ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, August 22, 2013

የፆመ-ፍልሰታ መፈታት ሀዘኔ እና የሀገሬ እድገት ጉዳይ

 

ዛሬ ነሐሴ 16/2005 ዓም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስትያን ተከታዮች ዘንድ ፆመ ፍልሰታ የተፈታበት ቀን ነው።ይህ ፆም በሀገራችን በክረምት ወራት እንደመዋሉ ተማሪ እና መምህራን በእረፍት ላይ ያሉበት፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው በቤተክርስቲያን የሚገኙበት ባጠቃላይ እጅግ ብዛት ያለው ምዕመን በተለይ ታዳጊ ወጣቶች እና ወጣቶችም የሚታደሙበት ነው።የፆሙ መፈታት አንዱ መታወቅያው ታድያ በቤተክርስቲያን አለምላሚ ተበለው ከሚጠሩት ምግቦች እንደ ስጋ፣እንቁላል፣ወተት የመሳሰሉት ምግቦችን ለመመገብ መቻሉ ነው።

ለመሆኑ ስንቶቻችን ምን ያህል ሕዝብ ፆሙ ሲፈታ ከላይ በተጠቀሱት ምግቦች ፆሙን በአግባቡ የመፍታት አቅም አለው? ብለን በስሌት አስበነው እናውቃለን? ሀገሪቱ እያደገች ነው በተባለበት በእዚህ ዘመን የድህነት ደረጃው ምን ላይ እንደሆነ እንቅውቀዋለን? ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ብዙ ''አንጀት የሚበሉ'' ነገሮችን በፆም ፍቺ ወቅት መመልከት የተለመደ እየሆነ መጥቷል።ሲፆም ከከረመው ክርስቲያን ስንቱ አንድ ኪሎ ስጋ የመግዛት አቅም አለው?'' ብሎ መጠየቅ ተገቢ እና ሰብአዊ ጥያቄ ነው።

አስተዋዩ መምህር እና ታዳጊ ህፃናቱ 


ከጥቂት አመታት በፊት  በአንድ በሀገራችን በሚታተም ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ፅሁፍ እጅግ አስተማሪ እንደነበር አስታውሳለሁ።ጋዜጣው በአዲስ አበባ የሚገኝ አንድ የቱጃሮች እና የባለስልጣናት ልጆች የሚማሩበት ትምህርት ቤት የ አምስተኛ ክፍል ተማሪዎች በመምህራቸው አነሳሽነት ከእነርሱ የኑሮ ደረጃ በታች ስላሉት ሕፃናት እንዲማሩ በአዲስ አበባ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚኖሩ የምስኪኖችን መንደር እንዲጎበኙ አደረገ።ከጉብኝቱ በኃላ ታድያ ተማሪዎቹ  ለመምህራቸው የተመለከቱትን እንዲፅፉ በተነገራቸው መሰረት በእንግሊዝኛ ፃፉ።እነኚሁ እድሚያቸው ከአስራ ሁለት የማይዘለው ተማሪዎች ያሉትን  ለእዚሁ ጋዜጣ ከመግቢያ ፅሁፍ ጋር ላከው።በተለይ የታዳጊ ሕፃናቱ ፅሁፍ ቀጥታ ፎቶ ተደርጎ የቀረበ ነበር እና አሳዛኝ ነበር።መምህሩ በመግቢያው ላይ ተማሪዎቹ ከጉብኝቱ ከተመለሱ በኃላ እጅግ የመንፈስ መረበሽ መመልከቱን እና በሕይወታቸው አይተውት የማያውቁት መሆኑን እንደነገሩት ከእዚህ በኃላ የተቸገሩትን ለመርዳት አባት እና እናታቸውን ይዘው መምጣት እንደሚፈልጉ እንደገለፁለት ያትታል።

