ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, April 28, 2015

የሰማዕታቱ ሰማዕትነት ለቤተ መንግስቱ እና ቤተ ክህነቱ የመጨረሻው የማስጠንቀቅያ ደወል ነው (የጉዳያችን ልዩ ማስታወሻ)

ለሰማዕታቱ ለቅሶ አዲስ አበባ 

ያለፈው ሳምንት እሁድ ለኢትዮጵያውያን እና ለመላው ዓለም አእምሮ የሚነሳ ግፍ ተፈፀመ። በአክራሪው አይ ኤስ ኤስ ስል ቢላዋ እና የጥይት አረር ሰላሳ ኢትዮያውያን ክርስቲያኖች ሊብያ ውስጥ ሰማዕትነት ተቀበሉ።ይህ መላው ዓለምን ያስደነገጠ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ቀልብ አስቶ ያስለቀሰ ጉዳይ ሌላ ሃዘን ተጨመረበት።ይሄውም ድርጊቱ ለመላው ዓለም የዜና አውታሮች በተለቀቀበት ሚያዝያ  የሰንበት እለት ምሽት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገር ውስጡ ኢቲቪ ዜና ላይ  ስለ ስማዕታቱ ለማየት እና የመንግስት የጉዳዩን አተያይ፣ቀጥሎም ስለሚወሰዱ እርምጃዎች ይናገራል ተብሎ ሲጠበቅ የዕለቱ የመጀመርያ ዜና ሳይሆን ቀረ።ኢቲቪ የቱርክን ውለታ በቀዳሚ ዜናነት በጨርቃ ጨርቅ ምርት እያደረገች ያለችውን፣ቀጥሎ ኮርያ እያለ በሶስተኛ ደረጃ ድርጊቱን  ''አይ ኤስ ኤስ የለቀቀው ዜና'' የሚል ስም ከሰጠው በኃላ ''የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ለመሆናቸው ካይሮ የሚገኘው ኤምባሲያችን እያጣራ ነው'' በሚል ሰማዕታቱ ገና ለሞታቸውም እውቅና እንዳልሰጣቸው ተናገረ።የሚገርመው ይህንኑ ''ኢትዮጵያውያን መሆናቸው እየተጣራ ነው'' የሚለውን አባባል ቤተ ክህነቱም ዘግየት ብሎ ደገመው።ይህ የሆነው የዓለም ታላላቅ የዜና አውታሮች ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ባረጋገጡበት፣ገዳዩ ቡድንም በቪድዮ መልካቸውን እያሳየ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን በገለፀበት እና የሰማዕታቱ ቪድዮ በትትክክል ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን አይደለም እኛ ኢትዮጵያውያን የውጭ ዜጎች በቀላሉ ሊለይ በሚችልበት መንገድ ነበር።

በሚቀጥሉት ቀናት የአዲስ አበባ ሕዝብ ማንም ሳይጠራው በእራሱ ያደረገው ሰልፍ እና ግፈኛውን ፅንፈኛ ቡድን አይ ኤስ ኤስ እና ኢህአዲግ/ወያኔን ያወገዘበት ሰልፍ የገዢዎቻችንን ልብ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሕዝብ ደም መክበራቸውን የዘነጉ የዘመናችን ቅምጥሎች የጥቅም ተጋሪዎችንም ሰውነት አራደ።የሚይዙት የሚጨብጡትን አጡ።የአዲስ አበባ ሕዝብ ''ሉዓላዊነት ማለት በየትኛውም ቦታ የሚገኙ ዜጎችን መብት ማስከበር ማለት ነው!'' የሚል እና ሌሎች መፈክሮችን ይዞ ወደ ቤተ መንግስት ተመመ።ስርዓቱ ሰራዊቱን አሰልፎ ለመግታት ሞከረ።ነገሩ ልመናም ነበረበት።ለተማፅኖ ከቀረበው መባ ውስጥ አንዱ እና ዋናው ''እባካችሁ ነገ ሮብ ሰልፍ ስለምንፈቅድ ያኔ በደንብ መሰልፍ ትችላላችሁ'' የሚል ነበር።ህዝቡ ቤተ መንግስቱን ትቶ ወደ መስቀል አደባባይ እና ዋና ዋና መንገዶች ተመመ።በቀጣዩ ቀን ሮብ ሚያዝያ 14/2007 ዓም አዲስ አበባ ከአስር ዓመት በፊት ሚያዝያ 30፣1997 ዓም ወደነበረችበት የተቃውሞ መልክ ተቀየረች።ያለፈው ሳምንት ግን ከቀድሞው እጅግ በላቀ መልኩ ቁጣ፣ለቅሶ እና እልህ የተቀላቀለበት ነበር።


ፖሊሶች ለሀዘን የወጣውን ወጣት ሲደበድቡ 

ቤተ ክህነቱ

ሰማዕታቱ የህዝብን አይን ይበልጥ ገለጡ፣የመሪዎቻችንን የስብዕና ደረጃ አየንባቸው  

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ የሆኑት በሊብያ ሰማዕትነት የተቀበሉ 30 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ጉዳይ በመንፈሳዊ ሚዛን ሲመዘን የቤተ ክርስቲያኒቱ የ21ኛው ክ/ዘመን መንፈሳዊ ተጋድሎ ውስጥ በወርቅ ቀለም የሚፃፍ ታላቅ የሰማዕትነት ተግባር የፈፀሙ ናቸው።ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሰማዕትነት አዲስ ክስተት አይደለም።በዮዲት ጉዲት፣በግራኝ መሐመድ፣በፋሺሽት ጣልያን የአምስት ዓመት ወረራ፣ባለፉት 24 አመታት በ ደቡባዊ፣ምዕራባዊ እና ምስራቃዊ ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ስፍራዎች እና በጅማ በርካታ ክርስቲያኖች ሰማዕትነት ተቀብለዋል።

ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሰማዕትነት ክብር እንጂ ውርደት አይደለም።ጌጥ እንጂ ጉድፍ አይደለም። የፅናት ምልክት እንጂ የድክመት መገለጫ አይደለም።ይልቁንም በእዚህ ዘመን ያውም በወጣት አማኞቿ በእዚያ በበረሃ ከሳሽ እና ወቃሽ በሌለበት  ለእምነታቸው የታመኑ ምዕመናን ዛሬም በፅናት መቆማቸውን የሚያሳይ ልዩ የተስፋ ችቦ ነው።የቅዱስ ጊዮርጊስን፣የቅዱስ ቂርቆስን እና የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን እና የሌሎች አያሌ ሰማዕታትን የምትዘክር ቤተ ክርስቲያን ሰማዕታቱ  አሁንም የክብር ፈርጦቿ ናቸው።በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን በሰማእታቷ ይበልጥ ትነጥራለች እንጂ ፈፅሞ የኃልዮሽ ጉዞ ምልክት አታሳይም።

ሰማዕታት ዓለምን የሚንጡበት ልዩ መንፈሳዊ ኃይል አላቸው።በ1929 ዓም በፋሽሽት ጣልያን በጥይት የተደበደቡት የአቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት መላ ኢትዮጵያን በአዲስ መንፈስ አስተሳሰረ።ከከተማ እስከ ገጠር ኢትዮጵያውያንን አነጋገረ። ፍርሃት ገፈፈ።ለኢትዮጵያ ነፃነት ኢትዮጵያውያንን አንድ ልብ አደረገ።በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ወዳጆችን አስነሳ።የኢትዮጵያ የታሪክ ተመራማሪ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስ እናት እንግሊዛዊቷ  ሲልቭያ ፓንክረስ ኢትዮጵያን ብላ ከሀገር ሀገር ተንከራተተች።በበረሃ ያሉ የኢትዮጵያ አርበኞች እና  የከተማ የውስጥ አርበኞች በአዲስ መልክ ተነሱ።ስማዕታት መላው አለምን የመናጥ ኃይላቸው ልዩ ነው። የቅዱስ እስጢፋኖስ መወገር ከስምንት ሺህ በላይ የሚሆኑ የጉባዔው ታዳሚዎች ይብሱን በየስፍራው ተበትነው ክርስትናን አፀኑ።የቅዱስ እስጢፋኖስ ስማዕትነት ይብሱን አፅናቸው።የቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ ጴጥሮስ ሰማዕትነትም እንዲሁ መላዋ ሮምን ብሎም አውሮፓን በሃይማኖት አፀና  ከእዚህ ሁሉ አልፎ ክርስትና የሮም ቤተ መንግስትን አንዘፍዝፎ ወደ ክርስትና ቀይሯል።

ዛሬም የዘመን ልዩነት ካልሆነ በቀር  የሰማዕታት ክብርም ሆነ የህዝብን አይን የመግለጥ ፀጋቸውን አይተንበታል።የመሪዎቻችንን የግፍ ዳር አየንባቸው፣ኢትዮጵያ ቤተ መንግስቷ ክፍት መሆኑን፣ውሳኔ የመስጠት ብቻ ሳይሆን ብሔራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን የማይድረዱ ሰዎች ስብስብ መሆኑን ከመቸውም ጊዜ በላይ ወደ አጥንታችን እስኪዘልቅ ድረስ ገባን።ከወጣት እስከ ሕፃን፣ ከህፃን እስከ ሽማግሌ በልበ ሙሉነት ኢትዮጵያን በጎሳ የከፋፈላትን ስርዓት በግልፅ በአደባባይ ''ሌባ ነህ'' አሉት።የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ከእረጅም ዓመታት መተኛት በኃላ የዩንቨርስቲውን ኩሩ ታሪክ ከተጣለበት አቧራውን አራግፈው የቤተ መንግስቱን አጥር ''የሀገር አንበሳ የውጭ ሬሳ'' እያሉ እየዘመሩ አለፉ። እርግጥ ነው።በእዚህ ሁሉ መሃል የስርዓቱ ቅልቦች ካለ አንዳች ርኅራኄ በወጣቶቹ ላይ የዱላ ውርጅብኝ አወረዱባቸው።ቂርቆስ የሚገኘው ሃዘንተኞቹ የተሰበሰቡበት ስፍራ በፖሊሶች ተበተነ።የኢትዮጵያ ልጆች በታሪካቸው ከተፈፀሙት አበይት ግፎች ውስጥ የሚዘከሩ ተግባራት በአዲስ አበባ ተደረገ።እናቶች አለቀሱ።ወጣቶች እግራቸው ተሰበረ፣እጃቸው በፖሊስ ዱላ ተቆለመመ።ሰማዕት በሆኑት ያለቀሰው ሕዝብ ዳግም በእራሱ ሀገር ፖሊስ ተደበደበ።በሺህ የሚቆጠሩ ታሰሩ።ወዳልታወቀ ቦታ ተውሰዱ። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክህነት በብዙ የአሰራር ጉድለቶች ሲወቀስ የነበረ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። የአስተዳደር መዋቅር ወጥነት አለመኖር፣ግልፅ የገንዘብ አያያዝ አለመኖር፣ካለ ችሎታችው አገልጋዮችን በማይመጥናቸው ቦታ መመደብ፣የቅዱስ ሲኖዶስ አሰራር እና ደንብ በፓትራሪኩ ጣልቃ ገብነት መበላሸት፣ቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢው ቦታዋን በሁለንተናዊው የሀገሪቱ እንቅስቃሴ አለማግኘት እና ቤተ ክርስቲያን ለተበደሉት፣ፍትህ ላጡት ፣ለታሰሩት እና ለተሰደዱት ድምፅ አልባ መሆኗ ሁሉ የቤተ ክህነቱ ትልቅ የቤት ሥራ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለፈው ሳምንት ያሰማው ድምፅ የመጨረሻ ደወል አይደለም ብሎ የሚከራከር ያለ አይመስለኝም።ቤተ ክህነቱ ከቤተ መንግስቱ ጋር የሚኖረው አግባብነት የሌለው መሞዳሞድ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለብዙ ትችቶች ብቻ ሳይሆን ምመናኗንም ከፍ ወዳለ ቅሬታ መርቶታል።ለችግሩ መፍትሄ ካልተሰጠው ሕዝብ አንድ ቀን በእራሱ ኃይል መፍትሄ እንደሚሰጠው መታወቅ አለበት።የሰማዕታቱ ደም በልቦናው የተቀበረ ምዕመን የኢህአዴግ/ወያኔ ቅልብ ወታደር ይፈራል ማለት ዘበት ነው። አሁንም ግን ቤተ ክህነቱ ይህንን ደውል በውቅቱ ተረድቶ ለማስተካከል መነሳት ካለበት አሁን ነበር።ግን አይመስልም።

ቤተ መንግስቱ 

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ በሕዝብ የታወቁ እና ያልታወቁ ሰማዕትነት የተቀበሉ ኢትዮጵያውያን ቢኖሩም ሕዝብ ክፉኛ ያስደነገጠው የዛሬ አርባ ዓመት በደርግ የተገደሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የወቅቱ ፓትሪያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ ነበሩ።ከእዛ ወዲህ የጅማው የፅንፈኞች በቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን ላይ የፈፀሙት ግድያ እና አሁን በሊብያ የተፈፀመው ዋነኞቹ ናቸው።እዚህ ላይ ኢህአዴግ/ወያኔ  ለሊብያው ጉዳይ የሰጠው ቸልተኝነት ብቻ ሳይሆን አሁን በፅንፈኛው አይ ኤስ ኤስ የተከበቡትን ኢትዮጵያውያውን ክርስቲያኖች ለመርዳትም ምንም አይነት እንቅስቃሴ አለማሳየቱ አሁንም ሕዝብ በመንግስቱ ተስፋ ከቆረጠበት አያሌ ጥፋቶች ጋር ተዳምሮ ዛሬም ትኩስ የሆነ ጉዳይ እንደሆነ አለ።

ማንም ሳያስገድዳቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች ሰልፍ ሲወጡ 

የኢህአዴግ/ወያኔ መንግስት ዘግይቶ የሶስት ቀን ሃዘን ማወጁን ይግለፅ እንጂ ይህንን ያደረገው በሕዝብ ተገዶ መሆኑ የድርግቶቹ ሂደት በእራሳቸው በሚገባ አጋልጠውታል።የኢትዮጵያ ሁኔታ በተለይ ለማንኛውም አደጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ መጋለጧ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ግልፅ ሆኗል።በመንግስትነት የተቀመጠው አካል በሁለት መልክ ይገለጣል።የመጀመርያው መገለጫ ለዜጎቹ ምንም የማያደርግ ባጭሩ ሽባነት (Non-functionality) ሲሆን ሁለተኛው መገለጫው ደግሞ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሳይሆን የጎሳ ዜጋ የሚያውቅ መሆኑ ነው። አሁን ጥያቄው ቤተ ክህነቱም ቤተ መንግሥቱም ቤተ ክህነቱም ያለፈው ሳምንት  የህዝብ እንቅስቃሴ የሚያስተምሩት እና ሹክ የሚሉት ጉዳይ አድርገው ወሰዱት። የመጨረሻ ደውል! ከእዚህ በኃላ ''ቀሚሰ አወላከፈኝ'' የለም።ሕዝብ ከተነሳ የሚመልሰው የለምና። 

ሽባነት (Non-functionality)

ኢህአዴግ/ወያኔ የመንግስት መዋቅሩም ሆነ አጠቃላይ እንቅስቃሴው ወደ ሽባነት (Non-functionality) መቀየሩ በግልፅ ታይቷል።አንድ መንግስት ወደ ሽባነት ሲቀየር የሀገር ውስጥ የፖለቲካ፣የምጣኔ ሀብት እና የማህበራዊ ችግሮችን ሁሉ በጉልበት ብቻ እና ብቻ ለመፍታት ይነሳል።እርግጥ ኢህአዴግ/ወያኔ ይህ በሽታ ከጀመረው መቆየቱ ይታወቃል።በእጅጉ የባሰበት ግን  በ1997 ዓም ምርጫ ክፉኛ ከተመታ በኃላ መሆኑ ይታወቃል።ላለፉት አስር አመታት ምንም የማይሰራ የሽባነት በሽታው አድጎ አሁን በመላው ዓለም ኢትዮጵያውያን በባዕዳን መከራ ሲቀበሉ ምንም ማድረግ የማይችል ተመልካች ወደመሆን መቀየሩ በግልፅ ታይቷል።በሳውዲ አረብያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩኢትዮጵያውያኖች በግፍ ሲባረሩ ጠንከር ያለ መግለጫ ማውጣት አልቻለም።በተመሳሳይ መንገድ ሊብያ ለተፈፀመው የግፍ ተግባርም ሆነ በደቡብ አፍሪካ በወገኖቻችን ላይ የተፈፀመውን ሁሉ ከዝምታ ባልተሻለ መልክ ማለፉ ሌላው የሽባ መንግስት መገለጫ ሆነው ቆትይተዋል።

ለጎሳ ዜጋ ቅድምያ የመስጠት አባዜ   

በሊብያ ሰማዕታት ጉዳይ የኢህአዲግ/ወያኔ መንግስት ''ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ላጣራ'' ያለበት ምክንያት እጅግ ታሪካዊ ስህተት የሰራበት ብቻ ሳይሆን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገዛውን ድርጅት ማንነት ለማወቅ የቻለበት ነበር።ምን ያህል ሰብዓዊ አስተሳሰብ የራቃቸው፣ከዓለም አቀፍ መረጃ የራቁ፣እንደመንግስት አይደለም እንደ አንድ የቤተሰብ አስተዳዳሪ በፍጥነት ውሳኔ የመስጠት የአቅም ድህነት ላይ ያሉ እና የሚመሩትን ሕዝብ በጥላቻ እና በቂም የሚመለከቱ መሪዎች ኢትዮጵያ እንደተሸከመች ፍንትው ብሎ ታየ።የሚገርመው መንግስት ''ላጣራ'' እያለ ሲያላግጥ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እና ዋይት ሃውስ ድርጊቱን ኮንነው ማዘናቸውን የሚገልፅ መግለጫ አወጡ።ሰማያዊ ፓርቲ ድርጊቱን ኮንኖ የመንግስትን ቸል ባይነት አስምሮ አወገዘ።ምን ይሄ ብቻ የሁለቱ የሟች ቤተሰቦች  ከቤተ መንግስቱ ዝቅ ብሎ ቂርቆስ ሰፈር እያነቡ፣ሕዝቡም ለቅሶ እየደረሰ ነበር።

ይህ ጉዳይ በጣም አስደንጋጭ ነው።መላው ዓለም ስለእኛ ያለቅሳል፣ሃገራት የሃዘን መግለጫ ይልካሉ፣ሃዘንተኞች ለቅሶ ላይ ናቸው፣መንግስት ግን ''ኢትዮጵያዊነታቸውን ገና እያጣራሁ ነው'' አለ።ይህንን ያለው ቪድዮው ለዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከተለቀቀ ከ 16 ሰዓታት በኃላ መሆኑን ልብ በሉ።ይህ ድርጊት ለመጪው ትውልድ አይደለም አሁን ላለነውስ ማን በትክክል ሊያስረዳን ይቻላል።ለምን አንድ መንግስት ነኝ ያለ አካል ዜጎቹን እና ሀገሪቱን በእንዲህ  ያህል ደረጃ ስልጣጣኑን ወዶ ህዝብን ጠልቶ ይገኛል።ለምን? መልሱን ታሪክ በሚገባ ይመረምረዋል።ለጊዜው ግን አንድ ነገር ማለት ይቻላል።ለኢሕአዴግ/ወያኔ ''ኢትዮጵያዊ ዜጋ'' የሚባለው ማን ነው? የሚለውን ጥያቄ ማንሳቱ ብዙውን ምላሽ ያሰጣል። እንደ ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በጎሳ ካልተጠራን እንደማያውቁን አልጠፋንም።ችግሩ በመንግሥትነት የተቀመጠው አካልም በእራሱ በፈጠረው ዓለም ውስጥም ከጎሳውም ''ዜጋ'' የሚለው ስም የተሰጣቸው ትናንሽ ''ልዑላን'' ሃገሩን እንደሞሉት ያስረዳል።ለህወሓት የኪነት ቡድን ለደረሰበት የመኪና አደጋ ከሰበር ዜና ባላነሰ መደናገጥ ዜናውን ያነበበው ኢቲቪ፣''አንድ የቀድሞ ታጋይ አረፉ'' ለሚል ዜና ቀዳሚ ዜናው የሚያደርገው ኢቲቪ፣ለሰላሳ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል ቀዳሚ ዜና ማድረግ አቃተው።ለዚያውም ኢትዮጵያዊነታቸው  አልተረጋገጠም አለን።

ባጠቃላይ 

በሊብያ ሰማዕትነት የተቀበሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በሶስት ቀናት ውስጥ ብዙ ነገሮችን ቀይረዋል።
 • የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር አስጠብቀዋል፣
 • ከሊቅ እስከደቂቅ ልቡ እየነደደ የቤተ ክህነቱ እና የቤተ መንግስቱን ጥፋት ካለ አንዳች ፍራቻ ከማውገዙም በላይ ለማስተካከል ቃል የገባበት ታሪካዊ ኩነት ሆኗል፣
 • ሕዝብ እርስ በርሱ እንዳይፈራራ ፈር ቀዷል፣
 • የችግሩ ምንጭ ውጫዊ ሳይሆን ውስጣዊ ማለትም የገዢው ኢህአዴግ/ወያኔ የተሳሳተ ፖሊሲ እና ስልጣን እንደ  ከረሜላ የጣማቸው የስርዓቱ መዘውሮች መሆኑን ከእዚህ በፊት የደመደመውን ለመጨረሻ ጊዜ አረጋግጧል፣
 • የኢትዮጵያ ሕዝብ ለህሊና በሚከብድ ደረጃ ለኢትዮጵያውያን ስቃይ እና መከራ ልባቸው የማይደነግጥ በባዕዳን ዘንድም የሌለ የጥላቻ እና የጭካኔ መንፈስ በመሪዎቹ ላይ ተመልክቷል።
 • በባዕድ ሀገር ስደት እና መገፋት ሊገታ የሚችለው ኢትዮጵያ በጎሳ ከፋፍሎ ከሚገዛት የኢህአዲግ/ወያኔ አገዛዝ ነፃ መውጣት ስትችል ብቻ መሆኑን ቀደም ብሎ በለዘብተኛነት የሀገሩን ጉዳይ ስመለከት የነበረው ኢትዮጵያዊ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተረዳበት እና የወሰነበት ጊዜ ነው።ያወቀ እና የወሰነ ሕዝብ ለማታለል መሞከር ደግሞ ብዙ ዋጋ ማስከፈል ብቻ ሳይሆን እንዳይሆኑ ሆኖ መውደቅን ያስከትላላ።
እነኝህ ሁሉ ክስተቶች ሕዝብ የመጨረሻ ጠርዝ ላይ እንደደረሰ በግልፅ አመላክተዋል።ጉዳዩን ኢህአዴግ/ወያኔም ምን ያህል በሕዝብ ታንቅሮ እንደተተፋ በአይኑ አይቷል።በጆሮው ሰምቷል።ይልቁንም በእዚህ ወቅት ብዙዎች ከጎኑ የነበሩ የስርዓቱ አካላት ትተው የሚኮበልሉበት ትክክለኛ ጊዜ መሆኑን ያለፈው ሳምንት ክስተቶች ሁሉ እንዳስተማሯቸው ከግምት በዘለለ መረዳት ይቻላል።አንድ ቀን የቦሌ መንገድም በሕዝብ ይዘጋል።አንድ ቀን ከቤት ሳሉ በሕዝብ ኃይል የመታሰር ዕጣ እንደሚገጥም ደጋፊዎቹ ከግምት የዘለለ እውነታ እየሸተታቸው ነው።ችግሩ ለመፍትሄው እራሳቸውን አንድ አካል ማድረግ እና ወደፊት ከመሄድ ይልቅ በትናንሽ አስተሳሰቦች እየተጠለፉ እራሳቸውን እየደለሉ መገኘታቸው ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ እና ጭላንጭል ማየት የጀመረው አሁን ነው። ያለው አማራጭ አንድ እና አንድ ብቻ መሆኑ በሰማእታቱ ደም ለኢትዮጵያ ሕዝብ  ከመቼውም በበለጠ ተከስቷ።ይሄውም ኢትዮጵያ  ኢትዮጵያዊ መንግስት አሁን በስልጣን ያለውን ስርዓት መቀየር ብቻ ነው።ይህ እንዴት ይሆናል?  የብዙዎች ጥያቄ ነው።መልሱ ብዙም እሩቅ አያስጉዝም በእያንዳንዱ ሰው ኃላፊነት መወጣት የሚል ነው።ሁሉም እንደ ችሎታው ያለበትን ሃገራዊ ኃላፊነት ይወጣ።የእያንዳንዱ ሰው ጠብታ ትልቅ ተራራ ይሰራል።


ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

Sunday, April 26, 2015

አርቲስት ጌትነት እንየው ዶ/ር ቴዎድሮስን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት በተገኙበት በኪነጥበብ ባለሙያዎች የሀዘን መግለጫ ስነ ስርዓት ላይ “እኛው ነን'' በሚል ርዕስ ያቀረበው ግጥም የችግሩን ምንጭ በሚገባ አሳይቶበታል (ቪድዮ እና ሙሉ ስንኙ)

እኛው ነን
============
(በጌትነት እንየው) የግጥሙን ሙሉ ስንኝ ከቪድዮው ስር ያገኙታል) 


እኛው ነን
********
(በጌትነት እንየው)
እኛ ነን; እኛው ነን; እኛ የዛሬዎች
በአጭር የተቀጩ ሩቅ መንገደኞች
ሰላሳ ህልመኞች፣ ሰላሳ ተስፈኞች፣ ሰላሳ ወጣቶች
ሀገር እንደሌለው በሰው ሀገር ምድር ሲቀላ አንገታቸው
ወገን እንደ ሌለው ከሰው ሀገር ባህር ሲቀየጥ ደማቸው
በአገር ቁጭ ብለን ከአለም ጋራ እያየን
ከሬት የመረረ ከቋጥኝ የሚከብድ
ከቶን የሚያቃጥል ከብራቅ የሚያርድ
ሀገር ያህል መርዶ በሰንበት አመሻሽ በአገር የተሸከምን
በገዛ ሞታችን እዝን የተቀመጥን፡፡
ካሳለፍነው ህይወት ካለፈው መከራ
መማር የተሳነን ደመና ወራሾች፣
የሞትነውም እኛ ያለነውም እኛ
ከፋይም ተቀባይ እኛው ነን ባለእዶች፡፡
እኛው ነን….
ከቅጣትም ቅጣት ከመርገምትም መርገት፣
የገዛ አንገታችን በስለት ሲቀላ
የገዛ ደማችን ባህሩን ሲያቀላ
የራሳችንን ሞት ቆሞ መመልከቱ፣
ምን ያህል ነው ፍሙ ምን ያህል ይከብዳል ሰቆቃው እሳቱ?
ምን ያህል ነው ሸክሙ? ምን ያህል ይዘፍቃል? መከራው ክብደቱ
ምን ያህል ይጠልቃል? ምን ያህል ይሰማል? መጠቃት ስለቱ
ሀዘን ነው? ቁጣ ነው? ጸጸት ነው? ምንድነው መጠሪያው? ምንድነው ስሜቱ?
እውን ይህን መአት ይኼን የእኛን መቅሰፍት
ቋንቋዎች በቃላት ችለው ይገልጹታል?
እውን ይህ ስቃይ፣ ይህንን ሰቆቃ፣ እናትና ሀገር ሸክሙን ይችሉታል?
እኛው ነን እኛው ነን…
ለዚህ ክፉ እጣችን ለዚህ መርገምታችን
ለአለም ለፈጣሪ አልፈታ ላለው እንቆቅልሻችን
መነሻም መድረሻም ጥያቄዎች እኛ መልሶችም እኛው ነን፡፡
እኛው ነን የገፋን፣ እኛው ነን የከፋን
እኛው ነን ያጠፋን ፣እኛው ነን ያጠፋን፡፡
ከዘመን ጋር አብሮ መዘመን ተስኖን
ሰፊ አገር ይዘን በሀሳብ እየጠበብን
በፍቅር ተሳስቦ አብሮ መራመዱ አቀበት የሆነን
ቂም እየቆነጠርን፣ ቂም እየመነዘርን
በዛሬ መንጋጋ የትናንቱን ድርቆሽ የምናመነዥክ
በዛሬ ምድጃ የትናንቱን አመድ ታቅፈን የምንሞቅ
ባንድ ላይ ከመጓዝ በየፊና ሩጫ አረፋ ምንደፍቅ
እኛው ነን እኛው ነን….
ከእምነት የተፋታን ከፈጣሪ የራቅን፡፡
እኛው ተጋፊዎች፣ እኛው ተገፊዎች
እኛው አሳዳጆች፣ እኛው ተሳዳጆች
ካሳለፍነው ህይወት ካለፍነው መከራ
መማር የተሳነን ደመና ወራሾች
እኛው ነን እኛው ነን እኛ የዛሬዎች
የነገ፣ የታሪክ ያገር ባለእዳዎች፡፡
እኛው ነን….
በንፍገት በስስት በስግብግብ መዳፍ
ከድሆች ጉሮሮ ካፋቸው መንጭቀን
ሌሎችን ረግጠን ሌሎችን ጨፍልቀን
በሌሎች ጀርባ በሌሎች ጫንቃ ላይ ወደ ላይ መሳቡ ቅንጣት የማይጨንቀን
በማስመሰል ጥበብ በአድርባይ አንደበት በሸፍጥ የሰለጠን
ከብዙዎች ድርሻ ተሻምተን ተናጥቀን
ላንድ ለራሳችን በወርቅ ላይ አልማዝ በህንጻ ላይ ህንጻ
ስንቆልል ስንከምር የማይሰቀጥጠን፣
የመንፈስ ድውዮች የንዋይ ምርከኞች
የወንበር ሱሰኞች የሆድ አምላኪዎች
ከሰውነት ወርደን በነፍስ የኮሰመን የስጋ ብኩኖች
የራሳችን ሀጢያት የራሳችን ሲኦል እኛው ነን መርገምቶች
እኛው ነን!
በዚህ ሁሉ ግና …..
መቼም ቢሆን መቼ ሰው ይሞታል እንጂ ተስፋ አይሞትምና
በመንገድ የቀሩት ወጣቶቻችን
በአጭር የተቀጨው ሀሳብ ምኞታቸው
ተስፋ አለን ተስፋቸው፡፡
በአገራቸው አፈር በታናሾቻቸው
ነገ ውብ ይሆናል ለምልሞ ይጸድቃል በዛሬው ደማቸው
ዛሬ የመከነው ውጥን ርዕያቸው
በጊዜና በአገር ነገ እውን ይሆናል ይፈታል ህልማቸው
ይህ ነው መጽናኛችን ይህ ነው መዕናኛቸው፡፡

ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

Wednesday, April 22, 2015

ኑ! ኢትዮጵያውያን በሙሉ በፍቅር እጅ ለእጅ ተያይዘን ኢትዮጵያን ተባብረን እናንሳት!

ኑ! ኢትዮጵያውያን በሙሉ በፍቅር እጅ ለእጅ ተያይዘን ኢትዮጵያን ተባብረን እናንሳት! ከግፈኞች እጅ እናስጥላት! ለነገው ብሩህ ሕይወት ዛሬ ለእውነት እንቁም! እንነሳ! (ጉዳያችን)

በአደባባይ እንዲህ የደበደባችሁት በእስር ቤት ብታገኙትማ እንዴት ታሰቃዩት ይሆን?  
ፎቶ - በዛሬው ሚያዝያ 14/2007 ሰልፍ ላይ መስቀል አደባባይ የህወሓት ፖሊሶች አንድ ወጣት ሲደበድቡ።


Sunday, April 19, 2015

ልብ የሚሰብር ዜና እስላማዊ አሸባሪ አይ ኤስ ኤስ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን ሊብያ ውስጥ በግፍ አረዳቸው። A heart breaking news: - Terrorist Organisation, ISIS, has released another graphic video showing the mass execution of Ethiopian Christians in Libya.

Another savage act of ISIS.
A heart breaking news.
Terrorist Organisation ISIS has released another graphic video showing the mass execution of 30 Ethiopian Christians in Libya.
ልብ የሚሰብር ዜና 
እስላማዊ አሸባሪ አይ ኤስ ኤስ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን ሊብያ ውስጥ በግፍ አረዳቸው።በጥይት ደበደባቸው። ይሄው ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን ሰልሳ ደቂቃ የፈጀ ኢትዮጵያውያንን ሲቀላ እና  በጥይት ሲፈጅ ደማቸው ወደ ባህር ሲቀላቀል አሳይቷል።ይህ በእንግሊዝኛ እና አረብኛ መግለጫ የሰጠው የአሸባሪ ድርጅቱ ቪድዮ ላይ ''የመስቀል ተከታዮች ከጠላታችን ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን'' የሚል ለጥፎ ተነቧል።


ከወራት በፊት በግብፅ ክርስቲያኖች ላይ ለተፈፀመው ተግባር ግብፅ ሊብያ የሚገኘውን የአሸባሪውን ይዞታ መደብደቧ እና የሃዘን ቀን ማወጇ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ መንግስት የላትም! አዎን የላትም!!!! አሁን ኢትዮጵያውያን በእራሳችን እኛነታችንን እና ኢትዮጵያዊነትን ለማስከበር ከመነሳት ሌላ እንጥፍጣፊ የቀረን ተስፋ የለም! 

ዛሬ ዕሁድ ሚያዝያ 11/2007 ዓም የዓለም የዜና አውታሮች እግረ መንገዴን ካየሁት ውስጥ -ሲኤን ኤን ፣አልጀዚራ የሩስያው ቲቪ ''አርቲ'' እና የግብፅ ዜና አገልግሎትሰላሳ ''ኢትዮጵያውያን'' ልብ በሉ ሁሉም የጠቀሱት ''ኢ ት ዮ ጵ ያ ው ያ ን'' ተገደሉ እያሉ ነው።አራጁ አሸባሪውም ''ኢትዮጵያውያንን'' ቀላሁ እያለ ነው ያቅራራው።
ይህ ይባል እንጂ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በዛሬው እሁድ የምሽት ዜናው ላይ የቀረበው እንዲህ ነበር።በመጀመርያ የኢትዮጵያውያኑ የመቀላት ዜና በቀዳሚ ዜናነት ሳይሆን ከሌላ ዜና በኃላ ዘግይቶ ነበር የተነበበው። 
በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች በሰበርነት ከማውራታቸው ጋር ስታነፃፅሩት ልባችሁ አሲድ ሲረጭ ይሰማችኃል። ቀጥሎ የቀረበው ዜና ላይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ተገደሉ ሳይል ''የተደረገውን ግድያ የኢትዮጵያ መንግስት ያወግዛል'' ይልና ''የሞቱት ኢትዮጵያውያን ለመሆናቸው ካይሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አላረጋገጠም'' በሚል ስሜት አልባ ዜና የአንድ 
ደቂቃው ወሬ ያበቃል።
ይህ እንግዲህ -
1ኛ/ ከላይ የተጠቀሱት እና ሌሎችም ዓለም ዓቀፍ የዜና አውታሮች ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን እየተናገሩ፣ 
2ኛ/ ገዳዩ አሸባሪ ድርጅት እራሱ ኢትዮጵያውያንን ገደልኩ እያለ ያቅራራበትን የ30 ደቂቃ 
ፊልም በአረብኛ እና እንግሊዝኛ የለቀቀው ቪድዮ ኢህአዴግ/ወያኔ እጅ ገብቶ እያለ፣
3ኛ/ ሰማዕትነት የተቀበሉት ወጣቶች አንዳንዶቹን በአይን የምናውቃቸው እስኪመስለን 
ድረስ አይናቸው ሲንከራተት እና የፊት ገፅታቸው ኢትዮጵያዊነታቸውን በግልፅ እያሳየ ነው እንግዲህ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ኢትዮጵያዊነታቸው ሊረጋገጥ ነው የሚለን።
ግን ኢህአዴግ/ወያኔ ለምንድነው በኢትዮጵያውያን ደም የምትቀልዱት???? 
ኢትዮጵያ እኮ ለግብፅ ክርስቲያኖች ለመሰዋት የዘመቱ መሪ የነበራት ሀገር ነች።
ኢትዮጵያ እኮ በየመን ለነበሩ ለናግራን ክርስቲያኖች የዘመቱ መሪዎች የነበሯት ሀገር ነች።
ኢህአዲግ/ወያኔዎች ኢትዮጵያን በእዚህ አይነት ጭካኔ ለምን ታደሟታላችሁ?
ደግሞስ ለእዚህ አይነቱ ሀገራችንን በመላው ዓለም ላስጠራ እኩይ ተግባር በመንግስት ፕሮቶኮል ደረጃስ በቃል አቀባይ ነው የሚነገረው ወይንስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ (ስልጣናቸው ባይጣራም) ደረጃ ነው ለኢትዮጵያ ሕዝብ መገለፅ ያለበት? 
እነዚህ ወገኖች እኮ በሀገራቸው እና በወገናቸው መሃል ሆነው መስራት ቢችሉ ባልተሰደዱ ነበር።እንደሚለፈፍልን አድገን ቢሆን ኖሮ ባልተሰደዱ ነበር።ለሞታቸው ተጠያቂነት ፈፅሞ ንፁህ ነው የሚል አንድም ሰው አይገኝም።
የኢትዮጵያ ህዝብስ ውሳኔህ ምንድነው? ልጆችህን የመጠየቅ ቢያንስ አደባባይ ወጥተህ ስለልጆችህ እና ስለጠፋችው ፈፅማም ልትከስም ስለምታጣጥረው ኢትዮጵያ ማልቀስም አቃተህ?እሪ መንግስት የለንም!!! ማለት አቃተህ??? ምነው አስከሬን ከቤልጅየም በምሽት ተቀብለህ በቦሌ መንገድ አላለቀስቅም ነበር እንዴ? እንደ በግ ለታረዱ ልጆችህ ኡ ኡ ታ! ደረቀብህ? ለምትፈራው ሰው ብቻ ነው የምታለቅሰው?
ኢትዮጵያውያን ሁሉ እግዚአብሔር ያፅናን።


Friday, April 17, 2015

በደቡብ አፍሪካ የሰሞኑ ክስተት የአፍሪካ መንግሥታት ፈጣን እርምጃ እየወሰዱ ነው።በሳውዲ፣ኬንያ፣የመን፣ዛሬ ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን ለደረሰባቸው የኢህአዲግ/ወያኔ ኢትዮጵያ ምን እርምጃ ወሰደች? (የጉዳያችን አጭር የዜና ጥንቅር)


የደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ሚኒስትር ማቴን ንኮናማሻባኔ (Photo-theafricareport.com)

በደቡብ አፍሪካ በያዝነው ሳምንት አጋማሽ ላይ በተለይ በደርባን ከተማ የተፈፀመው የአፍሪካ ሃገራት ተወላጆችን ለይቶ የመግደል፣የመደብደብ እና ንብረታቸውን የመዝረፍ ተግባር በርካታ አፍሪካውያንን በእጅጉ ያሳዘነ ተግባር ሆኖ ሰንብቷል።በተለይ በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው ግፍ በማህበራዊ መገናኛ ድረ-ገፆች ላይ የተለቀቁት ተንቀሳቃሽ ፊልሞች የብዙዎቻችንን ልብ ያደማ ነው።

ዛሬ ዓርብ ታድያ አፍሪካውያን መንግሥታት ድርጊቱን በመቃወም ፈጣን እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን በተግባር እያሳዩ ነው። በእዚሁ መሰረት 


 • ማላዊ እና ዙምባቤ ድርጊቱን በእጅጉ ኮንነው ዜጎቻቸውን ከደቡብ አፍሪካ  ማስወጣት መጀመራቸውን ''ዘ አፍሪኬር ሪፖርት'' አስታወቀ።
 • የናይጀርያ ፓርላማ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ናይጀርያ ጉዳዩን ተቃውማ አምባሳደሯን ወደ ሌጎስ እንድትጠራ ሲል ድምፅ መስጠቱን ''ናይጀርያ ዋች'' ዛሬ ዘግቧል።
 • የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የካቢኔ ጉዳዮች ፀሐፊ አሚና መሐመድ ''ኬንያ በደቡብ አፍሪቃው ግጭት የተጎዳባት ዜጋ ባይኖርም ጉዳዩ ሲስፋፋ ዜጎቻችን ሊጎዱ ይችላሉ እና ልንደርስባቸው የምንችላቸውን ዜጎቻችንን እናስወጣለን'' ሐሙስ እለት ማለታቸውን ሻንጋይ ዴይሊ ፅፏል።
 • የዩጋንዳ መንግስት በኤምባሲው አማካይነት ለዜጎቹ ተከታታይ መረጃ እየሰጠ ነው።የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው ኤምባሲ ማናቸውንም ድጋፍ ለማረግ መዘጋጀቱን ቻይና ዶት ኦርግ  ዘግቧል።
 • ከቀትር በኃላ ደግሞ የደቡብ አፍሪካ መንግስት ፕሪቶርያ የሚገኙ የአፍሪካ ዲፕሎማቶችን ሰብስባ በይፋ ይቅርታ ጠይቃለች።''ዘ አፍሪካን ሪፖርት'' እንደዘገበው የደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ሚኒስትር ማቴን ንኮናማሻባኔ የአፍሪካን ዲፕሎማቶች ይቅርታ ከጠየቁ በኃላ ድርጊቱን የፈፀሙ ሁሉ ለፍርድ እንደሚቀርቡ ቃላቸውን ሰጥተዋል ብሏል። 
 • በሌላ በኩል የናይጀርያው አዲስ ተመራጭ መንግስት ድርጊቱ በ24 ሰዓታት ውስጥ ካልቆመ የደቡብ አፍሪካ የንግድ ማዕከላት በናይጀርያ በሙሉ እንዲዘጉ እንደሚጠይቅ ከወደ ሌጎስ እየተደመጠ ነው።ናይጀርያውያን እና ምስራቅ አፍሪካውያን እንደ ዑጋንዳ ያሉት ሃገራት በቅድምያ ኢላማ ያደርጉታል የሚባለው ታዋቂውን የደቡብ አፍሪካ የሞባይል ስልክ አገልግሎት ሰጪ ''ኤም ቲ ኤን'' መሆኑ እየተሰማ ነው።ኩባንያው አፍሪካ ትልቁ ገበያው ከመሆኗም በላይ በሽርክና የሚሰሩ የአውሮፓ ሃገራት ሌሎቹ ተጎጂዎች የመሆን ዕድል እንዳላቸው እየተነገረ ነው።
እዚህ ላይ የአፍሪካ መንግሥታት ምላሽ ምን ያህል ፈጣን እንደሆነ መመልከት ይቻላል።ኬንያን ብንወስድ የተጎዳ ዜጋ ባይኖርም ዜጎቼን አስወጣለሁ ብላለች።ማላዊ እና ዙምባቤ ባጭር ጊዜ ማስወጣት ጀመሩ።ናይጄርያ አምባሳደሯን ለመጥራት ምክር ቤቷ ወሰነ።ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከመሆኗ አንፃር ጉዳዩን በቀላሉ ማለፍ ማለት ትልቅ ኪሳራ መሆኑ ግልፅ ነው።እስካሁን በሚወጡ መረጃዎች በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አምባሳደር ሙሉጌታ ከሌሎች የኤምባሲው ሰራተኞች ጋር ወደ ደርባን ተጉዘው ኢትዮጵያውያንን ማነጋገራቸውን እና የዙሉ ጎሳ ንጉስ ''ጉድ ዊልን'' ማነጋገራቸውን አፍቃሪ-ኢህአዴግ የሆነው ፋና ራድዮ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ ግን በአፍሪካ ካላት የእረጅም ጊዜ ተፅኖ ፈጣሪነት አንፃር የአምባሳደር ጉብኝት ''አጀብ፣ድንቅ ነው'' የሚባልለት አይደለም።ይህች ለዘመናት በነፃነት የኖረች ሀገር ኢትዮጵያ፣ይህች ለአፍሪካውያን ነፃነት ያላትን ለግሳ ለነፃነት ያበቃች ምድር-ኢትዮጵያ እንደ ሰሞኑ እንደ ደቡብ አፍሪካ ጥቂት ዜጎች ሳይሆኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቿ በሳውዲ አረብያ ሲደበደቡ፣ሲገደሉ እና ሲጋዙ አንዳች አይነት ዲፕሎማሲያዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ሕግን በተከተለ መንገድ እርምጃ አልተወሰደም።ይህ ምን ማለት እንደሆነ እንዴት እንደምንረዳው ያንስብኛል።አፍሪካውያን መንግሥታት በምን አይነት ፍጥነት እንደተንቀሳቀሱ እና እርምጃ እየወሰዱ እንዳሉ ተመልከቱ እና በሳውዲ፣የመን፣ኬንያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እየደረሰባቸው ላለው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምን ያህል የከሸፈ፣ብቃት ያነሰው እና የሃገራዊ ፍቅር ስሜት ቀልብ እንደራቀው መዝኑበት።

ይህ ብቻ አይደለም አዲስ አበባ ወደ ሚገኘው የሳውዲ አረብያ ኤምባሲ ለመቃወም ያመሩትን ወጣቶች የኢህአዲግ/ወያኔ ፖሊስ እንዴት እንደ ባዕድ ዜጋ እንዳባረራቸው አስታውሱ።ሰሞኑን በየመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ለደረሰው አደጋም በብዙ ሺ ኪሎ ሜትሮች እርቀው የሚገኙ  ሃገራት ዜጎቻቸውን ሲያስወጡ።የኢህአዲግ/ወያኔ ኢትዮጵያ ግን በቅርብ እርቀት ላይ ሆና ስለ ዜጎቿ አንዳች ሳትትነፍስ ይሄው ቀናት ነጎዱ። አፍሪካውያን በደቡብ አፍሪካ አንፃር የወሰዱትን እርምጃ አይቶ የኢህአዲግ/ወያኔ  በሳውዲ፣የመን፣ኬንያ እና ዛሬ ደቡብ አፍሪካ ላይ ለደረሰው የወሰደው እርምጃ ባዶነት መመልከት፣ማን፣እንዴት እና በምን እየመራን እንዳለን በአግባቡ ለማጤን ጥሩ ማሳያ ነው።ኢትዮጵያውያን ለእራሳችን መብት ከእኛ ሌላ  ማንም አለመኖሩን ከምር ማወቅ ካለብን አሁን ነው።

ጉዳያችን 
ሚያዝያ 9/2007 ዓም (አፕሪል 17/2015)

Wednesday, April 15, 2015

በኢትዮጵያውያን የተመሰረቱ የግል ባንኮችን ለማቀጨጭ የተሸረበ ሴራ (የጉዳያችን ልዩ ዘገባ)

አዲስ አበባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ህንፃ 

መግቢያ 

በአንድ ሀገር ምጣኔ ሀብት ውስጥ ቁልፍ ሚና ከሚጫወቱት ተቋማት ውስጥ ባንኮች ዋነኞቹ ናቸው።በኢትዮጵያ የዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ከተጀመረ ከአንድ መቶ አመታት በላይ ሆኖታል።ዳግማዊ ምንሊክ ''የሃበሻ ባንክ'' እንዲመሰረት ካደርጉ በኃላ ኢንዱስትሪው ከውጭ የገቡ ባንኮችን ጨምሮ እስከ 1966 ዓም አብዮት ድረስ በጥሩ ደረጃ ላይ ነበረ።ሆኖም ግን በደርግ ዘመነ መንግስት ሁሉም የውጭም ሆኑ የሀገር ውስጥ ባንኮች በመወረሳቸው እና ከሀገር እንዲወጡ በመደረጋቸው በመንግስት ስር የሚገኙት ባንኮች ብቻ በሥራ ላይ እንዲቆዩ ተደረገ።በእዚህም የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ በአካባቢው ካሉ የአፍሪካ ሃገራት ባንኮች አንፃርም በተወዳዳሪነት መቆም ተሳነው።በእዚህ መሃል ከሀገር ውጭ አንድ ቅርንጫፍ ያውም በጅቡቲ ብቻ የነበረው እና በብቸኝነት የሀገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ የተቆጣጠረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ሆነ። ሌሎቹ ማለትም በወቅቱ አጠራር የልማት እና ኢንዱስትሪ ባንክ እና የቤቶች እና ቁጠባ ባንክ በትልልቅ ፕሮጀክቶች እና የቤት ሥራ ብድር ላይ ብቻ ያተኮሩ ሆኑ።በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሁንም ከብዙ ዓመታት በኃላም ከሀገር ውጭ ያለው ቅርንጫው ደቡብ ሱዳን ብቻ ነው።

በደርግ ዘመን ከሶሻሊስቱ ዓለም ጋር ለተወዳጀችው ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል የውጭ ምንዛሪዋን የምታስቀምጥባቸው እንደ የአሜሪካው ''ሲቲ ባንክ'' የእንግሊዙ ''ስታንዳርድ ቻርተር'' እና የጀርመኑ ''ዶቼ'' ባንኮች በብድር አሰጣጥም ላይ ሆነ በ ''ሌተር ኦፍ ክረዲት'' ሰነዶች ሂደት ላይ የእራሳቸውን የሆነ በንግዱ ላይ ተፅኖ የመፍጠር አቅም ነበራቸው።ከእዚህ ሁሉ በኃላ ነበር በ1983 ዓም ከደርግ መውደቅ በኃላ የግል ባንኮች እንደገና የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ ማሟሟቅ የጀመሩት።በቀዳሚነት የአዋሽ ባንክ እና የአቢሲንያ ባንኮች በቀደዱት ገበያውን የማደፋፈር ተግባር በርካቶች ወደ ስራው ተስበዋል።በአሁኑ ወቅት ወደ 16 የሚሆኑ በግል ስም የተመዘገቡ የግል ባንኮች በኢትዮጵያ ይገኛሉ።እዚህ ላይ ኢትዮጵያን በእዚህ ዘርፍ ለየት የሚያደርጋት ከሣሃራ በታች ካሉ ሃገራት በተለየ የማናቸውም የውጭ ሃገራት ባንኮች በሀገሪቱ ውስጥ አለመኖራቸው ነው።እርግጥ ነው የውጭ ባንኮች ወደ ኢንዱስትሪው የመግባት እና አለመግባት ጉዳይ በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ዘንድ አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።

መሰረታቸውን በባህር ማዶ ያደረጉ ባንኮች ወደ ሀገር ቤት ቢገቡ ጥቅም አለው የሚሉ ወገኖች ከሚያነሷቸው ነጥቦች ውስጥ ባንኮቹ ከፍተኛ ካፒታል ከማምጣታቸው በላይ ባንኮቹን ተከትለው በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በሀገር ውስጥ መዋለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ይበረታታሉ የሚል ሲሆን።እዚህ ላይ የሚያሰምሩበት ጉዳይ ባንኮቹ ለኩባንያዎቹ የአማካሪነት ሚናም ጭምር ስለሚጫወቱ ኩባንያዎቹ ከዋስትና ጋር የገቡ ያህል ይሰማቸዋል የሚል ነው።ከእዚህ በተጨማሪ ዘመናዊ አሰራርን እና ቴክኖሎጅንም ለሀገራችን ያመጣሉ ሲሉ ይከራከራሉ።

 በሌላ በኩል የውጭ ባንኮችን መምጣት የሚቃወሙ ባለሙያዎች የሚያሰምሩበት ነጥብ ባንኮቹ የውጭ መዋለ ንዋይ አፍሳሽ ኩባንያዎችን ብቻ ሳይሆን ይዘውት የሚመጡት የተዛባ እና አድሏዊ የንግድ አሰራርን፣ሀገሪቱ በብዙ ልፋት ያገኘችውን የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገራቸው ለማሸሽ አመቺ ሁኔታን ፈጣሪዎች ናቸው ብለው ከመናገራቸውም በላይ መዋለ ንዋያቸውን የሚያፈሱት በዋና ከተሞች ላይ ብቻ ሲሆን ይህም የልማት ክፍፍልን ያዛባል ቆይቶም ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ  መናጋትን ያስከትላል በማለት ይከራከራሉ።እዚህ ላይ ኬንያ፣ታንዛንያ እና ዑጋንዳን ብንመልከት በርካታ የውጭ ሀገር ባንኮች የሀገር ውስጥ ባንኮችን ውጠው ወይንም ጭራሹን አጥፍተው እናገኛቸዋለን።እርግጥ ነው አሁን በምንኖርበት ዓለም የእራስን የገበያ ቦታ ዘግቶ 'መዋለ ንዋይ ቀረ' ብሎ ማላዘን የትም አያደርስም።ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት እና በተገደበ ሕግ ገበያን መክፈት የወቅቱ የዓለማችን ነባራዊ የገበያ ስርዓት መሆኑ አያጠያይቅም።

በኢትዮጵያ የግል ባንኮች ላይ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው አዲስ መመርያ የግል የባንክ ዘርፉን በስርዓቱ የምጣኔ ሀብት መዋቅር ውስጥ የማስገባት ሂደት አካል ነው።

ሰሞኑን የብሔራዊ ባንክ ለግል ባንኮች ያወጣዋል ተብሎ የሚጠበቀው መመርያ በዘርፉ የተሰማሩትን ባንኮች አቅም ያላገናዘበ ብቻ ሳይሆን መጭዎቹንም የማቀጨጭ ተግባር ነው።መመሪያው  በዋናነት ሶስት ነጥቦችን ይይዛል እነርሱም 

1/ የባንኮች መመሥረቻ ካፒታል መጠን አሁን ካለበት 500 ሚሊዮን ብር ወደ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ከፍ ማድረግን፣

2/ የግል ባንኮች ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ያሏቸውን ቅርንጫፎች በ25 በመቶ እንዲያሳድጉ፣

3/ ከተጨማሪዎቹ ቅርንጫፎች ውስጥ ሁለት-ሦስተኛው ከአዲስ አበባ ውጪ መክፈት ይገባቸዋል።የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው።

1/ የባንኮች መመሥረቻ ካፒታል መጠን አሁን ካለበት 500 ሚሊዮን ብር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ከፍ ማድረግን በተመለከተ 


ከላይ ከተጠቀሱት መመርያዎች ውስጥ የመመስረቻ ካፒታል ቀድሞ ከነበረበት ከ100 ሚልዮን ወደ 500 ሚልዮን ብር እንዲያድግ ከተደረገ አመታት ሳያስቆጥር ዛሬ ወደ 1 ቢልዮን ማደግ አለበት መባሉ እንደ ኢትዮጵያ ላለች የግሉ ዘርፍ በከፍተኛ የካፒታል እጥረት በሚሰቃይባት ሀገር ለምን ይህ ታሰበ? ብሎ መጠይቅ ተገቢ ነው።መንግስት ለምጣኔ ሃብቱ ማደግ ከማሰብ ቢሆን ኖሮ በተቻለ መጠን የማይክሮ ፋይናንስ ዘርፍ በጎጥ እና ክልል ከመመስረት ወደ መለስተኛ ባንክ እንዲያድጉ እድሉን በሰጣቸው እና የመመስረቻ ካፒታላቸውንም በእዚያው መጠን ዝቅ አድርገው ጀምረው ቀስ በቀስ እንዲያድጉ ባደረጋቸው ነበር።ይህ ግን አልሆነም። አሁን ግን የተፈለገው የስርዓቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተቀጥላ የሆኑ  ባንኮች (እንደ ወጋገን እና ዳሸን) ያሉ ባንኮች በሀገሪቱ ውስጥ በተንሰራፋው ፍትህ አልባ የንግድ ስርዓት መሰረት በብዙ ዘርፎች የተሰማሩ ኩባንያዎቻቸው ገንዘብ ስለታጨቁ ካፒታልን የማሳደግም ሆነ ሌሎች መሰል ''ግልገል'' ባንኮችን ለመመስረት ችግር ስለሌለባቸው ፖሊሲው እነርሱን እንዲደግፍ ተደርጎ ተቀረፀ።

በአቦይ ስብሐት በአንድ ወቅት ለ''ቪኦኤ'' የአማርኛው አገልግሎት ''በአፍሪካ ግዙፍ የሆነ ኩባንያ እንደ ''ኤፈርት'' ያለ የለም'' ብለው የተናገሩለት 'ኤፈርት' በፍትህ አልባው የንግድ ስርዓት ውስጥ ከመሰሎቹ ጋር እንደፈለገ ስለሚዋኝበት አንድ ቢልዮን የደረሰ የካፒታል ክፍያ የያዘ ባንክ መክፈት ቀላል ነው።በሌላ በኩል በሀገሪቱ ካሉት የወርቅ ማዕድን እስከ የቁም ከብት እና ዕብነ በረድ ወደ ውጭ በመላክ የሚታወቀው ''የሚድሮክ ኢትዮጵያ'' እህት ኩባንያ ''ዳሸን ባንክ'' የካፒታል ጉዳይ ብዙም አይሳስበውም።ምናልባትም ደካማ የግል ባንኮችን ለመግዛት ወይንም ለመዋሃድ ዳሸን እና ወጋገን አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር የታሰበ ጉዳይ ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት የሚሰጡ አሉ።

2/ ቅርንጫፎችን በ25% ማሳደግ እናሁለት-ሶስተኛው ከአዲስ አበባ ውጭ መከፈት አለባቸው የሚለው መመርያን በተመለከተ 

ይህ መመርያ ከላይ ሲመለከቱት ቀና ይመስላል። ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ የሰራው ትልቅ ስህተት ነፃ ገበያን በተመለከተ ባንኮቹ ቅርንጫፍ የምከፍቱትም ሆነ የት እንደሚከፍቱ የሚወስኑት በገበያ ጥናት ዲፓርትመንታቸው በሚሰራ ትልቅ እና ሁሉን አቀፍ ጥናት እንጂ በካድሬ የዘመቻ ሥራ አለመሆኑን ነው።አንድ ባንክ ቅርንጫፍ ሲከፍት ከፍተኛ የሆነ ወጭ የመድባል።ከሰው ኃይል አንስቶ እስከ ህንፃ ክራይ እና ተያያዥ ወጪዎች ሁሉ ይካተታሉ።የቅርንጫፍ እድገት ከባንኮቹ ፖሊሲ እና ስልት (ስትራቴጂ) ጋር በተናበበ መልክ እንጂ ብሔራዊ ባንክ ''ከመጪው ዓመት ጀምሮ 25% አሳድጉ ብሏል'' ተብሎ የሚከፈት ቅርንጫፍ በባንክ ሥራ ውስጥ በየትኛውም ዓለም ታይቶ አይታወቅም።ኢህአዲግ/ወያኔ በባንክ እና በሱቅ በደረቴ መካከል ልዩነት መኖሩን ማወቅ አለበት።በተመሳሳይ መንገድ ሁለት-ሶስተኛው ከአዲስ አበባ ውጭ መከፈት አለበት የሚለውም ከኢትዮጵያ አንፃር  በጣም የተጋነነ ነው።እርግጥ የባንክ ኢንዱስትሪው አዲስ አበባ ብቻ ከተከማቸ ሌላው የሀገሪቱ ክፍል ከአገልግሎቱ የመጠቀም እድሉ ዝቅተኛ ይሆናል።በመሆኑም ከአዲስ አበባ ውጭ መክፈት እንደ ግዴታ ማስቀመጥ ጥቅም አለው። ነገር ግን በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ወደ 4 ሚልዮን ሕዝብ የያዘች እና ከሀገሪቱ አጠቃላይ ንግድ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የምታንቀሳቅስ አዲስ አበባ ላይ መክፈት የምትችሉት አንድ-ሶስተኛውን ቅርንጫፍ ብቻ ነው ብሎ መገደብ ዕውነታውን ያላገናዘበ እና ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ነው።

የግል እና የመንግስት ባንኮች የቅርንጫፍ ስርጭት እና ካፒታል  

ምንጭ -የብሔራዊ ባንክ 2013/2014 አመታዊ ሪፖርት 

ባጠቃላይ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመርያ የነበሩትን የግል ባንኮች የሚያቀጭጭ መጪዎቹ ባንኮች እንዳይመሰረቱ መንገድ የሚዘጋ ብቻ ሳይሆን በፍትህ አልባው የንግድ ስርዓት ውስጥ የስርዓቱ ባንኮች ሌሎችን እንዲያቆረቁዙ የወጣ መመርያ ነው።እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ሌላው ጉዳይ የግል ባንኮቹ ለአባይ ቦንድ በግድ እንዲከፍሉ የሚደረገው የገንዘብ መጠን ብዙዎቹን ባንኮች ያስመረረ በትርፋማነታቸው ላይ የእራሱን የሆነ ጥላ ያጠላ ነው። 


ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ሚያዝያ 7/2007 ዓም (አፕሪል 15/2015)

Sunday, April 12, 2015

በዛሬዋ ሌሊት በመንፈስ ሀገር ቤት ደርሰን ተመለስን።የዘንድሮ የትንሣኤ በዓል አከባበር ኦስሎ (ቪድዮ ክፍል 1)

ምንጭ - በኖርዌይ፣ኦስሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ገብርኤል፣አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ድረ-ገፅ http://www.eotcnor.no/?page_id=118ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

Sunday, April 5, 2015

ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ ስለኢትዮጵያ ያጠኑ፣ኢትዮጵያን የተመለከቱ መፃህፍት እና በርካታ የምርምር ፅሁፎች ያቀረቡ የኢትዮጵያ ታላቅ ወዳጅ አሜሪካዊው ፕሮፌሠር ዶናልድ ሌቪን አረፉ።

እ.ኤ.አቆጣጠር 1931 ዓም በኒው ካስል፣ፔንሰሌቭያ፣አሜሪካ የተወለዱት ፕሮፌሠር ዶናልድ ሌቪን ከሁለት ዓመታት በፊት ከኢሳት ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ -ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

Friday, April 3, 2015

ሆሳዕና በመላው ዓለም በሚገኙ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋኅዶ አብያተ ክርስቲያናት በመጪው ዕሁድ መጋቢት 27/2007 ዓም (አፕሪል 5/2015) በድምቀት ይከበራል።(ቪድዮ)

ሆሳዕና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በኖርዌይ፣ኦስሎ የቅዱስ ገብርኤል እና የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን በመጪው ዕሁድ መጋቢት 27/2007 ዓም (አፕሪል 5/2015) በድምቀት ይከበራል።

On Sunday April 5/2015, Palm sunday (HOSA'ENA) will celebrate in Ethiopian Orthodox Tewahdo St.Gebreal and St.Teklehaymanot church.

Palm søndag ( HOSAENA)  skal feire i Etiopisk Ortodokse Kirke i Norge, Oslo St.Gebreal go St.Teklehaymanot på Søndag 05 April, 2015. Du kan se en av de sixte feiring video (Klikk nedenfor på videoen).
ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

Thursday, April 2, 2015

በቦሌ አየር ማረፊያ በሚስጢር የተመዘገቡ እና ሕጋዊ ውል የሌላቸው በርካታ ድርጅቶች በህገወጥ መንገድ እየነገዱ ነው። ያልተከፈለው የኪራይ ዋጋ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል፣የሚከፍሉት ወርሃዊ ክፍያም የት እንደገባ ሳይታወቅ ገንዘቡ በባለስልጣናት መበላቱ ተጠቁሟል። ለንደን ካፌና ሳተላይት ሬስቶራንትን ይጨምራል።


ምንጭ - ኢሳት (ኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን) መጋቢት 24/2007 ዓም ዜና 

መጋቢት ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢሳት ከታማኝ ምንጮች እንዳረጋገጠው በቦሌ አየር ማረፊያ  በሚስጢር ስም የተመዘገቡና ባለቤታቸው ተለይቶ ያልተመዘገቡ  ድርጅቶች ካለፉት 10 አመታት ጀምሮ የኮንትራት ጊዜያቸውን ሳያድሱ እና የቤት ኪራይ ክፍያቸውን ለመንግስት ገቢ ሳያደርጉ በመነገድ  ላይ ናቸው።በእነዚህ ድርጅቶች ጀርባ የከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እጅ እንዳለበትም ምንጮች ጠቁመዋል።

የኤርፖርቶች ድርጅት ፣ተከራዮችንና ሌሎች የሚመለከታቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚል ምክንያት በየካቲት 1999 ዓም ላይ ኤሮኔቲካል ያልሆኑ የገቢ ምንጮችን ለማስተዳደር የሚል መመሪያ ያወጣ ሲሆን፣ በመመሪያው መሰረትተከራዮቹ በየአምስት አመቱ በግልጽ ጨረታ እንደገና መወዳደር ይጠበቅባቸው ነበር።
ይሁን እንጅ ከእነዚህ መካከል፣8ት ባለቤታቸው የማይታወቅ በኮድ ስም የተመዘገቡ ድርጅቶችን ጨምሮ 15 የንግድ ድርጅቶች   የኮንትራት ጊዜያቸውን ሳያድሱ ፣ የሚከፍሉት ወርሃዊ ክፍያ የት እንደገባ ሳይታወቅ ገንዘቡ በባለስልጣናት መበላቱን ምንጮች ጠቁመዋል።ድርጅቶቹ በ1995 ዓም የኮንትራት ውል የፈረሙ ቢሆንም ፣ በ1999 ዓም በወጣው መመሪያ መሰረት እንደገና አለመመዝገባቸውን፣ ድርጅቶቹን ደፍሮ እንዲመዘገቡ የሚያደርግ አካል መጥፋቱን ምንጮች አክለዋል።
በተርሚናል ቁጥር 2   በኮድ ቁጥር AACS 02 የተመዘገበው ድርጅት፣ የህትመት ውጤቶችን ለመሸጥ በካሬ ሜትር 8 ሺ 100 ብር ክፍያ 54 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ክፍል ተከራይቶ የሚገኝ ሲሆን፣ በአመት 437 ሺ 400 ብር  ሂሳብ የአስር አመትጠቅላላ ክፍያ 4 ሚሊዮን 374 ሺ ብር ፤ በተርሚናል ቁጥር 2 በኮድ ቁጥር AACS 07 Cultural Cusin በሚል የይዞታ አይነት የተመዘገበው ድርጅት በአመት በካሬሜትር 5 ሺ 220 ብር ሂሳብ 54 ካሬ ሜትር ቦታ ቢወስድም የ10 አመታት የኪራይ ክፍያ  2 ሚሊዮን 818 ሺ 800 ብር የት እንደገባ አይታወቅም።
በተርሚናል ቁጥር 2 ለሻንጣ ማሸጊያ በሚል በኮድ ቁጥር AACS 22  የተመዘገበ ድርጅት ለ12 ካሬ ሜትር በአመት በካሬ ሜትር 4 ሺ 100 ሂሳብ በአስር አመት 492 ሺ ብር ለመክፈል ቢዋዋልም ክፍያው የት እንደገባ አልታወቀም።በተርሚናል 2 በኮድ ቁጥር AARS 12  ለካውንተር ሰርቪስ አገልግሎት ተመዝግቦ የሚገኘው ድርጅት 141.31 ካሬ ሜትር ቦታ ወስዶ በካሬሜትር በአመት 4 ፣ 100 ብር በ10 አመታት በአጠቃላይ 5 ሚሊዮን 793 ሺ 710 ብር ክፍያ እንዲሁም በዚሁ ተርሚናል በኮድ ቁጥር AACS 09 የተመዘገበው  የወርቅና ጌጣጌጦች ሱቅ ለያዘው 31.10 ካሬ ሜትር ቦታ በአመት በካሬ ሜትር 8 ሺ 100  ሂሳብ በአስር አመት 2 ሚሊዮን 519 ሺ 100 ብር ክፍያ የት እንደገባ አልታወቀም
በተርሚናል ቁጥር 2 በኮድ ቁጥር AACS 21 ለአበባ መሸጫነት የተከራየው በ25.9 ካሬ ሜትር የሰፈረው ቦታ በአመት በካሬ ሜትር 4 ሺ 100 ብር የሚከፈልበት ቢሆንም የ10 አመታት አመታዊ ክፍያው 1 ሚሊዮን 61 ሺ 900 ብር  እንዲሁም  በኮድ ቁጥር AACS 06  የይዞታዉ መጠን 31.10  ካሬ ሜትር ለብር ጌጣጌጥ/Silver  Shop/   የሚውለው መደብር በአመት በካሬሜትር 8 ሺ 100.00 ብር ተከራይቶ በአስር አመታት ውስጥ 2 ሚሊዮን 519 ሺ 100 ብር ክፍያ የት እንደገባ አይታወቅም።በተርሚናል ቁጥር 2 በኮድ ቁጥር AACS 16 ለሱፐር ማርኬት የተከራየው በ 33.4 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሰፈረው መደብር በአመት 8 ሺ 100 ብር የሚከፈልበት ቢሆንም አመታዊው ክፍያው 2 ሚሊዮን 700 ሺ ብር ከ40 ሳንቲም እንዲሁ የት እንደገባአይታወቅም።
እነዚህን ድርጅቶች በባለቤትነት የሚያስተዳድሩዋቸው ሰዎች በግልጽ ባይታወቁም ምንጮች : ” በህግ የማይጠየቁ የተወሰኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዘመዶችና ቤተሰቦች ናቸው” ይላሉ።በስማቸው ተመዝገበው የሚገኙት የንግድ ድርጅቶችም በአዲሱ መመሪያ መሰረት ውል ሳይገቡ በመነገድ ላይ ሲሆኑ  የሚከፍሉት ክፍያ ከወቅቱ ጋር የማይመጣጠንና ተቆጣጣሪ የሌለባቸው መሆናቸውን ምንጮች ገልጸዋል።በአዲሱ ውል መሰረት ውል ሳይዋዋሉ ለ5 አመታት ያክል በአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በመነገድ ላይ ካሉት ድርጅቶች መካከል ለንደን ካፌና ሳተላይት ሬስቶራንት 109.9 ካሬ ቦታ  በአመት ብር 138 ሺ 474 አላፋራጅ ትሬዲንግ ሃላፊነቱ  የተወሰነ የግል ማህበር ፣የይዞታ መጠን 631 ካሬ ሜትር፣ አመታዊ ክፍያ በካሬ ሜትር 8 ሺ 100 ብር ላሊበላ ወርቅ ቤት፣  31.10 ካሬ ሜትር፣ አመታዊ የክፍያ መጠን በካሬ ሜትር 8 ሺ 100 ብር ሲቲ ቢዝነስ ኮምፒዩተር ፣ 104 ካሬ ሜትር አመታዊ የክፍያ መጠን በካሬ ሜትር 8 ሺ 100 ብር  ድሬ ኢንዱስትሪ ሃ/የተወሰነ የግል ማህበር 54 ካሬ ሜትር አመታዊ የክፍያ መጠን በሄክታር 8 ሺ 100 ህይወት ለማ ትሬዲንግ 31.10 ካሬ ሜትር የክፍያ መጠን በካሬ ሜትር 8 ሺ 100 ብር ሲማት ትሬዲንግ 31.10 ካሬ ሜትር የክፍያ መጠኑ ባከሬ ሜትር 8 ሺ 100 ብር ይገኙበታል።
በአጠቃላይ አዲስ በወጣው መመሪያ መሰረት ህጋዊ ውል ሳይፈርሙ በመስራት ላይ የሚገኙት ደርጅቶች የ10 አመታት የኪራይ ዋጋ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ ኤርፖርቶች ድርጅት እስካሁን እርምጃ ለመውሰድ አለመድፈሩን ምንጮች ገልጸዋል።ጉዳዩ በተደጋጋሚ ለድርጅቱ ቢቀርብም ምላሽ መጥፋቱን ምንጮች አክለው ይገልጻሉ። በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ ኤርፖርት ኢንተርፕራይዝን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ምንጭ - ኢሳት መጋቢት 24/2007 ዓም ዜና