ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, May 30, 2020

ከሰሞኑ የአሜሪካ ክስተት መንግስት፣የሃይማኖት መሪዎች እና ፖለቲከኞች ምን ይማሩ?

  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ቀደምት ከሆኑት ውስጥ ከመሆኗ ፣ለአፍሪካ እናት ከመሆኗ እና ብዙ የዓለም ጥቁር ህዝቦች በማንነታቸው መኩርያ ከማየታቸው አንፃር፣የሰሞኑን የአሜሪካው ድርጊት እንዳሳዘናት እና እንዳሳሰባት በአባቶቿ መግለጫ መስጠቷ ብዙዎች የአፍሪካ፣የአሜሪካ፣እና የላቲን አሜሪካ ጥቁሮች እና ሌሎች በእኩልነት የሚያምኑ ሁሉ ጆርዎቻቸውን እንዲሰጡ የሚያደርግ መልካም አጋጣሚ ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል።

ክስተቱን ብዙ ነገሮችን አመላካች ነው 


ባሳለፍነው ሳምንት በአሜሪካ ምያፖሊስ አንድ አፍሪካ አሜሪካዊ ጥቁር በሌላ አሜሪካዊ ነጭ ፖሊስ፣ፖሊሱ ጥቁሩን መሬት ላይ አስተኝቶ በጉልበቱ የአንገቱን መተንፈሻ አካል በኃይል በመዝጋት ግለሰቡ ወደ ሆስፒታል ከተወሰደ በኃላ ህይወቱ አልፏል።አንድ አሜሪካዊ ሁኔታውን ሲገልጠው  ''በእዚህ በ21ኛው ክ/ዘመን አንድ ሰው ሌላውን እንደ አውሬ ሕዝብ በተሰበሰበበት ለዘጠኝ ደቂቃዎች አንገቱ ቆሞ ገደለው'' ብሏል።ይህንን ዓረፍተ ነገር ብቻ በደንብ ብናጎላው ብዙ ነገር ይነግረናል።ዘመኑ 21ኛው ክ/ዘመን ሰው ''ሰለጠነ'' የሚባልበት፣የሞተው ሰው እንደ አውሬ ሕዝብ በአደባባይ እየተመለከተ ለዘጠኝ ደቂቃዎች ያህል ታፍኖ፣እነኝህ ዘጠኝ ደቂቃዎች ሙሉ የግለሰቡን ሕይወት ለማትረፍ ከበቂ በላይ ነበሩ።ነገር ግን ዙርያ ያለው ሰው የእራሱ አምሳያ ታፍኖ ሲገደል በሞባይል ፊልም የምቀርፅበት እና ብዙ የሶሻል ሚድያ አድናቂ ለማግኘት የሚሰበሰብበት፣የግለሰቡን ሕይወት ለማትረፍ አንድ ነገር ከማድረግ ይልቅ ቃላትን እየወረወረ ፊልሙን የሚቀዳበት፣ገዳዩ ወንድሙ ጉሮሮ ላይ ቆሞ በኩራት እጁን ኪሱ ከቶ በትዕቢት ተወጥሮ የሚታይበት።አጠቃላይ ትዕይንቱ ሁሉ በደንብ በትነን እና ዘርዝረን ብንመለከተው ብዙ የሚነግረን ማኅበራዊ፣ሞራላዊ እና ፖለቲካዊ መልዕክቶች አሉ።ችግሩ ያለበትን ደረጃ ለመረዳት ግን በአሜሪካ በሚኒሶታ ግዛት የተንሳውን የህዝብ አመፅ ለማስቆም በግዛቷ  የመቶ ዓመታት ታሪክ ውስጥ ለሕዝብ አመፅ ለመበተን ወጥቶ የማያውቀው የአሜሪካ ብሔራዊ ዘብ (ናሽናል ጋርድ) በከተማዋ ውስጥ ከሙሉ ትጥቁ ጋር የወጣበት ነው።የእዚህ ሁሉ ችግር ግን በአንድ ቀን ተሰርቶ ያለቀ ጉዳይ አይደለም።ለዓመታት የተገነባ የተንሸዋረረ የማኅበረሰብ ግንባታ ውጤት ነው።ጉዳዩ ተመልካች ያጡ፣በአግባቡ የሚመራቸው ያላገኙ የልጆች፣ወጣቶች እና አዋቂዎች ሁሉ ድምር ውጤት ነው።ጉዳዩ ከአሜሪካ አንፃር ብቻ ሳይሆን ከዓለም አንፃርም አሁን ያለንበት የዝቅጠት ደረጃ የቱ ጋር እንደሆነ ትንሽ ወደኃላ ሄዶ መንደርደር ስለሚፈልግ ለጊዜው እርሱን ትቼ ከክስተቱ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግስት ምን ይማሩ? ወደሚለው አጭር ሃሳብ አመራለሁ።

መንግስት ምን ይማር?


የኢትዮጵያ መንግስት ከአሜሪካው ክስተት የሚማራቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ።የመጀመርያው እና ዋናው ጉዳይ የፀጥታ ኃይሉን ስነምግባራዊ፣ሞራላዊ፣የሕግ ዕውቀቱ እና ችግር ፈቺ አቅሙን መፈተሽ አለበት።በተለይ ከህዝብ ጋር ዕለት ከዕለት የሚገናኙ ፖሊሶች ላይ ብዙ መሰራት ያስፈልገዋል።ስራው ከባድ፣ጊዜ የሚጠይቅ እና ተከታታይ ተግባራትን ሁሉ የሚፈልግ ነው።ሆኖም ግን ቅድምያ የሚሰጣቸው እና ጊዜ የማይሰጡትን ማስቀደም ይገባል።በኢትዮጵያ በተለይ ያለፈው 27 ዓመት ጥሎብን የሄደው የጎሳ ፖለቲካ ቁስል እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ወደፊት አደጋ ሊሆኑ የሚችሉትን ቦታዎች መለየት እና ቅድምያ መስጠት ግን እጅግ አስፈላጊ ነው። ከእዚህ ውስጥ የአዲስ አበባ ጉዳይ አንዱ እና ዋናው ነው።ከእዚህ በፊት ደጋግመን እንዳልነው አዲስ አበባ የራሷ ስነ ልቦናዊ፣ባሕላዊ እና ታሪካዊ ዳራ ያላት እና ከሌላው አካባቢ ጋር ጨፍላቂ በሆነ ደረጃ መመልከት የማይገባ ከተማ ነች። እዚህ ላይ የከተማዋ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ ዛሬ የእስያ እና የላቲን አሜሪካ መሃል መሸጋገርያ ድልድይ እየሆነች ነው።ይሄውም የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ በመሆኗ፣በኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳረሻ መብዛት እና ባላት ቁልፍ መልከዓ ምድራዊ  አቀማመጥ ሳብያ ነው። 

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ከተማዋ የራሷ በበቂ ሁኔታ የተደራጀ፣ስልጡን፣ብቃት እና አቅም ያለው የራሷ የፖሊስ ኃይል የላትም።በቅርቡ ብንመለከት የአዲስ አበባ አስተዳደር ይህንኑ ጉዳይ ጠይቆ የፌድራል ፖሊስ ከመቆጣጠሩ አንፃር በጀት ከእኔ ወስዶ በሚገባ አላገለገለኝም በማለት በጀት ማቆሙ ሁሉ ተነግሯል።አሁን ሁኔታው ምን ላይ እንዳለ መረጃ ባይኖርም።የአዲስ አበባ መስተዳድርም ሆነ የአዲስ አበባ ሕዝብ ጥይቄ ሁለት ናቸው።አንዱ ከተማዋን የሚመጥን፣የከተማውን ሕዝብ ስነ ልቦና የሚጋራ፣አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ደረጃዋን ከግንዛቤ ያስገባ ፖሊስ ያስፈልጋታል።የሚል ሲሆን ሁለተኛው አሁን ያለውን ህገወጥ የመሬት ወረራ ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎችን የመከላከል ሥራ የፌድራል ፖሊስ አዲስ አበባ በምትጠብቀው ደረጃ እየሰጠ አይደለም  የሚሉት ናቸው።ይህንን በተመለከተ ጉዳያችን ከእዚህ በፊት ያነሳችው ስለሆነ ይህንኑ በእዚህ ሊንክ እንድትመለከቱት እጋብዛለሁ።ጉዳዩ ግን ትኩረት ማግኘት ያለበት ነው።በተለይ የኢትዮጵያን ቀጣይ ሽግግር ለማደናቀፍ ለሚፈልጉ የውስጥም ሆነ የውጭ ኃይሎች በቀዳሚነት የፀጥታ ኃይሉን ከህዝብ ጋር ማጋጨት ዋና ስራቸው በመሆኑ ቀዳዳዎቹን ሁሉ መድፈኑ ተገቢ ነው።

የሃይማኖት አባቶች ምን ይማሩ?

መማር ከሰው ልጅ በሙሉ የሚጠበቅ ነው።አንድ ሰው ሁሉን ነገር ሊያውቅ አይችልም።የሃይማኖት አባቶችም ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ሊያውቁ አይችሉም።እንደማንኛውም ሰው ከአሜሪካው ሁኔታ ምን እንማራለን? ማለት አለባቸው።በመጀመርያ መገንዘብ የሚገባው የሚመስለኝ የማኅበረሰብ መቀየርን በአንክሮ የመከታተል እና የማስተዋል ሥራ የሃይማኖት አባቶች ቀዳሚ  ሥራ መሆን አለበት።ዓለሙ እንዴት እየሄደ እንዳለ እና በምን ዓይነት ደረጃ እና ፍጥነት እየተቃወሰ እንደመጣ ለእዚህ መቃወስ አንዱ ተጠያቂ የእነርሱ በአግባቡ ስራቸውን አለመስራት መሆኑን ማወቅ አለባቸው።ወደ እኛ አገር ሁኔታ ስንመለከት የሃይማኖት ቤቶችን ከመሪዎቹ ይልቅ ሕዝቡ እራሱ ወደመምራት የሄደበት፣ይህም በበቂ ደረጃ ምሳሌ የሚሆነው ሰው ከማጣት የመጣ የተስፋ መቁረጥ ስሜት መሆኑን የሃይማኖት አባቶች መረዳት አለባቸው።በክርስትና ሃይማኖት 12 ሐዋርያት ዓለምን ያውም ምንም ዓይነት  የቴክኖሎጂ መሳርያ በሌለበት ሁኔታ መቀየር ከቻሉ በእዚህ ዘመን ይሄ ሁሉ የሃይማኖት ኮሌጅ፣ቴክኖሎጂ  ባለበት ሰው እንዴት በእዚህ ዓይነት 'የዘቀጠ' የሞራል ደረጃ ወረደ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።

በአሜሪካ ሰሞኑን የሆነው በኢትዮጵያ እንዳይሆን የሃይማኖት አባቶች ምን እንስራ፣ካለፈው ስህተት ምን እናስተካክል?፣ውስጣችን ያለው ድክመት ምንድነው? መጪውን ዘመን በምገዳደር ደረጃ የሕዝቡን ስነ ልቦና እና ስነምግባር ለማነፅ ምን እናድርግ? ከሚለው ጥያቄ መጀመር ያስፈልጋል።ይህ ካልሆነ የአሜሪካው ላይ ከንፈር እየመጠጡ ከስር ያለውን አለማየት ያመጣል። ስራው የአሜሪካውን ድርጊት ከማውገዝ ይጀምራል።ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ቀደምት ከሆኑት ውስጥ ከመሆኗ ፣ለአፍሪካ እናት ከመሆኗ እና ብዙ የዓለም ጥቁር ህዝቦች በማንነታቸው መኩርያ ከማየታቸው አንፃር፣የሰሞኑን የአሜሪካው ድርጊት እንዳሳዘናት እና እንዳሳሰባት በአባቶቿ መግለጫ መስጠቷ ብዙዎች የአፍሪካ፣የአሜሪካ፣እና የላቲን አሜሪካ ጥቁሮች እና ሌሎች በእኩልነት የሚያምኑ ሁሉ ጆርዎቻቸውን እንዲሰጡ የሚያደርግ መልካም አጋጣሚ ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል።

ጊዜው ይህንን ብቻ አይደለም የሚያሳየን በአረጀ እና በአፈጀ የአስተዳደር መዋቅር እና ብስልሹ አሰራር የተተበተቡ የእምነት ድርጅቶችም ሆኑ ማናቸው የሃይማኖት አደረጃጀቶች እራሳቸውን ሳያስተካክሉ ለሌላው መድረስ ስለማይችሉ በፍጥነት እና በአጭር ጊዜ ከእዚህ አይነቱ የተውተበተበ የኃጢያት ሥራ በቶሎ ተላቀው ሕዝባቸውን በእውነት ወደማገልገል ካልመጡ ነገ በአሜሪካ የደረሰው (እኛ ጋር አልደረሰም ለማለት ባያስደፍርም) በባሰ መልኩ እንዳይመጣ ያሰጋል።ከኢትዮጵያ አንፃር ከአሜሪካም ሆነ ከሌላው ዓለም የምንለይበት ተንጠፋጥፈው  ያላለቁ መልካም ዕሴቶች አሉን።ስለኢዚህ ነው እኛ ዕድለኞች ነን ግን አሁንም የዕምነት ቦታዎቻችን በሚገባ የእራሳቸውን አስተዳደራዊ እና የገንዘብ ብክነት ችግር ካላስተካከሉ የነበረችንን መልካም ዕሴት ጭራሹን እንዳያጠፉት የቤት ስራቸውን ተግተው መስራት አለባቸው።

የፖለቲካ ድርጅቶች ምን ያድርጉ?

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ዘመኑን በዋጀ እና የአዲሱን ትውልድ ርዕይ ባገናዘበ (የአዲሱ ትውልድ ርዕይ ምንድነው? የሚለው ራሱን የቻለ ጥይቄ ሆኖ) መልኩ ለመሄድ ውስጣዊ እና ውጪያዊ ተግዳሮቶች አሉባቸው።ከእዚህ ሁሉ ችግር ጎን ግን ቢያንስ የፖለቲካ ድርጅቶቹ የሚገለጡበት አንድ አይነት ወይንም የራሳቸው መገለጫ የሆነ የኢትዮጵያን ዕሴት በተለየ የምያጎሉበት እና ይህንንም ወደ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ቀይረው ሕዝብን የመምራት አቅም ገና እየተፈጠረ እና እየዳበረ ያለ በሂደት ላይ ያለ ይመስለኛል። ምክንያቱም በአሁኑ የፖለቲካ መድረክ ላይ አብዛኛዎቹ ተዋንያኖች በ1966 ዓም በንጉሡ ስርዓት ላይ ከተነሳው ትውልድ የሆኑ ወይንም በእነርሱ ግርፍነት ፖለቲካን የተማሩ ናቸው።ስለሆነም ማኅበራዊ እና ሞራላዊ ጉዳዮች ላይ ብዙ ለማተኮር አይፈልጉም። ለእዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ወደ ስልጣን ሲመጡ ያነሱት ቤተሰባዊ፣የእናቶች ጉዳይ፣የሴቶች ጉዳይ እና ሃይማኖታዊ ዕሴቶች ሁሉ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ዓለም ከአርባ አመታት በላይ የተለዩ ስለነበሩ የአዲሱን ትውልድ ሲስቡ  ለሌሎች ደግሞ አሁንም ያልገቧቸው።

በኢትዮጵያ ከፖለቲካ ድርጅቶች መፅሐፍ ቅዱስ ማስተማር እና ስለ ቁርዓን መስበክ አንጠብቅም ከፖለቲካ ድርጅቶች የምንጠብቀው አንዲት እና አንዲት ነገር ነች።ይህችውም ሕግ ማክበር፣እንዲከበር ማድረግ እና እንዲከበር ማስደረግ ነው።የሕግ ቦዩ ከተስተካከለ እንዴት በውስጡ እንዴት እንደሚፈስ እና እንደሚሄድ ሕዝብ ያውቅበታል።አሁን በምንመለከተው ጉነታ ግን በተለይ በተቃዋሚዎች በኩል የነበረው ሕግ ያለበትን ክፍተት እንዴት እናስተካከል ብሎ እንደአንድ አገር አካል አብሮ ከማሰብ ይልቅ እንደ ሶስተኛ ወገን እራሳቸው በነበረው የሕግ ክፍተት ላይ ሌላ ስንጥር እያስገቡ ሕዝቡን ማደናበር እና ደጋፊ ለማድረግ መጣር ነው። በተመሳሳይ መንገድ በመንግስት በኩልም ሕግ የሚጥሱትን በወቅቱ ቶሎ ከመቅጣት እና እንዲታረሙ ከማድረግ ይልቅ የመዘግየት እና እንዳላዩ የማለፍ ሂደት ታይቷል።ሰሞኑን በአሜሪካ የተመለከትነው ለእኛም ትምህርት ሊሆን ይገባል።በአሜሪካ የተነሳው የሕግ እና የፍትሃዊነት ጥያቄ ነው።በኢትዮጵያም ፖለቲከኞች ከስልጣናቸው በፊት የሕግ እና ፍትሃዊነት ጉዳይን በቀዳሚነት እራሳቸው አክብረው ሌላውን ሊያስተምሩ ይገባል።

ባጠቃላይ በሰሞኑ በአሜሪካ የተከሰተው ጉዳይ የዓለሙ ወቅታዊ ሁኔታ ነፀብራቅ ነው።ክስተቱ የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የትናንት ድምር ውጤት እና የነገውንም አመላካች ነው።መንግስት፣ፖለቲከኞች እና የሃይማኖት መሪዎች እና ድርጅቶች ያልተስተካከለ አካሄድ ቆይቶ ዋጋ እንዳያስከፍል ከወዲሁ መንቃት ተገቢ ነው።በእኛ ሀገር አንፃር ብዙ መልካም ዕሴቶች አሉን።ነገር ግን እነኝህ ዕሴቶች  በሁሉም አካሎች መጠበቅ ካልቻሉ አደጋው ትልቅ ነው።ለእዚህ ደግሞ መንግስት፣የሃይማኖት አባቶች እና የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ የቤት ስራቸውን በሚገባ መስራት አለባቸው።ኃላፊነቱ ደግሞ በድምር የሚሰጥ አይደለም።የእያንዳንዱ ግለሰብ ኃላፊነት እና የስራ ውጤት ድምር ነው አገር የሚጠብቀው።ሁሉም ምን እያደረኩ ነው? የእኔ ወደ እዚህ ዓለም መምጣት ከራሴ ሌላ ለሀገሬ እና ለሕዝቤ እንዲሁ ለዓለም ሕዝብ ምን ፋይዳ አደረገ? ብሎ መጠየቅ አለበት።ጥያቄው ሁላችንንም ይመለከታል።የአሜሪካው ክስተት በኢትዮጵያ መነፀር አይቶ መመርመር እና ቀድሞ ማስተካከል ተገቢ ነው።

  
ጉዳያችን GUDAYACHN 

No comments:

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል። በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡  ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?  የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመ...