ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, April 11, 2023

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከሰላም ውጪ ሌላ የምትሸከምበት ትከሻ የላትም። አሁን በአማራ ክልል ከመከላከያ ጋር የተፈጠረው ግጭት ተከትሎ ለተፈጠረው ችግር ሦስቱ አካላት መንግስት፣መከላከያ፣ልዩ ኃይልና ፋኖ መውሰድ ያለባቸው ፈጣን የመፍትሔ ተግባራት።


  • በዓለማችን ላይ የመፍረስ አደጋ የደረሰባቸው ሀገሮች የችግሩን አነሳስ ብንመለከት የመጀመርያው መጀመርያ በሀገር መከላከያ ላይ የሚተኮስ ተኩስ ነው።
  • መከላከያ አባትም ነው። ምን ቢከፋ፣ምን ቢያስከፋ፣ምን ቢማታ፣ምን ቢያጠፋ እና እየሰከረ ቢያስቸግር አባት ቁጣው በርዶ እስኪያዳምጥ ይጠበቃል እንጂ አባት አይደበደብም።ልጅ አባቱን ከደበደበ ቤቱን አፈረሰ ማለት ነው።

======
ጉዳያችን
======

ጦርነት እና ግጭት እንደውሃ ጠብታ ነው። ግጭቶች ሲጀመሩ በትንሽ እልህ መለዋወጥ በኋላ ይቆማሉ በሚል ዕሳቤ ትናንሽ ግጭቶች አቅልሎ የማየት እና ሃገር የሚያፈርሱ የማይመስሉት ሰው ቁጥሩ ቀላል አይደለም። ነገር ግን በዓለማችን ላይ የመፍረስ አደጋ የደረሰባቸው ሀገሮች የችግሩን አነሳስ ብንመለከት የመጀመርያው መጀመርያ በሀገር መከላከያ ላይ የሚተኮስ ተኩስ ነው።በሶርያም፣ሊብያም ሆነ የመን የሆነው ይሄው ነው። ስለሆነም ምንም ዓይነት ምክንያቶች ቢሰጡ መከላከያ መከላከያ ነው።መከላከያ ሀገር ነው።መከላከያ አባትም ነው። ምን ቢከፋ፣ምን ቢያስከፋ፣ምን ቢማታ፣ምን ቢያጠፋ አባት ቁጣው በርዶ እስኪያዳምጥ ይጠበቃል እንጂ አባት አይደበደብም። አባት እየሰከረ ቢያስቸግር ልጅ ተነስቶ አባቱን አይደበድብም። ልጅ አባቱን ከደበደበ ቤቱን አፈረሰ ማለት ነው።

አሁን በአማራ ክልል ከልዩ ኃይል ጋር ተያይዞ የተነሳው አለመግባባት  ፈጣን ምክንያቱ (immediate cause) የልዩ ኃይል ጉዳይ ይሁን እንጂ ዋና ምክንያቶቹ የብልጽግና ኦሮምያ በኢትዮጵያዊነት ላይ የጋረጠው ስጋት እና አደጋ እና የህዝብ ብሶት ነው። ይህንን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ብልጽግናም ሆነ የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች የአማር ክልል ጉዳይ የልዩ ኃይል ጉዳይ ሳይሆን ከእዚህ ይልቅ ስጋት እና ብሶት የሚሉት ቃላት በሚገባ እንደሚገልጹት መረዳት አለባቸው። ስጋት እና ብሶት ተደምረው በመከላከያ ላይ ያሉ መተማመኖችን የብልጽግና የፖለቲካ አመራር እንዲሸረሸር አድርጎታል።በእዚህ ላይ መተማመን ከተደረሰ ሦስቱ ፈጣን መፍትሔዎች ላይ መንግስት፣መከላከያ እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ፋኖ በጋራ መስራት አለባቸው። መፍትሔዎች በመንግስት፣በመከላከያ እና በአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ፋኖ መከናወን ያለባቸው ናቸው።

