ፎቶ ከ''የኔታ ትዩብ''
የጉዳያችን ማስታወሻ
የስርዓቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ድንግዝግዝ፣ሙስና-ገዝ እና ጥቂቶች በውስጥ ስብሰባ እንደፈለጉ የሚገለባብጡት ነው።በአደባባይ ባለስልጣናቱ የሚናገሩት እና በውስጥ መስመር የሚሰሩት ፈፅሞ አይገናኝም።ይህ ደግሞ በድንግዝግዝ፣ወጥነት እና አቅጣጫ የሌለው አሰራር እና ለአገር ጥቅም ሳይሆን ለጥቂቶች ብልፅግና የሚዋትት ስርዓት መለያ ነጥቦች ናቸው።በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው አምባገነን ስርዓት ምን እንደሚያቅድ፣የት ለመድረስ እንደሚያስብ እና ወጥ የሆነ ፖሊሲው ምንድነው? ብሎ ለማወቅ በጎሳ ላይ የተመሰረተ የምጣኔ ሀብት፣ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ መሰረቱን ከመናገር ውጭ ወጥ የሆነ ስዕሉን ለማግኘት ለባዕዳንም አስቸጋሪ ሆኗል።በመሆኑም በሚናገራቸው ነገሮች ከማመን ይልቅ ሊያደርግ የሚያስበው ይህንን ነው ብሎ መተንበዩ አዋጪ ነው።
ለእዚህም አመላካቾቹ ሁለት ነጥቦች ናቸው። እነርሱም
1/ የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ማጣኔ ሃብታዊ እና ወታደራዊ መዘውር የሚያሽከረክረው ህወሃት ዋናው አመራር እራሱን ከቤተ መንግስት ጀርባ ሆኖ አቶ ኃይለማርያም እና መሰሎቻቸውን ከማዘዝ በቀር ወደ አደባባይ ወጥቶ ጋዜጣዊም ሆነ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ አለመታየቱ እና
2/ ከፊት እንዲሰለፉ የተደረጉት እና የእራሳቸው ሃሳብ የማይናገሩቱ እነ አቶ ኃይለማርያም ነገር አሳመርን እያሉ ''ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ'' እንዲሉ የበለጠ ታማኝነታቸውን ለማፅናት የሚሉት ከሚፈፀመው ጋር አለመገናኘቱ የሚሉት ናቸው።
ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚሄድ አንድ የውጭ አገር ባለስልጣን ሁለት አይነት ባለስልጣናት እንዳሉ ጠንቅቆ ያውቃል።እነርሱም የይስሙላ እና ዋናው ባለስልጣን የሚባሉ ናቸው።በምጣኔ ሀብት ጥናት እውነተኛ (real) የሚሉት እና ''እውነተኛ'' ያልሆነው (nominal) የተሰኙ ሁለት አፈራረጆች እንዳሉ ሁሉ ባዕዳኑም ከባለስልጣናት ጋር የሚኖራቸውን ቀጠሮ ኤምባሲዎቻቸውን ''እውነተኛው ነው ወይንስ የይምሰሉ ባለስልጣን ነው?'' ( Is he nominal or real?) እያሉ መጠየቅ ይዘዋል።አቶ ኃይለማርያም ከይምሰል ውስጥ የሚመደቡ ሲሆኑ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ደግሞ ከዋናው ፖሊሲ ዘዋሪው ውስጥ ይመደባሉ።
የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ድምፃቸውን አጥፍተው እየገቡ ነው
በኢትዮጵያ የአደባባይ መግለጫዎች እና ከበሩ ጀርባ የሚሰሩ ስራዎች የመለያየት አይነተኛ ማሳያዎች ውስጥ አንዱ የግል ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ያለበት አግባብ ነው።የይምሰሉ የባለስልጣናት ቡድን በአደባባይ የውጭ ባንኮችን ወደ አገር ቤት ለማስገባት በቅድምያ የአገር ውስጥ ባንኮች መጠንከር አለባቸው ይላል።የውስጥ አመራሩ ደግሞ የግል ባንኮች ከገቢያቸው እስከ 27% ድረስ ለአባይ ቦንድ መግዛት አለባቸው እያለ የባንኮቹን አቅም ያዳክማል። የአደባባዩ አመራር ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች መብራት እና ስልክ ሽጡ ሲሉን አልተቀበልናቸውም ይላል።የውስጥ አመራሩ ግን በመብራት ሥራ ላይ የግል ባለሀብት መግባት ይችላል ይል እና እራሱ ያደራጀውን የግል ባለ ሀብት ቦታውን እንዲይዝ በጎን ይፈቅዳል።
የእዚህ አይነቱ አሰራር ኢትዮጵያ በምን ያህል ደረጃ ለባእዳን እንደተሸጠች ለመለካት በማያዳግት ደረጃ አደጋ ላይ መሆናችንን አመላካች ነው።ከእዚህ ጋር ተያይዞ የግል አለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት ወደ ኢትዮጵያ መግባት በእራሱ ጉዳት ወይንም ጥቅም አለው ብሎ ለመናገር የእራሱ የሆነ የተለያየ አቅጣጫዎችን እና የሌሎች አፍሪካ አገራትን ተሞክሮ አንስቶ መተንተን ስለሚጠይቅ በእርሱ ላይ ሃሳብ ለመስጠት ሌላ ጊዜ መመለሱ ይሻላል።ሆኖም ግን ኢትዮጵያ በአደባባይ ለሕዝቧ፣በአገር ውስጥ ላሉ የግል የገንዘብ ተቋማት እና ለዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ከፊት በተሰለፉ ፖሊስ አውጭ ባልሆኑት ባለስልጣናት እንዲናገሩ የሚደረገው እና በውስጥ መስመር ህወሃት የሚሰራው ሥራ መለያየቱን በትክክል መመልከት ጠቃሚ ነው።
በኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ በውጭ ባንኮች ላይ ያለው ፖሊሲ መቀየሩ በአደባባይ ሳይታወጅ እና በውጭ ያሉ ባንኮችም ፖሊሲው ግራ እንዳጋባቸው በውስጥ መስመር እየገቡ ከህወሃት ጋር በልዩ መስመር እየተደራደሩ አዲስ አበባ ላይ ቢሮ የከፈቱ የውጭ ባንኮች ቁጥር በርክቷል።ቢሮ ሲከፈት ደግሞ ሁለት ስራዎችን ለመስራት ይረዳል።አንዱየተከማቸ ገንዘባቸውን ለማበደር የሚደረጉ የውስጥ ድርድሮችን እና ባለስልጣናትን የማግባባት ሥራ ያቀላጥፉበታል።ሌላው ደግሞ ወደፊት ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ሲገቡ እንዴት የአገር ውስጥ ባንኮችን አሸንፈው ገበያውን እንደሚቆጣጠሩ ያጠኑበታል።ከእዚህ በተረፈ በተለያየ መንገድ ከአገር የሚወጣ የውጭ ምንዛሪ 'እኛጋር አስቀምጡ' ብለው ከባለስልጣናት ጋር ምንም አይነት ድርድር እንደማያደርጉ ተስፋ እናድርጋለን።
በነገራችን ላይ አሁን አዲስ አበባ ላይ ቢሮ እየከፈቱ የሚገኙት ባንኮች ብለን የምናነሳቸው አህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የልማት ባንኮች ማለትም የአፍሪካ ልማት ባንክ፣የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ እና የመሳሰሉትን አይጠቀልልም።እነኝህ በየትኛውም የዓለም ክፍል ቢሮ የሚኖራቸው እና በንግድ ባንክ ደረጃ የሚሰሩ ስራዎች ውስጥ የማይገቡ የልማት ባንኮች ናቸው።አሁን የምንነጋገረው በኢትዮጵያ ያሉትን የግል ባንኮች ሥራ ጋር ተመሳሳይ ሥራ ያላቸው ባንኮች ግልፅ ባልሆነ መንገድ የመግባታቸው አግባብ ላይ ነው።