በኖርዌይ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ (ኢትዮጵያ ኮሚኒቲ) ''የኢትዮጵያ ቀን'' የተሰኘ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች እና የቡና ማፍላት ስነ-ስርአት ያካተተ መርሃ ግብር ዛሬ ሐምሌ 27፣2005 ዓም በኦስሎ ከተማ ''ግሩን ላንድ'' መናፈሻ አካሂዶ ነበር።በቅድምያ ዝግጅቱን ለማዘጋጀት ለተነሳሱት እና ለዝግጅቱ ደፋ ቀና ያሉትን ሁሉ ማመስገን ተገቢ ይመስለኛል።በመሆኑም በጎ ተግባራትን ማበርታት እና ማጎልበት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ኃላፊነት መስሎ ስለተሰማኝ ይህችን አጭር ማስታወሻ ለመፃፍ ወደድኩ።
ሀ/ የመርሃብሩ ጥቅም
የእዚህ አይነቱ መርሃግብር ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍ ያለ ነው። ከጠቀሜታዎቹ ውስጥ ጥቂቶቹ -
1/ የኢትዮጵያውያንን ተሰሚነት በሚኖሩበት ሀገር ውስጥ በሚደረጉት ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ክንውኖች ውስጥ የጎላ ሚና እንዲኖረው ያደርጋል። ይሄውም በምንኖርበት ሀገር ማኅበረሰብ ውስጥ ውሎ አድሮ የተሰሚነት እና የተፅኖ ፈጣሪነት ሚናችንን ከፍ ማድረጉ አይቀርም፣
2/ የኢትዮጵያን ባህል ማለትም አመጋገብ፣አለባበስ፣ወዘተ በውጭው ማኅበረሰብ ዘንድ ያስተዋውቃል። ይህም የሀገራችንን ሌላውን በጎ ጎን ማለትም በባህላችን፣በታሪካችን እና በማንነታችን ዙርያ የሀገራችንን በጎ ገፅታ ለምንኖርበት ሀገር ለማሳየት ይረዳል።
3/ በውጭ ለተወለዱ ኢትዮጵያውያን ስለሀገራቸው የበለጠ እንዲያውቁ እና ፍቅር እንዲያድርባቸው ያደርጋል።
ለ/ በመጪው አመት ዝግጅቱን ይበልጥ ለማሳመር ምን ቢደረግ ጥሩ ነው?
''የኢትዮጵያ ቀን'' ዝግጅት ይበል የሚያሰኝ እና ለወደፊቱም ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአግባቡ ሊሳተፉበት እና የእኔነት ስሜትን ልያጎለብቱበት የሚገባ መሆን ይኖርበታል።ለእዚህም እንዲረዳ በመጪው አመት እነኚህ ተግባራት ቢከወኑ ዝግጅቱን የበለጠ ያስውበዋል እነርሱም-
1/ ''የኢትዮጵያ ቀን'' መርሃግብር የማስታወቅያ ሥራ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲሰራ ማበረታታ፣
2/ ከኦስሎ ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ቀኑን አስበው ቀድመው ኦስሎ እንዲመጡ ማድረግ እና የማረፍያ ቦታዎችን የኦስሎ ነዋሪዎች እንዲያግዙ ማነሳሳት፣
3/ በመላዋ ኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የንግድ ድርጅቶች የሚተዋወቁበት እና ስፖንሰር የሚያደርጉበት ሁኔታ ማመቻቸት፣
4/ በወጣቶች የሚዘጋጁ የተውኔት (ድራማ) መርሃግብሮችን በበዓሉ ወቅት ማቅረብ፣
5/ በዓመቱ ውስጥ በኖርዌይ ውስጥ ልዩ ልዩ ተግባራት የሰሩ ለምሳሌ በትምህርታቸው ላቅ ያለ ውጤት ያመጡ፣የኖርዌይ መገናኛ ብዙሃንን የሳበ ተግባር የሰሩ ወይንም ሀገራቸውን በተለያዩ በጎ ጎኖች ያስጠሩ ኢትዮጵያውያንን በኮሚቴ አስጠንቶ እና አወዳድሮ ለሽልማት ማብቃት እና
6/ ለኢትዮጵያውያን እና ለኢትዮጵያ በጎ ያደረጉ ኖርወጅያናውያን የሚሸለሙበት መርሃግብር እና የመሳሰሉት ቢካተቱ ዝግጅቱን የደመቀ እንደሚያደርገው እሙን ነው።
በመጨረሻም በኖርዌይ፣ኦስሎ የተደረገው የኢትዮጵያ ቀን ዝግጅት ጥሩ ተግባር በመሆኑ አዘጋጁ ኮሚቴ ለመጪው አመትም በበለጠ አቀራረብ እንደሚያዘጋጅ ተስፋ በማድረግ የእዚህ አይነት ዝግጅቶች ሃይማኖት፣ትውልድ፣ወዘተ የማይለዩ ስለሆኑ ኢትዮጵያውያንን በአንድ ህብረት የማስተሳሰር እና የማስተሳሰብ ኃይላቸው ከፍተኛ ነው።በመሆኑም ሁሉም በያገባኛል ስሜት ይሆናል የሚለውን ሃሳብ በመስጠት ቢያጎለብተው ጠቀሜታው ለእራሳችን፣ለልጆቻችን ከፍ ሲል ደግሞ ለጋራ ቤታችን-ኢትዮጵያችን መሆኑ እሙን ነው።
የኢትዮጵያ ቀን አከባበር በኦስሎ ግሩንላንድ መናፈሻ ፎቶዎች ይመልከቱ። ፎቶ(ጌታቸው)
ጌታቸው በቀለ
ኦስሎ
No comments:
Post a Comment