ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, August 8, 2013

በትልቋ ኢትዮጵያ ውስጥ የእስልምና ተከታዮች ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንም አሉ።


መግቢያ 

ኢትዮጵያ ዛሬ ከሰማንያ ሚልዮን በላይ ሕዝብ ያለባት ነገ ከመቶ ሚልዮኖች በላይ የሚኖሩባት ሀገር ናት።ባለፈው ታሪካችን በባህል፣በቋን እና በሃይማኖት ተከባብረን በመኖራችን እስከዛሬዋ ቀን ድረስ በሰላም ደርሰናል። አለም የመድን ዋስትና (ኢንሹራንስ) ሳይኖረው ዕድር በመፍትሄነት አስቀምጠን የሞተው ሲቀበር እና ሃዘንተኛ ሲደገፍ ዘመናት አልፈዋል።የባንክ አሰራር ገና ሳይተዋወቅ ዕቁብ በገንዘብ መቆጠብያነት ተጠቅመንበታል። ዕድር እና ዕቁብ አገልግሎታቸው ይህ ብቻ አይደለም።በማኅበራዊ ችግሮች ዙርያ በሚነሱ አለመግባባቶችም የመፍትሄ አካል ሆኖ አገልግሏል።ግጭቶች ለእድር አባላት ቀርቦ መፍትሄ ይፈለግለታል።አቅም ያነሰው እድርተኛ እንዲደጎም ይደረጋል።ህብረተሰቡን የበጠበጠ አጉራ ዘለል ከእድር እንደሚለይ ማስጠንቀቅያ ይሰጠዋል።በጥንቱ አገረ ገዢው በዘመኑ ቀበሌ ወይንም ገበሬ ማህበር የማይፈታው የአካባቢ ችግር በዕድር መፍትሄ ያገኛል። ይህ እንግዲህ የነበርንበት የአኗኗር ዘይቤ መሆኑ ነው።

ባለንበት ዘመን በትልልቅ ከተሞች የዕድር ተቅዋም አቅም እየቀነሰ ቢመጣም በገጠሩ እና መለስተኛ ከተሞች (ከ85% በላይ ሕዝብ በ  ሚኖርበት የሀገራችን ክፍል) ግን ዕድር በሕዝቡ ኑሮ ውስጥ ተደማጭ እና ተፅኖ ፈጣሪ ነው።ዕድርን የመሳሰሉ ማህበራዊ ተማት ለሕዝቡ የአብሮነት አኗኗር  ያላቸው ፋይዳ እጅግ ትልቅ ነው። ዕድር ዘመናዊ እና ቀልጣፋ አሰራርን ይዞ ቢቻል ከመድን ዋስትና ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ እስከ የጠለፋ ዋስትና አሰጣጥ ድረስ አዘምኖ ግን ማህበራዊ ትስስርን (ጊዜ፣ጉልበት እና ገንዘብን በቆጠበ መልክ) የሚያጎለብት  እንዲሆን ማድረግ  ተገቢ ነው። ኢትዮጵያ የምትገነባውም ሆነ የምትታወከው  በአራት ኪሎ ቤተመንግስት ስሜት ብቻ ሳይሆን ትንንሽ በሚመስሉ እንደ እድር ባሉት ተማት ሕልውና እና ሞት ጭምር መሆኑን  መዘንጋት አይገባም።

''የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ እንኳን እኛ ግመላችን ታውቀዋለች''

ኢትዮጵያን እድር ውስጥ ማየት ከቻልን የእስልምና ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እየደረሰባቸው ያለው የመንግስት በትር ምን ያህል የሚያም መሆኑ ወለል ብሎ ይታየናል።በእድራችን ውስጥ እማማ ዙቤዳ ሲልኩን ተልከን አድገናል። እትዬ ፋጡማ ሲቆጡን እሺ ብለን ሰምተናል።ሃጂ ኑር ከእድሜ እና ከልምድ ሲመክሩን አዳምጠናል። እኛ ያደግንባት ኢትዮጵያ ይህች ነች። ዛሬ ሃጂ ተገልብጠው የሚ ያከብሯትን፣የሚሽቆጠቆጡላትን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ''አጎሳቆሉት'' ብሎ ኢቲቪ ቢነግረኝ የምሰማበት ምን አይነት ሞራል ይኖረኛል? እንዴት ነው በኢትዮጵያ በጎ ዘመን ሲደሰቱ፣ኢትዮጵያ ስትከፋ ያነቡ የሰፈሬ የእድሩ ማገር የነበሩ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዛሬ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አዋረዱ ብሎ ኢቲቪ የሚነግረኝ? የአፋሩ ንጉስ አሊቢራ ''የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ እንኩዋን እኛ ግመላችን ታውቀዋለች'' ተብሎ ሲነገር እየሰማሁ አድጌ  ዛሬ ኢቲቪ ሌላ ታሪክ ሲያወራኝ በየትኛው ልቦናዬ ልስማው? 

