ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, April 15, 2015

በኢትዮጵያውያን የተመሰረቱ የግል ባንኮችን ለማቀጨጭ የተሸረበ ሴራ (የጉዳያችን ልዩ ዘገባ)

አዲስ አበባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ህንፃ 

መግቢያ 

በአንድ ሀገር ምጣኔ ሀብት ውስጥ ቁልፍ ሚና ከሚጫወቱት ተቋማት ውስጥ ባንኮች ዋነኞቹ ናቸው።በኢትዮጵያ የዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ከተጀመረ ከአንድ መቶ አመታት በላይ ሆኖታል።ዳግማዊ ምንሊክ ''የሃበሻ ባንክ'' እንዲመሰረት ካደርጉ በኃላ ኢንዱስትሪው ከውጭ የገቡ ባንኮችን ጨምሮ እስከ 1966 ዓም አብዮት ድረስ በጥሩ ደረጃ ላይ ነበረ።ሆኖም ግን በደርግ ዘመነ መንግስት ሁሉም የውጭም ሆኑ የሀገር ውስጥ ባንኮች በመወረሳቸው እና ከሀገር እንዲወጡ በመደረጋቸው በመንግስት ስር የሚገኙት ባንኮች ብቻ በሥራ ላይ እንዲቆዩ ተደረገ።በእዚህም የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ በአካባቢው ካሉ የአፍሪካ ሃገራት ባንኮች አንፃርም በተወዳዳሪነት መቆም ተሳነው።በእዚህ መሃል ከሀገር ውጭ አንድ ቅርንጫፍ ያውም በጅቡቲ ብቻ የነበረው እና በብቸኝነት የሀገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ የተቆጣጠረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ሆነ። ሌሎቹ ማለትም በወቅቱ አጠራር የልማት እና ኢንዱስትሪ ባንክ እና የቤቶች እና ቁጠባ ባንክ በትልልቅ ፕሮጀክቶች እና የቤት ሥራ ብድር ላይ ብቻ ያተኮሩ ሆኑ።በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሁንም ከብዙ ዓመታት በኃላም ከሀገር ውጭ ያለው ቅርንጫው ደቡብ ሱዳን ብቻ ነው።

በደርግ ዘመን ከሶሻሊስቱ ዓለም ጋር ለተወዳጀችው ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል የውጭ ምንዛሪዋን የምታስቀምጥባቸው እንደ የአሜሪካው ''ሲቲ ባንክ'' የእንግሊዙ ''ስታንዳርድ ቻርተር'' እና የጀርመኑ ''ዶቼ'' ባንኮች በብድር አሰጣጥም ላይ ሆነ በ ''ሌተር ኦፍ ክረዲት'' ሰነዶች ሂደት ላይ የእራሳቸውን የሆነ በንግዱ ላይ ተፅኖ የመፍጠር አቅም ነበራቸው።ከእዚህ ሁሉ በኃላ ነበር በ1983 ዓም ከደርግ መውደቅ በኃላ የግል ባንኮች እንደገና የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ ማሟሟቅ የጀመሩት።በቀዳሚነት የአዋሽ ባንክ እና የአቢሲንያ ባንኮች በቀደዱት ገበያውን የማደፋፈር ተግባር በርካቶች ወደ ስራው ተስበዋል።በአሁኑ ወቅት ወደ 16 የሚሆኑ በግል ስም የተመዘገቡ የግል ባንኮች በኢትዮጵያ ይገኛሉ።እዚህ ላይ ኢትዮጵያን በእዚህ ዘርፍ ለየት የሚያደርጋት ከሣሃራ በታች ካሉ ሃገራት በተለየ የማናቸውም የውጭ ሃገራት ባንኮች በሀገሪቱ ውስጥ አለመኖራቸው ነው።እርግጥ ነው የውጭ ባንኮች ወደ ኢንዱስትሪው የመግባት እና አለመግባት ጉዳይ በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ዘንድ አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።

መሰረታቸውን በባህር ማዶ ያደረጉ ባንኮች ወደ ሀገር ቤት ቢገቡ ጥቅም አለው የሚሉ ወገኖች ከሚያነሷቸው ነጥቦች ውስጥ ባንኮቹ ከፍተኛ ካፒታል ከማምጣታቸው በላይ ባንኮቹን ተከትለው በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በሀገር ውስጥ መዋለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ይበረታታሉ የሚል ሲሆን።እዚህ ላይ የሚያሰምሩበት ጉዳይ ባንኮቹ ለኩባንያዎቹ የአማካሪነት ሚናም ጭምር ስለሚጫወቱ ኩባንያዎቹ ከዋስትና ጋር የገቡ ያህል ይሰማቸዋል የሚል ነው።ከእዚህ በተጨማሪ ዘመናዊ አሰራርን እና ቴክኖሎጅንም ለሀገራችን ያመጣሉ ሲሉ ይከራከራሉ።

 በሌላ በኩል የውጭ ባንኮችን መምጣት የሚቃወሙ ባለሙያዎች የሚያሰምሩበት ነጥብ ባንኮቹ የውጭ መዋለ ንዋይ አፍሳሽ ኩባንያዎችን ብቻ ሳይሆን ይዘውት የሚመጡት የተዛባ እና አድሏዊ የንግድ አሰራርን፣ሀገሪቱ በብዙ ልፋት ያገኘችውን የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገራቸው ለማሸሽ አመቺ ሁኔታን ፈጣሪዎች ናቸው ብለው ከመናገራቸውም በላይ መዋለ ንዋያቸውን የሚያፈሱት በዋና ከተሞች ላይ ብቻ ሲሆን ይህም የልማት ክፍፍልን ያዛባል ቆይቶም ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ  መናጋትን ያስከትላል በማለት ይከራከራሉ።እዚህ ላይ ኬንያ፣ታንዛንያ እና ዑጋንዳን ብንመልከት በርካታ የውጭ ሀገር ባንኮች የሀገር ውስጥ ባንኮችን ውጠው ወይንም ጭራሹን አጥፍተው እናገኛቸዋለን።እርግጥ ነው አሁን በምንኖርበት ዓለም የእራስን የገበያ ቦታ ዘግቶ 'መዋለ ንዋይ ቀረ' ብሎ ማላዘን የትም አያደርስም።ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት እና በተገደበ ሕግ ገበያን መክፈት የወቅቱ የዓለማችን ነባራዊ የገበያ ስርዓት መሆኑ አያጠያይቅም።

በኢትዮጵያ የግል ባንኮች ላይ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው አዲስ መመርያ የግል የባንክ ዘርፉን በስርዓቱ የምጣኔ ሀብት መዋቅር ውስጥ የማስገባት ሂደት አካል ነው።

ሰሞኑን የብሔራዊ ባንክ ለግል ባንኮች ያወጣዋል ተብሎ የሚጠበቀው መመርያ በዘርፉ የተሰማሩትን ባንኮች አቅም ያላገናዘበ ብቻ ሳይሆን መጭዎቹንም የማቀጨጭ ተግባር ነው።መመሪያው  በዋናነት ሶስት ነጥቦችን ይይዛል እነርሱም 

1/ የባንኮች መመሥረቻ ካፒታል መጠን አሁን ካለበት 500 ሚሊዮን ብር ወደ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ከፍ ማድረግን፣

2/ የግል ባንኮች ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ያሏቸውን ቅርንጫፎች በ25 በመቶ እንዲያሳድጉ፣

3/ ከተጨማሪዎቹ ቅርንጫፎች ውስጥ ሁለት-ሦስተኛው ከአዲስ አበባ ውጪ መክፈት ይገባቸዋል።የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው።

1/ የባንኮች መመሥረቻ ካፒታል መጠን አሁን ካለበት 500 ሚሊዮን ብር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ከፍ ማድረግን በተመለከተ 


ከላይ ከተጠቀሱት መመርያዎች ውስጥ የመመስረቻ ካፒታል ቀድሞ ከነበረበት ከ100 ሚልዮን ወደ 500 ሚልዮን ብር እንዲያድግ ከተደረገ አመታት ሳያስቆጥር ዛሬ ወደ 1 ቢልዮን ማደግ አለበት መባሉ እንደ ኢትዮጵያ ላለች የግሉ ዘርፍ በከፍተኛ የካፒታል እጥረት በሚሰቃይባት ሀገር ለምን ይህ ታሰበ? ብሎ መጠይቅ ተገቢ ነው።መንግስት ለምጣኔ ሃብቱ ማደግ ከማሰብ ቢሆን ኖሮ በተቻለ መጠን የማይክሮ ፋይናንስ ዘርፍ በጎጥ እና ክልል ከመመስረት ወደ መለስተኛ ባንክ እንዲያድጉ እድሉን በሰጣቸው እና የመመስረቻ ካፒታላቸውንም በእዚያው መጠን ዝቅ አድርገው ጀምረው ቀስ በቀስ እንዲያድጉ ባደረጋቸው ነበር።ይህ ግን አልሆነም። አሁን ግን የተፈለገው የስርዓቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተቀጥላ የሆኑ  ባንኮች (እንደ ወጋገን እና ዳሸን) ያሉ ባንኮች በሀገሪቱ ውስጥ በተንሰራፋው ፍትህ አልባ የንግድ ስርዓት መሰረት በብዙ ዘርፎች የተሰማሩ ኩባንያዎቻቸው ገንዘብ ስለታጨቁ ካፒታልን የማሳደግም ሆነ ሌሎች መሰል ''ግልገል'' ባንኮችን ለመመስረት ችግር ስለሌለባቸው ፖሊሲው እነርሱን እንዲደግፍ ተደርጎ ተቀረፀ።

በአቦይ ስብሐት በአንድ ወቅት ለ''ቪኦኤ'' የአማርኛው አገልግሎት ''በአፍሪካ ግዙፍ የሆነ ኩባንያ እንደ ''ኤፈርት'' ያለ የለም'' ብለው የተናገሩለት 'ኤፈርት' በፍትህ አልባው የንግድ ስርዓት ውስጥ ከመሰሎቹ ጋር እንደፈለገ ስለሚዋኝበት አንድ ቢልዮን የደረሰ የካፒታል ክፍያ የያዘ ባንክ መክፈት ቀላል ነው።በሌላ በኩል በሀገሪቱ ካሉት የወርቅ ማዕድን እስከ የቁም ከብት እና ዕብነ በረድ ወደ ውጭ በመላክ የሚታወቀው ''የሚድሮክ ኢትዮጵያ'' እህት ኩባንያ ''ዳሸን ባንክ'' የካፒታል ጉዳይ ብዙም አይሳስበውም።ምናልባትም ደካማ የግል ባንኮችን ለመግዛት ወይንም ለመዋሃድ ዳሸን እና ወጋገን አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር የታሰበ ጉዳይ ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት የሚሰጡ አሉ።

2/ ቅርንጫፎችን በ25% ማሳደግ እናሁለት-ሶስተኛው ከአዲስ አበባ ውጭ መከፈት አለባቸው የሚለው መመርያን በተመለከተ 

ይህ መመርያ ከላይ ሲመለከቱት ቀና ይመስላል። ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ የሰራው ትልቅ ስህተት ነፃ ገበያን በተመለከተ ባንኮቹ ቅርንጫፍ የምከፍቱትም ሆነ የት እንደሚከፍቱ የሚወስኑት በገበያ ጥናት ዲፓርትመንታቸው በሚሰራ ትልቅ እና ሁሉን አቀፍ ጥናት እንጂ በካድሬ የዘመቻ ሥራ አለመሆኑን ነው።አንድ ባንክ ቅርንጫፍ ሲከፍት ከፍተኛ የሆነ ወጭ የመድባል።ከሰው ኃይል አንስቶ እስከ ህንፃ ክራይ እና ተያያዥ ወጪዎች ሁሉ ይካተታሉ።የቅርንጫፍ እድገት ከባንኮቹ ፖሊሲ እና ስልት (ስትራቴጂ) ጋር በተናበበ መልክ እንጂ ብሔራዊ ባንክ ''ከመጪው ዓመት ጀምሮ 25% አሳድጉ ብሏል'' ተብሎ የሚከፈት ቅርንጫፍ በባንክ ሥራ ውስጥ በየትኛውም ዓለም ታይቶ አይታወቅም።ኢህአዲግ/ወያኔ በባንክ እና በሱቅ በደረቴ መካከል ልዩነት መኖሩን ማወቅ አለበት።በተመሳሳይ መንገድ ሁለት-ሶስተኛው ከአዲስ አበባ ውጭ መከፈት አለበት የሚለውም ከኢትዮጵያ አንፃር  በጣም የተጋነነ ነው።እርግጥ የባንክ ኢንዱስትሪው አዲስ አበባ ብቻ ከተከማቸ ሌላው የሀገሪቱ ክፍል ከአገልግሎቱ የመጠቀም እድሉ ዝቅተኛ ይሆናል።በመሆኑም ከአዲስ አበባ ውጭ መክፈት እንደ ግዴታ ማስቀመጥ ጥቅም አለው። ነገር ግን በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ወደ 4 ሚልዮን ሕዝብ የያዘች እና ከሀገሪቱ አጠቃላይ ንግድ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የምታንቀሳቅስ አዲስ አበባ ላይ መክፈት የምትችሉት አንድ-ሶስተኛውን ቅርንጫፍ ብቻ ነው ብሎ መገደብ ዕውነታውን ያላገናዘበ እና ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ነው።

የግል እና የመንግስት ባንኮች የቅርንጫፍ ስርጭት እና ካፒታል  

ምንጭ -የብሔራዊ ባንክ 2013/2014 አመታዊ ሪፖርት 

ባጠቃላይ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመርያ የነበሩትን የግል ባንኮች የሚያቀጭጭ መጪዎቹ ባንኮች እንዳይመሰረቱ መንገድ የሚዘጋ ብቻ ሳይሆን በፍትህ አልባው የንግድ ስርዓት ውስጥ የስርዓቱ ባንኮች ሌሎችን እንዲያቆረቁዙ የወጣ መመርያ ነው።እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ሌላው ጉዳይ የግል ባንኮቹ ለአባይ ቦንድ በግድ እንዲከፍሉ የሚደረገው የገንዘብ መጠን ብዙዎቹን ባንኮች ያስመረረ በትርፋማነታቸው ላይ የእራሱን የሆነ ጥላ ያጠላ ነው። 


ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ሚያዝያ 7/2007 ዓም (አፕሪል 15/2015)

No comments: