ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, May 11, 2020

የዓባይ ጉዳይ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው።ከዓባይ ወንዝ ተጠቃሚ የገልፍ አገሮች፣ ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት ለፀጥታው ምክርቤት ደብዳቤ የፃፈችባቸው ሁለት ዓላማዎች።

የዓባይ ግድብ 
=========   

የዓባይ ጉዳይ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው።ከዓባይ ወንዝ ተጠቃሚ የገልፍ አገሮች

ግብፅ የኢትዮጵያን የዓባይ ግድብ ጉዳይ ባላት ኃይል ሁሉ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።የውሃው ተጠቃሚ አገራት ደግሞ ግብፅ ብቻ አይደለችም።በዓባይ ውሃ እየተጠቀሙ ያሉት የመካከለኛው ምስራቅ በተለይ የገልፍ አገራት፣እስራኤል ጭምር ናቸው።ሳውዳረብያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በዓባይ ውሃ ተጠቃሚዎች ናቸው። ብዙዎች ውሃው በቀጥታ የሚሄድበትን አገር እንጂ ከጀርባ በውሃው እየተጠቀሙ ያሉ አገሮች አናስባቸውም።ይህንን ጉዳይ በሰፌው ወደፊት እመለስበታለሁ።ሆኖም ግን የአገራችን ምሑራን ጉዳዩ ከጀርባው ያሉትን የውሃው ተጠቃሚዎች በደንብ ማሳየት እና የኢትዮጵያ ህዝብም እንዲያውቀው ማድረግ አለባቸው ብዬ አስባለሁ። 

የገልፍ  አገሮች  ከአባይ የሚጠቀሙት ከመጠጥ ውሃ ሽያጭ ብቻ ሳይሆን ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ በምታመርተው መስኖ የሚገኘውን የእርሻ ምርት በቀላል የትራንስፖርት ወጪ ደጃቸው ድረስ ስለሚደርስ ነው።ከፍራፍሬ እስከ ሩዝ እና ጥጥ ምርት በዓባይ መስኖ ይመረታል።አንዳንዶቹ  ዘመናዊ የእርሻ ቦታዎች ደግሞ በገልፍ አገሮች ቱጃሮች እና ንጉሳውያን ቤተሰቦች የገንዘብ ድጎማ የተመሰረቱ ናቸው። 

ሰኔ 7/2018 ዓም እኤአ  የገልፍ ዜና አገልግሎት   የተባበሩት አረብ ኢምረት እና ሳውዲ አረብያ 12 ወራት የፈጀ ፣ከሁለቱም አገሮች 350 ባለስልጣናት እና ባለሙያዎች የተወያዩበት በ44 የጋራ ስልታዊ ፕሮጀክት ላይ ተስማሙ።ፕሮጀክቱ በሶስት ምሰሶዎች ላይ የተመሰረተ ነበር።እነርሱም የምጣኔ ሀብት፣ዕውቀት እና የሰው ኃይል እና ፖለቲካ፣ወታደራዊ እና ፀጥታ ምሰሶዎች ናቸው።
''The UAE and Saudi Arabia announced on Tuesday a joint vision for economic, developmental and military integration through 44 joint strategic projects.A total of 350 government officials from different fields prepared “The Strategy of Resolve” within 12 months. The strategy outlines three main axes: the economic axis, the human and knowledge axis, and the political, security and military axis'' Gulf news June 07,2018.
ይህ ስምምነት ሁለቱ አገሮች በግብፅ ያላቸውን ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅም ሁሉ የሚያጠቃልል ነው።የግብፅ ኢኮኖሚ ደግሞ ከዓባይ ወንዝ ውጪ ሌላ ሕይወት የለውም።በተመሳሳይ መንገድም የፀጥታ ጉዳዩን ስንቃኝ ተመሳሳይ የጥቅም መተሳሰር ይታያል።ስለሆነም የእዚህ ሁሉ ማሰርያው ''ሪሞት'' ኢትዮጵያ ጋር እንዳለ መገንዘብ ይቻላል።ኢትዮጵያ ግብፅን ብቻ ሳይሆን የገልፍ አገሮችን ምጣኔ ሃብታዊ እና ፀጥታ ሁሉ የመቆጣጠር አቅሟ በዓባይ ግድብ ሳብያ እጇ ላይ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ስለሆነም ይህ ግድብ የሞት ሽረት እና የህልውናችን ጉዳይ መሆኑን መረዳት ይቻላል።በሌላ በኩል የግድቡን አለመሳካት የሚመኙ አገሮች ስፋት እና ስብጥርም በሚገባ መረዳት ተገቢ ነው።
 ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክርቤት ደብዳቤ የፃፈችበት ምክንያት ሁለት ጉዳዮችን ያለመ ይመስላል
ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ መፃፍ በየቀኑ በሚባል ደረጃ በዜና ድረ ገፆች ይወጣል።ይህም አንዱ የግብፅ መረብ ዓላማ ነው። ደብዳቤውን የፃፈችበት ምክንያት ግን ሁለት ዓላማዎች እንዳለው ከሚወጡት ተደጋጋሚ ዜናዎች መረዳት ይቻላል። እነርሱም -
1ኛ) ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ብዙ ምላሽ እንድትሰጥ እና ጉዳዩን በዓለም አቀፍ ደረጃ አጀንዳ ለማድረግ 
ግብፆች ለፀጥታው ምክርቤት የፃፉት ደብዳቤ ምንም ያህል በየቀኑ በተለያዩ ገፆች እንዲወጣ ለማድረግ ቢሞክሩም በኮሮና ወረርሽኝ ሳብያ አገሮች እና ዓለም አቀፍ ሚድያዎች ሽፋን ሰጥተው አላወሩትም።የአገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም በጉዳዩ ላይ ሃሳብ ሲሰጡ አልታዩም። በእርግጥ የአረብ ሊግ በፓርላማ አባላት ስብስብ እና ከወራት በፊት በካይሮ ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት መግለጫ አውጥቷል።ይህ ግን የተለመደ ጭፍን ግብፅን የመደገፍ እና ኢትዮጵያን እንደ ስልታዊ ጠላት የማየት የተሳሳተ አመለካከት ውጤት ነው።ባጭሩ ግን የግብፅ ደብዳቤ ዓለም አቀፍ ትኩረት አልሳበም ስለሆነም ኢትዮጵያ እንድታጮህላት ግብፅ ትፈልጋለች።ስለሆነም ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መውሰዱ አዋጪ ነው ብላ አሰበች።ከእዚህ ጋር ተያይዞ ጉዳዩን ፖለቲካዊ እና ዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነት እንዲኖር የማድረግ ፍላጎቷ በዋናነት እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።
2ኛ) ሁለተኛው ፍላጎቷ በኢትዮጵያ በግንባታ ላይ ያሉ ዓለም አቀፍ የግንባታ ኩባንያዎች ለምሳሌ የጣልያኑን ሳሊኒ እና የቻያና ኩባንያዎችንም ለማስፈራራት እና አገሮቻቸው ጉዳዩ በፀጥታው ምክር ቤት እየታየ ያለ ጉዳይ አድርገው በማቅረብ በኩባንያዎቹ ላይ ተፅኖ ለማስፈጠር  ነው።ከሁለት ወራት በፊት ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ከመፃፉ በፊት፣ የግብፅ ፓርላማ  ድንገተኛ ስብሰባ ጠርቶ ነበር።ስብሰባው ሁለት ዓላማዎች የያዘ ነበር።እነርሱም በአባይ ግድብ ላይ እየተሳተፉ ያሉ ኩባንያዎች በግብፅ ምንም አይነት ፕሮጀክት ወደፊት እንዳይሰጣቸው፣አሁንም የወሰዱት ካለ በፍጥነት እንዲዘጋ የሚል እና የዓለም አቀፍ አበዳሪ ባንኮች ለኢትዮጵያ ምንም አይነት ብድር እንዳይሰጡ ለመጠየቅ ነበር።ሆኖም የተጠራው ስብሰባ ከ24 ሰዓታት ያነሰ ጊዜ ሲቀረው  በወረርሽኙ ተሳቦ እንደተሰረዘ  ተሰማ።ሆኖም ጉዳዩ ቆይቶ በተደረገ ምክክክር ለፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን በመምራት ፓርላማው ያሰባቸውን ሁለት ጉዳዮች ማሳካት ይቻላል የሚል ምክረ ሃሳብ ተነስቶ እንደሆነ ቀጥሎ ከተደረጉት ሂደቶች መረዳት ይቻላል።ፓርላማው ጠርቶት የነበረውን ድንገተኛ ስብሰባ እና ስለ ግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማንነት ለማንበብ ይህንን ይጫኑ።
ባጠቃላይ ኢትዮጵያ የዓባይ ግድብ ጉዳይ ላይ ፈፅሞ ወደኃላ ማለት የሌለባት የሞት እና የሽረት እንዲሁም የህልውና ጉዳይ መሆኑን መረዳት አለባት። ይህ ጊዜ ደግሞ ዓለም በወረርሽኙ ሳብያ በብዙ ውስጣዊ ጉዳዮች የተወጠረበት ከመሆኑ አንፃር  ምንም ዓይነት ችግር ለመፍጠር በተቀናቃኝ መንግሥታት ቢሞከረም ጊዜው ግን ከብዙ ትግል ጋር መወጣት ከተቻለ ለኢትዮጵያ መልካም ዕድል ይዞ መጥቷል።ሕዝቡም ጉዳዩን በእዚህ ደረጃ መረዳት አለበት።
ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት 
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant
Gudayachn Multimedia, Kommunikasjon og Konsultent 

No comments: