ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, June 29, 2020

የስምዖን ጉዳይ ተገቢው ምርመራ እና ፍትሕ ይፈልጋል

 ወጣት ስምዖን ደስታ (ፎቶ ኤንአርኮ)

(ጉዳያችን ሪፖርት)

ስምዖን ደስታ ይባላል።በኦስሎ፣ኖርዌይ ነዋሪ ነው።ስምዖን በስነ ምግባሩም፣በትምህርቱ እና ከሰዎች ጋር ባለው መግባባት ሁሉ የሚያውቁት ብቻ ሳይሆን በአንድ ቀን የተዋወቁት ሁሉ የሚወዱት ነው።በኦስሎ መካነ ቅዱሳን ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት አባል እና በሚታዘዘው አገልግሎት ሁሉ  በማገልገል በምሳሌነት የሚጠቀስ ቅን ወጣት ነው።

ይህ ወጣት ባሳለፍነው ወር ማለትም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ግንቦት 17/2020 ዓም የኖርዌይ ብሔራዊ በዓል ቀን የሚከበርበት ዕለት እንደመሆኑ እርሱም የበዓሉን ዝግጅት ከቅርብ ባልንጀሮቹ ጋር ለማክበር በኦስሎ የከተማ አውቶብስ  እየሄደ ነበር። በመጨርሻም ''ልሳከር'' የአውቶብስ ጣብያ (የመውረጃ ቦታው) ሲደርስ እንደማንኛውም ተሳፋሪ ከአውቶብሱ ሲወጣ የገጠመው እጅግ አስደንጋጭ ጉዳይ ነበር። ስምዖን ለኖርዌይ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን (ኤንአርኮ) እንደ አውሮፓውያ አቆጣጠር ሰኔ  24/2020 ዓም እንደገለጠው እና ጋዜጠኛ አኔት ሁብሰን እንደዘገበችው -

'' ከአውቶብሱ እንደወረድኩ አንድ ሰው ወደ እኔ እየተጠጋ ፀያፍ ስድቦችን ሰደበኝ፣ከሰደበኝ ውስጥ አንተ የውጭ ሰው ነህ ወደ መጣህበት ተመለስ ! እና ሌሎች ይገኙበታል።በመቀጠል እጄን፣ክንዴን እና በመቀጠል ጥርሶቼ ላይ መላልሶ መታኝ'' ማለቱን ጠቅሳለች።

ስምዖን የእዚህ ዓይነት ጥቃት በአደባባይ ሰው እየተመለከተ በማያውቀው ሰው ከተፈፀመበት በኃላ ደም እየፈሰሰው እና አንድ ጥርሱን እንዲያጣ ተደርጎ እራሱን ለመከላከል ያደረገው ጥረትም ሳይሳካ ከወረደበት የከተማ አውቶብስ ማረፍያ ወደ ሆስፒታል ለመሄድ ተገዷል።ድርጊቱ የዘረኝነት ጥቃት ለመሆኑ ስምዖንም፣የኤንአርኮ ዘጋቢም ሆነ ጉዳዩን መመርመር የጀመረው የኖርዌይ  ፖሊስ ሁሉም በጋራ ያመኑበት ጉዳይ ነው።

ወንጀሉ የኖርዌይ ፖሊስ የመዘገበበት ክፍል (የወንጀሉ ''ካታጎሪ'') ''በቆዳ ቀለም እና ማንነት ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ንግግር እና ጥቃት'' በሚል ርዕስ ስር መሆኑን በእዚሁ በኤንአርኮ ዘገባ በተገለጠው መሰረት ለማወቅ ተችሏል።የኖርዌይ ፖሊስ ዳይሬክቶሬት የወንጀል ምርመራ ክፍል ''አክቲንግ'' ኃላፊ አስትሪድ ቡርገ፣ የኖርዌይ ፖሊስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኖርዌይ የእዚህ ዓይነቱ የዘረኝነት ጥቃቶች ላይ ትኩረት እንደሰጠ እና በማኅበረሰቡም ውስጥ የበለጠ ትኩረት እያገኘ እንደመጣ ለኤንአርኮ እንደገለጡለት ዜናው በተጨማሪ ያብራራል።

የኖርዌይ ፖሊስ ዳይሬክቶሬት የወንጀል ምርመራ ክፍል ''አክቲንግ'' ኃላፊ አስትሪድ ቡርገ (ፎቶ ሸትል ግሩድ)

ለማጠቃለል የእዚህ ዘገባ ጸሐፊም ስምዖንን እንደሚያውቀው፣ ወጣቱ ፈፅሞ ከማንም ጋር ግጭት የመፍጠር ስብዕና ያለው ወጣት አይደለም።ወጣቱ በክርስትና ሃይማኖት የታነፀ እና እጅግ የሰከነ ስብዕና ያለው ወጣት ነው።በመሆኑም በስምዖን ላይ የእዚህ ዓይነት ጥቃት ፈፅሞ ሊፈፀምበት የሚገባ አይደለም።በስምዖን ላይ ብቻ አይደለም፣ድርጊቱ በማንም ላይ ሊፈፀም የማይገባ ድርጊት ነው።በመሆኑም ፖሊስ ተገቢ ምርመራ አድርጎ በወጣቱ ላይ የዘረኛ ጥቃት የፈፀመው ወንጀለኛ እና ተባባሪዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲያደረግ የሁሉም ፅኑ ፍላጎት ነው።


No comments: