ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, August 10, 2013

በኢትዮጵያ በእስልምና ስም የሚንቀሳቀስ የፅንፈኛ እንቅስቃሴ የለም?

በቂ የመወያያ መድረክ የሌለው እና የዲሞክራሲ መብቱ የታፈነ ሕዝብ በከፍተኛ የመረጃ እጥረት የመሰቃየቱ አንዱ አመላካች መንገድ እጅግ የበዙ አስተያየቶችን እንደትክክለኛ የመረጃ ምንጭ አድርጎ የመውሰድ ክፉ አባዜ ተጠቂ መሆን ነው። በተለይ  መረጃዎችን ከየት፣ለምን እና ለማን ተብሎ ተሰጠ? ከሚሉ መጠይቆች ተነስቶ ለመተንተን አቅም እንዲያዳብር የባለሙያ ትንተናዎችን በመገናኛ ብዙሃኑ ማግኘት ያልቻለ ሕዝብ በትናንሽ እና ቁርጥራጭ መረጃዎች ወደ አልተፈለገ ድምዳሜ የመድረስ አደጋው ቀላል አይደለም።

ሰሞኑን በሀገራችን የተከሰተው(ድንገተኛ ስላልሆነ ተከሰተ ማለት ባያስደፍርም) በሙስሊሙ ሕብረተሰብ ጋር ተያይዞ ከመንግስት ፌድራል  ፖሊስ ጋር የነበረው ግጭት ብዙዎች እንደመሰላቸው እና ካላቸው ፖለቲካውም ሆነ ሃይማኖታዊ አመለካከት አንፃር ሲተረጉሙት ይታያል።''ግርግር ለሌባ ይመቻል'' እንዲሉ የአንዳንድ ወገኖች ጉዳዩን አስመልክተው የሚያተኩሩበት የትኩረት አቅጣጫ በራሱ አንዳንድ እውነታዎችን እንዳይሸፍናቸው ስጋት አለኝ።

በእኔ አመለካከት የእዚህ አይነቱ ከሀገር ውስጥ የፖለቲካ አሰላለፍ፣ኢትዮጵያ ካለችበት ጅኦ-ፖለቲካዊ (አካባቢያዊ) አቀማመጥ እና ከሀገራችን መፃኢ ዕድል ጋር የራሱ ተፅኖ ያለው ጉዳይ ለጊዚያዊ ፖለቲካዊ ጥላ ተብሎ የነበሩ እውነታዎችን ማለፍ ተገቢ አይደለም።በመሆኑም የሚከተሉት እውነታዎች ከግንዛቤ መግባት ያለባቸው መሆናቸውን መረሳት ያለባቸው አይመስለኝም።

1/  አክራሪ እና ፅንፈኛ የእስልምና እንቅስቃሴ በሀገራችን አለ።


ከአክራሪ እና ፅንፈኛ የእስልምና እንቅስቃሴ እንደማንኛውም የዓለም ክፍሎች ሀገራችንም ነፃ አይደለችም። የሀገራችንን ለየት የሚያደርገው አለምአቀፉ ፅንፈኛ የእስልምና እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ካላት ጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ አንፃር በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ሕይወት ውስጥ ለመንሰራፋት በአዲስ መልክ ካለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን ጀመሮ ሲሰራ የነበረ ለመሆኑ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል።ይህንንም አሁን ያለውም መንግስት ሆነ  የቀደሙት ሁለት መንግሥታት የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴም ሆነ የደርግ መንግስት ጠንቅቀው የሚያውቁት ነው።

2/ ፅንፈኛው የእስልምና እንቅስቃሴ ላለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን በሀገራችን ፖለቲካዊ ክስተቶች ላይ እጁ ነበሩበት።


በኢትዮጵያ መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር ብዙ ልዩ ፍላጎት ያላቸው (interested groups) ኃይሎች የተፅኖ እጃቸውን ለማርዘም የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ለእዚህም ነው አንዳንድ የመንግስታቶቻችን እርምጃዎች በሰው አይምሮ የማይታሰቡ እራሳቸው መንግሥታቱ ካለፉ በኃላም የሚገርሙ እና የሚያስደነግጡ የሚሆኑባቸው።ይሄው በወቅቱ በአግባቡ ማየት ያልቻሏቸው 'የልዩ ፍላጎት ኃይሎች' ተፅኖን ማየት የሚችሉት ከጊዜ በኃላ በመሆኑ ነው።አክራሪ እና ፅንፈኛ የእስልምና እንቅስቃሴ መኖሩን ከሁሉ በላይ የእስልምና እምነት ተከታይ ወንድሞች እና እህቶች ሂደቱን በቅርብ በእምነት ቦታዎቻቸው ያሉትን ዘገምተኛ የሂደት ለውጦች ስለሚረዱት  ቢገልፁት በጣም ያማረ ነበር። ሆኖም ግን  አሁን ላለንበት አንዳንድ የሀገራችን ሁኔታ የፅንፈኛው አክራሪ እንቅስቃሴ (በአንዳንድ የውጭ መንግሥታትም ታግዞ) ነፀብራቅ አይደለም ለማለት አያስደፍርም።

3/ ፅንፈኛው እንቅስቃሴ እንደ አለፉት ሃያ አመታት የተመቸ ጊዜ አግኝቶ አያውቅም 


ከላይ በተራ ቁጥር ሁለት ላይ እንደተገለፀው የፅንፈኛው አስተሳሰብ አራማጅ አንዳንድ የአረብ መንግሥታት በዲፕሎማሲያዊ  እና በገንዘብ ተፅኖ ያለፉትን መንግሥታትም ሆነ የአሁኑን ኢህአዲግ ላይ ተፅኖ በመፍጠር ወደ ዋናው ግብ የሚያደርሳቸውን አንዳንድ የጥርጊያ ጎዳናዎች ለመጥረግ አልቻሉም ማለት አይቻልም። በብዙዎች ዘንድ እንደሚታመነውም በሱዳን ቱጃር የግል አይሮፕላን ወደ ሀገር ውስጥ የገቡት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ የሚመሩት ኢህአዲግ ከፅንፈኛ እና አክራሪነት ጋር በተያያዘ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ሁሉ ''የአፈጀ አመለካከት፣የድሮ ስርዓት ናፋቂዎች፣የደርግ ርዝራዥ አስተሳሰብ'' እያሉ ያጥላሏቸው ነበር። በተለይ   በጅማ፣በአጋሮ(በሻሻ)፣በኢሊባቦር፣በባሌ እና በአሩሲ አብያተ ክርስቲያናትን ሲያቃጥሉ እና የነበሩ ኢትዮጵያዊ የሙስሊም እምነት አባቶችን መስጊድ እንዳይመጡ ሲከለክሉ ሁሉ መንግስት ተገቢውን እና የማያዳግም እርምጃ በፍጥነት ሲወስድ አልታየም። በተለይ በአንዳንድ ዞኖች የድርጊቱ ፈፃሚዎች የኢህአዲግ አጋር ድርጅቶች  አመራር መሆናቸው ጉዳዩ የበለጠ እንዲደፋፈን እና የፅንፈኛ አስተሳሰቦች ስር እንዲሰዱ ጊዜ ሰጥቷል።

4/የእስልምና አክራሪ እና ፅንፈኛ ኃይሎች የስትራቴጂ(የስልት) ለውጥ 


ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው  የሀገራችን የመናገር ነፃነት መገደብ እና መረጃዎች ለፕሮፓጋንዳ ሥራ ብቻ በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን የመለቀቃቸው ፋይዳ  እና ሕዝቡም እምነቱን በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ላይ ስሌለው፣ ስለአክራሪ እና ፅንፈኛው እንቅስቃሴ ትክክለኛ መረጃ በእነኚህ የመገናኛ ብዙሃን ቢሰጠውም በአግባቡ አይረዳውም።ይህ ደግሞ የእረኛውን ታሪክ የሚያስታውስ ነው።እረኛው ቤተሰቡን ለማስደገጥ  የውሸቱን ''ቀበሮ መጣብኝ!'' እያለ ይጮህ ነበር። ቤተሰቡ አንድ ሁለት ጊዜ የእውነት መስሎት ደንግጦ ወጣ ውሸቱን መሆኑን አወቀ።በሶስተኛው እረኛው የእውነት ቀበሮ መጣበት ቤተሰቡ ግን ''ልማዱ ነው ተዉት'' ብሎ ቁጭ አለ።ቀብሮው ደርሶ በጎቹን በላ። የኢቴቪ   ሂደትም የእረኛው ይመስላል። ሕዝብ ስለምን እንደፃፉ የሚያውቃቸውን ጋዜጠኞች ሁሉ ''አሸባሪ'' እያለ ሲፈርጅ ከርሞ የእውነተኛው አሸባሪ የመጣ ጊዜ እንደ እረኛው ቤተሰቦች ''ልማዱ ነው'' እንደሚባል ልብ ያለው አይመስልም።

አሁን ባለንበት ዘመን ፅንፈኛ የእስልምና ኃይሎች የስልት ለውጥ እያደረጉ መሆኑን ከአለምአቀፍ ሁኔታዎች መረዳት ይቻላል።እዚህ ላይ በእዚህ ፅሁፍ ''በፅንፈኝነት'' ለመመደብ ማስረጃ ባይኖርም በአንድወቅት ግን በእዚሁ ዘርፍ ተመድበው የነበሩት የ''ህዝቦላህ'' እና የግብፁ ''እስላማዊ ወንድማማቾች ህብረት'' ከአስር አመታት በፊት  ያደርጉት የነበረው የፅንፍ ተግባር በለዘበ እና በለሰለሰ አሰራር መቀየራቸውን ለማየት እንችላለን።ለምሳሌ ''ህዝቦላህ'' በሊባኖስ የድነብር ከተሞች ላይ መሰረቱን ከጣለ ወዲህ ለሊባኖስ ሕዝብ ብዙ ትምህርት ቤቶችን፣የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ውዘተ በመክፈት ከሕዝቡ ልብ ውስጥ ከመግባት አልፎ በሊባኖስ መንግስት ላይ ተፅኖ ፈጣሪ ከመሆን እና ምክርቤት ድረስ ደጋፊዎቹን የማስመረጥ ደረጃ ደርሷል።ይህም በኃይል ህዝብን ከማስገደድ በልማት ስራዎች አላማን ማሳካት እንደሚቻል ለማሳየት ያደረገው ስኬታማ ሙከራ ነው።

በሌላ በኩል የግብፁ ''እስላማዊ ውንድማማቾች ህብረት'' በግብፅ የሚታወቀው በነውፀኛ ተግባሩ እና እንዲያውም በአዲስ አበባ የእራሱን ሀገር ፕሬዝዳንት ሙባረክን ለመግደል ሙከራ በማድረግ ነው።ከጊዜ በኃላ ግን ይህ ፅንፈኛ ስልት ተቀይሮ እራሱን ዲሞክራስያዊ ፓርቲ አድርጎ ቀረበ።በግብፅ አብዮት ውስጥ አይነተኛ ተሳታፊ የነበረው ይህ ቡድን ከሙባረክ መውደቅ በኃላ ብቸኛ የተደራጀ ኃይል በመሆኑ እና በፈጠረው ተፅኖ ፕሬዝዳንት ሞሪስን ለፕሬዝዳንትነት አብቅቶ ነበር። ይህንን ቡድን ግን ከታሪኩ የምንረዳው  በፅንፈኛ እርምጃው ሲሆን ከጊዜ በኃላ ግን እጅግ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሆኖ ቀርቧል።የግብፅ ሕዝብ ግን አሁንም የጦር ሰራዊቱን ይዞ ከስልጣን አውርዶ ፕሬዝዳንት ሞሪስን በቁም እስረኝነት አስሯል።

5/ ለማጠቃለል 


ባጠቃላይ የአክራሪነት እንቅስቃሴን የእስልምና ተከታይ ኢትዮጵያውያንን እና የመንግስት የመፍትሄ አሰጣጥ ሁኔታዎችን በተመለከተ የሚከተሉት ሁኔታዎች ከግንዛቤ ማስገባት እና መረጃዎቹን ለሕዝብ በአግባቡ ማድረስ ይመለከተኛል የሚል ዜጋ ሁሉ ኃላፊነት ይመስለኛል።ይሄውም

  •  አክራሪ እና ፅንፈኛ የእስልምና እንቅስቃሴ ባለፉት መንግሥታትም ወቅት የነበረ ነገር ግን እንደ ኢህአዲግ ዘመን አመቺ ጊዜ ያላገኘ መሆኑ፣
  • መንግስት የእስልምና ተከታይ ወገኖች ያነሱትን ጥያቄ እና ሰላማዊ የመጠየቅ ሂደትን በተሻለ የመፍትሄ አሰጣጥ መንገድ አለመጠቀሙ ችግሩን የማባባስ ሚና መጫወቱ ይህም ብዙ ንፁሃን የእምነቱን ተከታዮች ወደ አላስፈላጊ አስተሳሰብ ውስጥ የሚከት መሆኑ እና


  • ጥያቄው እራሱ የስልት ለውጥ ባደረገው ፅንፈኛ እንቅስቃሴ የሙስሊሞችን ጥያቄ የመምራት ሚና እንዳይኖረው የሚያሰጉ ምልክቶች መኖራቸውን መገንዘብ የሚሉት ይጠቀሳሉ።


አበቃሁ
ጌታቸው
ኦስሎ

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...