ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, May 31, 2020

ሰኔ እና ሰኞ ዘንድሮ በፈረንጆቹም በኢትዮጵያውያንም ገጥሟል።ጉዳያችን ከአድዋ ጦርነት ጀምሮ የሰኔና ሰኞ ግጥም ለመቃኘት ሞክራለች



(በጌታቸው በቀለ የጉዳያችን ገፅ አዘጋጅ)
''ሰኔ እና ሰኞ ሲገጥም ጥሩ አይደለም'' የሚለውን አባባል በተለምዶ ይነገራል።ለምን? ለሚለው ምላሽ ግን አላገኘሁም።ሰኔ እና ሰኞ ገጠመ ለመጥፎ አባባል ብቻ ነው የሚባለው? አንዳንዴ ሰኔ እና ሰኞ ገጥሞ፣ነገሩ ተሳክቶ እየተባለም  ይነገራል።
ሰኔ እና ሰኞ ዘንድሮ በኢትዮጵያም ሆነ በፈረጅንጆቹ ገጥሟል። የፈረንጆቹ ''ጁን'' 1 እና ''መንደይ'' ፣የኢትዮጵያ ሰኔ1 እና ሰኞ ዘንድሮ ገጥሟል።በእዚህ ዓመት ደግሞ ዓለም በኮሮና ወረርሽኝ ትልቅ ፈተና ላይ የወደቀችበት ነው።ስለሆነም በፈረንጆቹም በእኛም መግጠሙ እና ሰኔ እና ሰኞ የሚባለው ነገር እንዴት ነው ብዬ ትንሽ ወደኃላ ለመፈተሽ ሞከርኩ።ውጤቱ የሚገርም ሆኖ አግኝቼዋለሁ።ከአጋጣሚዎቹ ለመረዳት የቻልኩት ግን ወደኃላ ታሪካችን ስንመለከት ሰኔ ሰኞ የገጠሙባቸው ዓመቶች  አንዳንዶቹ ፈተና የመጣባቸው ቢሆኑም ሌሎቹ ደግሞ መልካም ጊዜዎች ነበሩ።

የሰኔ እና ሰኞ መግጠም ለምን ብዙ ይወራል ብዬ ወደ ሀገርቤት አንድ ወዳጄ ጋር ደውዬ ስጠይቅ ያለኝ -ነገሩ አፈ ታሪክ ነው። ግን አንድ ጊዜ አንድ ሰው ሲያወራ የሰማሁት እና  የማስታውሰው ጉዳይ በኢትዮጵያ መኪና እንደ እንግሊዞች በግራ መስመር ብቻ ይነዳ ነበር፣በኃላ በአሜሪካኞቹ አነዳድ በቀኝ በኩል እንዲሆን ተብሎ ሲታወጅ ዓመቱ ሰኔ 1 እና ሰኞ የገጠመበት ነበር።በጊዜው አዋጁን እየረሳ የተጋጨ ብዙ ሰው ነበር በእዚህ ሳብያ ሰኔ ሰኞ ይባላል ሲሉ ሰምቻለሁ አለኝ።ለማንኛውም የሰኔ እና ሰኞ ገጠመኝ የሚገርም ነው።

ሰኔ እና ሰኞ በአድዋ የዘመቻ ዓመት 
የአድዋ ዘመቻ በ1888 ዓም ሲደረግ ሰኔ እና ሰኞ ገጥሞ ነበር።ይህ ዘመቻ ብዙ ፈተና ቢኖርበትም ድሉ ግን እስካሁን ለጥቁር ሕዝቦች በሙሉ እንዳንፀባረቀ ነው።

ሰኔ እና ሰኞ ዳግማዊ አፄ ምንሊክ ያረፉበት ዓመት 
ሰኔ እና ሰኞ የገጠሙበት 1906 ዓም ዳግማዊ ምንሊክ ያረፉበት፣እና ልጅ ኢያሱ ወደ ንግስናው የመጡበት ነበር።ይህ ዓመት እንደ አውሮፓውያ አቆጣጠር 1914 ሲሆን የመጀመርያው ዓለም ጦርነት የተጀመረበት ዓመትም ነው።

ሰኔ እና ሰኞ በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ንግሥ ዓመት 
ሰኔ እና ሰኞ የገጠሙበት ጥቅምት 23/1923 ዓም አፄ ኃይለሥላሴ ከራስ ተፈሪነት ወደ ንጉሰ ነገስት ኢትዮጵያ ተብለው በአዲስ አበባ ደብረገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ስርዓተ ንግሥ የፈፀሙበት ዓመት ነው።

ሰኔ እና ሰኞ የገጠሙበት የጣልያን ወረራ 
በ1928 ዓም (1935 ዓም) በኢትዮጵያም በፈረንጆቹም እንዲሁ ሰኔ እና ሰኞ በኢትዮጵያ ገጥሞ ነበር።በእዛን ዓመት ዓለምም ሆነ ኢትዮጵያ የገጠማቸው አሳዛኝ ጉዳይ ነበር።በኢትዮጵያ የፋሺሽት ጣልያን ኢትዮጵያን የወረረበት ዓመት ነበር።በዓለም ላይም ጀርመን የአንደኛው ዓለም ጦርነት ማብቅያ ላይ የፈረመችው እና ጀርመን  እራሷን እንዳታስታጥቅ የሚለው የ''ቨርሳይለስ ትርቲ'' የሚባለውን ያፈረሰችበት ዓመት ነበር።ይህንን ውል በማፍረስም ሂትለር ጀርመንን መልሶ በማስታጠቅ የሁለተኛው ዓለም ጦርነትን በዓለም ላይ ለማወጅ በሩን የከፈተለት ቁልፍ ተግባር ሆነ።

 ሰኔ እና ሰኞ የገጠሙበት የደርግ እና የኢህአዴግ/ህወሓት ስልጣን መደላደል 
በ1973 ዓም ደርግ ከወታደራዊ ስሙ ወደ ድርጅት ማለትም በ1972 ዓም ወታደሮቹን በሙሉ በኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሰፓአኮ) ብሎ በ1972 ዓም መስርቶ እራሱን ያደላደለበት ጊዜ ነበር።በተመሳሳይ ኢህአዴግ/ህወሓት በ1984 ዓም እራሱን ከሽምቅ ተዋጊነት ባንዴ የሽግግር መንግስት በሚል እራሱን ወደ ስልጣን ያመጣበት ዓመት ነበር።ሁለቱም 1973 ዓም እና 1984 ዓም የዋሉት ሰኔዎች ሰኔ 1 የዋሉት ሰኞ ቀን ነበር።

ሰኔ እና ሰኞ የገጠሙበት የሻብያ እና ህወሓት ጦርነት 
 የአቶ ኢሳያስ እና የአቶ መለስ ግጭት የተጀመረው ሰኔ እና ሰኞ በገጠሙበት በ1990 ዓም አቶ ኢሳያስ ባድሜን ሲወሩ ነበር።

 ሰኔ እና ሰኞ የገጠሙበት የኮሮና ወረርሽኝ 
ዘንድሮ 2012 ዓም (2020 ዓም እኤአ) በፈረንጆቹም ሆነ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሰኔ 1 እና ሰኞ ገጥሟል።ዘንድሮ መላው ዓለም በኮሮና ወረርሽኝ የታመሰችበት ዓመት ነው።ሁሉም በሚባል ደረጃ የአይሮፕላን በረራዎች ቆመዋል፣አገሮች ድንበሮቻቸውን ዘግተዋል።መጪው ሁኔታ ምን እንደሚሆን አይታወቀም።

ከላይ ከተጠቀሱት ቀናት በተጨማሪ የሚከተሉት ዓመታት ሰኔ እና ሰኞ የገጠመባቸው ናቸው።ዓመቶቹ በኢትዮጵያ እና በቅንፍ ውስጥ ያለው የአውሮፓውያኑ አቆጣጠሮች ናቸው። እነርሱም 1895 ዓም (1903)፣1900ዓም (1908)፣1934ዓም (1942)፣1951 ዓም (1959)፣1956ዓም (1964)፣1962ዓም (1970)፣1979ዓም (1987) ይጠቀሳሉ። 

ለማጠቃለል በዓለማችን እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ይከሰታሉ።ከላይ ካሉት ዓመታት ብቻ ብንመለከት ሁሉ መጥፎ ቀኖች አይደሉም።መጥፎ የምናደርጋቸው እኛ እና የእኛ አካሄድ ነው። ለምሳሌ የአድዋ ጦርነት ላይ ከንጉሡ ጀምሮ ህዝቡ ዝግጅት አድርጎ ከአምላኩ ታርቆ ባይነሳ እስካሁን በባርነት ውስጥ የገባን ህዝቦች በሆንን ነበር።ጥሩ ቀኖች እንዳሉ ሁሉ ክፉ ቀኖች አሉ። ይህ የምናውቀው ነው።ሁሉንም ጥሩ ለማድረግ ግን የእኛው ውሳኔ ነው።ይሄውም መስራት የሚገባንን በመስራት፣ስንሰራ ደግሞ በትዕቢት ሳይሆን እግዚአብሔር ክፉውን ቀኖች እርሱ ባወቀ እንዲያሳልፍ በመጸለይ ነው።ዓድዋ ለእዚህ አስተማሪ ነው።ጦርነት መጣ ብለው አባቶቻችን በመተከዝ ጊዜያቸውን አላጠፉም።እግዚአብሔር እንዳደረገ ያድርገው ብለውም የጣልያንን ወረራ ተቀምጠው አልተመለከቱም። የራሳቸውን ድርሻ ለመወጣቱ ተነሱ፣እግዚአብሔር ደግሞ የእርሱን ሥራ እንዲሰራ ታቦተ ሕጉን ይዘው ቄሱ ከመቅደስ፣ሼሁ ከመስጊድ ተጠራርተው ከሰራዊቱ ጋር ዘምተው፣ለሞቱትም ሆነ በሕይወት ላሉት አብረው ጸለዩ።ስለሆነም የቀን መጥፎ የለውም።ቀኑን መጥፎም በጎም የምናደርገው እኛው ነን።ይሄውም በሁለት ነገሮች ነው።አንድ፣ የሚመጣውን ፈተና ለመጋፈጥ በኅብረት ባለመስራት እና ሁለት፣ወደ እግዚአብሔር ባለመጸለይ።

መልካም ሰኔ እና ሰኞ 

ማሳሰቢያ 
የጉዳያችን ጽሁፍ  በየትኛውም ገፅ እና ሚድያ ላይ ሲወጣ ከጉዳያችን ገፅ ማግኘትን መግለጥ ጨዋነት ነው 

 




ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Saturday, May 30, 2020

ከሰሞኑ የአሜሪካ ክስተት መንግስት፣የሃይማኖት መሪዎች እና ፖለቲከኞች ምን ይማሩ?

  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ቀደምት ከሆኑት ውስጥ ከመሆኗ ፣ለአፍሪካ እናት ከመሆኗ እና ብዙ የዓለም ጥቁር ህዝቦች በማንነታቸው መኩርያ ከማየታቸው አንፃር፣የሰሞኑን የአሜሪካው ድርጊት እንዳሳዘናት እና እንዳሳሰባት በአባቶቿ መግለጫ መስጠቷ ብዙዎች የአፍሪካ፣የአሜሪካ፣እና የላቲን አሜሪካ ጥቁሮች እና ሌሎች በእኩልነት የሚያምኑ ሁሉ ጆርዎቻቸውን እንዲሰጡ የሚያደርግ መልካም አጋጣሚ ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል።

ክስተቱን ብዙ ነገሮችን አመላካች ነው 


ባሳለፍነው ሳምንት በአሜሪካ ምያፖሊስ አንድ አፍሪካ አሜሪካዊ ጥቁር በሌላ አሜሪካዊ ነጭ ፖሊስ፣ፖሊሱ ጥቁሩን መሬት ላይ አስተኝቶ በጉልበቱ የአንገቱን መተንፈሻ አካል በኃይል በመዝጋት ግለሰቡ ወደ ሆስፒታል ከተወሰደ በኃላ ህይወቱ አልፏል።አንድ አሜሪካዊ ሁኔታውን ሲገልጠው  ''በእዚህ በ21ኛው ክ/ዘመን አንድ ሰው ሌላውን እንደ አውሬ ሕዝብ በተሰበሰበበት ለዘጠኝ ደቂቃዎች አንገቱ ቆሞ ገደለው'' ብሏል።ይህንን ዓረፍተ ነገር ብቻ በደንብ ብናጎላው ብዙ ነገር ይነግረናል።ዘመኑ 21ኛው ክ/ዘመን ሰው ''ሰለጠነ'' የሚባልበት፣የሞተው ሰው እንደ አውሬ ሕዝብ በአደባባይ እየተመለከተ ለዘጠኝ ደቂቃዎች ያህል ታፍኖ፣እነኝህ ዘጠኝ ደቂቃዎች ሙሉ የግለሰቡን ሕይወት ለማትረፍ ከበቂ በላይ ነበሩ።ነገር ግን ዙርያ ያለው ሰው የእራሱ አምሳያ ታፍኖ ሲገደል በሞባይል ፊልም የምቀርፅበት እና ብዙ የሶሻል ሚድያ አድናቂ ለማግኘት የሚሰበሰብበት፣የግለሰቡን ሕይወት ለማትረፍ አንድ ነገር ከማድረግ ይልቅ ቃላትን እየወረወረ ፊልሙን የሚቀዳበት፣ገዳዩ ወንድሙ ጉሮሮ ላይ ቆሞ በኩራት እጁን ኪሱ ከቶ በትዕቢት ተወጥሮ የሚታይበት።አጠቃላይ ትዕይንቱ ሁሉ በደንብ በትነን እና ዘርዝረን ብንመለከተው ብዙ የሚነግረን ማኅበራዊ፣ሞራላዊ እና ፖለቲካዊ መልዕክቶች አሉ።ችግሩ ያለበትን ደረጃ ለመረዳት ግን በአሜሪካ በሚኒሶታ ግዛት የተንሳውን የህዝብ አመፅ ለማስቆም በግዛቷ  የመቶ ዓመታት ታሪክ ውስጥ ለሕዝብ አመፅ ለመበተን ወጥቶ የማያውቀው የአሜሪካ ብሔራዊ ዘብ (ናሽናል ጋርድ) በከተማዋ ውስጥ ከሙሉ ትጥቁ ጋር የወጣበት ነው።የእዚህ ሁሉ ችግር ግን በአንድ ቀን ተሰርቶ ያለቀ ጉዳይ አይደለም።ለዓመታት የተገነባ የተንሸዋረረ የማኅበረሰብ ግንባታ ውጤት ነው።ጉዳዩ ተመልካች ያጡ፣በአግባቡ የሚመራቸው ያላገኙ የልጆች፣ወጣቶች እና አዋቂዎች ሁሉ ድምር ውጤት ነው።ጉዳዩ ከአሜሪካ አንፃር ብቻ ሳይሆን ከዓለም አንፃርም አሁን ያለንበት የዝቅጠት ደረጃ የቱ ጋር እንደሆነ ትንሽ ወደኃላ ሄዶ መንደርደር ስለሚፈልግ ለጊዜው እርሱን ትቼ ከክስተቱ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግስት ምን ይማሩ? ወደሚለው አጭር ሃሳብ አመራለሁ።

መንግስት ምን ይማር?


የኢትዮጵያ መንግስት ከአሜሪካው ክስተት የሚማራቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ።የመጀመርያው እና ዋናው ጉዳይ የፀጥታ ኃይሉን ስነምግባራዊ፣ሞራላዊ፣የሕግ ዕውቀቱ እና ችግር ፈቺ አቅሙን መፈተሽ አለበት።በተለይ ከህዝብ ጋር ዕለት ከዕለት የሚገናኙ ፖሊሶች ላይ ብዙ መሰራት ያስፈልገዋል።ስራው ከባድ፣ጊዜ የሚጠይቅ እና ተከታታይ ተግባራትን ሁሉ የሚፈልግ ነው።ሆኖም ግን ቅድምያ የሚሰጣቸው እና ጊዜ የማይሰጡትን ማስቀደም ይገባል።በኢትዮጵያ በተለይ ያለፈው 27 ዓመት ጥሎብን የሄደው የጎሳ ፖለቲካ ቁስል እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ወደፊት አደጋ ሊሆኑ የሚችሉትን ቦታዎች መለየት እና ቅድምያ መስጠት ግን እጅግ አስፈላጊ ነው። ከእዚህ ውስጥ የአዲስ አበባ ጉዳይ አንዱ እና ዋናው ነው።ከእዚህ በፊት ደጋግመን እንዳልነው አዲስ አበባ የራሷ ስነ ልቦናዊ፣ባሕላዊ እና ታሪካዊ ዳራ ያላት እና ከሌላው አካባቢ ጋር ጨፍላቂ በሆነ ደረጃ መመልከት የማይገባ ከተማ ነች። እዚህ ላይ የከተማዋ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ ዛሬ የእስያ እና የላቲን አሜሪካ መሃል መሸጋገርያ ድልድይ እየሆነች ነው።ይሄውም የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ በመሆኗ፣በኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳረሻ መብዛት እና ባላት ቁልፍ መልከዓ ምድራዊ  አቀማመጥ ሳብያ ነው። 

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ከተማዋ የራሷ በበቂ ሁኔታ የተደራጀ፣ስልጡን፣ብቃት እና አቅም ያለው የራሷ የፖሊስ ኃይል የላትም።በቅርቡ ብንመለከት የአዲስ አበባ አስተዳደር ይህንኑ ጉዳይ ጠይቆ የፌድራል ፖሊስ ከመቆጣጠሩ አንፃር በጀት ከእኔ ወስዶ በሚገባ አላገለገለኝም በማለት በጀት ማቆሙ ሁሉ ተነግሯል።አሁን ሁኔታው ምን ላይ እንዳለ መረጃ ባይኖርም።የአዲስ አበባ መስተዳድርም ሆነ የአዲስ አበባ ሕዝብ ጥይቄ ሁለት ናቸው።አንዱ ከተማዋን የሚመጥን፣የከተማውን ሕዝብ ስነ ልቦና የሚጋራ፣አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ደረጃዋን ከግንዛቤ ያስገባ ፖሊስ ያስፈልጋታል።የሚል ሲሆን ሁለተኛው አሁን ያለውን ህገወጥ የመሬት ወረራ ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎችን የመከላከል ሥራ የፌድራል ፖሊስ አዲስ አበባ በምትጠብቀው ደረጃ እየሰጠ አይደለም  የሚሉት ናቸው።ይህንን በተመለከተ ጉዳያችን ከእዚህ በፊት ያነሳችው ስለሆነ ይህንኑ በእዚህ ሊንክ እንድትመለከቱት እጋብዛለሁ።ጉዳዩ ግን ትኩረት ማግኘት ያለበት ነው።በተለይ የኢትዮጵያን ቀጣይ ሽግግር ለማደናቀፍ ለሚፈልጉ የውስጥም ሆነ የውጭ ኃይሎች በቀዳሚነት የፀጥታ ኃይሉን ከህዝብ ጋር ማጋጨት ዋና ስራቸው በመሆኑ ቀዳዳዎቹን ሁሉ መድፈኑ ተገቢ ነው።

የሃይማኖት አባቶች ምን ይማሩ?

መማር ከሰው ልጅ በሙሉ የሚጠበቅ ነው።አንድ ሰው ሁሉን ነገር ሊያውቅ አይችልም።የሃይማኖት አባቶችም ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ሊያውቁ አይችሉም።እንደማንኛውም ሰው ከአሜሪካው ሁኔታ ምን እንማራለን? ማለት አለባቸው።በመጀመርያ መገንዘብ የሚገባው የሚመስለኝ የማኅበረሰብ መቀየርን በአንክሮ የመከታተል እና የማስተዋል ሥራ የሃይማኖት አባቶች ቀዳሚ  ሥራ መሆን አለበት።ዓለሙ እንዴት እየሄደ እንዳለ እና በምን ዓይነት ደረጃ እና ፍጥነት እየተቃወሰ እንደመጣ ለእዚህ መቃወስ አንዱ ተጠያቂ የእነርሱ በአግባቡ ስራቸውን አለመስራት መሆኑን ማወቅ አለባቸው።ወደ እኛ አገር ሁኔታ ስንመለከት የሃይማኖት ቤቶችን ከመሪዎቹ ይልቅ ሕዝቡ እራሱ ወደመምራት የሄደበት፣ይህም በበቂ ደረጃ ምሳሌ የሚሆነው ሰው ከማጣት የመጣ የተስፋ መቁረጥ ስሜት መሆኑን የሃይማኖት አባቶች መረዳት አለባቸው።በክርስትና ሃይማኖት 12 ሐዋርያት ዓለምን ያውም ምንም ዓይነት  የቴክኖሎጂ መሳርያ በሌለበት ሁኔታ መቀየር ከቻሉ በእዚህ ዘመን ይሄ ሁሉ የሃይማኖት ኮሌጅ፣ቴክኖሎጂ  ባለበት ሰው እንዴት በእዚህ ዓይነት 'የዘቀጠ' የሞራል ደረጃ ወረደ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።

በአሜሪካ ሰሞኑን የሆነው በኢትዮጵያ እንዳይሆን የሃይማኖት አባቶች ምን እንስራ፣ካለፈው ስህተት ምን እናስተካክል?፣ውስጣችን ያለው ድክመት ምንድነው? መጪውን ዘመን በምገዳደር ደረጃ የሕዝቡን ስነ ልቦና እና ስነምግባር ለማነፅ ምን እናድርግ? ከሚለው ጥያቄ መጀመር ያስፈልጋል።ይህ ካልሆነ የአሜሪካው ላይ ከንፈር እየመጠጡ ከስር ያለውን አለማየት ያመጣል። ስራው የአሜሪካውን ድርጊት ከማውገዝ ይጀምራል።ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ቀደምት ከሆኑት ውስጥ ከመሆኗ ፣ለአፍሪካ እናት ከመሆኗ እና ብዙ የዓለም ጥቁር ህዝቦች በማንነታቸው መኩርያ ከማየታቸው አንፃር፣የሰሞኑን የአሜሪካው ድርጊት እንዳሳዘናት እና እንዳሳሰባት በአባቶቿ መግለጫ መስጠቷ ብዙዎች የአፍሪካ፣የአሜሪካ፣እና የላቲን አሜሪካ ጥቁሮች እና ሌሎች በእኩልነት የሚያምኑ ሁሉ ጆርዎቻቸውን እንዲሰጡ የሚያደርግ መልካም አጋጣሚ ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል።

ጊዜው ይህንን ብቻ አይደለም የሚያሳየን በአረጀ እና በአፈጀ የአስተዳደር መዋቅር እና ብስልሹ አሰራር የተተበተቡ የእምነት ድርጅቶችም ሆኑ ማናቸው የሃይማኖት አደረጃጀቶች እራሳቸውን ሳያስተካክሉ ለሌላው መድረስ ስለማይችሉ በፍጥነት እና በአጭር ጊዜ ከእዚህ አይነቱ የተውተበተበ የኃጢያት ሥራ በቶሎ ተላቀው ሕዝባቸውን በእውነት ወደማገልገል ካልመጡ ነገ በአሜሪካ የደረሰው (እኛ ጋር አልደረሰም ለማለት ባያስደፍርም) በባሰ መልኩ እንዳይመጣ ያሰጋል።ከኢትዮጵያ አንፃር ከአሜሪካም ሆነ ከሌላው ዓለም የምንለይበት ተንጠፋጥፈው  ያላለቁ መልካም ዕሴቶች አሉን።ስለኢዚህ ነው እኛ ዕድለኞች ነን ግን አሁንም የዕምነት ቦታዎቻችን በሚገባ የእራሳቸውን አስተዳደራዊ እና የገንዘብ ብክነት ችግር ካላስተካከሉ የነበረችንን መልካም ዕሴት ጭራሹን እንዳያጠፉት የቤት ስራቸውን ተግተው መስራት አለባቸው።

የፖለቲካ ድርጅቶች ምን ያድርጉ?

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ዘመኑን በዋጀ እና የአዲሱን ትውልድ ርዕይ ባገናዘበ (የአዲሱ ትውልድ ርዕይ ምንድነው? የሚለው ራሱን የቻለ ጥይቄ ሆኖ) መልኩ ለመሄድ ውስጣዊ እና ውጪያዊ ተግዳሮቶች አሉባቸው።ከእዚህ ሁሉ ችግር ጎን ግን ቢያንስ የፖለቲካ ድርጅቶቹ የሚገለጡበት አንድ አይነት ወይንም የራሳቸው መገለጫ የሆነ የኢትዮጵያን ዕሴት በተለየ የምያጎሉበት እና ይህንንም ወደ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ቀይረው ሕዝብን የመምራት አቅም ገና እየተፈጠረ እና እየዳበረ ያለ በሂደት ላይ ያለ ይመስለኛል። ምክንያቱም በአሁኑ የፖለቲካ መድረክ ላይ አብዛኛዎቹ ተዋንያኖች በ1966 ዓም በንጉሡ ስርዓት ላይ ከተነሳው ትውልድ የሆኑ ወይንም በእነርሱ ግርፍነት ፖለቲካን የተማሩ ናቸው።ስለሆነም ማኅበራዊ እና ሞራላዊ ጉዳዮች ላይ ብዙ ለማተኮር አይፈልጉም። ለእዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ወደ ስልጣን ሲመጡ ያነሱት ቤተሰባዊ፣የእናቶች ጉዳይ፣የሴቶች ጉዳይ እና ሃይማኖታዊ ዕሴቶች ሁሉ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ዓለም ከአርባ አመታት በላይ የተለዩ ስለነበሩ የአዲሱን ትውልድ ሲስቡ  ለሌሎች ደግሞ አሁንም ያልገቧቸው።

በኢትዮጵያ ከፖለቲካ ድርጅቶች መፅሐፍ ቅዱስ ማስተማር እና ስለ ቁርዓን መስበክ አንጠብቅም ከፖለቲካ ድርጅቶች የምንጠብቀው አንዲት እና አንዲት ነገር ነች።ይህችውም ሕግ ማክበር፣እንዲከበር ማድረግ እና እንዲከበር ማስደረግ ነው።የሕግ ቦዩ ከተስተካከለ እንዴት በውስጡ እንዴት እንደሚፈስ እና እንደሚሄድ ሕዝብ ያውቅበታል።አሁን በምንመለከተው ጉነታ ግን በተለይ በተቃዋሚዎች በኩል የነበረው ሕግ ያለበትን ክፍተት እንዴት እናስተካከል ብሎ እንደአንድ አገር አካል አብሮ ከማሰብ ይልቅ እንደ ሶስተኛ ወገን እራሳቸው በነበረው የሕግ ክፍተት ላይ ሌላ ስንጥር እያስገቡ ሕዝቡን ማደናበር እና ደጋፊ ለማድረግ መጣር ነው። በተመሳሳይ መንገድ በመንግስት በኩልም ሕግ የሚጥሱትን በወቅቱ ቶሎ ከመቅጣት እና እንዲታረሙ ከማድረግ ይልቅ የመዘግየት እና እንዳላዩ የማለፍ ሂደት ታይቷል።ሰሞኑን በአሜሪካ የተመለከትነው ለእኛም ትምህርት ሊሆን ይገባል።በአሜሪካ የተነሳው የሕግ እና የፍትሃዊነት ጥያቄ ነው።በኢትዮጵያም ፖለቲከኞች ከስልጣናቸው በፊት የሕግ እና ፍትሃዊነት ጉዳይን በቀዳሚነት እራሳቸው አክብረው ሌላውን ሊያስተምሩ ይገባል።

ባጠቃላይ በሰሞኑ በአሜሪካ የተከሰተው ጉዳይ የዓለሙ ወቅታዊ ሁኔታ ነፀብራቅ ነው።ክስተቱ የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የትናንት ድምር ውጤት እና የነገውንም አመላካች ነው።መንግስት፣ፖለቲከኞች እና የሃይማኖት መሪዎች እና ድርጅቶች ያልተስተካከለ አካሄድ ቆይቶ ዋጋ እንዳያስከፍል ከወዲሁ መንቃት ተገቢ ነው።በእኛ ሀገር አንፃር ብዙ መልካም ዕሴቶች አሉን።ነገር ግን እነኝህ ዕሴቶች  በሁሉም አካሎች መጠበቅ ካልቻሉ አደጋው ትልቅ ነው።ለእዚህ ደግሞ መንግስት፣የሃይማኖት አባቶች እና የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ የቤት ስራቸውን በሚገባ መስራት አለባቸው።ኃላፊነቱ ደግሞ በድምር የሚሰጥ አይደለም።የእያንዳንዱ ግለሰብ ኃላፊነት እና የስራ ውጤት ድምር ነው አገር የሚጠብቀው።ሁሉም ምን እያደረኩ ነው? የእኔ ወደ እዚህ ዓለም መምጣት ከራሴ ሌላ ለሀገሬ እና ለሕዝቤ እንዲሁ ለዓለም ሕዝብ ምን ፋይዳ አደረገ? ብሎ መጠየቅ አለበት።ጥያቄው ሁላችንንም ይመለከታል።የአሜሪካው ክስተት በኢትዮጵያ መነፀር አይቶ መመርመር እና ቀድሞ ማስተካከል ተገቢ ነው።

  
ጉዳያችን GUDAYACHN 

Sunday, May 24, 2020

በትግራይ ፀረ-ህወሓት ሕዝባዊ አመፅ መነሳቱ ተሰማ።

በትግራይ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ፀረ-ህወሓት ተቃውሞዎች ሲሰሙ ነበር።ባሳለፍነው ሳምንትመጀመርያ ላይ ግን የተቃውሞ እንቅስቃሴው በነጋዴዎች በኩል ተጀመረ።ትግራይ የአንድ የህወሓት ፊውዳል ስርዓት ሰለባ ሆናለች ያሉት ነጋዴዎች፣የፖለቲካ ስልጣን ከቀበሌ እስከ ርዕሰ መስተዳድሩ ድረስ በአንድ ቤተሰብ ስር ወድቃለች ብለዋል።ፖለቲካው ብቻ ሳይሆን የምጣኔ ሃብቱም እንዲሁ በአንድ የአቦይ ስብሐት ቤተሰብ ስር መውደቁን ነጋዴዎቹ አምርረው አስታውቀዋል።ለእዚህም በማስረጃነት ነጋዴዎቹ ያነሱት የመሶበ ሲቢንቶ ምርትን እንደማሳያነት ያወሳሉ።በመሶበ ስቢንቶ ፋብሪካ ከስራ አስኪያጅ እስከ ዘበኛ የአቦይ ስብሐት ዘመዶች መሆናቸው ሳያንስ ህዝቡ በቀነሰ ዋጋ ከቀረው የኢትዮያ ክፍል ማለትም ከዳንጎቴ፣ ሓበሻ፣ ሙገር ስቢንቶ ፋብሪካዎች የሚመረተው ምርት እንዳይገበይ የተደረገው በእዚሁ የቤተሰብ ትስስር ያለበት የህወሓት አሰራር መሆኑን ነጋዴዎቹ ተቃወሙ።በመቀጠልም ትግራይን ከአንድ አምባገነን ቡድን አገዛዝ ነፃ እንናድርጋት የሚለው እንቅስቃሴ ተጀመረ።
የትግራይ ነጋዴዎች በአመፅ ላይ  (ፎቶ አምዶም ገ/ስላሴ)

የተቃውሞ እንቅስቃሴው ቀደም ብሎ በዋናነት የተነሳበት ህወሓት የትግል መነሻዋ እንደሆነ ብዙ ጊዜ የምትኩራራበት የማይሓንሰ ደደቢት ላይ ነው።በእዚህ ቦታ ያለው ተቃውሞ ከሰላማዊ ሰልፍ ባለፈ የመንገድ የመዝጋት እንቅስቃሴ ሁሉ ያጠቃለለ ነበር። በትግራይ ሰሞኑን የነበሩት ፀረ-ህወሓት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች አድገው በአሁኑ ጊዜ ወደአጠቃላይ የተደራጀ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እየተቀየረ እንደሆነ ነው የተሰማው።

በሌላ በኩል ይሄው የትግራይ ፀረ ህወሓቱ ትግል ሕዝባዊ መሰረት ከመያዙ በላይ የራሱን አመራር እንዳደራጀ ነው የሚሰማው።በእዚህም መሰረት እንቅስቃሴው ''ፈንቅል'' የሚል ስያሜ እንደተሰጠው እና ህውሃትን መፈንቀል ዋነኛ ግቡ እንደሆነ ተሰምቷል።በመሆኑም በሽሬ እንዳስላሴ እና በዋጀራት እስከ ዛሬ ድረስ ተቃውሞው የቀጠለ ሲሆን የህዝቡ ጥያቄ ከመሰረተ ልማት ወደ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች እያደገ እና  የአስተዳደር መዋቅሮች ላይ ሁሉ ላይ ጥያቄዎች መነሳታቸው ተሰምቷል።

''እኛ በውሃ ጥም እያለቅን እነርሱ ውስኪ መሯቸዋል፣ወንድሞቻችን ዛሬም በደደቢት በረሃ እና ሌሎች ቦታዎች በህወሓት ታስረው እየተሰቃዩብን ነው  አሁን ግን ይበቃናል!'' ያሉት የሽሬ እንዳስላሴ ነዋሪ ነበሩ።ከእዚህ በፊት ለዓመታት በስማችን ነገዱ ከአሁን በኃላ ግን እንዲነገድብን አንፈቅድም ያሉት ሌላው የሽሬ እንዳስላሴ ነዋሪ፣በቅርቡ ትምህርት ቤት እንዲሰራ በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው መሰረት ድንጋይ ተጥሎ  እና ገንዘቡ ለክልሉ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ገቢ ተደርጎ የውሃ ሽታ መሆኑን ለአብነት ያነሳሉ።ፋና ብሮድካስቲንግም የቀዳማዊ እመቤት ፅህፈት ቤት ገንዘቡን ለክልሉ ገንዘብ እአ ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ገቢ መደረጉን እንዳረጋገጠለት ዛሬ ማምሻውን ገልጧል።በሌላ በኩል የተቃውሞውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ፋና ከትግራይ ተቃዋሚ ወጣቶች የደረሰው መረጃ አስመልክቶ እንደዘገበው የክልሉ መንግስት ነዋሪዎቹ ለሚያነሷቸው ረጅም ዓመታት ለፈጁ ጥያቄዎች ምላሽ የማይሰጣቸው ከሆነ የፌዴራል መንግስት ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንደመሆናችን ለጥያቄዎቻችን ምላሽ ያሰጥልን ሲሉም ሃሳባቸውን ገልጸዋል።

ህወሓት በትግራይ ሕዝብ ላይ ለሰራችው ግፍ ማስፈራርያ የምትጠቀመው የኤርትራ መንግስት ሊወረን ነው የሚል ነበር።ሆኖም ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ስያሻሽሉ ሌላው ብሔር ትግራይ ላይ ሊዘምት ነው የሚል ሰፊ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ሕዝቡን ለማደናበር ሙከራ አደረገች።በእዚህም ሳብያ ከአንዳንድ ቦታዎች ትግርኛ ተናጋሪዎች ለቀው እንዲወጡ የሚል ትዕዛዝ ሳይቀር አሰራጨች። ሆኖም የህወሓት ወሬ ሐሰት መሆኑ ሲጋለጥ የበለጠ ማጣፍያው አጠራት።አሁን ሕዝቡ ለራሱ  ቀዳሚ አደጋ ህወሓት መሆኗን ከምንግዜውም በላይ ተገነዘበ።እነሆ ፈንቅል የተሰኘው ሕዝባዊ አመፅ በይፋ ተጀመረ። 

በእዚህ ሳምንት ከነበሩት ተቃውሞዎች ውስጥ ጥቂቱን በፎቶ ከስር ይመልከቱ።
በደደቢት የነበረው ተቃውሞ (ፎቶ አምዶም ገብረስላሴ ገፅ የተገኘ)
ተቃውሞ በወጀራት (ከአምዶም ገብረስላሴ ፎቶ)





ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Saturday, May 23, 2020

የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መደመር የተሰኘው መፅሐፍ በድምፅ ቀርቦልዎታል።ያድምጡ!

የጉዳያችን ማስታወሻ
**************
ኢትዮጵያውያን በእየዘመናችን ለአገራቸው ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም የሚተርፍ ዕውቀት፣ብልሃት እና አርቆ ማስተዋል የታደሉ ሰዎች ተነስተውላታል።በቅርብ ዘመን ብናነሳ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሃብተወልድ እና ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴን መጥቀስ ይቻላል።ሁለቱም አፍሪካን ጨምሮ በመላው ዓለም ዛሬም ድረስ የተከበሩ ናቸው።ሁለቱም መላ ዘመናቸውን ለኢትዮጵያ ሲሰሩ ቢኖሩም ሕይወታቸው ያለፈው ግን በኢትዮጵያውያን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር  አክሊሉ ህዳር 14/1967 ዓም ከስልሳዎቹ ጋር በጥይት ተደብድበው ሞቱ።አፄ ኃይለስላሴም እንዲሁ በምስጢር ተገድለው 17 ዓመት ሙሉ ከቤተመንግስት ስር ተቀብረው ኖሩ።እኛ እንዲህም ነን።እራሳችንን በራሳችን እጃችንን የምንቆርጥ።ዛሬም በአፄ ምንሊክ ላይ የሚከራከር ትውልድ፣ አክሊሉ ሀብተወልድንም ሆነ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴን ቢያገኝ ከመስቀል የማይመለስ ትውልድ ተዋፅኦም ነን።ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እና ሰላም ቤተሰባቸውን በትነው በረሃ የወረዱት አንዳርጋቸው ፅጌንና ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአግባቡ ማክበር ያቃተው ትውልድ የቀደሙትን ከመስቀል የማይመለስ ነው።እኛ እንዲህም ነን።በእርግጥ ሁላችንም እንዲህ አይደለንም።ታሪካችን ላይ ግን እንዲህ ዓይነት ክፉ ታሪኮችም አሉብን።ቁምነገሩ ካለፈው ስህተት ዛሬ ምን ተማርን? ነው።

በዘመናችን ከተነሱት ነገን የሚመለከቱ ብቻ ሳይሆን በአጭር ጊዜ ዓለም ያደነቃቸው እና ከፍተኛውን የኖቤል ሽልማት ያጎናፀፋቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ ለአንዳንዶች ዛሬም እንደቀደሙት ዕንቁዎቻችን ካለ በቂ ምክንያት ''በውሃ ቀጠነ'' ጉዳይ ሊያጣጥሉ ሲሞክሩ ያለፈው የታሪካችን ጠባሳ እንዳይደገም ብለው ለአፍታም ያህል እያሰቡ አይመስልም።እስኪ ቢያንስ በእዚህ ዘመን ያለን እንንቃ! ሃሳቦችን በመመርመር እና በመተቸት ላይ የተመሰረተ ስብዕና እናዳብር።
*************
የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ መደመር መፅሐፍ በድምፅ ለመከታተል ወይንም ወደ ኮምፕዩተርዎ ወይንም ስልክዎ ለማውረድ (''ዳውንሎድ'' ለማድረግ) ይህንን ገፅ ይክፈቱ እና ያዳምጡ።
ገጹን ለመክፈት ይህንን ይጫኑ >> https://medemer.et/am/book/?fbclid=IwAR1VOjUk_2anOT8hP0L9nXAWMU0bzk6DqyrNswRLxQUAFiQ5bzLvynPc2XE

ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት 
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant
Gudayachn Multimedia, Kommunikasjon og Konsultent 

Friday, May 22, 2020

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግስት ለጣና ሐይቅ እንቦጭ አረም አደጋ ምን ያህል ትኩረት ሰጥቶታል? ጣና እየታዘበ ነው።

የእንቦጭ አረም ነቀላ በጣና ሐይቅ ዙርያ 

ጉዳያችን ልዩ 
በእዚህ ፅሁፍ ስር የሚከተሉትን ንዑስ ርዕሶች ያገኛሉ።እነርሱም - 

>> የፌድራል መንግስት የጣና ሐይቅ የአረም ብክለትን በተመለከተ ምን እየሰራ ነው?
>> የአካባቢ፣የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ጉዳይ፣
>> የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ መስርያቤት የማስፈፀም አቅም ከአፍሪካውያን ጋር ሲነፃፀር 
*********

የአካባቢ፣የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ጉዳይ 

በኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ላይ ግዙፍ አደጋ ከጋረጠው ቀዳሚ የአካባቢ ጥበቃ አደጋ ውስጥ በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተው የእንቦጭ አረም አንዱ ነው።ሐይቅ እንክብካቤ ከተነፈገው ይጠፋል።የሐረማያ ሐይቅ ከጥቂት ዓመታት በፊት የሆነውን መመልከቱ በቂ ነው።በሐረማያ ሐይቅ ላይ አደጋ እንደተጋረጠ የጥናት ውጤቶች ከዓመታት በፊት ለመንግስት እንዲያውቀው አድርገው ነበር።ሆኖም ግን የተወስደ እርምጃ ካለመኖሩ እና የተደረጉ ጥረቶችም ከዘገዩ በኃላ በመደረጋቸው አሁን ላለበት አደጋ ተጋልጧል።ኢትዮጵያ ካሏት ሃይቆች ውስጥ የሐዋሳ ሐይቅ፣የጣና ሐይቅ፣የዝዋይ ሐይቅ እና ሌሎችም ውስጥ የሐረማያ ሐይቅ ወደ ድርቀት ተቀይሮ፣ዛሬ ድካሙ ሁሉ ሐይቁን ወደነበረበት እንዴት እንመልሰው? የሚል ነው።

የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 9/1987 ራሱን ችሎ በፌደራል የመንግስት መስሪያቤትነት የተመሰረተ ነው።መስርያቤቱ ''ዘላቂ የአካባቢና የደን አያያዝ፣ ልማትና አጠቃቀምን በማረጋገጥ በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን የገነባች መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር ሆና ማየት'' የሚል ርዕይ ያለው ሲሆን  ከተልኮው ውስጥ ደግሞ ''ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን  ለመገንባት የሚያስችሉ የአካባቢ ጥበቃና የደን ሃብት አያያዝ፣ ልማትና አጠቃቀም ለዛላቂ ልማትና ለድህነት ቅነሣ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የአካባቢ ሥርዓቶችን ማዘጋጀትና ተፈፃሚነታቸዉን ማረጋገጥ'' የሚል ይገኝበታል።

ከመስርያቤቱ  ስልጣን እና ተግባር ውስጥ ደግሞ  ''የሀገሪቱን የአካባቢና የደን እንዲሁም ለአየር ንብረት ለዉጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን በሚመለከት ዘገባን በየወቅቱ እያዘጋጀ ያሰራጫል፣'' የሚል ይገኝበታል። በተጨማሪም መስሪያ ቤቱ የአካባቢ ፖሊሲና ህጎችን፣ የተፈጥሮ ሃብት ስነህይወታዊ ስርዓቶችን የሚያስጠብቁ ደረጃዎን በማውጣት፣ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማን በመከታተል እና የአካባቢ ጥበቃን በሚመለከት ሀገሪቱ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በስራ ላይ መዋላቸውን ከትትል የማድረግ ስልጣን እና ኃላፊነትም ተሰጥቶታል፡፡

የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ መስርያቤት የማስፈፀም አቅም ከአፍሪካውያን ጋር ሲነፃፀር 

ብዙ የአፍሪካ አገሮች ከጎረበቶቻችን ጀምሮ ቀድመውን የሄዱት እና በእኛ ሀገር ፖሊሲ እና መመርያ ወጥቶለታል ቢባል በቂ ግንዛቤ በሕዝቡ ዘንድም ሆነ የማስፈፀም ስልጣን ከክልል እስከ ፌድራል በተገቢ ደረጃ የሌለው የአካባቢ ጥበቃ መስርያቤት በመንግስትም ሆነ በግል ሚድያዎች ድምፁ አይሰማም።ኢትዮጵያ ግን በዓለም ላይ በተደጋጋሚ በድርቅ ከሚጠቁት አገሮች ውስጥ ነች።በእርግጥ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በአካባቢ ጥበቃ ላይ በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ አላት።ሆኖም ግን በአገር ውስጥ የሚሰሩ ልማቶች እና አዳዲስ የንግድ ፈቃዶች በአግባቡ እና ደረጃውን በጠበቀ ደረጃ የአካባቢ ተፅኖ ግምገማ (Environmental Impact Assessment -EIA) በምን ያህል ጥብቅ በሆነ መንገድ ይደረጋል? መልሱን በዘርፉ ላይ ላሉት እተወዋለሁ።ሆኖም ግን አንድ ነገር ማለት ይችላል።እስካሁን በኢትዮጵያ ለሚደረጉ አዳዲስ የፕሮጀክት ፍቃዶች ያጨቃጨቁ ፕሮጀክቶች አልተሰሙም።በሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንደ ኬንያ፣ዑጋንዳ እና ታንዛንያ የፕሮጀክት ፍቃድ ከአካባቢ ጥበቃ መስርያቤት ማግኘት ከባንክ የንግድ ሥራ ዕቅድ (Business Plan) አቅርቦ ብድር ከመጠየቅ በላይ አስጨናቂ የሚሆንበት ምክንያት አለ።ለእዚህ ምክንያቱ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ፖሊሲ እና መመርያ በአግባቡ ስለሚተገበር እና መስርያቤቶቹ የማስፈፀም አቅማቸው በሕግ ከለላ ጥብቅ በመሆኑ  እና ባለሙያዎቹም የሚጠቀሙት ዝርዝር መመርያ በአግባቡ ሥራ ላይ ስለሚያውሉት ነው።


በኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ በተመለከተ ያሉት ችግሮች አራት ናቸው።እነርሱም በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያለው ግንዛቤ በሕዝቡ ዘንድ ዝቅተኛ መሆን፣ በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ በአግባቡ ገብቶ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ አለመሰጠቱ እና የሚመለከተው መስርያቤትም የማስፈፀም አቅም ማነስ እና በቂ የሰው ኃይል አለመኖር ነው።የማስፈፀም አቅም ሲነሳ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የአካባቢ ጥበቃ መስርያቤት የከለከላቸው ፕሮጀክቶች በሀገሪቱ ፓርላማ ካልሆነ ማንም እንደፈለገ ሊወስንባቸው የማይችልበት አሰራር የዘረጉ የአፍሪካ አገሮች መኖራቸውን ማስገንዘቡ አንዱ ማሳያ ነው።በዑጋንዳ ከአስር ዓመት በፊት በዋና ከተማዋ ካምፓላ በነበረ ረግረግ ውሃማ ቦታ ደልድሎ ለጎልፍ መጫወቻ ለማድረግ የከተማው ምክር ቤት  ፈቅዶ የአካባቢ ጥበቃ መስርያ ቤት በመከልከሉ ጉዳዩ እስከ ፓርላማ ደርሶ የወራት ክርክር ተደርጎበት ፓርላማው ቦታው እንዳይነካ  የወሰነበትን ጉዳይ የእዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ያስታውሳል።የአፍሪካ አገሮች የአካባቢ ጥበቃ መስርያቤቶች  ምን ያህል የማስፈፀም አቅም እንዳላቸው በእዚህ መገንዘብ ይቻላል።በነገራችን ላይ የአካባቢ ጥበቃ መስርያ ቤቶች የተፈጥሮ ሃብትን ብቻ ሳይሆን የድምፅ ብክለት በተመለከተ መግለጫ የሚያወጡ የአካባቢ ጥበቃ መስርያ ቤቶች ያሉባት አህጉር ነች አፍሪካ።ከአፍሪካዎች የምንወስደው ብዙ ልምድ አለ።ችግሩ ግን በአንዳንድ ጉዳዮች በጣም መራመዳቸውን አለመስማታችን ነው። ኢትዮጵያ የምትሻልባቸው ጉዳዮች የመኖራቸውን ያህል የአፍሪካ አገሮች ቀድመው የሄዱበት ዘርፎችን መለየት ተገቢ ነው።

የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ መስርያ ቤት በጣና ሐይቅ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም በተመለከተ የዓማራ ክልል ቅርንጫፍ መስርያቤቱ ከሚሰጠው አንዳንድ መግለጫዎች ባለፈ ለእዚህ ዓይነት ግዙፍ አደጋ ምን እየሰራ እንደሆነ ግልጥ አይደለም።ከመስርያቤቱ ባለፈስ የፌድራል መንግስት ምን እያደረገ ነው?

የፌድራል መንግስት የጣና ሐይቅ የአረም ብክለትን በተመለከተ ምን እየሰራ ነው?

የአካባቢ፣የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በጣና ሐይቅ ላይ የተፈጠረውን አረም (ይሄው ወደ ሶስት ዓመት ሆኖታል) ተከታታይ የትግበራ እና ክትትል ሪፖርት ሲያወጣም ሆነ ችግሩን ለመፍታት የመሪነት ሚና ሲወጣ አይታይም።በእርግጥ መስርያ ቤቱ በእየክልሎች መዋቅር አለው።በክልል ደረጃ ብቻ የማይፈታ ችግር ግን ብሔራዊ መፍትሄ ይፈልጋል።አሁን ባለው ሁኔታ የጣና ሐይቅ አረም ችግርን ለመፍታት ሲዋትቱ የሚታዩት፣የእነርሱ ብቻ አደጋ ይመስል የአካባቢው ነዋሪዎች እና ግለሰቦች ናቸው።ጉዳዩ ግን ብሔራዊ ጉዳይ ነው።አሁን ባለንበት ዘመን የጣና ሐይቅ ችግር የመላዋ ኢትዮጵያን የአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን እስከ ግብፅ እና ሱዳን ድረስ ያለውን ስነ-ምሕዳር ላይ ሁሉ ተፅዕኖ ይኖረዋል።

የጣና ሀይቅ አረም በተመለከተ በርካታ ብጥስጣሽ ዜናዎች ሰምተናል።ገበሬዎች እና ተማሪዎች ውሃው እስከ አንገታቸው ድረስ እየዋጣቸው በጥንታዊ አሰራር መንገድ አረሙን ስነቅሉ የማኅበራዊ ሚድያው እያዳነቀ የአንድ ሰሞን ርዕስ ሆኗል።አንድ ጊዜ ደግሞ በውጪ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በመቶ ሺህ ዶላር እንዳዋጡ ተነገረ።ሌላ ጊዜ ደግሞ አረሙን የሚያጠፋ መድሃኒት በምርምር ተገኘ ተባለ፣አዲስ ማሽንም ተፈበረከ፣እገሌ የተባሉ ባለሀብት አዲስ ማሽን አስረከቡ ተባለ።ሆኖም ግን የዛሬ ሦስት ዓመት የሐይቁ 50 ሺህ ሄክታር በአረሙ መሸፈኑ እንደተነገረ ሁሉ (ሪፖርተር፣ጁላይ 12/2017 ዓም እኤአ) ዛሬም አረሙ ተባብሶ መቀጠሉ እየተነገረ ነው።ቢቢሲ የአማርኛው አገልግሎት ግንቦት 14/2012 ዓም ባስተላለፈው ዘገባ የጣና ሐይቅ እንቦጭ አረም መባባሱን እና ሰፊ ቦታ እያካለለ መሆኑን ዘግቧል።በአሁኑ ሰዓት ችግሩን ያባባሰው ደግሞ ከእዚህ በፊት ያቅሙን አረሙን ለማጥፋት  የሚጥረው ሕዝብ (ብዙ ለውጥ ባያመጣም) በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ምንም ማድረግ ባለመቻሉ ነው።

በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ጉዳዩን አስመልክተው ችግሩን ለመፍታት በምርምር የተደገፈ ሥራ ይሰራል ማለታቸው ይታወሳል።አሁን ጉዳዩ ምን ላይ ደረሰ? ይህ ብሔራዊ አደጋ በየትኛው የብሔራዊ መስርያቤት እየተማራ ነው።ችግሩ በዓማራ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ብቻ እንደማይፈታ ግልጥ ነው።የፌድራል መንግስት ችግሩን ለመፍታት የማስተባበር ሥራ መስራት የለበትም ወይ? ለተወካዮች ምክር ቤት ችግሩን እና ችግሩን ለመፍታት የተወሰዱ ተግባራት እና ግምገማ ቀርቦ ለውይይት ቀርቧል ወይ? የመረጃ ክፍተቱ ትልቅ ነው። ችግሩ ብሔራዊ እስከሆነ ድረስ ብሔራዊ መፍትሄ ይፈልጋል።

በእርግጥ ከችግሩ ግዝፈት የተነሳ ስራው ከፍተኛ በጀት እና የሰው ኃይል ይጠይቃል።ሆኖም ግን የአካባቢ ጥበቃ ችግሮች ዓለምአቀፋዊ ከመሆናቸው አንፃር ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ሆኑ ሌሎች አገራት የእዚህ ዓይነቱን ችግር ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ለመፍታት የሚሰሩ ስራዎችን በገንዘብ ለመደገፍ ወደኃላ እንደማይሉ ይታወቃል።የጣና ሐይቅ በተመለከተ ያለው መሰረታዊ ችግር ለመፍትሄው የሚንቀሳቀስ ማዕከላዊ አስተባባሪ ከፌድራል መንግስት አለመኖሩ ነው።ይህ በራሱ ትልቅ ስብራት ነው። ግለሰቦች ከአሜሪካ እስከ ጎንደር ጥረት ሲያደርጉ እንቅስቃሴውን በማዕከልነት ሰብስቦ የሚሰራ የፌድራል ቢሮ እንዴት አይኖርም? የአካባቢ፣የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አልፎ አልፎ በዓማራ ክልል ቢሮው ከሚላቸው አንዳንድ ጉዳዮች ውጪ ከፌድራል መንግስት ጋር በመሆን ዘላቂ የመፍትሄ ዕቅድም ሆነ የተግባር ክትትል ሪፖርቱ በድረገፁም ላይ አላስቀመጠም።

ባጠቃላይ የጣና ሐይቅ እምቦጭ ዓረም ጉዳይ የፌድራል መንግስት በኃላፊነት ሊሰራቸው ከሚገባቸው ብሔራዊ ጉዳዮች ውስጥ መግባት ያለበት እንጂ ለክልል የሚተው ጉዳይ አይደለም።ችግሩን በአንድ ወቅት ከማንሳት ባለፈ እስካሁን ምን እንደተደረገ፣ ምን እንዳልተደረገ እና ጉዳዩን በማዕከል የሚያስተባብረው መስርያቤት ማን እንደሆነ ለማወቅ ሳይቀር ለሕዝብ እንግዳ ጉዳይ ሆኗል።ይህ አሳዛኝ ጉዳይ ነው።በተለያየ ቦታዎች የሚደረጉ ጥረቶችን በማዕከልነት አምጥቶ መስራት እንዴት እንዳልተቻለ በራሱ ጋራ ያጋባል።በኢትዮጵያ የዛፍ መትከል ጥሩ ተግባር ከአለፈው ዓመት ጀምሮ እያየን ነው።ይህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ሥራ በእዚህ ዓመትም እንደሚቀጥል ይታወቃል።ይህ በራሱ መልካም ተግባር ሆኖ የነበረውን የኢትዮጵያ ስነ-ምሕዳር ከመመለስ ጎን ለጎን ያለውን መጠበቅም ሊዘነጋ አይገባውም።ጣና እየታዘበ ነው።


ጌታቸው በቀለ 

Monday, May 18, 2020

የዓባይ ግድብን፣የሱዳን እና የአፍሪካን ቀንድ በተመለከተ የተጠናቀረ - ልዩ ወቅታዊ


ሰኞ ግንቦት 10/2012 ዓም 
=================
በእዚህ ዘገባ ስር የሚከተሉትን ርዕሶች ስር ማብራርያ ያገኛሉ።
>> የዓባይን ግድብ ውሃ ሙሌት በተመለከተ ኢትዮጵያ ቁርጥ ያለ መልስ በውጪ ጉዳይ በኩል ሰጥታለች

>> የሱዳን ልዑክ በኢትዮጵያ ስለ ምን ተወያየ? የሱዳን በግድቡ ጉዳይ የመዋዥቅ ምክንያት

>> በግድቡ ዙርያ የኤርትራ ግልጥ አቋም ምንድነው? ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በው ጪ ጉዳይ እና በወታደራዊ ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም ቶሎ የመድረሳቸው አስፈላጊነት

>> የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ አጣብቂኝ ውስጥ እንዳይገባ ኢትዮጵያ አጥብቃ መከተል ያለባት መንገድ

******************
የዓባይን ግድብ ውሃ ሙሌት በተመለከተ ኢትዮጵያ ቁርጥ ያለ መልስ በውጪ ጉዳይ በኩል ሰጥታለች 

ግብፅ የዓባይን ጉዳይ ፖለቲካዊ ለማድረግ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ብትመራውም በዓለም ላይ ቁጥር አንድ ለሆነው ለኮሮና ወረርሽኝአንድ ጊዜ ብቻ እንደተነጋገረ የሚወራለት ምክርቤቱ በዓባይ ጉዳይ ላይ ገፍቶ የሚሄድበት ምንም መንገድ ሊኖር እንደማይችል የብዙዎች ግምት ነው።በእዚህ ላይ በፀጥታው ምክርቤት አባላት ውስጥ ያለው ወቅታዊ ፍጥጫም፣ እንበል አሜሪካ ጉዳዩን አሁን ብታነሳው የግድቡ ጉዳይ የመካከለኛው ምሥራቅን  በተዘዋዋሪ የመቆጣጠር ጉዳይ ስለሆነ ቻይናም ሆነች ሩስያ ጉዳዩ ላይ እንዲገቡ ዕድል የሚሰጥ ስለሆነ ቢያንስ አሜሪካ በተወሰነ ደረጃ የቅርቦቹ ውይይቶች ላይ ስለነበረች ከእጄ የወጣ ጉዳይ ነው የማለት ያህል ቢያንስ አሁን የፀጥታው ምክር ቤት የሚነሳበት ''ወርቃማ'' ጊዜ እንዳልሆነ ማሰብ ያቅታታል ማለት አይቻልም።ስለሆነም መንገዶች ሁሉ የሚያሳዩት ዝናቡን ለመምጣት ያበቃው እንጂ ኢትዮጵያ በትክክል ግድቡን የመሙላት ስራዋን በፍጥነት መጀመር የኢትዮጵያ ወርቃማ ጊዜ እንደሆነ ነው።

 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ አምሳሉ ትዛዙ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት ''የግድቡን ውሃ  በተመለከተ ለእነርሱ(ለግብፆች እና ሱዳኖች) ማሳወቅ አይጠበቅብንም።ግድቡ ስራው  ሲደርስ ውሃ መሙላት ቀጣዩ ሥራ እንደሆነ እነርሱ  የሚያውቁት ጉዳይ ስለሆነ እኛ ማሳወቅ ያለብን ጉዳይ አይደለም።ውኃ የመሙላቱ ሂደት የግንባታው አካል እንደሆነ እና ግንባታው የሆነ ደረጃ ሲደርስ ውሃ እንደሚሞላ ያውቃሉ።'' ብለዋል።
There is no way that we have necessarily inform them (Egypt and Sudan) when we will start filling. Nothing is expected of us with regard to the filling of dam. This is because they know that will happen when construction of the dam reaches at a certain level and after all it is being built to be filled. We do not have the obligation of informing,” Amsalu Tizasu spokesman of Ethiopian foreign Affairs minister.

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ አምሳሉባለፈው ዓርብ ግንቦት 7/2012ዓም  በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላይ በተለቀቀው  መግለጫቸው ላይ በግልፅ ደግመው እንዳሳወቁት ''ኢትዮጵያ የውሃውን ሙሊት በተመለከተ ማሳወቅ ያለባት ምንም መንገድ የለም'' ብለዋል።
“There is no way that we have necessarily inform them when we will start filling.''

የግብፅ ለፀጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ማስገባቷን አስመልክተው ቃል አቀባዩ ሲናገሩ።የግብፅ ደብዳቤ በነበረው የድርድር ሂደት ላይ ምንም የሚያመጣው ውጤት አይኖርም ካሉ በኃላ ኢትዮጵያ ለግብፅ ደብዳቤ ምላሽ እንድትሰጥ በግልጥ እስካሁን ከማንም አካል አልተጠየቀችም ሆኖም ግን እኛ ለምላሽ የሚሆን የዲፕሎማሲ ሕግ ባለሙያዎቻችን እና የውሃ ኤክስፐርቶቻችን የተሳተፉበት ዝርዝር መረጃ የያዘ ዶክመንት አዘጋጅተናል አስፈላጊው የመንግስት ውይይት አድርገን በቶሎ የሚላክ ነው'' ብለዋል።

የሱዳን ልዑክ በኢትዮጵያ ስለ ምን ተወያየ? ሱዳን በግድቡ ጉዳይ የሱዳን መዋዥቅ ምክንያት 

ይህ በእንዲህ እያለ የኢትዮ-ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተለይ በድንበር ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ኢትዮጵያ የገባ እና ካለፈው ሳምንት ማገባደጃ ጀምሮ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ጋር መወያየቱ በመቀጠልም በዝርዝር ጉዳዮች ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ለሁለት ቀናት ተወያይቷል።ውይይቱ ዛሬ ሰኞ ማምሻውን ያበቃ ሲሆን  ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውይይቱ መጠናቀቁን አስመልክቶ የተገኘው ቃል እንዲህ ይላል - 
''በሁለቱ ወገኖች በተደረገው ውይይት በተለይ በሁለቱ አገራት አዋሳኝ አካባቢዎች በየጊዜው የሚያጋጥሙ የጸጥታና የደህንነት ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ እና የሁለቱን አገሮች የድንበር ጉዳይ በተመለከተም የህዝቦችን አብሮነትና የግንኙነቱን ታሪካዊ ዳራ ግምት ውስጥ በማስገባት ማስቀጠል የሚያስችል ውይይት ተካሂዷል።
ውይይቱ በሁለቱ አገራት አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፤ ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውር፣ አፈናና የመሳሰሉ ህገ ወጥ ድርጊቶችን በጋራ ለመከላከልና መፍትሄ ለመሻት የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጧል። በአካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች ተረጋግተው ያለምንም መስተጓጎል የእርሻ ስራቸውን መቀጠል እንዳለባቸው እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ የመጣ የደህንነት ስጋት እና የነዋሪዎችን የተረጋጋ ህይወት የሚያውኩ አዳዲስ የጸጥታ ሃይል እንቅስቃሴዎች በአፋጣኝ እንዲስተካከሉ በተደረገው ውይይት የጋራ ግንዛቤ ተይዞበታል''
የዛሬው ውይይት መደምደምያ ላይ የታወቀው ሌላው ጉዳይ፣ የኢትዮ-ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ስብሰባ በሰኔ ወር 2012 ዓም አጋማሽ በካርቱም ላይ ለማድረግ መስማማታቸው ነው።።ሱዳን በግድቡ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በውስጥ ፖለቲካ እየተናጠች በመሆኗ ወጥ የሆነ አመለካከት በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ላይ ለመያዝ ተቸግራለች።የሽግግር መንግስቱ ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት እያያሻሻለ ቢመጣም፣ሱዳንን እንደ ዋና የውጭ ፖሊሲያቸው ማስፈፀምያ ሊጠቀሙ የሚፈልጉ ኃይሎች በተለይ ቱርክ፣ግብፅ፣ሳውዲአረብያ እና ኩዋታር አዲሱን የሱዳን መንግስት በሚፈልጉት መልክ ለመቅረፅ ወይንም አዲስ መፈንቅል አድርገው ሌላ የሚመቻቸውን መንግስት ለማምጣት ሩጫ ላይ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።ስለሆነም የሱዳን መንግስት ሁለት፣ሶስት ዓይነት ካርዶችን የሚጫወተው በውስጡ ካሉት የተለያዩ ኃይሎች ፍላጎት ጉተታ አንፃር መሆኑን መረዳት ይቻላል። ባለፈው በአረብ ሊግ ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ላይ የሚያድም ሰነድ ላይ ያለመፈረም ቆራጥ እምቢተኝነት ያሳዩትን አመለካከት አሁን ለመድገም የተቸገሩት ከእዚህ አንፃር እንደሆነ መገመት ይችላል።
ይህ ማለት ግን ሱዳን አደገኛ አካሄድ አትሄድም ማለት አይደለም።ምክንያቱም ሱዳን የውክልና ጦርነት ወይንም ግጭት ከኢትዮጵያ ጋር እንድታደርግ እና ኢትዮጵያን እንድትረብሽ ጦርነቱን ተከትሎ የሚመጣወጪ ብቻ ሳይሆን ሌላ ጠቀም ያለ ድጎማ ለመስጠት የምያባብሉ አገራት አሁንም የሉም ማለት ሞኝነት ነው።ሰሞኑን የሱዳን ከፍተኛ ልዑክ በኢትዮጵያ መጥቶ የሚወያየው ከእዚህ በፊት ቀዝቀዝ ብሎ የነበረውን የድንበር ጉዳይ እንደ አዲስ እንዲያነሱ ከመካከለኛው ምስራቅ አለቆቻቸው የተሰጣቸው የቤት ሥራ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ማንም የሽግግር መንግስት የድንበር ጉዳይን እንደ አፋጣኝ አጀንዳ አድርጎ የማንሳት ልማድ በብዙ አገሮች አይታይም። በሽግግር ወቅት ከሁሉም ጋር ሰላማዊ ሁኔታ መፍጠር የተለመደ ነው።ስለሆነም የሱዳን ተለዋዋጭ ሁኔታ በቀጣይ ቀናትም ሊቀጥል ይችላል።

በግድቡ ዙርያ የኤርትራ ግልጥ አቋም ምንድነው? ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በው ጪ ጉዳይ እና በወታደራዊ ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም ቶሎ የመድረሳቸው አስፈላጊነት
የዓባይን ግድብ በተመለከተ አቶ ኢሳያስ እስካሁን በግልጥ የተናገሩት ጉዳይ ብዙም ለአደባባይ አልበቃም።በእርግጥ አቶ ኢሳያስ በእዚህ ዓይነት ወሳኝ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተቃራኒ ቦታ ይይዛሉ? ወይንስ አይዙም? ሱዳንን ለማባባል እንደተሞከረ እሳቸውንስ ላይ ሙከራው የለም? እዚህ ላይ አንድ መሰረታዊ ጉዳይ አቶ ኢሳያስን ያህል የመካከለኛውን ምስራቅ ስነ ልቦና የሚያውቅ ላይኖር ይችላል።ከሱዳን ያአሁኑ መሪዎች በላይ ጥርሳቸውን የነቀሉበት ጉዳይ ነው።አረብኛ ተናጋሪው ኢሳያስ በጀብሃ ላይ እርምጃ ከተወሰደ በኃላም ሆነ በፊት ካይሮ የውሃ መንገዳቸው ብቻ ሳትሆን የመጀመርያ የድርጅታቸውን ካፒታል ካይሮ ላይ በተከፈተ የነዳጅ ማደያ ንግድ የጀመሩ ናቸው።ሰውየው የአረቦችን እጅ የመልመዳቸውን ያህል ተንኮላቸው እና ልባቸውን ያውቁታል።ስለሆነም በኢትዮጵያ ላይ ቀንደኛ አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች እና የሱዳን የከሰሩ ባለስልጣናት ሳይቀሩ ከእዚህ በፊት ምን ያስቡ እንደነበር አሁንም ምን ዓይነት ተንኮል እንደሚያውጠነጥኑ ያውቃሉ ወይንም ካለፈ ልምድ ግምታቸው ለእውነት የቀረበ ይሆናል።
አሁን ጥያቄው ለኢሳያስ ውሃ፣ የእርሻ ምርት፣ትልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል የምታመነጭ እና ከመቶ ሚልዮን ሕዝብ በላይ የገበያ ዕድል ያላት ኢትዮጵያ ነች ወይንስ በሶስት ጎራ ተከፍሎ ሊራኮት ጫፍ የደረሰ እና የኃይል ምንጩ ነዳጅ በሌላ ኃይል እየተቀየረ ያለው የመካከለኛው ምስራቅ ነው ለነገ የሚያዋጣው? የሚለው ነው።የእዚህ መልስ ለአቶ ኢሳያስ ግልጥ ነው።ይህ ሲሆን ግን አንዳንድ ነገሮችን በማቀበል ከኢትዮጵያ በኩል ሳይታወቅ የሚሰሩት ሥራ የለም ብንል እራስን ማታለል ነው።ሆኖም ግን ከእዚህ ባለፈ በተቃራኒ የሚቆሙበት ምንም ሜዳ ግን አይኖርም።
አንዳንዶች አሁን በአቶ ኢሳያስ እና በኢትዮጵያ መሃከል ያለው መልካም ግንኙነት አቶ ኢሳያስ ስሌት የተሳሳተ አድርገው ያስባሉ።አቶ ኢሳያስን የሚወቅሱት ደግሞ ከአቶ ኢሳያስ የባሱ የመገንጠል ዘብ የቆሙ በራሳቸው ዙርያ ያሉ ባለስልጣኖቻቸው ናቸው። እዚህ ላይ ኢትዮጵያ ወደብ የማግኘቷ ሂደት እና በዝርዝር የኢኮኖሚ ግንኙነት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ መንግስት በሚያደርጋቸው ንግግሮች ላይ ነገሩ ቀስ እንዲል የሚጥሩ አሉ።ሆኖም ግን እዚህ ላይ አቶ ኢሳያስም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አልተሳሳቱም።ይልቁንም ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለራሳቸው ሲሉ የጋራ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ እና የጋራ መከላከያ ስምምነት በፍጥነት መፈራረም አለባቸው። ምክንያቱም አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ ፅንፍ ኃይሎች ሁለቱን ማለያየት የመጀመርያ ምዕራፍ፣በመቀጠል ደግሞ ሁለቱንም ማጥፋት አጀንዳቸው ከሆነ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ሆኖታል።የኤርትራን መገንጠል በገፍ በደርግ ዘመን ሲደግፉ የኖሩትም ከእዚሁ ምዕራፍ አንድ ስልት አንፃር ነበር።አሁን በድንገት ሁለቱ አገሮች መግጠማቸው የቀይ ባህር ጉዳይ ከእጃቸው እንደሚወጣ ያስባሉ።አቶ ኢሳያስ አንድ ሺህ ኪሎሜትር የምያካልለውን የቀይ ባህርን የመቶ ሚልዮን ሕዝብ ባለቤት ከሆነች ኢትዮጵያ ጋር ሆነው ካልሆነ መጠበቅ እንደማይችሉ ሁሉም ያውቀዋል።በእዚህ ላይ አቶ ኢሳያስን የሃማሴን ደገኛ እና የቆላው ኤርትራ በሚል በውስጣቸው ለመከፋፈል እና ኤርትራ ላይ የፅንፈኛ መንግስት ለማቆም እነኝህ ፅንፈኛ አገሮች ብዙ ጊዜ ሞክረዋል። ሙከራው የመፈንቅለ መንግስት እስከማድረግ የደረሰ እና አሁንም ድረስ ያልቆመ የውስጥ ውጥረት ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ የአሁኑ ግንኙነት ወደበለጠ ደረጃ ማደግ ሳይወዱ በግድ ማድረግ ያለባቸው ይህ ካልሆነ ግን ከፍተኛ የውጭ ጥቃት ሁለቱንም ሊያጋጥማቸው ይችላል።
ስለሆነም አቶ ኢሳያስ የኢትዮጵያ ግድብ ላይ የግብፆችን ወይንም የሌላ ተቃራኒ አገር ስሜት የሚያስተናግዱበት ምንም ዓይነት ቦታ ለጊዜው አሁን የለም።ይህ ማለት ግን ገለልተኛ ሆነው በመቆየት ክፉውን ጊዜ ሊያሳልፉ መሞከራቸው አይቀርም ማለት አይደለም።ይህ ግን እስከ መቼ? የሚለውን ጥያቄ ያመጣል።ምክንያቱም ውጥረቶች እየባሱ ሲመጡ ከእኛ ነህ ከእነርሱ? የሚል የ''ሰኔ 30'' ዓይነት ጥያቄ ይፈጥራል። ይህ ጊዜ ሳይመጣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በውጪ ፖሊሲ በተለይ በአፍሪካ ቀንድ እና በመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ እና በወታደራዊ የጋራ ስምምነት ላይ አንድ ዓይነት ስምምነት ላይ መድረሱ የጋራ ጥቅም ማስከበሪያ አንዱ መንገድ ነው።እዚህ ላይ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን በቀይ ባሕር ላይ የመመስረት እና የአሰብ ወደብ ጉዳይም በፍጥነት የማግኘት መብቷ መከበር አለበት።ይህ የልመና ወይንም የበጎ ቸርነት ጉዳይ አይደለም።አቶ ኢሳያስ በቀላል የመደመር ስሌት ኢትዮጵያን ወደ ቀይባሕር አምጥቶ የኤርትራንም ሆነ የኢትዮጵያን የፀጥታ ጉዳይ ማረጋገጥ ወይንም በቀላሉ በፅንፈኛ ኃይሎች መጥፋት መሃል ቀላል ምርጫ ቀርቦላቸዋል።
እዚህ ላይ የህወሓት እና የአቶ ኢሳያስ ፀብ ጉዳይ እንደ የውስጥ ጉዳይ ተመልክተን በሂደት ህወሓት በዲሞክራሲያዊ የትግራይ ወጣቶች ስትተካ የሚስተካከል ውስጣዊ ጉዳይ ነው ከሚል እሳቤ በመነሳት ነው።ሆኖም ግን ህወሓት አሁን እንዳለው የተነጠለ ፖለቲካ የማራመድ ዕድሉን ካገኘች ለምስራቅ አፍሪካ ሌላዋ አደጋ መሆኗ እና ለውጭ ኃይሎች መረማመጃ አጀንዳ አስፈፃሚ እንዳትሆን ያሰጋል።ጉዳዩ በሂደት የሚታይ ነው።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ አጣብቂኝ ውስጥ እንዳይገባ ኢትዮጵያ አጥብቃ መከተል ያለባት መንገድ
የኢትዮጵያ የግድብ ውሃ መሙላት ሂደት ኢትዮጵያ አጣድፋ ልትጀምረው የሚገባ አመቺ ጊዜ ላይ ነች።በሌላ በኩል የሰሜን ሱዳንን ወደ ምስራቅ አፍሪካ እና መካከለኛው እንዲሁም ደቡባዊ አፍሪካ አክራሪነትን ለማስፋፍያ እንደዋና በር የሚጠቀሙት ከላይ ልማታዊ ውስጣቸው ግን የሽብር ቡድኖችን የሚያስፋፉ አገሮች አጥብቀው የሚፈሩት የኢትዮጵያ፣ኡጋንዳ፣ኬንያ።ደቡብ ሱዳን፣ኤርትራ እና ጅቡቲን ጥምረት እና የጋራ የውጭ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ፖሊሲ መቅረፅ ነው።እዚህ ላይ የምዕራቡ ዓለምም ሰሜን ሱዳንን እንደመረማመጃ አድርገው አክራሪነት ወደ አፍሪካ ለማስፋፋት ፍላጎት ያላቸውን ኃይሎችን አይደግፍም ተብሎ ይታመናል።ለእዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ በእነኝህ የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ውስጥ የፖለቲካም ሆነ ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅም ስላላቸው የእነኝህ የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ስምምነት፣ ቢያንስ በሱዳን አስጊነት ላይ እና ከጀርባዋ በሚሰለፉ አገሮች በተቃራኒ የሚቆሙ እስከሆኑ ድረስ መደገፉ አይቀርም። ለእዚህ ሁሉ ዋና ሞተሯ እና በሕዝብ ብዛት ከመቶ ሚልዮን የላቀ ሕዝብ ያላት፣በወታደራዊ አቅምም የተሻለ የምትባል ኢትዮጵያ ነች።በመሆኑም የኢትዮጵያ የውስጥ ሰላም በምንም ዓይነት መንገድ መናጋት መላው ምስራቅ አፍሪካን የሚያናጋ እንደሚሆን እና በሱማሌ የመሸገው የአልቃይዳ አንጃ አልሸባብ ሌላ ስጋት በመሆኑ የኢትዮጵያ የተረጋጋ ሰላም አስፈላጊ መሆኑን አሜሪካንን ጨምሮ ሁሉም የሚስማሙበት የማይሆን ጉዳይ ሊሆን አይችልም። በምዕራቡ በተለይ በአሜሪካ በኩል ያለው ሌላ ራስ ምታት የቻይና እግር ኢትዮጵያ ላይ መግባቱ ነው።ቻይና ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ አገሮችንም በብድር ይዛለች።ስለሆነም የቻይና ፕሮጀክት ለምዕራቡ የረጅም ጊዜ ፕሮጀክት ነው።ኮሮናን ከተሻገሩ በኃላ የሚመክሩበት ፕሮጀክት።
ስለሆነም ኢትዮጵያ ከላይ የተጠቀሰውን ሚዛን ጠባቂ ሚናዋ መጉላቱን ከመቸውም ጊዜ ተረድታ የዓባይ ግድብ ስራዋን ማፋጠን እና ከግብ ማድረስ በሌላ በኩል ሙሉ በሙሉ ከቻይና እጅ እንዳትገባ ብዙ አሰራሯ፣የተማረው ኃይሏ እና የገንዘብ ምንጩም ከምዕራቡ ከመሆኑ አንፃር ዲፕሎማሲዋ ገለልተኛ እና ከሁሉም ልትጠቀም የምትችልበትን ማዕከላዊ መስመር ተከትላ እና ከአፍሪካውያን ጋር ወዳጅነቷን አጠናክራ መቀጠል ይገባታል። እዚህ ላይ አንዳንድ መንግስት ውስጥ ያሉ ምሁራን በስሜት ወደ አንዱ ኃያል መንግስት ያጋደለ ስሜት እንድታሳይ በመገፋፋት የሚደረጉ አጉል አካሄዶችን በትክክል መቆጣጠር እና ከሁሉም ጋር ያላት መልካም ግንኙነትን ማራመድ ይጠቅማታል።በግድቡ ዙርያም በተመሳሳይ መንገድ ግብፅ ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት የወሰደችበት አንዱ እና ዓይነተኛው መንገድ ፖለቲካዊ ቃና ለመስጠት ስለሆነ መጪው የኢትዮጵያ ጥንቃቄም አንዱን ሃያል በአንዱ የማስፈራራት ሳይሆን ሁሉም ለልማቷ እንደሚጠቅሟት ተረድታ የገለልተኛ ግን የራሷን ጥቅም በምንም ዓይነት መንገድ ለድርድር የማያቀርበውን መስመር መከተል ቢያንስ ባለፈው ክፍለዘመን ከተሰሩት ስህተቶች ያድናታል።የደርግ የውጪ ፖሊሲ ክስረት ዋነኛ መነሻውም ይህ ነበር።ጥቂት ፅንፈኛ ምሁራን አስደንብረው ወደ ቀድሞዋ ሶቬትሕብረት ጎራ ሲያስገቡት ፣ግንኙነታችን ገለልተኛውን መስመር ፣ምጣኔ ሃብቱ ቅይጥ ኢኮኖሚ እንከተል ያሉትን በፀረ አብዮተኝነት ፈርጆ እርምጃ ያለውን ወስዶባቸዋል።በመጨረሻ እራሱ ደርግ ከመውረዱ ጥቂት ወራት በፊት ቅይጥ ኢኮኖሚ ብሎ ማወጁ ላይቀር ማለት ነው።ስለሆነም ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ጥሩ ሁኔታ የማንንም ኃያል መንግስት ያላዳላ ግን ጥቅሟን ያስከበረ የገለልተኛ መስመሯ አዋጪ ነው።ግድቡን ተከትሎ የሚመጡ ሽምያዎችም ላይ ይህንኑ መስመር ይዛ መሄድ አለባት።እርግጥ ነው የቁርጡ ቁርጥ ቀን ስመጣ ግብፅ በአንዋር ሳዳት ዘመን በአስዋን ግድብ የገባችበት አጣብቂኝ ውስጥ ከገባች ያኔ ሌላ ቀን ይሆናል።ይህ ግን የሃያላኑ ፍጥጫ ከኮሮና በኃላ ከባሰ አጀንዳ በየስርቻው መፈለጋቸው ስለማይቀር ያኔ የሚሆን ነው።ከእዛ በፊት ኢትዮጵያ ግድቡን ከጨረሰች ግን ሁሉ ተረት ይሆናል።ጉዳዩ ማን የበለጠ ኤሌክትሪክ ያግኝ? ማን አያግኝ? ይሆናል።
ጌታቸው በቀለ

ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት 
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant
Gudayachn Multimedia, Kommunikasjon og Konsultent



Saturday, May 16, 2020

የእናት ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያወጣው መግለጫ እና ያቀረባቸው አማራጭ ሃሳቦች።ሙሉ ይዘቱን ያንብቡ።

እናት ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሰጠው የአቋም መግለጫ!
የምንመርጠው ከብዙ ጥሩዎች ሳይሆን ከብዙ መጥፎዎች የተሻለውን ነውና ሁሉም ውግንናው ሀገርንና ሕዝብን ከመታደግ ይሁን!
በሀገራችን ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የመጣውን የኖቭል ኮሮና ቫይረስ /COVID-19/ ሥርጭት ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በዘንድሮ ዓመት ነሐሴ 23/2012 ዓ.ም ሊያካሂድ ላቀደው የሀገር አቀፍ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ መቸገሩን መጋቢት 22/2012 ዓ.ም አሳውቋል፡፡ ወትሮም ብዙዎች ከመነሻው፣ አንዳንዶች ከአተገባበሩ የሚያብጠለጥሉትና ክፍተቱ የበዛው ሕገ መንግስቱ በእንዲህ ዓይነት አጣብቂኝ ወቅት ማለትም የምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ባለቀበትና ምርጫ ማከናወን ባልተቻለበት ሁኔታ ሀገር በማንና እንዴት ትመራ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት አለመቻሉ ሕገ መንግስቱ ብዙ መሠረታዊ ችግሮች እንዳሉበት ማሳያ ነውና በአግባቡ ሊፈተሽ እና ሊከለስ ይገባል የሚለውን ሃሳብ የሚያጠናክረው ሲሆን በሌላ በኩል  ሲሞቅ ሲቀዘቅዝ የነበረውን የኢትዮጵያን ነባራዊ ፖለቲካ ይባስ ብሎ ቅርቃር ውስጥ ከቶታል፡፡ 
በዚህ መሐል ጠቅላይ ሚንስትሩ ድንገቴ የሚባል የተናጠል አራት አማራጮች ይዘው ብቅ አሉ፡፡ ከነዚሁ ውስጥ እንደፓርላማ መበተንና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ የሚሉ ለአቅመ አማራጭነት የማይቀርቡ ወይም የሌሎችን ምርጫዎች ተፈላጊነት የሚጨምሩ ምክረ ሀሳቦች ቀረቡ፤ ፓርላማውም “የሕገ መንግስት ትርጉም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት መጠየቅ” የሚለው በአብላጫ ድምጽ አጽድቆ ጉዳዩን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መርቶታል፡፡
እዚህም ላይ ቆም ብሎ ካለፈ ታሪካችን በመማር፣ ወደፊትም ትውልድ በበጎ የሚያነሳውና በምሳሌነት የሚጠቀስ ውሳኔ ማሳለፍ ተገቢ ነው ብለን እናስባለን፡፡ እናት ፓርቲ ሁልጊዜ እንደሚለው ከታሪካችን ዳበስ ዳበስ ብናደርግ ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችንን ብንመረምር፣ ከላይ ወደታች ሳይሆን ከታች ወደላይ የሚያድግ አሠራር መከተሉ ብዙ ርቀት ለመጓዝ ይረዳል ብሎ ስለሚያምን በዚህ ጉዳይ ላይ ከልዩ ልዩ  የማኅበረሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ አካላት ጋር /ከምሑራን፣ ማለትም የሕግ አማካሪዎች፣ የፖለቲካ ተንታኞች፣ አባላትና ደጋፊዎች/ በተለያዩ አማራጮች ውይይትና ምክክር ሲያድርገበት ቆይቷል፡፡ 
ፓርቲያችን መጠይቅ አዘጋጅቶ በሰበሰበው መረጃ መሠረት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ምርጫው መራዘሙ አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን፣ አብዛኛዎቹ በመንግስት ከቀረቡት አራት አማራጮች የሕገ መንግስት ትርጉም መጠየቅ የሚለው የተሻለ እንደሆነ፣ አሁን ያለው መንግስት በገደብ ቢቀጥል እንደሚያምኑ፣ በአንጻሩ አንዳንድ ምልክቶቹ ያለፍንበትን እንዳያስደግመን ስለሚያስፈራ በገደብ /conditions/ ቢታይ፣ መፍትሔዎችም ተናጠላዊና ብቸኛ ሳይሆኑ የብዙኃንን ምክክርና ብዙ/Multiple/ አማራጮችን መዳሰስ የሚገባ እንደሆነ አበክረው ገልጸዋል፡፡   
በሌላ በኩል አሁን ያለው ዓለምአቀፋዊና ሀገራዊ ሁኔታ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ ዓለማችን በኮሮና ወረርሽኝ ከፍተኛ ሥጋት ላይ በወደቀችበትና ሚሊዮኖች በወረርሽኙ ተማርከው፣ ብዙ መቶ ሺዎች ሕይወታቸውን እያጡ ባለበት፣ በዐይን ጥቅሻ ሺዎች በበሽታው የሚያዙበት መሆኑ እንኳንስ እንደኛ ላለች በዐይነ ቁራኛ ለሚመለከቷት ታዳጊ ሀገር ዴሞክራሲያዊ ምርጫና ሀገር ግንባታ ለራሳቸውም ሁለንተናዊ ብርክ ውስጥ የገቡበትና የሟች ብዛትን ሲያሰሉ የሚከርሙበት ሁኔታ መኖሩ፤ አህጉረ አፍሪካም ቢሆን ከድጡ ወደማጡ ነው፡፡ በዓለምአቀፉ የጤና ድርጅት/WHO/ ግምት ቀጣይዋ ተረኛ እንደሆነች ተደጋግሞ ተገልጿል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም ከሌሎች ስህተት ልትማርባቸው የሚገቡ እድሎችን አምክና ይሄው ሞቱም ቀስ እያለ የበሽታውም ተያዥ ቍጥርም ከዕለት ወደዕለት በአስፈሪ ሁኔታ እየጨመረ ነው (መንግስት የሚያወጣውን አኃዝ እንኳን ብናምን እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ሞት 5፣ 272 በወረርሽኙ የተጠቃ)፡፡ አሁን ደግሞ ገና እንደሀገር ለመቆም ድክ ድክ የምትለው ሶማሊያ ያለው የወረርሽኙ መስፋፋት፣ የጅቡቲ፣ ሱዳን ከቀን ወደቀን የሚሰሙ የተያዥ ቍጥር ጭማሬና ካለን ሁሉን አቀፍ ንክኪ አደጋው የከፋ መሆኑን ለመገንዘብ ችለናል፡፡  
ወረርሽኙን ተከትሎ የሚመጣው የምጣኔ ሀብት ድቀት፣ ብድር ጣሪያ መድረስ/በዚሁ ሰበብ የአበዳሪዎች ቸልታ/፣ የአምራች ክፍሉ የሥነልቡና ጉዳት፣ የትምህርት ቤቶች መዘጋት፣ የሥራ አጡ መብዛት፣ ለዕለት የሚላስ የሚቀመስ የሚያጣው ኢትዮጵያዊ መብዛት (መንግስት 30 ሚሊዮን ሕዝብ ይራብብኛል ብሏል)፣ እንደምዕራብ ኦሮሚያና ጉጂ የመሰሉ አምራች አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርት ማጣት፣ የአንበጣ መንጋ መዛመት፣ የውስጥ ፓለቲካው ጫፍና ጫፍ መርገጥ፣… ወዘተ ከውስጥ ከሚነሱ ዋና ዋና ውስጣዊ ተግዳሮቶች በግንባር ቀደም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከባቢያዊ ፓለቲካው /Geopolitics/ ደግሞ ከአባይ ግድብ ጋር ተያይዞ ግብጽ ራሷን በውሃው ላይ እንደ ብቸኛ አድራጊ ፈጣሪ በመቁጠር ልትወስዳቸውና ልትሔድባቸው የምታስባቸው እርምጃዎች ጤናማነት መጓደል ምልክቶች፣ ገባወጣ የሚለው በውል ያልረጉት የሁለቱ ሱዳኖች አቋም፣ ይህንኑ ተከትሎ በራሱ የቤት ሥራ የተጠመደው የዓለምአቀፉ ማኅበረስብ ገለልተኛ ያልሆነ ዕይታ የሚያመላክተን አብዛኛውን ነገር የውስጥ የቤት ሥራችንን ሳንሳሳት መሥመር በመሥመር ሠርተን እጅ ለእጅ መያያዝ እንደሚገባን አመላካች ናቸው፡፡     
በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግስት ላለፉት ሁለት ዓመታት የጀመረውንና ተስፋ የተጣለበትን ፍጥነት ትቶ አንዳንዴ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት ወደኋላ ሲል ሌላ ጊዜ ደግሞ በደከመው ላይ የፈሪ በትር ሲያሳርፍ ከርሟል፡፡ ሥርዓት አልበኝነት ነግሶ ጣሪያ ነክቷል፤ ሊቀራረቡ ነው ያልናቸው ማኅበረሰብና የፖለቲካ ልኺቃን ሆድና ጀርባ እየሆኑ ጭራሽ እስከ የክልል መንግስት ግልበጣ ድረስ መተማማት ደርሰዋል፤ በመንግስት ላይ የሚተማመን ሳይሆን የሚያኮርፈው በዝቷል፡፡ ታሪክ እያስተማረን የወደፊቱን ለማበጀት ከየትኛውም ወገን ጋር ቁጭ ብሎ በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ደንብ ማውራት ሲቻል በመካረር ሌላ ጥሩ እድል እያለፈን እንደሆነ ይታየናል፡፡ በዚህ መሐል አልፎ አልፎ የሚደረጉት ተግባራት የጠቅላይነትና ያለፈውን ስህተት የመድገም፣ ችግርን/Crises/ ለፖለቲካ ፍጆታ የማዋል አዝማሚያዎች፣ ጥልቀትና ሁሉን አቀፍነት የጎደላቸው መፍትሔዎች መጉላት፣ መንግስታዊ ትንኮሳዎች፣ የታይታና ድንገቴ ሥራዎች/Projects/ መብዛት ደግሞ በሌላው ጽንፍ መታየት ለንጽጽሩ የሚበጁ ናቸው ብለን ወስደናል፡፡
ታዲያ የምንመርጠው ምርጫ በነዚህ አጣብቂኝ መሐል የሚያልፍ ስለሆነ መንግስት ሲጀመር የተናጠል አማራጮችን አቅርቦ “ኑና ስሙልኝ” ከሚል “ቅርቃር ውስጥ የገባውን አጠቃላይ ሁኔታ እንዴት እንወጣው?” የሚል ጥያቄ ብቻ ይዞ ቢቀርብ ማለፊያ ይሆን ነበር እንላለን፡፡ ከገባንበት አጣብቂኝ አንጻር ግን አሁንም አልረፈደምና መለስ ብሎ ማየት ተገቢ ነው፡፡ 
ፓርቲያችን እነዚህን ችግሮች ታሳቢ አድርጎ ባካሄደው የማኅበረሰብ ውይይትና እና የባለሙያዎች ትንተና በእንዲህ ዓይነት አጣብቂኝ ጊዜ ውስጥ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 60/1 እና 3 መሠረት ፓርላማውን መበተን ሊከሰቱ የሚችሉ ድንገተኛ የሀገርና ሕዝብን ደኅንነት እና ጥቅም አደጋ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባና የፌዴራል መንግስትን እንጂ የክልል ምክር ቤቶችን ታሳቢ ያላደረገ መሆኑን፣ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 93 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እና ምርጫውን ማራዘም በዴሞክራሲ እጦት ሲሰቃይ ለኖረ ማኅበረሰብ በፍጹም የሚቀርብ ምከረ ሀሳብ እንዳልሆነ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥላ ሥር የሚደረግ ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ ስለማይሆን እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችም ተመራጭ ሀሳብ አለመሆኑን በአንድም በሌላም መልኩ ያራመዱት አቋም ተገቢ መሆኑን እናት ፓርቲም የሚያምንበት ነው፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ደካማ አማራጮችም ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡ 
