ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, June 8, 2020

በኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ አስተባባሪነት የተጠራው ስብሰባ በስቶኮልም የኢትዮጵያ ኤምባሲ የፖለቲካ፣ኢኮኖሚ እና ዲያስፖራ ጉዳዮች ኃላፊ እና ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ባለሙያዎች በተገኙበት በኦስሎ ተካሄደ።



በእዚህ ጽሁፍ ውስጥ የሚከተሉትን ያገኛሉ 
>> ''የዓባይ ግድብ የሚመጣው ትውልድን ዕጣ የሚወስን የአሁኑ ትውልድ የሚከፍለው ዕዳ ነው'' ዶ/ር ሙሉጌታ በረደድ ሃይድሮሎጅስት ኢንጅነር 
>> ''ከኢትዮጵያ 12 ዋና ዋና ወንዞች ውስጥ 10ሩ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚሄዱ ናቸው።ከኢትዮጵያ ስፋት 1ሚልዮን 1መቶ ሺህ ስኩኤር ኪሎሜትር ስፋት ውስጥ  ውኃማ አካሏ 0.7% ነው።''  ዶ/ር አሸናፊ ሰይፉ 
>> ''በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ላይ በቅርብ እየታየ ያለው የማሽተት እና የመቅመስ ስሜታቸው የቀነሰበት ሁኔታ ታይቷል'' ዶ/ር አንተነህ መኩሪያ ።
>> ''በአባይ ተፋሰስ ዙርያ የተፈረመው ውል ስድስት አገሮች ፈርመዋል፣አራቱ በፓርላማ አፅድቀዋል፣በፓርላማ ያፀደቁት ስድስት ሲሆኑ አስገዳጅ ሕግ ሆኖ ይወጣል'' አቶ ተስፋዬ ይታይህ በስቶኮልም የኢትዮጵያ ኤምባሲ የፖለቲካ፣ኤኮኖሚ እና ዲያስፖራ ጉዳዮች ካውንስል ሚኒስትር።

+++++++++++++++++++++++++++++ 

የስብሰባው መግቢያ 

መሰረቱን በኖርዌይ ያደረገው የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ግንቦት 30/2012 ዓም (ጁን 7/2020 ዓም) በ''ጎቱሚቲንግ'' የመገናኛ መረብ አማካይነት ስብሰባ አካሂዶ ነበር።የስብሰባው ሁለት አጀንዳዎች ማለትም በዓባይ ግድብ ጅኦ-ፖለቲካ ጉዳይ እና የዲያስፖራው ሚና እና  የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጤና፣በማኅበራዊ እና በምጣኔ ሃብት ባመጣው በሚያመጣው ችግር ዙርያ ላይ ያተኮሩ ነበሩ።

በስብሰባው መጀመርያ ላይ የኢትዮጵያውያን የጋር መድረክ፣ በኖርዌይ መንግስት በሕጋዊ መልክ የተመዘገበ የየትኛውንም የፖለቲካ ድርጅት ሃሳብ የማያንፀባርቅ ነገር ግን በሲቪክ ድርጅትነት እየሰራ እንደሚገኝ የተገለጠ ሲሆን፣ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ብቻ የጋራ መድረኩ ባዘጋጃቸው የውይይት መርሃግብሮች ዙርያ በአስተባባሪዎቹ በአቶ ጌታቸው እና አቶ ወርቁ ቀርበዋል።በእዚህም መሰረት መድረኩ ላለፉት አራት ዓመታት ብቻ በብሔር ፖለቲካ እና በኢትዮጵያዊነት ዙርያ፣ በሶሻል ካፒታል በተመለከተ፣በኢትዮጵያ የተነሳው ሕዝባዊ አመፅ ዙርያ፣በለውጡ አንደምታ ዙርያ፣የምርጫ ሴናርዮ ዙርያ፣በኖበል ሽልማት ስነስርዓት ሂደት ላይ በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሚና፣በስብስባ አዳራሾች ያካሄደ ሲሆን ከእዚህ በተጨማሪ የጠረንጴዛ ዙርያ ውይይት በተለያየ የፖለቲካ አመለካከቶች ዙርያ  ማድረጉ ተብራርቷል። የጋራ መድረኩ እነኝህን ውይቶች ሲያዘጋጅ ሁሉንም በነፃ የተከናወኑ እና አዳራሾችንም ባብዛኛው በነፃ እያፈላለገ መስራቱ እና ላለፉት አራት ዓመታት ለተወሰኑ የአዳራሽ ክራይ ብቻ የነበሩበት ወጪዎች ከስምንት መቶ ክሮነር ያልበለጠ መሆኑም ተወስቷል።

''የዓባይ ግድብ የሚመጣው ትውልድን ዕጣ የሚወስን የአሁኑ ትውልድ የሚከፍለው ዕዳ ነው'' ዶ/ር ሙሉጌታ በረደድ ሃይድሮሎጅስት ኢንጅነር 

የዓባይን ግድብ በተመለከተ መግቢያ መንደርደርያውን ዶ/ር ሙሉጌታ በረደድ ያቀረቡ ሲሆን።ዶ/ር ሙሉጌታ ማስተርሳቸውን በዓባይ ጉዳይ ላይ ያጠኑ፣ዶክትረታቸውን ደግሞ በሃይድሮሎጂ ኢንጂነሪንግ አጠናቀው በአሁኑ ጊዜ በኖርዌይ በሚገኘው መልቲ ኮንሰልት ድርጅት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት እየሰሩ እንደሚገኙ በስብሰባው መግቢያ ላይ ተገልጧል።እርሳቸውም በመግቢያ ማብራሪያቸው ላይ በዓባይ ዙርያ ቀደም ብለው የተደረጉ ስምምነቶች ትውልድ የሚገድቡ ስምምነቶች ነበሩ ካሉ በኃላ አሁን ግድቡ ያለበት ደረጃ አበረታች መሆኑን ገልጠው ግድቡ የሚመጣው ትውልድን ዕጣ የሚወስን የአሁኑ ትውልድ የሚከፍለው ዕዳ መሆኑ መታወቅ አለበት ብለዋል። 

ዶ/ር ሙሉጌታ ግብፆችን አስመልክተው ሲያብራሩ ባብዛኛው ራሳቸውን እንደተጠቂ አድርገው ማቅረብ ለምደዋል ካሉ በኃላ ጊዜው ቀድሞ ማጮህ ቀድሞ ያሰማል በሚል በዲያስፖራቸው 'ዊንግ' አማካይነት እየተጠቀሙ እንደሚገኙ አብራርተዋል።በመጨረሻም በመግቢያ ነጥቦቻቸው ላይ ዶ/ር ሙሉጌታ ኢትዮጵያውያን በዓባይ ግድብ ጉዳይ ብዙ ማለት አለብን፣እውነትኛውን ነገር ለቀሪው ዓለም ማሳወቅ ተገቢ መሆኑን አበክረው ተናግረዋል።

''ከኢትዮጵያ 12 ዋና ዋና ወንዞች ውስጥ 10ሩ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚሄዱ ናቸው።ከኢትዮጵያ ስፋት 1ሚልዮን 1መቶ ሺህ ስኩኤር ኪሎሜትር ስፋት ውስጥ  ውኃማ አካሏ 0.7% ነው።'' ዶ/ር አሸናፊ ሰይፉ 

በመቀጠል በውይይት መድረኩ ላይ በሰፊው  ያቀረቡት ዶ/ር አሸናፊ ሰይፉ ሲሆኑ እርሳቸውም በሃይድሮሎጅስትና ኢንቫይሮመንት የፔኤች ዲ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከውሃ ጋር በተያያዙ ፕሮጀክቶች ላይ እና በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች እያስተማሩ ይገኛሉ።ዶ/ር አሸናፊ የጀመሩት ኢትዮጵያ ከስፋቷ 1ሚልዮን 1መቶሺህ ስኩአር ኪሎ ሜትር ውስጥ  0.7% የሚሆነው ብቻ ውሃማ ሲሆን በእዚህ ብቻ ነው የውሃ ማማ የምንባለው።በእዚህ አንፃር ኖርዌይን ስንመለከት 5% መሆኑን ገልጠዋል።የኢትዮጵያ ቶፖግራፊ ከዝቅተኛ ቦታ እስከ ከፍተኛ ቦታ ድረስ በመሆኑ ለውሃ አጠቃቀም አመቺ መሆኑን ገልጠው ብዙ ውሃዋ በምድረ ገፅ ላይ ከዝናብ መጥቶ የሚያልፍ ስለሆነ መገደብ የግድ አስፈላጊ ነው ብለዋል።በመቀጠልም ኢትዮጵያ ካሏት 12 ዋና ዋና ወንዞች ውስጥ 10ሩ ከኢትዮጵያ መንጭተው ወደ ሌላ አገር የሚሄዱ መሆናቸውን ማወቅ አለብን ብለዋል።ዶ/ር አሸናፊ የኢትዮጵያን ሁኔታ ሲያብራሩ በአሁኑ ጊዜ 11% ብቻ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ዘመናዊ የውሃ ማውረጃ ያለው ሽንትቤት ተጠቃሚ ነው።የኢትዮጵያ የሃይድሮ ፓወር አስተዋፅኦ ከአጠቃላይ የኃይል ጥያቄ ውስጥ 11% ብቻ ነው የቀረው ኃይል አሁንም የሚገኘው ከደን ወዘተ የሚገኝ መሆኑን ገልጠዋል።

ዶ/ር አሸናፊ የኢትዮጵያ ወንዞች ውስጥ ሶስቱ ማለትም አባይ፣ተከዜና ባሮ ብቻ 70% የወንዝ ውሃ ይሸፍናሉ ያሉ ሲሆን።የኢትዮጵያ 1/3ኛ የቆዳ ሽፋን የሚሸፈነው ደግሞ በእነኝህ ወንዞች ተፋሰስ ስር  መሆኑን አብራርተዋል።በመቀጠል የዓባይ ግድብን በተመለከተ ማብራርያ ሲሰጡ ግድቡ 175 ሜትር ከፍታ፣1874 ስኩኤር ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በ13 ተርባይነር 5150 ሜጋዋት በሰከንድ ማመንጨት ይችላል ብለዋል።በመቀጠል ዶ/ር አሸናፊ የገቡት ከግድቡ ጋር በተያያዘ የነበሩ ውሎች ላይ ነው። 

በዓባይ ዙርያ ከተደረጉት ውሎች ውስጥ የ1891 ዓም በእንግሊዝ እና ጣልያን መሃል ተከዜ ወንዝ ላይ ያደረጉት ስምምነት ጣልያን ምንም ልማት እንዳትሰራ የሚያግድ ነበር።በ1906 ዓም በእንግሊዝ እና በቤልጅየም መሃል የተደረገው ደግሞ በኮንጎ ወንዝ ላይ ምንም ሥራ እንዳይሰራ የሚያግድ ነበር።ይህ ከእኛ የራቀ ቢሆንም የኮሎኒያል ውሎች የሚያሳይ ነው።ሌላው በ1959 ዓም በሱዳንና ግብፅ መሃል የተደረገው ኢትዮጵያን ያገለለ ውል ነው።ግብፅ አሁን ድረስ የምትጠቅሰው ይህንን ውል መሆኑን ያወሱትዶ/ር አሸናፊ፣በወቅቱ በንጉሡ ዘመን ኢትዮጵያ ይህንን ውል በኦፊሴል ተቃውማለች ብለዋል።ሌላው የኢንተቤ ውል የሚባለው በ2010 ዓም የተደረገው ሲሆን ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ውል የሚባለው ዋናው ውል ግን በመጋቢት 2015 ዓም ላይ የኢትዮጵያ፣ግብፅ እና ሱዳን ግድቡን በጋራ እናለማለን የሚለው ውል ነው። ይህ ውል ለኢትዮጵያ ትልቅ በር የከፈተ ነው። በቅርቡ ግብፆች ለማምለጥ የሚሞክሩት ከእዚህ ከ2015ቱ ውል ነው በማለት አብራርተዋል።

