ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, February 14, 2017

በሃያ ስድስት አመታት ውስጥ አራቱ የህወሓት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውጤት - ኢትዮጵያን በአረብ ሀገር የጦር ሰፈሮች ማስከበብ


ላለፉት 26 አመታት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን፣አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም እና አቶ ወርቅነህ ገበየሁ 

ጉዳያችን/Gudayachn
የካቲት 7፣2009 ዓም (ፈብሯሪ 14፣2017)
=======================
ባለፈው ቅዳሜ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ርዕዮት በተሰኘ የማኅበራዊ ሚድያ ቀጥታ ውይይት መርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አካባቢያዊ ተፅኖ በሱማሌ ካለው አንፃር ከባልደረቦቹ ጋር ጥሩ አድርገው ሲተነትኑ ነበር።በተለይ በእዚህ ውይይት ላይ ኢትዮጵያ ሱማሌ ውስጥ እንድትገባ ሲደረግ ሕወሓት ያስቀመጠው ግብ እና ስትራቴጂ ሳይኖር ዝም ብሎ ሽርፍራፊ ገንዘብ ከአሜሪካ የማግኘት ላይ ያለመ ነገር ግን ሃገራዊ ራእይ የሌለው መሆኑ ሰራዊታችን ከሱማልያ ሲወጣ አንዳች የኢትዮጵያን ጥቅም ሳያስከብር መሆኑን በመቆጨት ቀርቧል።ኢትዮጵያ ደማች አሁን ምንም ያልደከሙት የአረብ ሃገራት በነፃ የጦር ሰፈር እየመሰረቱ ነው።በእዚሁ የኢትዮያ ተፅኖ ፈጣሪነት ከጅኦ ፖለቲካ አንፃር ያለው ዋጋ በሕወሐቷ ኢትዮጵያ እየረከሰ መምጣቱን ጋዜጠኛ መሳይ ከበደም በፌስ ቡክ ገፁ ላይ በሚገባ አስቀምጦታል።

ሁለቱም ያነሱት ጭብጥ በጣም ትክክል ነው።ኢትዮጵያ ዙርያዋን እየተከበበች ነው ጅቡቲ፣ሱማልያ ላንድ፣አሰብ፣ምፅዋ እነኝህ ሁሉ የአረብ ሃገራት የጦር ሰፈሮች የተመሰረቱባቸው እና ለመመስረት ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ናቸው።ሕወሓት አሁንም የኢትዮጵያን ሕዝብ አዋጅ አውጥቶ በመግደል እና በማሰር ላይ እንጂ የኢትዮጵያን ጥቅም በታሪክ በሚያስጠይቅ ደረጃ አሳልፎ ሰጥቷል። ይህ ጉዳይ ደግሞ ከባድ ዋጋ የሚያስከፍለን እንደሚሆን ማወቅ አለብን።

በሃያ ስድስት አመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የተቀመጡት ከእዚህ በታች ያሉትን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ እና አካባቢ ዲፕሎማሲ ምን ሰሩ? ውጤቱ ምን ሆነ ብላችሁ ስትጠይቁ መልሱ የኢትዮጵያን ጥቅም የበለጠ አሳልፎ የሰጠ፣ግብ እና ስልት የሌለው፣ኢትዮጵያ ያጣችውን ጥቅም ከሕዝቡ እየደበቁ የማታለል ´ተግባር የተሰራበት እና ባብዛኛው የሀገርን ጥቅም ለግል እና ለመንደር ጥቅም ብቻ የዋለ ሆኖ ታገኙታላችሁ።ለእዚህ ምሳሌ የሚሆነው የደቡብ ሱዳን እና የሱማሊያ ጉዳይ ነው።ደቡብ ሱዳን ከግብፅ ጋር ከመግጠሟ በፊት ኢትዮጵያ በደርግ ዘመን ጀምሮ ዋጋ ከፍላባታለች። ከ80 ሺህ በላይ ሰራዊት ስንቅ እና ትጥቅ እየተሰጠው ሰልጥኗል።ደቡብ ሱዳን መንግስት ከሆነች በኃላ ህወሓት እንደ ትልቅ ግብ የወሰደው የእራሱ የሆኑ ሰዎች ግዝያዊ ለሆነ የንግድ ሥራ እንዲጠቀሙ መንገድ ማመቻቸት እንጂ ሃገራዊ ራእይ ያለው የኢትዮጵያን ጥቅም ያስጠበቀ ሥራ ባለመስራቱ አቶ ስዩም መስፍን ይዘውታል የተባለው የደቡብ ሱዳን ሽምግልና ኢትዮያን ከጫወታ ውጭ አድርጎ በርቀት ሪሞት ትከታተል የንበረችው ግብፅ የደቡብ ሱዳን ወዳጅ ሆና መጥታለች።

በሱማሌም የሆነው ይሄው ነው።ኢትዮጵያ በተለይ በሰሜን ሱማሌ እራሱን ከዋናው ሱማሌ ለይቶ በመንግሥትነት እንዲታወቅ ሲጥር የነበረው ክፍል ከኢትዮጵያ ከቀድሞ መንግስት ጀምሮ ከፍተኛ ድጋፍ ተደርጎለታል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ጀምሮ እስከ አድማስ ዩንቨርስቲ ቅርንጫፍ ከፍቶ እስከ ማስተማር ድረስ ኢትዮጵያ እጇ እረጅም ነበር።ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ስራዋ በግብ እና ስልት በማያውቁ እጅ ስለወደቀ በመጨረሻ ትናንት ከቢቢሲ እንዳነበብነው ዩናይትድ አረብ ኤምሬት ከእዚሁ የሱማሌ ክፍል ላይ የጦር ሰፈር ለመመስረት ስምምነት ላይ ደርሳለች።በሰሜን ሱዳን ያለው ግንኙነትንም ብንመለከት ከኢትዮጵያ ዘለቄታዊ የጥቅም ተግባር ላይ የተሳሰረ ሳይሆን የጎንደር ገበሬዎችን ከጀርባ የመደብደብ እና ከትግራይ ጥቅም ጋር ብቻ የተሳሰረ እንዲሆን ተደርጎ ተቀርፆ እናየዋለን።ለእዚህም ምስክሩ የሱዳኑ አልበሽር አዲስ አበባ ከምመጡበት ጊዜ ይልቅ መቀሌ ለህወሓት የምስረታ በዓል ላይ ሲገኙ ላቅ ያለ አቀባበል እንደሚደረግላቸው እና ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ለትግራይ ደህንነት በሚሰጡት ዋስትና ላይ እንጂ ለኢትዮጵያ መሆኑ ላይ እንዳይጨነቁ የተነገራቸው እስኪመስል ድረስ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ይልቅ የትግራይ ክልል አስተዳዳሪ ጋር ማውራት ይመርጣሉ።

በጅቡቲም የሆነው ይሄው ነው።ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ትኩስ እንጀራ ተጋሮላት የምትኖር ሀገር ተብላ ትነገር ነበር።በእውነትም ጅቡቲ ከንፁህ ውሃ እስከ ጫት ከወደብ ከምታገኘው ጥቅም አንፃር ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ ጥገኛ የሆነች ሀገር ነበረች።በጊዜ ብዛት ግን የእራሷን አቅም ከኢትዮጵያ በምታገኘው የወደብ ክፍያ እያዳበረች መጥታለች።መሪዋ አማርኛ ከመናገር ጀምሮ ድሬዳዋ እስከመማር ኢትዮጵያም ሰፋፊ ግቢ ቤቶችን እንደገዙ የሚነገርላቸው  ፕሬዝዳንቷ በአግባቡ የሚይዛቸው የኢትዮጵያ አስተዳደር ቢኖር ከኢትዮጵያ ወጥተው ለአረብ ሃገራት የጦር ሰፈር የመፍቀድ ያህል ርቀት አይሄዱም ነበር።የኢትዮጵያ የአሁኖቹ ባለሥልጣናቶቿ በቀላሉ የሚደለሉ መሆናቸውን ተረድተውታል።

ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ዙርያዋን እይተከበበች ነው።ሕወሓት በትናንሽ የጎሳ እና የመንደር ጉዳዮች ላይ እንጂ የኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ዓለም አቀፋዊም ሆነ አካብቢያዊ ተፅኖ ፈጣሪነት ላይ የመስራት ፍላጎቱም ሆነ ያለው የሰው ኃይል አቅም አይፈቅድለትም።ባለፉት 26 አመታት በስልጣን ላይ የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን አቅም፣የዲፕሎማሲ እውቀት፣ልምድ እና የትምህርት ዝግጅት ገምግማችሁ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ደረጃ ስትመዝኑት በተሰፈረው ልክ እንዳገኘን ትረዱታላችሁ። ችግሩ ከአሁኑ ይልቅ ወደፊት የከፋ ዋጋ እንደሚያስከፍለን ያለመረዳቱ ላይ ነው። ለእዚህ ሁሉ ችግር መፍትሄ ለመስጠት ግን አሁንም አልረፈደም።ሕወሓት የገዛ ሕዝቡን ከመግደል እና ከማሰር ይልቅ ከልብ ለሆነ ሃገራዊ እርቅ እንዲነሳ በመጠኑ ንቃት አለን የምትሉ የጦር ሰራዊቱ እና የቢሮ ክራሲው አካላት በውድም ይሁን በግድ ማስገደድ አለባችሁ። ውስጣዊ ችግሮች በፍጥነት እንዲፈቱ  ለለውጥ እና ሃገራዊ እርቅ አልገዛም የሚል ፅንፈኛ የህወሓት አመራር መታሰር ያለበት ይታሰራል።ለፍርድ መቅረብ ያለበት ይቀርባል።ጉዳዩ የሀገር ጉዳይ ነው።ቆይቶ እንደ ሀገር የሚከፈለው ከቸልተኝነት የተነሳ የሚመጣ ፈተና ሁሉንም ይዞ ወደ ገደል የሚገባ ነው።ከእዚህ በተለየ ግን የሕወሓት በስልጣን መቆየት ኢትዮጵያን የበለጠ ዋጋ እያስከፈላት እንደሆነ መታወቅ አለበት።ከእዚህ ጋር በተያያዘ ከእዚህ በፊት በጉዳያችን ላይ የወጣውን ማስታወሻ ለማንበብ ይህንን ይጫኑ።


ጉዳያችን GUDAYACHN 

 www.gudayachn.com

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።