ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, August 15, 2013

በኢትዮጵያ የሚድያ ታሪክ በአይነቱ ልዩ ሃገራዊ ውይይት





አቶ ሕሊና ዳኛቸው ከኢሳት አስተዳደር ለኢሳት ራድዮ  ዛሬ ነሐሴ 9/2005 ዓም እንደገለፁት ኢሳት በሰሜን አሜሪካ ቨርጂንያ፣ አርልንግተን ሸራተን ሆቴል  በአይነቱ ልዩ የሆነ የመወያያ መድረክ በመጪው ዕሁድ ነሐሴ 12/2005 ዓም ማዘጋጀቱን ገልፀዋል።

በዝጅቱ ላይ ጥሪ የተደረገላችው የፖለቲካ ድርጅቶች፣የሲቪል ማህበራት፣የሃይማኖት መሪዎች፣ታዋቂ ግለሰቦች፣የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች ከውጭ እና ከሀገርውስጥ ይሳተፉበታል። እንደ አቶ ሕሊና ዳኛቸው ገለፃ ይህ መድረክ የኢትዮጵያን የፖለቲካ አቅጣጫ ለማመላከት እና መፍትሄ ለማስቀመጥ አይነተኛ ድርሻ ይኖረዋል።
 የሕዝባዊ ስብሰባው አላማ አሁን ያስፈለገበት ዋና ምክንያትን አቶ ሕሊና ሲያብራሩ ኢትዮጵያ አስጊ ደረጃ ላይ በመሆኗ መሆኑን ገልፀዋል።

'' ኢሳት የፖለቲካ ድርጅቶችን ሚና አልወሰደም ወይ? '' ለሚለው ጥያቄ ደግሞ አቶ ሕሊና ሲያብራሩ ''ኢሳት አቅዋም አይወስድም ፕላትፎርም የመፍጠር ሥራ ነው የሚያደርገው።መድረኩን መፍጠር  ብቻ ነው እንጂ የሚመሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው----ኢሳት እንደሚድያ የጠራው የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ብቻ አይደለም መንግሥትንም ነው'' ብለዋል።

የእዚህ አይነቱ በኢትዮጵያ የሚድያ ታሪክ የመጀመርያ የሆነውን ስብሰባ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መንግስትም ጨምሮ በጎ ምላሽ ሰጥቶ መነጋገር የሚገባው ይመስለኛል።ኢትዮጵያ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ፣የአንድ ብሔር ወይንም ግለሰብ ንብረት አይደለችም የሁላችንም የጋራችን ነች።ያለፈ የአምባገነንነት ዘፈን ጊዜው ተቃጥሏል።አሁን ሁሉም ያለው አማራጭ አንድ ነው።ይሄውም ከፖለቲካ ታክቲክነት በዘለለ መልክ ወደ ግልፅ ውይይት እና መፍትሄ መምጣት።እኔ  ይህ ስብሰባ ውጤታማ እንደሚሆን የሚያሳምኑኝ  ሶስት  ምክንያቶች አሉ።እነርሱም-

1/ አዲሱ የኢትዮጵያ ትውልድ ኃላፊነት የሚወስድበት ነውና 


ባለፉት አርባ አመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች የቀደሙ ስኬታቸውን እና ድክመቶችን የሚለኩበት ዛሬ እድሜ ቢጫናቸው በጎውን ልምዳቸውን በማካፈል ያለፈ ስህተታቸውን በመንቀስ እራሳቸውን የሚመለከቱበት  አይነተኛ መድረክም ነው። ኢትዮጵያ የትውልድ ሽግግር ላይ መሆኗን ከ አዲሱ የኢትዮጵያ ሚሊንየም ወዲህ የተነሱትን በወጣቶች የተገነቡ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶችን ማየት ይቻላል።ኢሳት በራሱ የእዚህ ማሳያ ነው። ይህ ማለት አዳዲስ አስተሳሰቦች ገዢ ሆነው የመውጣታቸው ዕድል ትልቅ ነው ማለት ነው።

2/ የኢሳት ሚዛናዊ ሚድያነት የተገለፀበት ስለሆነ   


መንግስት በስብሰባው ላይ ተጋብዟል።ይህ ትልቅ እመርታ ነው።ኢሳት ሚዛናዊ የሚድያ ተቁአምነቱን አስመሰከረ ማለት ነው።ኢሳትን መንግስት በመግለጫው አያመስግን እንጂ ለኢሳት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ሃሳባቸውን ገልፀዋል።አቦይ ስብሐት፣የመንግስት መስርያ ቤት የመምርያ ኃላፊዎች፣የፖሊስ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣የጦርሃይሉ ከፍተኛ መኮንኖች፣የሃይማኖት አባቶች እነኚህ ሁሉ ከሀገር ቤት ለኢሳት ግልፅ የሆነ ሃሳባቸውን እና የመስርያቤታቸውን ሥራ ገልፀዋል።ይህ ኢሳትን ታላቅ ከበሬታ ያጎናፅፈዋል።ከበሬታው ሚዛናዊ የሆነ ሚድያ ለወደፊቷ ኢትዮጵያም ወሳኝ በሆነ መልክ መሰረት የሚጥል ነው። የኢሳት ተሳትፎም የተራራቁትን አቀራርቦ በሀገራቸው ጉዳይ እንዲወያዩ ውይይቱን የማመቻቸት ሥራ ብቻ ነውና ከእዚህ በፊት ከሚጠሩት ሃገራዊ ስብሰባዎች በአይነቱ የተለየ እና ሚዛናዊነቱን ያጎላዋል።

3/ ወቅቱ የእዚህ አይነቱን ጥሪ ብቻ የሚናፍቅ መሆኑ 


በመጪው እሁድ የሚደረገው ስብሰባ ብዙ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ወዳጆችም ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሄ ብቸኛው መንገድ ፊት ለፊት ተቀምጦ መወያየት ብቻ መሆኑን ብዙዎቹ የፖለቲካ ፕሮግራማቸው ልዩነት የጎላ አለመሆኑ ግን አለመነጋገር የፈጠረው ችግር መሆኑን የሚያምኑበት ጊዜ ነው- ይህ ጊዜ።የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች ከመቸውም ጊዜ በላይ የናሩበት፣መንግስት እራሱን ለመቆጣጠር ከሙስና እስከ ተለዋዋጭ መመርያዎች ግራ የተጋባበት፣ባለስልጣናቱ ነገን እየፈሩ ያሉበት ጊዜ ነው ይህ ጊዜ።ወጣቱ የሀገሩን  ችግር ከበቂ በላይ የተረዳበት፣ሀገሩንም ከገባችበት አዘቅት ለማውጣት ብቸኛ መፍትሄ እሱ እና እሱ
ብቻ መሆኑን የተረዳበት ጊዜ ነው-ይህ ጊዜ። በመሆኑም የስብሰባው የጥሪ ወቅት እራሱ በትክክለኛ ጊዜ ላይ ነው እና ስኬታማነቱ የጎላ ነው።

በመጨረሻ የእዚህ አይነቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደ ሕዝብ አደባባይ አውጥቶ ሃሳባቸውን መስማት እጅግ ጠቃሚ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።ይሄውም የበረቱትን ወደ አንድ ሳጥን ገብተው በሕብረት  ሕዝብ እንዲመሩ ለማበርታት እና  ያልበረቱት ደግሞ ከፖለቲካው አለም እረፍት እንዲወስዱ ለመለየት።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክልን

ጌታቸው

ኦስሎ

No comments:

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሃራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሐራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)