ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, May 16, 2020

የእናት ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያወጣው መግለጫ እና ያቀረባቸው አማራጭ ሃሳቦች።ሙሉ ይዘቱን ያንብቡ።

እናት ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሰጠው የአቋም መግለጫ!
የምንመርጠው ከብዙ ጥሩዎች ሳይሆን ከብዙ መጥፎዎች የተሻለውን ነውና ሁሉም ውግንናው ሀገርንና ሕዝብን ከመታደግ ይሁን!
በሀገራችን ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የመጣውን የኖቭል ኮሮና ቫይረስ /COVID-19/ ሥርጭት ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በዘንድሮ ዓመት ነሐሴ 23/2012 ዓ.ም ሊያካሂድ ላቀደው የሀገር አቀፍ ምርጫ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ መቸገሩን መጋቢት 22/2012 ዓ.ም አሳውቋል፡፡ ወትሮም ብዙዎች ከመነሻው፣ አንዳንዶች ከአተገባበሩ የሚያብጠለጥሉትና ክፍተቱ የበዛው ሕገ መንግስቱ በእንዲህ ዓይነት አጣብቂኝ ወቅት ማለትም የምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ባለቀበትና ምርጫ ማከናወን ባልተቻለበት ሁኔታ ሀገር በማንና እንዴት ትመራ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት አለመቻሉ ሕገ መንግስቱ ብዙ መሠረታዊ ችግሮች እንዳሉበት ማሳያ ነውና በአግባቡ ሊፈተሽ እና ሊከለስ ይገባል የሚለውን ሃሳብ የሚያጠናክረው ሲሆን በሌላ በኩል  ሲሞቅ ሲቀዘቅዝ የነበረውን የኢትዮጵያን ነባራዊ ፖለቲካ ይባስ ብሎ ቅርቃር ውስጥ ከቶታል፡፡ 
በዚህ መሐል ጠቅላይ ሚንስትሩ ድንገቴ የሚባል የተናጠል አራት አማራጮች ይዘው ብቅ አሉ፡፡ ከነዚሁ ውስጥ እንደፓርላማ መበተንና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ የሚሉ ለአቅመ አማራጭነት የማይቀርቡ ወይም የሌሎችን ምርጫዎች ተፈላጊነት የሚጨምሩ ምክረ ሀሳቦች ቀረቡ፤ ፓርላማውም “የሕገ መንግስት ትርጉም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት መጠየቅ” የሚለው በአብላጫ ድምጽ አጽድቆ ጉዳዩን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መርቶታል፡፡
እዚህም ላይ ቆም ብሎ ካለፈ ታሪካችን በመማር፣ ወደፊትም ትውልድ በበጎ የሚያነሳውና በምሳሌነት የሚጠቀስ ውሳኔ ማሳለፍ ተገቢ ነው ብለን እናስባለን፡፡ እናት ፓርቲ ሁልጊዜ እንደሚለው ከታሪካችን ዳበስ ዳበስ ብናደርግ ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችንን ብንመረምር፣ ከላይ ወደታች ሳይሆን ከታች ወደላይ የሚያድግ አሠራር መከተሉ ብዙ ርቀት ለመጓዝ ይረዳል ብሎ ስለሚያምን በዚህ ጉዳይ ላይ ከልዩ ልዩ  የማኅበረሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ አካላት ጋር /ከምሑራን፣ ማለትም የሕግ አማካሪዎች፣ የፖለቲካ ተንታኞች፣ አባላትና ደጋፊዎች/ በተለያዩ አማራጮች ውይይትና ምክክር ሲያድርገበት ቆይቷል፡፡ 
