ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, May 9, 2020

አትታለሉ! በታኝ ኃይሎች ዛሬ ቀድመው ያሉት በምርጫው ውጤት ማግስት ሊሉት የነበረውን ነው።


አዲስ አበባ Addis Ababa

የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደሰንሰለት ተያይዞ የሚመጣ ነው።ከዘመናት በፊት ኢትዮጵያን የገጠሟት ጠላቶች አዎን! ጠላቶች ናቸው መልክ፣ጊዜ፣እና ድምፅ ቀይረው የመጡት።ኢትዮጵያ የተዳከመች በመሰላቸው ጊዜ ሁሉ በግርግር ከጉዞ ምሕዋሯ አስተው እነሱ ወደሚፈጉት  የሲዖል መንገድ ሊመሯት ይፈልጋሉ።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላለፉት ሁለት ዓመታት የሄደበት ውጣ ውረድ በራሱ ጥሩ ተሞክሮ ነው።ለውጡ ከሰማይ በድንገት የመጣ አይደለም።ዛሬ አንዳንድ አክትቪስቶች የመገናኛ ብዙሃኑን ስለያዙ ብቻ ጧት ማታ እንደሚነግሩን እነርሱ ብቻ ከኮምፕዩተር ጀርባ ተቀምጠው ባደረጉት ቅስቀሳ ወይንም እስር ቤት ወርደው ስለወጡ የመጣ አይደለም። አንድ ትልቅ ዛፍ ለመጣል የዛፍ ቆራጩ እና የገመድ ሳቢው ሚና ወይንም የዛፉ ማርጀት ብቻ መተረክ ያላዋቂነት መለያ ነው። ዛፉ እንዲቆረጥ ቆራጩ ጫካውን አልፎ እንዲመጣ መንገድ የመራ አለ።ቀድሞ ዛፍ በምላጭ እንደማይቆረጥ አውቆ ብረት ከአፈር ለይቶ ያነጠረ፣በመጥረብያ መልክ የሰራ፣የሳለ፣ለመጥረብያው እጀታ ያበጀ፣መጥረብያውን ለሕዝብ ለማድረስ ገበያ ወስዶ የሸጠ ሁሉ ለዛፉ መቆረጥ አስተዋፅኦ አለው።

የኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ፣በ1985 ዓም በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ግቢ እየጮሁ ሕይወታቸው ካለፈው፣በስደት ተንከራተው በምዕራብ አገር ሄደው ለኢትዮጵያ ድምፅ ለመሆን የራድዮ እና ቴሌቭዥን ጣብያ መስርተው ስርዓቱን ካጋለጡት እስከ ኤርትራ በረሃ የትጥቅ ትግል ለማድረግ የሞከሩት፣በፋኖ ተደራጅተው ከተፋለሙት እስከ በቄሮ ተደራጅተው አደባባይ እስከወጡት፣በኢህአዴግ ውስጥ ሆነው ከታገሉት ከአሁኑ አመራሮች እስከ አገር ወዳድ እና በታማኝነት አገሩን እስካገለገለው ባለሙያ ሁሉ ለለውጡ አስተዋፅኦ ማድረጉን መረዳት ይገባል።

በታኝ ኃይሎች ይህንን ሁሉ ክደው እነርሱ መንግስት አውጪ እና አውራጅ፣እነርሱ ብቻ ለለውጥ የታገሉ፣ሌላው ጠባቂ ሆኖ የኖረ፣እነርሱ ብቻ ስልት እና ግብ የሚያውቁ ሌላው የእነርሱን ያህል ያልተማረ፣የማይመራመር እና የማይገባው አድርገው የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ቆይቶ እራሳቸውንም አታልሏቸው አፋቸውን ሞልተው በብቸኝነት ስለለውጡ እንዲያወሩ ብዙዎች በዝምታችን ፈቅደንላቸው ኖረናል።ከአሁን በኃላ ግን ይህ መቆም አለበት።ኢትዮጵያ በክብር ከትውልድ ወደ ትውልድ እስከተሸጋገረች ድረስ እንጂ  የመበተን ዓላማቸውን ባመቻቸው ጊዜ ለማሳካት ከሚጥሩ ጋር ብዙ እርቀት መሄድ አይቻልም።

ሰሞኑን በታኝ ኃይሎች ከህወሓት እስከ ጀዋር መሐመድ፣ከበቀለ ገርባ እስከ አልሸባብ የሚናገሩት ንግግር አንድ ነው።ለሰበብ የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ መቀየሩን እንደምክንያት ያንሱት እንጂ ዋና ግቡ ግን ቀድሞውንም ያሰቡበት ምርጫው ተደረገም አልተደረገ በኃይል አተራምሰው የኢትዮጵያን ማንነት ማጥፋት ነው። ለእዚህ ደግሞ ኢትዮጵያን ቀድሞም ለማጥፋት የረጅም ጊዜ ምኞት የነበራቸው  ባዕዳን የቆየ ዕቅዳቸውን አቧራ እያራገፉ ዛሬ ላይ ለማስፈፀም ከምንጊዜውም በላይ ተጠራርተዋል።

በታኝ ኃይሎች ዛሬ የሚያነሱት ጉዳይ ማለትም የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ መቀየር እና እርሱን ተከትሎ ከመስከረም 30 ወዲህ የሽግግር መንግስት መመስረት አለበት የሚለው አባባል ከምርጫው በኃላም ሊያነሱት የነበረውን ጉዳይ ነው አሁን እየነገሩን ያለው። አሁን ያለው በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የሚመራው መንግስት ምርጫ እንደሚያደርግ ያስታወቀው ከ ስድስት ወራት በፊት ነው። ቀድም ብሎም የምርጫ ቦርድ በሕግ እንዲመሰረት ማድረጉ ይታወቃል።የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ለነሐሴ ወር ተይዞ ቢቆይም በመላው ዓለም በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ሳብያ ምርጫው በነሐሴ ሊደረግ እንደማይችል አስታወቀ።ምርጫው መደረግ የማይችልበት ምክንያት የሚያሳምን ነው።ኮሮና ወረርሽኝ ካለው አደገኛ የመዛመት አቅም አንፃር ምርጫ ማድረግ ይቻላል እያሉ እየሞገቱ ያሉ ህወሓቶች እና የቀሩት በታኝ ኃይሎች ሃሳብ በራሱ ከህዝብ ይልቅ የስልጣን ወንበራቸውን ማጠናከርን ብቻ እንደሚፈልጉ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።

በታኝ ኃይሎች ከጀዋር ጀምሮ በምርጫው ሂደት ይዘውት የነበረው ስልት ሁለት ነው።የመጀመርያው በምርጫው ሂደት ከልባቸው የሚሳተፉ መስለውመቅረብ፣ሂደቱን ማሰናከል እና በመጨረሻ የምርጫው ውጤት ለእነርሱ የማያዳለ ከሆነ በምርጫ ያሸነፈውን ኃይል አሁን እንደሚሉት ሕጋዊ መንግስት አይደለም የሽግግር መንግስት ይመስረት በሚል ሁከት መፍጠር ነው። ይህንን ሃሳባቸውን ሳያውቁት ብዙ ጊዜ ተንፍሰውታል።ለማስረጃነት ጀዋር እራሱ ከቤተመንግሥቱ የአንድነት ፓርክ ጀምሮ የኢትዮጵያ መሠረትነት የሚያሳዩ ነገሮች ጋር አንድነት የፈጠረ ሃሳብ አላቸው ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር መስራት እንደማይፈልግ ብዙ ጊዜ ተናግሯል።ይህ ማለት በምርጫ ቢያሸንፉም አሁን ከሚለው የተሻለ ነገር እንደማይል ጥሩ ማሳያ ነው።

ስለሆነም ለማጠቃለል፣በታኝ ኃይሎች ዛሬ ገና ምርጫው ሳይደረግ የሚያነሱት የግርግር መንግስት ጥያቄ ከምርጫው ማግስት ሊያነሱት የነበረ ጉዳይ እንደነበር እና የምርጫው ሂደትም ሆነ ውጤት ምንም ይሁን ምን ቀድሞም  የነበራቸው ዓላማ አገር በማተራመስ ወደ ስልጣን መውጣት እና ኢትዮጵያን እንዳልነበረች ማድረግ በመቀጠልም ለቀጣሪ ባእዳን አሳልፎ መስጠት እና  የራሳቸውን የስልጣን እና የንዋይ ፍላጎት ከማርካት ውጪ ሌላ ፍላጎት እንደሌላቸው መታወቅ አለበት።በመሆኑም በታኝ ኃይሎች ዛሬ የሚሉት ሁሉ ወደፊት ያሰቡት ተንኮል የነበረና ዛሬ በኮሮና ምክንያት ሳያስቡት የተፉት መርዝ መሆኑን ሁሉም አውቆ ኢትዮጵያ ወይንም ሞት! ብሎ ቆርጦ ሊነሳ የሚገባበት ጊዜ ነው።እርግጥ ነው፣ኢትዮጵያውያን ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ብዙ ሕዝብ ከምጣኔ ሀብት ድቀቱ ሆነ ወረርሽኙ ከሚያስከትለው ጉዳት አንፃር  ቀላል ፈተና አይደለም።ሆኖም ግን አገር የምትፈተነው በእንዲህ ያለ ጊዜ በመሆኑ ለበታኝ ኃይሎች ፈፅሞ ላለመንብርከክ እና አገርንም ለጥፋት ኃይሎች ላለመስጠት በንቃት እና በትጋት መከታተል እና መነሳት ያስፈጋል።ምርጫው የጊዜ ሰለዳው የተቀየረበት ምክንያት አሳማኝም ብቻ ሳይሆን ተገቢ ነው።ከወረርሽኙ በኃላ የሚደረገው ምርጫ የኢትዮጵያ ወሳኝ መንገድ ነው።በታኝ ኃይሎች የሚጨፍሩበት የፖለቲካ መድረክ ከሆነ ደግሞ ምርጫ አስር ዓመትም  ዘግይቶ የአገር ህልውና መከበር ቅድምያ ማግኘት አለበት።


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments: