ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, October 23, 2015

''ጉዳያችን'' ጡመራ ከጡመራነት ወደ ድረ-ገፅነት ጉዞ እና ያለፉት አራት አመታት ሂደት አጭር ዳሰሳጉዳያችን ጡመራ ባለፉት አራት አመታት ውስጥ ብዙ ጉዳዮችን ለማንሳት ሞክራለች።ባለፈው ነሐሴ/ 2007 ዓም ጡመራዋ ሙሉ አራት ዓመት ሞላት።ሆኖም ግን ገና በአራት አመቷ፣አራት አመታትን አሳለፍኩ  ብላ ግርግር ለመፍጠር አትደፍርም።ምክንያቱም በድፍረት እና በቁጭት ለመፃፍ ልሞክር እንጂ ብዙ የሚቀሩ እና በሚፈለገው የይዘት እና የጥራት ደረጃ ለአንባብያን እየቀረበ እንዳልሆነ ይሰማኛል።ሆኖም አብሻቂው የአገራችን ፖለቲካ ጤነኛንም ናላ የማዞር አቅም አለው እና ይዘት ላይ ለማተኮር ጊዜ የማይገኝበት ወቅት ነበር።በእዛ ላይ በውጭ አገር ሲኖር ስራው፣ትምህርቱ፣ማኅበራዊ ኑሮው ሁሉ በእራሱ ሌላ የቤት ሥራ ነው።ሆኖም ግን በቀጣዩ ጊዜዎች  ከብሽሽቅ ፖለቲካ የዘለሉ እና የበሰሉ ጉዳዮችን ለማትኮር እሞክራለሁ።ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ተጠርንፋ የተያዘችበት የጎጥ እና የአምባገነንነት ስርዓትን ስህተቶች እየነቀሱ ማቅረብ ችላ የሚባል ጉዳይ ነው ለማለት አይደለም።

ጉዳያችን ባለፉት አራት አመታት ውስጥ  ከ500 በላይ በሆኑ በአብዛኛው በአገራችን ኢትዮጵያ ጉዳይ እና ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ አተኩራ ለአንባብያን አቅርባለች።በእዚህም ወደ ግማሽ ሚልዮን የተጠጋ ጊዜ ከሰሜን አሜሪካ እስከ ኢንዶኔዣ፣ከደቡብ አፍሪካ እስከ ሩስያ የሚደርሱ አንባቢዎች ጎብኝተዋታል። እዚህ ላይ በኢትዮጵያ የሚኖሩ አንባቢዎች ቁጥር ከሰሜን አሜሪካ ቀጥሎ የሚቀመጥ ነው።ይህም ከሁሉ በተሻለ  ያስደስታል።ምክንያቱም በመረጃ እጥረት የሚሰቃየው የአገር ልጅ መረጃ ማግኘቱ በእራሱ አንድ እርካታ ነው።

በመጀመርያ ጡመራውን ለመጀመር ያነሳሱኝ ሁለት ጉዳዮች -አንደኛው፣በድረ-ገፆች ላይ የሚታዩት ሊተኮርባቸው የሚገቡት ማለትም ሊጎሉ (መጉላት) የሚገባቸው ጉዳዮች በአግባቡ አለመጉላታቸው እና ለአንዳንዶች እንደ ግንዛቤ ልካቸው ዝቅ አድርገው ሲመለከቱት በመመልከቴ ሲሆን ሁለተኛው፣ አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው ስርዓት በቀጣይ አመታት ከቀደመው የከፋ ተግባር እንደሚፈፅም በማመኔ ነበር።በእዚህም አንዳንዶች የአገራችንን ፖለቲካ ከሚመለከቱበት የቸል ባይነት አስተያየት ወደ ያገባኛል ስሜት እንደመጡ አጫውተውኛል።ይህ ማለት በጭፍን ስርዓቱን የሚደግፉቱ በምን ያህል ደረጃ እንደሚናደዱብኝ አይገባኝም ማለት አይደለም።ይህ ግን ከቁብ የሚቆጠር አይደለም።ምክንያቱም ጊዜዬን ወስጄ በጡመራው ላይ የሚወጡ ጉዳዮች ሁሉ የማምንባቸው፣ምክንያታዊ እና በማስረጃ የተደገፉ መሆናቸውን እረዳለሁ።ከእዚህ በላይ ፅሁፎቹ  ከጭፍን ጥላቻ አለመሆናቸውን እና ዘመን ተሻግረውም ቢጠየቁ የማያሳፍሩ ባለማስረጃ እንደሆኑ ለእራሴ ለመመለስ እሞክራለሁ።የስርዓቱ ጭፍን ደጋፊዎችም አንድ ቀን አይናቸው እንደሚገለጥ እና ችግሩ የሁላችንም እና በጭፍን የሚደግፉትም ችግር መሆኑን የሚረዱበት ቀን እሩቅ እንደማይሆን ተስፋ አለኝ።

ባለፉት አራት አመታት ውስጥ የኢትዮጵያ የሆኑ ጉዳዮች እንዲነሱ እና ትኩረት እንዲያገኙ ለማድረግ የተሞከረባቸው ሆኖም ግን የተሳኩም ያልተሳኩም ነበሩ።አንዳንዶቹ ጉዳዮች ቢነሱም ትኩረት ሳያገኙ ማለፋቸው የሚቆጩኝ አሉ።ለምሳሌ የኔልሰን ማንዴላን ሕይወት የታደጉት የሻምበል ጉታ ዲንቃ ዜና ለመጀመርያ ጊዜ በሸገር እንደተላለፈ ዜናውን ከሌሎች ድረ-ገፆች በቀዳሚነት በጉዳያችን ላይ ወጥቶ ነበር።በወቅቱም የፃፍኩት  ኔልሰን ማንዴላ በሕይወት እያሉ ሻምበል ጉታ በቶሎ ደቡብ አፍሪካ ቢሄዱ የዓለም ቁጥር አንድ ዜና ይሆናል ኢትዮጵያንም ያስጠራል። የሚል ሃሳብ ነበር።ሻምበል ጉታ የፖሊስ ሰራዊት አባል እንደመሆናቸው መጠን ለኢትዮጵያ ፖሊስ ትልቅ ዝናም ነበር።በሙዚየሙ የሚያስቀምጠው  ፎቶ በኖረው እና የአፍሪካ ፖሊስነታችን በታየ ነበር።''ነበር ለካ እንዲህ ቅርብ ነው'' እንዳሉት ይህ ሳይሆን ቀርቶ ማንዴላ አረፉ።ማንዴላ ሲያርፉ ሻምበል ጉታ እንዲሄዱ (ያውም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አስተባብረው) ተደረገ።ይህ እንግዲህ ከሚቆጨኝ ውስጥ ሲሆን ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ግን ግንዛቤ ሲሰጣቸው እና ሲሰጡ ተመልክቻለሁ።ይህ ማለት ግን ካለምንም ማጋነን ብዙ የሚቀሩ ስራዎች እንዳሉ ከመገንዘብ ጋር ነው።እዚህ ላይ መጥቀስ የምፈልገው የተነሱት ጉዳዮች ጡመራውን ጠቅሰው በድረ-ገፃቸው ላይ የሚያትሙ በርካታ ድረ-ገፆች እና ጡመራዎችን ሳላመሰግን አላልፍም።ይህም አስፈላጊ ጉዳዮች በበለጠ ጎልተው እንዲታዩ እና በሁሉም ዘንድ ትኩረት እንዲያገኙ ለማድረግ በመቻላቸው ነው።አንዳንዶች ደግሞ በጉዳያችን ላይ ፅሁፉ በወጣ በሰአታት ውስጥ የእራሳቸው አስመስለው ስለጥፉት ታይቷል።ይህ እንግዲህ ሌላው ጉድለት ነው።

ባጠቃላይ  ከእዚህ በፊት የነበረው የጉዳያችን አካሄድ አገራዊ ጉዳዮች ትኩረት እንዲያገኙ ማድረግ እና ቢያንስ በእኔ ትውልድ ያለውን ኢትዮጵያዊ ነባራዊ እውነታዎችን እንዲገነዘብ ማድረግ ነበር።ለእዚህም ሲባል የጉዳያችን ያልሆኑ ነገር ግን በሌሎች የተፃፉም ሆኑ የተቀረፁ የድምፅ እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች መጉላት ስላለባቸው ምንጫቸውን እየጠቀስኩ በጡመራዬ ላይ ለማስተናገድ ሞክርያለሁ።ገፁን በተለያዩ አርእስቶች መከፋፈል እና ፅሁፎቹን በእየዘርፋቸው የማሰናዳት ሥራ መሰራት ያለበት መሆኑን እረዳለሁ።ሌላው ገፁ የእንግሊዝኛ ገፅ እንዲኖረው ማድረግ ቀጣይ ስራዎች ናቸው።

በመጨረሻም ጉዳያችንን  ከጡመራ ወደ ድረ-ገፅነት የማሳደጉ ሂደትን እነሆ በአራተኛ አመቷ ተከናውኗል።ይህ ማለት በቀጥታ www.gudayachn.com በመጫን መክፈት ይቻላል ማለት ነው።ከእዚህ በተጨማሪ ጉግል ላይ gudayachn ብሎ በመፃፍ ብቻ መክፈት ሌላው አማራጭ ነው። ድረ-ገፁ አስተማሪ፣የመረጃ ምንጭ፣ በኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በእውቀት ላይ ተመስርቶ ያተኮረ  ለማድረግ ዋናው ግብ ነው።ለእዚህም ብዙ ቅን አእምሮዎች ያስፈልጋሉ እና ሃሳባችሁን ከመስጠት አትቦዝኑ።እስከ አሁን ድረስ በማበረታታት፣ሃሳብ በመስጠትም ሆነ 'እንዲህ በማለቱ ምን ይሆን ይሆን?' እያላችሁ ለተጨነቃችሁ ሁሉ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው። ከሁሉም በላይ ግን ''ማሰብን  የሚሰጥ አምላክ ነው'' እና ይህንን እንዳስብ፣እንድጀምረው እና እንድቀጥል የፈቀደልኝ ልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይግባው።ጉዳያችን በድረ-ገፅነት ትቀጥላለች።


ጉዳያችን GUDAYACHN
ጥቅምት 12/2008 ዓም (Oct.23/2015)
www.gudayachn.com  

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...