ወደፊት መደረግ ባለበት ጉዳይ ላይ አስመልክተው ዶ/ር አሸናፊ ሲያብራሩ ኢትዮጵያ በዋናነት ግድቡን መጨረስ እና የመደራደር አቅሟን ማሳደግ ወሳኙ ጉዳይ ነው ብለዋል። በመቀጠልም እስካሁን ያጣነው የራሳችንን ሀብት በጋራ የመጠቀም መብት ነው ያጣነው።ግድቡ ኢትዮጵያን ከእርሻ መር ኢኮኖሚ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢኮኖሚ የሚያሻግር እና የውጭ ምንዛሪ ለማፍራት ወሳኝ ነው ብለዋል።ግብፅ ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውሃ ያላት ሀገር መሆኗን ያብራሩት ዶ/ር አሸናፊ እኛ የመሬት ላይ ውሃችንን  መጠበቅ የግድ መሆኑን ገልጠዋል።በመጨረሻም ዶ/ር አሸናፊ የዓባይ ግድብ ዙርያ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምሑራን መንግስትን የሚያማክሩበት እና ስለ ግድቡ እውነተኛውን ገፅታ ለዓለም የሚያሳዩበት  የሙያተኞች ስብስብ መኖሩን ገልጠው ድረ ገፁም http://www.eipsa1.com/cms/ መሆኑን ለተሰብሳቢዎቹ አስረድተዋል።ዶ/ር አሸናፊም የእዚሁ የባለሙያዎች አካል መሆናቸውን ገልጠው የዕለቱን ገለጣ አጠናቀዋል።

በመቀጠል በተሰጡት አስተያየቶች በኖርዌይ ከፍተኛ የውሃ ባለሙያ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ተጠቅሶ እነኝህ ሃይድሮሎጅስቶች በኖርዌይ ብቻ ሳይሆን በስካንድንቭያን አገሮች ደረጃም መደራጀት እና የድፕሎማሲውን ሥራ ቢሰሩ ብዙ ውጤት ማግኘት እንደሚቻል ተገልጧል።

''በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ላይ በቅርብ እየታየ ያለው የማሽተት እና የመቅመስ ስሜታቸው የቀነሰበት ሁኔታ ነው ።'' ዶ/ር አንተነህ መኩሪያ 

ከዓባይ ጉዳይ በመቀጠል በኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ ስብሰባ ላይ የቀረበው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በጤና፣በማኅበራዊ እና በኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ዙርያ ነበር።በዚህ ዙርያ ያቀረቡት ዶ/ር አንተነህ መኩርያ ነበሩ። ዶ/ር አንተነህ መኩርያ አገራቸውን በጀት አብራሪነት በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ ያገለገሉ፣ ከዝነኛው የሕክምና ዩንቨርስቲ ፓዝናን የሕክምና ዩንቨርስቲ የሜዲካል ዶክትሬታቸውን ያገኙ እና በአሁኑ ጊዜ በኖርዌይ የተለያዩ ሆስፒታሎች በሕክምና ሙያ እያገለገሉ የሚገኙ ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው። 

ዶ/ር አንተነህ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተመለከተ የህመሙ ስሜት ከ2 እስከ 7 ቀኖች እንደሚታይ ገልጠው በቅርቡ የታዩ ውጤቶች ደግሞ በአንዳንዶች ላይ የማሽተት እና የመቅመስ ስሜታቸውን፣ የመቀነስ አልፎ አልፎም የማቅለሽለሽ ስሜት የታየባቸው መኖራቸውን ጠቁመዋል።በመቀጠልም እስከ ስብሰባው የተደረገበት ቀን ድረስ በኖርዌይ 8542 ሰዎች፣ በስዊድን ደግሞ 44 ሺህ ሰዎች መያዛቸውን ገልጠው፣በሁለቱ አገሮች መሃል ያለው ልዩነት የመጣው የፖሊሲ ልዩነት መሆኑን እና ኖርዌይ ቀድማ ጥንቃቄ ስታደርግ ስዊድን ደግሞ መዘግየቷ ያስከተለው መሆኑን አብራርተዋል።በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ስንመለከት በ10% በፍጥነት የማደግ ሁኔታ እየታየበት መሆኑን የገለጡት ዶ/ር አንተነህ በኖርዌይ ለምሳሌ የማኅበራዊ ትስስሩ በጠነከረበት ማኅበረሰብ ውስጥ እስከ 7 ቤተሰብ የተያዘበት ታሪክ መኖሩን ገልጠዋል።

ዶ/ር አንተነህ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለውን ሁኔታ ሲያብራሩም በኢትዮጵያ በሽታው ለፍቶ አዳሪውን፣ቱሪዝምን እና የአየር አገልግሎቱን በሌላው ዓለም እንደታየው ሁሉ መጉዳቱን ገልጠው፣በዋናነት መመርያዎችን ማክበር አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።በመቀጠልም ስነልቦናዊ ተፅኖው ለሌሎች በሽታዎች ስለሚዳርግ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በሌላ በኩል የኮሮና ወረርሽኝ ከጤና ባሻገር በኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት የምናየው ሲሆን ሌላው አስቸጋሪ የሚያደርገው ከኮሮና በኃላ የሚመጣው አስቸጋሪ ጊዜ መሆኑን አብራርተዋል።ይሄውም በዓለም ዓቀፍ ጥናቶች የሚያሳዩት ኮሮና ቢጠፋም ከ12 እስከ 18 ወሮች የሚፈጅ ትግል ዓለምን ከኮሮና በፊት ወደነበረችበት ቦታ ለመመለስ እንደሚጠይቅ ገልጠዋል።

በመፍትሄነት ዶ/ር አንተነህ ያስቀመጧቸው ነጥቦች ውስጥ የቤተሰብ በግልጥ መወያየት፣ሕፃናትን ማስተማር፣ቤተሰባዊ ትስስር በመጠበቅ ፈጠራን ማዳበር የሚጠቀሱ ሲሆኑ በተጨማሪ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ርቀት ከመጠበቅ ጋራ በኢትየጵያ ኤምባሲ የተመሰረተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተመለከተውን ግብረ ኃይል ማገዝ፣አስፈላጊ የህክምና ቁሳቁሶችን አሰባስቦ ወደ አገር ቤት መላክ፣ማኅበራዊ ግዴታን መወጣት፣አዳዲስ ሃሳቦችን ማመንጨት እና በቅርቡ የተመሰረተው የኢትዮ ኖርዲክ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ማጠናከር እና የምታውቁትን ኢትዮጵያዊ የህክምና ባለሙያ ወደ እዚህ ማኅበር ማምጣት ጠቃሚ ነው ብለዋል።ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የሕዝቡን ስነ ልቦና ለመጠበቅ የማማከር ሥራ አስፈላጊ መሆኑን በማስመር ዶ/ር አንተነህ የዕለቱን ማብራርያ አጠናቀዋል።

በመቀጠል ከተሳታፊዎች  ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የነጭ ሽንኩርት፣ዝንጅብል ጥቅም፣በኖርዌይ የውጭ ዜጎች በብዛት ተጠቅተዋል ስለተባለው እና በሽታው በሰገራ ይተላለፋል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተው ዶ/ር አንተነህ ነጭ ሽንኩርት እና ዝንጅብል የመሳሰሉትን በተመለከተ ያድናሉ የሚል ጥናት የለም።ሆኖም ከመያዝ በፊት ግን እንደማንኛውም ሚንራል እና ንጥረ ነገር እንዳለው ምግብ የመከላከል አቅምን በያዙት ንጥረ ነገር ሊያሳድጉ ይችላሉ በአዳኝነታቸው ግን የተረጋገጠ ጥናት የለም ብለዋል።በመቀጠልም በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች አልኮል እንደሚያድን ይናገራሉ ይህ ግን ስህተት ነው ብለዋል ዶ/ር አንተነህ።በሌላ በኩል ሰገራ በተመለከተ በመጀመርያ ቫይረሱ ውጪ ብዙ የመቆየት ዕድል ስለሌለው ከእዚህ አንፃር ማየቱ ተገቢ ሲሆን በእዚህ ዙርያም በቂ ጥናት አለመደረጉን ገልጠዋል። በመጨረሻም ዶ/ር አንተነህ ያሰመሩበት ጉዳይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት በዋናነት የቫይታሚን ዲ  እጥረት ታይቷል። ስለሆነም ቫይታሚን ዲ አንዱ እና አስፈላጊ መሆኑን ማወቅ ይገባናል ብለዋል።

''በአባይ ተፋሰስ ዙርያ የተፈረመው ውል ስድስት አገሮች ፈርመዋል፣አራቱ በፓርላማ አፅድቀዋል፣በፓርላማ ያፀደቁት ስድስት ሲሆኑ አስገዳጅ ሕግ ሆኖ ይወጣል'' አቶ ተስፋዬ ይታይህ በስቶኮልም የኢትዮጵያ ኤምባሲ የፖለቲካ፣ኤኮኖሚ እና ዲያስፖራ ጉዳዮች ካውንስል ሚኒስትር 

በመጨረሻ በቀረቡት ጉዳዮች ዙርያ እና በኢትየጵያ መንግስት ፖሊሲ በኩል ያሉት ሁኔታዎች ላይ ማብራርያ የሰጡት አቶ ተስፋዬ ይታይህ በስቶኮልም የኢትዮጵያ ኤምባሲ የፖለቲካ፣ኤኮኖሚ እና ዲያስፖራ ጉዳዮች ካውንስል ሚኒስትር ነበሩ።አቶ ተስፋዬ በቅድሚያ የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ ይህንን ዝግጅት በማዘጋጀቱ አመስግነው በውይይቱ ላይ የተሳተፉ እና ጥናታዊ ዝግጅታቸውን ያቀረቡትን ምሁራንን  አመስግነዋል።በመቀጠልም የዓባይ ግድብ በተመለከተ እንግሊዝ ሱዳን እና ግብፅ በቅኝ ግዛት ዘመን ውል እንዲገቡ ያደረገችው በዋናነት በማንቸስተር የነበረው የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎቹ በዓባይ ላይ ከሚመረተው ጥጥ ተጠቃሚነታቸው እንዳይጎድ መሆኑን ገልጠዋል።ከእዚህ በመቀጠል የአባይ ተፋሰስ አገሮች ውስጥ ስድስቱ የፈረሙት ውል በአራቱ አገሮች ፓርላማዎች  የፀደቀ ሲሆን በቀሩት ሁለቱ አገሮች ፓርላማ ሲፀድቅ አስገዳጅ ሕግ ሆኖ እንደሚወጣ ገልጠዋል። ቀደም ብሎ በዶ/ር አሸናፊ የቀረበው የመጋቢት 2015 ዓም ውል አስር አንቀፆች ያሉት ሲሆን ውሉ በዋናነት የተፋሰሱ አገሮች የጋራ ተጠቃምነትን የሚያጎላ መሆኑን አቶ ተስፋዬ አብራርተዋል።

የግብፅ መንግስት ባለፈው የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይ አልሲሲ (የግብፅ ፕሬዝዳንት) የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ትራምፕን አደራድረን ማለታቸውን ያስታወሱት አቶ ተስፋዬ።ድርድሩ በአግባቡ ባለመሄዱ  ኢትዮጵያ እንዳልተስማማችበት ያያችሁት ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ በቅርቡ ደግሞ ግብፅ ወደድርድር እንመጣለን ማለታቸውን ሰምተናል ብለዋል።ሱዳንን አስመልክቶ አቶ ተስፋዬ ሲያብራሩ፣ ሱዳን በቅርቡ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት የላከችው ደብዳቤ ላይ የኢትዮጵያን የመልማት መብት ሳይነካ የግድቡ ደህንነት ጉዳይ የተመለከተ ሃሳብ የያዘ ነው።ኢትዮጵያ ግን በሐምሌ ወር የግድቡን የተወሰነ ክፍል ትሞላለች ቀሪውን  ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት ይሞላል ያሉት አቶ ተስፋዬ ግብፅ ጉዳዩን ወደ ውስብስብ ዲፕሎማሲ ለመውሰድ ትሞክራለች፣ዘመቻው ደግሞ በራሳቸው ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሁሉ የታገዘ ነው ብለዋል።

አቶ ተስፋዬ ማብራሪያቸውን በመቀጠል ኢትዮጵያውያንም የፐብሊክ ዲፕሎማሲ መስራት እና በውጭ ያለ ኢትዮጵያዊም የእየሀገሩ የፓርላማ ሰዎች ጨምሮ እውነታውን ማስረዳት አስፈላጊ መሆኑን አበክረው ተናግረዋል።እውነታው ደግሞ ኢትዮጵያ ከ70% በላይ ሕዝብ አሁንም መብራት የሌለው፣የውሃ ማማ እንባል እንጂ አብዛኛው ሕዝብ በቂ ውሃ የሌለው ነው።ግብፅን ብንመለከት ግን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የሕዝቧን የውሃ እና የኤሌክትሪክ ፍላጎት አሟልታለች።ስለሆነም ይህንን እውነታ ለሌላው ዓለም መንገር ያስፈልጋል ያሉት አቶ ተስፋዬ በቅርቡ በስዊድን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሑራን የስዊድንን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አግኝተው በግድቡ ዙርያ እና በኮቪድ 19 ዙርያ መወያየታቸው ጥሩ አብነት መሆኑን ጠቅሰዋል።በኢትየጵያ መንግስት በሁሉም መስክ ጥረቱ እንደቀጠለ እና ቀደም ብሎ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የተመሰረተው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ውስጥ የኢትዮጵያ የተለያዩ ቤተእምነቶች ያሉበት ቡድን አሁንም አለ ብለዋል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተመለከተ አቶ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የተደረጉትን ቅድመ ጥንቃቄዎች ካወሱ በኃላ ኤምባሲያቸው የኮቪድ 19 ግብረ ኃይል በስካንድንቭያ አገሮች ባሉ ኢትዮጵያውያን እያስተባበረ ሲሆን በእዚህም መሰረት እስካሁን 675 ሺህ ክሮነር ከስዊድን እና ኖርዌይ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተሰብስቧል ብለዋል።በሕክምና ቁሳቁስ በኩል ደግሞ 270 ሺህ ብር የሚያወጣ ቁሳቁስ መገኘቱን አቶ ተስፋዬ ገልጠዋል።በመጨረሻም አቶ ተስፋዬ በድጋሚ መድረኩን እና የተሳተፉ ምሁራንን አመስግነው ወደአገር ቤት የሚላኩ የህክምና ቁሳቁስ ላይ እና ግድቡን በተመለከተ የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ሥራ ከኢትዮጵያውያን እንደሚጠበቅ አፅኖት ሰጥተው  ገለፃቸውን አጠናቀዋል። 

በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተመለከቱ አስተያየት ከተሰጠ በኃላ የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ ወደፊት የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኖርዌይ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ የሚመካከሩበት መድረክ እንደሚያመቻች ተገልጦ በዕለቱ ለተሳተፉት ተሰብሳቢዎች፣ጥናታዊ መረጃዎችን ላቀረቡ ምሁራን እና ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ኃላፊ ምስጋና ከኢትዮያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ ከቀረበ በኃላ የዕለቱ ስብሰባው ተፈፅሟል።

 
ጉዳያችን ሚድያ፣ኮሚኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት 
Gudayachn Multimedia, Communication and Consultant
Gudayachn Multimedia, Kommunikasjon og Konsultent 

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...