የትምህርት ሚኒስቴር ህንፃ አዲስ አበባ
የዛሬው ''የትምህርታችን ነገር'' እንዳነሳው ያደረገኝ ግን የዛሬ ነሐሴ 1/2005 ዓም ምሽት በሸገር (አዲስ አበባ) ኤፍ ኤም ራድዮ በተሰማው ዜና ''ኢትዮጵያ ያለፈው አመትን የትምህርት ሂደት ገመገመች'' በሚለው ዜና ስር የ ኤፍ ኤም ጋዜጠኛ ለትምህርት ሚኒስትር ዴታው ያነሳው ጥያቄ መሰረታዊ እና የመንግስትን የፖሊሲ ድክመት የሚያመላክት ብቻ ሳይሆን ለምን? የሚል ጥያቄን ጥያቄዎች ውስጥ-የሚጭር ሆኖ ስላገኘሁት ነው።
በመጀመርያ ወቅቱ ክረምቱ ተገባዶ አዲሱ የትምህርት ዘመን የሚጀመርበት ወር- መስከረም እየመጣ ከመሆኑ አንፃር የሸገር ኤፍ ኤም ራድዮ ዛሬ ከዜና ዘገባዎቹ ውስጥ አንዱ መሆኑ ተገቢ እና ወቅታዊ ነው።
በእዚሁ መሰረት በዜና ዘገባው ላይ ትምህርትን በተመለከተ የትምህርት ሚኒስትር ዴታ የተጠየቁት ግን ለእኔ በአግባቡ አለመመለሳቸው ከተሰሙኝ ጥያቄዎች ውስጥ-
ሀ/ መንግስት (ትምህርት ሚኒስቴር) ኢትዮጵያዊ እና ወጥ የሆነ ስርዓተ ትምህርት በመላ ሀገሪቱ እየተሰጠ እንዳልሆነ እያወቀ ለምን እንዳላየ አለፈው?
ለ/ በአዲሱ የትምህርት ፖሊስ መሰረት አንዳንድ የትምህርት አይነቶች ጭራሹን ተዘግተዋል። ለምሳሌ የፍልስፍና እና የታሪክ ትምህርቶች በዲፓርትመንት ከዩንቨርስቲ መሰጠት ቀርተዋል ለምን? የሚሉ ጥያቄዎች ነበሩ።
አንዲት ሀገር ወጥ የሆነ የትምህርት ፖሊሲ የላትም ማለት ምን ማለት ነው?
ከመጀመርያው ጥያቄ (ሀ) ስንነሳ ኢትዮጵያዊ እና ወጥ የሆነ ስርዓተ-ትምህርት በመላ ሀገሪቱ ያለመሰጠቱ ምክንያት እና መንግስት ለምን ይህንን ለማስተካከል እርምጃ አይወስድም? በሚል ሃሳብ ዙርያ ያጠነጥናል። አንዲት ሀገር ወጥ የሆነ የትምህርት ፖሊሲ የላትም ማለት ምን ማለት ነው? ለእኔ የምረዳው የሚከተሉትን ማለት መሆኑን ነው።እነርሱም-
- በተለያዩ የሀገሪቱ ቦታዎች የሚኖሩ ዜጎች የተለያየ የትምህርት አሰጣጥ አላቸው።ይህ ማለት ስለ አንድ ነገር አሰራር በተለያየ መንገድ እንዲመለከቱ የተለያየ አመለካከት ይዘው እንዲወጡ ይደረጋሉ ማለት ነው።እነኚህ ተማሪዎች ወደ ዩንቨርሲቲ ሲመጡ ከስር ወጥ የሆነ ትምህርት ስላልያዙ በነገሮች ላይ የጋራ እና ወጥ ሃሳብ ብሎም ውሳኔ ላይ መድረስ አያስችላቸውም። ለምሳሌ በፖለቲካ፣በታሪክ፣በሀገራችን የምጣኔ ሀብት መሰረታዊ ችግሮች እና መፍትሄዎች ላይ ወዘተ የጋራ የመነሻ ግንዛቤ ስለማይኖራቸው ከመጡበት ክልል ወይም ትምህርት ቤት አልያም መምህር አስተሳሰብ ተነስተው ለነገሮች ድምዳሜ ለመስጠት ይቸኩላሉ ማለት ነው። ይህም ውሎ አድሮ ወደተሳሳተ ግንዛቤ እና ድምዳሜ ላይ ያደርሳቸዋል።
እዚህ ላይ ወጥ የሆነ እና ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ትምህርት በሀገራችን ያለመሰጠቱ መዘዙ በዩንቨርስቲ ብቻ የሚወሰን እንዳልሆነ መገንዘብ አለብን።
