ዛሬ ነሐሴ 25/2005 ዓም በአዲስ አበባ አራት ኪሎ (ግንፍሌ አካባቢ) የሚገኘው የሰማያዊ ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት የእገታ-ሽብር ተግባር እንደተፈፀመበት ተገለፀ።ፓርቲው ቀደም ብሎ ለነሐሴ 26/2005ዓም ፍፁም ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ ለመንግስት ከሶስት ወር በፊት ማስታወቁ ይታወቃል።ከቀናት በኃላ መንግስት ቀደም ብሎ በሰማያዊ ፓርቲ እንዲያውቀው የተደረገውን ፍፁም ሰላማዊ ሰልፍ ማስታወሻ ወደጎን በማለት ''የሃይማኖት ተቁዋማት የጋራ ጉባኤ'' የጠራው ሰልፍ ቅድሚያ እንደተሰጠው የሚገልፅ መግለጫ ዛሬ ነሐሴ 25/2005 ዓም በቀኑ የኢቲቪ ዜና ላይ አስታወቀ።በእዚሁ ዜና ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር በመጀመርያ የሰማያዊ ፓርቲን ፍፁም ሰላማዊ ሰልፍ መጠየቁን ''እንዳልሰሙ'' ከገለፁ በኃላ ቆይተው የተናገሩትን እረስተውት'' የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግረን ነበር'' ሲሉ ተደምጠዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መግለጫውን በሰጡ በሰአታት ውስጥ ከአንድ መቶ ያላነሱ የፓርቲው አባላት ባሉበት የሰማያዊ ፓርቲ ዋና ቢሮ ግቢውን እና በሩን ጥሰው የገቡ ከባድ መሳርያ የታጠቁ የፈድራል ፖሊስ አባላት የእገታ-ሽብር ፈፀሙ። ድርጊቱን ሽብር የሚያሰኙት ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም በግቢው ውስጥ የነበሩት የፓርቲው አባላት ከትጥቅ ትግል ይልቅ ፍፁም ሰላማዊ ትግል ለሀገራችን ይበጃል ያሉ ከመፈክር እና ብእር ሌላ ምንም መሳርያ የሌላቸው ንፁሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመ የእገታ ተግባር በመሆኑ እና የፈድራል ፖሊስ ግቢውን ለመውረር የፍርድቤት ትእዛዝ አለመያዙ ነው።
የእዚህ አይነቱ የማሸበር ተግባር በመንግሥትነት ደረጃ ባሉ ፖሊሶች መፈፀሙ እጅግ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን ''ተከታታይ ትውልድ ለሰላማዊ ትግል አልታደለምን?'' የሚለውን ጥያቄ ይጭራል። ከ 1997 ዓም ወዲህ መንግስት ስምንት አመታት ሙሉ የሰላማዊ ትግልን የማክበር እና የማስከበር ልምድ ለማዳበር አለመቻሉ በእራሱ የሰላማዊ ትግል አስፈላጊነት እና አላስፈላጊነት ላይ ትልቅ እና ወሳኝ ጥያቄ መጫሩ እንደማይቀር ብዙዎች ይስማማሉ።
ምናልባትም በሰማያዊ ፓርቲ ላይ መንግስት የሚያሳየው ''አክብሮት'' ወይንም ''ንቀት'' የኢትዮጵያን የፖለቲካ የትግል አቅጣጫ ወሳኝ ደረጃ ላይ የሚያደርሰው ለመሆኑ መጠራጠር አይቻልም። ምክንያቱም ይህ ትውልድ ተመሳሳይ የእገታ-ሽብር ከተፈፀመበት ወዳልወደደው ግን ብቸኛው አማራጭ ቢሄድ ለፍርድ የሚቻኮል እንደማይኖር እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ምርጫው አሁንም የወያኔ ባለስልጣናት ነው።ትውልዱን እያሸበሩ መኖር አልያም በቅንነት የትውልዱን ጥያቄ መስማት።
የሰማያዊ ፓርቲ የማህበራዊ መገናኛ ድህረገፅ (ፌስ ቡክ) ላይ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የተለቀቀው መረጃን ከእዚህ በታች ይመልከቱ።
በአዲስ አበባ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ የተለቀቀው የሰማያዊ ፓርቲ የማህበራዊ መገናኛ ድህረገፅ (ፌስ ቡክ) ማስታወቂያ እንዲህ ይነበባል -
''በአሁኑ ሰዓት የሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ በታጠቁ ፌደራል ፖሊሶች ተከቧል
በፓርቲው ጽ/ቤት ውስጥ ወደ 100 የሚጠጉ አባላት የሚገኙ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ወደ 60 የሚሆኔ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ የፌደራል ፖሊስ በግቢው ውስጥ ይገኛል ማንም መውጣትም ሆነ መግባት አይችልም፡፡ ያለውን ሁኔታ እየተከታተልን እንገልጽላችኋለን''
በአዲስ አበባ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ላይ የተለቀቀው የሰማያዊ ፓርቲ የማህበራዊ መገናኛ ድህረገፅ (ፌስ ቡክ) ማስታወቂያ እንዲህ ይነበባል-
''በአሁኑ ወቅት በግምት ወደ 100 የሚጠጉ የፓርቲው አመራሮች የምክርቤት አባላት እንዲሁም ደጋፊዎችና አባላት በተሽከርካሪ ተጭነው ለጊዜው ወዳልታወቀ ቦታ ተወስደዋል፡፡ የድረጅቱን ቀጣይ አቋምና እንቅስቃሴ በሂደት እናሳውቃለን''
1/ የኢሳት ሰበር ዜና
2/ ከሽብሩ በኃላ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ከ ኢትዮጵያ የመወያያ መድረክ ( ECADF) ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