ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, March 27, 2018

ዶ/ር አብይ አህመድ የኢትዮጵያን መጪ ነባራዊ የፖለቲካ ሂደት ለመቀየር ሊያስቀድሟቸው የሚገቡ አስር ተግባሮች


ዶ/ር አብይ አህመድ 

ጉዳያችን/ Gudayachn
 መጋቢት 19/2010 ዓም (ማርች 28/ 2019)

ዶ/ር አብይ አህመድ ከቀናት የኢህአዴግ ስብሰባ በኃላ የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸውን የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በሁለት ሰዓቱ የዜና እወጃ ላይ ይናገራል ተብሎ ሲጠበቅ ምንም ሳይናገር ማለፉ የመጋቢት 18/2010 ዓም ግርምታ በሕዝቡ ዘንድ ፈጥሮ አመሸ።በእርግጥ ቀደም ብሎ ከቀኑ አስር ሰዓት ጀምሮ የተመረጡ ጋዜጠኞች ተጠርተው መግለጫ እየተጠባበቁ መሆናቸውን እና ኢህአዴግ በስብሰባው ላይ የአቶ ኃይለማርያምን መልቀቅያ መቀበሉን ሸገር በአስራ ሁለት ሰዓት ዜና ላይ በቀዳሚነት አሰምቶ ነበር።ከእዚህ ሁሉ በኃላ ግን ከሁለት ሰዓቱ ዜና በኃላ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በሰበር ዜናነት ዶ/ር አብይ የድርጅቱ ሊቀመንበር መሆናቸውን አስደመጠ። ዶ/ር አብይ በ108 ድምፅ፣ አቶ ሽፈራው በ59 ድምፅ እና ዶ/ር ደብረ ፅዮን በሁለት ድምፅ ብቻ መመረጣቸው ተከትሎ በማኅበራዊ ሚድያ ጭምር ተገለጠ።

ዶ/ር አብይ አህመድ የኢትዮጵያን ነባራዊ ፖለቲካ ሁኔታ መቀየር ይችላሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ጥያቄ ነው።ከእዚህ በፊት ግን መሬት ላይ ያለውን እውነታ ዶ/ር አብይ ወደ ሊቀመንበርነቱ የመጡት በህወሓት በጎ ፈቃድ አለመሆኑ ነው።ህወሓት ለደጋፊዎቹ አቶ ሃይለማርያም የመጨረሻ ከህወሓት ውጭ የሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ እየማለ እና እየዛተ ደጋግሞ ተናግሮ ነበር።ለእዚህም ነበር ዶ/ር ደብረ ፅዮን የህወሓት ሊቀመንበር እንዲሆኑ የፈለገው እና ወደፊት ያመጣበት አንዱ ዓላማም ይሄው ነበር።ሆኖም ግን ይህ ሁሉ ጥረት በህዝባዊ አመፁ ከጥቅም ውጭ ሆኗል።ዶ/ር አብይ አህመድ የድርጅቱ ሊቀመንበር መሆናቸውን ዘግይቶም ቢሆን ለመግለጥ ተገዷል።

ዶ/ር አብይ ነባራዊውን የፖለቲካ ሁኔታ ለመቀየር ይችላሉ? ለሚለው ጥያቄ ዶ/ር አብይ የመቀየር እና ያለመቀየር እድላቸው የሚወሰነው በሚመርጡት የትኩረት አቅጣጫ የሚወሰን ይሆናል።ኢትዮጵያ በህወሓት ለለውጥ አለመዘጋጀት ምክንያት አሁን ያለችበት ሁኔታ ወደ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ልትገባ ጫፍ ላይ ያለችበት ወቅት ነው። በኃይል የሚመጣ የለውጥ ሂደት ይዞት የሚመጣው የስልጣን መመንጨቅ ተከትሎ የሚመጣው የደም መፍሰስ እና የሚፈጥረው መቃቃር፣ምጣኔ ሃብታዊ ድቀት እና ቀውስ ሁሉ በአደጋ ያልተከበበ ነው ማለት አይቻልም።በእዚህ ላይ የጎሳ ፖለቲካው እንደ ነዳጅ ሀገር  እንዲያቀጣጥል  እየተርከፈከፈ ነው።የጎሳ ፖለቲካ በምጣኔ ሀብት በተቃወሰ እና የሀብት ክፍፍል አድሏዊ በሆነበት ማህበረሰብ ውስጥ ደግሞ ትልቅ ቀውስ እንደሚከተለው ማወቅ ተገቢ ነው። ስለሆነም ዶ/ር አብይ የህዝብ ድጋፍን ተንተርሰው ሊያተኩሩበት የሚገባው በሚከተሉት ስልታዊ  ነጥቦች ላይ ነው።እነኝህ ስልታዊ ነጥቦች በእራሳቸው የጎሳ ፖለቲካውን ሕዝባዊ መሰረት የማሳጣት ተልኮ የያዘ ይሆናል። እነርሱም : -

1ኛ) በጎሳ ፖለቲካ የተጎሳቆለውን ማኅበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነት ወደ ሃገራዊ የጋራ ደረጃ ማድረስ። ይህንንም የፖለቲካ ድርጅቶች ከጎሳ ፖለቲካ ወደ ሃገራዊ አጀንዳ እና አደረጃጀት እንዲቀየሩ ሁኔታውችን ማመቻቸት።ሀገር አቀፍ የሙያ ማኅበራት፣የሰራተኛ ማህበራት እና የዩንቨርስቲ እና ኮሌጅ ተማሪዎች ህብረቶች ሁሉ ከጎሳዊ አደረጃጀት ይልቅ  በሃገራዊ አደረጃጀት እንዲጠናከሩ ማድረግ፣

2ኛ) ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት የመገለል ስሜት የተሰማቸው ክልሎችን ሃገራዊ ሚናቸውን ከፍ ማድረግ እና የታወጀውን አዋጅ መሻር፣

3ኛ) የፍትህ ስርዓቱ፣የመገናኛ ብዙሃን፣ጋዜጦች እና ጋዜጠኝነት ደረጃቸውን የጠበቁ እና ነፃነት ያላቸው ሙያዎች እንዲሆኑ በብቁ የሰው ኃይል ማጠናከር እና በቂ ጥበቃ እና ዋስትና መስጠት፣

4ኛ) ሙስና የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብታዊ፣ማህበራዊ እና መንግስታዊ ድርጅቶች ሁሉ የጎዳ በመሆኑ በሙስና የተተበተቡ ሁሉ ለፍርድ የማቅረብ ሥራ መስራት ለእዚህም ሕዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር እና እርምጃው በሕዝብ የጀርባ ድጋፍ እና ደጀንነት እንዲታገዝ  በማድረግ ወደ ማይቀለበስ ደረጃ ማድረስ፣

5ኛ) የትግራይ ሕዝብ ከህወሓት ይልቅ ኢትዮጵያ እንደምታዋጣ በማሳየት ህወሓት የትግራይ ሕዝብ ዋስትና አለመሆኑን ማሳየት፣

6ኛ) የጦር ሰራዊቱ ከመስመር መኮንኖች ጀምሮ እስከጠራው ድረስ ከላይ በምተገበሩት ተግባሮች ሁሉ በሃሳብ እንዲሳተፍ በሕዝብ መገናኛ ሚድያ አማካይነት ድጋፍ እንዲሰጥ ድምፁን ለሕዝብ እንዲያሰማ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች ማዘጋጀት እና የተናበበ እንዲሆን ማድረግ፣

7ኛ) የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ቃል አቀባይ ከፍተኛ ባለሙያ እና የሚሰሩትን ስራዎች በእየሳምንቱ ለሕዝብ የምገልጡበት መድረክ ማዘጋጀት፣ እርሳቸው በማይመቻቸው ጊዜ በሕዝብ አእምሮ ሊቀር በሚችል መልክ በተክለ ሰውነት፣በአገላለጥ ጥራት እና የሚለውን ወይንም የምትለውን በመግለጥ ሕዝብ የሚያስደምም ወይንም የምታስደምም ቃል አቀባይ መመደብ፣

8ኛ) የሀብት ክፍፍሉ አድሏዊ የሆነበትን መንገድ ለማስተካከል ከአሁኑ መሰረት መጣል።ይህም ስልታዊ በሆነ የቀረጥ ፖሊሲ በሂደት ለውጥ በሚያመጣ መልኩ መሄድ እና 

9ኛ) ኢትዮጵያ በሶስት ወይንም ሁለት ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር የሚደረግባት ለማድረግ የፖለቲካ ድርጅቶች አደረጃጀት ላይ አቅጣጫ መስጠት፣

10ኛ) ጠንካራ እና ታማኝ የምርጫ ቦርድ መመስረት እና ከላይ የተጠቀሱት ስራዎች ወደ ኃላ እንዳይመለሱ ዋስትና የሆነ ስልታዊ አደረጃጀት ላይ መስራት እና የህዝቡን አቅም ማጎልበት የሚሉት አስፈላጊ ስራዎች ናቸው።

ባጠቃላይ ዶ/ር አብይ ሁሉን ሥራ እንዲሰሩ አንጠብቅም።ያለባቸውን ተግዳሮት ይታወቃል።ሆኖም ግን ኢትዮጵያ በኃይል በሚፈጠረው ቅራኔ ወደ አልታወቀ መንገድ እንዳትሄድ የሚያስፈልጋትን የሽግግር ወቅት ላለፉት 27 አመታት የተጎሳቆሉት ዋና ዋና እሴቶቻችንን ማስመለስ እና ማጠናከር በእራሱ የህወሓትን የጎሳ ፖለቲካ የሚያደክም ብቻ ሳይሆን ነገ ለሚመጣው ዘገምተኛ ወይንም ፈጣን ለውጥ ዋስትና መስጠት ነው። ዶ/ር አብይን ብዙ ከባድ ነገሮች አንጠብቅም ከላይ የጠቀሱትን በፅኑ መሰረት ላይ ካስቀመጡ ትልቅ ሥራ ሰሩ በማለት ታሪክ ያስታውስዎታል።

ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Friday, March 23, 2018

በጥንታውቷ ግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከስድስት ሺህ ካሬ በላይ ስፋት ያለው በአውሮፓ የመጀመርያዋ የሆነውን ገዳም ገዛች

Greek Ethiopian Orthodox Tewahido church
በግሪክ አቴንስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የገዛችው ገዳም  ቤተ ክርስቲያን 

ጉዳያችን / Gudayachn 
መጋቢት 15/2010 ዓም (ማርች 24/2018)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በውጭ ሃገራት ያላት ይዞታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው።በያዝነው 2010 ዓም በአውሮፓ ብቻ ቤተ ክርስቲያኒቱ በአራት ሀገሮች ውስጥ የራሷ ይዞታ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናትን ገዝታለች።እነርሱም በእንግሊዝ፣ለንደን የደብረ ገነት ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን፣ በኦስሎ፣ኖርዌይ የቅዱስ ገብርኤል አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን፣በጀርመን ፍራንክፈርት የመድሃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ሲሆኑ በእዚህ ዜና ላይ ትኩረት የሚደረግበት አዲሱ ገዳም ደግሞ በግሪክ አቴንስ ከስድስት ሺህ ካሬ በላይ ስፋት ያለው ገዳም ነው።

በጥንታዊቷ ግሪክ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የገዛችው ገዳም የመሬቱ ስፋት ብቻ ሳይሆን ግቢውን አልፎ የሚሄድ ክረምት ከበጋ የሚፈስ ወንዝ ፣ባለ አንድ ፎቅ ሰፊ ህንፃ ቤተ ክርስቲያን፣የዘንባባ እና የወይራ ዛፎች ያሉት ሲሆን የወይራ ዘይት ለማምረት የሚያስችል አቅም የፈጠረ ነው። ክረምት ከበጋ የሚፈሰው ወንዝ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የገዳሙ ይዞታ የመስኖ ልማት ለማልማት የሚያስችለው ነው። ገዳሙ የተገዛበት ቦታ ከአቴንስ ዋና ከተማ ወደ አየር መንገዱ ወጣ ያለ በመሆኑ ፍፁም የሆነ ፀጥታ የሰፈነበት እና ለፀሎትም ሆነ ለአርምሞ የተመቸ ነው። ከእዚህ በተጨማሪ ገዳሙ በቂ የእንግዶች ማረፍያ ክፍሎች እና ሽንት ቤት ስላለው ለሱባኤ የሚመጡ ምእመናንን ወደፊት የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው ይታሰባል።


ከሀገር ውጭ ገዳማትን በመግዛት የሚታወቁት የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በአውሮፓ፣አሜሪካ እና አውስትራልያ ገዳማት እየገዙ እንደሚያለሙ ይታወቃል።የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሚልዮን የሚቆጠሩ ምዕመናን ይዛ አጥብያ አብያተ ክርስቲያናት ማስፋፋት ላይ እንጂ ገዳማትን መገደም ላይ ብዙ እንዳልሰራችበት ይታወቃል። የገዳማት መኖር ግን ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው።የመጀመርያ ጥቅሙ ለመንፈሳዊ ሕይወት ነው።ሁከት በመላበት ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ምዕመናን አእምሮ የሚያረጋጋ፣አርምሞ የተሞላበት ህሊና የሚሰበሰብበት ገዳማት ሄደው ከአምላካቸው ጋር መነጋገር ይፈልጋሉ።ሆኖም ግን ገዳማት ባለመኖራቸው ይቸገራሉ።


በክረምት ወር የሚጨምረው በበጋ ወቅት የማይደርገው በገዳሙ መሃል የሚያልፈው ወንዝ 

ሁለተኛው ጥቅም ካህናትን ለማሰልጠን ይረዳል።ይሄውም ኢትዮጵያዊም ሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎችን ስልጠና ለመስጠት ገዳማት ያስፈልጋሉ።ሶስተኛው በውጭ ለተወለደው ትውልድ ገዳማት ማለት ብዙ ነገር ናቸው።በገዳማት የአጭር ጊዜ ስልጠና በውጭ ለተወለዱ ወጣቶች መስጠት ይቻላል።በውጭ የተወለዱ ወጣቶች በእረፍት ሰዓት የአጭር ጊዜ ስልጠና ለመስጠት ለተወሰኑ ቀናት ገዳማቱ ውስጥ እያደሩ ማስተማር እና ለአገልግሎት ማብቃት ይቻላል።ከእዚህ ውጭ ማንነታቸውን የሚረዱበት አይነተኛ ቦታም ገዳማት ናቸው።በውጭ ከተወለዱት ኢትዮጵያውያን በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን ወደ ውጭ ሀገር ዜጎች አገልግሎቷን ለማድረስ የገዳማት ሚና ቀላል አይደለም።ይህ እንግዲህ ከመንፈሳዊ ጥቅሞቹ ሁሉ ጋር ነው።

የግብፅ ቤተ ክርስቲያን በአውሮፓ ካሏት ገዳማት ውስጥ ጀርመን ከፍራንክፈርት የአንድ ሰዓት የመኪና ጉዞ ርቀት የሚገኘው የአቡነ እንጦስ ገዳም ተጠቃሽ ነው። የእዚህ ፅሁፍ ፀሐፊ እንደተመለከተው ይህ ገዳም ከሃምሳ በላይ ሰዎች ሊያሳድር የሚችሉ ከመታጠብያ እና መመገብያ አዳራሽ ጋር የተሟሉ የመኝታ ክፍሎች፣ እራሱን የቻለ ዘመናዊ የመሰብሰብያ አዳራሽ፣እና ሰፊ ቤተ ክርስቲያን የያዘ ነው። በእዚህም ግብፃውያን ብቻ ሳይሆኑ ለኢትዮጵያውያን ምዕመናን ጭምር በነፃ ያስተናግዱበታል።


የገዳሙ የውስጥ ክፍል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስርዓት መሰረት እየተሰራ ያለ 

በግሪክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የገዛቸው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምትገባው ለረጅም ዓመታት በአቴንስ ከተማ አገልግሎት በመስጠት ላይ የምትገኘው የመክሐ ደናግል ቅድስት ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ታቦተ ሕግ ሲሆን ታቦቱ በአቡነ ኤልያስ ከዓመታት በፊት በአቴንስ ከተማ የተተከለ ነው።የግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ በአቡነ ተክለሃይማኖት ፕትርክና ወቅት  አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ እና አቡነ ኤልያስ የቲዎሎጂ ትምህርት የተማሩባት ከተማ ነች።ይህች ታቦት ነች ወደ አዲስ ወደተገዛው ገዳም የምትሄደው።

ይህ በግሪክ አቴንስ የተገዛው የቤተ ክርስቲያን ቦታ እና ህንፃ ቤተ ክርስቲያን በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2017 ዓም የተገዛ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ቀላል የውስጥ እድሳት ወይንም የቀለም መቀባት ሥራ እየተደረገለት እና በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን  የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በነፃ እያገለገሉ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።በአሁኑ ሰዓት ቤተ ክርስቲያኑን በማገልገል ላይ ያሉት አባ ወልደ ሚካኤል እና አባ ናሁ ሰናይ በምዕመናን የሚወደዱ እና ምዕመናኑን በማስተባበር የገዳሙ ግዥ እንዲፈፀም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረጉ ምዕመናን ይናገራሉ። የአዲሱ ቤተ ክርስቲያን እድሳት እንደተጠናቀቀ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከሀገር ቤት መጥተው ቡራኬ እንዲያደርጉ መልዕክት ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደላከች እና (ይህንን ዜና ጉዳያችን እስካጠናከረችበት ያለፈው የካቲት ወር 2010 ዓም የመጀመርያ ሳምንት ድረስ)ቤተ ክርስቲያን  ምላሽ እየጠበቀች እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። እዚህ ላይ ጉዳያችን እንደተረዳችው የምእመናን እና የአባቶች አገልግሎት በተሳካ መንገድ የቤተ ክርስቲያን ግዥ ቢፈፅሙም ከቤተ ክህነት በኩል ተገቢው ድጋፍ እና በተለይ ቤተ ክርስቲያኑን በገዳምነት የመገደም እና የመባረክ አገልግሎቱን በማቀላጠፍ በኩል ከአገልጋይ አባቶች አይሰማ እንጂ  ዘገምተኛ ምላሽ እንዳለ ግን አንዳንድ ምዕመናን ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ተደምጧል። በአቡነ ማትያስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ትልቅ ትኩረት የሚሻ የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዞታ በሁሉም መልክ ማገዝ ሲገባ የተሰጠው ትኩረት ግን ምዕመናን እና በቦታው ያሉት ካህናት ያላቸውን ትጋት ልክ አለመሆኑን ጉዳያችን በቦታው በምዕመናን ዙርያ የሚሰማውን ቅሬታ ለማዳመጥ ችላለች።በመሆኑም ይህንኑ ጉዳይ ለአባቶች በማድረስ እና አገልጋይ ሰባክያንም ምዕመናኑን በማፅናት በኩል ትኩረት እንዲያደርጉ በእዚህ አጋጣሚ ጉዳያችን ታሳስባለች።

በግሪክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የገዛችው ገዳም  ቀደም ብሎም በግሪክ ቤተ ክርስቲያን በቅድስት አያፎሎፊ በተሰኘች ቅድስት ስም የሚጠራ የሴቶች ገዳም ሆኖ ለብዙ ዓመታት ማገልገሉን ለማወቅ ተችሏል።ገዳሙ  በአውሮፓ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ሆነ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አንዱ መዳረሻ የፀሎት እና የሱባኤ ቦታ እንደሚሆን ይታመናል።በሌላ በኩል በግሪክ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያላቸው የእርስ በርስ ግንኙነት፣መረዳዳት እና መተሳሰብ በሌሎች ቦታዎች ከሚታዩት የተለየ ነው። በስደት ከሊብያ፣ከቱርክ እና ከአረብ ሀገሮች የመጡ በርካታ ወጣቶች በስደት እና በመሸጋገርያነት የሚጠቀሙባት ግሪክ ሥራ ያላቸው ወጣቶች ሥራ ለሌላቸው ወጣቶች ቤት ተከራይተው ሙሉ የምግብ ውጪያቸውን እየቻሉ የሚያደርጉት መረዳዳት ክርስትና እና ኢትዮጵያዊነት በትክክል የሚንፀባረቅባቸው ወጣቶች መሆናቸውን ያስመሰከሩበት ትልቅ አብነት ነው።የእዚህ ዜና አቅራቢ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚያገለግሉ ወጣቶች  ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ እጅግ አስደማሚ ንግግሮችን ሰምቷል። ለምሳሌ አንድ መንፈሳዊ መርሃ ግብር ላይ የተሰበሰቡ ወንድ ወጣቶች ጋር በተደረገ ውይይት እንደተገነዘበው እንባ እየተናነቃቸው እርስ በርስ እየተቀባበሉ ወጣቶቹ የተናገሩትን እዚህ ላይ ማስፈሩ ሁኔታውን በደንብ ሊገልጠው ይቻላል።የወጣቶቹ ንግግር እንዴት ወጣቶች ተሳስበው እንደሚኖሩ ስለሚያሳይ በመጠቅለል እንዲህ አቀርበዋለሁ።
" እኛ እዚህ ሀገር ከወገኖቻችን ያገኘነው ደግነት በእውነት ክርስትና ምን እንደሆነ የተረዳንበት ነው።አውደ ምህረት ላይ ከምንማረው ባላነሰ ወንጌል የተማርነው ሥራ ካላቸው እህቶቻችን ነው።እዚህ ሀገር እንደምታውቁት ሥራ ብዙ ያለው ለሴቶች ነው ወንዶች በብዛት የለንም።ሴቶቹ ግን ተሰባስበው እዚህ ለምታዩን ወጣቶች በሙሉ በአንድ ላይ ቤተ ተከራይተው ኪራያችንን እየከፈሉ ፍሪጁ አንድ ቀን ሳይጎድል አንድ ላይ እያዋጡ ሞልተውልን ይሄዳሉ።እዚህ  እነርሱ የተከራዩት ቤት ውስጥ ማንም ስደተኛ መጥቶ ያድራል።ከእዚህ ወደ ሌላ ሀገር ሲሄድም ይህንን ቤት አይረሳም ደብዳቤ እየፃፉ እስካሁን ሰላም የሚሉን የሚረዱንም አሉ።በእየዕለቱ ፀሎት አለን።ትምህርት እንማማራለን።ባለን ጊዜ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንም እናገለግላለን።ዛሬ ሰው እንድንሆን የረዱን እህቶቻችንን በጣም እናመሰግናለን እግዚአብሔር ዋጋቸውን ይክፈላቸው።ቤተ ክርስቲያናችንን እንድንወድ  ክርስትናን እንድናውቅ አድርገውናል።'በጣም አመስግኑልን። " ብለዋል።

የገዳሙ ግቢ መግቢያ ውጭያዊ ክፍልም የገዳሙ ይዞታ ነው 

በመጨረሻም ለማጠቃለል  ግሪክ የአዲሱ ትውልድ የእርስ በርስ መረዳዳት እና የእውነተኛ ኢትዮጵያዊ መልክ የሚታይበት ቦታ ነች።ቤተ ክህነት በሙስና እና በጎሳ ያልተማከለ አገልግሎቱን ለእዚህ ገዳም መስጠት ሐዋርያዊ ግዴታው ሲሆን  አገልጋይ ሰባክያንም ለወጣቶቹ ትኩረት ሰጥተው ሊያገለግሏቸው  ይገባል በማለት  ዘገባውን  እደመድማለሁ።

ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Wednesday, March 21, 2018

ማኅበረ ቅዱሳን በዋልድባ ጉዳይ ዝም ብሎ አያውቅም።ለመጀመርያ ጊዜ በጥናት በተደገፈ ማስረጃ መንግስት እጁን እንዲያነሳ የጠየቀም ማኅበረ ቅዱሳን ነው።

የማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል ጽህፈት ቤት 

ከእዚህ በታች ያለው ፅሁፍ በአብርሃም ሲሳይ የቀረበ ፅሁፍ ነው።
+++++++++++++++
ማኅበረ ቅዱሳን በዋልድባ አባቶች ጉዳይ የት ነው ያለው? የሚል ነገር ፤ እዚህም እዛም እየተነሳ አየሁ። በርግጥ ማኅበሩ በዋልድባ ጉዳይ ዝም ብሏል?ለጉዳዩ ቀረብ ያላችሁ የገዳሙ ጉዳይ መዘዝ ምን እንዳመጣ ታቁታላችሁ። ለሌሎቻችሁ በአጭሩ ለመግለጽ ያክል 

ዋልድባ፤ በምሥራቅ ጎንደር እና በምዕራብ ትግራይ መካከል የሚገኝ ታላቅ ገዳም ነው። ምሥረታው በ485 ዓ. ም. ገደማ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ገዳም ጥንታዊ እና ታሪካዊ ሀገራዊ ቅርሶችን እንዲሁም ከ3000 በላይ መናንያንን የያዘ ገዳም እንደሆነ ይነገርለታል። ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ከ፴ እስከ ፵ ኪሎሜትር ርቀት ስኖረው ከሰሜን ወደ ደቡብ ከ፹—፺ ኪሎ ሜትር ስፋት ነበረው፡፡ ገዳሙ ዙሪያውን በአራት አፍላጋት(ወንዞች) በምስራቅ የእንስያ፣በምእራብ የዛሬማ፣በደቡብ የማይወባ፣በሰሜን የተከዜ ወንዞች አጥር ቅጥር ሆነው ገዳሙን ይከልሉት ነበር። አዎ ነበር፡፡
...
ለሺህ ዓመታት ተከብሮ የኖረው ገዳም ዙሪያውን ከብበው አጥር ቅጥር ሆነው የነበሩት ወንዞች ላይ መሰረት ያደረግ ለስኳር ማምረቻ የሚሆን የሸንኮራ ልማት በገዳሙ ክፍል ላይ እንገነባለን ሲባል ነው ጉዳዩ የሚጀምረው። ቀደም ብሎ በዋልድባ ገዳም በማኅበረ ቤተ-ሚናስ እና ቤተ-ጣዕመ መካከል ቅራኔ ነበር ፤ በገዳሙ ታላላቅ አባቶች ቅራኔዎቹ ሊፈቱ ካለመቻላቸውም ባሻገር አገልግሎታቸው እንኳን በየተራ እስኪሆን ድረስ የደረሰ ትልቅ ልዩነት ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል፥ ለዓመታት ጉዳዩ ከወረዳ ቤተክህነት አንስቶ ፣ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ የደረሰ ቢሆንም፤ አባቶች ጉዳዩን ከማስታረቅ ከመፍታት ይልቅ ለቤተ መንግሥቱ መንገድ በመክፈት፤ ገዳሙ እንዲደፈር አድርገዋል።
..,
መንግስት በ2004 ዓ.ም በገዳሙ ክልል እና ዙሪያ የፓርክ ይዞታ ለመከለል እና የስኳር ፋብሪካ ለማቋቋም እንቅስቃሴ ሲጀምር በገዳሙ የነበሩ አባቶችተቃውሟቸውን ማሰማት ጀመሩ። በዚህም አባቶት ያን ጊዜ ለነበሩት ፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስ፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽህፈትቤት፣ ለትግራይ እና ለአማራ ክልል ፣ እንዲሁም ለጠቅላይ ሚንስትሩ ደብዳቤ በተደጋጋሚ አስገብተዋል።
የገዳሙ አባቶች ከደብዳቤ ባለፈ ፓትሪያሪኩንና ፤ ጠቅላይ ምንስቲሩን በአካል ሄደው የሚያናግሩ አባቶችን በመምረጥ ወደ አዲስ አበባ እንዲሄዱ አደረገ። ያን ጊዜ ከገዳሙተወክለው ጠቅላይ ምንስትር መለስ ዜናዊን ሊያናግሩ የመጡት አባቶች ናቸው ዛሬ በማሰቃያ ወህኒቤት ያሉት።
...
ማኀበረ ቅዱሳን በገዳሙ ክልል ውስጥ በጊዜው ሊሰራ የታሰበውን ፕሮጀክት በቦታው ተገኝቶ ግድቡ ገዳሙ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ለመጀመሪያ ጊዜ በጥናት አስደግፎ ለህዝብ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል። ማኀበሩ ጥናታዊ ጽሁፍ ከማቅረብ ባሻገር በይፋ መንግስት እጁን ከደሙ ላይ እንዲያነሳ በተደጋጋሚ ጠይቋል፡ ጉዳዩ በቤተ ክህነት ሰዎ ችና በምንግስቱ ባለስልጣናት የዘር መልክ እንዲይዝ ተደረገ እንጂ።
ሪፖርቱ በአጭሩ
ሀ. ግድቡ 16.6 ሔክታር ከገዳሙ ቅዱስ ቦታ ገብቶ እንደሚያርፍ፤
ለ. አጽመ ቅዱሳን መነሳቱን አረጋግጦልናል
ሐ. 500 ሜትር ስፋት ያህል ያለው መንገድ በገዳሙ ውስጥመቀደዱን
መ. አብያተክርስትያናት እንደሚፈርሱ
ሠ.ገዳሙ የእርሻ መሬቱን እንደሚያጣ
እና ሌሎች ጉዳዮችን በመጀመሪያ ጥናቱ ለህዝብም ለመንግስትም ያቀረበ ሲሆን፡። ያንን ተከትሎ በገዳሙ ሆናችሁ መረጃ ታቀብላላችሁ በማለት መነኮሳቱ በሱባዔ ላይ እያሉ ተደበደቡ ከገዳሙ ተሰደዱ። ለአቤቱታና ጠቅላይ ምንስትሩን ለማናገር አዲስ አበባ የመጡት መነኮሳት ከዛንጊዜ አንስቶ ሲሳደዱ ቆዩ።ማኅበሩንም ቀደም ብሎ ከተጀመረው ከአልቃይዳና ከአልሰለፊያ ጋር የማመሳሰሉንና የመምታቱን አላማ የዋልድባ ጥናት ሪፖርት ለመንግስት እንደምክንያት በመጠቀም ማህበሩን ለማፈራረስ እንደ አቅማቸው ሞከራ ጀመሩ። ላይጨርሱ ጀመሩ እንጂ። በዋልድባ አባቶች ሃዘንና ለቅሶ ሁለቱም ተከታትለው ተወሰዱ።
...
ሳጠቃልል፡ ማኅበረ ቅዱሳን ላለፉት ስድስት ዓመታት በዋልድባ ጉዳይ ዝም አላለም!ምን አልባት ለብዙዎ ቻችን አባቶቹ በወህኒ ቤት ምን እየደረሰባቸው እንዳለ በዚህ ወር ይሆናል ያወቅነው ፡ ድምጽ አሰማን ብለን የምናስበውም የFacebook Profile ሰለቀየርን ይሆናል፡ ማህበሩ እንደ ማህበርም ይሁን እንደ አባላት(በግል)አባቶቻችን ለአቤቱታ ከመጡበት እለት አንስቶ(ምን አልባትም ስለጉዳዩ በማንቃትና፡ መንገድ በማሳየት በኋላም ጉዳያቸውን በመከታተል) የሚያውቃቸውም ሆነ የሚገባውን ሲያደርገ የነበረ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።











ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Tuesday, March 20, 2018

አሁንም ትኩረት የመኖርያ ፍቃድ ላላገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች

ጉዳያችን/Gudayachn
መጋቢት 12/2010 ዓም (ማርች 21/2018)

በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም ተበትነው ይኖራሉ።ከእነኝህ ውስጥ የሚኖሩበት ሀገር ሕግ ተከትለው የስደተኛነት ከለላ ጠይቀው ያላገኙ ነገር ግን በከፍተኝ ችግር ውስጥ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን በአውሮፓ እና አሜሪካ ይገኛሉ።ችግሩ በተለይ በአውሮፓ የከፋ ነው።በአውሮፓ ውስጥ የስደተኛ ከሌላ ያላገኙ ኢትዮጵያውያን የስራ ፈቃድም ስለማያገኙ ለእለት መኖርያ እጅግ ይቸገራሉ።

በአውሮፓ ውስጥ ስደተኞች ከሚቸገሩባቸው ሀገሮች አንዷ ኖርዌይ ነች።በኖርዌይ ውስጥ የመኖርያ ፍቃድ ሳያገኙ ሥራ መስራት ክልክል ነው።እንደ አሜሪካ በጥቁር (በድብቅ) ሰርቶ መኖር አይቻላም።ምክንያቱም የግል ዘርፉ በኖርዌይ እንደ አሜሪካ የተስፋፋ አይደለም።ከእዚህ በከፋ ሁኔታ ደግሞ የኖርዌይ መንግስት ፍቃድ የሌላቸው ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ሲገፋፋ እና አንዳንዴ በግዳጅ ለመውሰድ ሲሞክር ይታያል።ይህ ተግባር ኖርዌይ ከገባችው የዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር ፈፅሞ የሚቃረን ነው።እንደ ኖርዌይ ያሉ ከበርቴ የአውሮፓ ሀገሮች ይህንን የዓለም አቀፍ ሕግ በተለይ ስደተኞችን አስመልክቶ የሚጠቀሱ ሕጎችን የተለያዩ የሕግ ትርጉም እየሰጡ ሲጥሱት ይስተዋላል።ሕጉ የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን የመሳሰሉ ድርጅቶች ሁኔታውን እንዳላዩ ሆነው ሲያልፉት ይታያል።ለእዚህም ዋናው ምክንያት ሀብታሞቹ ሀገሮች ለዓለም አቀፍ ድርጅቶቹ መንቀሳቀሻ ዳጎስ ያለ በጀት ስለሚለቁ ነው።

በኖርዌይ የሚኖሩ መኖርያ ፍቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ችግሮች 

በኖርዌይ የሚኖሩ መኖርያ ፍቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ችግሮች ዘርፈ ብዙ ናቸው።በመጀመርያ ደረጃ በእድሜ ስንመለከት አብዛኞቹ ወጣቶች ከመሆናቸውም በላይ የመስራት፣የመማር እና ጊዜያቸውን በሚገባ ለመጠቀም ጉጉት ያላቸው ናቸው።ከእዚህም በላይ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ጉልህ እና ግንባር ቀደም ተሳትፎ ያላቸው ናቸው።ሆኖም ግን በመስራት እራሳቸውን እና ሀገራቸውን እንዳይረዱ አስፈላጊውን የመኖርያ ፍቃድ ስላላገኙ ብቻ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብተዋል።ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ ደግሞ የኖርዌይ መንግስት አብዛኞቹን የስደተኛ ካምፖች እየዘጋ ስደተኞቹን ኢራቅ ወዳሉ ቦታዎች ስለወሰዳቸው ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሆኑ እየተሰማ ነው።የስደተኛ ካምፖቹን መዘጋት ተከትሎ በርካቶች ከተማ የሚያውቁት ወዳጅ ጋር ተጠግተው ለመኖር ተገደዋል።ከእዚህ በባሰ ደግሞ የኖርዌይ ፖሊስ አንዳንዶቹን እየያዘ በግዳጅ ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑ ተሰምቷል።በእዚህም ሳብያ ብዙዎች ተስፋ መቁረጥ፣የአዕምሮ ጭንቀት እና ስጋት ተዳርገዋል።

የመኖርያ ፍቃድ የሌላቸው ስደተኞች ለመርዳት ምን አይነት የመፍትሄ እርምጃዎች ይወሰዱ?

በርካታ የመኖርያ ፍቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን እነኝህን ስደተኞች ለመርዳት ይፈልጋሉ። ሆኖም ግን እንዴት የሚለው ጥያቄ ያሳስባቸዋል።ሆኖም ግን እነኝህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እንዲደግፉ የሚያስተባብርላቸው አካል ይፈልጋሉ።እዚህ ላይ አንዳንዶች የፖለቲካ ድርጅቶች የስደተኞችን ጉዳይ እንዲሰሩ ሃሳብ ያቀርባሉ። ሆኖም ግን ይህ ስህተት ነው።ምክንያቱም የፖለቲካ ድርጅቶች ስራቸው ሰብዓዊ ተግባር ላይ ያተኮረ አይደለም።የስደተኞች ጉዳይ ፖለቲካዊ ቃና ብቻ ሳይሆን ያለው ሰብአዊነት ተግባርም ጭምር ነው።
የመኖርያ ፍቃድ የሌላቸው ስደተኞች ለመርዳት የሚከተሉት የመፍትሄ እርምጃዎች ቢወሰዱ ብዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ይቻላል። እነርሱም :-

1/የስደተኞች ማኅበርን በአዲስ መልክ ማጠናከር፣ አመራሩ ላይ ፍቃድ የሌላቸው ብቻ ሳይሆን በስደተኛ መስመር አልፈው ፍቃድ ያገኙትን ወደ አመራር ማምጣት እና የስደተኛውን ማኅበረሰብ ችግር በጋራ እንዲቀርፉ ማድረግ፣

2/በሰው ኃይል እና በገንዘብ የተጠናከረው የስደተኛው ማህበር ከማህበረሰቡ ጋር እንዲገናኝ ልዩ ልዩ መድረኮች ማዘጋጀት።

3/  የሃይማኖት ድርጅቶች፣የማኅበረሰብ ማኅበራት ማስተባበር እና ፍቃድ የሌላቸው ስደተኞች እንዴት፣በምን እና መቼ ሊደገፉ እንደሚችል የአንድ ዓመት እቅድ ማዘጋጀት እና እቅዱን ለሁሉም በግልጥ ማስተዋወቅ።

4/ፍቃድ የሌላቸው ስደተኞች አቅም፣ችግር እና መፍትሄዎች መለየት እና ከተጨባጭ ስራዎች ጋር ማኅበረሰቡ እንዲያግዝ ከበቂ ሥራ ጋር ማውረድ የሚሉት ዋና ዋናዎች ናቸው።

ባጠቃላይ ግን ትልቁ እና ዋናው ቁምነገር የስደተኛ ማኅበሩን ማጠናከር እና ሕጋዊ ሰውነቱን አስከብሮ በየትኛውም የኖርዌይ ቢሮ ውስጥ ገብቶ ችግሩን ለመግለጥ በቂ ቁመና ያለው ድርጅት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህ ካልሆነ ግን አሁንም እሳት የማጥፋት ሥራ ላይ ብቻ መጠመድ ይሆናል።የስደተኛ ማኅበር አቅሙን አጠናክሮ በእዚህ ዓመት ሊሰራ ካቀደው እቅድ ጋር በመሃል የሚያጋጥሙ ስደተኞችን በኃይል ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶችን ለግብር ከፋዩ የኖርዌይ ሕዝብ በቀላሉ የሚያደርስበት መረብ ዘርግቶ መጠባበቅ አለበት።ከእዚህ ውስጥ አንዱ በግድ ሊመለሱ ተፅኖ የተፈተረባቸው ግለሰቦችን ታሪክ እና የደረሰባቸውን በደል በማኅበራዊ ሚድያ እና የኖርዌይ የዜና አውታሮች እንዲዘግቡ የመጠየቅ ተግባር አስፈላጊ ነው።በአሁኑ ወቅት የምዕራብ መንግሥታት ከቀረጥ ከፋይ ሕዝብ የሚመጣ ጥያቄ መስማት ግዴታቸው እንደሆነ ያምናሉ።ቀረጥ ከፋይ ሕዝብ የሚገኝበት አንዱ መንገድ ደግሞ ማኅበራዊ ሚድያ ነው። በመሆኑም የስደተኛ ማኅበር እራሱን በሰው ኃይል፣በገንዘብ እና በመገናኛ መረብ ማጠናከሩ በድንገተኛ መልክ በስደተኛው ኢትዮጵያዊ ላይ ለሚደርሰው ችግር በቶሎ መፍትሄ ለመስጠት ያስችለዋል።

ስደት የተሰኘው በተለይ ለዘመን ድራማ የተዘጋጀ ዜማ 


ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

Sunday, March 11, 2018

Gudayachn Breaking News in English March 12/2018 (Audio)

ጉዳያችን ሰበር ዜና የሞያሌ ከተማ ጭፍጨፋ ተከትሎ የነዳጅ ማመላለሻ መኪናዎች ከማክሰኞ መጋቢት 4/2010 ዓም ጀምሮ ወደየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ነዳጅ እንዳያደርሱ የዐማራ እና ኦሮሞ አክትቪስቶች ጥሪ አቅርበዋል። March 12/2018 Following the Moyale town massacre by TPLF, a New Fuel ban strike is called by Amhara and Oromo activists. ጉዳያችን / Gudayachn March 12, 2018 https://www.youtube.com/watch?v=B5oO5QeHFRY .
Subscribe and click Gudayachn Youtube to listen the news.


ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

Tuesday, March 6, 2018

Gudayachn / ጉዳያችን News in English (Audio) March 7,2018

በዛሬው የጉዳያችን የድምፅ ዜና ውስጥ በያዝነው ሳምንት ውስጥ  የአሜሪካ፣ሩስያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሰዓታት ልዩነት ወደ አዲስ አበባ ለምን ያመራሉ?በሚሉት እና የእንግሊዝ መንግስት ገንዘብ የነፈገው ጠቃሚ ፕሮጀክት በኢትዮጵያውያን በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ስለመሆኑ ያትታል።ዝርዝሩን ከዜናው ያዳምጡ።
The Head lines in today's News are  - US, Russia and UAE foreign ministers travel to Ethiopia. What is their purpose?- Ethiopian spice girls project on building girls confidence and capacity did not affect by UK fund cut. You can listn also from Youtube link



ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

Thursday, March 1, 2018

Ethiopia - GUDAYACHN / ጉዳያችን News in English (Audio)

Gudayachn/ጉዳያችን  News, views and analysis. 
March 2, 2018
===============
The headlines : - 

- The question of legitimacy is raised on the state of emergency declared in Ethiopia.
- Who is the expected Prime Ministr of Ethiopia?
Click here below to listen Audio


ጉዳያችን GUDAYACHN 

 www.gudayachn.com

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።