- ከዩንቨርስቲ በኃላ ወደ ስራ አለም የተሰማሩ ነገ የሀገራችን ፖሊሲ አውጪዎች በአንድ ጉዳይ ላይ ለመወሰን ስብሰባ ተቀምጠው የማይስማሙ እና በነገሮች ላይ የጋራ ሃሳብ ማመንጨት ያቃታቸው የካምፓኒ ሥራ አስክያጆች፣ሚኒስትሮች፣መምህራን ወዘተ ይኖሩናል ማለት ነው። ኢትዮጵያዊ እና ወጥ ያልሆነ ትምህርት አለመስጠት ውጤቱ በአጭር አማርኛ ለመግለፅ ሃገርን በጆግራፍያዊ አቀማመጥ እና በብሄር ከመከፋፈል በከፋ መልኩ ትውልድን እንዳይታረቅ አድርጎ የመግደያ 'መርዝ' ነው።
የሸገር ኤፍ ኤም ጋዜጠኛ የጠየቀው ጥያቄ እጅግ ወሳኝ እና አንገብጋቢ ነው።የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ከሚያነሷቸው እጅግ አንገብጋቢ ሃገራዊ ጉዳዮች ውስጥ የእዚህ አይነቶቹን የመንግስት የትምህርት ፖሊስ ጥመቶችን (መንጋደዶችን) በወቅቱ ነቅሰው አውጥተው እንዲስተካከሉ ተፅኖ መፍጠር ይገባቸዋል።ምክንያቱም ችግሩ ጊዜ ከተሰጠው እና ትውልድን ካጣመመ በኃላ ለመመለስ ሌላ አንድ መቶ አመት ላለመጠየቁ ምንም ዋስትና የለም።
ዶ/ር ታዬ ወ/ሰማያት (የቀድሞ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ሊቀመንበር) የተናገሩትን እዚህ ላይ መጥቀስ ተገቢ ነው።''ዛፍ ተጣሞ ቢያድግ ሌላ ዛፍ በመትከል በጥቂት አመታት ታስተካክለው ይሆናል። በተሳሳተ የትምህርት ፖሊስ ምክንያት ትውልድ ተጣሞ ካደገ ግን በምን እና በስንት አመት ታስተካክለዋለህ?'' ነበር ያሉት።
የታሪክ እና የፍልስፍና የትምህርት ክፍሎች(ዲፓርትመንቶች) መዘጋት ጉዳይ
ሁለተኛውን የጋዜጠኛውን ጥያቄ ማለትም ''ለምን የታሪክ እና የፍልስፍና ትምህርት ክፍሎች ከዩንቨርስቲ ተዘጉ?'' ለሚለው ጥያቄ እንደተባለው የትምህርት ክፍሎቹ ከዩንቨርስቲ ውስጥ ከተባረሩ ጉዳዩን በአሳዛኝነት በማለፍ ብቻ ሳይሆን ተያያዥ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ለመሆኑ እማኝ እንደማይፈልግ እርግጠኛ ነኝ። ጥያቄዎቹም -
- ፍልስፍና የሌለው ኅብረተሰ እንዴት ማደግ ይችላል?
- ኢትዮጵያዊ ፍልስፍናዎቻችንን ትውልዱ እንዳይማር እና እንዳይመራመር ማድረግ ብሎም ከዩንቨርስቲ የትምህርት ክፍልነት መሰረዝ እና ተማሪዎች እንዳይማሩ ማድረግ ምን አይነት ሃገራዊ የትምህርት ፖሊሲ ነው?
- ፍልስፍና የሌለው ፖለቲካ፣ፍልስፍና የሌለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ፍልስፍና የሌለው የማህበረሰብ ፖሊሲ ይዘን እስከመቼ እንኖራለን? በምን ያህል እርቀት ሀገራችንን ያስጉዛል?
የታሪክን ትምህርት ክፍል መዘጋትን በተመለከተ ግን ጥያቄዬ አንድ እና አንድ ነው። ባለታሪክ ሀገር ኢትዮጵያ የታሪክ ተመራማሪ እና ተማሪ ከሌላት የትኛዋ ሀገር ናት ሊኖራት የሚገባትና የሚታሰብላት?
አበቃሁ
ጌታቸው
ኦስሎ
No comments:
Post a Comment