እዚህ ላይ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት የፖሊሲ ለውጥ ኖሮ የኢትዮጵያ ህዝብም ጥቅምና ጉዳቱ ተነግሮት፣የአገር ውስጥ ባንኮችም በግልፅ ተነግሯቸው እና ብሔራዊ ባንክ ግልፅ የሆነ መመሪያ እና ፖሊሲ አውጥቶ የሚገቡ ቢሆን ለአገር ጉዳት ያለው አይመስለኝም።በእርግጥ ከኢትዮጵያ አንፃር የእራሱ የሆነ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም።እስካሁን በሌሎች አፍሪካ አገራት የታየው ተሞክሮ ብዙ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ክስተቶች ተስተውለውበታል።ባጭሩ ግን አሁንም ሊሰመርበት እና አደገኛ አገባብ ያለው ያለ አንዳች መመርያ እና ፖሊሲ ወይንም ድብቅ ስምምነት እየተስማሙ ቢሮ ስለሚከፍቱት ባንኮች ጉዳይ ነው።
በመጨረሻም እስከ ያዝነው ዓመት ድረስ ብቻ ድምፃቸውን አጥፍተው አዲስ አበባ ላይ ቢሮ የከፈቱ እና የብሔራዊ ባንክ በየትኛው ፖሊሲ ቢሮ እንዲከፍቱ እንደፈቀደ ግልፅ ያልሆኑት የውጭ ዓለም አቀፍ ባንኮች ዝርዝር አይተን ፅሁፌን ልደምድም። እዚህ ላይ ከተዘረዘሩት በላይ ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል።እዚህ ላይ ባንኮቹ በአገር ውስጥ ቢሮ መክፈታቸውን የምንሰማው በውጭ አገር ከሚወጡ ዜናዎች እና አልፎ አልፎ የአገር ውስጥ ጋዜጦች የሚያወጡት ዜና ላይ እንጂ የመንግስት የዜና አውታሮች ለጉዳዩ እንግዳ መሆናቸው በእራሱ አነጋጋሪ ነው።
እስከያዝነው ወር ጥቅምት/2008 ዓም ድረስ በአዲስ አበባ ቢሮ የከፈቱ ዓለም አቀፍ ባንኮች ዝርዝር : -1/ የቱርክ መንግስት ባንክ ''ዚራት ባንክ'' በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ውስጥ ቢሮ የሚከፍት፣
2/ የእንግሊዙ እና ደቡብ አፍሪካ መሰረቱን ያደረገው ''ስታንዳርድ ባንክ'' በአዲስ አበባ ቢሮ የከፈተ፣
3/ የጀርመኑ ግዙፉ ''ኮሜርዝ ባንክ'' በአዲስ አበባ ቢሮ የከፈተ እና
4/ ግዙፉ የአሜሪካ ባንክ ''ሲቲ ባንክ'' በአዲስ አበባ ቢሮ የከፈተ የሚሉት ይጠቀሳሉ።
ባጠቃላይ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ጉዳት ወይንም ጥቅም አለው ብሎ ለመደምደም ማጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም በአገር ውስጥ ያሉ የግል ባንኮች አድገው ድንበር ተሻጋሪ ቢያንስ አፍሪካ ከተሞች ላይ የመድረስ አቅማቸው እንዲጎለብት መንግስት ምን አደረገ? ብሎ መጠየቅ ግን ተገቢ ነው።ባንኮች የአንድ ምጣኔ ሀብት ዋና አነሳቃሽ ሞተሮች ናቸው።የመንግስት ጥበቃ እና እንክብካቤ ይሻሉ።በተቃራኒው በኢትዮጵያ ግን ከባእዳን የተሰጠ ተልኮ እስኪመስል ድረስ በተለያዩ መመሪያዎች እንዲታነቁ ተደርገዋል።እዚህ ላይ በግድ የተጫነባቸው እና በግል ባንኮች ማኅበር ጭምር ክፉኛ የተተቸው የአባይ ቦንድ ግዥ ግዳጅን መጥቀስ ይቻላል።ባንኮቹ እንዲገዙ በግድ የተነገራቸው የአባይ ቦንድ ግዥ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ እና ተወዳዳሪነታቸውን በእጅጉ እንደሚጎዳው ቢገልፁም ሰሚ አላገኙም።
ጉዳያችን GUDAYACHN
ጥቅምት 20/2008 ዓም (Oct.31,2015)
www.gudayachn.com