ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, May 18, 2020

የዓባይ ግድብን፣የሱዳን እና የአፍሪካን ቀንድ በተመለከተ የተጠናቀረ - ልዩ ወቅታዊ


ሰኞ ግንቦት 10/2012 ዓም 
=================
በእዚህ ዘገባ ስር የሚከተሉትን ርዕሶች ስር ማብራርያ ያገኛሉ።
>> የዓባይን ግድብ ውሃ ሙሌት በተመለከተ ኢትዮጵያ ቁርጥ ያለ መልስ በውጪ ጉዳይ በኩል ሰጥታለች

>> የሱዳን ልዑክ በኢትዮጵያ ስለ ምን ተወያየ? የሱዳን በግድቡ ጉዳይ የመዋዥቅ ምክንያት

>> በግድቡ ዙርያ የኤርትራ ግልጥ አቋም ምንድነው? ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በው ጪ ጉዳይ እና በወታደራዊ ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም ቶሎ የመድረሳቸው አስፈላጊነት

>> የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ አጣብቂኝ ውስጥ እንዳይገባ ኢትዮጵያ አጥብቃ መከተል ያለባት መንገድ

******************
የዓባይን ግድብ ውሃ ሙሌት በተመለከተ ኢትዮጵያ ቁርጥ ያለ መልስ በውጪ ጉዳይ በኩል ሰጥታለች 

ግብፅ የዓባይን ጉዳይ ፖለቲካዊ ለማድረግ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ብትመራውም በዓለም ላይ ቁጥር አንድ ለሆነው ለኮሮና ወረርሽኝአንድ ጊዜ ብቻ እንደተነጋገረ የሚወራለት ምክርቤቱ በዓባይ ጉዳይ ላይ ገፍቶ የሚሄድበት ምንም መንገድ ሊኖር እንደማይችል የብዙዎች ግምት ነው።በእዚህ ላይ በፀጥታው ምክርቤት አባላት ውስጥ ያለው ወቅታዊ ፍጥጫም፣ እንበል አሜሪካ ጉዳዩን አሁን ብታነሳው የግድቡ ጉዳይ የመካከለኛው ምሥራቅን  በተዘዋዋሪ የመቆጣጠር ጉዳይ ስለሆነ ቻይናም ሆነች ሩስያ ጉዳዩ ላይ እንዲገቡ ዕድል የሚሰጥ ስለሆነ ቢያንስ አሜሪካ በተወሰነ ደረጃ የቅርቦቹ ውይይቶች ላይ ስለነበረች ከእጄ የወጣ ጉዳይ ነው የማለት ያህል ቢያንስ አሁን የፀጥታው ምክር ቤት የሚነሳበት ''ወርቃማ'' ጊዜ እንዳልሆነ ማሰብ ያቅታታል ማለት አይቻልም።ስለሆነም መንገዶች ሁሉ የሚያሳዩት ዝናቡን ለመምጣት ያበቃው እንጂ ኢትዮጵያ በትክክል ግድቡን የመሙላት ስራዋን በፍጥነት መጀመር የኢትዮጵያ ወርቃማ ጊዜ እንደሆነ ነው።

 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ አምሳሉ ትዛዙ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት ''የግድቡን ውሃ  በተመለከተ ለእነርሱ(ለግብፆች እና ሱዳኖች) ማሳወቅ አይጠበቅብንም።ግድቡ ስራው  ሲደርስ ውሃ መሙላት ቀጣዩ ሥራ እንደሆነ እነርሱ  የሚያውቁት ጉዳይ ስለሆነ እኛ ማሳወቅ ያለብን ጉዳይ አይደለም።ውኃ የመሙላቱ ሂደት የግንባታው አካል እንደሆነ እና ግንባታው የሆነ ደረጃ ሲደርስ ውሃ እንደሚሞላ ያውቃሉ።'' ብለዋል።
There is no way that we have necessarily inform them (Egypt and Sudan) when we will start filling. Nothing is expected of us with regard to the filling of dam. This is because they know that will happen when construction of the dam reaches at a certain level and after all it is being built to be filled. We do not have the obligation of informing,” Amsalu Tizasu spokesman of Ethiopian foreign Affairs minister.

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ አምሳሉባለፈው ዓርብ ግንቦት 7/2012ዓም  በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ላይ በተለቀቀው  መግለጫቸው ላይ በግልፅ ደግመው እንዳሳወቁት ''ኢትዮጵያ የውሃውን ሙሊት በተመለከተ ማሳወቅ ያለባት ምንም መንገድ የለም'' ብለዋል።
“There is no way that we have necessarily inform them when we will start filling.''

የግብፅ ለፀጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ማስገባቷን አስመልክተው ቃል አቀባዩ ሲናገሩ።የግብፅ ደብዳቤ በነበረው የድርድር ሂደት ላይ ምንም የሚያመጣው ውጤት አይኖርም ካሉ በኃላ ኢትዮጵያ ለግብፅ ደብዳቤ ምላሽ እንድትሰጥ በግልጥ እስካሁን ከማንም አካል አልተጠየቀችም ሆኖም ግን እኛ ለምላሽ የሚሆን የዲፕሎማሲ ሕግ ባለሙያዎቻችን እና የውሃ ኤክስፐርቶቻችን የተሳተፉበት ዝርዝር መረጃ የያዘ ዶክመንት አዘጋጅተናል አስፈላጊው የመንግስት ውይይት አድርገን በቶሎ የሚላክ ነው'' ብለዋል።

የሱዳን ልዑክ በኢትዮጵያ ስለ ምን ተወያየ? ሱዳን በግድቡ ጉዳይ የሱዳን መዋዥቅ ምክንያት 

ይህ በእንዲህ እያለ የኢትዮ-ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተለይ በድንበር ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ኢትዮጵያ የገባ እና ካለፈው ሳምንት ማገባደጃ ጀምሮ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ጋር መወያየቱ በመቀጠልም በዝርዝር ጉዳዮች ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ለሁለት ቀናት ተወያይቷል።ውይይቱ ዛሬ ሰኞ ማምሻውን ያበቃ ሲሆን  ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውይይቱ መጠናቀቁን አስመልክቶ የተገኘው ቃል እንዲህ ይላል - 
''በሁለቱ ወገኖች በተደረገው ውይይት በተለይ በሁለቱ አገራት አዋሳኝ አካባቢዎች በየጊዜው የሚያጋጥሙ የጸጥታና የደህንነት ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ እና የሁለቱን አገሮች የድንበር ጉዳይ በተመለከተም የህዝቦችን አብሮነትና የግንኙነቱን ታሪካዊ ዳራ ግምት ውስጥ በማስገባት ማስቀጠል የሚያስችል ውይይት ተካሂዷል።
ውይይቱ በሁለቱ አገራት አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፤ ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውር፣ አፈናና የመሳሰሉ ህገ ወጥ ድርጊቶችን በጋራ ለመከላከልና መፍትሄ ለመሻት የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጧል። በአካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች ተረጋግተው ያለምንም መስተጓጎል የእርሻ ስራቸውን መቀጠል እንዳለባቸው እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ የመጣ የደህንነት ስጋት እና የነዋሪዎችን የተረጋጋ ህይወት የሚያውኩ አዳዲስ የጸጥታ ሃይል እንቅስቃሴዎች በአፋጣኝ እንዲስተካከሉ በተደረገው ውይይት የጋራ ግንዛቤ ተይዞበታል''
የዛሬው ውይይት መደምደምያ ላይ የታወቀው ሌላው ጉዳይ፣ የኢትዮ-ሱዳን ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ ስብሰባ በሰኔ ወር 2012 ዓም አጋማሽ በካርቱም ላይ ለማድረግ መስማማታቸው ነው።።ሱዳን በግድቡ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በውስጥ ፖለቲካ እየተናጠች በመሆኗ ወጥ የሆነ አመለካከት በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ላይ ለመያዝ ተቸግራለች።የሽግግር መንግስቱ ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት እያያሻሻለ ቢመጣም፣ሱዳንን እንደ ዋና የውጭ ፖሊሲያቸው ማስፈፀምያ ሊጠቀሙ የሚፈልጉ ኃይሎች በተለይ ቱርክ፣ግብፅ፣ሳውዲአረብያ እና ኩዋታር አዲሱን የሱዳን መንግስት በሚፈልጉት መልክ ለመቅረፅ ወይንም አዲስ መፈንቅል አድርገው ሌላ የሚመቻቸውን መንግስት ለማምጣት ሩጫ ላይ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።ስለሆነም የሱዳን መንግስት ሁለት፣ሶስት ዓይነት ካርዶችን የሚጫወተው በውስጡ ካሉት የተለያዩ ኃይሎች ፍላጎት ጉተታ አንፃር መሆኑን መረዳት ይቻላል። ባለፈው በአረብ ሊግ ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ላይ የሚያድም ሰነድ ላይ ያለመፈረም ቆራጥ እምቢተኝነት ያሳዩትን አመለካከት አሁን ለመድገም የተቸገሩት ከእዚህ አንፃር እንደሆነ መገመት ይችላል።
ይህ ማለት ግን ሱዳን አደገኛ አካሄድ አትሄድም ማለት አይደለም።ምክንያቱም ሱዳን የውክልና ጦርነት ወይንም ግጭት ከኢትዮጵያ ጋር እንድታደርግ እና ኢትዮጵያን እንድትረብሽ ጦርነቱን ተከትሎ የሚመጣወጪ ብቻ ሳይሆን ሌላ ጠቀም ያለ ድጎማ ለመስጠት የምያባብሉ አገራት አሁንም የሉም ማለት ሞኝነት ነው።ሰሞኑን የሱዳን ከፍተኛ ልዑክ በኢትዮጵያ መጥቶ የሚወያየው ከእዚህ በፊት ቀዝቀዝ ብሎ የነበረውን የድንበር ጉዳይ እንደ አዲስ እንዲያነሱ ከመካከለኛው ምስራቅ አለቆቻቸው የተሰጣቸው የቤት ሥራ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ማንም የሽግግር መንግስት የድንበር ጉዳይን እንደ አፋጣኝ አጀንዳ አድርጎ የማንሳት ልማድ በብዙ አገሮች አይታይም። በሽግግር ወቅት ከሁሉም ጋር ሰላማዊ ሁኔታ መፍጠር የተለመደ ነው።ስለሆነም የሱዳን ተለዋዋጭ ሁኔታ በቀጣይ ቀናትም ሊቀጥል ይችላል።

በግድቡ ዙርያ የኤርትራ ግልጥ አቋም ምንድነው? ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በው ጪ ጉዳይ እና በወታደራዊ ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም ቶሎ የመድረሳቸው አስፈላጊነት
የዓባይን ግድብ በተመለከተ አቶ ኢሳያስ እስካሁን በግልጥ የተናገሩት ጉዳይ ብዙም ለአደባባይ አልበቃም።በእርግጥ አቶ ኢሳያስ በእዚህ ዓይነት ወሳኝ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተቃራኒ ቦታ ይይዛሉ? ወይንስ አይዙም? ሱዳንን ለማባባል እንደተሞከረ እሳቸውንስ ላይ ሙከራው የለም? እዚህ ላይ አንድ መሰረታዊ ጉዳይ አቶ ኢሳያስን ያህል የመካከለኛውን ምስራቅ ስነ ልቦና የሚያውቅ ላይኖር ይችላል።ከሱዳን ያአሁኑ መሪዎች በላይ ጥርሳቸውን የነቀሉበት ጉዳይ ነው።አረብኛ ተናጋሪው ኢሳያስ በጀብሃ ላይ እርምጃ ከተወሰደ በኃላም ሆነ በፊት ካይሮ የውሃ መንገዳቸው ብቻ ሳትሆን የመጀመርያ የድርጅታቸውን ካፒታል ካይሮ ላይ በተከፈተ የነዳጅ ማደያ ንግድ የጀመሩ ናቸው።ሰውየው የአረቦችን እጅ የመልመዳቸውን ያህል ተንኮላቸው እና ልባቸውን ያውቁታል።ስለሆነም በኢትዮጵያ ላይ ቀንደኛ አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች እና የሱዳን የከሰሩ ባለስልጣናት ሳይቀሩ ከእዚህ በፊት ምን ያስቡ እንደነበር አሁንም ምን ዓይነት ተንኮል እንደሚያውጠነጥኑ ያውቃሉ ወይንም ካለፈ ልምድ ግምታቸው ለእውነት የቀረበ ይሆናል።
አሁን ጥያቄው ለኢሳያስ ውሃ፣ የእርሻ ምርት፣ትልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል የምታመነጭ እና ከመቶ ሚልዮን ሕዝብ በላይ የገበያ ዕድል ያላት ኢትዮጵያ ነች ወይንስ በሶስት ጎራ ተከፍሎ ሊራኮት ጫፍ የደረሰ እና የኃይል ምንጩ ነዳጅ በሌላ ኃይል እየተቀየረ ያለው የመካከለኛው ምስራቅ ነው ለነገ የሚያዋጣው? የሚለው ነው።የእዚህ መልስ ለአቶ ኢሳያስ ግልጥ ነው።ይህ ሲሆን ግን አንዳንድ ነገሮችን በማቀበል ከኢትዮጵያ በኩል ሳይታወቅ የሚሰሩት ሥራ የለም ብንል እራስን ማታለል ነው።ሆኖም ግን ከእዚህ ባለፈ በተቃራኒ የሚቆሙበት ምንም ሜዳ ግን አይኖርም።
አንዳንዶች አሁን በአቶ ኢሳያስ እና በኢትዮጵያ መሃከል ያለው መልካም ግንኙነት አቶ ኢሳያስ ስሌት የተሳሳተ አድርገው ያስባሉ።አቶ ኢሳያስን የሚወቅሱት ደግሞ ከአቶ ኢሳያስ የባሱ የመገንጠል ዘብ የቆሙ በራሳቸው ዙርያ ያሉ ባለስልጣኖቻቸው ናቸው። እዚህ ላይ ኢትዮጵያ ወደብ የማግኘቷ ሂደት እና በዝርዝር የኢኮኖሚ ግንኙነት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ መንግስት በሚያደርጋቸው ንግግሮች ላይ ነገሩ ቀስ እንዲል የሚጥሩ አሉ።ሆኖም ግን እዚህ ላይ አቶ ኢሳያስም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አልተሳሳቱም።ይልቁንም ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለራሳቸው ሲሉ የጋራ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ እና የጋራ መከላከያ ስምምነት በፍጥነት መፈራረም አለባቸው። ምክንያቱም አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ ፅንፍ ኃይሎች ሁለቱን ማለያየት የመጀመርያ ምዕራፍ፣በመቀጠል ደግሞ ሁለቱንም ማጥፋት አጀንዳቸው ከሆነ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ሆኖታል።የኤርትራን መገንጠል በገፍ በደርግ ዘመን ሲደግፉ የኖሩትም ከእዚሁ ምዕራፍ አንድ ስልት አንፃር ነበር።አሁን በድንገት ሁለቱ አገሮች መግጠማቸው የቀይ ባህር ጉዳይ ከእጃቸው እንደሚወጣ ያስባሉ።አቶ ኢሳያስ አንድ ሺህ ኪሎሜትር የምያካልለውን የቀይ ባህርን የመቶ ሚልዮን ሕዝብ ባለቤት ከሆነች ኢትዮጵያ ጋር ሆነው ካልሆነ መጠበቅ እንደማይችሉ ሁሉም ያውቀዋል።በእዚህ ላይ አቶ ኢሳያስን የሃማሴን ደገኛ እና የቆላው ኤርትራ በሚል በውስጣቸው ለመከፋፈል እና ኤርትራ ላይ የፅንፈኛ መንግስት ለማቆም እነኝህ ፅንፈኛ አገሮች ብዙ ጊዜ ሞክረዋል። ሙከራው የመፈንቅለ መንግስት እስከማድረግ የደረሰ እና አሁንም ድረስ ያልቆመ የውስጥ ውጥረት ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ የአሁኑ ግንኙነት ወደበለጠ ደረጃ ማደግ ሳይወዱ በግድ ማድረግ ያለባቸው ይህ ካልሆነ ግን ከፍተኛ የውጭ ጥቃት ሁለቱንም ሊያጋጥማቸው ይችላል።
ስለሆነም አቶ ኢሳያስ የኢትዮጵያ ግድብ ላይ የግብፆችን ወይንም የሌላ ተቃራኒ አገር ስሜት የሚያስተናግዱበት ምንም ዓይነት ቦታ ለጊዜው አሁን የለም።ይህ ማለት ግን ገለልተኛ ሆነው በመቆየት ክፉውን ጊዜ ሊያሳልፉ መሞከራቸው አይቀርም ማለት አይደለም።ይህ ግን እስከ መቼ? የሚለውን ጥያቄ ያመጣል።ምክንያቱም ውጥረቶች እየባሱ ሲመጡ ከእኛ ነህ ከእነርሱ? የሚል የ''ሰኔ 30'' ዓይነት ጥያቄ ይፈጥራል። ይህ ጊዜ ሳይመጣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በውጪ ፖሊሲ በተለይ በአፍሪካ ቀንድ እና በመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ እና በወታደራዊ የጋራ ስምምነት ላይ አንድ ዓይነት ስምምነት ላይ መድረሱ የጋራ ጥቅም ማስከበሪያ አንዱ መንገድ ነው።እዚህ ላይ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን በቀይ ባሕር ላይ የመመስረት እና የአሰብ ወደብ ጉዳይም በፍጥነት የማግኘት መብቷ መከበር አለበት።ይህ የልመና ወይንም የበጎ ቸርነት ጉዳይ አይደለም።አቶ ኢሳያስ በቀላል የመደመር ስሌት ኢትዮጵያን ወደ ቀይባሕር አምጥቶ የኤርትራንም ሆነ የኢትዮጵያን የፀጥታ ጉዳይ ማረጋገጥ ወይንም በቀላሉ በፅንፈኛ ኃይሎች መጥፋት መሃል ቀላል ምርጫ ቀርቦላቸዋል።
እዚህ ላይ የህወሓት እና የአቶ ኢሳያስ ፀብ ጉዳይ እንደ የውስጥ ጉዳይ ተመልክተን በሂደት ህወሓት በዲሞክራሲያዊ የትግራይ ወጣቶች ስትተካ የሚስተካከል ውስጣዊ ጉዳይ ነው ከሚል እሳቤ በመነሳት ነው።ሆኖም ግን ህወሓት አሁን እንዳለው የተነጠለ ፖለቲካ የማራመድ ዕድሉን ካገኘች ለምስራቅ አፍሪካ ሌላዋ አደጋ መሆኗ እና ለውጭ ኃይሎች መረማመጃ አጀንዳ አስፈፃሚ እንዳትሆን ያሰጋል።ጉዳዩ በሂደት የሚታይ ነው።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ አጣብቂኝ ውስጥ እንዳይገባ ኢትዮጵያ አጥብቃ መከተል ያለባት መንገድ
የኢትዮጵያ የግድብ ውሃ መሙላት ሂደት ኢትዮጵያ አጣድፋ ልትጀምረው የሚገባ አመቺ ጊዜ ላይ ነች።በሌላ በኩል የሰሜን ሱዳንን ወደ ምስራቅ አፍሪካ እና መካከለኛው እንዲሁም ደቡባዊ አፍሪካ አክራሪነትን ለማስፋፍያ እንደዋና በር የሚጠቀሙት ከላይ ልማታዊ ውስጣቸው ግን የሽብር ቡድኖችን የሚያስፋፉ አገሮች አጥብቀው የሚፈሩት የኢትዮጵያ፣ኡጋንዳ፣ኬንያ።ደቡብ ሱዳን፣ኤርትራ እና ጅቡቲን ጥምረት እና የጋራ የውጭ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ፖሊሲ መቅረፅ ነው።እዚህ ላይ የምዕራቡ ዓለምም ሰሜን ሱዳንን እንደመረማመጃ አድርገው አክራሪነት ወደ አፍሪካ ለማስፋፋት ፍላጎት ያላቸውን ኃይሎችን አይደግፍም ተብሎ ይታመናል።ለእዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ በእነኝህ የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ውስጥ የፖለቲካም ሆነ ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅም ስላላቸው የእነኝህ የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ስምምነት፣ ቢያንስ በሱዳን አስጊነት ላይ እና ከጀርባዋ በሚሰለፉ አገሮች በተቃራኒ የሚቆሙ እስከሆኑ ድረስ መደገፉ አይቀርም። ለእዚህ ሁሉ ዋና ሞተሯ እና በሕዝብ ብዛት ከመቶ ሚልዮን የላቀ ሕዝብ ያላት፣በወታደራዊ አቅምም የተሻለ የምትባል ኢትዮጵያ ነች።በመሆኑም የኢትዮጵያ የውስጥ ሰላም በምንም ዓይነት መንገድ መናጋት መላው ምስራቅ አፍሪካን የሚያናጋ እንደሚሆን እና በሱማሌ የመሸገው የአልቃይዳ አንጃ አልሸባብ ሌላ ስጋት በመሆኑ የኢትዮጵያ የተረጋጋ ሰላም አስፈላጊ መሆኑን አሜሪካንን ጨምሮ ሁሉም የሚስማሙበት የማይሆን ጉዳይ ሊሆን አይችልም። በምዕራቡ በተለይ በአሜሪካ በኩል ያለው ሌላ ራስ ምታት የቻይና እግር ኢትዮጵያ ላይ መግባቱ ነው።ቻይና ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ አገሮችንም በብድር ይዛለች።ስለሆነም የቻይና ፕሮጀክት ለምዕራቡ የረጅም ጊዜ ፕሮጀክት ነው።ኮሮናን ከተሻገሩ በኃላ የሚመክሩበት ፕሮጀክት።
ስለሆነም ኢትዮጵያ ከላይ የተጠቀሰውን ሚዛን ጠባቂ ሚናዋ መጉላቱን ከመቸውም ጊዜ ተረድታ የዓባይ ግድብ ስራዋን ማፋጠን እና ከግብ ማድረስ በሌላ በኩል ሙሉ በሙሉ ከቻይና እጅ እንዳትገባ ብዙ አሰራሯ፣የተማረው ኃይሏ እና የገንዘብ ምንጩም ከምዕራቡ ከመሆኑ አንፃር ዲፕሎማሲዋ ገለልተኛ እና ከሁሉም ልትጠቀም የምትችልበትን ማዕከላዊ መስመር ተከትላ እና ከአፍሪካውያን ጋር ወዳጅነቷን አጠናክራ መቀጠል ይገባታል። እዚህ ላይ አንዳንድ መንግስት ውስጥ ያሉ ምሁራን በስሜት ወደ አንዱ ኃያል መንግስት ያጋደለ ስሜት እንድታሳይ በመገፋፋት የሚደረጉ አጉል አካሄዶችን በትክክል መቆጣጠር እና ከሁሉም ጋር ያላት መልካም ግንኙነትን ማራመድ ይጠቅማታል።በግድቡ ዙርያም በተመሳሳይ መንገድ ግብፅ ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት የወሰደችበት አንዱ እና ዓይነተኛው መንገድ ፖለቲካዊ ቃና ለመስጠት ስለሆነ መጪው የኢትዮጵያ ጥንቃቄም አንዱን ሃያል በአንዱ የማስፈራራት ሳይሆን ሁሉም ለልማቷ እንደሚጠቅሟት ተረድታ የገለልተኛ ግን የራሷን ጥቅም በምንም ዓይነት መንገድ ለድርድር የማያቀርበውን መስመር መከተል ቢያንስ ባለፈው ክፍለዘመን ከተሰሩት ስህተቶች ያድናታል።የደርግ የውጪ ፖሊሲ ክስረት ዋነኛ መነሻውም ይህ ነበር።ጥቂት ፅንፈኛ ምሁራን አስደንብረው ወደ ቀድሞዋ ሶቬትሕብረት ጎራ ሲያስገቡት ፣ግንኙነታችን ገለልተኛውን መስመር ፣ምጣኔ ሃብቱ ቅይጥ ኢኮኖሚ እንከተል ያሉትን በፀረ አብዮተኝነት ፈርጆ እርምጃ ያለውን ወስዶባቸዋል።በመጨረሻ እራሱ ደርግ ከመውረዱ ጥቂት ወራት በፊት ቅይጥ ኢኮኖሚ ብሎ ማወጁ ላይቀር ማለት ነው።ስለሆነም ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ጥሩ ሁኔታ የማንንም ኃያል መንግስት ያላዳላ ግን ጥቅሟን ያስከበረ የገለልተኛ መስመሯ አዋጪ ነው።ግድቡን ተከትሎ የሚመጡ ሽምያዎችም ላይ ይህንኑ መስመር ይዛ መሄድ አለባት።እርግጥ ነው የቁርጡ ቁርጥ ቀን ስመጣ ግብፅ በአንዋር ሳዳት ዘመን በአስዋን ግድብ የገባችበት አጣብቂኝ ውስጥ ከገባች ያኔ ሌላ ቀን ይሆናል።ይህ ግን የሃያላኑ ፍጥጫ ከኮሮና በኃላ ከባሰ አጀንዳ በየስርቻው መፈለጋቸው ስለማይቀር ያኔ የሚሆን ነው።ከእዛ በፊት ኢትዮጵያ ግድቡን ከጨረሰች ግን ሁሉ ተረት ይሆናል።ጉዳዩ ማን የበለጠ ኤሌክትሪክ ያግኝ? ማን አያግኝ? ይሆናል።
ጌታቸው በቀለ

ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት 
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant
Gudayachn Multimedia, Kommunikasjon og Konsultent



No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...