==========
ጉዳያችን ምጥን
=========
ወቅታዊው ሁኔታ
አሁን ባለው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ትልቁ አጀንዳ በአማራ ክልል በታጣቂዎች እና በመከላከያ መሃከል እየተደረገ ያለው ጦርነት ነው።''ሁለት ሰዎች ሲጣሉ ችግሩ ቀላል ሊሆን ይችላል።ሁለት ሺህ ህዝብ ከሁለት ሺህ ህዝብ ጋር ሲጣላ ግን ጉዳዩ ጦርነት ነው '' የሚል አባባል አለ። በኢትዮጵያ አሁን እየሆነ ያለው ከተራ ግጭት ባለፈ ትርጉም የማይሰጥ የወንድማማቾች አሳዛኝ ጦርነት እየተደረገ ነው። ጦርነቱ ከመከላከያም ከታጣቂዎችም ሆነ ከሰላማዊው ህዝብ የሚወድቀው ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ የማትተካው ውድ የሰው ህይወት ነው። በአማራ ክልል አሁን ያለው ጦርነት መነሻ ምክንያት እና መፍትሄው በተመለከተ ከስድስት ወር በፊት ጉዳያችን ላይ ''የኦነግ/ኦህዴድ እና የህወሓት ጽንፈኝነት የአማራ ጽንፈኝነትን ወለደ። ኢትዮጵያን መልሰን ወደ አንደኛ ክ/ዘመን እንዳንከታት መንግስት የኃይል መንገድን ብቻ ከማሰብ ይልቅ ቀድሞ መከወን ያለበት ተግባር ላይ ያተኩር።'' በሚል ርዕስ ላይ ለመግለጽ ስለሞከርኩ እርሱን እዚህ ላይ ለመድገም አልፈልግም።ከእዚህ ይልቅ በወቅታዊው የአማራ ክልል ሁኔታ አንጻር ህዝቡ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ ዙርያ የተወሰኑ ነጥቦችን ላንሳ። እዚህ ላይ በአማራ ክልል ህዝብ ላይ በእዚህ ጦርነት ሳብያ እየደረሰ ያለውን ፈተና በውጭ የሚገኙ ዩቱበሮች ፈጽመው አያነሱትም።ዩቱበሮቹ ''ታጣቂዎች ይህንን ያዙ'' የሚል ዜና ላይ እንጂ በእዚህ ጦርነት የክልሉ ህዝብ የደረሰበት ማኅበራዊ፣ምጣኒያዊ ሐብታዊና ስነልቦናዊ ችግር ጥልቀት የሚናገር የለም።
አሁን በአማራ ክልል በሚደረገው ጦርነት ሳብያ የአማራ ክልል ህዝብ ላይ እየደረሰ ስላለው ሰቆቃ ያልሰማነው ከሰማነው ይበልጣል።
በአማራ ክልል ከተነሳው ጦርነት በኋላ የህዝብ ትራንስፖርት በአብዛኛው የክልሉ ከተማና ገጠር መሃል ግንኙነት ተቋርጧል፣ኢንተርኔት ለተወሰኑ ተቋማት ከመፈቀዱ በላይ ባብዛኛው ቦታ አይሰራም፣ከሁለት ሚልዮን ያላነሱ ህጻናት፣ታዳጊዎችና ወጣቶች ወደ ትምህርት ቤት እየሄዱ አይደለም።በጦርነቱ ሳብያ ከታጣቂዎችም ሆነ ከመንግስት ድሮን ጭምር የሚወነጨፉ አረሮች ሰላማዊ ህዝብንም ለሞት እየዳረገ ነው።የድሮን ጥቃቶቹን ተከትሎ ቢቢሲ ያነጋገራቸውን ጨምሮ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አረጋግጠውታል።
የክልሉ ህዝብ መከራ ግን በእዚህ አላበቃም ጉዳያችን በክልሉ ከሚገኙ ሦስት ከተሞች ለማጣራት እንደሞከረችው በአማራ ክልሎች ውስጥ የሚኖረው ህዝብ በቀትር ፀሐይ በሚዘርፉ ሌቦች ችግር ላይ ነው።''ቀን በቀን ይዘርፉሃል።'' አለ አንድ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ደብረታቦር ነዋሪ የሆነ ወጣት ለጉዳያችን አሁን ያለውን ሁኔታ ሲናገር።'' መንገድ ላይ ጩቤ አውጥቶ ሞባይል ይሁን ምንም የያዝከውን ይዘርፍሃል።'' በማለት ቃሉን ሰጥቷል። ወጣቱ ማን እንደሚዘርፍ ሲጠየቅ ''ማን እንደሆኑ አይታወቅም። ዝርፍያው በምሽትም ነው።አጋጣሚውን ተጠቅሞ ለመክበር የሚፈልግ አለ።'' በማለት አብራርቷል።
በተመሳሳይ በምስራቅ ጎጃም ነዋሪ ከሆነ ወንድሙ ጋር የተገናኘ የጉዳያችን አንባቢ በከተማዋ ያለውን ሁኔታ ሲገልጽ ወጥተን መግባት ስጋት ሆኖብናል።ከየት እንደተተኮሰ በማታውቀው ጥይት የመሞት አደጋ በራችን ላይ ነው በማለት የነገረውንና ከወጣቱ አንደበት የሰማው ከፍተኛ የፍርሃት፣የተስፋ መቁረጥና የሃዘን ስሜት ባነጋገረው ወቅት እንደተረዳ ሲገልጽ። '' እኔ በባህር ማዶ እያለሁ።ከርሱ ጋር ባደረኩት ንግግር እስካሁን ያጋባብኝ የሃዘን ስሜት አልለቀቀኝም'' በማለት ነበር የገለጸው።
አሁን በአማራ ክልል ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው የጦር ሜዳው ገባ ወጣ ዜና ነው እንጂ የህዝቡን እውነተኛ ሰቆቃ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ግብ ተብሎ በዩቱበርም በመንግስት ሚድያም አይነገርም። ይህ በራሱ የሚያም ትልቅ ስብራት ነው።በአማራ ክልል ውስጥ ያለው ህዝብ ከረሃብ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የሃብት ውድመት እና ስነልቦናዊ ጥቃት ደርሶበታል።መንግስት በሚጠራቸው ስብሰባዎች ላይ የተለየ ሃሳብ ቢናገር ከታጣቂዎቹ ደጋፊዎችም ሆነ ከመንግስት ካድሬ ነገ እንዲህ ሊያደርጉኝ ይችላሉ በሚል ተሳቆ እውነቱን ለመናገር ተቸግሯል።
የክልሉ ህዝብ አሁን የናፈቀው ሰላም መቼ ነው የሚመጣው የሚለውን ጥያቄ የሚመልስለት ነው።ጉዳያችን ያነጋገረችው የደቡብ ጎንደር ነዋሪም ስራ ሁሉ መቆሙን ህዝብ ያለበትን የፈተና ደረጃ ከገለጸ በኋላ ችግሩ የሚፈታበት መንገድ እንዳይመጣ አንዱ ሽማግሌ ሃሳብ ቢያነሳ የመንግስት ደጋፊ ፋኖ ስለሆንክ ነው ይሉታል፣ ስለሰላማዊ ሃሳብ የሚያነሳ ሲሆን ደግሞ የብልጽግና ካድሬ ነህ ይሉታል።ስለሆነም የችግሩ ስፋት እንዲህ ቀላል አይደለም።በማለት አብራርቷል።በምስራቅ ጎጃም ነዋሪን ያነጋገረው የጉዳያችን አንባቢም ተመሳሳይ ሃሳብ አግኝቷል።በምስራቅ ጎጃም ነዋሪ የሆነው የክልሉ ነዋሪ ከሁሉም ያናደደው በክልሉ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር በውጭ ያሉ ዩቱበሮች እንደማይናገሩ መስማቱን ነበር። ኢንተርኔት ከመጥፋቱ በፊትም ሆነ አሁን በሚሰራበት መስርያቤት አልፎ አልፎ በሚለቀቀው የኢንተርኔት መስመሮች በውጭ የሚኖሩ ዩቱበሮች ስለ ታጣቂዎቹ እንጂ በህዝቡ ላይ እየደረሰ ስላለው መከራ አንዳች አለማውራታቸው በስማችን የሚነግዱ ለመሆናቸው ማስረጃ ነው በማለት በብሽቀት ገልጾለታል።
አንዳንዶች ይህ ተራ የስም ማጥፋት ወይንም የዩቱበሮቹን አመለካከት ለመጻረር የቀረበ ሊመስለው ይችል ይሆናል።ነገ ህዝቡ የሚናገረው እውነት ይሄው እንደሚሆን ጊዜ ያሳየናል።በክልሉ እየሆነ ያለው ብዙ ያልተነገረ ጉዳይ አለ።ከዘረፋው ወደትምህርት ቤት መሄድ ካልቻለው በላይ በክልሉ ከአስር ሺህ በላይ ቀዶ ጥገና ቀጠሮ ያላቸው የክልሉ ነዋሪ ህሙማን በጊዜ ቀዶ ጥገና ማድረግ ባለመቻላቸው ህይወታቸው አደጋ ላይ መሆኑን የራሱ የክልሉ ሚድያ የዘገበው ነው።ችግሩ የትዬለሌ ነው።ይህንኑ ግን የሚነግረን ሚድያ የለም።
መከላከያ ክልሉን ለቆ ይውጣ የሚለው አባባል የአማራ ክልል ጥያቄ ነው?
''መከላከያ ክልሉን ለቆ ይውጣ'' የሚለው አባባል በመጀመርያ ህወሃት በትግራይ ሲያቀነቅነው ነበር። ዛሬ ላይ ደግሞ ሸኔ ይህንኑ በኦሮምያ እንዲደረግ ሲጠይቅ ተሰምቷል። ይህንን ጥያቄ የአማራ ክልል ህዝብ እንደጠየቀ ተደርጎ በአንዳንድ ዩቱበሮች ሲነገር መስማት ደግሞ የቅርቡ ክስተት ነው።የአማራ ክልል ህዝብ ከመከላከያው መሃል ህዝብ የበደሉ ለፍርድ ይቅረቡ ይላል እንጂ መከላከያ ክልሉን ለቆ ወጥቶ የመንግስት መዋቅር ለቆ እንዲወጣ አይፈልግም።መከላከያ አንድ ክልል ለቆ ወጣ ማለት ትርጉሙ ምን ማለት ነው? ይህንን ተከትሎ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖር ክልል ምን ሊገጥመው ይችላል? አሁን ከደረሰበት ፈተና መልኩን ቀይሮ በምን ዓይነት የከፋ ችግር ላይ እንደሚወድቅ ለመተንበይ ሊቅ መሆን አይጠይቅም። ዛሬም ግን በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ በሚጠይቁ ሳይቀር መከላከያ ከ''ክልሉ ይውጣ'' ንግግር ሲነገር እየሰማን ነው።መከላከያ ከክልሎች ለቆ ይውጣ በራሴ ታጣቂ እተዳደራለሁ ማለት ሌላ ምንም ትርጉም ያለው ሳይሆን ኢትዮጵያ ትፍረስ፣በእየጎጣችን እንግባ የማለት ያህል ነው። አንዳንዶች ይህ ሲነገር ጉዳዩን ከጦርነቱ ጋር አያይዘው ብዙ ጉዳዮች ሊያነሱ ይችላሉ። ይህ መከላከያ ለቆ ይውጣ የሚለው አባባል ሶርያዎችም፣ሊብያዎችም ሆኑ የመኖች ከመፍረሳቸው በፊት የነበረ ዜማ ነው። አንዳንዴ አጀንዳዎቹን እነማን ከየት ቀድተው እንደሚያቀብሉን እየተረዳን ያለን አንመስልም።
ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሌላው ዓለም የተለየ ችግር አልገጠመውም።መፍትሄ የሌለው ችግርም የለም። የችግሮቻችን መነሻ ምክንያቶች በዛሬዋ ቀን ወይንም ምሽት የተፈጠሩባት አይደሉም።የረጅም ጊዜ የከመርናቸው የተሳሳቱ ትርክቶች፣የውስጥ ሴራዎች እና የባዕዳን እጅ ጭምር ናቸው። በእዚህ ጹሑፍ መነሻ ላይ በተያያዘው ሊንክ ላይ እንደተገለጸው በአማራ ክልል ላለው ችግር መነሻው በኦሮምያ ክልል የተነሳው የጽንፍ ኃይልና ይሄው ኃይል ደግሞ በመንግስት መዋቅር ውስጥ እንደፈለገ መስራቱ እንደሆነ ተብራርቷል።ወደመፍትሄው ለመምጣት ግን አሁንም ከእዚህ በፊት የክልሉ ግጭት ሲጀምር በነሐሴ ወር በጉዳያችን ላይ ቢወሰዱ ያልኳቸው የመፍትሄ ሃሳቦች አሁንም ዳግም ቢታዩ በማለት ይህንን የጉዳያችን ምጥን እቋጫለሁ።የመፍትሄ ሃሳቡ ሊንክ ''በአማራ ክልል የተነሳው አለመረጋጋትን በፍትሐዊ እና ርቱዕ በሆነ መንገድ ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማድረግ የሚገባቸው ሦስት ተግባራት።'' በሚል ርዕስ የጻፍኩትን ሳላስታውስ አላልፍም።
==================//////==========