ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, June 2, 2020

ኢትዮጵያ ተጠባባቂ ጦር ማሰልጠን አለባት።በሱዳን በኩል በኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ሊሰነዝሩ የሚያስቡ የአረብ አገራት ለኢትዮጵያ ስጋት ሆነዋል። (ጉዳያችን ልዩ ዘገባ)


>> ''ግድቡ ለሱዳን አደጋ ሊሆን ይችላል'' ሱዳን ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክርቤት የላከችው  መልዕክት፣
>> ሱዳን ዛሬ አዲስ መከላከያ ሚኒስትር ሾማለች፣
>> ''ከቱርክ፣ኢራን እና እስራኤል በኃላ ኢትዮጵያ የአረቡን ዓለም ሰብራ ልትገባ ነው?'' ሚድል ኢስት ሞንተር ዛሬ ማክሰኞ የፃፈው

ሰሞነኛው የአሜሪካ ስፕሪንግ 

የዓለም ፖለቲካ በፍጥነት እየተቀየረ ነው።የኮሮና ወረርሽኙ ተፅዕኖ በሀገሮች ግንኙነት፣በሕዝብ ማኅበራዊ ኑሮ እና የምጣኔ ሃብቱ ሚዛን ሳያሳክረው የሚያልፍ አይመስልም።የሰሞኑ የአሜሪካ የውስጥ ቀውስ ከኮሮና ወረርሽኝ በላይ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ገብታለች።ፕሬዝዳንት ትራምፕ ራሳቸው የሴራ ፖለቲካ ውስጥ እንደገቡ የሚናገሩ የአሜሪካንን ፖለቲካ የሚያውቁ ሰዎች ናቸው።ዛሬ ግንቦት 25/2012 ዓም በአልጀዚራ ቀርቦ የወቅቱን የአሜሪካ ፖለቲካ ላይ ሃሳብ የሰጠ ምሑር ያለውም ይሄንኑ ነው።ትራምፕ ሰሞኑን የተነሳውን የአፍሪካ አሜሪካውያን የመብት ትግል (ከአረብ ስፕሪንግ ስሙን ወስደው  የአሜሪካ ስፕሪንግም የሚሉት አሉ) ትራምፕ ሆን ብለው ያደረጉት እና የሚፈልጉት ነው ነበር ያለው።ለእዚህ ምክንያቱን ሲሰጥ ደግሞ በኮሮና ወረርሽኝ አያያዛቸው ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ስለገቡ፣የአፍሪካ አሜሪካውያን መነሳት ትራምፕ አካራሪ የቀኝ ኃይሎች ደህንነት እንዳይሰማቸው ስለሚያደርግ በእዚህ በመጪው ሕዳር ወር በሚደረገው ምርጫ የብዙ ነጭ አሜሪካውያንን ድጋፍ እንደሚያገኙ ያስባሉ ብሏል። 

የፕሬዝዳንቱ አካሄድም ነገር የሚያበርድ ሳይሆን ግጭት የሚያካርር ነው።የመብት ተሟጋቾቹን ''ግራ ክንፍ አክራሪ፣የአገር ውስጥ ሽብርተኞች እና አናርኪስቶች'' ያሏቸው ፕሬዝዳንቱ ዛሬ ደግሞ መፅሐፍ ቅዱስ ይዘው አንድ ቤተክርስቲያን ፊት ቆመው ታይተዋል። ይህ ድርጊታቸው በተለይ ጉዳዩን ሃይማኖታዊ ሽፋን ለመስጠት ወይንስ የትኛውን ዕምነት ለመንቀፍ እንዳሰቡ ስትመለከቱ በእውነትም አሜሪካ በግልጥ ልዩነት የሚጭር ፕሬዝዳንት ላይ እንደወደቀች መረዳት ቀላል ነው።

ግልገል የአካባቢ ኃያላን መነቃቃት 

የአሜሪካ በእዚህ ደረጃ መታመስ የሚፈጥረው ሌላ ጉዳይ የግልገል ኃያላን መንግሥታትን መነቃቃት ነው።ከባሕረሰላጤው ጦርነት በኃላ አሜሪካ የመካከለኛውን ምስራቅ ከእጇ እንዳይወጣ መንገድ የሶርያ  አደገኛ አማፅያንን ለመደገፍ የሄደችበት እርቀት እና ሂደቷ የሩስያን ጣልቃ ገብነት መጋበዙ ነው። የሩስያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ''ሶርያ ሊብያ አይደለችም።በሊብያ የደረሰው በሶርያ አይደገምም'' በሚል ከሶርያ ማዕከላዊ መንግስት ጋር እስከመጨረሻው ቆመዋል።በመቀጠል አሜሪካ ያደረገችው የመካከለኛው ምስራቅ ግልገል ኃያላን እንዲነቃቁ ማድረግ ነው።ለእዚህም ሳውዲ አረብያ እና የተባበሩት ዓረብ ኢምረቶች የመሳሰሉ መንግሥታት ለጆሮ በሚከብድ ደረጃ ዘመናዊ የጦር መሳርያ አስታጠቀቻቸው። በተለይ ለሳውዲ አረብያ ያስታጠቀቻት ዘመናዊ የጦር አይሮፕላኖች የሳውዲ አየር ኃይል አባላት በአግባቡ ያልተለማመዷቸው እና ለትንሽ እክል ፔንታጎን እየደወሉ የሚጠይቁት መሆኑ ነው የሚነገረው። እነኝህን ግለገል የአካባቢ ኃያላንን ለማጠናከር አሜሪካ ትኩረት ከመስጠቷ የተነሳ በስምንት ዓመታት ውስጥ ሁለቱም የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ፕሬዝዳንት ኦባማ እና ትራምፕ ሳውዲ አረብያን ጎብኝተዋል። የአሜሪካ በሳውዲ የጦር ሰፈር ያላት ከመሆኑ አንፃር እና ዋና ዓላማዋ የኢራን እና የቱርክን መስፋፋት እንድትገታላት ቢሆንም፣ግልገል ኃያልነቷን በሌሎች የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ላይ ብታሳይም እንደማስታገሻ ጉርሻ እንዳላየች ዝም አትልም አለማለት አይቻልም። 

የግብፁ ፕሬዝዳንት አልሲሲ፣የሳውዲው ንጉስ ሳልማን እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሳውዲ ግንቦት፣2017 ዓም እኤአ (ፎቶ የሳውዲ ዜና አገልግሎት)

''ዎል ስትሪት'' ግንቦት 20/2017 ዓም እኤአ ባወጣው ዘገባ አሜሪካ በእዚህ ወቅት ለሳውዲ አረብያ ወታደራዊ ትጥቅ ለማቅረብ በፕሬዝዳንት ትራምፕ አማካይነት የተስማማችው 110 ቢልዮን ዶላር የሚያወጣ እንደሆነ ዘግቧል።እነኝህ የትጥቅ መዥጎድጎዶች ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ ያላትን ተፅኖ ለማድከም ነው ቢባልም የእነሳውዲን ልብ ግን ማሳበጡ አልቀረም።ለእዚህም ነው የመካከለኛው ምስራቅ ጥምር ጦር በሚል ከኤርትራ (ኤርትራ ብታስተባብልም) እስከ ሱማሌ ጠረፍ መስፈር የያዙት።ይህ አካሄድ ለኢትዮጵያ አስጊ ሁኔታ ነው።

 ኢትዮጵያን ለማጥቃት ሱዳን ብቸኛ የአረብ አገሮች አማራጭ 

ሱዳን ከእዚህ በፊት በጉዳያችን ላይ የዓባይ ግድብን፣የሱዳን እና የአፍሪካን ቀንድ--- በሚለው ርዕስ ስር እንደተገለጠው ሱዳን አጣብቂኝ ውስጥ ያለች አገር ነች።ትርፍ እና ኪሳራዋን ስታሰላው ዞራ ዞራ እንደፈለጉ ሊያሽከረክሯት የሚችሉት አገሮች አረቦቹ እንደሆኑ ይገባታል።ለእዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ በውስጧ ያሉት ፅንፈኛ ኃይሎች የፖለቲካ ስልጣን ላይ ባይታዩም አሁንም በወታደራዊ መዋቅር እና በከፍተኛ የሀብት ደረጃ ላይ አሉ።ስለሆነም የአሁኑ የሱዳን ሽግግር  መንግስት የሚያደርገው እና የጦር አበጋዞቹ የሚሰሩት ላይገናኝ ይችላል።የትዕዛዝ ሰንሰለቱም የተዘባረቀ እና አገሪቱን ማን እንደሚመራ ያማይታወቅበት ሁኔታ ወደፊት እንዳያጋጥም ወይንም ሌላ አረብ-መር መፈንቅል ሊያጋጥማት ይችላል።በቅርቡ አልባሽርን ከስልጣን ያስወገደው የሱዳን አብዮት ከተደረገ በኃላ የተላያዩ የጦር መሪዎች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ የኩአታር፣ሌላው የሳውዲ ተብለው በግልጥ ታውቀው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በመሀከል ገብተው ካስታረቁት እና ለጊዜው የተሳካ የመሰለው የሽግግር ሂደት በእነኝህ አገራት ደጋፊ ኃይሎች የተወጠረ መሆኑ ነው አሁንም ድረስ የሚነገረው።

ሱዳን በያዝነው ሳምንት ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ እና ግብፅ አንድ ዓይነት የተናጥል እርምጃ እንዳይወስዱ የሚል ደብዳቤ ፃፈች የሚለው ዜናም የእዚህ ሁሉ ተቀጥያ ነው። ይህ ውትወታ የግብፅ እና የአረብ አገሮች ውትወታ መሆኑ ግልጥ ነው።ለአካባቢው ፀጥታ ስጋት አለብኝ ብላ ሱዳን እንድትጮህ የሚያደርጉት እነኝሁ አካላት ናቸው። ይህ በእንዲህ እያለ ሱዳን በእዚሁ ደብዳቤዋ ላይ ሌላም ዘባርቃለች።ይሄውም ከእዚህ በፊት ግድቡ  በክረምት ወራት የነበረውን የጎርፍ አደጋ ያበርድልኛል እንዳላለች፣ አሁን ግን ግድቡ በአግባቡ ካልተሞላ ለሱዳንም ''ሪስክ'' (አደጋ) አይኖረውም ማለት አይቻልም፣የሚልዮን ሱዳናውያንን ሕይወት አደጋ ይጥላል ብላለች ሲል የዘገበው አልሃራም የግብፁ ጋዜጣ በዛሬው ግንቦት 25/2012 ዓም ዘገባው ነው።ይህ ብቻ አይደለም ሱዳን የጦር አለቆቿን በምዕራብ ጎንደር በኩል ልካ ጥቃት ለመፈፀም ሞክራ የጦር አበጋዞቿን ሕይወት ከኢትዮጵያ ሰራዊት በኩል በተሰጠ የአፀፋ ምት መመለሷ እና ጉዳዩ ገና አለመብረዱ ነው የተነገረው።ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 25/2012 ዓም ደግሞ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እና የዓማራ ክልል የፀጥታ ጉዳይ ኃላፊዎች የሱዳን ኢትዮጵያን ድንበር መጎብኘታቸው ተነግሯል።ይህ በንዲህ እያለ የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጉዳዩን አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት ላይ በሰጠው መግለጫ  የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን በሰላማዊ ንግግር መፍታት እንደሚያስብ ገልጧል።

በሌላ በኩል ደግሞ ሱዳን ዛሬ ግንቦት 25/2012 ዓም አዲስ የመከላከያ ሚኒስትር ሾማለች።አዲሱ መከላከያ ሚኒስትር ሜጀር ጀነራል ኢብራሂም ያሲን ሲሆኑ ሚኒስትሩ በቅርቡ በደቡብ ሱዳን ጉብኝት ላይ ሳሉ በድንገት ያረፉትን የሱዳን መከላከያ ሚኒስትር  ጀነራል ጋማል አልድን ይተካሉ።አዲሱ መከላከያ ሚንስትር በ1958 ዓም በካርቱም የተወለዱ ሲሆን ከዮርዳኖስ ሙታህ ዩንቨርስቲ በወታደራዊ ሳይንስ በመጀመርያ ዲግሪ መመረቃቸው እና በ2010 ዓም እኤአ ጡረታ ወጥተው የነበረ እና አሁን ተመልሰው የተሾሙ  መሆናቸውን ጉዳያችን ለመረዳት ችላለች።ይህ በእንዲህ እያለ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የገባችው መጠነኛ ግጭት ብቻ ሳይሆን በዳርፉር ግዛቷ ጀበል ማራ በተባለ አካባቢ ከሽምቅ ተዋጊዎች ጥቃት እንደደረሰባት ለማወቅ ተችሏል።የአዲሱ መከላከያ ሚኒስትር  የሹመት ስነ ስርዓት ሲካሄድ ጀነራል እብራሂም ያሲን የሽግግር መንግስቱን ዓላማዎች እንደሚያስፈፅሙ በኮሮና ወረርሽኝ ሳብያ አፍና አፍንጫቸውን እንደሸፈኑ  ቃል መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል።

                                     ዛሬ ግንቦት 25/2012 ዓም የተሾሙት አዲሱ የሱዳን መከላከያ ሚኒስትር 


''ከቱርክ፣ኢራን እና እስራኤል በኃላ ኢትዮጵያ የአረቡን ዓለም ሰብራ ልትገባ ነው?'' ሚድል ኢስት ሞንተር ዛሬ ማክሰኞ የፃፈው

 ''ከቱርክ፣ኢራን እና እስራኤል በኃላ ኢትዮጵያ የአረቡን ዓለም ሰብራ ልትገባ ነው?''  በማለት በጥያቄ አርዕስት የሰጠው የዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 25/2012 ዓም  በሚድል ኢስት ሞንተር ላይ የወጣው ፅሁፍ በሱዳን እና በኢትዮጵያ ድንበር መካከል ያለው ግጭት ላለፉት አስር ዓመታት የነበረ እና ችግሩ ድንበራቸውን ስላላካለሉ ብቻ መሆኑን ያወሳል።ሆኖም ይላል ሚድል ኢስት ሞኒተር የአሁኑ ግጭት የተለየ የሚያደርገው የድንበር ግጭት ብቻ ሳይሆን ዲፕሎማሲያዊ ግጭትም በካርቱም እና በአዲስ አበባ መሃል ይዞ መምጣቱ እና እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ ከጀርባ በመደበኛ ሰራዊቱ በሚደገፍ በሽፍቶች መሃል የተደረገ ግጭት ሳይሆን በሁለቱም አገሮች መደበኛ ሰራዊት መሃል የተደረገ ግጭት መሆኑን ያትታል።ይህንን ተከትሎ የሱዳን ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በመቀጠልም የሱዳኑ ሽግግር መንግስት አብደላ ሃምዶክ ግጭቱ የተፈጠረበትን ቦታ መጎብኘታቸው እና መልዕክቱ ሱዳን ለሉዓላውነቷ የማትደራደር ነች የሚል መልዕክት ለኢትዮጵያ መንግስት ለማስተላለፍ መፈለጋቸው መሆኑን ሚድል ኢስት ሞንተር ያወሳል። እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ከፍተኛ መኮንኖች የግጭቱን ቦታዎች ሄደው ስለማየታቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር ምንም አላለም። ምናልባት ዘገባው ገና ዛሬ ከመሆኑ አንፃር ለሕትመቱ  አልደረሰለት ሊሆን ይችላል።

ሚድል ኢስት ሞኒተር የኢትዮጵያ አካሄድ ''በአገር ውስጥ የፖለቲካ እና ምጣኔ ሃብታዊ ድል በማስመዝገብ፣ዓለም አቀፍ ግንኙነቷን በማጠናከር፣በአካባቢው ኃይል ሆና ለመውጣት ታስባለች።ይህንን ደግሞ በአረብ የውሃ መብት (ዓባይን መሆኑ ነው) እና በሱዳን ሉዓላዊነት ኪሳራ ለማሳካት ታስባለች'' ብሏል 
''It apparently believes that with its political and economic achievements at home and the expansion of its international relations abroad, it will be able to go ahead and become a major regional power, even if this comes at the expense of Arab water rights and the sovereignty of its neighbour Sudan።''

ሚድል ኢስት ሞኒተር ቀጠለ ''አዲስ አበባ የኢራንን፣ቱርክን እና እስራኤልን የአረቡን ዓለም  በስልት፣የመልከዓ ምድር፣የውሃ እና የፀጥታ ኃይል ስረ-መሰረት እንዴት መቦርቦር እንደሚቻል  በሚገባ አጥንታለች።'' ብሏል።
''Addis Ababa has studied the Iranian, Turkish and Israeli penetrations of the Arab world’s strategic, geographical, water and security depths''

ኢትዮጵያ ተጠባባቂ ጦር ማሰልጠን ያስፈልጋታል

በእዚህ ፅሁፍ መግቢያ ላይ እንደተገለጠው የአሜሪካ በውስጥ ጉዳይ መወጠር ለብዙ ግልገል  ሃያላን መንግሥታት መልካም ዕድል ይፈጥራል።ዕድል የሚለው ቃል በትክክል ባይገልጠውም መደናበር ይፈጥራል የሚለው ሊስማማ ይችላል።የመካከለኛው ምስራቅ አንዳንድ አገሮች እና ግብፅ አሁን ዓለም አቀፍ ሕጎች የሚጣሱበት፣የነዳጅ ምርት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ የዓለም ምጣኔ ሀብት በመውረዱ በነዳጅ የበለፀጉ አገሮች አሁን ያላቸውን እያወጡ ሌላ አገሮች ለመውረር እና የውስጥ የፖለቲካ ቀውሳቸውን ለማስቀየስ የሚጥሩበት ወቅት ነው።በሌላ በኩል የቱርክ፣ኢራን እና ሳውዲ አረብያ መሃከል ያለው ፍጥጫ በራሱ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን ወደ አዲስ ትኩሳት የሚከት ሊሆን ይችላል።ሌላው ቀርቶ ኃያላኑም ቢሆኑ ከወረርሽኙ በኃላ የምጣኔ ሃብቱ ጦርነት እና የግዙፎቹ ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖች ገቢ መውረድ እና መክሰር በራሱ  ምጣኔ ሀብታቸውን ወደ ጦርነት ኢኮኖሚ ቀይረው አዳዲስ ፍጥጫ ከቻይና፣ሩስያ እና ቱርክ ጋር አይገቡም ማለት አይቻልም።በእዚህ ሁሉ መሃል ኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ ሳብያ የመካከለኛው ምስራቅ አንዱ ካርድ እርሷ ጋር እንዳለ ግልጥ ሆኗል።ስለሆነም ይህንን ካርድ በሚገባ እንድትጫወተው የተጠባባቂ ጦር በፍጥነት ማሰልጠን አስፈላጊ ይሆናል።ወደፊትም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ወጣቶች ብሔራዊ ውትድርና ሰልጥነው መቀመጥ አንዱ ግዴታ መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል።ሰልጥነው የጨረሱ የተሻለ የትምህርት እና የስራ ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ ብቁ ዜጋ የማፍራት አንዱ እና አስፈላጊ ጉዳይ ነው።ዛሬ በሰለጠኑት አገሮች ሳይቀር ወጣቶች ብሔራዊ ውትድርና ሰልጥነው ወደ ቤተሰቦቻቸው ይመለሳሉ። በእዚህም ንቁ እና የፈጠራ ችሎታ ያለው ወጣት አፍርተዋል።እኛ ሀገር ያለው የብሔራዊ ውትድርና በደርግ ዘመን ያተረፈው ''ጥቁር ስም'' በአዲስ ስም መቀየር ሳያስፈልግ አይቀርም። የሆነው ሆኖ ጊዜው የሚያሳየው ኢትዮጵያ ተጠባባቂ ጦር ማሰልጠን እንዳለባት ነው።ኢትዮጵያ ውስጣዊ የፖለቲካ ሰላሟን እስካረጋጋች ድረስ እና በግድቡ ዙርያ ያላት ባለቤትነት አስጠብቃ እስከሄደች፣እንዲሁ የጦር ኃይሏን በተተኪ ኃይል ካጠናከረች፣አሁን ለኢትዮጵያ የተሻለ ጊዜ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም።



ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...