ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, October 8, 2015

ያጣነው ነፃነታችንን ብቻ አይደለም አገራችንንም ጭምር እንጂ።ኮ/ል ባጫ፣ጋዜጠኛ ሙሉጌታ እና አምባሳደር ዘውዴ አገሩን ባልተነጠቀ ሕዝብ መሃከል አርፈው ቢሆን ኖሮ (የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ)


አገር የሰንደቅ አላማ በምሰሶ ላይ በነፋስ የመወዛወዙ ፋይዳ ብቻ አይደለም።አገር የይስሙላ ምክር ቤት ለምን እንደተሰበሰቡ እና ምን እንደሚሰሩ በማያውቁ ሰዎች ሞልቶ የካሜራ ጋጋታ ከፊታቸው ማርመስመስ አይደለም።

አዎን! ኢትዮጵያውያን በእዚች ሰአት አገራቸውን  በባንዳ እና ለገንዘብ ባደሩ የጊዜው ገዢዎች መነጠቃችንን ለማወቅ ብዙ መመራመር አያስፈልገንም።አገራችንን ያልተነጠቅን ቢሆን ኖሮማ ከሁለት ሚልዮን በላይ ስደተኛ በመላው ዓለም ተበትኖ አይገኝም ነበር።አገራችንን ያልተነጠቅን ቢሆን ኖሮማ ከአፍሪካ የተማረ የሰው ኃይሏን በማሰደድ ቀዳሚ ሀገር መሆናችንን የጎረቤታችን የሱዳን ጋዜጣ አይነግረንም ነበር።አገራችንን ያልተነጠቅን ቢሆን ኖሮ እህቶቻችን የአረብ ሀገር ዘመናዊ ባርነት ባልተዳረጉ ነበር። አገራችንን ያልተነጠቅን ቢሆን ኖሮ ከአፍሪካውያን አቅም ስደተኛ ተብለን መኖርያ የምንለምን አንሆንም ነበር።አገራችንን ያልተነጠቅን ቢሆን ኖሮማ ከመቶሺህ  በላይ ኢትዮጵያውያን ሕፃናት በኢትዮጵያ ከተሞች የጎዳና ተዳዳሪ ሆነው በእየቆሻሻው ላይ የተደፋ ፍርፋሪ ለቀማ ባልተዳረጉ ነበር።አገራችንን ያልተቀማን ቢሆን ኖሮማ በእየዓመቱ ሕፃናት ከእናት አባታቸው ጉያ እየተነጠቁ ለባእዳን በማደጎነት እየተላኩ የዶላር መሰብሰብያ ባልሆኑ ነበር።

አዎን! ያጣነው ነፃነታችንን ብቻ አይደለም አገራችንንም ጭምር ነው።

ነፃነታችንን እና አገራችንን የነጠቁን እና አምባገነንነትን አጥፍተን እኩልነት እናሰፍናለን ብለው ስልጣን ላይ ሲወጡ የከዱን ከሃዲዎች የክህደታቸውን ዳር ለእራሳቸው ደጋፊዎች ግራ እስከሚያጋባ ድረስ ኢትዮጵያን የባእዳን የረከሰ ባህል መፈንጫ፣አንጡራ ሀብቷን በሰንሰለት ለተሳሰሩት ባንዳ  እያከፋፈሉ የድሃ ድሃ አድርገው የእነርሱን ኪስ እየሞሉ ይሄው ሁለት አስርተ አመታት አለፉ።ሕዝቡን የማደህየታቸው ማሳያ ዛሬ በልቶ ለማደር ምን ያህል ፈታኝ ተግባር እንደሆነ መመልከት በእራሱ በቂ ነው።የአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ አሳፋሪ ደረጃ ደርሷል። መብራት ከአዲስ አበባ አንስታችሁ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል በማንኛውም ጊዜ ይጠፋል።ይልቁንም አንዳንድ ቦታዎች ላይ የእዚህ ፅሁፍ አቅራቢ እንዳለው መረጃ ካለምንም ማጋነን እስከ ሶስት ቀናት ጠፍቶ የሚመጣበት ለእዚህም ሕዝብ ይቅርታ የማይጠየቅባት አገር ነች ኢትዮጵያ።ከሃያ አመታት በፊት መብራት ኃይል በእዚህ አይነት ደረጃ አገልግሎቱን ቀልዶበት አያውቅም ነበር።ከሃያ አመታት በፊት በደርግ ዘመን መብራት ከመጥፋቱ ከ72 ሰዓት በፊት መጥፋቱን በራድዮ እና ቴሌቭዥን ይነገር ነበር። ዛሬ በ21ኛው ክ/ዘመን የደንበኛ ፅንሰ ሃሳብን አፈር ድሜ ያስገቡ የአገራችን እና የነፃነታችን ነጣቂዎች  ለሱዳን እና ለጅቡቲ መብራት እያደሉ ኢትዮጵያን እንድትጨልም ፈርደው እነርሱ ጀነሬተር እያስመጡ ይቸበችቡልን ገቡ። 

ኮ/ል ባጫ ሁንዴ፣ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ እና አምባሳደር ዘውዴ ረታ ነፃነቱን እና አገሩን ባልተነጠቀ ሕዝብ መሃከል አርፈው ቢሆን ኖሮ 


ሰሞኑን ለኢትዮጵያ በጎ የሰሩ ሶስት የታሪክ ፈርጦች ከእዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።እነርሱም ኮ/ል ባጫ ሁንዴ፣ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ እና አምባሳደር ዘውዴ ረታ ናቸው።ኮ/ል ባጫ ሁንዴ ኢትዮጵያ ከዚያድባሬዋ ሱማሌ በ1969 ዓም በተሰነዘረባት ጥቃት በኢትዮጵያ አየር ኃይል በጀት አብራሪነት በጀግንነት ጀብዱ የሰሩ እና ዛሬ በነፃነት እና ካለምንም የታሪክ ጠባሳ አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ ያደረጉን ኩሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው።ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ቀደም ብለው በማስታወቂያ መስርያ ቤት ቀጥለው የመጀመርያው የነፃ ፕሬስ ፈር ቀዳጅ ሆነው በተለይ ''ሰው ማለት ሰው የሆነ ነው ሰው የጠፋለት'' እንደሚባለው ለኢትዮጵያ የሚናገር ሰው በሌለበት ፈር ቀደው መናገርን፣መፃፍን እና የመፃፍ ኃይል ምን ያህል አምባገነኖችን እንደሚያንቀጠቅጥ ያሳዩ፣አሁን ላሉት ወጣት ጋዜጠኞች መንገድ እና ወኔ ያስተማሩ፣ከእዚህም ሁሉ በላይ እስከ ሕይወታቸው ፍፃሜ ድረስ ስለ ኢትዮጵያ ሲናገሩ ያለፉ የብእር አርበኛ ናቸው።አምባሳደር ዘውዴ ረታ በቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ዘመን በኢትዮጵያ ራድዮ እና ቴሌቭዥን በጋዜጠኝነት፣በማስታወቂያ ሚኒስትር ምክትል ሚኒስትርነት፣በምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ደረጃ አገራቸውን አገልግለዋል።አምባሳደር ዘውዴ ለመጪው ትውልድ ለምርምርም የሚረዱ ''የኤርትራ ጉዳይ''፣''ተፈሪ መኮንን ረዥሙ የስልጣን ጉዞ''፣''የቀዳማዊ ኃ/ስላሴ መንግስት'' የተባሉ መፃህፍቶቻቸው ለትውልድ የተሰሩ ቅርሶች ናቸው።

ወደ ፅሁፌ ዋና ነጥብ ልመለስ።ኮ/ል ባጫ ሁንዴ፣ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ እና አምባሳደር ዘውዴ ረታ ነፃነቱን እና አገሩን ባልተነጠቀ ሕዝብ መሃከል አርፈው ቢሆን ኖሮ የእረፍታቸው ዜና ለኢትዮጵያ እንዴት ይነገር ነበር? ብለን እናስብ።የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በድንገት መርሃ ግብሩን ያቆምና በሰበር ዜናነት የ1969 ዓም የኢትዮጵያ እና የሱማልያ ጦርነትን እያሳየ ኮ/ል ባጫን ፎቶ እያሳየ እረፍታቸውን ባረዳን ነበር።ቀብራቸውንም  በታላቅ ወታደራዊ ሰልፍ እና ከትውልድ ቦታቸው ግንጪ፣ወለጋ በመጡ ፈረሰኞች ከፊት እየመሩ እና የአዲስ አበባ ሕዝብ አጅቦ ቀብራቸው በተፈፀመ ነበር።ጀግና እና ለሀገሩ የሰራ ሲከበር የተመለከተ ወጣት እንደ ጀግናው ለመሆን ይመኛልና የእዚህ አይነት ቀብር በእራሱ ጀግና ወልዶ ያድር ነበር።አገራችንን ተነጥቀን ባይሆን ኖሮ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በቀብሩ ስርዓት ላይ በአዲስ አበባ ሰማዮች ላይ እየተስገመገመ ሲበር ይታይ ነበር።አገር እና ነፃነትን ባንነጠቅ ኖሮ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሚገነባው ሙዚየም ውስጥ የኮ/ል ባጫ እና ሌሎች ጀግና የአየር ኃይሉ ባለ ገድሎች ታሪክ ተዘርዝሮ ለሕዝብ በታየ ነበር።አገር እና ነፃነታችንን ተነጥቀን ባይሆን ኖሮ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ እና አምባሳደር ዘውዴ እንዲህ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን 50ኛ አመቱ ዋዜማ ላይ ሆኖ የቀደሙትን የሚያስብበት ትልቅ አጋጣሚ በሆነለት ነበር።በተለይ አምባሳደር ዘውዴ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ባለፈ የሰሩበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንጋፋው ዲፕሎማት በማረፋቸው ሃዘናችንን እንገልፃለን ብሎ መግለጫ ያወጣ ነበር።

ባጠቃላይ ነፃነታችንን ብቻ ሳይሆን አገራችንንም ጭምር መነጠቃችንን ለማጤን ከላይ የተጠቀሱትን የኢትዮጵያ ውድ ልጆች ከእዚህ ዓለም በሞት መለየት በስልጣን ላይ ያሉት አሁን በኢትዮጵያ ሕዝብ የሚነግዱት አምባገነን ገዢዎች እንዳልሰሙ ዝም የሚሉት ለምን እንደሆነ ይገባን ይሆን? ኮ/ል ባጫ ሁንዴን የዚያድባሬ ቴሌቭዥን ጣቢያ እንዲያመሰግናቸው እና ማረፋቸውን በሃዘን እንዲዘግብ አይጠብቅም።የዛሬዋ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንም ተመሳሳይ ሥራ ሰራ።ስለ አምባሳደር ዘውዴ ረታ ታላላቅ ስራዎች በማመስገን እና እረፍታቸውን በሃዘን እንዲዘግቡ ኢትዮጵያን እንደ አገር የሚጠሉ አገራት የዜና አውታሮች እንዲናገሩ አይጠበቅም።ይልቁንም ጀግኖቹ ኮ/ል ባጫ እና ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ቀብራቸው በሚወዷት አገራቸው አፈር ላይ ሳይሆን በምድረ አሜሪካ ሆነ።ቀብራቸውን ጨምሮ የማለፋቸው ዜና ግን በኢትዮጵያ ስም በተሰየመ መንግስት እና የቴሌቭዥን ጣቢያ ላይ እንደ አንድ አገር ወዳዶች ቀርቶ በውጭ አገር በጎርፍ አደጋ የሞቱ ሰዎች ዜና የሚሰጠውን ሽፋን አለማግኘቱ  ግን እየቆየ የሚያንገበግበንን አንድ  ጉዳይን ያስረግጥልናል።ይሄውም ያጣነው ነፃነታችንን ብቻ ሳይሆን አገራችንንም ጭምር መሆኑን።


ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ጥቅምት 27/2008 ዓም (ኦክቶበር 8/2015)

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።