ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, April 20, 2024

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።


በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል
ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ

  • ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል 
  • ''ስኩዌር ዋን'' ህወሓት ወደ ቀደመ ፕሮፓጋንዳውና የጦርነት ገንዘብ ማሰባሰቡ ተመልሷል።
  • ህወሓት ለአራተኛ ጊዜ ''አደገኛ ወጥ እረግጧል'' 

========
ጉዳያችን
========

''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል 

ከተፈረመ ዓመት ያለፈው የፕሪቶርያ ውል ህወሓት እንደፈለገ እየተረጎመ እና እያብጠለጠለ፣ መንግስት አንድ ጊዜ የህወሓትን ትጥቅ አስፈታሁ፣ዛሬ ይህን ያህል ከባድ መሳርያ ተረከብኩ እያለ በቴሌቭዥን እያሳየ፣ ቆየት ብሎ ደግሞ ህወሓት ትጥቅ አልፈታሁም እያለ ሲደነፋ ስንሰማ ውሉ ዓመት አልፎት ሌላ  ዓመቱን ተያይዞታል።

ባለፈው ዓመት ውስጥ ህወሓት በሚልዮን የሚቆጠር የትግራይ ሕዝብ አስፈጅቶ፣ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ኮሚሽን ባወጣው አዲስ ጥናት ደግሞ ከአንድ ሚልዮን በላይ የትግራይ ተወላጅ ልጆች በእዚች ሰዓትም ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው ታውቋል። ይህ በእንዲህ እያለ ከፕሪቶርያው ውል ወዲህ የትግራይ ክልል በቢልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከማዕከላዊ መንግስት ማግኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የትግራይ ተወላጆችን በቢሯቸው አዳራሽ ሲያነጋግሩ ሲነግሩን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ከጎናቸው አስቀምጠው ምስክር ይዘው ነበር። ይህ ገንዘብ ግን ለትግራይ ህዝብ አንድ ሚልዮን ልጆቹን ወደ ትምሕርት ቤት ለመስደድም ሆነ ከደረሰበት ጉስቁልና ለማገገም አልረዳውም። ይልቁንም ህወሓት ከህዝቡ ጉሮሮ የነጠቀውን ምግብ ለትታጣቂው እያበላ ሰሜን ወሎን መወረሩን የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ መገናኛዎች ከነገሩን ቀናት ተቆጠሩ።

እንደ ቢቢሲ አማርኛ የዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 12፣2016 ዓም (እኤአ ሚያዝያ 20፣2024 ዓም) ዘገባ  በወረራው ሳብያ አስር ሺዎች ተፈናቅለዋል። ዘገባው እንዲህ ይነበባል ፡ 

''ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ከትግራይ ኃይሎች በተደረጉ የተኩስ ልውውጦች አለመረጋጋት ውስጥ የገቡት ስድስቱ የራያ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደሮች፤ በአማራ ክልል መንግሥት ስር በተመሠረቱላቸው መዋቅሮች ስር መተዳደር ማቆማቸውን አራት የወረዳዎቹ አመራሮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የትግራይ ኃይሎች በተለይም የገጠር ቀበሌዎችን መቆጣጠራቸውን የዛታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሳሁን መኮንን እና የወፍላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍሰሐ ሞላ ገልፀዋል። ይህንን ተከትሎም የሁለቱ ወረዳዎች አመራሮች እና ነዋሪዎች ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ ወደ አጎራባች አካባቢዎች መሸሻቸውን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት የኮረም እና አላማጣ ከተማዎች ነዋሪዎች በሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙት ቆቦ እና ወልዲያ ከተሞች እንዲሁም ሰቆጣ ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስር በሚገኙት ሰቆጣ ከተማ እና ሐሙሲት ቀበሌ መጠለላቸውን ገልጸዋል።

ተፈናቃዮቹ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከእነዚህ አካባቢዎች መጠለላቸውን ተናግረው፤ የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ በበኩላቸው 30 ሺህ ገደማ የራያ አካባቢ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አስረድተዋል።'' የቢቢሲ ዘገባ መጨረሻ።

''ስኩዌር ዋን'' ህወሓት ወደ ቀደመ ፕሮፓጋንዳውና የጦርነት ገንዘብ ማሰባሰቡ ተመልሷል።

የህወሓትን ወረራ አስመልክቶ የውጭ ሚድያዎች በለሆሳስ እየተናገሩ ነው።በለሆሳስ ያልኩበት ምክንያት የህወሓት ውል ጥሶ ብቻ ሳይሆን ከአንድሚልዮን ህዝብ እልቂት በኋላም መልሶ ለስልጣኑ ወደ ጦርነት አረንቋ ለመግባት የሚያደርገውን መላላጥ ለመውቀስ ሲሽኮረመሙ ብቻ ሳይሆን በሚገባ እና በሚወቅስ መልክ የጻፈ አላጋጠመኝም። ይህ የደንባራው እና የራሱን ጥቅም ብቻ ከሚያነፈንፈው የባዕዳን የሚድያ ፖሊሲ የሚመነጭ ምግባር የለሽ የአለቆቻቸውን አስተያየት እና አቅጣጫ ከመጠበቅ የመጣ እንጂ የህወሓት ድርጊት እጅግ ግዙፍ እና ሌላ ወንጀል በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመበት ተግባር መሆኑ ጠፍቷቸው አይደለም። 

ባትሰባ ሰይፉ የኒውዮርክ ዩንቨርስቲ የሕዝብ አስተዳደር ማስተርስ ተመራቂ ነች። ዛሬ ''ሞደርን ዲፕሎማሲ ዶት ኢዩ''ላይ  የፕሪቶርያ ውል መክሸፍን በገለጸችበት ጽሑፍ ጉዳዩ የሕገመንግስታዊ ቀውስ መሆኑን፣ትግራይ በቂ እርዳታ በመንግስት ቢሮክራሲ አለማግኘቷንና ሌላው ቀርቶ በህወሓት በራሱ የተዘረፈውን የዕርዳታ እህል ህወሓትን ለመውቀስ ወደ ሌላ በመቀሰር ለማብራራት ሞክራለች። ባትሰባ ሰይፉ በእዚሁ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በጻፈችው እና ''The Fractured Reality After the Pretoria Peace Agreement'' የሚል ርዕስ የሰጠችው ጽሑፍ ውስጥ የፕሪቶርያው ውል ሦስት ምሰሶዎች እንደነበሩት ታብራራለች። እነርሱም ፡ የሰብዓዊ ርዳታ ተደራሽነት፣ሕገመንግስታዊ ስርዓት ማስከበር እና ሰብዓዊ መብት የሚሉ ሲሆኑ የህገመንግስታዊ ስርዓትን እንደ እርሷ አገላለጽ ''የአማራ ክልል ኃይሎች እና የኤርትራ ወረራ'' የፕሪቶርያን ውል ዋጋ እንዳሳጣው ለማሳየት በእዚሁ ጽሑፏ የውጪውን ዓለም ለማታለል ተጠቅማበታለች። በእዚህ ሁሉ ገለጻ ውስጥ ግን ህወሓት ሰሜን ወሎን ውርሮ በአስር ሺዎች ማፈናቀሉን፣ ትጥቅ እፈታለሁ ብሎ ዛሬም ክላሽ እየወዘወዙ የአማራ ክልልን የሚወሩ በሺህ የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ለፕሪቶርያ ውል መፍረስ ምክንያት እንደሆነ ማብራራ አልሞከረችም። 

ይህ ጽሑፍ የሕወሃት ፕሮፓጋንዳ ማሽን መልሶ ዓለምን ለማታለል ለመጋጋጥ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት መጀመሩን ያሳያል። በሌላ በኩል በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ ህወሓት የዲያስፖራ ክንፉ ገንዘብ እንዲያዋጣ መጎትጎት ይዟል። ለምሳሌ በጣልያን የሚኖሩ የዲያስፖራ ክንፉ ገንዘብ የሚያዋጡበትን መርሐግብር ቀርጾ በፖስተር ማሰራጨት ጀምሯል።ዛሬ በወጡ ዘገባዎች ደግሞ ህወሓት በሰሜን ወሎ የገጠር ወረዳዎች ግልጽ ዘረፋ ላይ እንደተሰማራ ከስፍራው በቀጥታ የሚመጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ህወሓት ለአራተኛ ጊዜ ''አደገኛ ወጥ እረግጧል'' 

ህወሓት ለአራተኛ ጊዜ ''አደገኛ ወጥ እረግጧል''። የአሁኑ አረጋገጥ ካለፈው ተሞክሮ ተምሮ በተለየ ስልት እንደሚሆን መገመት ቀላል ነው። አቶ ጌታቸው ረዳ አዲስ አበባ ሆኖ ስለ ሰላም እያወራ፣ ታደሰ ወረደ ከትግራይ ሆኖ ከመንግስት ጋር ተነጋግረን ነው እያለ የሚያምታቱበት አዲስ ታክቲክ ይዘው መምጣታቸውን ሕጻን ልጅም ይረዳዋል። በህወሓት ውስጥ የሰላም ፈላጊና የጦርነት ናፋቂ ሁለት አንጃ ካለ አንዱ አንዱን አስሮ ያሳየን እና እንመነው። ከእዚህ ውጪ ''በዕቃ ዕቃ ጨዋታ'' የኢትዮጵያን ሕዝብ ዳግም ማደናገር አይቻልም። የትግራይ ሕዝብ በሚልዮን የሚቆጠር ልጆቹን ቀብሮ ዛሬም ህወሓት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሲያጋጨው ተቅምጦ የሚመለከተው ከሆነ ሌላ አደገኛ የታሪክ ስብራት ምናልባትም ክልሉ የሚበተንበት አደጋ ውስጥ እንደሚገባ መረዳት አለበት። በእዚሁ በጉዳያችን ላይ ለዓመታት በህወሓት አመራር በትግራይ ይደርሳል ህዝብ መቃወም አለበት እያልን ስንጮህ የሰማ አልነበረም።ዛሪ የትግራይ ህዝብ የደረሰበትም ሆነ የሆነው ግን ያኔ የተናገርነው ነው።ዛሬ የሚነገረውም ሰሚ ካላገኘ ነገ በህዝቡ ላይ የበለጠ መከራ ህወሓት ይዞ እንደሚመጣ ለማወቅ ነቢይ መሆን አይጠይቅም።

በመጨረሻው መጨረሻ ግን ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።ህወሓት ትጥቅ መፍታት አለበት። ይህ የፕሪቶርያው ውል አካል ካልሆነ ይነገርን።አልያም የፕሪቶርያውን ውል ህወሓት እንዳፈረሰ የመንግስት የፖለቲካውም ሆነ የወታደራዊው አመራር በግልጽ ይንገረን።

==================///=============



 






በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...