1) መንግስት 

በብልጽግና የሚመራው የአሁኑ መንግስት ያለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ስለኢትዮጵያ ብዙ ቢናገርም መሬት ላይ ያሳየው በተለይ ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ ደረጃ በትምሕርት ካሪኩለም፣መገናኛ ብዙኃን ስለ ኢትዮጵያ እንዲናገሩ በማድረግ፣ተቋማትን በኢትዮጵያዊነት ለመቃኘት እና የኢትዮጵያ የሆኑ ቅርሶችን መልሶ ለመስራት (ለምሣሌ የቤተመንግስት ሙዚየም) ጥረቶች ቢያሳይም በሌላ በኩል ደግሞ ከኢሃዴግ አስተዳደር በባሰ ደረጃ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ዕሴቶች ሲጎሳቆሉ የተመለከተ ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛ ጸረ ኢትዮጵያ ሥራዎች በራሱ በብልጽግና መዋቅር ሲሰራ ሰንብቷል። ከእነዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በኢሃዴግ ዘመን ለምሣሌ በኦሮምያ ክልል ይውለበለብ የነበረበትን ያህል አሁን አይውለበለብም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ያዛችሁ ተብለው የኢትዮጵያን እንጀራ በልቶ በሚያድር ፖሊስ ተደብድበዋል፣ታስረዋል ተንገላተዋል። ይህ ኢትዮጵያውያንን ሲያንገበግብ የሚኖር ብቻ ሳይሆን አሁን በአማር ክልል ለተነሳው ዓይነት ህዝባዊ አመጽ እንደሚያስነሳ ግልጽ ነበር። እዚህ ላይ የሰንደቅ ዓላማው ጉዳይ ቀላል የሚመስላቸው አንዳንድ ወገኖች ቢኖሩም የሚያመላክተው መልዕክት እና የኦሮምያ ብልጽግና ሊፈጥራት የሚፈልጋት ኢትዮጵያ ለብዙዎቻችን ግልጽ ያደረገ ቁልፍ ጉዳይ ነው።

ከእዚህ በተጨማሪ ሰዎች በአማራነታቸው እየተለዩ ከወለጋ እና ሌሎች ቦታዎች አዲስ አበባ ዙርያ እና አዲስ አበባ ጨምሮ ሲፈናቀሉ፣ሲገደሉ እና የተለያዩ ግፍ ሲፈጸምባቸው በተለያዩ የኦሮምያ ክልል የብልጽግና ባለስልጣናት ግልጽ ዘርና ታሪክን የሚያንቋሽሽ ንግግሮች ህዝብ አቁስለዋል ብቻ ሳይሆን ብልጽግና እየሄደበት ያለው ግልጽ እና የከረረ የጎሳ ፖለቲካ እንደሆነ የብዙ ህዝብ ድምዳሜ ነው። በመሆኑም መፍትሔው ይህንን ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት።

 መንግስት የሚከተሉትን ፈጣን የመፍትሔ እርምጃዎች መውሰድ አለበት።

1) መንግስት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ከደብረብርሃን እስከ ባሕርዳር እና አዲስ አበባ የተበተኑት ከወለጋ እና ከተለያዩ ቦታዎች የተፈናቀሉ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ መንግስት በቅድምያ በልመና እና በችግር የተበተነው ቤተሰብ በቶሎ ድጋፍ እንዲደረግለት ጥሪ አድርጎ ሰብስቦ ይዞ የሚመለሱበትን መንገድ በቶሎ መጀመር፣ይህንንም የሚከታተለው የአደጋ እና ዝግጁነት ኮሚሽን በየጊዜው ሁኔታውን እያሳወቀ እንዲሰራ ማድረግ።

2) መንግግስት አሁን በአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ፋኖ ጋር በተያያዘ ከአማራ ክልል የሃገር ሽማግሌዎች፣ አማራ ብሔራዊ ንቅናቄና ሌሎች ህዝቡን ይወክላሉ ካላቸው ጋር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደረጃ ቁጭ ብለው መነጋገር እና አንድ ልዩ ኮሚቴ በጋር መስርቶ የመፍትሄ መንገዶች ማፈላለግ። በአማራ ክልል ያለው ህዝብ እንደየቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ህግ የሚያክበር እና መንግስት የሚለው ተቋም ከሕግ ውጭ እስካልሆነበት ድረስ አክብሮ ለመኖር እንግዳ ህዝብ አይደለም። 

