዴውን ከፈጠሩ በኋላ ሌሊቱን ሙሉ ”ጌታዬ እኔን ባርያህን አታሳፍረኝ በነገሬም ግባበት ርዳታ ትችላለህና” እያሉ ይጸልዩ እንደነበር ታውቋል፡፡ 

በየካቲት 14 ቀን 1888 ዓ.ም አፄ ምኒልክ አድዋ ሲደርሱ ከመላው ትግራይ የተውጣጡ ካህናትና ሊቃውንት የየደብራቸውን ታቦታት ይዘው ልብሰ ተክህኖ ለብሰው በደማቅ ሁኔታ ተቀብለዋቸዋል ፡፡ ከዚያም በመላ ትግራይ ለአንድ ሱባኤ ምህላ ታዟል፡፡ አጤ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ሱባኤ ይዘው የቆዩት በእንዳ አባ ገሪማ ገዳም ነበር፡፡ ለጦርነቱ ዝግጅትና መሰናዶ ሲጀመርም አስቀድሞ የታወጀው የጸሎትና የምህላ ዓዋጅ ነበር፡፡ ወደ  ጦር ግንባር ሲዘምቱ ታቦታት፣ መስቀሎችና ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳት ተይዘው ነበር፡፡ የሃይማኖት አባቶችና የቆሎ ተማሪዎች ሳይቀር በጦርነቱ ተሳትፈዋል፡፡ በመጨረሻም ለመላው ዘማች ለሰባት ቀናት የቁም ፍታት ተካሂዷል፡፡ ጀግናው  አውአሎም ሀገረጎት እና  መሰል አርበኞች ለኢጣሊያን  የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ለአድዋ ድል አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ይታወቃል፡፡  ከጦርነት አንድ ቀን በፊት የካቲት 22 ቀን እቴጌ ጣይቱ ለአውአሎም ምግብ  አቅርበው  “እንካ ይህን እንጀራ እንደ ሥጋ ወደሙ ቆጥረህ ብላው ብትከዳ እግዚአብሔር ይፈርድበኋል ”  ብለው እንደ ሰጡት ይነገራል፡፡የካቲት 22  ለየካቲት 23 አጥቢያ በአውአሎም መረጃ ምክንያት  ጥላት ከምሽጉ እንዲወጣ ስለተደረገ ሌሊት ሲጓዝ አድሮ አድዋ እንደገባ በመረጋገጡ ቅዳሴው ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ እንዲፈጸም ተወሰነ፡፡    

በጦርነቱ ዋዜማ አፄ ምኒልክ ፣  ንጉሥ ተ/ሃይማኖት፣ ራስ መኰንን፣  ራስ መንገሻ ፣  ፊታውራሪ ገበየሁ  ዓድዋ በሚገኘው የቅዱስ ገብኤል ቤተክርስቲያን  ያስቀድሱ ነበር፣  ቅዳሴውም የተመራው በጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ ነበር፡፡ አቡነ ማቴዎስ “ልጆቼ ሆይ ዛሬ የእግዚአብሔር ፍርድ የሚፈጸምበት ቀን ነውና ሂዱ ለሃይማኖታችሁ ለአገራችሁ ሙቱ እግዚአብሔር ይፍታህ” ሲሉ መኳንንቱ ሁሉ እየተሽቀዳደሙ የአቡኑን መስቀል ተሳልመው ወደጦርነት መሄዳቸው፣ ሊቀጳጳሱም ወደ ጦርነት የሚገባውን ወታደር ሁሉ እግዚአብሔር ይፍታህ እያሉ ይናዝዙ እንደነበር ይነገራል፡፡  አፄ ምኒልክም በበኩላቸው ነጋሪት እያስጐሰሙ ሠራዊቱን “ጦርነትና የጦርነት ድምፅ ብትሰሙም አትደንግጡ፣ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ሆኖ ጠላቶቻችሁን ስለሚዋጋ አትፍሩ፣ እግዚአብሔር አምላካችሁ በፊታችሁ እየኼደ ጠላቶቻችሁን ስለሚዋጋላችሁ እናንተንም ስለሚያድናችሁ ከፊታቸው አትሽሹ” በማለት ያበረታቱ ነበር፡፡  ከዚህ ሁሉ በኋላም አንጸባራቂው የአድዋ ድል በየካቲት 23 ቀን በዕለተ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተበሰረ፡፡ 

የአድዋ ድል ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በነጻነት የግዛት አንድነቷ ተጠብቆ ዳር ደንበሯ ተከብሮ ለዚህ ትውልድ እንድትደርስ በማድረግ በኩል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያደረገችው የላቀ፣ ዘመን ተሻጋሪና ዘርፈ በዙ አስተዋጽኦ  አንዱና ዋነኛው ማሳያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን  አባቶችና እናቶች ታሪክና ቅርስን ብቻ ሳይሆን በከፈሉት መሰዋዕትነት ሀገርንም አቆይተውልናል፡፡ ይህ ትውልድ እንደ አባቶቹ ታሪክ መሥራት ባይችልም እንኳ ታሪኩንና ቅርሱን ማወቅና መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ የቤተክርስቲያንንም አስተዋጽኦና ውለታ መርሳት የለበትም፡፡ የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊ አንድነታችን ውጤትና ምልክት በመሆኑ ጎሰኝነትን ለሚያቀነቅነው ትውልድ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ከታሪክ የማይማር ትውልድ መነሻ  እንደሌለው ሁሉ መድረሻም የለውም፡፡ 

ማጣቀሻ ዎች

ቤካ ናሞ፣  አደዋና ምኒልክ::  አርቲስትክ ማተሚያ ቤት (1956)

ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣  አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት :: ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት (1983)

ተወልደ ትኩእ ፣  የኢትዮጵያ አንድነትና ኢጣልያ:: አዲስ አበባ (1990)

ገብረ ሥላሴ ወልደ አረጋይ፣   ታሪክ ዘዳግማዊ  ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ :: አዲስ አበባ፣
አርቲስትክ ማተሚያ ቤት (1959)

ጳውሎስ ኞኞ፣   ዳግማዊ አጤ ምኒልክ:: (1984)

Marcus, Harold, 1975. The Life and Times of Menelik II of Ethiopia 1844-1913.
Oxford: Clarendon Press

Milkias, Pawlos & Metaferia, Getachew (ed.) 2005. The Battle of Adowa: Reflections on Ethiopia’s Historic Victory against European Colonialism. New York: Algora Publishing

Weldegebreil, Biniam, 2004. ‘Memories of the Victory of Adwa: A Focus on Its commemoration (1941-1999)’. A Thesis Presented to the School of Graduate Studies of Addis Ababa University In Partial Fulfillment of the Requirements of Masters of Arts in History. 

Monday, February 27, 2017

ከቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ የልጅ ልጅ ልዑል ኤርምያስ ሳህለ ስላሴ ጋር የተደረገ አዲስ ቃለ መጠይቅ (ኢቢኤስ ሄለን ሾው)

Interview with Ethiopian exile prince Ermias
EBS Television Helen Show




የልዑል ኤርምያስ የጀማይካ ጉብኝት የተመለከተ ሪፖርት ለማንበብ ይህንን ይጫኑ።

ጉዳያችን GUDAYACHN

www.gudayachn.com

Wednesday, February 22, 2017

የአድዋ ድል አስመልክቶ በዝርዝር የሚያብራራ በአማርኛ የተዘጋጀ ልዩ ጥናታዊ ፊልም

The battle of Adwa documentary film

የአድዋ ድል አስመልክቶ በዝርዝር የሚያብራራ በአማርኛ የተዘጋጀ ልዩ ጥናታዊ ፊልም
በአብርሃም ዕውቀቱ ተዘጋጅ በሸገር ራድዮ የቀረበ።
====================================== 
ፊልሙን በትዕግስት ተመልክተው አባቶቻችን የከፈሉትንዲፕሎማሲያዊ እና የሕይወት መስዋዕትነት ምን ያህል ውጣ ውረድ የተሞላበት እንደነበር ይረዳሉ።በተለይ ታሪኩ በአዲሱ ትውልድ ዘንድ በሚገባ ስለማይታወቅ ትክክለኛውን ታሪክ የማሳወቅ የሁሉም ግዴታ ነው። 
የአድዋ ድል 121ኛው ዓመት በመጪው የካቲት 23 (ማርች 2) ቀን ይከበራል።
ከእዚህ በፊት ስለ አድዋ ጦርነት ሰምተውት የማያውቋቸው በርካታ ሚስጥሮች የያዘ ፊልም ነው።ፊልሙን ባይመለከቱ ይቆጫሉ።



ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

Monday, February 20, 2017

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በክርስትና ስማቸው ገብረ ሐና ቀብር ወደ ማክሰኞ የካቲት 14፣2009 ዓም ተቀይሯል።ቀብራቸው ከቀኑ በ9 ሰዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ሪታ ፓንክረስት፣ሲልቭያ ፓንክረስት፣ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፣ ገጣሚ እና ደራሲ መንግስቱ ለማ (ፎቶ:-pinterest.com) 

ባለፈው ሐሙስ የካቲት 9፣2009 ዓም ከእዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ቀብር  ሰኞ ታስቦ የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅፅር ግቢ የሚቀብረው የቤተ ክርስቲያኒቱ እምነት ተከታይ መሆን ስለሚገባው ይሄው ጥያቄ ተነስቶ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በክርስትና ስማቸው ገብረ ሐና በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ በሚገኘው ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባል መሆናቸው መረጋገጡን ሐራ ዘተዋህዶ ድረ- ገፅ ማምሻውን ባወጣው ዘገባ ገልጧል። ፕሮፌሰሩ ካቶሊክ ናቸው የሚል ዜና ወደ ቤተ ክህነት ይዘው የሄዱት የፕሮፌሰሩ የቅርብ ወዳጅ ነኝ ያሉ ግለሰብ መረጃ ሐሰት መሆኑን ቤተሰቦቻቸው ከፕሮፌሰሩ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ደብተር ጋር ማረጋገጥ መቻላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ሐራ ዘተዋሕዶ ጉዳዩን አስመልክቶ ያወጣውን ዘገባ ይህንን በመጫን ያንብቡ።


ከቶ አይቀርም ሞቱ




ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com

Thursday, February 16, 2017

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በ90 ዓመታቸው አረፉ ቀብራቸው በመጪው ሰኞ ቅድስት ስላሴ ቤ/ክርስቲያን በ9 ሰዓት ይፈፀማል



እናታቸው እንግሊዛዊቷ ሲልቭያ ፓንክረስት ኢትዮጵያ በጣልያን ስትወረር በእንግሊዝ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በማቀጣጠል ተቃውመዋል።ንጉሡ በስደት በነበሩበት ወቅት አብረው ወጥተዋል ወርደዋል። በኃላም ከልጃቸው ሪቻርድ ፓንክረስት ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በኢትዮጵያ እስከ ሕይወታቸው ፍፃሜ ድረስ ኖረዋል።

ወ/ሮ ስልቭያ ፓንክረስት ዕረፍታቸውም ቀብራቸውም በኢትዮጵያ ነበር።የተቀበሩት በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው በመጪው ሰኞ የካቲት 13፣2009 ዓም ልጃቸው በሚቀበሩበት ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ነበር።

የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እናት የኢትዮጵያ ወዳጅ ወ/ሮ ስልቭያ ፓንክረስ 


ሲልቭያ ፓንክረስት መቃብር ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን አዲስ አበባ 

የስልቭያ ፓንክረስት ልጅ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የኢትዮጵያ ጥናት ማዕከል እንዲመሰረት ያደረጉ ስለ ኢትዮጵያ ሲፅፉ እና ሲመራመሩ የኖሩ ምሁር ናቸው።ፕሮፌሰሩ ከ1940ዎቹ ጀምሮ እስከ ንጉሡ መውረድ ድረስ በኢትዮጵያ ከኖሩ በኃላ በ1970ዎቹ መጨረሻ እንደገና ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ምርምራቸውን ቀጥለዋል።ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስ በ90 አመታቸው ማረፋቸው እና በመጪው ሰኞ አዲስ አበባ በሚገኘው ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን የቀብራቸው ስነ ስርዓት እንደሚፈፀም ተነግሯል።

እረፍተ ነፍስ ለፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት መፅናናትን ለቤተሰቦቻቸው ይስጥልን።

የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ልጅ ፕሮፌሰር አሉላ ፓንክረስ ግጥም ከእዚህ በታች ይመልከቱ።



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Tuesday, February 14, 2017

በሃያ ስድስት አመታት ውስጥ አራቱ የህወሓት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውጤት - ኢትዮጵያን በአረብ ሀገር የጦር ሰፈሮች ማስከበብ


ላለፉት 26 አመታት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን፣አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም እና አቶ ወርቅነህ ገበየሁ 

ጉዳያችን/Gudayachn
የካቲት 7፣2009 ዓም (ፈብሯሪ 14፣2017)
=======================
ባለፈው ቅዳሜ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ርዕዮት በተሰኘ የማኅበራዊ ሚድያ ቀጥታ ውይይት መርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አካባቢያዊ ተፅኖ በሱማሌ ካለው አንፃር ከባልደረቦቹ ጋር ጥሩ አድርገው ሲተነትኑ ነበር።በተለይ በእዚህ ውይይት ላይ ኢትዮጵያ ሱማሌ ውስጥ እንድትገባ ሲደረግ ሕወሓት ያስቀመጠው ግብ እና ስትራቴጂ ሳይኖር ዝም ብሎ ሽርፍራፊ ገንዘብ ከአሜሪካ የማግኘት ላይ ያለመ ነገር ግን ሃገራዊ ራእይ የሌለው መሆኑ ሰራዊታችን ከሱማልያ ሲወጣ አንዳች የኢትዮጵያን ጥቅም ሳያስከብር መሆኑን በመቆጨት ቀርቧል።ኢትዮጵያ ደማች አሁን ምንም ያልደከሙት የአረብ ሃገራት በነፃ የጦር ሰፈር እየመሰረቱ ነው።በእዚሁ የኢትዮያ ተፅኖ ፈጣሪነት ከጅኦ ፖለቲካ አንፃር ያለው ዋጋ በሕወሐቷ ኢትዮጵያ እየረከሰ መምጣቱን ጋዜጠኛ መሳይ ከበደም በፌስ ቡክ ገፁ ላይ በሚገባ አስቀምጦታል።

ሁለቱም ያነሱት ጭብጥ በጣም ትክክል ነው።ኢትዮጵያ ዙርያዋን እየተከበበች ነው ጅቡቲ፣ሱማልያ ላንድ፣አሰብ፣ምፅዋ እነኝህ ሁሉ የአረብ ሃገራት የጦር ሰፈሮች የተመሰረቱባቸው እና ለመመስረት ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ናቸው።ሕወሓት አሁንም የኢትዮጵያን ሕዝብ አዋጅ አውጥቶ በመግደል እና በማሰር ላይ እንጂ የኢትዮጵያን ጥቅም በታሪክ በሚያስጠይቅ ደረጃ አሳልፎ ሰጥቷል። ይህ ጉዳይ ደግሞ ከባድ ዋጋ የሚያስከፍለን እንደሚሆን ማወቅ አለብን።

በሃያ ስድስት አመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የተቀመጡት ከእዚህ በታች ያሉትን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ እና አካባቢ ዲፕሎማሲ ምን ሰሩ? ውጤቱ ምን ሆነ ብላችሁ ስትጠይቁ መልሱ የኢትዮጵያን ጥቅም የበለጠ አሳልፎ የሰጠ፣ግብ እና ስልት የሌለው፣ኢትዮጵያ ያጣችውን ጥቅም ከሕዝቡ እየደበቁ የማታለል ´ተግባር የተሰራበት እና ባብዛኛው የሀገርን ጥቅም ለግል እና ለመንደር ጥቅም ብቻ የዋለ ሆኖ ታገኙታላችሁ።ለእዚህ ምሳሌ የሚሆነው የደቡብ ሱዳን እና የሱማሊያ ጉዳይ ነው።ደቡብ ሱዳን ከግብፅ ጋር ከመግጠሟ በፊት ኢትዮጵያ በደርግ ዘመን ጀምሮ ዋጋ ከፍላባታለች። ከ80 ሺህ በላይ ሰራዊት ስንቅ እና ትጥቅ እየተሰጠው ሰልጥኗል።ደቡብ ሱዳን መንግስት ከሆነች በኃላ ህወሓት እንደ ትልቅ ግብ የወሰደው የእራሱ የሆኑ ሰዎች ግዝያዊ ለሆነ የንግድ ሥራ እንዲጠቀሙ መንገድ ማመቻቸት እንጂ ሃገራዊ ራእይ ያለው የኢትዮጵያን ጥቅም ያስጠበቀ ሥራ ባለመስራቱ አቶ ስዩም መስፍን ይዘውታል የተባለው የደቡብ ሱዳን ሽምግልና ኢትዮያን ከጫወታ ውጭ አድርጎ በርቀት ሪሞት ትከታተል የንበረችው ግብፅ የደቡብ ሱዳን ወዳጅ ሆና መጥታለች።

በሱማሌም የሆነው ይሄው ነው።ኢትዮጵያ በተለይ በሰሜን ሱማሌ እራሱን ከዋናው ሱማሌ ለይቶ በመንግሥትነት እንዲታወቅ ሲጥር የነበረው ክፍል ከኢትዮጵያ ከቀድሞ መንግስት ጀምሮ ከፍተኛ ድጋፍ ተደርጎለታል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ጀምሮ እስከ አድማስ ዩንቨርስቲ ቅርንጫፍ ከፍቶ እስከ ማስተማር ድረስ ኢትዮጵያ እጇ እረጅም ነበር።ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ስራዋ በግብ እና ስልት በማያውቁ እጅ ስለወደቀ በመጨረሻ ትናንት ከቢቢሲ እንዳነበብነው ዩናይትድ አረብ ኤምሬት ከእዚሁ የሱማሌ ክፍል ላይ የጦር ሰፈር ለመመስረት ስምምነት ላይ ደርሳለች።በሰሜን ሱዳን ያለው ግንኙነትንም ብንመለከት ከኢትዮጵያ ዘለቄታዊ የጥቅም ተግባር ላይ የተሳሰረ ሳይሆን የጎንደር ገበሬዎችን ከጀርባ የመደብደብ እና ከትግራይ ጥቅም ጋር ብቻ የተሳሰረ እንዲሆን ተደርጎ ተቀርፆ እናየዋለን።ለእዚህም ምስክሩ የሱዳኑ አልበሽር አዲስ አበባ ከምመጡበት ጊዜ ይልቅ መቀሌ ለህወሓት የምስረታ በዓል ላይ ሲገኙ ላቅ ያለ አቀባበል እንደሚደረግላቸው እና ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ለትግራይ ደህንነት በሚሰጡት ዋስትና ላይ እንጂ ለኢትዮጵያ መሆኑ ላይ እንዳይጨነቁ የተነገራቸው እስኪመስል ድረስ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ይልቅ የትግራይ ክልል አስተዳዳሪ ጋር ማውራት ይመርጣሉ።

በጅቡቲም የሆነው ይሄው ነው።ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ትኩስ እንጀራ ተጋሮላት የምትኖር ሀገር ተብላ ትነገር ነበር።በእውነትም ጅቡቲ ከንፁህ ውሃ እስከ ጫት ከወደብ ከምታገኘው ጥቅም አንፃር ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ ጥገኛ የሆነች ሀገር ነበረች።በጊዜ ብዛት ግን የእራሷን አቅም ከኢትዮጵያ በምታገኘው የወደብ ክፍያ እያዳበረች መጥታለች።መሪዋ አማርኛ ከመናገር ጀምሮ ድሬዳዋ እስከመማር ኢትዮጵያም ሰፋፊ ግቢ ቤቶችን እንደገዙ የሚነገርላቸው  ፕሬዝዳንቷ በአግባቡ የሚይዛቸው የኢትዮጵያ አስተዳደር ቢኖር ከኢትዮጵያ ወጥተው ለአረብ ሃገራት የጦር ሰፈር የመፍቀድ ያህል ርቀት አይሄዱም ነበር።የኢትዮጵያ የአሁኖቹ ባለሥልጣናቶቿ በቀላሉ የሚደለሉ መሆናቸውን ተረድተውታል።

ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ዙርያዋን እይተከበበች ነው።ሕወሓት በትናንሽ የጎሳ እና የመንደር ጉዳዮች ላይ እንጂ የኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ዓለም አቀፋዊም ሆነ አካብቢያዊ ተፅኖ ፈጣሪነት ላይ የመስራት ፍላጎቱም ሆነ ያለው የሰው ኃይል አቅም አይፈቅድለትም።ባለፉት 26 አመታት በስልጣን ላይ የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን አቅም፣የዲፕሎማሲ እውቀት፣ልምድ እና የትምህርት ዝግጅት ገምግማችሁ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ደረጃ ስትመዝኑት በተሰፈረው ልክ እንዳገኘን ትረዱታላችሁ። ችግሩ ከአሁኑ ይልቅ ወደፊት የከፋ ዋጋ እንደሚያስከፍለን ያለመረዳቱ ላይ ነው። ለእዚህ ሁሉ ችግር መፍትሄ ለመስጠት ግን አሁንም አልረፈደም።ሕወሓት የገዛ ሕዝቡን ከመግደል እና ከማሰር ይልቅ ከልብ ለሆነ ሃገራዊ እርቅ እንዲነሳ በመጠኑ ንቃት አለን የምትሉ የጦር ሰራዊቱ እና የቢሮ ክራሲው አካላት በውድም ይሁን በግድ ማስገደድ አለባችሁ። ውስጣዊ ችግሮች በፍጥነት እንዲፈቱ  ለለውጥ እና ሃገራዊ እርቅ አልገዛም የሚል ፅንፈኛ የህወሓት አመራር መታሰር ያለበት ይታሰራል።ለፍርድ መቅረብ ያለበት ይቀርባል።ጉዳዩ የሀገር ጉዳይ ነው።ቆይቶ እንደ ሀገር የሚከፈለው ከቸልተኝነት የተነሳ የሚመጣ ፈተና ሁሉንም ይዞ ወደ ገደል የሚገባ ነው።ከእዚህ በተለየ ግን የሕወሓት በስልጣን መቆየት ኢትዮጵያን የበለጠ ዋጋ እያስከፈላት እንደሆነ መታወቅ አለበት።ከእዚህ ጋር በተያያዘ ከእዚህ በፊት በጉዳያችን ላይ የወጣውን ማስታወሻ ለማንበብ ይህንን ይጫኑ።


ጉዳያችን GUDAYACHN 

 www.gudayachn.com

Thursday, February 9, 2017

ዛሬ የምታየውን ጀግና ማድነቅ ካልቻልክ ነገ ሌላ ጀግና አይወለድልህም።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ 

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ እንዲህ እንዲህ እያለ ዛሬ ላይ ደርሷል።በጎንደር ልዩ ልዩ ስፍራዎች በሕዝብ እና በሕወሓት መካከል ከፍተኛ ውግያ እየተደረገ ነው።ከሱዳን በኩል ዋስትና እስካለኝ ድረስ ምንም አይፈጠርም ብሎ ያስብ የነበረው ስርዓት ከውስጥ የተነሳው አመፅ በኃይል ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት በትትክክልም መክኗል።አመፁ እንደተጀመረ ግጭቱ በአማራ እና ትግራይ መካከል ለማስመሰል ብዙ ጥረት ያደረገውም የሕወሓት ቡድን ነበር።የወልቃይት ኮሚቴ አባላት ¨ችግሩ በአማራ እና ትግራይ አይደለም የኮሚቴ አባላት የሆነው ውስጥም ከትግራይ የምንወለድ አለን ጉዳዩ የማንነት መብት ነው¨ ብለው እየተናገሩም በሕዝብ መካከል ግጭት ለመፍጠር ሙከራው ቀጠለ።ሆኖም አልተሳካም።

በአሁኑ ሰዓት የጎሳ የግጭት ስሜቶች በሙሉ ያነሳሳ የነበረው አካል ተስፋ በመቁረጡ እና ህዝብም እውነቱን እየተረዳ በመጣበት ሰዓት ነው ¨በዜግነት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን ግባችን ማድረግ ካልቻልን ትግላችን መና ቀረ ማለት ነው ¨ የሚል ንግግር ባለፈው ዓመት ያሰሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በመላው ዓለም ከሰላሳ በላይ ከተሞች በሚደረገው የአርበኞች ግንቦት ሰባት የገቢ ማሰባሰብያ መርሃ ግብር ላይ ካሉበት በኤሌክትሮኒክስ መገናኛ በመጪው ቅዳሜ እና እሁድ ንግግር ያደርጋሉ።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአሁኑ ወቅት በፖለቲካው መድረክ ላይ ትግሉን ሳያቆሙ የተለያዩ ስልቶችን በመከተል ከቀጠሉት ጥቂት የሀገራችን አንጋፋ የፖለቲካ ሰዎች ውስጥ ናቸው።

  • ሰውዬው ወደ አሲምባ በረሃ ደርግን ለመታገል ብረት ይዘው ሲሄዱ ወቅቱ የሚጠይቀው የሀገር መውደድ እንደሆነ አምነው ነው።
  • ሰውዬው ሕወሓት ስልጣን ሲይዝ በሰላማዊ ትግል ሀገር ካዳንኩ እራሴን ዝቅ አድርጌ ወደ ሀገሬ ገብቼ ልግባ ብለው ውሳኔያቸውን ገልፀው ወደ ሀገር ቤት ሲመጡ እና በቅንነት የአቶ መለስን እጅ ሲጨብጡ በወቅቱ ¨ ባንዳ¨የሚል ስም እየሰጠ እንደ እሳት የሚፋጀውን በውጭ የነበረውን ፖለቲከኛ ከኢትዮጵያ ፍቅር አይበልጥም ብለው ነበር።
  • ሰውዬው ከምርጫ 97 በኃላ ከሀገር ወጥተው እንደማንም ሰው ማክያቶ ፉት እያሉ ሁሉን ትተው መቀመጥ ሲችሉ ቢሸሹት የማይሸሸውን የእናት ሀገር ፍቅር ይዘው አሁንም እራሳቸውን ዝቅ አድርገው አቶ ኢሳያስ ሀገር የተገኙት ስለ ግል ጥቅም አይደለም።መተኪያ ስለሌላት ስለ ኢትዮጵያ ብለው ነው።
እኛ ለእኛ ብሎ የሚለፋልንን  ማጀገን እና ሌላ ጀግና እንዲወለድ ማድረግ አለመደብንም።ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴን ገድለን የምንፎክር፣ አፄ ቴዎድሮስን እንዲይዝልን ለእንግሊዝ መንገድ አሳይተን (ደጃች በዝብዝን ያስታውሷል) ልጃቸውን እና ባለቤታቸውን አስማርከን የምንሰጥ፣ ሌላም ሌላም ስህተት የተሞላ ተግባር ሰሪዎች ነን።ካለፈ ታሪክ መማር ብልህነት ነው።

ፕሮፌሰር ብርሃኑን ዛሬ ማጀገን ካልቻልክ ነገ ሌላ ጀግና እንዲወለድ መጠበቅ አይቻልም።ነገ ፕሮፌሰሩ የፈለጉትን መሆን ይችላሉ።በእዚች ሰዓት ግን የምናየው ጊዜያቸውን እና እውቀታቸውን ለኢትዮጵያ ጉዳይ እንደሰጡ ነው።ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ  በመጪዎቹ ቅዳሜ እና እሁዶች በሰላሳ የዓለም ከተሞች ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ንግግር ያደርጋሉ።ፕሮፌሰሩ ህይወታቸውን ለመስጠት መወሰናቸውን ቢነግሩንም በሕይወት ኖረው ሁላችን የምንናፍቃትን ኢትዮጵያ እንዲመለከቱ ሁል ጊዜ ምኞታችን ነው።ጀግና ማከበር ይልመድብን።




ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

Wednesday, February 8, 2017

የመሰረታዊ ውሃ አቅርቦት ቀውስ በኢትዮጵያ (ጉዳያችን አጭር ዘገባ)

ጉዳያችን/ Gudayachn
የካቲት 2/2009 ዓም (ፈብርዋሪ 9/2017)
=========================

  • 42.5 ሚልዮን ሕዝብ ከፍተኛ የመሰረታዊ የውሃ እጥረት ላይ ነው።
  • በእዚህ ሳቢያ 71 ሚልዮን ሕዝብ መሰረታዊ ንፅህና ለመጠበቅ ተቸግሯል።
  • 71% የሚሆነው ሕዝብ ከ3.10 ዶላር በታች የሚያገኝ ሕዝብ ነው።
  • የቢራ ፋብሪካ ከመደርደር ይልቅ የውሃ ፕሮጀክት መስራት ይገባ ነበር።
  • ውሃ ጠማኝ በምከፍለው የቀረጥ ገንዘብ መንግስት ውሃ ያቅርብ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካ ተብሎ ሊያሳስር ይችላል።

በኢትዮጵያ ከዋና ከተማ አዲስ አበባ  እስከ አዲግራት፣ ከደሴ እስከ ሻሸመኔ የሚጠጣ ውሃ ብቻ ሳይሆን ለገላ መታጠብያ ውሃ ብርቅ እየሆነ ነው።አዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች ላይ አንድ ጀርካል ውሃ ከእነተሸካሚው እስከ 20 ብር በሻሸመኔ ደግሞ እስከ 15 ብር እንደሚያወጣ እራሱ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንም በይፋ ያወጀው ዜና ነው።

ለውሃ እጥረቱ ዋነኛ ምክንያት ዝርክርክ፣እቅድ የለሽ እና ቅድምያ የሚሰጡ ፕሮጀክቶችን ቅድምያ የማይሰጥ  የመንግስት ፖሊሲ ሳብያ ነው።በቀደሙት መንግሥታት ወቅት የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት የሚሰራው ከከተሞች እድገት ጋር እየተሰላ ሲሆን በህወሓት ዘመን ግን የከተሞች እድገት ቁጥርን ታሳቢ አድርገው የሚያቅዱ የከተማ ምክርቤት ባለሙያም ሆነ እራሱ ሕወሓት የሚመድባቸው ባለሥልጣናቶች ሁሉ ከእዚህ አይነቱ አስተሳሰብ መራቃቸውን አመላካች ነው።

በኢትዮጵያ የውሃ አቅርቦት ላይ ኢትዮጵያ በውሃ ቀውስ ላይ ነች በማለት ዜናውን የሚያትተው water.org   የተሰኘው ድረ ገፅ 45.5 ሚልዮን ሕዝብ ከፍተኛ የውሃ እጥረት ላይ መሆኑን ገልፆ፣ በእዚሁ ሳብያ 71 ሚልዮን ሕዝብ መሰረታዊ ንፅህና ለመጠበቅ አለመቻሉን በተጨማሪም የውሃ እጥረቱ ህዝቡ በገንዘብ አቅምም የማይችለው መሆኑን ሲገልፅ 71% የሚሆነው ሕዝብ ከ3.10 ዶላር በታች የሚያገኝ ሕዝብ መሆኑ በእራሱ ፈታኝ መሆኑን ይገልጣል።

ባጠቃላይ የመሰረታዊ ነገሮች አቅርቦት ውስጥ ዋናው የሆነው የውሃ ነገር በእራሱ ውሃ እየሆነ ነው።ለእዚህ ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስደው ስልጣን ላይ የሚገኘው የሕውሓት መንግስት ዕቅድ አለማወቅ፣ቅድምይ በጀት አመዳዳብ ስህተት እና የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍልሰት ሁሉ ተጠቃሾች ናቸው።በአንፃሩ ደግሞ የስርዓቱ የጥቅም ተጋሪዎች የሆኑ እንደ አሸን የፈሉት የታሸገ ውሃ አምራቾች ይህንን የውሃ እጥረት እንደ ሰርግ እና ምላሽ ነው የሚመለከቱት።ይህንን ደግሞ ስርዓቱ ላይ በስልጣን ላይ ያሉት ግለሰቦች የእነኝህ የታሸገ ውሃ አምራች ድርጅቶች ባለቤቶች ናቸው። ለእነርሱ ትርፍ ሲባል ሕዝብ የሚጠጣው ውሃ ላይ በቂ ትኩረት አይሰጠውም። ለውሃ እጥረት ምክንያቱም ምን እንደሆነ የተጠየቀው የሕወሓት መንግስት እስካሁን የረባ መልስ ሲሰጥ አልተደመጠም። አንድ ወቅት አቶ ሃይለማርያም የውሃ እጥረት ሕዝብ መብዛቱን እንደ ምክንያት ሲያቀርቡ መንግስት ቀድሞ ማቀድ ይገባው እንደነበር እና የቢራ ፋብሪካ ከመደርደር ይልቅ የውሃ ፕሮጀክት መስራት ይገባው እንደነበር ተናግረው አያውቁም።የውሃ ፍሳሽ ቢሮም ስለ ችግሩ ሲጠየቅ የሚሰጠው ምክንያት መብራት አለመኖር እና አዲስ አበባም የተቆፈረው ጉድጉአድ እየጎደለ ነው የሚል ነው።ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከኮንጎ ቀጥሎ የውሃ ማማ ተብላ የምትጠራ ሀገር ነች።ነዳጅ ከጅቡቲ በቧንቧ እስባለሁ ያለ መንግስት እንዴት ለአዲስ አበባ ጉድጉአድ በመቆፈር ችግሩን ለመፍታት እየሞከርኩ ነው ብሎ ይናገራል? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። 

ከእዚህ በታች የምትሰሙት ዜና ከስድስት ወራት በፊት የወጣ የፋና ዘገባ ሲሆን በዘገባው በርካታ ምክንያቶች ለመስጠት ቢሞከርም ዋናው ምክንያት ከላይ የተጠቀሰው ቀድሞ የሚያቅድ መንግስት አለመኖር እና የሀገሪቱን ገንዘብ ቅድምያ ለሚሰጡ ጉዳዮች ላይ ያለመመደብ እንዲሁም የተማረ የሰው ኃይል እጥረት ከመብራት እጥረት ጋር ተዳምሮ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ይህ ዜና ከተወራ  ከወራት ወዲህም  አሁንም  ችግሩ በበለጠ ተባብሶ ይገኛል።የፈረቃ አገልግሎቱ የተጀመረው ያለፈው ዓመት እንደነበር ከእዚህ በታች ያለው ዜና ይነግረናል።አሁን ያለው ችግር ግን እራሱ ፈረቃው በተባለው ቀን አለመምጣቱ ነው።ውሃ ጠማኝ በምከፍለው የቀረጥ ገንዘብ መንግስት ውሃ ያቅርብ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካ ተብሎ ሊያሳስር ይችላል።




ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com

Monday, February 6, 2017

ኢትዮጵያውያን በአካባቢያዊ ስሜት እንዳንለያይ ያደረገን አንዱ የአብሮነታችንን ቦታ(ትምህርት ቤቶቻችንን) ሁለቱን ቪድዮዎች ከተመለከቱ በኃላ ያገኛሉ።

በእነኝህ ሁለት ቪድዮዎች ውስጥ : - 

- ድምፃዊት ኩኩ ሰብስቤ ተወስታለች፣
- የኮ/ል መንግስቱ ሃይለማርያም ሁለት ልጆች የደረሰባቸው ገጠመኞች በአድራጊዋ ይተረካል፣
- ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር ይጠየቃል፣
- ጋሽ  ጫሊ በትጋት የሰሩት ሥራ ስንቶችን ለቁም ነገር አብቅቶ እስከ ናሳ የጠፈር ምርምር ድረስ እንዳደረሰ  ይመለከቱበታል።
- ወ/ሮ አይኗዓለም በትዝታቸው ያለቅሳሉ።
የእዚህ ቪድዮ አላማ ኢትዮጵያዊነት ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ።በእየእለቱ የሚሰሩ ስራዎች ሁሉ ማንን እንደሚገነቡ እንድናስተውል እና የጎሰኝነት አስተሳሰብን በልጆች ላይ እንዳያድር ብርቱ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ለማሳሳብ ነው።ልጆቻቸውን በጎሳ ስሜት የምቀርፁ ቆም ብለው እንዲያስቡ እነኝህ ቪድዮዎች አስተማሪ ናቸው።
ቪድዮው ከጀመሩት አያቆሙትም። 

ክፍል 1



ክፍል 2


የሁለቱም ቪድዮዎች ምንጭ = መሰረቱን አሜሪካ ያደረገው ኢቢኤስ ቴሌቭዥን
Source= EBS TV WORLD WIDE


ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com

Friday, February 3, 2017

ሰበር ዜና - ግብፅ የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ ይዞታዎችን በጦር ጀት ደበደበች።ጉዳዩ አዲስ አካባቢያዊ ውጥረት ይፈጥራል።Egyptian Air Force bombs South Sudanese rebels




ጉዳያችን / Gudayachn 
ጥር 27/2009 ዓም  (ፈብርዋሪ 4፣2017)
========================
የሱዳን ህዝቦች ነፃነት ጦር የተሰኘው የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ ይዞታ ላይ የግብፅ የጦር አይሮፕላኖች ቢያንስ ዘጠኝ ቦንቦች መጣላቸውን የተቃዋሚ ጦሩ ቃል አቀባይ ኮ/ል ዊልያም ጋትጅአዝ ደንግ አስታውቀዋል።ቃል አቀባዩ አክለው እንደተናገሩት የግብፅ ድርጊት አካባቢያዊ ጦርነት ሊጭር ይችላል ማለታቸውን የደቡብ ሱዳን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።ግብፅ የአየር ጥቃት ትናንት ሐሙስ እለት መፈፀሟን የገለፀው የሱዳን ህዝቦች ነፃነት ጦር የተሰኘው የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ ኃይል በጥር ወር ላይ ግብፅ እና የጁባ መንግስት የፈፀሙትን ውል ¨ቆሻሻ ውል¨በማለት ከጠራው በኃላ በስምምነቱ መሰረት ደቡብ ሱዳን ጠቀም ያለ የጦር መሳርያ ከግብፅ እንደምታገኝ ቃል እንደተገባላት በመጥቀስ መክሰሱ ይታወሳል።ከእዚህ በተጨማሪም የሁለቱ ሀገሮች ውል ኢትዮጵያ ላይ ያለመ መሆኑን ይሄው ተቃዋሚ ኃይል ባወጣው መግለጫ መጥቀሱ ይታወቃል።

በሌላ በኩል ዩጋንዳ ሰራዊቷን ከደቡብ ሱዳን ማውጣት ማሰቧን እና ይህም ለሱዳን ሰላም ወሳኝ መሆኑን ደግማ ያስተጋባችው በእዚህ ሳምንት ነበር።በተለይ የዩጋንዳ የእዚህ ሳምንት ሰራዊቷ እንደሚወጣ መግለጧ ከግብፅ ጉዳይ ጋር ለማያይዝ ግርታ ፈጥሮ ነበር።ይህ የግብፅ የአየር ጥቃት ጋር ጉዳዩ ሲያያዝ ግን ምናልባት የአየር ጥቃቱን ዩጋንዳም ከግብፅ ጋር ካደረገችው ንግግር ጋር የሚገናኝ ነጥብ ሊኖረው ይችላል የሚል ጥርጣሬ ያጭራል።የዛሬውን የግብፅ የአየር ጥቃት አስመልክተው መግለጫ የሰጡት ኮ/ል ዊልያም ጋትጅአዝ ደንግ (Colonel William Gatjiath Deng) የግብፅን ድርጊት የአፍሪካ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምርመራ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የሕወሓት መንግስት በእዚህ ሳምንት ለአፍሪካ ህብረት ስብሰባ አዲስ አበባ የገቡትን የግብፅ እና የደቡብ ሱዳን መሪዎች ጋር ያደረገውን የእግረ መንገድ ስብሰባ እያስታከከ ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳንም ሆነ ከግብፅ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላት ከመግለፅ አልፎ የመንግስት ቃል አቀባይ በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መሃል ችግር እንዳለ የሚያወሩ ፀረ ሰላም እንደሆኑ መግለፃቸው እና ፋና ብሮድካስቲንግም ይህንኑ ከፍ አድርጎ ለማስተጋባት ሲሞክር ሰንብቷል።ብዙዎች የስርዓቱ ደጋፊዎችም ጭምር አቶ ኃይለማርያም ፈፅሞ የዲፕሎማሲው ደንብም ሆነ ፕሮቶኮሉ በማይፈቅደው ደረጃ ከመጠን ያለፈ ¨ተለማማጭ¨ የመሰለ ፈገግታ ለግብፁም ሆነ ለደቡብ ሱዳን መሪዎች በማሳየት በመታየታቸው ሕወሓት ኢትዮጵያን ምን ያህል ደረጃ እያወረዳት እንደሆነ በቁጭት የሚገልፁ ብዙዎች ናቸው።

ከእዚህ በታች የደቡብ ሱዳን ዜና አገልግሎት ከሰዓታት በፊት ግብፅ የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚዎች ይዞታን በጦር ጀት መደብደቧን የገለፀበትን ሙሉ ዜና ይመልከቱ።

Egyptian Air Force bombs South Sudanese rebels in Upper Nile

February 3, 2017Breaking News, News, South Sudan

 The military command of the Sudan People’s Liberation Army-In Opposition (SPLA-IO) has accused Egyptian air force of carrying out air attacks on its bases in Kaka town, saying Cairo dropped at least nine bombs and explosions.

Rebel military spokesperson Colonel William Gatjiath Deng, who declined to offer more details, warned that the involvement of JEM, the SPLM-North, and Egypt in the ongoing civil war could provoke a regional war.

“The continuous involvement of the Sudanese rebels and the escalation of the Egyptian participation in the ongoing war in South Sudan are clear indications to the people of South Sudan, the African Union (AU), the United Nations (UN) and the international community that the Juba regime is provoking the region and tilting South Sudan for a regional war,” he said.

Col. Deng also claimed two Sudanese rebel groups: Justice and Equality Movement (JEM) and the SPLM-North sneaked into South Sudan Thursday from their northern base called Angathna in the Blue Nile and that their intention is to attack and retake Mustakbal, Wadekona, and Detang from the armed opposition.

He further asserted in a statement that combined forces of government and Sudanese rebels launched a coordinated attack on SPLA-IO positions in Detang today, which he said resulted in a shocking defeat to Lelo, adding rebel forces inflicted heavy losses on the enemies forcing them to flee to areas in Renk, Malakal, and Paloch.

He added the SPLA-IO captured 43 PKMs and 300 AK-47s in good condition.

The rebel spokesman further explained that Juba-backed forces were also repulsed in Booth and Mayom of Unity State. He claimed SPLA-IO Special Division captured nine government soldiers and that they are being treated as Prisoners of War.

South Sudanese rebels have increasingly become suspicious of recent bilateral agreements Cairo strucked with Juba.

In January, the SPLM/A-IO accused South Sudan and Egypt of striking a “dirty deal,” saying the agreement would allow Kiir to receive lethal weapons and ammunition from Egypt to wage a full-scale war against the armed opposition.

“There is a dirty deal going between Kiir and El-Sisi. the issue of Grand Ethiopian Renaissance Dam is one of the main deals being finalized in Cairo. Our intelligence sources in Kampala and Juba confirmed that Egypt wants South Sudan and Uganda to be her regional allies so that she can advance its covert sabotage campaign against the Ethiopian Dam. The man [Kiir] is a double agent; he will cause many problems for the entire East Africa region,” a senior rebel official told the South Sudan News Agency last month.

The official added that Egyptian military experts and engineers have been in Juba for months and that the entire secret military deal between Juba and Cairo was orchestrated by Kampala last year.

Col. Deng calls on the AU, UN, and the international community to investigate Egypt’s involvement in South Sudan civil war.

 Source: - ደቡብ ሱዳን ዜና አገልግሎት / South Sudan News Agency 

ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

Thursday, February 2, 2017

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ተመሰቃቅሏል መጪው የህዝብ አመፅ ይህንን መሰረት አድርጎ ይነሳል (የጉዳያችን ልዩ ሪፖርት)

ጉዳያችን / Gudayachn
ጥር 26፣2009 ዓም ( ፈብርዋሪ 3፣2017)
============================
የኢትዮጵያን የአሁኑን ምጣኔ ሀብት ሁኔታ ለመግለፅ በጣም ከባድ ነው።የተመሰቃቀለ፣አቅጣጫ እና ግብ ያልተቀመጠለት ነገር ግን ለጥቂት ወገኖች ብቻ የተመቻቸ መንገድ ሲፈልግ የሚውል ባለ አነፍናፊ ፖሊሲ  እና በማናቸውም ጊዜ ለጥቂት ወገኖች እስከተመቸ ድረስ ኢትዮጵያን እና ጥቅሟን ለሽያጭ ለማቅረብ የተዘጋጀ ግብስባሽ ሃሳቦች ውስጥ የታጨቀ ምጣኔ ሀብት ነው።

ምጣኔ ሀብት ሂደቱን በደምሳሳው ለማየት ፈልጋችሁ አንዲት ስኒ ቡና አስቀድታችሁ ለማሰብ ስትሞክሩም ብዙ የተዘባረቀ ሁኔታ ግልጥ ብሎ ይታያል።የዋጋ ንረቱ ከሚጠበቀው በላይ እየጨመረ ነው።የውጭ ምንዛሬ ተሟጦ ከውጭ ዕቃ ለማስመጣት የመዳኒት እና ነዳጅ ካልሆነ በቀር ሌላው በትንሹ ለሶስት ወራት ጠብቆ ማግኘት የሎተሪ ያህል መቆጠር ጀምሯል።የሀገሪቱ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ ለማስገባት አልቻሉም።የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች አቅም ሙሉ በሙሉ በመዳከሙ ህዝቡ የቻይና ልብስ ለባሽ ሆኗል።ወደ ዱባይ እና ቻይና የሚበሩ ነጋዴዎች ያገኙትን ጨርቅ እየለቀሙ ሕዝቡን ማልበስ ይዘዋል።ባንኮች የሰጡት ብድር በተበላሸ ብድር እና ገንዘባቸው በተበሉ የከተማ ፎቆች ተጥለቅልቀዋል።ከቱርክ እና ህንድ ድረስ መጥተው ከኢትዮጵያ ባንኮች ለተወሰዱ ብድሮች እና ጥለው ለጠፉ ኩባንያዎች ተከታትሎ የሚጠይቅ የለም።

ምንጭ:የኢትዮጵያስታትስቲክስቢሮ

ከላይ የምትመለከቱት ግራፍ ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ቢሮ የሸማቾች ዋጋ እንዴክስ ላይ የተወሰደ ሲሆን በአለፈው ዓመት እና በዘንድሮው ዓመት ብቻ ከፍተኛ የዋጋ ንረት መኖሩን እና ይህም አዲስ አበባ ላይ ከፍተኛ እንደሆነ እንመለከታለን።በተለይ በ2011 እና በ2016 እኤአ ኢትዮጵያ አደገች ተብሎ የተነገረበት እና ስርዓቱ ¨ሁለት ዲጅት በተከታታይ ያደግንበት¨ ያለባቸው አመታት ሕዝብ የመግዛት አቅሙ ምን ያህል እንደወረደ ለመረዳት የዋጋ ግሽበቱን ብቻ መመልከት በቂ ነው።

ከምግብ ዋጋ በተለየ የችርቻሮ ዋጋ መጨመር የተጠቁትን አካባቢዎች ለመመልከት አሁንም ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ቢሮ ገፅ የዘንድሮ እና የአለፈ አመትን ያነፃፀረበት አረፍተ ነገሮች ከእዚህ በታች እንዳለ ቀርበዋል።በንፅፅሩ መሰረት ባለፈው ዓመት ከነበረው ጋር ብቻ የዋጋ ንረቱን ብናስተያየው የአገር አቀፍ ጭማሪው 6.7% መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል።

እዚህ ላይ ግን አንድ አስገራሚ ጉዳይ አለ። ይሄውም ለምግብ እንዴክስ መጨመር ምክንያት ከሆኑት ውስጥ ከፍተኛ የምግብ አምራቾቹ ለምሳሌ የአማራ ክልል 8.5%  ሲሆን እና የደቡብ ክልል 13.2% ሲያሳይ ትግራይ 3.6% ብቻ ያሳያል።ይህ ማለት ደቡብ እና አማራ ከሚያመርተው የትግራይ የምግብ ምርት ጨመረ እና የዋጋ ንረቱን ተቆጣጠረ? ወይንስ ስርጭቱ ላይ ፍትሃዊ አሰራር ስለሌለ? ይህንን ለአንባቢ ኢትወዋለሁ።የቢሮው የእዚህ ወር ዘገባ ከእዚህ በታች ይመልከቱት።


ምንጭ : - ኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ቢሮ

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት የህወሓት ውላጅ በሆኑ ኩባንያዎች ሙሉ በሙሉ ከመውደቁ በላይ የእራሱም ኩባንያዎች አሁን በአጠቃላይ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል።ውላጅ ኩባንያዎቹ በቢራ፣በኮንስትራክሽን፣በጨርቃጨርቅ እና በባንክ ዘርፍ የተሰማሩት በህዝባዊ አመፁ ከፍተኛ ኪሳራ ላይ ወድቀዋል ለብቻ ሳይሆን አሁንም ድረስ ህዝቡ ያልታወጀ እቀባ በሕወሓት ውላጅ ኩባንያዎች ላይ እንደጣለ ነው።አዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች ሀበሻ ቢራ እና ቅዱስ ጊዮርጊስን እንጂ ዳሸን የሚጠጣ ሰው ገና ቢራውን ሳይከፍት የህዝብ ግልምጫ ብቻ ሳይሆን አስተናጋጁ እራሱ የመዛት ያህል ይመለከተዋል።ስለሆነም የስርዓቱ ሰዎችም ደፍረው የሕወሓት ውላጅ ኩባንያዎችን እቃዎች መጠቀም አይችሉም።

ሕወሓት ምጣኔ ሃብቱን እንዴት እንደሚመራ ሃሳብ ማመንጨት አቅቶታል።የተቀዳደደ ልብስ ለመጣፍ እንደሚያስቸግር ሁሉ።የኑሮ ውድነቱ የምያስነሳውን አዲስ ሕዝባዊ አመፅ በመፍራት ብቻ ገና የዘንድሮውን በጀት ሥራ ላይ ሳያውል ለሠራተኛ ደሞዝ ልጨምር ነው፣ የደሞዝ ጭማሪው የዋጋ ንረት አያስከትልም፣ ለወጣቱ ሥራ ዕድል ፈጠርኩ እና ሌሎችም ተስፋዎችን በእየቀኑ እየፈጠረ በራድዮ እና ቴሌቭዥን መልቀቅ ይዟል።ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የትግራይ ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ በጋምቤላ መሬት ወስደው በቢልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለወሰዱ እና ላከሰሩ ግብረ አበሮቹ ተጨማሪ ብድር ሰጠሁ ብሎ ባንኮችን አደጋ ላይ ጥሏል።የባንኮች ኪሳራ ሲያሰጋው ደግሞ የባንክ መነሻ ካፒታል አሳድጋለሁ እና ባንኮች መዋሃዳቸው አይቀርም ይልሃል።ባጭሩ መያዣ መጨበጫው ጠፍቷል።በእዚህ ሁሉ ላይ የአውሮፓ ህብረት እና አዲሱ የትራምፕ መንግስት አስተማማኝ ምንጭ እንደማይሆኑ ከወዲሁ ብዙ ምልክቶች ይታያሉ።


ምንጭ: - አይኤምኤፍ ኢትዮጵያ ሪፖርት 2016

ከላይ በግራፉ ላይ እንደተመለከተው የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ አስገኝ ቀዳሚ ድርሻ የሚይዙት ቡና እና የቅባት እህሎች ናቸው።እነኝህ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ በግራፉ ላይ እንደተመለክተው ባለፉት ሁለት አመታት ይህንንም ዓመት ጨምሮ ዓለም አቀፍ ዋጋቸው በጣም ቀንሷል።ይህም ያለችውን ጭላንጭል ገበያ (ከሕዝባዊ አመፁ የተረፈውን) ምን ያህል እንደሚጎዳ መገመት ይቻላል።ሕወሓት ግን በእዚህ ደረጃ ታሞም ደህና እንደሆነ እና እድገቱ ´እየገሰገሰ መሆኑን ለወዳጆቹ ይነግራቸዋል።

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በሕወሓት እና ውላጅ ኩባንያዎቹ የመጠቃለሉን ያህል አሁን ያለበት ሁኔታ ትልቅ ተሳቢ መኪና ግማሽ አካሉን ትልቅ ገደል ጫፍ ላይ አድርጎ በትንሽ ንቅናቄ የመንኮታኮት እጣ የሚጠብቅ ይመስላል።ላለፉት አንድ አመታት ያህል በኦሮምያ ክልል የሚገኙት ወደውጭ ከሚላኩ ምርቶች ውስጥ ቡና እና ከደቡብ የሚላኩት ቅመማ ቅመም ወቅቱን ጠብቀው ወደውጭ ሊደርሱ አልቻሉም። በመሆኑም በርካታ ኩባንያዎች ውላቸውን እንደሰረዙ ተሰምቷል።ሌላው የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ ቱሪዝም በአማራ ክልል ባለው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የለም ማለት ይቻላል። የኢትዮጵያ የቱሪስት ፍሰት ባብዛኛው የሚታይባቸው የመስቀል እና የጥምቀት በዓላት ዘንድሮ ዋና ዋና የሚባሉ የአውሮፓ እና አሜሪካ መንግሥታት ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይሄዱ ባወጡት ማሳስቢያ ሳብያ ዘንድሮ ቱሪስት በኢትዮጵያ የለም።ይህ ማለት ከቱሪስት ጋር ተያያዥ ገብ የሚያስገኙ እንደ ሆቴል እና ትራንስፖርት ገበያ የላቸውም ማለት ነው።በእዚህ ሳብያ በርካታ የንግድ ድርጅቶች አመታዊ የገቢ ግብር መክፈል አይችሉም።የሕወሓት አፍቃሪ ኩባንያዎችም የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት መውረድ ወደ የቁልቁለት መንገድ እየመራቸው ነው።በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማራው የተክለብርሃን አምባዬ ድርጅት በርካታ ሰራተኞቹን ደሞዝ መክፈል ባለመቻሉ ምክንያት ከስራ ማስወጣቱ የተሰማው በያዝነው ወር ውስጥ ነው።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ውጭ ምንዛሬ አስገኝ የቆዳ ምርት ከፍተኛ ደረጃ ምርቱ ቀንሷል። ለእዚህም ዋናው ምክንያት የአሜሪካ አግዋ ስምምነት ሥራ መታጠፍ እና ለምርቱ ግባት የሚሆን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ ነው።ይህንን ተከትሎ ከጥቂት አመታት በፊት ውድ የነበረው የበግ እና የፍየል ቆዳ ዛሬ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ወደ ነበረበት ዋጋ ወርዷል።ምክንያቱም የሀገር ውስጥ የቆዳ ምርት ወድቆ የቻይና ላስቲክ ለበስ ቆዳ መሰል ልብሶች ሀገሪቱን አጥለቅልቀዋል። ይህ ትልቅ ራእይ የነበረው እና የቆዳ ምርት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት እስከመመሥረት የተደረሰበት ሥራ ዛሬ እንዳይሆኑ ሆኗል።የአርባ ምንጭ እና የባህርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎችን ብንመለከት ፋርብካዎቹን ሕወሓት በውላጅ ኩባንያዎቹ ማለትም የአርባ ምንጭ ጨርቃጨርቅን አልመዳን እንዲወስደው የባርዳሩን ደግሞ የአማራ ክልል ውላጅ ኩባንያ እንዲወስደው ተደርጎ ዛሬ የአርባምንጭ ፋብሪካ ከነበሩት ከአንድ ሺህ በላይ ሰራተኞች ዛሬ ወደ መቶዎች ወርዶ የፋብሪካው እቃዎች እየተነቀሉ ወደ ትግራይ ተወስደዋል።ይህ እንደ አገር ስንመለከት ትልቅ ውደመት ነው።የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ግን አሁንም የአቶ ኃይለማርያምን በደንብ ስላልጮህን ነው እንጂ አድገናል ንግግር ያሳያል።

ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ይህንን ያህል ደረጃ መድረስ በመጀመርያ ደረጃ ተጎጂ ያደረገው ከታች ያለውን በዝቅተኛ ገቢ ደረጃ የሚገኘውን ሕዝብ ነው። ይህ ሕዝብ የሚበላው አጥቶ እየተንቀራተተ ጥቂት ቅምጥሎች በሚልዮን የሚቆጠር ብር የሚያወጣ መኪና እየነዱ ሲያልፉ እየተመለከተ ነው። ይህ ሕዝብ ልጆቹ ትምህርት ቤት ይዘው የሚሄዱት ምሳ እያጣ ጥቂቶች የበሉትን ለማግሳት ቦታ ሲመርጡ እየታዘበ ነው።ይህ ሕዝብ አንገቱን የሚያስገባበት ቦታ እየጠየቀ ጥቂቶች አንድ ካሬ መሬት በ50 ሺህ ብር ጨረታ ማሸነፋቸውን እየነገሩት ነው። የፈረንሳይ አብዮት ከጨረቃ ላይ አልወረደም የ1966ቱ የየካቲት ወር አብዮት ከውጭ ሀገር አልተፈበረከም። የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ነው።ባጭሩ እያጣጣረ ነው።ለጊዜው አስታማሚ ሀኪም የተመደበለት የቻይና ጊዚያዊ የራስ ምታት ማስታገሻ ነው። ተወደደም ተጠላ መሪ እና አስተባባሪ የማይፈልግ ግብታዊ የነፃነት፣የመኖር እና የህልውና ሕዝባዊ አመፅ የምጣኔ ሃብቱ መመሰቃቀል ብቻ ያስነሳዋል።ለእዚህ ሁሉም ወገኖች ዝግጅት ሊያደርጉ ይገባል።የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ተመሰቃቅሏል። መጪው የህዝብ አመፅ ይህንን መሰረት አድርጎ ይነሳል። 

ጉዳያችን GUDAYACHN 

 www.gudayachn.com

ማጣቀሻ መረጃዎች
- አይ ኤም ኤፍ
 https://www.imf.org/external/pubs/ft/scr/2016/cr16322.pdf

- የኢትዮጵያ ስታስቲክስ ቢሮ http://www.csa.gov.et/images/documents/pdf_files/CPI/cpi_december_2016

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...