ፓርቲያችን መጠይቅ አዘጋጅቶ በሰበሰበው መረጃ መሠረት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ምርጫው መራዘሙ አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን፣ አብዛኛዎቹ በመንግስት ከቀረቡት አራት አማራጮች የሕገ መንግስት ትርጉም መጠየቅ የሚለው የተሻለ እንደሆነ፣ አሁን ያለው መንግስት በገደብ ቢቀጥል እንደሚያምኑ፣ በአንጻሩ አንዳንድ ምልክቶቹ ያለፍንበትን እንዳያስደግመን ስለሚያስፈራ በገደብ /conditions/ ቢታይ፣ መፍትሔዎችም ተናጠላዊና ብቸኛ ሳይሆኑ የብዙኃንን ምክክርና ብዙ/Multiple/ አማራጮችን መዳሰስ የሚገባ እንደሆነ አበክረው ገልጸዋል፡፡   
በሌላ በኩል አሁን ያለው ዓለምአቀፋዊና ሀገራዊ ሁኔታ ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ ዓለማችን በኮሮና ወረርሽኝ ከፍተኛ ሥጋት ላይ በወደቀችበትና ሚሊዮኖች በወረርሽኙ ተማርከው፣ ብዙ መቶ ሺዎች ሕይወታቸውን እያጡ ባለበት፣ በዐይን ጥቅሻ ሺዎች በበሽታው የሚያዙበት መሆኑ እንኳንስ እንደኛ ላለች በዐይነ ቁራኛ ለሚመለከቷት ታዳጊ ሀገር ዴሞክራሲያዊ ምርጫና ሀገር ግንባታ ለራሳቸውም ሁለንተናዊ ብርክ ውስጥ የገቡበትና የሟች ብዛትን ሲያሰሉ የሚከርሙበት ሁኔታ መኖሩ፤ አህጉረ አፍሪካም ቢሆን ከድጡ ወደማጡ ነው፡፡ በዓለምአቀፉ የጤና ድርጅት/WHO/ ግምት ቀጣይዋ ተረኛ እንደሆነች ተደጋግሞ ተገልጿል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም ከሌሎች ስህተት ልትማርባቸው የሚገቡ እድሎችን አምክና ይሄው ሞቱም ቀስ እያለ የበሽታውም ተያዥ ቍጥርም ከዕለት ወደዕለት በአስፈሪ ሁኔታ እየጨመረ ነው (መንግስት የሚያወጣውን አኃዝ እንኳን ብናምን እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ሞት 5፣ 272 በወረርሽኙ የተጠቃ)፡፡ አሁን ደግሞ ገና እንደሀገር ለመቆም ድክ ድክ የምትለው ሶማሊያ ያለው የወረርሽኙ መስፋፋት፣ የጅቡቲ፣ ሱዳን ከቀን ወደቀን የሚሰሙ የተያዥ ቍጥር ጭማሬና ካለን ሁሉን አቀፍ ንክኪ አደጋው የከፋ መሆኑን ለመገንዘብ ችለናል፡፡  
ወረርሽኙን ተከትሎ የሚመጣው የምጣኔ ሀብት ድቀት፣ ብድር ጣሪያ መድረስ/በዚሁ ሰበብ የአበዳሪዎች ቸልታ/፣ የአምራች ክፍሉ የሥነልቡና ጉዳት፣ የትምህርት ቤቶች መዘጋት፣ የሥራ አጡ መብዛት፣ ለዕለት የሚላስ የሚቀመስ የሚያጣው ኢትዮጵያዊ መብዛት (መንግስት 30 ሚሊዮን ሕዝብ ይራብብኛል ብሏል)፣ እንደምዕራብ ኦሮሚያና ጉጂ የመሰሉ አምራች አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርት ማጣት፣ የአንበጣ መንጋ መዛመት፣ የውስጥ ፓለቲካው ጫፍና ጫፍ መርገጥ፣… ወዘተ ከውስጥ ከሚነሱ ዋና ዋና ውስጣዊ ተግዳሮቶች በግንባር ቀደም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከባቢያዊ ፓለቲካው /Geopolitics/ ደግሞ ከአባይ ግድብ ጋር ተያይዞ ግብጽ ራሷን በውሃው ላይ እንደ ብቸኛ አድራጊ ፈጣሪ በመቁጠር ልትወስዳቸውና ልትሔድባቸው የምታስባቸው እርምጃዎች ጤናማነት መጓደል ምልክቶች፣ ገባወጣ የሚለው በውል ያልረጉት የሁለቱ ሱዳኖች አቋም፣ ይህንኑ ተከትሎ በራሱ የቤት ሥራ የተጠመደው የዓለምአቀፉ ማኅበረስብ ገለልተኛ ያልሆነ ዕይታ የሚያመላክተን አብዛኛውን ነገር የውስጥ የቤት ሥራችንን ሳንሳሳት መሥመር በመሥመር ሠርተን እጅ ለእጅ መያያዝ እንደሚገባን አመላካች ናቸው፡፡     
በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግስት ላለፉት ሁለት ዓመታት የጀመረውንና ተስፋ የተጣለበትን ፍጥነት ትቶ አንዳንዴ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት ወደኋላ ሲል ሌላ ጊዜ ደግሞ በደከመው ላይ የፈሪ በትር ሲያሳርፍ ከርሟል፡፡ ሥርዓት አልበኝነት ነግሶ ጣሪያ ነክቷል፤ ሊቀራረቡ ነው ያልናቸው ማኅበረሰብና የፖለቲካ ልኺቃን ሆድና ጀርባ እየሆኑ ጭራሽ እስከ የክልል መንግስት ግልበጣ ድረስ መተማማት ደርሰዋል፤ በመንግስት ላይ የሚተማመን ሳይሆን የሚያኮርፈው በዝቷል፡፡ ታሪክ እያስተማረን የወደፊቱን ለማበጀት ከየትኛውም ወገን ጋር ቁጭ ብሎ በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ደንብ ማውራት ሲቻል በመካረር ሌላ ጥሩ እድል እያለፈን እንደሆነ ይታየናል፡፡ በዚህ መሐል አልፎ አልፎ የሚደረጉት ተግባራት የጠቅላይነትና ያለፈውን ስህተት የመድገም፣ ችግርን/Crises/ ለፖለቲካ ፍጆታ የማዋል አዝማሚያዎች፣ ጥልቀትና ሁሉን አቀፍነት የጎደላቸው መፍትሔዎች መጉላት፣ መንግስታዊ ትንኮሳዎች፣ የታይታና ድንገቴ ሥራዎች/Projects/ መብዛት ደግሞ በሌላው ጽንፍ መታየት ለንጽጽሩ የሚበጁ ናቸው ብለን ወስደናል፡፡
ታዲያ የምንመርጠው ምርጫ በነዚህ አጣብቂኝ መሐል የሚያልፍ ስለሆነ መንግስት ሲጀመር የተናጠል አማራጮችን አቅርቦ “ኑና ስሙልኝ” ከሚል “ቅርቃር ውስጥ የገባውን አጠቃላይ ሁኔታ እንዴት እንወጣው?” የሚል ጥያቄ ብቻ ይዞ ቢቀርብ ማለፊያ ይሆን ነበር እንላለን፡፡ ከገባንበት አጣብቂኝ አንጻር ግን አሁንም አልረፈደምና መለስ ብሎ ማየት ተገቢ ነው፡፡ 
ፓርቲያችን እነዚህን ችግሮች ታሳቢ አድርጎ ባካሄደው የማኅበረሰብ ውይይትና እና የባለሙያዎች ትንተና በእንዲህ ዓይነት አጣብቂኝ ጊዜ ውስጥ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 60/1 እና 3 መሠረት ፓርላማውን መበተን ሊከሰቱ የሚችሉ ድንገተኛ የሀገርና ሕዝብን ደኅንነት እና ጥቅም አደጋ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባና የፌዴራል መንግስትን እንጂ የክልል ምክር ቤቶችን ታሳቢ ያላደረገ መሆኑን፣ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 93 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እና ምርጫውን ማራዘም በዴሞክራሲ እጦት ሲሰቃይ ለኖረ ማኅበረሰብ በፍጹም የሚቀርብ ምከረ ሀሳብ እንዳልሆነ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥላ ሥር የሚደረግ ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ ስለማይሆን እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችም ተመራጭ ሀሳብ አለመሆኑን በአንድም በሌላም መልኩ ያራመዱት አቋም ተገቢ መሆኑን እናት ፓርቲም የሚያምንበት ነው፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ደካማ አማራጮችም ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡ 
በአንጻሩ በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 104 እና 105 መሠረት የሕገ መንግስት ማሻሻያ ማድረግ ጥሩ አማራጭ ቢሆንም ሕገ መንግስቱን ለማሻሻልም ጠንከር ያለ እርምጃ መሄድ ያስፈልጋል፤ በእንዲህ መልኩ የሚሻሻል ከሆነ ሥልጣን ላይ በተቀመጠው አካል ሊደፈጠጥ እና ወደሚፈልገው አቅጣጫ ሊወሰድ ስለሚችል ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ሕገ መንግስት ሲሻሻል ጠንከር ያለና የብዙኃኑን ድምጽ፣ ሀሳብ እና ይሁንታ ያገኘ ሊሆን ይገባዋል፤ የሕገ መንግስት ማሻሻያን በተመለከተ ሁለት አንኳር ነጥቦች ይነሳሉ፡፡ የመጀመሪያው ሀሳቡን ስለማመንጨት /initiation/ ወይም ምክረ ሀሳብን ስለማቅረብ ነው፡፡ በቀጣይ ደግሞ ማን እንደሚያሻሽለው የሚደነግገውን ነው፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ተወካዮች እና  የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በጋራ ስብሰባ በ2/3ኛ ድምጽ ሲያጸድቁት ነው፡፡ ይህንን የሕገ መንግስት ማሻሻል ጥሩ ምርጫ ሆኖ ሳለ ተመራጭ የማያደርገው የብዙኃኑን ድምጽና ውይይት እንዲሁም ይሁንታ የሚፈልግ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ እነዚህ ምክር ቤቶች ብቻቸውን አይወስኑም ሰፊ የሕዝብ ውይይት እና ስምምነት ይፈልጋል፡፡ ከማሻሻያው በኋላም የመንግስት ሥልጣን ምን ይሁን የሚለውን ለመወሰንም አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 62 (1) መሠረት ሕገ መንግስቱን የመተርጎም ሥልጣን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሰጣል፡፡ መንግስት በተናጠል ካቀረባቸው አማራጮች ከነችግሩ ይሄኛው ይሻላል የሚል እምነት አለን፡፡ ፓርላማውም በይሁንታ ወደፌደሬሽን ምክር ቤት የመራው ይሄንኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እዚህም አማራጭ ላይ ትልቅ ሥጋትና ድክመት እንዳለ ሳይጠቀስ ሊታለፍ አይገባም፡፡ የምክር ቤቱ ገለልተኛነት! እንደሚታወቀው ፌደሬሽን ምክር ቤቱ የቅርብ ጊዜያት ግብሩ እንኳን ቢታይ የበዙ ቀጥታ የሚመለከቱት ጥያቄዎች ቀርበውለት በቸልታ ወይም ባላዬ ያለፈ ምክር ቤት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር የሚነሱ ገዢው መንግስት ሀሳብ ማስፈጸሚያ እጅ መሆን፣ የአባላቱ ብቃትና እውቀት/Professionalism/ እንዲሁ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባ ነው፡፡ 
በሌላ በኩል የሽግግር መንግስት ከተለያዩ አካላት ተደጋግሞ የሚነሳ መፍትሔ ሀሳብ ስለሆነ እሱም ላይ ሰፊ ውይይት፣ ትንተናና ክርክር ለማድረግ ሞክረናል፡፡ የመጀመሪያው የሽግግር መንግስት ለማለት የሕግ መሠረት የለንም፡፡ ሕጋዊ መንግስት እያለና ምርጫ አላካሂድም ባላለበት ሁኔታ ይህ አማራጭ አይታሰብም፡፡ ከ100 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች ባለባት እና ዋልታ ረገጥ (Polarized) የሆነ አቋምና አስተሳሰብ በሚራመድባትና እነኚህ አመለካከቶች ወደመሐል እንዲመጡ ሥራ ባልተሠራበት ሁኔታ ውስጥ ተወያይቶ መግባባት ይቻላል ማለት ሆድ ሲያውቅ… ይሆንብናል፡፡ በዚያውም ላይ የወረርሽኙ ጠባይ በውል ባልታወቀበትና ከፍተኛ ሥጋት ወቅት መወያየትስ ይቻላል ወይ? አዲስ ተረካቢ መንግስትስ አሁን ያለውን አጣብቂኝ ምኑን ከምን ሊያደርገው? ብሎ ማየት ይገባል እንላለን፡፡ 
 እንግዲህ የገባንበት አጣብቂኝ አለ፡፡ የገዢው መንግስት ከጥንካሬ ጉድለት እስከ ጠቅላይነትና ወንበር የማደላደል አዝማሚያ በሚዛኑ ሌላ ጎን የሚቀመጡ ናቸው፡፡ የምንመርጠውም ምርጫ እነኚህን የሚያስታርቅ፣ ሀገርን ከገባችበት ችግር የሚያወጣ መሆን ይኖርበታል፡፡ 
እናት ፓርቲ ሕጋዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ ተጣምረው ቢወሰዱ ከገባንበት አጣብቂኝ ያወጣናል ብሎ አበክሮ ያምናል፡፡ ሆኖም በእያንዳንዳቸው ውስጥ ቢሆኑ ያዋጣል የምንለውን እናስቀምጥ፡፡
የመፍትሔ ሀሳብና ቅድመ ሁኔታዎች፡- 
ፓርቲያችን የሕገ መንግስት ትርጉም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት መጠየቅ የሚለው ሀሳብ የተሻለ በመሆኑ የሚቀበለው ሲሆን በተጨማሪም ግን ፓለቲካዊ መፍትሔም ካልተጨመረበት ይህ ብቻውን ከገባንበት ቅርቃር ያወጣናል ብሎ የማያምን ሲሆን ከዚህ በታች የተገለጹት ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት እንዳለባቸው በአጽንዖት ያስገነዝባል፡፡
ቅድመ ሁኔታዎች/Conditions/፡-
  • የሕገ መንግስት አጣሪ ኮሚቴ ውሳኔ የሚሰጥበት አካሄድ፣ ግልጽና አሳታፊ መሆን ይኖርበታል፤ የሚሰጠው ትርጓሜም የተወሰነና ዓለማው የተገደበ (Limited and Purposive) መሆን ይኖርበታል፡፡ 
  • የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ የሕግ ባለሙያዎችን፣ ምሑራንንና የሚመለከታቸውን ሲቪክ ማኅበራት ወዘተ  በማሳተፍ ሕጋዊ፣ ሙያዊ፣ ግልጽና ተአማኒነት ያለው መሆን ይኖርበታል፡፡
  • የሚሰጠው ሕገ መንግስታዊ ትርጓሜ ዴሞክራሲዊ ባህልን ሊያጎለብት፣ ነጻና ፍትሓዊ ምርጫ ለማካሄድ በሚቻልበት አግባብ ሊሆን ይገባል፡፡
  • ካለንበት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ውድቀትና እጅግ ተስፋፊና ገዳይ ወረርሽን/pandemic/ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊታደግ የሚችልበትን ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆን ይኖርበታል፡፡ 
