ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, April 28, 2023

የኦነግ/ኦህዴድ እና የህወሓት ጽንፈኝነት የአማራ ጽንፈኝነትን ወለደ። ኢትዮጵያን መልሰን ወደ አንደኛ ክ/ዘመን እንዳንከታት መንግስት የኃይል መንገድን ብቻ ከማሰብ ይልቅ ቀድሞ መከወን ያለበት ተግባር ላይ ያተኩር።

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም እና ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

በእዚህ ጽሑፍ ሥር 
  • '' ዐማራን እናንተ ትፈጥሩታላችሁ የሚል ስጋት ነው ያለኝ '' ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ለአቶ መለስ የነገሯቸው።
  • የኦነግ/ኦህዴድ እና የህወሓት ጽንፈኝነት የአማራ ጽንፈኝነትን ወለደ።
  • ህወሃት እና ኦነግ/ኦህዴድ የአማራ ብሔርተኝነትን እንዴት ፈጠሩት?
  • የአማራ ብሔርተኝነትን ያባባሱት የቅርብ ክስተቶች 
  • መንግስት ሊያስተካክላቸው የሚገቡ ሦስት ጉዳዮች

=========
ጉዳያችን ምጥን
=========

በኢትዮጵያ የፖለቲካ እና ምጣኔ ሃብት ችግሮች ውስጥ ሁሉም በጋራ የሚያዜማት ዜማ አለች።የዜማው አቀራርብ ይለያይ እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ ሕዝብም፣ ጋዜጠኛውም ሆነ ጸሓፊው የሚለው የሚያጠነጥነው የሃሳብ መቋጠሪያ  ''የሁላችንም የሆነች ኢትዮጵያ ''የጋራ ተጠቃሚነት"  እና ''እኩልነት '' የሚሉት ናቸው። እነኝህ ዜማዎች አሁን እንደቅንጦት እየተቆጠሩ መጥተው ሌላው አንገብጋቢው ጥያቄ ''የሕግ የበላይነት '' እና ''የጸጥታ ደህንነት '' የሚሉት እየገዘፉ መጥተዋል።

ኢትዮጵያውያን ቤተመንግስት ውስጥ ማንም ከየት ብሔር መጣ እምነት ዋና ጉዳያቸው አይደለም። ይህ ማለት ግን ቤተመንግስት የገባው ሁሉ የራሱን የጎሳ አስተሳሰብ ያለውን ወይንም የግል የእምነት መንገዱን ሕዝብ ላይ እንዲጭን ወይንም የህዝብን መልካም ዕሴት እንደፈለገ እንዲያጎሳቁል ይፈቅዳሉ ማለት አይደለም። እነኝህ ጉዳዮች በተለይ ህወሃት/ኢህአዴግ አራት ኪሎ ከገባ ወዲህ ይዞት የመጣው የጎሳ ፖለቲካ ብዙ ነገራችንን ጎድቶብናል። 

'' ዐማራን እናንተ ትፈጥሩታላችሁ የሚል ስጋት ነው ያለኝ '' ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ለአቶ መለስ የነገሯቸው።

አቶ መለስ ወደ አራት ኪሎ እንደገቡ ፊት ለፊት አግኝተው ካነጋገሯቸው ውስጥ ፕሮፌሰር  መስፍን ወልደማርያም አንዱ ነበሩ። ፕሮፈሰር መስፍን በወቅቱ የዐማራ ብሔርተኝነት የአሁኑን ያህል ገንግኖ ሳይወጣ የብሔርተኝነት አካሄድ ያለውን ችግር ብቻ ሳይሆን አማራ የምትሉት እራሱ አማራ እንደሆነ አያምንም እኔ በተወለድኩበት አካባቢ እናቴም አማራ የሚለውን የምትጠቀመው ለብሄር አይደለም በሚል ለማስረዳት ሞከሩ። አቶ መለስ ግን ስለ ጭቁን አማራ እና ገዢ አማራ እያሉ በጫካ ስላነበቡት እና ካድሬዎቻቸውን ሲያሰለጥኑ የነበረበትን ትርክት መንገር ጀመሩ። በመጨረሻ ፕሮፌሰር መስፍን ተናገሩ '' አሁን በሚሉት ደረጃ የአማራ ብሔር ብሎ እራሱን አገንግኖ የወጣ የለም። ሆኖም ግን የእኔ ስጋት ይህንን አማራ የሚባል የብሔርተኝነት ስሜት እናንተ እንዳትፈጥሩት ነው።'' በማለት ተናገሩ። 

ይህንን የፕሮፌሰር መስፍን አማራን ትፈጥሩታላችሁ ንግግር አንዳንዶች ፕሮፌሰር የአማራን ህልውና ከድተውታል በሚል ሲወቅሷቸው ነበር።የፕሮፌሰሩ ሃሳብ ግን መሬት ላይ የአማራ ማኅበረሰብም የሚያስበውን (በወቅቱ የነበረውን) እና ወደፊት የሚሆነውን ነበር ለማንጸባረቅ የሞከሩት። ዛሬ ላይ ስንመለከት የኦነግ እና የህወሃት ጽንፈኛ የብሔርተኝነት አካሄድ የአማራ ብሔርተኝነት አገንግኖ እንዲወጣ እያደረገው እንደሆነ እንመለከታለን።

የኦነግ/ኦህዴድ እና የህወሓት ጽንፈኝነት የአማራ ጽንፈኝነትን ወለደ።

በኢትዮጵያ ያለፉት ሃምሳ ዓመታት የፖለቲካ ትግል ውስጥ ከጎሰኝነት ፖለቲካ ከማገንገኑ በፊት የኢትዮጵያ ወጣቶች የትግል ማጠንጠኛ የነበረው የርዕዮተ ዓለም ፍትጊያ ነበር። ይህ ሁኔታ ግን ህወሃት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ግን የፖለቲካ አውዱ ተቀየረ። የጎሳ ፖለቲካ አስተሳሰብ ተማርን እና ነቃን በሚሉ ጥቅም ፈላጊዎች እየተቀነቀነ በህወሃት ዙርያ የተኮለኮሉ አዳዲስ የጎሳ ፖለቲከኞች መፈልፈል ጀመሩ። እነኝህ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኝ ፖለቲከኞች በኢህአዴግ ጥላ ውስት ቆይተው የብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረትም ኢትዮጵያ የሚለውን አጀንዳ ይዘው ቀጠሉ። በብልጽግና ዘመን የጎሳ ፖለቲካ በእየክልላቸው ሲያራምዱ የነበሩ አመራሮች ላይ የበለጠ ጽንፈኛ የሆነው የኦነግ ፖለቲከኞች ከክልል ምክርቤት እስከ የጸጥታ መዋቅር ተቀላቀሉ። በአዲስ አበባ ከተማ ሳይቀር የኢትዮጵያ አረንጓዴ፣ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ምልክት ያለበት መኪናቸው ላይ እና እጃቸው ላይ አድርገው ሃይማኖታዊም ሆነ ሌላ ክብረበዓላት ላይ የሚገኙትን እነኝህ ከኦነግ የተቀላቀሉ እና ቀድሞም በኦህዴድ ስር የነበሩ ጽንፈኞች ሲያስወልቋቸው የህዝብ ቁጣ ቀሰቀሰ።

የለውጡ ሂደትን በከፍተኛ ደረጃ በተለይ የዶ/ር ዐቢይ ኢትዮጵያዊነትን በቦታው እንመልሳለን፣ኢትዮጵያ የሁሉም ትሆናለች የሚሉት ንግግሮች ተከትሎ የአማራ ክልል ህዝብ ደግፎ ቆሟል። አንድወቅትም በመላው የአማራ ክልል የዶ/ር አብይን የለውጥ ሂደት የደገፈ ሰልፍ ሲደረግ በኦሮምያ ክልል ምንም ዓይነት ሰልፍ ሳይደረግ የዋለባቸው ጊዜዎች ነበሩ። ይህ ሁኔታ ደግሞ በቅርቡ ተገልብጦ በኦሮምያ ክልል ከተሞች የድጋፍ ሰልፍ ሲደረግ በአማራ ክልል ደግሞ ምንም ዓይነት የድጋፍ ሰልፍ ሳይደረግ አልፏል። 

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የአማራ ክልል ህዝብ በብሔር ፖለቲካ ውስጥ የገባበት ሂደት በራሱ ዘገምተኛ ቢሆንም በሂደት ግን የህወሃት እና የኦነግ የጽንፍ እና የጥላቻ ትርክቶች ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት የአማራ ብሔርተኝነትን የጽንፈኞቹ መግፋት ፈጥሮታል። ይህንን ሁሉም ወገን ሊያምነው የሚገባው እውነታ ነው። የአማራ ክልል ህዝብም ሆነ ፖለቲከኞች በአሁኑ የለውጥ ሂደት ላይ እጅግ አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጡ ቤተመንግስት የገባው ከኦሮሞ ሆነ ከበሻሻ፣ከባሌ ሆነ ከአፋር የሚል ትንተና ውስጥ አልገቡም። ይህንን የጎሳ አስተሳሰብ ከመጸየፋቸው የተነሳም ነው የህውሃትን ያንን ሁሉ የጎሳ ጥላቻ ውርጅብኝ እየታየ እንዳላዩ በማለፍ የኢትዮጵያን ህልውና ላይ ሌላ እራስ ምታት ሳይሆኑ ያለፉት ብሎ መውሰድ ይቻላል። ይህንን በተለያዩ ጥናቶች ቢዳሰስ ከእዚህ የተለየ ውጤት የሚያሳይ አይመስለኝም።

ህወሃት እና ኦነግ/ኦህዴድ የአማራ ብሔርተኝነትን እንዴት ፈጠሩት?

አንዳዶች ከኦነግም ሆነ ከህወሃት መንደር የአማራ ብሔርተኝነትን አስመልክተው የሚሉት ቀድሞ በነበሩ መንግስታት ውስጥ እንደነበረ አድርገው ለመተረት ይሞክራሉ። በመጀመርያ ደረጃ በኢትዮጵያ የጥንትም ሆነ የመካከለኛው ዘመን ታሪክ ውስጥ የጎሳ ፖለቲካ ብሎ ጉዳይ የለም።ከእዚህ ይልቅ የሃይማኖት ጉዳይ ቀዳሚ ጉዳይ ሆኖ እንደኖረ ማንም የኢትዮጵያን ታሪክ የሚዳስስ የሚረዳው ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ ነገስታት ለስልጣን በሚያደርጉት ሹክቻ የሚነሱት ከመንደራቸው ሰው በማሰባሰብ ስለሆነ በዙርያቸው የቅርብ ዘመዶቻቸው እና የተወለዱበት መንደር ሊገኙ ይችላሉ። እንደ መዋቅር እና የመንግስት ስሪት ግን የገበረላቸው ሁሉ ልጃቸውን ሳይቀር እየዳሩ ግዛት ያስፋፋሉ እንጂ በጎሳ ስሜት መሄድ በራሱ የታየ ክስተት አይደለም።ለእዚህም የእርስ በርስ ጦርነት ሲያደርጉ በቦታው ይጠራሉ እንጂ የእገሌ ጎሳን እንዲህ አድርጌ ወይንም የእኔ ይህ ጎሳዬ ብለው የጻፉት ጽሁፍ የለም። በወቅቱ ከወሎው ገዢ ከትግራዩ ባላባት ወይንም ከሐረሩ ባላባት እያሉ ከመጻፍ ውጪ ያ ባላባት በትውልዱ ሌላ ቢሆንም የትውልድ ሃረጉን እንደ የግጭት ወይንም የስልጣን መፋተጊያ ምክንያት አልነበረም። ከእዚህ ይልቅ የስልጣን ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ ነበር።

የአማራ ክልልም የሚያውቃት ኢትዮጵያ ይህች ነች።ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ወደ ስልጣን ሲመጡም ኢትዮጵያዊ ናቸው የሚለው ገዢ ሃሳብ ብቻ በውስጡ የነበረ እና አንዳንድ በውጪ የነበሩ የአማራ ብሔርተኝነት ገንግኖ እንዲወጣ የሚወተውቱትን ሁሉ የማይሰማ ህዝብ ነበር። ይህ ሁኔታ ግን በኦነግ የለየለት አማራን የለየ የዘር ጭፍጨፋ ከወለጋ እስከ ሌሎች የኦሮምያ ክልሎች እና የህወሃት የቅርብ ወረራ ወደ የአማራ ክልል የፈጸማቸው ጸያፍ ዘርን ምክንያት ያደርጉ ግፎች የአማራ ክልል ህዝብ የብሔርተኝነት ወይንም የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች የአማራ አክቲቪስቶችን ወደ መስማት አዘነበለ። የአማራ የጎሳ የጽንፍ አስተሳሰብ አወላለድ እንዲህ በግፊት እና ኢትዮጵያዊነትን እና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚገፋ አሰራር በኦነግ እና በህወሃት የጽንፍ አካሄድ የተወለደ የቅርብ ክስተት ነው።

የአማራ ብሔርተኝነትን ያባባሱት የቅርብ ክስተቶች 

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የአማራ የብሔርተኝነት ስሜት የቅርብ ክስተት ነው። ያባባሱት ደግሞ የብልጽግና መንግስት ጥንቃቄ የጎደለው አሰራር ብቻ ሳይሆን ከጽንፈኛ የህወሃት እና የኦነግ አካላት ጋር እየተሞዳሞደ የኢትዮጵያዊነት እሴቶችን እየገፈተረ መምጣቱ ነው። ለእዚህ ብዙ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል።ከወለጋ በመቶሺዎች ተፈናቅለው ከአዲስ አበባ እስከ ደብረብርሃን፣ደሴ እና ባሕርዳር ሲበተኑ። የተፈናቀሉትን በመጠለያ ቦታቸው ሄዶ ያጽናና ከፍተኛ ባለስልጣን አልታየም።የምግብ አቅርቦቱ ተጓድሎ፣ፍትህ ተረግጣ እና ኦነግ ሸኔ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ገበሬዎችን እየሰበሰበ ሲገድል የህመሙን መጠን የሚያስተናግድ ስሜት ከብልጽግና ከፍተኛ ባለስልጣናት አለመታየቱ ለአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን ለተቀረው ኢትዮጵያዊም ያስደነገጠ ነበር። 

ከእዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያዊነት እሴቶች እና መገለጫዎች ውስጥ የሆኑ ህዝባዊ በዓላት ሳይቀሩ በብልጽግና ፖሊሶች ሲበተኑ የመንግስት መግለጫ የሆኑ ኃይሎች ያደረጉት ነው እያለ መግለጫ ሲያወጣ የሚያርም የለም። ለእዚህ የዘንድሮውን የዓድዋ በዓል በምንሊክ አደባባይ እንዴት በፖሊሶች እንደተበተነ እና በአራዳ መናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ ውስጥ ታቦተ ሕጉ በወጣበት አስለቃሽ ጋዝ በመርጨት በኢትዮጵያውያን ላይ ፋሺሽታዊ ግፍ ተፈጸመ። ይህ ሁሉ ሲሆን የኦነግ እና የህወሃት ጽንፈኛ አክቲቪስቶች በማኅበራዊ ሚድያ ተሳለቁ። መንግስት እራሱ ሕግ ከማክበር ይልቅ ጥፋቱን ለመሸፈን ያወጣቸው መግለጫዎች የግፍ ግፍ የሚያሳዩ ሆኑ። 

በእነኝህ ሁሉ ግፎች ውስጥ መንግስት ማስተካከል ያለበትን ሳያስተካክል የኦነግ የጽንፍ ቡድን ሲነካ የሚያለቅሰው የኦፌኮው ጀዋር መሐመድ የጽንፍ ቡድኑ ስልጣን መያዙን ዳጎስ ባለ መግለጫ ጽፎ ሲበትን መንግስት ሊጠይቀው አልደፈረም።ከእዚህ ይልቅ አስተያየት ሰጡ፣ዜና አሰራጩ እየተባሉ የማኅበራዊ ሚድያ አሰራጮች እና ጋዜጠኞች ካለ ፍርድቤት ትዕዛዝ እየታፈኑ ተወስደው ሲለቀቁ ህዝብ ተመለከተ። መንግስት ገልብጠናል የእኛ የጽንፍ መንግስት ነው አሁን ያለው። ቀሪው ሥራችን ይህንን እንዴት እናጽናው ነው ብሎ የጻፈን የማይጠይቅ የመንግስት አሰራር እንዴት ታቦት ሊያነግስ በተሰበሰበ ህዝብ ላይ የተወረወረውን የአስለቃሽ ቦንብ የማውገዝ ድፍረት አጣ? የብዙዎች ጥያቄ ሆኖ ከረመ።

ይህ ሁሉ በእንዲህ እያለ በኦሮምያ የጽንፍ ቡድን የተደራጁ እና የኦሮሞ ሚድያ ኔትዎርክ ብቻ ሳይሆን በአቶ ሽመልስ የሚመራው የኦሮምያ ክልል የጸጥታ አካል ሙሉ ጥበቃ የተደረገለት እንዲሁም በመጀመርያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር የተሞገሰ (በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስህተታቸውን አርመው የማስታረቅ ደረጃ ቢሄዱበትም) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለመክፈል የተደረገው የድፍረት የእርቀት ሂደት የኢትዮጵያን ህዝብ በተለይ የአማራ ክልልን ህዝብ በመንግስት ላይ ያለውን ተስፋ መቁረጥ ብቻ ሳይሆን የኦነግ የጽንፍ ቡድን የቱን ያህል ለመሄድ የድፍረት ድፍረት እንዳለው አሳየው። ''ይህንን ያህል ይባልጋሉም ሃይማኖትን ይደፍራሉ ብዬ አልጠበኩም" ያሉት አንድ ኢትዮጵያዊ የድርጊቱ እርቀት የኢትዮጵያን ህዝብ በመንግስት ላይ ያለውን ተስፋ መቁረጥ ግልጽ አደረገው። ሃገር ለሦስት ቀናት ጥቁር የለበሰበት እናቶች መሬት ተኝተው ያለቀሱበት እና ገዳማውያን እና የሙስሊም አባቶች ሳይቀሩ ወደ ፈጣሪያቸው በኦርቶዶክስ ላይ የተሰራውን ግፍ ያመለከቱበት ይህ ድርጊት በኦሮምያ ክልል ህገወጦቹ አብያተክርስቲያናትን ለመቆጣጠር ያደረጉት ሙከራ በተቃወመ ህዝብ ላይ በተወሰደ የግፍ እርምጃ ወጣቶች ህይወታቸው አጡ።

እነኝህ የቅርብ ጊዜ ድርጊቶች የአማራ ብሄርተኝነትን የሚጠላው እና ኢትዮጵያዊነት ብሎ የሚያስበውን የአማራ፣የደቡብ እና የሱማሌ ክልል እና ሌሎች ሳይቀሩ ከጎኑ በሃሳብ ደረጃ ማሰለፍ ቻለ። ይህ በራሱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ስብራት ነው። ሂደቱ የጽንፈኝነት መንገድ ከመሆን አልፎ አንዱ ከአንዱ የበለጠ ጽንፈኛ ለመሆን የሚጋጋጥበት መሆኑ በራሱ ሌላው አሳዛኝና ለኢትዮጵያ ምንም የማይፈይድ ክስተት መሆኑ ግልጽ ነው። ይህ ችግር ግን መንግስትም ሆነ የጽንፍ ኃይሎች ከስህተቶቻቸው ታርመው የማያስተካክሉት ጉዳይ ሊሆን አይችልም። 

መንግስት ሊያስተካክላቸው የሚገቡ ሦስት ጉዳዮች

መንግስት በመጀመርያ የጽንፈኝነት ሃሳብን ሌሎች ላይ እያላከከ በቃላት ከመጫወት በፊት ከጉያው ያሉትን የጽንፍ አስተሳሰብ ያላቸውን በሁሉም የቢሮክራሲ እና የጸጥታ አካላት ውስጥ ያሉትን ያስወጣ። ይህ የመጀመርያው መጀመርያ ይመስለኛል። ይህ ሳይደረግ ምንም ዓይነት ጽንፈኝነት የመዋጋት ስራ መስራት አይቻልም። ከእዚህ በፊት በጉዳያችን ላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ጽንፈኞች ይመጋገባሉ። ምንም ያህል በተቃራኔ ጎራ ቢሆኑ የአንዱ ፍም ለሌላው ደጋፊ ስለሚያስገኝ ተናበው ነው እሳቱን የሚያፋፍሙት።ስለሆነም ከውስጥ ያሉ ጽንፈኞች መንግስትን ወደየተሳሳተ የመረጃ ማመሳቀል እየወሰዱ እንዲደነብር በማድረግ ለግድያ እና ለእስር እንዲፈጥን በማድረግ ጠላት ያሉትን ብሔር ለማጥቃት ሲሰሩ መንግስት እራሱ በሕዝብ የተጠላ ያደርጉታል። ስለሆነም መንግስት ከውስጡ ያሉትን የጽንፍ አራማጆች እንደ የፖለቲካ ስልጣኑ መጠበቂያ ሚዛን የማየት የእብደት አስተሳሰቡን መተው አለበት።

ሁለተኛው ጉዳይ ስህተቶችን ማረም ነው። ከወለጋ እና ከሌሎች ቦታዎች የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሜዳ ላይ ወድቀው የአዲስ አበባ አስተዳደር መንገድ ላይ አንድ ጭልፋ ወጥ እያሳየ ድሆችን እረዳን ቢል ድርጊቱ ምን ያህል መልካም እና መሆን ያለበት ቢሆንም ከሌላ በኩል ያለውን ህመም የሚያይ ባለመኖሩ መፍትሄ አይሆንም። በዘንድሮው የትንሣዔ በዓል ዋዜማ ላይ የአሚኮ የክልል ቴሌቭዥን ከወለጋ የተፈናቀሉ በደሴ ዙርያ ገራዶ መጠለያ ጣቢያ ወደ አራት መቶ ሺህ የሚሆኑ የአማራ ክልል ተወላጆች ምግብ ካገኘን ወራት ተቆጠሩ የሚረዳን የለም ረሃብ ላይ ነን ብለው ሲናገሩ እና የደቡብ ወሎ የምግብ ዋስትና ሃላፊም ይህንኑ ምስክርነት ሲሰጡ ለህዝብ ተላልፏል። ይህንን ተከትሎ የተወሰደ እርምጃ ግን በየትኛውም ሚድያ ላይ አልታየም። ይህ ምን ማለት እንደሆነ የሚያውቀው የሚመለከተው ብቻ ሳይሆን የንግድ ማኅበረሰቡም ሆነ የዲይስፖራውም ማኅበረሰብን የሚመለከት ነው። አሁንም መንግስት እነኝህን ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው ለመመለስ ምን እያደረገ ነው? ከኦነግ ጋርም የሚደረገው ድርድር እንደወጡ ይቅሩ የማያስብል እና ኦነግ ሸኔም ይህንን መቀበል ካልፈለገ መንግስት በሕግ እንዴት ወደቀያቸው ሊመልስ ይፍለጋል? በእዚህ ዙርያ ላይ እነኝህ በኢትዮጵያዊነታቸው የተገፉ ግፏን ላይ አንዳች ሥራ እየተሰራ ለመሆኑ የሚጠቅስ አንድ ሪፖርት እንዴት ይጠፋል? ይህንን ከልብ እንደመንግስት መንግስት የደህንነታቸው ከለላ ባለመሆኑ የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ሃላፊነት በራሱ ላይ ነው የሚወድቀው።

ሦስተኛው ጉዳይ ብልጽግና እንደገና ከጎሳ ፖለቲካ በራቀ መልኩ መበወዝ እና አዳዲስ አዕምሮዎችን ወደ አመራራ ማምጣት አለበት። የብልጽግና የሰው ኃይል ምንጭ በጎሳ ፖለቲካ የታሸው ያው የኢህአዴግ የሰው ኃይል ነው። ይህ የሰው ኃይል አሁንም ከጎሳ እና ከክክልል አስተሳሰብ መራቅ አልቻለም። አንዳንዴ አብሮ ተሰፍቶ ያደገበት ስለሆነ ይህንን የጎሳ አስተሳሰብ ለመንቀል ይቸገራል።ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደሚናገሩት መደመርንና ኢትዮጵያዊነትን የሚይራምዱ ከሆነ በጎሳ ፖለቲካ የታሹ አስተሳሰቦች ብቻ ሳይሆን የክልል አወቃቀሮች፣የሕገመንግስቶ አንቀጾች እና ከላይ እስከታች ያሉ አመራሮች ከጎሰኝነት የጸዱ እና ሁሉን አቀፍ አመለካከት ተቀብለው ሌሎች ላይ ማስረጽ የሚችሉ መሆን አለባቸው። 

ባጠቃላይ የጎሰኝነት የጽንፍ አስተሳሰብ እያገነገነ እንዲመጣ ያደረገው የራሱ የመንግስት ደካማ አሰራር ብቻ ሳይሆን በጽንፈኞች መዋቅሩ ሲንገዳገድ አብሮ በመሞዳሞዱም ጭምር ነው። በአማራ አንጻር ያለውን የጽንፍ የጎሳ አስተሳሰብ የወለዱትም ይሄው የኦነግ እና የህወሃት የጽንፍ መንገድ ነው። ይህ ማለት ግን ምክንያቱም ምንም ይሁን ምን የጽንፍ የጎሳ አስተሳሰብ አማራ ጋር ሲሆን ትክክል ሌላው ጋር ሲሆን ኝ ኃጢአት ነው ማለት አይደለም። በየትኛውም መንገድ ቢከሰት የጽንፍ የጎሳ ፖለቲካ ኢትዮጵያን ከመበተን ያነሰ ነገር ይዞ አይመጣም። ችግሩን ለመፍታት ግን ቁልፉ አሁንም መንግስት ጋር ነው።መንግስት ሥራውን በትክክል ሲሰራ ሕዝብ በራሱ የጽንፈኝነትን ሰንኮፍ ከውስጡ እንዴት እንደሚነቅል ያውቅበታል።

==============/////=========
No comments:

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል። በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡  ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?  የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመ...