ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, April 20, 2023

በህወሓት አፍቃሪዎችና መዋቅር የሚዘወረው የአማራ እና የኦሮሞ ብሔርተኝነትና በ''ሪሞት'' እየዘወራቸው እንደሆነ የሚያውቁም፣ የማያውቁም በአንድ ጎዳና የመንጎድ ተውኔት።=========
ጉዳያችን ምጥን
=========

የብሔርተኝነት አንዱ ገጽታ ከራሱ ብሔር ውስጥ የሚቃወሙትን ለመቀንጠስ ይሉኝታ የማይዘው ብቻ ሳይሆን ለማግለልም ሲውተረተር የሚገኝ ነው።''በሮማዊነት ከሆነ ከእኔ በላይ ሮማዊ'' አይደላችሁም እንዲል፣ዛሬ ደርሰው ፖለቲካ ሁሉ የአማራ ብሔርተኝነት፣ወይንም የኦሮሞ ትግል የሚል ትርክት በማውራት አድርገው የሚመለከቱ፣ ነገር ግን ማን ለምን ዓላማ እየነዳኝ ነው ብለው ማሰብ የማይችሉ ከዩቱብ ሚድያ እስከ መስጊድ እና አብያተ ክርስቲያናት ጭምር እነርሱ በጠፋባቸው የፖለቲካ ምህዋር ሌላውም እንዲገባ ሲደክሙ ይታያሉ።

ህወሓት በወታደራዊ መስክ ቢሸነፍም ሰንኮፍ የመከፋፈል እና በጥቅም የመግዛት ልምዱም ሆነ አቅሙ አሁንም ባለው መዋቅር እየሰራበት ነው። በህወሓት በኩል ያለው አዲሱ ክስተት ከወታደራዊ ሽንፈቱ በላይ የትግራይ ተወላጆች በብዙ መዋቅሩ እርግፍ አድርገው የተዉት እና በሰላም ለመኖር የሚፈልጉት ከቀደመው በበለጠ መበራከታቸው መዋቅሩ ከመንገዳገድ አልፎ የሚያርፍበት ማረፍያ ቅርንጫፍ እያጣ በማኅበራዊ መዋቅሮች ውስጥ ብቻ ለመሰግሰግ እየጣረ መሆኑ ነው።

በእዚህ ዘመን ማንም ማንንም አያታልለውም። በአማራ ብሔርተኝነት መዋቅር በማደራጀት ህወሓትን የማይነቅፉ ነገር ግን ዐቢይን እና መንግስትን (በሰሞኑ ክስተቶች ተጠቅሞ አሁን ወደ መከላከያም ተመንድጓል) የማጥላላት የፖለቲካ አጀንዳ የተሰጣቸው የህወሃት የቀድሞ አፍቃሪዎች ብቻ ሳይሆኑ በህወሃት የውጭ መዋቅር ውስጥ በስደተኛው መካከል ተሰግስገው ማኅበራዊ ሰላም ሲነሱ የነበሩ፣ዛሬ ተነስተው የአማራ ብሔርተኝነት አደራጅ እና ያዙኝ ልቀቁኝ ባዮች ሆኖ ማየት ያስደምማል። የሚገርመው የዋሁ እና ከእዚህ በፊት ፖለቲካ አይሽተተኝ የሚለው፣ውሎ እና አዳሩ መስጊድና አብያተክርስቲያናት የሆነ ሁሉ የህወሃት መዋቅሮች ቀድመው በቀረቡት በእዚሁ የማኅበራዊ መረብ ተለሳልሰው እየቀረቡ በብሔሩ ካልተደራጀ እና ሌላውን ካልራቀ በቀር አደጋ ላይ ነህ፣መጥፋትህ ነው፣ወዘተ በሚል የማስደንበርያ መንገድ በስራቸው እየኮለኮሉት ነው።

በመጀመርያ ደረጃ ይህ በመስጊድ እና አብያተክርስቲያናት የነበረ አካል ስለ ፖለቲካ በህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን አልሰማም፣አላይም እኔ ስለሰማያዊ ህይወት ብቻ ነው የማውቀው ሲል ስለነበር፣ የሴራ ፖለቲከኞች አደረጃጀት እና እራሱ ህወሃት እንዴት ከርቀት ሆኖ በ''ሪሞት'' እንደሚነዳ አያውቅም። ስለሆነም በቅርቡ የሚያውቀው ጥሩ ያለው ሰው በዘረጋለት የጎሳ የአደረጃጀት መረብ ውስጥ ሆኖ ፖለቲከኝ እንደሆነ እየተነገረው እራሱን በራሱ እንዲያዝናና ይደረጋል። እዚህ ላይ የጥቅምም ጉዳይ ስለሚጨመርበት አንዳንዴ ይህ የጎሳ መዋቅር የህወሃት መሆኑ ቢሸተውም እንዳላወቀ እራሱን በመደለል የመውቅሩ ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ፣ህወሃትበኢትዮጵያ ላይ የዘራውን የጎሳ ፖለቲካ እንደ የተሻለ አድርጎ ለመስበክ ደፋር ምላስ ሊኖረው ሁሉ ይችላል።

ቀልዱ በእዚህ አያበቃም።በአማራ ብሔርተኝነት በኩል የተደራጀው ቡድን ያህል ደግሞ በኦሮሞ ብሔርተኝነት የተደራጀው አቀጣጣይ እና ከዋናው የብልጽግና አክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኛ ቢሮክራሲ እና የጸጥታ አካል ጋር የሚናበበው ቡድን ደግሞ ከህወሓት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እየሰራ ያለ ነው።ይህ ቡድን በህወሃት ስር ሙሉ በሙሉ በገንዘብም በመዋቅር ድጋፍም የሚንቀሳቀስ የመኖሩን ያህል ከህወሃት ውጭ የሆነ በጋራ ግንኙነት ብቻ ህወሓትን የሚያገኝ አክራሪ እና ፍጹም የጥፋት ኃይልም በውስጡ ይዟል። በህወሓት ስር የሚንቀሳቀሰው ኦሮምኛ ተናጋሪ አንዳንድ የትግራይ ተወላጆችን ይዞ እና በኦሮምያ ያደጉ የአማራም ሆነ የኦሮሞ ተወላጆችን ያቀፈ ነው። የእዚህ ቡድን ተልዕኮ በአማራ ብሔርተኝነት ላይ የማጥላላት ሥራ ከመስራት ባለፈ የኦሮሞ ተወላጆችን የሚያስደነብሩ ሃሳቦች እያፈለቀ የህዝቦች ግንኙነት እንዲሻክር ከማኅበራዊ ሚድያ እስከ ታች ጠላ ቤት የሚሰራ መዋቅር ነው።እነኝህ ሁለት ቡድኖች እራሳቸውን አንዳንዴ ኦነግ ሸኔ በማድረግ ሌላ ጊዜ የብልጽግና የኦሮሞ ወኪል በመሆን የሚያተራምሱ ናቸው። አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ ከኦነግሸኔ እና የብልጽግና ውስጥ ከተሰገሰገው ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኛ ከሚያገኙት ሙገሳ ባለፈ፣አልፎ አልፎ በህወሃት ከሚዘወረው የአማራ ብሔርተኛ እንቅስቃሴ ቀንደኛ መሪዎች ጋር የሁሉም ቡድን አባላት ባላወቁት መስመር እየተገናኙ አንዱ ለአንዱ ቤንዚን የሚያርከፈክፉበትን መንገድ በገደምዳሜ እየተናበቡ ይሰራሉ።

ይህንን አጭር ምጥን ለማጠቃለል፣ የአማራም ሆነ የኦሮሞ ብሔርተኝነት እንዲያቀጣጥሉ የሚዘወሩ ቡድኖች ከባሕር ማዶ እስከ ሃገር ቤት እንዳሉ እና የወቅቱ አንዱ የችግራችን ምክንያቶች እንደሆኑ በማሳሰብ ነው።በውጭ ሃገር በተለይ የህወሓት ስውር መዋቅር ውስጥ የነበሩ ዛሬ ''እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው '' አማራ ሁሉ በኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በብሔርተኝነት ተደራጅቶ መጀመርያ ዐብይና መንግስትን እና መከላከያን እንዲያጥላላ፣ህወሓትን እና ኦነግ ሸኔን ግን አልፎ አልፎ ለኮፍ አድርጎ እያለፈ እንዲሄድ የቤት ሥራ ተሰጥቷቸው እየከወኑት ነው። እስኪ ኦነግ ሸኔን የሚቃወሙበትን ድምጸት ልክ ዛሬ ዛሬ መከላከያን የሚነቅፉበትን ድምጽ ለኩበት።

ነገሩ ''ለማያውቅሽ ታጠኚ '' ነው። ዛሬ ማንንም ማታለል አይቻልም።የዋሆች ገራገር በመሰሏቸው እና በማኅበራዊ ሚድያም ሆነ በእምነት ዙርያ የሚያውቋቸው የህወሓት መዋቅር አስተባባሪ መሆናቸውን ያላወቁ በማያውቁት የብሔር መዋቅር እየተነዱ ነው።  በሴል መደራጀት፣ፖለቲካ በዙም ማውራት፣ተልዕኮ መቀበል ወዘተ ብርቃቸው ስለሆነ የሆነ ትልቅ ሥራ ለሃገር እየሰሩ እንደሆነ እንዲያስቡ ሲጣደፉ ያሳዝናሉ። የጉዳያችን ምክር አንድ እና አንድ ነው።ፖለቲካው የረቀቀበትን ደረጃ ካልገባን በደንብ ማን፣ምን እያለ ነው? ለምን? ብሎ ከመጠየቅ አንስቶ ዋና ማገናዘቢያችን (reference) መሆን የሚገባው ኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያዊነት ብቻ መሆኑን መረዳት ብልሕነት ነው። ሕሊናም፣ታሪክም፣ፈጣሪም የማያዝኑበት እና ካለው ሰውነት የማያወርደን ሁሉንም ጉዳይ ከኢትዮጵያዊነት አንጻር አይተን ስንሰራ ብቻ እና ብቻ ነው።ከእዚህ ውጪ አዎን! ስሜት የሚያቆስሉ የጽንፈኞች ድርጊት ከመንግስት መዋቅር ጀምሮ እስከ የተለያዩ ቡድኖች በተለይ አማራን ለይቶ የማጥቃት ሂደቶች የሉም ማለት አይደለም። ይህ ጥቃት ግን ዋና የጀርባ ግቡ ኢትዮጵያን የማጥቃት ግብ መሆኑን ላወቀ ሰው፣ነገ ለደቡቡ፣ለሱማሌው፣ለአፋሩና ለሌላውም የማይቀር መሆኑን ተረድቶ ለሙሉዋ ኢትዮጵያ በመቆም መፍትሄ ላይ መድረስ ይቻላል። ልጆቹና ሚስቱ እንዳይጠቁበት የፈለገ አስተዋይ አባወራ የግቢውን በር ብቻ በመጠበቅ እንደማያድን ያውቃል።ከእዚህ ይልቅ የመንደሩን ሰዎች በህብረት አስተባብሮ እንደሃገር የመጣውን ፈተና በመቋቋም መንደሩንም፣ግቢውንም፣ቤቱንም ሆነ ቤተሰቡን አብሮ ይጠብቃል። ተነጣጥለህ በጎሳ ፖለቲካ እንድትነከር የሚፈልጉ ሁሉ ነጣጥለው ሊበሉህ እና ሊያስበሉህ የሚፈልጉ መሆናቸውን ማወቅ እና እውቀትንም፣ጊዜንም ሆነ ሃብትን ከመባከን በጊዜ ማዳን ተገቢ ነው።
===============//////==========


No comments:

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል። በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡  ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?  የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመ...