ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, October 4, 2015

ኮ/ል ባጫ ሁንዴ እና ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ለኢትዮጵያ የሆናችሁላት ሁሉ በልቦናችን ፅላት ላይ ተፅፎ ይኖራል። (የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ)

ኢትዮጵያ ከዓለም ካርታ ላይ ለመፋቅ የሞከሩ የአካባቢም ሆነ የሩቅ ሃገራት በታሪካችን አጋጥመውናል።ዛሬ በብዙ ፈተናም ላይ ሆነን እኛነታችን እንዳይጠፋ ባለፉት ዘመናት እራሳቸውን ለሞት ያቀረቡ ጀግኖች ባለውለታችን ናቸው።እነኝህ ጀግኖቻችን በሀገራቸው ከእጅ ወደአፍ በሆነች ጡረታ በችግር ላይ የሚገኙ ብዙዎች አሉ።የቀሩት ደግሞ በስደት እየተንከራተቱ እራሳቸውን አሳልፈው የሰጡላትን ሀገር በእሩቁ እየናፈቁ ሕይወታቸው ሲያልፍ መስማት ልብ ያደማል።

1/ ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ 

ኢትዮጵያ በሱማሌ በተወረረችበት ዘመን የአየር ኃይል ጀት አብራሪ ነበሩ።ኢሳት ሰሞኑን ኮሎኔል ባጫን አስመልክቶ ባቀረበው ልዩ የውይይት መርሃ ግብር ላይ ለመረዳት እንደተቻለው ኮሎኔል ባጫ ኢትዮጵያ ከዚያድባሬዋ ሱማሌ ጋር ጦርነት በገጠመችበት ዘመን በ1969 ዓም ትልቅ ገድል የሰሩ ታላቅ ጀግና ነበሩ።ኮ/ል ባጫ በስደት ይኖሩባት ከነበሩት አሜሪካ ሕይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል።የቀብራቸው ስነ ስርዓት ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 22/2008 ዓም እዚያው በምድረ አሜሪካ ፣ሳንፍራንሲስኮ  መፈፀሙ ተሰምቷል።ኢሳት ስለ ኮ/ል ባጫ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ የሰሩትን ጀብዱ በማስመልከት ያደረገው ልዩ ቃለ ምልልስ ለመመልከት ይህንን  ይጫኑ።

ኮ/ል ባጫ ሁንዴ 

2/ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ

በአገር ቤት በማስታወቂያ ሚኒስቴር በኃላም በጦቢያ መፅሄት ''ፀጋዬ ገብረ መድህን አርአያ'' በሚል የብእር ስም እጅግ ጥልቅ የሆነ የፖለቲካ ትንታኔ በመፃፍ ይታወቃሉ።ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ለበርካታ ወጣት ጋዜጠኞች አርአያ የነበሩ እና በምሳሌነት የሚጠቀሱ፣በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን እየቀረቡ በወቅታዊ የሀገራችን፣የአካባቢያችን እና የዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን በመስጠት ይታወቃሉ።ጋዜጠኛ ሙሉጌታ እሁድ መስከረም 23/2008 ዓም በሰላም ውለው በድንገት እቤታቸው ከእዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተሰምቷል።

ሞት ለማንም አይቀርም።ኮ/ል ባጫ ሁንዴም ሆኑ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ዘላለማዊ አይደሉም።ሰው ናቸው እና አንድ ቀን መጠራታቸው አይቀርም ነበር። ይህ የተፈጥሮ ሂደት መሆኑን ማንም አይስተውም።ነገር ግን ይህንን ዓለም ከተሰናበቱት ይልቅ እኛ በቁም ያለነውን ልብ የሚሰብር ጉዳይ አለ።የኢትዮጵያ ጀግኖች፣እራሳቸውን አሳልፈው የሰጡላት ኢትዮጵያ ሀገራቸውን እንደናፈቁ፣የሞቱለት ሕዝብ በሀገሩ ጀግኖቹን ለማወደስ ሳይችል፣ኢትዮጵያ በጎጥ እና አምባገነን ቆፈን ተይዛ እያለ ልጆቿ በባዕድ ሀገር ተንከራተው እዚያው ሲቀበሩ መስማት እጅግ ልብ ያደማል።

ለኮ/ል ባጫ እና ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ እግዚአብሔር እረፍተ ነፍስ ለቤተሰቦቻችው መፅናናትን ይስጥልን።የእናንተ ስደት እና እልፈት አገራችንም ሆነ ሕዝቧም ያለበትን የአደጋ ደረጃ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው።ለኢትዮጵያ የሆናችሁላት ሁሉ በልቦናችን ፅላት ላይ ተፅፎ ይኖራል።
ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ 





ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
መስከረም 24/2008 ዓም (ኦክቶበር 5/2015)

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።