ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, August 14, 2013

በግብፅ እየሆነ ያለው ለእኛ ምን ትምህርት ይሰጣል?




ከትናንት ጀምሮ ብዙዎች በግብፅ እየሆነ ያለውን በማህበራዊ ድህረ ገፆቻቸው ላይ በፎቶ የተደገፈ መረጃ እየሰጡ ነው።ሁኔታው እጅግ ዘግናኝ እና አሳዛኝም ነው።በተለይ ከጉዳዩ ጋር ምንም ተያያዥነት የሌላቸው አብያተ ክርስትያናት መቃጠል አጋጣሚን ተጠቅሞ የእረጅም ጊዜ እኩይ ዕቅድን የመፈፀም ድርጊት ነው። እኔን የሚያሳስበኝ እኛ በተወሳሰበ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ውስጥ ያለን ተመሳሳይ የታሪክ ክስተት ያሳለፍነው ኢትዮጵያውያን ከእዚህ ተምረን ምን እናድርግ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው ቁም ነገሩ።ከእዚህ በተረፈ ግን ለሀገራችን መፍትሄ የምንለውን ለመናገር ፈርተን ወይንም የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታዎችን ሳናነሳ ስለ ግብፅ ብንናገር ምን ይሆን ፋይዳው? 



የፖለቲካ ለውጥ ከመነሻው እስከመድረሻው የሚሄድባቸው ሂደቶች እጅግ አስገራሚ እና ውጤቱም ከተጠበቀው ይልቅ ያልተጠበቀው ክስተት የበላይ መሆኑ አንዱ እና አይነተኛው ተፈጥሮው ነው።ለእዚህም የቅርብ ጊዜ ምሳሌ የሚሆነን የሰሜን አፍሪካው የለውጥ ማዕበል ነው።የለውጥ ማዕበሉ አነሳስ፣ሂደት፣ግብ እና ውጤት የሃገራቱን ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ቢሆንም በአግባቡ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉባቸው እና የሌሉባቸው ሃገራት ልዩነት ግን ፍንትው ብሎ ታይቷል። የቱኒስያን እና የአልጀርያ የለውጥ ማዕበል ከሊብያ ጋር ያለው ልዩነት እና  በአንፃሩ ደግሞ የግብፅ እና የየመን ሁኔታ አሁንም ድረስ በእንጥልጥል መሆኑ ለሰሜን አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ብሎም ለኢትዮጵያ የሚኖረው ተዘዋዋሪ ተፅኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።ቢያንስ የሁለቱ ሃገራት አለመረጋጋት በእዚሁ ከቀጠለ የአካባቢ ትናንሽ ጉልበተኞች የመፈጠራቸው አባዜ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የጦር መሳርያ ንግድ የሚደራባቸው ሃገራት የመሆናቸው ፋይዳ ውሎ አድሮ እንደ ኢትዮጵያ ላለች ሃገር አይነተኛ ፈተና መሆኑ አይቀርም።ፈተናውም ከሃይማኖታዊ ነውጠኞች እስከ ንግድ አዋኪዎች ድረስ የሚፈጥረው ተፅኖ ቀላል አይደለም።

የአፍሪካ ቀንድን እና ቀጠናውን ስንመለከት በብዙ ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ እና ማህበራዊ ችግሮች የተወጠረ በመለስተኛ የነገሮች ክስተት ከባድ ስብአዊ ቀውስ የመድረሱ ዕድል ከፍተኛ እንደሆነ እንመለከታለን። የአሁኑ ጊዜ የአካባቢው የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊ  ኃይላት(የኢህአዲግ መንግስትም ሆነ ተቃዋሚ ኃይሎች) ነገሮችን በአንክሮ አይተው አማራጩን እና አዋጪውን የፖለቲካ መስመር የመቀየሻ ወሳኝ ጊዜ ላይ  መሆናቸውን ቢረዱት ለሀገራችን አንዱን የፈተና ወቅት የምታልፍበት ጊዜ ሆነላት ነበር።ብልህ እና ቆራጥ መሪ የሚናፈቀው የእዚህ ጊዜ ነው። ከእዚህ ባለፈ ግን ውጥረቶችን ለማርገብ በመሞከር መተኮር በሚገባው በዋናው እና እጅግ አደገኛው ሁኔታ ላይ ማትኮር ካልተቻለ ተያይዞ መጥፋት ብቸኛ ዕጣ መሆኑ የማይቀር መሆኑን መረዳት ብዙም ብልህነት አይጠይቅም።

በሰላማዊ መንገድ መንግስት መቀየር ያልታደለቸው ሀገራችን ከውጭ ያሉት ቅራኔዎች ነፀብራቅ እና በውስጥ በእራሷ እና ከቀጠናው ጋር ያሉት ቅራኔዎች ወደ አልታሰበ እና አልተፈለገ ጫፍ ኢትዮጵያን ይዘዋት እንዳይሄዱ ማሰብ የዜጎች ትልቁ ድርሻ መሆን አለበት።ለመሆኑ ውሎ አድሮ ኢትዮጵያ ላይ በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ  ተፅኖ ከሚፈጥሩት ቅራኔዎች እና ቀውሶች ውስጥ-

ከውጭ -

- በሱማሌ ያለው የአልሸባብ እንቅስቃሴ፣
- የዑጋዴን ግጭት፣
- የግብፅ ሁኔታ አለመረጋጋት እና እስካሁን ወጥ የውጭ ፖሊስዋ አለመታወቁ፣
- የአቶ ኢሳያስ ድብቅ እና ግልፅ ያልሆነ አስተዳደር በኤርትራ መኖሩ፣
- የፅንፈኛ እስልምና እንቅስቃሴ፣
- ጠንካራ ያልሆነው የደቡብ ሱዳን መንግስት ቅርፅ ገና በአግባቡ አለመለየቱ የሚሉት ጥቂቶቹ ሲሆኑ፣


ከውስጥ -


 - ኢህአዲግ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ከህዝብ እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የገባው ቅራኔ፣
- ኢህአዲግ ከተለያዩ ባለድርሻ የህብረተሰብ አካላት ጋር የፈጠራቸው ቅራኔዎች።(ለምሳሌ ከሙስሊሙ ህብረተስብ ጋር፣ከዋልድባ ገዳም ይዞታ ጋር ይጠቀሳሉ)፣
- የሕዝብ ብዛት እየጨመረ መሄድ፣
- የዋጋ ግሽበቱ ጭማሪ አለማቆም (ባለፈው ወር ብቻ በመንግስት ዘገባ መሰረት አጠቃላይ ግሽበቱ በ 8% መጨመሩ ይታወቃል)፣
- የሐብት ክፍፍሉ መራራቅ፣
- የስራ አጥነት መጨመር፣
- የማህበራዊ ኑሮ ቀውስ (ከቀዬው የሚፈናቀለው መብዛት፣የጎዳና ተዳዳሪ መጨመር፣ሃገሩን ጥሎ የሚሰደደው መብዛት ወዘተ) የሚሉት ከብዙ በጥቂቱ ናቸው።


ከኢህአዲግ መንግስት እና ከተቃዋሚ ኃይሎች ምን ይጠበቃል?

እነኚህ ከላይ የተመለከትናቸው ቅራኔዎች እና ቀውሶች በአግባቡ ካልተፈቱ እና ለመፍትሄነት ሁሉም ድርሻ እንዳለበት ካልተገነዘበ ነገ ሀገራችን ብለን የምንጠራት ምድር እንዳናጣ ባንመኘውም መፍራት ግን ለጥንቃቄ ይረዳል።ለሀገራችን ውስብስብ ችግር መፍትሄ ለመስጠት ተቃዋሚ መሆን ብቻ መድሃኒት አይሆንም።የመንግስትን ታላቅነት በመስበክ እና አቶ መለስ ታላቅ መሪ ነበሩ እያሉ በማስተጋባትም ሀገር አይገነባም።በሆደ ሰፊነት፣በጋራ ነጥቦች ላይ በማተኮር፣እጅግ አደገኛ የሆኑትን የሀገሪቱን ችግር ቀድሞ ለመቅረፍ በመሞከር፣ኢትዮጵያዊነትን መሰረት አድርጎ ሀገራችንን የነበረ እሷነቷን በክብር በማስቀጠል ግን በጋራ ከመጥፋት ያድናል።እዚህ ላይ ትልቁን በሃጋራችን ላይ የሚያንዣብበውን አደጋ  የተጠያቂነት  ድርሻ የሚይዘው የኢህአዲግ መንግስት መሆኑን መርሳት አይገባም።ለእዚህም ዋናው እና አቢይ ምክንያት ኢህአዲግ  በመንግሥትነት እስከተቀመጠ ድረስ ቅራኔዎችን ለመፍታትም ሆነ የፖለቲካ ኃይላትን እና የህብረተሰቡን አካላት ጥያቄ ለመመለስ የዋና ባለድርሻ አካልነቱን በመያዙ ነው።በሌላ በኩል የተቃዋሚ ኃይላትም ከኢህአዲግ ጋር የሚያደርጉት ማናቸውም አይነት የፖለቲካ ለውጥ ማ ምጫ የተፅኖ መፍጠርያ መንገዶች ማለትም ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ  የትጥቅ ትግል የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የማይጎዳ እና ለዘመናት ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ለሚሹ ኃይላት የማይመች ሀገሪቱንም ወደማትነሳበት አዘቅት የማይከት መሆኑን በሚገባ ማጤን ተገቢ ነው።