ይህንን መሰረታዊ የህዝብ ባህሪ መረዳት ብልህነት ነው።የኢትዮጵያ ህዝብ ከናቁት ይንቃል፣ካከበሩት ያከብራል።ሕግ ጥሶ ሕግ አክብር ከሚለው ይልቅ ሕግ ያከበረ ሲያገኝ መሬት ላይ ይነጠፋል። በእዚህ ጉዳይ የሚታማ ሕዝብ አይደለም። መንግስት ዘሎ በኃይል አስፈጽማለሁ ከማለት በፊት የህዝብን ባህሪ ማወቅ ጠቃሚ ይመስላል። ሁሉም ህዝብ ደግሞ የራሱ ባሕል እና አቀራረብ ዘይቤ አለው። ቤኒሻንጉል የራሱ ባህል አለው። አማራ ጋር ስትሄድ የራሱ ዕሴት የሚለው አለው። ኦሮሞው፣ ትግራይ ሁሉም የራሱ የባህል ዕሴቱ አቀራረቡን ሊቀርጸው ይችላል። ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመተኮስ ይልቅ ወረድ ብለው የህዝቡን ተወካዮች  ማነጋገር አለባቸው።አሁን በሚታየው ሁኔታ ህዝብ ነው በከተሞች እየወጣ ያለው። ይህ ማለት ተወካዮችን ማናገር ህዝብን ማናገር ሲያንስ እንጂ የሚበዛ ጉዳይ አይደለም።

3) መንግስት ከኢህአዴግ የጎሳ የዘውግ ፖለቲካ የተለየ ለመሆኑ ጎሰኛ ፖለቲከኞቹን በሙሉ ከቢሮክራሲው ውስጥ እና ከክልል አስተዳደሮች ውስጥ በቶሎ መንጥሮ ማውጣት እና በትክክል የኢትዮጵያዊነትን ፖለቲካ ያስፍን። ኢትዮጵያ ለገጠማት ችግር ቢያንስ ዛሬ ላይ የመደመር መጽሐፍ በመድረክ ላይ መነገሩ እና መነበቡ ብቻ መፍትሔ አልሆነም። መጪው ትውልድ ሲደርስ አሁን ያለው የጎሳ ፖለቲካ ይቀየራል ብለው ለሚያስቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ እየዘነጉት የመጣው ዛሬ ከወለጋ የተሰደደው ታዳጊ ህጻን፣ዛሬ ዘሩ እየተለይ ከአዲስ አበባ ዙርይ የተፈናቀለው ወጣት ነገ የመደመር ትውልድ እንዴን ሊሆን ይችላል? ይህ ትውልድ እናቱ በዘር ተገፍታ መንገድ ዳር ስታለቅስ እያየ አድጎ መደመር ይቀበላል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። ስለሆነም አሁን ያለው ትውልድ መከላከያ ላይ ድንጋይ ሳይሆን ክላሽ መተኮስ የጀመረው በብልጽግና አካሄድ ተስፋ ስለቆረጠ ነው። አሁንም መንግስት የጎሳ ፖለቲካ ያዋጣኛል ካላለ በቀር በቢሮክራሲው የሰገሰጋቸውን የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች በፍጥነት በተለይ ከኦሮምያ ክልል እና ከፌድራል ክልል ማስወጣት አለበት። የጎሰኝነት ችግሩ በእርግጥ በኦሮምያ ብቻ የሚታይ በሽታ እንዳልሆነ ሳይረሳ ማለት ነው።

መከላከያ ሊወስድ የሚገባው እርምጃ 

መከላከያ ሦስት ተግባራትን በፍጥነት ሊሰራ ይገባል።

1) መከላከያ የኢትዮጵያ የመንግስትም ሆነ የግል ሚድያዎችን በመጠቀም የሕዝብ ግንኙነት እንዲሰራ በተለይ ከሰሞኑ በልዩ ሁኔታ ሊፈቀድለት ይገባል።የግል ቴሌቭዥኖችም የመከላከያን የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች የማስተላለፍ ግዴታ ሊጣልባቸው ይገባል። የሕዝብ ግንኙነት ሥራውን እንዴት እንደሚሰራ ለመከላከያ ተዉለት። እንዴት እንደሚያቀርቡት ብቃት ያለው የሰው ኃይል መከላከያ አለው።

2) መከላከያ አሁን በአማራ ክልል ያለው ግጭት በቀናት ውስጥ እንደረገበ ሀገር አቀፍ መከላከያን የሚደግፍ እና ከመከላከያ ጎን ነኝ የሚል የድጋፍ ሰልፍ በሁሉም ክልሎች ከተሞች እና የገጠር ቦታዎች በምሽት መከላከያ ከገበሬው ጋር በጋራ ችቦ የሚያበራበት ልዩ ሰልፎች ማዘጋጀት እና አሁን ያለውን መንፈስ በፍጥነት መቀየር ይቻላል። ይህ ከጊዜ ጋር መሰራት ያለበት የሚያደርገው ደግሞ በማንኛውም ሰዓት እነኝህ ሥራዎች በፍትነት ሳይሰሩ የውጭ ወረራ አያጋጥምም የሚል የሞኝ ሃሳብ ሊኖር አይገባም። አሁን ያለንበት ዓለም ተለዋዋጭ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ የሚነሱ ግጭቶች ከየት እንደሚነሱ ስለማይታወቅ እያንዳንዱ ኮሽታ ተጠቅመው ጠላቶቻችን አይጠቀሙበትም ማለት አይቻልም።

3) መከላከያ የኢትዮጵያን አጠቃላይ ጸጥታ በተመለከት የራሱን ''ሮድ ማፕ '' አዘጋጅቶ ያቅርብ በእዚህ መሰረት አፈጻጸሙን ህዝብ አሳትፎ እንዴት እንደሚፈጽም ከላይ በተሰጠው የመንግስት እና የግል ሚድያዎች ተጠቅሞ ይከውን። እዚህ ላይ መከላከያ በሳምን ሁለት ሳምንት የራሱ የጸጥታ ጉዳይን በተመለከተ የሚያቀርብበት የግማሽ ሰዓት የቴሌቭዥን እና ራድዮ መርሐግብር ሊኖረው ይችላል። አሁን ያለው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ማቅረብ ያለበትን በቀጥታ ከመከላከያ ወስዶ ሊያቅርብ ይችላል። እዚህ ላይ መከላከያ ለብቻው ተነጥሎ የእዚህ ያህል በጸጥታ ጉዳይ የሚያቀርብ ከሆነ የመንግስት ሚና ምንድነው? የሚል ጥያቄ ሊኖር ይችላል። ነገር ግን አሁን በኢትዮጵያ ካለው ሁኔታ አንጻር የጸጥታው ጉዳይ እስኪረጋገጥ ድረስ ለአንድ ዓመት ወይንም ለስድስት ወራት ይህ አካሄድ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ወቅታዊ ህመም የሚያክም ነው።

በልዩ ኃይሎች እና በአማራ ፋኖ አንጻር መወሰድ ያለበት የመፍትሔ እርምጃ 

1) በሁሉም ክልሎች ያሉ ልዩ ኃይሎች አመራሮች እና የታች መኮንኖች ጭምር ቢያንስ ለሳምንታት ያህል አብረው በአንድ የመዝናኛ ወይንም ቀንና ሌሊት አብረው የሚቆዩበት እና መደበኛ ያልሆነ የግንኙነት እና የመወያያ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። በማኅበራዊ ሚድያ እርስ በርስ እንዲፈራሩ የተደረገው ሥራ መፍረስ አለበት። ይህንን የጋራ ጊዜ ለምሳሌ መከላከያ ሚኒስቴር በሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ወይንም ሌላ ምቹ ቦታ ወስዶ ማወያያት እና አብረው የጋራ ጊዜ እንዲያሳልፉ ማድረግ ይገባል።

2) ልዩ ኃይሎችም ሆኑ የአማራ ፋኖ መከላከያ የማይገሰስ ሀገራዊ የጋራ ኃይል መሆኑን በውድም በግድም የመቀበል ስነልቦና ማዳበር አለበት። ልዩ ኃይልም ሆነ ፋኖ የኢትዮጵያ መከላከያ ሳይሆኑ ድጋፍ ሰጪ ናቸው።

3) ልዩ ኃይል ወደ መከላከያ፣ፌድራል ፖሊስ፣ክልል ፖሊስ ወይንም ሰላማዊ ሕይወት መግባት ዛሬ ባይሆን ነገ፣ነገ ባይሆን ከነገ ወዲያ የማይቀር ነው።ይህንን ዝርዝር አሰራር ከላይ መንግስት መስራት ከሚገባው ሥራዎች ስር በተጠቀሰው መሰረት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሲነጋገሩ ዝርዝር ጉዳይ ላይ መነጋገር የሚከወን እንዲሆን መስራት።
በፋኖ አንጻር ግን በአማራ ክልል ፋኖ ማኅበራዊ እውቅና በክልል ደረጃ እንዲያገኙ መጠየቅ እና የአማራ ክልልም ማኅበራዊ ዕውቅና የሚሰጥበት አንድ ዓይነት መንገድ መፈለግ እና ቢያንስ የያዙት ትጥቅ ከማኅበራዊ ዕውቅና ጋር ሃላፊነት በተሰማ መልኩ ከግዴታ እና ውል ጋር እንዲፈቀድላቸው ቢደረግ ምንም ዓይነት ጉዳይ ለኢትዮጵያ ጸጥታ የሚያመጣው ችግር አይኖርም። ፋኖ ቢያንስ ኢትዮጵያ ቀውጢ በሆነችበት ጊዜ ህይወቱን ለመስጠት የቆመ ብቻ ሳይሆን ወደፊት እራሱ ባሕሉን ጠብቆ መኖር ኢትዮጵያን ከውጭ ጠላት ጭምር ለሚመጣ ጠላት መከላከያን የሚያግዝ ባሕላዊ ዕሴት በመሆኑ መጠበቅ ያለበት መሆኑን መንግስትንም፣መከላከያና የኢትዮጵያን ሕዝብ በፍቅር የማሳመን ሥራ በሁሉም ክልሎች ለመከወን መነሳት አለበት። አሁን ፋኖ ለሌላው ክልል የሚያስፈራ ተደርጎ እንዲቀርብ የተሳለው ስዕል ለአማራ ክልል ብቻ ጀግና መሆኑ ታውቆ እንዲቀር ባልሆነ ነበር። ችግሩ ያለው የምንመርጠው መንገድ አጠቃቀማችን ነው እንጂ ሁሉም የሚግባባት የጋራ መንገድ ከተፈለገ በርካታ መንገድ አለ።

ለማጠቃላል ኢትዮጵያ ከሰላም ሌላ መሸከም የምትችለው ሌላ ምንም ዓይነት ነገር የለም።አሁን ያለው ውጥረት በቶሎ መስተካክለ ይችላል። ጉዳዩ በማባባስ ሌላ ዙር ንትርክ ውስጥ ኢትዮጵያ በመግባቷ የተሻለ መንገድ ላይ ትገባለች ብለው የሚያስቡ ምን ያህል እንደተሳሳቱ የሚገባቸው ኢትዮጵያ በውስጧ እና በውጭ ያሉ ጠላቶቿ አሰላለፍ ማየት ያልቻሉ ናቸው። ከሰላም የአሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይሆን መጪው ትውልድም ይጠቀማል። መንግስት ተሳስቷል፣አዎን ተሳስቷል። እንዲስተካከል መንግስትን በሰላማዊ መንገድ የማስገደድ ሥራ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው። መከላከያን ተገዳድሮ የሚመጣ ለውጥ መጀመርያ በር ከፍቶ ብር የመቁጠር ያህል ነው። በሩን ከፍቶ ብር የሚቆጥር ሰው ሌባ ያልሆነ አላፊ አግዳሚም ይዘርፈዋል። የኢትዮጵያን ሰላም በማደፍረስ ኢትዮጵያ ወደየባሰ አዘቅት የማትገባ ብቻ ሳይሆን እንደእነ ሶርያ የማንሆን እንዳመስለንና እንዳንሳሳት። የሰላም አስፈላጊነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የስልጣን ዕድሜ አይደለም። ለኢትዮጵያ እና ለሁላችንም የጋራ ደህንነት ሰላምን በማደፍረስ ኢትዮጵያን ማንም እንደማይጠቅማት ማወቅ አለብን። ከላይ የተጠቀሱት በመንግስት፣በመከላከያ እና በልዩ ኃይሎች እና ፋኖ መሰራት ያለባቸው ሥራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ መስራት እጅግ እጅግ አስፈላጊ ነው። ዓለማችን ካለችበት ተለዋዋጭ ጊዜ አንጻር ከሁለት ሳምንት በኋላ የሚሆነው አካባቢያዊና ዓለማቀፋዊ ሁኔታ ስለማይታወቅ ሁሉ ሥራ ከጊዜ ጋር ተሻምቶ መስተካከል ነው ያለበት።
==================////===========

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...