  • ለቀጣይ የሕገ መንግስት ማሻሻያዎችና መሰል ትርጉሞች የተሻለ በር የሚከፍትና ጥሩ ልምድ ጥሎ የሚያልፍ እንጂ እንደመጥፎ ልምድ ተወስዶ እንደዶግማ ከተጻፈ ተነክቶ የማያውቀውንና “ጉድለት የበዛውን” ሕገ መንግስት ጭራሽ የማይደፈር እንዳያደርገው በከፍተኛ ሓላፊነትና ጥንቃቄ እንዲከወን ማድረግ፤ 
  • በዚህ ረገድ ያሉ ዓለምአቀፍ ልምድን የዳሰሰ መሆን ይኖርበታል፡፡
  • በሌላ በኩል ፓለቲካዊ መፍትሔው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያሳተፈ የሽግግር ጊዜውን እንዴት ለሀገር ግንባታ፣ ለብሔራዊ እርቅና መግባባት እንጠቀምበታለን? የሚሉ በጋራ ታስበው በጋራ የሚከወኑ መርሐ ግብራት አስፈላጊ ናቸው፡፡
  • ከምርጫው በኋላም ሊፈጠሩ የሚችሉ ሥጋቶችንና አደጋዎችን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል ፖለቲካዊ መፍትሔን የግድ አብሮ እንዲፈጸም ንግግሩ አስገዳጅ ነው ብለንም እናምናለን፡፡ 
  • መንግስት ወረርሽኙን እንደ አንዳንድ ዓለም ሀገራት ፖለቲካ በማድረግ ለራሱ ሥልጣን ማራዘሚያና የምርጫ ወንበር ማግኛነት ሊጠቀምበት ይችላል የሚል ሥጋት ፓርቲያችን ያለው ሲሆን ይህንንም ሀቀኝነተን በተላበሰ ሁኔታ ሊመራው እንደሚገባና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመሻገር ሁሉን አቀፍ  እና ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርበታ እንላለን፡፡
  • የምርጫው ሂደት በመንግስት ቁጥጥርና ፍላጎት ሥር ሊወድቅ የማይችል መሆኑን ሊያረጋግጥ በሚችልበት አኳኋን ሊከወን ይገባል፡፡
  • ለዚህም ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ የመንግስትን እንቅስቃሴና ተግባር በአባታዊ፣ ጠባቂነት መንፈስ በጋራ የሚሠራ ለኅሊናቸው ተገዥ ከሆኑና ማኅበረሰቡ በሚመርጣቸው ከሀይማኖት ተቋማት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሀገር ሽማግሌዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት የተውጣጣ አንድ ስብስብ/watchdog/ በማስቀመጥ እንደ ጸጥታ ተቋማት፣ ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤት የመሰሉ ለቀጣዩ ምርጫ ወሳኝ ሚና ያላቸውን ተቋማት በንቃት የሚጠብቅ፣ መንግስት እነዚህን ተቋማት እጅ ጠምዝዞ እኩይ ምግባራትን ቢፈጽም፣ ሀዲዱን ቢስት የሚገስጽና ማኅበረሰቡን የሚያነቃ ስብስብ/Organ/ ማቋቋም አስፈላጊ እንደሆነ ፓርቲያችን ያምናል፡፡
ለመላው የሀገራችን ሕዝብ፡-
ብዙ ጥሩ ምርጫዎች ኖረውን ከዚያው መሐል የምንመርጥ ቢሆን እንዴት በታደልን ነበር፡፡ የሆነው ግን እንደሱ አይደለም፡፡ የሆነው ተቃራኒው፣ ከብዙ መጥፎ አማራጮች የተሻለውን መጥፎ የምንመርጥ መሆኑ ታውቆ ሰው ከሰው ጋር፣ ማኅበረሰብ ከማኅበረሰብ መስተጋብሩን ይበልጥ ማጠንከርና መተዛዘን እንጂ አጋጣሚ በተፈጠረ ቁጥር ወጊድልኝ በመባባልና በመገዳዳል፣ የውሸትና ሴራ ትርክቶችን እያደባለቁ በመበላላት እንደማንወጣው ታምኖ በጣም በጥንቃቄ ይህን ጊዜ እንድናልፈው አበክረን እንገልጻለን፡፡ ሕዝብ ያለመንግስት ኖሮ ያውቃል መንግስት ግን ያለሕዝብ በባዶ ሜዳ ኖሮ አያውቅምና ራስን የመግዛት ባህላችንን እንድናጎለብተው ከአደራ ጭምር ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡  
ለሃይማኖት ተቋማት መሪዎች አባቶቻችን፡-
ወደፊት መጥታችሁ አባታዊና መንፈሳዊ ልዕልናችሁን ተጠቅማችሁ ማንንም ሳትፈሩና ሳታፍሩ በጥፋቱ መገሰጽ፣ መፍትሔ ማመላከት ከመቸውም ጊዜ በላይ ይጠበቅባችኋልና ይህን ባታደርጉ እዳ በደሉ በታሪክ ፊት የሚያስወቅሳችሁ እንደሆነ ማስታወስ ብቻ እንወዳለን፡፡ 
የፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎች፡-
በእንዲህ ዓይነት ዙሪያው ገደል በሆነበት ወቅት በእናታዊ ጠባይ በሁሉን አቃፊነት፣ ይቅር ባይነትና እንተ ትብስ አንቺ ትብሽ በመባባል እንድናልፈው፣ በአንጻሩ ደግሞ የሀገራችሁን ሁኔታ ነቅቶ በመከታተል፣ በመረጃና ማስረጃ በመደገፍ ስለመብታችሁ ያለፍርሃት እንድትሞግቱ አደራ አንላለን፡፡ 
ዓለምና ሀገር አቀፍ ሲቪክ ማኅበራትና ተቋማት፡-
ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚመጥን ሥርዓት እስኪዘረጋ ውሎ ከመግባትና ጊዜ ከመቁጠር ያለፈ፣ የመጣውን ከማዳነቅ ያለፈ ሚና ተጫወቱና አሳዩን፣ እርዱን እንላለን፡፡ 
ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፡-
አሁን ይበልጥ የምንፈተንበትና ለታሪክ ተጠያቂነት የምንዳረግበት ጊዜ ከፊታችን አፍጥጦ መጥቷል፡፡ መቸም ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን ቁጭ ብለው ሲጫወቱ አንዱ የሌላኛውን አባት በባንዳነትና በጥቅም ፈላጊነት እየከሰሰና እየሰደበ ሲያሸማቅቀው ማየት የምንሻ ያለን አይመስለንም፡፡ ብዙ ሳንርቅ በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ወቅት ተከስቶ ለመናገር እስኪያሳፍር ድረስ ስማቸውን ስንጠራቸው የምንሸማቀቀው ሰዎች ቤተሰብ እማኞቻችን ናቸው፡፡ ስለሆነም ከራስ ጥቅምና “ቡድን” ፍላጎት ወጥተን፣ አሁንም ከገልባጭነትና የራስን አንቋሾ ከመነሳት ርቀን በየጓዳችን ካሉ መፍትሔዎች መልከኛውን ሰንቀን በምክክሩ አደባባይ እየተገናኘን እንደየአቅማችን ተሟግተንና ተፋጭተን የተሻለውን እየወሰድን ይህችን በችጋርና ረሃብ የምትታወቅ ሀገር እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንታደጋት፣ ልጆቻችን ሌላ የአበሳ ዓመታት ሳይሆን ነጋቸውን በናፍቆትና በብዙ ተስፋ የሚኖሩበት ዘመን ለማድረግ እንድንተጋ እናታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ 
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅልን
ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም
እናት ፓርቲ


አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...