(በጌታቸው በቀለ የጉዳያችን ገፅ አዘጋጅ)
''ሰኔ እና ሰኞ ሲገጥም ጥሩ አይደለም'' የሚለውን አባባል በተለምዶ ይነገራል።ለምን? ለሚለው ምላሽ ግን አላገኘሁም።ሰኔ እና ሰኞ ገጠመ ለመጥፎ አባባል ብቻ ነው የሚባለው? አንዳንዴ ሰኔ እና ሰኞ ገጥሞ፣ነገሩ ተሳክቶ እየተባለም ይነገራል።
ሰኔ እና ሰኞ ዘንድሮ በኢትዮጵያም ሆነ በፈረጅንጆቹ ገጥሟል። የፈረንጆቹ ''ጁን'' 1 እና ''መንደይ'' ፣የኢትዮጵያ ሰኔ1 እና ሰኞ ዘንድሮ ገጥሟል።በእዚህ ዓመት ደግሞ ዓለም በኮሮና ወረርሽኝ ትልቅ ፈተና ላይ የወደቀችበት ነው።ስለሆነም በፈረንጆቹም በእኛም መግጠሙ እና ሰኔ እና ሰኞ የሚባለው ነገር እንዴት ነው ብዬ ትንሽ ወደኃላ ለመፈተሽ ሞከርኩ።ውጤቱ የሚገርም ሆኖ አግኝቼዋለሁ።ከአጋጣሚዎቹ ለመረዳት የቻልኩት ግን ወደኃላ ታሪካችን ስንመለከት ሰኔ ሰኞ የገጠሙባቸው ዓመቶች አንዳንዶቹ ፈተና የመጣባቸው ቢሆኑም ሌሎቹ ደግሞ መልካም ጊዜዎች ነበሩ።
የሰኔ እና ሰኞ መግጠም ለምን ብዙ ይወራል ብዬ ወደ ሀገርቤት አንድ ወዳጄ ጋር ደውዬ ስጠይቅ ያለኝ -ነገሩ አፈ ታሪክ ነው። ግን አንድ ጊዜ አንድ ሰው ሲያወራ የሰማሁት እና የማስታውሰው ጉዳይ በኢትዮጵያ መኪና እንደ እንግሊዞች በግራ መስመር ብቻ ይነዳ ነበር፣በኃላ በአሜሪካኞቹ አነዳድ በቀኝ በኩል እንዲሆን ተብሎ ሲታወጅ ዓመቱ ሰኔ 1 እና ሰኞ የገጠመበት ነበር።በጊዜው አዋጁን እየረሳ የተጋጨ ብዙ ሰው ነበር በእዚህ ሳብያ ሰኔ ሰኞ ይባላል ሲሉ ሰምቻለሁ አለኝ።ለማንኛውም የሰኔ እና ሰኞ ገጠመኝ የሚገርም ነው።
ሰኔ እና ሰኞ በአድዋ የዘመቻ ዓመት
የአድዋ ዘመቻ በ1888 ዓም ሲደረግ ሰኔ እና ሰኞ ገጥሞ ነበር።ይህ ዘመቻ ብዙ ፈተና ቢኖርበትም ድሉ ግን እስካሁን ለጥቁር ሕዝቦች በሙሉ እንዳንፀባረቀ ነው።
ሰኔ እና ሰኞ ዳግማዊ አፄ ምንሊክ ያረፉበት ዓመት
ሰኔ እና ሰኞ የገጠሙበት 1906 ዓም ዳግማዊ ምንሊክ ያረፉበት፣እና ልጅ ኢያሱ ወደ ንግስናው የመጡበት ነበር።ይህ ዓመት እንደ አውሮፓውያ አቆጣጠር 1914 ሲሆን የመጀመርያው ዓለም ጦርነት የተጀመረበት ዓመትም ነው።
ሰኔ እና ሰኞ በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ንግሥ ዓመት
ሰኔ እና ሰኞ የገጠሙበት ጥቅምት 23/1923 ዓም አፄ ኃይለሥላሴ ከራስ ተፈሪነት ወደ ንጉሰ ነገስት ኢትዮጵያ ተብለው በአዲስ አበባ ደብረገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ስርዓተ ንግሥ የፈፀሙበት ዓመት ነው።
ሰኔ እና ሰኞ የገጠሙበት የጣልያን ወረራ
በ1928 ዓም (1935 ዓም) በኢትዮጵያም በፈረንጆቹም እንዲሁ ሰኔ እና ሰኞ በኢትዮጵያ ገጥሞ ነበር።በእዛን ዓመት ዓለምም ሆነ ኢትዮጵያ የገጠማቸው አሳዛኝ ጉዳይ ነበር።በኢትዮጵያ የፋሺሽት ጣልያን ኢትዮጵያን የወረረበት ዓመት ነበር።በዓለም ላይም ጀርመን የአንደኛው ዓለም ጦርነት ማብቅያ ላይ የፈረመችው እና ጀርመን እራሷን እንዳታስታጥቅ የሚለው የ''ቨርሳይለስ ትርቲ'' የሚባለውን ያፈረሰችበት ዓመት ነበር።ይህንን ውል በማፍረስም ሂትለር ጀርመንን መልሶ በማስታጠቅ የሁለተኛው ዓለም ጦርነትን በዓለም ላይ ለማወጅ በሩን የከፈተለት ቁልፍ ተግባር ሆነ።
ሰኔ እና ሰኞ የገጠሙበት የደርግ እና የኢህአዴግ/ህወሓት ስልጣን መደላደል
በ1973 ዓም ደርግ ከወታደራዊ ስሙ ወደ ድርጅት ማለትም በ1972 ዓም ወታደሮቹን በሙሉ በኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሰፓአኮ) ብሎ በ1972 ዓም መስርቶ እራሱን ያደላደለበት ጊዜ ነበር።በተመሳሳይ ኢህአዴግ/ህወሓት በ1984 ዓም እራሱን ከሽምቅ ተዋጊነት ባንዴ የሽግግር መንግስት በሚል እራሱን ወደ ስልጣን ያመጣበት ዓመት ነበር።ሁለቱም 1973 ዓም እና 1984 ዓም የዋሉት ሰኔዎች ሰኔ 1 የዋሉት ሰኞ ቀን ነበር።
ሰኔ እና ሰኞ የገጠሙበት የሻብያ እና ህወሓት ጦርነት
የአቶ ኢሳያስ እና የአቶ መለስ ግጭት የተጀመረው ሰኔ እና ሰኞ በገጠሙበት በ1990 ዓም አቶ ኢሳያስ ባድሜን ሲወሩ ነበር።
ሰኔ እና ሰኞ የገጠሙበት የኮሮና ወረርሽኝ
ዘንድሮ 2012 ዓም (2020 ዓም እኤአ) በፈረንጆቹም ሆነ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሰኔ 1 እና ሰኞ ገጥሟል።ዘንድሮ መላው ዓለም በኮሮና ወረርሽኝ የታመሰችበት ዓመት ነው።ሁሉም በሚባል ደረጃ የአይሮፕላን በረራዎች ቆመዋል፣አገሮች ድንበሮቻቸውን ዘግተዋል።መጪው ሁኔታ ምን እንደሚሆን አይታወቀም።
ከላይ ከተጠቀሱት ቀናት በተጨማሪ የሚከተሉት ዓመታት ሰኔ እና ሰኞ የገጠመባቸው ናቸው።ዓመቶቹ በኢትዮጵያ እና በቅንፍ ውስጥ ያለው የአውሮፓውያኑ አቆጣጠሮች ናቸው። እነርሱም 1895 ዓም (1903)፣1900ዓም (1908)፣1934ዓም (1942)፣1951 ዓም (1959)፣1956ዓም (1964)፣1962ዓም (1970)፣1979ዓም (1987) ይጠቀሳሉ።
ለማጠቃለል በዓለማችን እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ይከሰታሉ።ከላይ ካሉት ዓመታት ብቻ ብንመለከት ሁሉ መጥፎ ቀኖች አይደሉም።መጥፎ የምናደርጋቸው እኛ እና የእኛ አካሄድ ነው። ለምሳሌ የአድዋ ጦርነት ላይ ከንጉሡ ጀምሮ ህዝቡ ዝግጅት አድርጎ ከአምላኩ ታርቆ ባይነሳ እስካሁን በባርነት ውስጥ የገባን ህዝቦች በሆንን ነበር።ጥሩ ቀኖች እንዳሉ ሁሉ ክፉ ቀኖች አሉ። ይህ የምናውቀው ነው።ሁሉንም ጥሩ ለማድረግ ግን የእኛው ውሳኔ ነው።ይሄውም መስራት የሚገባንን በመስራት፣ስንሰራ ደግሞ በትዕቢት ሳይሆን እግዚአብሔር ክፉውን ቀኖች እርሱ ባወቀ እንዲያሳልፍ በመጸለይ ነው።ዓድዋ ለእዚህ አስተማሪ ነው።ጦርነት መጣ ብለው አባቶቻችን በመተከዝ ጊዜያቸውን አላጠፉም።እግዚአብሔር እንዳደረገ ያድርገው ብለውም የጣልያንን ወረራ ተቀምጠው አልተመለከቱም። የራሳቸውን ድርሻ ለመወጣቱ ተነሱ፣እግዚአብሔር ደግሞ የእርሱን ሥራ እንዲሰራ ታቦተ ሕጉን ይዘው ቄሱ ከመቅደስ፣ሼሁ ከመስጊድ ተጠራርተው ከሰራዊቱ ጋር ዘምተው፣ለሞቱትም ሆነ በሕይወት ላሉት አብረው ጸለዩ።ስለሆነም የቀን መጥፎ የለውም።ቀኑን መጥፎም በጎም የምናደርገው እኛው ነን።ይሄውም በሁለት ነገሮች ነው።አንድ፣ የሚመጣውን ፈተና ለመጋፈጥ በኅብረት ባለመስራት እና ሁለት፣ወደ እግዚአብሔር ባለመጸለይ።
መልካም ሰኔ እና ሰኞ
ማሳሰቢያ
የጉዳያችን ጽሁፍ በየትኛውም ገፅ እና ሚድያ ላይ ሲወጣ ከጉዳያችን ገፅ ማግኘትን መግለጥ ጨዋነት ነው
www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment