ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, February 2, 2017

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ተመሰቃቅሏል መጪው የህዝብ አመፅ ይህንን መሰረት አድርጎ ይነሳል (የጉዳያችን ልዩ ሪፖርት)

ጉዳያችን / Gudayachn
ጥር 26፣2009 ዓም ( ፈብርዋሪ 3፣2017)
============================
የኢትዮጵያን የአሁኑን ምጣኔ ሀብት ሁኔታ ለመግለፅ በጣም ከባድ ነው።የተመሰቃቀለ፣አቅጣጫ እና ግብ ያልተቀመጠለት ነገር ግን ለጥቂት ወገኖች ብቻ የተመቻቸ መንገድ ሲፈልግ የሚውል ባለ አነፍናፊ ፖሊሲ  እና በማናቸውም ጊዜ ለጥቂት ወገኖች እስከተመቸ ድረስ ኢትዮጵያን እና ጥቅሟን ለሽያጭ ለማቅረብ የተዘጋጀ ግብስባሽ ሃሳቦች ውስጥ የታጨቀ ምጣኔ ሀብት ነው።

ምጣኔ ሀብት ሂደቱን በደምሳሳው ለማየት ፈልጋችሁ አንዲት ስኒ ቡና አስቀድታችሁ ለማሰብ ስትሞክሩም ብዙ የተዘባረቀ ሁኔታ ግልጥ ብሎ ይታያል።የዋጋ ንረቱ ከሚጠበቀው በላይ እየጨመረ ነው።የውጭ ምንዛሬ ተሟጦ ከውጭ ዕቃ ለማስመጣት የመዳኒት እና ነዳጅ ካልሆነ በቀር ሌላው በትንሹ ለሶስት ወራት ጠብቆ ማግኘት የሎተሪ ያህል መቆጠር ጀምሯል።የሀገሪቱ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ ለማስገባት አልቻሉም።የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች አቅም ሙሉ በሙሉ በመዳከሙ ህዝቡ የቻይና ልብስ ለባሽ ሆኗል።ወደ ዱባይ እና ቻይና የሚበሩ ነጋዴዎች ያገኙትን ጨርቅ እየለቀሙ ሕዝቡን ማልበስ ይዘዋል።ባንኮች የሰጡት ብድር በተበላሸ ብድር እና ገንዘባቸው በተበሉ የከተማ ፎቆች ተጥለቅልቀዋል።ከቱርክ እና ህንድ ድረስ መጥተው ከኢትዮጵያ ባንኮች ለተወሰዱ ብድሮች እና ጥለው ለጠፉ ኩባንያዎች ተከታትሎ የሚጠይቅ የለም።

ምንጭ:የኢትዮጵያስታትስቲክስቢሮ

ከላይ የምትመለከቱት ግራፍ ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ቢሮ የሸማቾች ዋጋ እንዴክስ ላይ የተወሰደ ሲሆን በአለፈው ዓመት እና በዘንድሮው ዓመት ብቻ ከፍተኛ የዋጋ ንረት መኖሩን እና ይህም አዲስ አበባ ላይ ከፍተኛ እንደሆነ እንመለከታለን።በተለይ በ2011 እና በ2016 እኤአ ኢትዮጵያ አደገች ተብሎ የተነገረበት እና ስርዓቱ ¨ሁለት ዲጅት በተከታታይ ያደግንበት¨ ያለባቸው አመታት ሕዝብ የመግዛት አቅሙ ምን ያህል እንደወረደ ለመረዳት የዋጋ ግሽበቱን ብቻ መመልከት በቂ ነው።

ከምግብ ዋጋ በተለየ የችርቻሮ ዋጋ መጨመር የተጠቁትን አካባቢዎች ለመመልከት አሁንም ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ቢሮ ገፅ የዘንድሮ እና የአለፈ አመትን ያነፃፀረበት አረፍተ ነገሮች ከእዚህ በታች እንዳለ ቀርበዋል።በንፅፅሩ መሰረት ባለፈው ዓመት ከነበረው ጋር ብቻ የዋጋ ንረቱን ብናስተያየው የአገር አቀፍ ጭማሪው 6.7% መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል።

እዚህ ላይ ግን አንድ አስገራሚ ጉዳይ አለ። ይሄውም ለምግብ እንዴክስ መጨመር ምክንያት ከሆኑት ውስጥ ከፍተኛ የምግብ አምራቾቹ ለምሳሌ የአማራ ክልል 8.5%  ሲሆን እና የደቡብ ክልል 13.2% ሲያሳይ ትግራይ 3.6% ብቻ ያሳያል።ይህ ማለት ደቡብ እና አማራ ከሚያመርተው የትግራይ የምግብ ምርት ጨመረ እና የዋጋ ንረቱን ተቆጣጠረ? ወይንስ ስርጭቱ ላይ ፍትሃዊ አሰራር ስለሌለ? ይህንን ለአንባቢ ኢትወዋለሁ።የቢሮው የእዚህ ወር ዘገባ ከእዚህ በታች ይመልከቱት።


ምንጭ : - ኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ቢሮ

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት የህወሓት ውላጅ በሆኑ ኩባንያዎች ሙሉ በሙሉ ከመውደቁ በላይ የእራሱም ኩባንያዎች አሁን በአጠቃላይ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል።ውላጅ ኩባንያዎቹ በቢራ፣በኮንስትራክሽን፣በጨርቃጨርቅ እና በባንክ ዘርፍ የተሰማሩት በህዝባዊ አመፁ ከፍተኛ ኪሳራ ላይ ወድቀዋል ለብቻ ሳይሆን አሁንም ድረስ ህዝቡ ያልታወጀ እቀባ በሕወሓት ውላጅ ኩባንያዎች ላይ እንደጣለ ነው።አዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች ሀበሻ ቢራ እና ቅዱስ ጊዮርጊስን እንጂ ዳሸን የሚጠጣ ሰው ገና ቢራውን ሳይከፍት የህዝብ ግልምጫ ብቻ ሳይሆን አስተናጋጁ እራሱ የመዛት ያህል ይመለከተዋል።ስለሆነም የስርዓቱ ሰዎችም ደፍረው የሕወሓት ውላጅ ኩባንያዎችን እቃዎች መጠቀም አይችሉም።

ሕወሓት ምጣኔ ሃብቱን እንዴት እንደሚመራ ሃሳብ ማመንጨት አቅቶታል።የተቀዳደደ ልብስ ለመጣፍ እንደሚያስቸግር ሁሉ።የኑሮ ውድነቱ የምያስነሳውን አዲስ ሕዝባዊ አመፅ በመፍራት ብቻ ገና የዘንድሮውን በጀት ሥራ ላይ ሳያውል ለሠራተኛ ደሞዝ ልጨምር ነው፣ የደሞዝ ጭማሪው የዋጋ ንረት አያስከትልም፣ ለወጣቱ ሥራ ዕድል ፈጠርኩ እና ሌሎችም ተስፋዎችን በእየቀኑ እየፈጠረ በራድዮ እና ቴሌቭዥን መልቀቅ ይዟል።ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የትግራይ ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ በጋምቤላ መሬት ወስደው በቢልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለወሰዱ እና ላከሰሩ ግብረ አበሮቹ ተጨማሪ ብድር ሰጠሁ ብሎ ባንኮችን አደጋ ላይ ጥሏል።የባንኮች ኪሳራ ሲያሰጋው ደግሞ የባንክ መነሻ ካፒታል አሳድጋለሁ እና ባንኮች መዋሃዳቸው አይቀርም ይልሃል።ባጭሩ መያዣ መጨበጫው ጠፍቷል።በእዚህ ሁሉ ላይ የአውሮፓ ህብረት እና አዲሱ የትራምፕ መንግስት አስተማማኝ ምንጭ እንደማይሆኑ ከወዲሁ ብዙ ምልክቶች ይታያሉ።


ምንጭ: - አይኤምኤፍ ኢትዮጵያ ሪፖርት 2016

ከላይ በግራፉ ላይ እንደተመለከተው የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ አስገኝ ቀዳሚ ድርሻ የሚይዙት ቡና እና የቅባት እህሎች ናቸው።እነኝህ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ በግራፉ ላይ እንደተመለክተው ባለፉት ሁለት አመታት ይህንንም ዓመት ጨምሮ ዓለም አቀፍ ዋጋቸው በጣም ቀንሷል።ይህም ያለችውን ጭላንጭል ገበያ (ከሕዝባዊ አመፁ የተረፈውን) ምን ያህል እንደሚጎዳ መገመት ይቻላል።ሕወሓት ግን በእዚህ ደረጃ ታሞም ደህና እንደሆነ እና እድገቱ ´እየገሰገሰ መሆኑን ለወዳጆቹ ይነግራቸዋል።

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በሕወሓት እና ውላጅ ኩባንያዎቹ የመጠቃለሉን ያህል አሁን ያለበት ሁኔታ ትልቅ ተሳቢ መኪና ግማሽ አካሉን ትልቅ ገደል ጫፍ ላይ አድርጎ በትንሽ ንቅናቄ የመንኮታኮት እጣ የሚጠብቅ ይመስላል።ላለፉት አንድ አመታት ያህል በኦሮምያ ክልል የሚገኙት ወደውጭ ከሚላኩ ምርቶች ውስጥ ቡና እና ከደቡብ የሚላኩት ቅመማ ቅመም ወቅቱን ጠብቀው ወደውጭ ሊደርሱ አልቻሉም። በመሆኑም በርካታ ኩባንያዎች ውላቸውን እንደሰረዙ ተሰምቷል።ሌላው የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ ቱሪዝም በአማራ ክልል ባለው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የለም ማለት ይቻላል። የኢትዮጵያ የቱሪስት ፍሰት ባብዛኛው የሚታይባቸው የመስቀል እና የጥምቀት በዓላት ዘንድሮ ዋና ዋና የሚባሉ የአውሮፓ እና አሜሪካ መንግሥታት ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይሄዱ ባወጡት ማሳስቢያ ሳብያ ዘንድሮ ቱሪስት በኢትዮጵያ የለም።ይህ ማለት ከቱሪስት ጋር ተያያዥ ገብ የሚያስገኙ እንደ ሆቴል እና ትራንስፖርት ገበያ የላቸውም ማለት ነው።በእዚህ ሳብያ በርካታ የንግድ ድርጅቶች አመታዊ የገቢ ግብር መክፈል አይችሉም።የሕወሓት አፍቃሪ ኩባንያዎችም የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት መውረድ ወደ የቁልቁለት መንገድ እየመራቸው ነው።በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማራው የተክለብርሃን አምባዬ ድርጅት በርካታ ሰራተኞቹን ደሞዝ መክፈል ባለመቻሉ ምክንያት ከስራ ማስወጣቱ የተሰማው በያዝነው ወር ውስጥ ነው።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ውጭ ምንዛሬ አስገኝ የቆዳ ምርት ከፍተኛ ደረጃ ምርቱ ቀንሷል። ለእዚህም ዋናው ምክንያት የአሜሪካ አግዋ ስምምነት ሥራ መታጠፍ እና ለምርቱ ግባት የሚሆን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ ነው።ይህንን ተከትሎ ከጥቂት አመታት በፊት ውድ የነበረው የበግ እና የፍየል ቆዳ ዛሬ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ወደ ነበረበት ዋጋ ወርዷል።ምክንያቱም የሀገር ውስጥ የቆዳ ምርት ወድቆ የቻይና ላስቲክ ለበስ ቆዳ መሰል ልብሶች ሀገሪቱን አጥለቅልቀዋል። ይህ ትልቅ ራእይ የነበረው እና የቆዳ ምርት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት እስከመመሥረት የተደረሰበት ሥራ ዛሬ እንዳይሆኑ ሆኗል።የአርባ ምንጭ እና የባህርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎችን ብንመለከት ፋርብካዎቹን ሕወሓት በውላጅ ኩባንያዎቹ ማለትም የአርባ ምንጭ ጨርቃጨርቅን አልመዳን እንዲወስደው የባርዳሩን ደግሞ የአማራ ክልል ውላጅ ኩባንያ እንዲወስደው ተደርጎ ዛሬ የአርባምንጭ ፋብሪካ ከነበሩት ከአንድ ሺህ በላይ ሰራተኞች ዛሬ ወደ መቶዎች ወርዶ የፋብሪካው እቃዎች እየተነቀሉ ወደ ትግራይ ተወስደዋል።ይህ እንደ አገር ስንመለከት ትልቅ ውደመት ነው።የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ግን አሁንም የአቶ ኃይለማርያምን በደንብ ስላልጮህን ነው እንጂ አድገናል ንግግር ያሳያል።

ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ይህንን ያህል ደረጃ መድረስ በመጀመርያ ደረጃ ተጎጂ ያደረገው ከታች ያለውን በዝቅተኛ ገቢ ደረጃ የሚገኘውን ሕዝብ ነው። ይህ ሕዝብ የሚበላው አጥቶ እየተንቀራተተ ጥቂት ቅምጥሎች በሚልዮን የሚቆጠር ብር የሚያወጣ መኪና እየነዱ ሲያልፉ እየተመለከተ ነው። ይህ ሕዝብ ልጆቹ ትምህርት ቤት ይዘው የሚሄዱት ምሳ እያጣ ጥቂቶች የበሉትን ለማግሳት ቦታ ሲመርጡ እየታዘበ ነው።ይህ ሕዝብ አንገቱን የሚያስገባበት ቦታ እየጠየቀ ጥቂቶች አንድ ካሬ መሬት በ50 ሺህ ብር ጨረታ ማሸነፋቸውን እየነገሩት ነው። የፈረንሳይ አብዮት ከጨረቃ ላይ አልወረደም የ1966ቱ የየካቲት ወር አብዮት ከውጭ ሀገር አልተፈበረከም። የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ነው።ባጭሩ እያጣጣረ ነው።ለጊዜው አስታማሚ ሀኪም የተመደበለት የቻይና ጊዚያዊ የራስ ምታት ማስታገሻ ነው። ተወደደም ተጠላ መሪ እና አስተባባሪ የማይፈልግ ግብታዊ የነፃነት፣የመኖር እና የህልውና ሕዝባዊ አመፅ የምጣኔ ሃብቱ መመሰቃቀል ብቻ ያስነሳዋል።ለእዚህ ሁሉም ወገኖች ዝግጅት ሊያደርጉ ይገባል።የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ተመሰቃቅሏል። መጪው የህዝብ አመፅ ይህንን መሰረት አድርጎ ይነሳል። 

ጉዳያችን GUDAYACHN 

 www.gudayachn.com

ማጣቀሻ መረጃዎች
- አይ ኤም ኤፍ
 https://www.imf.org/external/pubs/ft/scr/2016/cr16322.pdf

- የኢትዮጵያ ስታስቲክስ ቢሮ http://www.csa.gov.et/images/documents/pdf_files/CPI/cpi_december_2016

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...