ታዳጊ ሕፃናቱ ከፃፉት ውስጥ ቃል በቃል ባይሆንም የሚከተሉት አረፍተ ነገሮችን አስታውሳለሁ።

የመጀመርያዋ ታዳጊ ሕፃን- 

'' እኔ ያሳዘነኝ የሕፃን ትግስት(ስሙ ለምሳሌ የተሰጠ ነው) አኗኗር ነው። እናቷ ጠላ በመሸጥ ትተዳደራለች።ከርሷ ጋር አንድ አልጋ በተዘረጋባት ክፍል ውስጥ አምስት ሆነው ይኖራሉ።አልጋው  ቀን ቀን  ልጆቹ  እንደወንበር የሚቀመጡበት እና ማታ የቤት ስራ የሚሰሩበት ነው።አልጋው በመጋረጃ በመጋረዱ ከመጋረጃ ውጭ ያሉ ጠላ ሊጠጡ ለሚመጡ ሰዎች አይታዩም።ጠላ የሚጠጡት ሰዎች ይጮሃሉ።እናም ትግስት ከቤት ወጥታ በመንገድ መብራት ድንጋይ ላይ ቁጭ ብላ የቤት ስራዋን እንደምትሰራ ነገረችኝ።እማዬን ኪችን ያለው ወንበር ለትግስት እንድትሰጣት ነግርያታለሁ።ትግስትን እንደምደውልላት ነግርያታለሁ።የጎረበታቸውን ስልክ ወስጃለሁ።''

ሁለተኛዋ ታዳጊ ሕፃን-

''  ኃይሉ እና ወንድሞቹ ቤታቸው ትንሽዬ ነች።ምሳ የት እንደሚበሉ ኃይሉን ጠየቅሁት።እዝያው እቆምኩበት በሩ ላይ ነው ለካ። ምሳ የሚበሉት በቤታቸው በር ላይ የሚሄደው የሽንት ቤት ፍሳሽ እየሸተታቸው ነው።ይህንን ሳይ አለቀስኩ።''

ሦስተኛዋ ታዳጊ ሕፃን-
 
'' እማዬ ለእኔ ኮካ እና ኬክ የምትገዛልኝ ብር ሰላም በወር አይታው አታውቅም። ከአሁን በኃላ እማዬ ኬክ እንዳትገዛ ከገዛችም ለሰላም መጀመርያ እንድትገዛላት ነግርያታለሁ።''
ከእዚህ በላይ የተፃፉት የታዳጊ ህፃናቱ አስተያየት ቃል በቃል ለማስታወስ ባለመቻሌ እንጂ ከእዚህ በላይ በጣም በሚያሳዝኑ ቃላት የተሞሉ መሆናቸውን ግን አስታውሳለሁ።

 የምስክኑን ሕዝብ ችግር ለመረዳት ቁልቁለቱን መውረድ ይሻል


የሶስተኛው አለም የሀገራችንም ትልቁ ችግር የመረጃ ክፍተት መኖር ነው።አዲስ አበባ ውስጥ ያለውን የድህነት መጠን የህዝቡን ከኑሮ ጋር የሚያደርገውን ግብግብ የሚያውቀው ህዝቡ ብቻ ነው።ሌላው ፖሊሲ አውጭው፣የከተማው ከንቲባ፣የክፍለ ከተማ ሊቀመንበሩ፣ወዘተ ድህነትን ሊሰሙት ይችላሉ። ያለበትን ደረጃ(የድህነቱን ዲግሪ) ግን ለማወቅ እንደ እነኚህ ሕፃናት ወደተቸገሩት መንደር በአካል መግባት፣ማውራት፣መጠየቅን ይሻል።የመንግስት ባለስልጣናትም ሆኑ ቱጃር ነጋዴ ድህነትን የሚያውቀው በስም ነው።የከተማውንም ሆነ የገጠሩን የአመት የስራ ፕሮግራም የሚያወጣው ግን እርሱ ነው።አዋጁን የሚያፀድቀው ግን አሁንም እርሱ ነው። የሀገሪቱ ገንዘብ እና በጀት ቅድምያ ውስኪ ማስመጣት ላይ ይሁን ወይንስ ታላላቅ ፎቆችን በአየር መንገድ አካባቢ መገንባት ይሁን? ብሎ የሚወስነው ግን ስለድህነት ምንም መረጃ የሌለው ባለሥልጣኑ ነው።''ኢትዮጵያ አድጋለች ተመንድጋለች ምክንያቱም ከቤቴ ስመጣ በቀለበት መንገድ ላይ ነው የመጣሁት'' መሰል ንግግር የሚያደርገው ግን የሀገሪቱ ሕዝብ የመግዛት አቅሙ ወርዶ ፆም ለመፍታት አንድ ኪሎ ስጋ ሕልም እንደሆነበት የማያውቀው ምናልባት እርሱ በቤቱ በአንድ ሺህ አምስመቶ ብር(የወቅቱ የበግ ዋጋ ነው) በግ ገዝቶ አስሮ ከልጆቹ ጋር እየሳቀ እየበላ ያለው ነው።

ዛሬ ፆመ ፍልሰታ ሲፈታ ሌሊቱን  በሰዓታት፣ቀን በቅዳሴ አምላካቸውን ሲማፀኑ የነበሩት በሚልዮን ከሚቆጠሩ በተለይ ከከተማ ነዋሪዎች (የገጠር ነዋሪ በእንፃሩ ከሚያረባው ዶሮም ሆነ እንቁላል ይፈስጋል ብዬ በማሰብ) ስንቱ አንድ ኪሎ ስጋን ከ125 ብር በላይ ከፍሎ ይገዛል? ልጆች ያሉት መካከለኛ ገቢ የሚባለው (የመካከለኛ ገቢ የሚባል የህብረተሰብ ክፍል በኢትዮጵያ እየጠፋ መሆኑን ሳንዘነጋ) ስንት ኪሎ ስጋ ለስንት ልጆቹ ያዳርሳል?

በቀድሞ መንግስት ዘመን አንድ በግ በሃምሳ እና ስልሳ ብር ይገዛ የነበረበት ጊዜ ዋጋው በአስራዎቹ ውስጥ በመጨመሩ መንግስት ለመንግስት ሰራተኞች በየመስርያ ቤታቸው ለነዋሪው በማከፋፈያ ቦታዎች ከምስራቃዊው የሀገራችን ክፍል ''ዋንኬ'' የተሰኙ (አንገታቸው ጥቁር ሌላው አካላቸው ሙሉ ነጭ) በጎች በቅናሽ ሲከፋፈሉ እንደነበር በትምህርት ቤት ሕይወቴ አስታውሳለሁ።መንግስት እንደ አባት ማሰብ ህዝብ ለሚገጥመው ችግር አብሮ መፍትሄ ማፈላለግ ነበር ባህሪው ሊሆን የሚገባው።ሕዝብ ግራ ገብቶት ሲንከራተት ''የእኔ ቤት ከሞላ'' አለም ሁሉ ጠግቧል ማለት ግን ጤናማ አስተሳሰብ አይደለም።በሀገራችን የከብት እርባታም ሆነ የወተት ውጤቶች የሀገር ውስጥ ምርቶች ናቸው።ችግሩ የሚስተዋለው ስርጭት ላይ ነው።ምክንያቱም ከከተሞች በራቁ አካባቢዎች አሁንም ምርቱ በተነፃፃሪ የተሻለ ዋጋ ላይ መገኘቱ ነው።

 አናዳጁ ነገር  ማኪያቶ መዘግየቱ 

እድገት የቁሳቁስ ምርት መጨመር ወይንም የመሰረተ ልማት መስፋፋት ብቻ እንዳልሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች አበክረው ያሳስባሉ።አድገት ሰው ላይ የሚሰራ ልማት ነው።ሰው ማለት ደግሞ በትንሹ የመኖር ዋስትና አለው የሚባለው መሰረታዊ ነገሮች ማለትም ምግብ፣መጠለያ እና ልብስ ሲሟሉለት ነው።እድገት ግን ከእነዚህ በላይ ፀጥታ፣የትምህርት ዕድል፣ገበያ ለማግኘት ያለው ዕድል፣ሕክምና ለማግኘት ያለው ዕድል ወዘተን ይለካል። የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራምም ሀገሮችን ለመኖርያ ምቹ የሆኑ እና ያልሆኑ ብሎ የሚለይበት መስፈርትም እነኚሁ ናቸው።ጥያቄው ግን የፖሊሲ አውጭው እና በጀት መዳቢው ባለስልጣን  የህዝቡን የድህነት መጠን ከላይ እንደተጠቀሱት  ህፃናት ተዘዋውረው ካልተመለከቱት እንዴት ከቢሮ ሆነው ለማወቅ ይችላሉ? ነው።ቢሮ ውስጥ ሁሉ ሰላም ነው።ኢትዮጵያም አድጋለች፣ሕዝቡም ተመችቶታል፣ምን ቀረ ከቢሮ ለተቀመጠ ባለስልጣን ቢያንስ የሚያናድደው ነገር አይጠፋም የህዝቡ ድህነት የኑሮ ውድነቱ አይደለም፣በእዚህ ወር የኢትዮጵያ ስታትስክስ ቢሮ ያወጣው የዋጋ ንረቱ በ 8% መጨመሩም አይደለም። በስልክ የታዘዘው ማኪያቶ መዘግየቱ ነው።ልብ ይስጠን።

አበቃሁ 

ጌታቸው በቀለ 
ኦስሎ  

1 comment:

Anonymous said...

waw!!! waw!!! nice article.