ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, April 10, 2023

በአማራ ክልል ከልዩ ኃይል ጋር በተያያዘ ለተነሳው አለመግባባት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ሆኑ መከላከያ በሰላም ከመነጋገርና ከመተማመን ውጪ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ የማይችሉባቸው ሦስቱ ሕጋዊ ምክንያቶች።


  • የኃይል እርምጃ ፈጽሞ መፍትሄ አይሆንም።
  • የልዩ ኃይል ወደመደበኛ ሰራዊት መግባቱ  ላይ የአማራ ክልል ነዋሪዎችም ሆኑ መንግስት እኩል አንድ ዓይነት ቃላት ነው የሚናገሩት። ልዩነቱ አካሄድ እና ጊዜው አሁን ነው ወይ? የሚለው ላይ ነው።
  • ብልጽግና ከዥዋዥዌ ፖለቲካ መውጣት አለበት።


==========
ጉዳያችን ምጥን
==========

የኃይል እርምጃ ፈጽሞ መፍትሄ አይሆንም።

ሰሞኑን መንግስት በእየክልሉ የሚገኙ የልዩ ኃይሎችን በሦስት መንገድ ወደ መደበኛ የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን መግለጹ ይታወቃል። ይሄውም በልዩ ኃይል ውስጥ የሚገኘው ሰራዊት ከቀረቡለት አማራጮች ውስጥ ወደ መከላከያ መቀላቀል፣ወደ ፌድራል ፖሊስ መግባት፣ወደ ክልሉ ፖሊስ መጋባት ወይንም ሰላማዊ ኑሮ መኖር የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።እነኝህ ጉዳዮች በቅርቡ የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄነራል አበባው እንደገለጹት ቀደም ብለው ሲጠኑ የነበረ እና የታሰበባቸው ነበሩ። የክልል ልዩ ኃይል በመደበኛው የጸጥታ ኃይል መተካት እንዳለበት እና የክልል ልዩ ኃይል የሚባል በህገ መንግስቱ ውስጥ አለመኖሩ መንግስትም በተደጋጋሚ ገልጿል። የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ኢትዮጵያውያን በተለያየ ጊዜ ብዙ ያሉበት ነው። እዚህ ላይ ብዙዎች የማያነሱት ግን በህገመንግስት ውስጥ የሌለ ከሆነ መንግስት በምን ህጋዊ ከለላ እና አንድ ጊዚያዊ ህግ ሳያወጣላቸው ይህንን ያህል ዓመታት ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረጉ እራሱ መንግስትን አያስጠይቀውም ወይ? የህግ አውጪው ፓርላማውስ በእዚህ ጉዳይ ላይ ምን ውሳኔ አሳለፈ? ብሎ የሚጠይቅ የለም። አንዱ ሲመዘዝ ብዙ የሚወጣ ጉዳይ አለ። ለጊዜው ይህንን ጉዳይ እናቆየው እና ወደ ወቅታዊው ጉዳይ እንምጣ።

በአማራ ክልል ከልዩ ኃይል ጋር በተያያዘ ለተነሳው አለመግባባት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ሆኑ መከላከያ በሰላም ከመነጋገርና ከመተማመን ውጪ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ የማይችሉበት ሦስቱ ሕጋዊ  ምክንያቶች።

አሁን በአማራ ክልል ልዩ ኃይል በተመለከተ ለተነሳው አለመግባባት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ሆኑ መከላከያ በጉዳዩ ላይ በሰላም ከመነጋገር ውጭ በኃይል እርምጃ ለመውሰድ የማይችሉበት ሁለት ሕጋዊ ምክንያቶች፣

1) የልዩ ኃይል በተመለከተ በሕጉ የሚመለከታቸው የክልሉ ካቢኔ እና ምክርቤቶች ውሳኔ ለሕዝብ አልተነገረም

የልዩ ኃይል ወደመደበኛ ሰራዊት መግባቱ ለሃገር አንድነት እና ሰላም ጠቃሚ መሆኑ ላይ የአማራ ክልል ነዋሪዎችም ሆኑ መንግስት እኩል አንድ ዓይነት ቃላት ነው የሚናገሩት። ልዩነቱ አካሄድ ላይ ነው።ከአካሄዱ አንዱ ደግሞ የክልል ልዩ ኃይሎችን በበጀትም ሆነ በማናቸውም መንገድ ሲደግፉ የነበሩት ክልሎች ስለ ልዩ ኃይሉ ወደ መደበኛ ሰራዊት መግባት ዙርያ ተሰብስበው ወስነው ሳይሆን እንደሌላው ከብልጽግና ስራ አስፈጻሚ ውሳኔ መስማታቸው ነው ጉዳዩን ያወሳሰበው።ይህ ከፍተኛ አለመተማመን ፈጥሯል።ይህ ሁኔታ በተመሳሳይ በኦሮምያም ሆነ በሌሎች ክልሎች ይሄው ጉዳይ አለ።ካቢኔዎቹ እና የክልሎቹ ምክርቤቶች በክልላቸው ውስጥ ህጉ በሚፈቅደው መልክ መወሰን ይጠበቅባቸዋል። እዚህ ላይ በ''ፕሮሲጀር '' ደረጃ ሂደቱን ማለፉ አስፈላጊ ነው ቢባልም የሃገር መከላከያ ጉዳይ በመሆኑ እና የክልል ልዩ ኃይልም የተመሰረተበት ምንም ህጋዊ መሰረት በሃገሪቱ ህገ መንግስት ውሳጥ እንዳለመኖሩ ግን የክልል ካቢኔም ሆነ ምክርቤት ውሳኔዎቹን የሚቃወምበት ሕጋዊ መሰረት የለውም። ነገር ግን የውሳኔው ሂደት መስመሩን መጠበቁ አስፈላጊ እንደሆነ አያጠራጥርም።በመሆኑም በእዚህ ሁኔታ አሁንም በጉዳዩ ላይ በሰላም ከመምከር እና ሂደቱን በትክክል እንዲያልፍ ከማግባባት ውጭ የኃይል እርምጃ መውሰድ ኢትዮጵያን ወደ የባሰ ዝቅጠት መክተት በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ መከላከያ በጥብቅ ሊያስቡበት ይገባል።

2) መንግስት በዓለማቀፍ ደረጃ የተፈራረመው የፕሪቶርያን ስምምነት በትክክል ለማስፈጸም አለመቻሉ 

መንግስት ከህወሃት ጋር በፕሪቶርያ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት ከተስማማበት ጉዳይ አንዱና ዋነኛው ህወሃት ትጥቅ ይፈታል የሚል ነው። ይህንን ውል ያላስፈጸመ መንግስት እንዴት እና በምን ዋስትና ነው የአማራ ክልል ትጥቅ ይፍታ እኔ ዋስትና እሆንሃለሁ የሚለው? የሚል የሕግ ጥያቄ ቀርቧል።ይህ መሰረታዊ ጥያቄ ነው።በእዚህ አንጻር መንግስት ሁለት ነገሮችን ማስፈጸም አልቻለም። አንድ የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ ተጠቅሞ ትጥቅ አላስፈታም። ሁለት፣ትጥቅ ፈቱ የተባሉ የሕወሃት ታጣቂዎች ቁጥር ቢያንስ በዝርዝር አላስቀመጠም የትኛው ካምፕ ገብተው ተሃድሶ እየተሰጣቸው እንደሆነም የነገረን ነገር የለም።ሌላው ቀርቶ መከላከያ መቀሌ ውስጥ ስንት ካምፕ እንዳለው አይታወቅም። ይህንን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈረመ ፊርማ በትክክል ማስፈጸም ያልቻለ መንግስት በአማራ ክልል ምንም ያህል ትክክለኛ ውሳኔ ቢሆን የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደተለያዩ የመንግስት የጸጥታ ተቋማት ለመበተን የሚያስችል አስተማማኝ የሕግ ማዕቀፍ ይኖረዋል? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው።

የአንድ መንግስት ግልጽነት (transparency) ጉዳይ የሚለካው እንዲህ ባሉ ውሎች እና አፈጻጸሞች ነው። እዚህ ላይ መንግስት በትክክል ድክመቱን መገምገም እና ማረም ያለበት ጉዳይ ነው። ስህተትን በኃይል እርምጃ መሸፈን አያዋጣም።ወደ የባሰ አዘቅት ሃገርንም ህዝብንም ይዞ የሚሄድ አደገኛ መንገድ ነው።

3) መንግስት በኦሮምያ የጽንፍ የብሔር ዘውግ አራማጆች የሃገሪቱን ሕገ መንግስት እንደፈለጉ ሲጥሱ እንደየቤት ልጅ እየተመለከተ፣ በሕጋዊ መንገድ ስሜታቸውን በሰልፍ የገለጹት ላይ መትረጌስ እንዲተኩስ የሚያዝ ሕግ የለም።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የብልጽግና መንግስት የሚኮነንበት አንዱ ጉዳይ የጸጥታ እና የሕግ የማስከበር ድክመት ነው። ይህ ጉዳይ እራሱ መከላከያንም የሚያበሳጨው እንደሆነ በሰሞኑን የጄነራል አበባው መግለጫ መረዳት ይቻላል። ፖለቲካና ጠብመንዣ አብረው አይሄዱም፣ፖለቲከኞች በጸጥታ ጉዳይ ላይ እየገቡ የሚዘባርቁበትን ጉዳይ ጀነራሉ ኮንነዋል። ይህ ማለት መከላከያ እንዲህ ይደረግ ሲል የፖለቲካ ሹፌሩ ብልጽግና የሚሉት ሌላ ነበር ማለት ነው። በተለይ ብልጽግና በኦሮምያ ክልል በሺህ የሚቆጠሩ የአማራ እና የኦሮሞ ተወላጆች ሲፈናቀሉ፣በግፍ ሲገደሉ፣በአዲስ አበባና ዙርያዋ ሺዎች ከመኖርያቸው ሲፈናቀሉ፣እናቶች መንገድ ላይ ሲወድቁ፣የአቶ ሽመልስ የኦሮምያ ክልል አስትዳደር ድንገት ተነስቶ በአዲስ አበባ ዙርያ እንደፈለገ የራሱን የክልል አስተዳደር ሲዘረጋ እና ይህንንም የቦረና እና የጉጂ እንዲሁም የባሌ ኦሮሞዎች አዲስ አበባ ድረስ እየመጡ አቤት ሲሉ ብልጽግና አንድም ሕጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ህገወጦችን በሚያበረታታ መልኩ ሲደግፍ ነበር። በመሆኑም ሕግ ያከበረ መንግስት ይከበራል። ሕግን በእዚህ ደረጃ የጣሰ መንግስት ደግሞ በእራሱ ዙርያ ሕግ ሲጣስ ዝም ብሎ ሌላ አካባቢ ሰልፍ በወጡ ላይ መትረጌስ እንዲተኩስ የሚፈቅድ ሕግ የለም። ስለሆነም አሁንም የቀደመውን ስህተት ማረም መጪውን በጋራ ማስተካከል እንጂ በሆይ ሆይታ በሕጋዊ መስመር የሄዱ ለመምሰል የሚደረገው መሸፋፈን አያዋጣም። እልህ እልህን ይወልዳል።በተለይ ብሶት ያንገበገበው እና የሕግ መጣስ ያበሳጨው ሕዝብ ሕግ እና ሥርዓትን በቦታው በመመለስ እና መተማመን በመፍጠር እንጂ በማስፈራራት የሚመጣ አንዳች መፍትሄ የለም። ሊኖርም አይችልም።

ብልጽግና ከዥዋዥዌ ፖለቲካ መውጣት አለበት።
 
ብልጽግና ከዥዋዥዌ ፖለቲካ ወጥቶ ከበታኝና የጽንፍ የብሔር ዘውግ ድርጅቶች ጋር የሚያደርገውን መሞዳሞድ ካላቆመ ከአማራ ማኅበረሰብ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በደቡብም፣በሱማሌም፣በአፋር፣ በቤኒሻንጉል እና ከኦሮምያም ጭምር በቅርብ ሌላ ዙር ተቃውሞ ይገጥመዋል።ብልጽግን ፖለቲካን የተረዳበት መንገድ በሃገሮች መካከል በሚኖር ጊዜያዊ የጥቅም ግንኙነት መለኪያ ይመስላል። በሃገሮች መካከል ዘለቄታዊ ጥቅም የለም። በሃገር ውስጥ ማኅበረሰብ እና የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ግን ዘላቂ እና ታሪካዊ ወዳጅነት ነው መፈጠር ያለበት። ብልጽግና አንዴ ከአማራ ክልል፣ ሌላ ጊዜ ከኦሮምያ ቀጥሎ ከትግራይ እያለ አንዱን እያገለለ ሌላውን እየተጠጋ የሚያራምደው ፖለቲካ በመጨረሻ ሁሉም የተነጋገሩ ቀን ውሃ ላይ እንደፈረሰ ኩበት ይሆናል። ሃገር እንዲህ አይመራም። ሃገር ግልጽ በሆነ መርህ እና ሕግ ነው የሚመራው። በዓለም ላይ የሚገኙ ሃገሮች ዋስትናቸው ግልጽ እና ለሁሉም እኩል የሚሰር ሕግ እና አፈጻጸም ነው ቆመው እንዲሄዱ ያደረጋቸው። 

ባጠቃላይ ሕጋዊ አሰራር ሳይሰፍን ሕግን በኃይል ማስፈጸም ሃገር ይጎዳል።መንግስት ያልታመነባቸውን ጉዳዮች ላይ ይስራ።በኦሮምያ አጉራ ዘለል የሆኑ አካሄዶች አዲስ አበባ ድረስ እየዘለቀ ህዝብ ሲያውክ ህዝብ እራሱ ተነስቶ ለማስተካከል ከመሞከሩ በፊት መንግስት እራሱን ማረሙ የተሻለ ነው።ባጭሩ ህጋዊ እና መንግስታዊ የሕግ ከለላ ወለጋ ላለችው የአማራ እናትም፣ጎንደር ለሚኖረው ኦሮሞም፣ጅጅጋ ለሚገኘው ጉራጌም እኩል ማስፈጸም የሚችል የሕግ አሰራር እና የሕግ አስፈጻሚ አካል መኖሩ ላይ ማትኮር ቀዳሚ ሥራ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ መንግስት ያልታመነበትን ጉዳዮች ዘርዝሮ ነቅሶ ማውጣትና ይህንንም በመመካከር መፈጸም ከሁሉም በላይ ደግሞ ተአማኒ በሆነ መልኩ ሰፊ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በጣም በጣም ማድረግ ይገባዋል።
============//////=========

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...