ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, October 12, 2015

''ስደት፣ክርስትናና ኢትዮጵያዊነት'' በሚል ርዕስ ልዩ መርሃ ግብር በኦስሎ፣ኖርዌይ ቀረበ፣''ኅዳገ ተዋሕዶ'' የተሰኘች ልዩ መፅሔት ተመርቃለች የመፅሄቷን ይዘት ይዘናል።(ጉዳያችን ልዩ ጥንቅር)



ኅዳገ ተዋሕዶ ሽፋን እና የውስጥ ማውጫ 

በኖርዌይ፣ኦስሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የቅዱስ ገብርኤልና አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ''ስደት ክርስትናና ኢትዮጵያዊነት'' በሚል ርዕስ ያዘጋጀው መርሐ ግብር ብዙ ምዕመናንና ኖርዌጅያን እንግዶች በተገኙበት ቅዳሜ መስከረም 22 ቀን 2008 ዓ/ም (03/10/2015)  በደማቅ ሁኔታ በኦስሎ፣ማየሽቷ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የቅዱስ ገብርኤልና አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ተካሄደ::ከመርሃ ግብሮቹ ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል።እነርሱም፣
  • ሰቆቃወ ጴጥሮስ የሚለው የሎሬንት ፀጋዬ ገ/መድህን መነባንብ  ''እመቤቴ ምነው ኢትዮጵያን ጨቀንሽባት'' የሚለው ክፍል በአርቲስት እንዳለ በቃል ቀርቦ አድናቆትን አትርፏል፣
  • ግጥም በገጣሚት አፎምያ ተደርሶ መድረክ ላይ ቀርቧል፣
  • የሐዲስ አለማየሁ ልብ ወለድ መፅሐፍ ፍቅር እስከ መቃብርን ወደ ኖርወጅኛ የተረጎሙት ዶ/ር ረዱልፍ ሞልቨር ( D/R Redulf Molvær) ከመፅሃፋቸው ጋር መድረክ ላይ ቀርበው ስለመፅሐፉ ማብራርያ ሰጥተዋል፣
  • ''ኅዳገ ተዋሕዶ'' የተሰኘ መፅሄት ልዩ እትም ተመርቋል።መፅሄቱ ካካተታቸው ቁምነገሮች ውስጥ ስለ ቤተክርስቲያኒቱ መሰረተ-እምነት፣የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ባጭሩ፣ስለ ሕፃናት  አስተዳደግ፣የኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር ከአውሮፓውያን የተለየበት ምክንያት፣የምእመናን ድርሻ በቤተ ክርስቲያን ምን መሆን አለበት፣የተሐድሶ እንቅስቃሴ  ምንነት፣ስልት እና እንቅስቃሴ፣ እና የአማርኛ እና ግዕዝ  መንታ ሆሄያት አፃፃፍ የሚገልፅ ልዩ ጥናታዊ ፅሁፍ እና ሌሎች ጠቃሚ አርስቶችን ይዟል፣
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትምህርት፣ ሕግ፣ ማኅበራዊ ሕይወት፣አገር አስተዳደር፣ነፃነት፣እና ጤና እንክብካቤ ዘርፍ ያደረገችው አስተዋፅኦ የሚገልፅ በስላይድ የተደገፈ ገለፃ ቀርቧል፣
  • የኢትዮጵያ ታሪክ ከጥንት እስከ ዛሬ  የሚገልፅ ገለፃ ቀርቧል፣
  • ከምእመናን ምን ይጠበቃል በሚል አርእስት ስር አሁንም በስላይድ የቀረበ አስተማሪ ገለፃ ቀርቧል፣
  • አስተማሪ እና ሁሉንም ያስደመመ ድራማ ታይቷል።

ህዳገ ተዋሕዶ በይፋ በመላከ ብስራት ቆሞስ አባ ሀብተየሱስ ስትመረቅ (ፎቶ ጉዳያችን)

ህዳገ ተዋሕዶ መፅሄት  በውስጧ የያዘችው ፅሁፎች ማውጫ 

በመቀጠልም ለተጋበዙት ኖርዌጅያን እንግዶች  የእንኳን ደህና መጣችህ መልእክት ካስተላለፈ በኋላ የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪክና መሠረተ ክርስትና ባጭሩ ለኖርዌይ እንግዶች ገለፃ ተሰጥቷል። ከተጋባዥ እንግዶች ለመጀመሪያ ጊዜ “ፍቅር እስከ መቃብር” የሚለውን የታዋቂው የሀዲስ ዓለማየሁ መጽሐፍ ወደ ኖርዌጅያን የተረጎሙት ዶ/ር ረዱልፍ ሞልቫር  ስለ ኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ጥራት የመጽሐፉን ገጸ ባህርያት ፊታውራሪ መሸሻ፣በዛብህ፣ጉዱ ካሳ፣ሰብለ ወንጌልን በመጥቀስ አብራርተዋል:: በተለይ የመጨረሻውን የሰብለ ወንጌል፣በዛብህ እና ጉዱ ካሳ መገናኘት እና ሞት እንዲሁም የሰብለ ወንጌልን በምንኩስና ሕይወት ሆና የበዛብህን መቃብር ለጉዱ ካሳ ስታሳይ የሚገልጠው ክፍልን ሲያነሱ እንባ ሲተናነቃቸው ከንግግራቸው መቆራረጥ ይታወቅ ነበር።

“ፍቅር እስከ መቃብር” የሚለውን የታዋቂው የሀዲስ ዓለማየሁ መጽሐፍ ወደ ኖርዌጅያን የተረጎሙት  ኖርዌጅያዊው ዶ/ር ረዱልፍ ሞልቫር ስለ መፅሃፉ ሲናገሩ (ፎቶ ጉዳያችን)

በማስከተለም  በኖርዌይ ኦስሎ ዩኒቨርስቲ የህክምና ፕሮፌሰር የሆኑት ፕሮፌሰር ጉናር አክሰል ብዩነ  ለብዙ ጊዜ በሥራ ምክንያት ኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ የሀገራችን ባህል ምን እንደሚመስል ለመረዳት እንደቻሉ በሰፊው አብራርተዋል:: እንዲሁም ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እምቅ ሀብትና ታሪክ እንዳላት መስክረዋል::ዝግጅቱ የበለጠ እንዲያምር ያደረጉት ሌላው እንግዳ  ጥርት ያለ አማርኛ ተናጋሪ የሆኑትና ለምእመኑ ባቀረቡት የእራሳቸው ድርሰት በሆነ አማርኛ ግጥም ተደጋጋሚ ጭብጨባ የተቸራቸው ሚስተር ሸል ኡስትቢ ነበሩ:: በሚናገሩት አማርኛ ምእመኑን ከማስደመማቸው በተጨማሪ ብዙ እድሜአቸውን ያሳለፉባትን ኢትዮጵያን የማንነታቸው አንዱ ገጽታ እንደሆነ በስሜት አስረድተዋል:: በተለይ እዚህ ሀገር ተወልደው ያደጉም ሆነ በማደጎነት የመጡ ሕጻናት ቅይጥ ባህሪ ይዘው እንደሚያድጉ ይህም ጥሩና መጥፎ ገጽታ ሊኖረው እንደሚችል አስረድተዋል:: ነገር ግን ባህላቸውን መርሳት እንደሌሌባቸውና ወላጆችም ማስተማር እንዳለባቸው መክረዋል:: 

ሚስተር ሸል ኡስትቢ ስደት እና ማንነት ዙርያ ገለፃ ሲያደርጉ (ፎቶ ህንፃ አሰሪ ኮሚቴ ፌስ ቡክ ገፅ)

ከሁሉም የምእመኑን ልብ የነካው ሚስተር ሸል ኡስትቢ በስደት የምንኖረውን ኢትዮጵያዊያንን ሲያፃናኑ ''አውቃለሁ እዚህ ሀገር ስትመጡ ማልቀሳችሁ አይቀርም።ብቸኝነት ከአገር መለየት በእራሱ ያሳዝናል ግን አይዟችሁ'' ብለው ሲናገሩ ነበር።

የደብሩ ታዳጊ ወጣት መዘምራን በፀናፅል  ያሬዳዊ ዜማ ሲያቀርቡ (ፎቶ ህንፃ አሰሪ ኮሚቴ ፌስ ቡክ ገፅ)

የመዘምራኑ ያሬዳዊ ዜማ - 
''እግዚአብሔር ሀበነ ልሳነ ጥበብ፣ከመናእምር ሕጋ ለቤተ ክርስትያን'' የሚል ሲሆን ትርጉሙም ''እግዚአብሔር ሆይ የቤተ ክርስትያንን ሕግ እናውቅ ዘንድ ዕውቀትን ስጠን'' ማለት ነው። 

ሌላው ለዝግጅቱ ልዩ ድምቀት ሰጥቶት የነበረው በአርቲስት ሶስና ግዛው ደራሲነት እና የመድረክ ዝግጅት የቀረበው ተውኔት (ድራማ) ነበር።ተውኔቱ በአንድ ስደት በወጣ አባወራ እና በቤተሰቡ ዙርያ የደረሰውን ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን  ሲሆን ብዙ ምእመናን ከታሪኩ ጠቃሚ ምክር በዘለለ በአሳዛኝ የቤተሰቡ ሁኔታ ሲያለቅሱ ተስተውለዋል።

በመጨረሻም መርሃ ግብሩ  በጸሎት ከመጠናቀቁ በፊት የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብስራት ቆሞስ አባ ሀብተ ኢየሱስ ለገሠ የዕለቱን ዝግጀት በተመለከተ ማጠቃለያ መልእክት አስተላልፈዋል:: በመልዕክታቸውም መርሐ ግብሩ እጅግ አስተማሪ እንደነበር ገልፀው የእዚህ ዓይነት መርሐ ግብሮች በቀጣይነት መዘጋጀት እንዳለባቸው አባታዊ ምክራቸውን ሰጥተዋል::

ማሳሰቢያ - ከእዚህ በላይ የተገኘው ጥንቅር ከሕንፃ አሰሪው ኮሚቴ ፌስ ቡክ  እና ጉዳያችን በአካል ካጠናቀረችው ነው።



ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ጥቅምት 2/2008 ዓም (ኦክቶበር 13/2015)

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።