በአንጻሩ በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 104 እና 105 መሠረት የሕገ መንግስት ማሻሻያ ማድረግ ጥሩ አማራጭ ቢሆንም ሕገ መንግስቱን ለማሻሻልም ጠንከር ያለ እርምጃ መሄድ ያስፈልጋል፤ በእንዲህ መልኩ የሚሻሻል ከሆነ ሥልጣን ላይ በተቀመጠው አካል ሊደፈጠጥ እና ወደሚፈልገው አቅጣጫ ሊወሰድ ስለሚችል ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ሕገ መንግስት ሲሻሻል ጠንከር ያለና የብዙኃኑን ድምጽ፣ ሀሳብ እና ይሁንታ ያገኘ ሊሆን ይገባዋል፤ የሕገ መንግስት ማሻሻያን በተመለከተ ሁለት አንኳር ነጥቦች ይነሳሉ፡፡ የመጀመሪያው ሀሳቡን ስለማመንጨት /initiation/ ወይም ምክረ ሀሳብን ስለማቅረብ ነው፡፡ በቀጣይ ደግሞ ማን እንደሚያሻሽለው የሚደነግገውን ነው፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ተወካዮች እና  የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በጋራ ስብሰባ በ2/3ኛ ድምጽ ሲያጸድቁት ነው፡፡ ይህንን የሕገ መንግስት ማሻሻል ጥሩ ምርጫ ሆኖ ሳለ ተመራጭ የማያደርገው የብዙኃኑን ድምጽና ውይይት እንዲሁም ይሁንታ የሚፈልግ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ እነዚህ ምክር ቤቶች ብቻቸውን አይወስኑም ሰፊ የሕዝብ ውይይት እና ስምምነት ይፈልጋል፡፡ ከማሻሻያው በኋላም የመንግስት ሥልጣን ምን ይሁን የሚለውን ለመወሰንም አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 62 (1) መሠረት ሕገ መንግስቱን የመተርጎም ሥልጣን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሰጣል፡፡ መንግስት በተናጠል ካቀረባቸው አማራጮች ከነችግሩ ይሄኛው ይሻላል የሚል እምነት አለን፡፡ ፓርላማውም በይሁንታ ወደፌደሬሽን ምክር ቤት የመራው ይሄንኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እዚህም አማራጭ ላይ ትልቅ ሥጋትና ድክመት እንዳለ ሳይጠቀስ ሊታለፍ አይገባም፡፡ የምክር ቤቱ ገለልተኛነት! እንደሚታወቀው ፌደሬሽን ምክር ቤቱ የቅርብ ጊዜያት ግብሩ እንኳን ቢታይ የበዙ ቀጥታ የሚመለከቱት ጥያቄዎች ቀርበውለት በቸልታ ወይም ባላዬ ያለፈ ምክር ቤት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር የሚነሱ ገዢው መንግስት ሀሳብ ማስፈጸሚያ እጅ መሆን፣ የአባላቱ ብቃትና እውቀት/Professionalism/ እንዲሁ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባ ነው፡፡ 
በሌላ በኩል የሽግግር መንግስት ከተለያዩ አካላት ተደጋግሞ የሚነሳ መፍትሔ ሀሳብ ስለሆነ እሱም ላይ ሰፊ ውይይት፣ ትንተናና ክርክር ለማድረግ ሞክረናል፡፡ የመጀመሪያው የሽግግር መንግስት ለማለት የሕግ መሠረት የለንም፡፡ ሕጋዊ መንግስት እያለና ምርጫ አላካሂድም ባላለበት ሁኔታ ይህ አማራጭ አይታሰብም፡፡ ከ100 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች ባለባት እና ዋልታ ረገጥ (Polarized) የሆነ አቋምና አስተሳሰብ በሚራመድባትና እነኚህ አመለካከቶች ወደመሐል እንዲመጡ ሥራ ባልተሠራበት ሁኔታ ውስጥ ተወያይቶ መግባባት ይቻላል ማለት ሆድ ሲያውቅ… ይሆንብናል፡፡ በዚያውም ላይ የወረርሽኙ ጠባይ በውል ባልታወቀበትና ከፍተኛ ሥጋት ወቅት መወያየትስ ይቻላል ወይ? አዲስ ተረካቢ መንግስትስ አሁን ያለውን አጣብቂኝ ምኑን ከምን ሊያደርገው? ብሎ ማየት ይገባል እንላለን፡፡ 
 እንግዲህ የገባንበት አጣብቂኝ አለ፡፡ የገዢው መንግስት ከጥንካሬ ጉድለት እስከ ጠቅላይነትና ወንበር የማደላደል አዝማሚያ በሚዛኑ ሌላ ጎን የሚቀመጡ ናቸው፡፡ የምንመርጠውም ምርጫ እነኚህን የሚያስታርቅ፣ ሀገርን ከገባችበት ችግር የሚያወጣ መሆን ይኖርበታል፡፡ 
እናት ፓርቲ ሕጋዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ ተጣምረው ቢወሰዱ ከገባንበት አጣብቂኝ ያወጣናል ብሎ አበክሮ ያምናል፡፡ ሆኖም በእያንዳንዳቸው ውስጥ ቢሆኑ ያዋጣል የምንለውን እናስቀምጥ፡፡
የመፍትሔ ሀሳብና ቅድመ ሁኔታዎች፡- 
ፓርቲያችን የሕገ መንግስት ትርጉም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት መጠየቅ የሚለው ሀሳብ የተሻለ በመሆኑ የሚቀበለው ሲሆን በተጨማሪም ግን ፓለቲካዊ መፍትሔም ካልተጨመረበት ይህ ብቻውን ከገባንበት ቅርቃር ያወጣናል ብሎ የማያምን ሲሆን ከዚህ በታች የተገለጹት ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት እንዳለባቸው በአጽንዖት ያስገነዝባል፡፡
ቅድመ ሁኔታዎች/Conditions/፡-
  • የሕገ መንግስት አጣሪ ኮሚቴ ውሳኔ የሚሰጥበት አካሄድ፣ ግልጽና አሳታፊ መሆን ይኖርበታል፤ የሚሰጠው ትርጓሜም የተወሰነና ዓለማው የተገደበ (Limited and Purposive) መሆን ይኖርበታል፡፡ 
  • የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ የሕግ ባለሙያዎችን፣ ምሑራንንና የሚመለከታቸውን ሲቪክ ማኅበራት ወዘተ  በማሳተፍ ሕጋዊ፣ ሙያዊ፣ ግልጽና ተአማኒነት ያለው መሆን ይኖርበታል፡፡
  • የሚሰጠው ሕገ መንግስታዊ ትርጓሜ ዴሞክራሲዊ ባህልን ሊያጎለብት፣ ነጻና ፍትሓዊ ምርጫ ለማካሄድ በሚቻልበት አግባብ ሊሆን ይገባል፡፡
  • ካለንበት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ውድቀትና እጅግ ተስፋፊና ገዳይ ወረርሽን/pandemic/ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊታደግ የሚችልበትን ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆን ይኖርበታል፡፡ 
  • ለቀጣይ የሕገ መንግስት ማሻሻያዎችና መሰል ትርጉሞች የተሻለ በር የሚከፍትና ጥሩ ልምድ ጥሎ የሚያልፍ እንጂ እንደመጥፎ ልምድ ተወስዶ እንደዶግማ ከተጻፈ ተነክቶ የማያውቀውንና “ጉድለት የበዛውን” ሕገ መንግስት ጭራሽ የማይደፈር እንዳያደርገው በከፍተኛ ሓላፊነትና ጥንቃቄ እንዲከወን ማድረግ፤ 
  • በዚህ ረገድ ያሉ ዓለምአቀፍ ልምድን የዳሰሰ መሆን ይኖርበታል፡፡
  • በሌላ በኩል ፓለቲካዊ መፍትሔው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያሳተፈ የሽግግር ጊዜውን እንዴት ለሀገር ግንባታ፣ ለብሔራዊ እርቅና መግባባት እንጠቀምበታለን? የሚሉ በጋራ ታስበው በጋራ የሚከወኑ መርሐ ግብራት አስፈላጊ ናቸው፡፡
  • ከምርጫው በኋላም ሊፈጠሩ የሚችሉ ሥጋቶችንና አደጋዎችን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል ፖለቲካዊ መፍትሔን የግድ አብሮ እንዲፈጸም ንግግሩ አስገዳጅ ነው ብለንም እናምናለን፡፡ 
  • መንግስት ወረርሽኙን እንደ አንዳንድ ዓለም ሀገራት ፖለቲካ በማድረግ ለራሱ ሥልጣን ማራዘሚያና የምርጫ ወንበር ማግኛነት ሊጠቀምበት ይችላል የሚል ሥጋት ፓርቲያችን ያለው ሲሆን ይህንንም ሀቀኝነተን በተላበሰ ሁኔታ ሊመራው እንደሚገባና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመሻገር ሁሉን አቀፍ  እና ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርበታ እንላለን፡፡
  • የምርጫው ሂደት በመንግስት ቁጥጥርና ፍላጎት ሥር ሊወድቅ የማይችል መሆኑን ሊያረጋግጥ በሚችልበት አኳኋን ሊከወን ይገባል፡፡
  • ለዚህም ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ የመንግስትን እንቅስቃሴና ተግባር በአባታዊ፣ ጠባቂነት መንፈስ በጋራ የሚሠራ ለኅሊናቸው ተገዥ ከሆኑና ማኅበረሰቡ በሚመርጣቸው ከሀይማኖት ተቋማት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሀገር ሽማግሌዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት የተውጣጣ አንድ ስብስብ/watchdog/ በማስቀመጥ እንደ ጸጥታ ተቋማት፣ ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤት የመሰሉ ለቀጣዩ ምርጫ ወሳኝ ሚና ያላቸውን ተቋማት በንቃት የሚጠብቅ፣ መንግስት እነዚህን ተቋማት እጅ ጠምዝዞ እኩይ ምግባራትን ቢፈጽም፣ ሀዲዱን ቢስት የሚገስጽና ማኅበረሰቡን የሚያነቃ ስብስብ/Organ/ ማቋቋም አስፈላጊ እንደሆነ ፓርቲያችን ያምናል፡፡
ለመላው የሀገራችን ሕዝብ፡-
ብዙ ጥሩ ምርጫዎች ኖረውን ከዚያው መሐል የምንመርጥ ቢሆን እንዴት በታደልን ነበር፡፡ የሆነው ግን እንደሱ አይደለም፡፡ የሆነው ተቃራኒው፣ ከብዙ መጥፎ አማራጮች የተሻለውን መጥፎ የምንመርጥ መሆኑ ታውቆ ሰው ከሰው ጋር፣ ማኅበረሰብ ከማኅበረሰብ መስተጋብሩን ይበልጥ ማጠንከርና መተዛዘን እንጂ አጋጣሚ በተፈጠረ ቁጥር ወጊድልኝ በመባባልና በመገዳዳል፣ የውሸትና ሴራ ትርክቶችን እያደባለቁ በመበላላት እንደማንወጣው ታምኖ በጣም በጥንቃቄ ይህን ጊዜ እንድናልፈው አበክረን እንገልጻለን፡፡ ሕዝብ ያለመንግስት ኖሮ ያውቃል መንግስት ግን ያለሕዝብ በባዶ ሜዳ ኖሮ አያውቅምና ራስን የመግዛት ባህላችንን እንድናጎለብተው ከአደራ ጭምር ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡  
ለሃይማኖት ተቋማት መሪዎች አባቶቻችን፡-
ወደፊት መጥታችሁ አባታዊና መንፈሳዊ ልዕልናችሁን ተጠቅማችሁ ማንንም ሳትፈሩና ሳታፍሩ በጥፋቱ መገሰጽ፣ መፍትሔ ማመላከት ከመቸውም ጊዜ በላይ ይጠበቅባችኋልና ይህን ባታደርጉ እዳ በደሉ በታሪክ ፊት የሚያስወቅሳችሁ እንደሆነ ማስታወስ ብቻ እንወዳለን፡፡ 
የፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎች፡-
በእንዲህ ዓይነት ዙሪያው ገደል በሆነበት ወቅት በእናታዊ ጠባይ በሁሉን አቃፊነት፣ ይቅር ባይነትና እንተ ትብስ አንቺ ትብሽ በመባባል እንድናልፈው፣ በአንጻሩ ደግሞ የሀገራችሁን ሁኔታ ነቅቶ በመከታተል፣ በመረጃና ማስረጃ በመደገፍ ስለመብታችሁ ያለፍርሃት እንድትሞግቱ አደራ አንላለን፡፡ 
ዓለምና ሀገር አቀፍ ሲቪክ ማኅበራትና ተቋማት፡-
ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚመጥን ሥርዓት እስኪዘረጋ ውሎ ከመግባትና ጊዜ ከመቁጠር ያለፈ፣ የመጣውን ከማዳነቅ ያለፈ ሚና ተጫወቱና አሳዩን፣ እርዱን እንላለን፡፡ 
ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፡-
አሁን ይበልጥ የምንፈተንበትና ለታሪክ ተጠያቂነት የምንዳረግበት ጊዜ ከፊታችን አፍጥጦ መጥቷል፡፡ መቸም ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን ቁጭ ብለው ሲጫወቱ አንዱ የሌላኛውን አባት በባንዳነትና በጥቅም ፈላጊነት እየከሰሰና እየሰደበ ሲያሸማቅቀው ማየት የምንሻ ያለን አይመስለንም፡፡ ብዙ ሳንርቅ በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ወቅት ተከስቶ ለመናገር እስኪያሳፍር ድረስ ስማቸውን ስንጠራቸው የምንሸማቀቀው ሰዎች ቤተሰብ እማኞቻችን ናቸው፡፡ ስለሆነም ከራስ ጥቅምና “ቡድን” ፍላጎት ወጥተን፣ አሁንም ከገልባጭነትና የራስን አንቋሾ ከመነሳት ርቀን በየጓዳችን ካሉ መፍትሔዎች መልከኛውን ሰንቀን በምክክሩ አደባባይ እየተገናኘን እንደየአቅማችን ተሟግተንና ተፋጭተን የተሻለውን እየወሰድን ይህችን በችጋርና ረሃብ የምትታወቅ ሀገር እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንታደጋት፣ ልጆቻችን ሌላ የአበሳ ዓመታት ሳይሆን ነጋቸውን በናፍቆትና በብዙ ተስፋ የሚኖሩበት ዘመን ለማድረግ እንድንተጋ እናታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ 
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅልን
ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም
እናት ፓርቲ


አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።