ከባህር ውስጥ አንዱ ወይም ሁለቱ አሳ ቢገማ በባህር ውስጥ ያሉትን አሳዎች በሙሉ አይወክልም።

መንግስት ትልን ኢትዮጵያ ማየት ቢችል ኖሮ በቲቪ መነገር የሚገባውን ከማይገባው ለይቶ ማቅረብ በቻለ ነበር።ሆኖም ግን  ከዛሬ አስር አመት ወዲህ በአንዳንድ ቦታዎች ኢትዮጵያዊውን ሙስሊም ከኖረበት አብሮነት ስሜት ለመለየት ሙከራ እያደረጉ ያሉ የሉም ማለት አይደለም። በጅማ ዙርያ፣በአጋሮ ዙርያ፣በአሩሲ አንዳንድ ቦታዎች፣በባሌ ደቡባዊ ክፍል እና በሌሎች ከተሞች አዲስ አበባን ጨምሮ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር  አብረው ለዘመናት በእድር አባልነት የኖሩ የእስልምና ወንድሞች እና እህቶች እንዲሁም አባቶች እና እናቶች በፅንፈኛ ''የሙስሊም ሃይማኖት ተከታዮች'' እንግልት ደርሶባቸዋል፣ተደብድበዋል እንዲሁም ለስደት ተዳርገዋል።ኢቲቪ እና መንግስት ይህንን ያውቃሉ እንድያውም አንዳንድ ቦታዎች ለዘመናት ከኖሩበት የቡና እርሻ ተገፍተዋል።ይህ ተግባር በእስልምና ተከታዮች  ላይ ብቻ ሳይሆን በክርስቲያኖች ላይም ደርሷል። ይህ ማለት ግን እነኚህ እኩይ ተግባር ላይ የተጠመዱ ፅንፈኛ አስተሳሰብ አራማጆች ሌላውን ኢትዮጵያዊ የእስልምና ተከታይ ወንድሞች እና እህቶችን አይወክልም። ከባህር ውስጥ አንዱ ወይም ሁለቱ አሳ ቢገማ በባህር ውስጥ ያሉትን አሳዎች በሙሉ አይወክልም።

የኢህአዲግ ''አጋር'' ተብዬ ድርጅቶች የፅንፈኞች መንፈላሰሻ!

እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን መንግስት ከላይ የጠቀስኩት አይነት የፅንፈኛ ሃሳቦች ሙስሊሙ ሕብረተሰብን እየረበሹ መሆኑን እያወቀ በወቅቱ ቢያንስ ከእድርም ሆነ ከማህበራዊ ኑሮ እንዲባረሩ እና እንዲገፉ የተደረጉትን ወደ ሚድያ ከማቅረብ ይልቅ ሲሸፋፍን ነበር የከረመው።ይልቁንም የእስልምና ተከታይ ወንድሞች እና እህቶች እነኚህን ፅንፈኛ አስተሳሰብ ያላቸውን እንዳይከላከሉ ትልቅ እንቅፋት የሆነባቸው እራሱ መንግስት ነበር። ምክንያቱም እነኚህ ፅንፈኛ ሃሳብ አራማጆች የተጠለሉት ''የኢህአዲግ አጋር '' በተሰኙ የጎሳ ድርጅቶች ስር ነበር። በመሆኑም በምስራቅ፣በደቡብ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በእነኚሁ ፅንፈኛ አካላት ለደረሱ አደጋዎች (በሙስልሙም ሆነ በክርስቲያኑ ላይ) ተገቢውን ቅጣት መንግስት ሳይሰጥ አጥፊዎቹ እንዲቀጡ የሙስሊሙ ሕብረተሰብም ጭምር መንግስትን እየተማፀነ በጥፋቱ ላይ እጃቸው እንዳለ የታወቁት የኢህአዲግ አጋር ድርጅቶች አባላት ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረው እንዲሰሩ መደረጉ ብዙዎችን ያስቆጨ ጉዳይ እንደሆነ ይሄው አሁንም አለ።ዛሬም ሳላት ሊሰግድ መስግድ የሚገኘው ንፁሁ ሙስሊም ሳይሆን አክራሪነት የተፀናወተው በኢህአዲግ አጋር ድርጅት አባልነት ስር የተኮለኮሉ በርካታ አባላቱ ኢትዮጵያዊ ስሜቱ ያየለበትን ሙስሊም ሳይቀር ቁም ስቅሉን ማሳየታቸውን ተያይዘውታል።ስለሆነም የኢህአዲግ አጋር ተብዬ ድርጅቶች የፅንፈኛ መንፈላሰሻነታቸው እና ለወዳጃቸው ካሮት ለሚቃወማቸው ዱላ እየሰጡ  አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናትን ያልሆነ እርምጃ እንዲወስዱ ሲወተውቱ ይስተዋላሉ።ለምሳሌ በዛሬው የኢድ በዓል ላይ የመግቢያ ካርድ ይዘጋጅ ባዮቹ እኚሁ ''አጋር'' ተብዬዎች ውስጣቸው ፅንፈኛ ከላይ ግን ንፁሃን መስለው ለመቅረብ የሚጥሩቱ አይነተኛ ማሳያዎች ናቸው። 

ባጠቃላይ መንግስት ትልን ኢትዮጵያ በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች መተሳሰብ፣መፈቃቀር እና አንድነት የኖረች ስለሆነ መንግስት ለችግሮች የሚሰጠው መፍትሄ ከጠበበ አስተሳሰብ ወደ ሰፋ አስተሳሰብ መምጣት መቻል ነበረበት።በተለይ የመገናኛ ብዙሃኑ ፕሮፓጋንዳ አሰራር የዛሬዋን ትንሿን ኢትዮጵያ ሳይሆን ወደታች ህዝቡ የሚኖርበት የአኗኗር ዘይቤ እንደ እድር በመሳሰሉት የማህበራዊ ተም ውስጥም ትልን ኢትዮጵያ ማየት የሚችል መሆን ይገባዋል።ኢትዮጵያውያን ሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን አለአግባባ እየተገፉ እድራችን ሰላም ሊሆን አይችልም።ፅንፈኛ የእምነት አራማጆችበኢህአዲግ አጋር ድርጅትነት ስር ተጠልለው መንግስትን እያማከሩ በጎ ምክር አይገኝም።ከእድራችን አባላት ንፁህ ኢትዮጵያውያን ሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የመለያ ልቦና ያድለን።

አበቃሁ 
ጌታቸው በቀለ 
ኦስሎ 

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...