ባጠቃላይ የሀገራችን ውስጣዊ የፖለቲካ ቅራኔ፣የኢህአዲግ ግትር እና ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ አሰልቺ ፖሊሲ፣የአካባቢያችን ሃገራት የፖለቲካ ንፋስ ተለዋዋጭነት፣የኢትዮጵያን የመኖር ህልውና የሚፈታተኑ እንቅስቃሴዎች መኖር (የኑሮውድነቱ፣የህዝብ ብዛት መጨመር) ስንመለከት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ በመጣው መንገድ ቢመጣ በነበረ እሷነቷ የማስቀጠል ዋስትናውን ያሳንሰዋል።ይህ ማለት ደግሞ ኢህአዲግም ሆነ ተቃዋሚዎች በጋራ ስለሚጠሯት ሀገር ለማውራት ዕድል የማያገኙበት አስከፊ ጊዜ ይመጣል ማለት ነው።ስለዚህ ኢህአዲግ የዲሞክራሲውን መንገድ እና እውነተኛ የምርጫ ስርዓት ከልብ ባሳየ መንገድ መከወን (እውነተኛ የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ ለምሳሌ በዋና ዋና ቁልፍ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ላይ) ፣ ነፃ የሚድያ አገልግሎት እንዲኖር ከልዩነት ይልቅ አንድነትን የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ላይ መስራት ቢጀምር (ሃያ አንድ አመት ሙሉ ሲጠየቅ የነበረን ጉዳይ ካለመሰልቸት ስደግመው አንባቢ እንዳይሰለች ይቅርታ ከመጠየቅ ጋር) እና  እራሱንም ሆነ ሀገሪቱን ወደማትወጣበት አዘቅት ከመክተቱ በፊት በ2006 ዓም  በአንክሮ ቢያስበበት ለኢትዮጵያ ትልቅ ውለታ እንደዋለ ይቆጠርለት ነበር።እዚህ ላይ ላሰምርበት የምፈልገው እነኚህን ተግባራት ቀድሞ ኢህአዲግ ማድረግ ካልቻለ የለውጥ ማዕበሉ በተፈለገውም ሆነ ባልተፈለገው መንገድ መምጣቱ የግድ ነው።አሳዛኙ ግን ውጤቱ እና የመጨረሻ ግቡን በጥሩ መልኩ ለመተንበይ አለመቻሉ ነው።በትንሹ ለመተንበይ ግን የተቃዋሚዎችን አያያዝም ሆነ የመንግስትን ቅራኔ አፈታት መንገድ መመልከት በቂ ነው። ሁለቱም የሚቀራቸው መንገድ እንዳለ ይስተዋላል።ለኢህአዲግ ግን እራሱን የእውነተኛ ለውጥ ማዕበል ለማድረግ እና ሀገርንም ህዝብንም ይቅርታ ለመጠየቅ ከነገ ይልቅ ዛሬ ይቀርበዋል።2006 ዓም ምን እንሰማብሽ ይሆን?

ጌታቸው በቀለ
ኦስሎ

1 comment:

Anonymous said...

Every body must stand up for solution.

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...