የደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ሚኒስትር ማቴን ንኮናማሻባኔ (Photo-theafricareport.com)
በደቡብ አፍሪካ በያዝነው ሳምንት አጋማሽ ላይ በተለይ በደርባን ከተማ የተፈፀመው የአፍሪካ ሃገራት ተወላጆችን ለይቶ የመግደል፣የመደብደብ እና ንብረታቸውን የመዝረፍ ተግባር በርካታ አፍሪካውያንን በእጅጉ ያሳዘነ ተግባር ሆኖ ሰንብቷል።በተለይ በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው ግፍ በማህበራዊ መገናኛ ድረ-ገፆች ላይ የተለቀቁት ተንቀሳቃሽ ፊልሞች የብዙዎቻችንን ልብ ያደማ ነው።
ዛሬ ዓርብ ታድያ አፍሪካውያን መንግሥታት ድርጊቱን በመቃወም ፈጣን እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን በተግባር እያሳዩ ነው። በእዚሁ መሰረት
- ማላዊ እና ዙምባቤ ድርጊቱን በእጅጉ ኮንነው ዜጎቻቸውን ከደቡብ አፍሪካ ማስወጣት መጀመራቸውን ''ዘ አፍሪኬር ሪፖርት'' አስታወቀ።
- የናይጀርያ ፓርላማ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ናይጀርያ ጉዳዩን ተቃውማ አምባሳደሯን ወደ ሌጎስ እንድትጠራ ሲል ድምፅ መስጠቱን ''ናይጀርያ ዋች'' ዛሬ ዘግቧል።
- የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የካቢኔ ጉዳዮች ፀሐፊ አሚና መሐመድ ''ኬንያ በደቡብ አፍሪቃው ግጭት የተጎዳባት ዜጋ ባይኖርም ጉዳዩ ሲስፋፋ ዜጎቻችን ሊጎዱ ይችላሉ እና ልንደርስባቸው የምንችላቸውን ዜጎቻችንን እናስወጣለን'' ሐሙስ እለት ማለታቸውን ሻንጋይ ዴይሊ ፅፏል።
- የዩጋንዳ መንግስት በኤምባሲው አማካይነት ለዜጎቹ ተከታታይ መረጃ እየሰጠ ነው።የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው ኤምባሲ ማናቸውንም ድጋፍ ለማረግ መዘጋጀቱን ቻይና ዶት ኦርግ ዘግቧል።
- ከቀትር በኃላ ደግሞ የደቡብ አፍሪካ መንግስት ፕሪቶርያ የሚገኙ የአፍሪካ ዲፕሎማቶችን ሰብስባ በይፋ ይቅርታ ጠይቃለች።''ዘ አፍሪካን ሪፖርት'' እንደዘገበው የደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ሚኒስትር ማቴን ንኮናማሻባኔ የአፍሪካን ዲፕሎማቶች ይቅርታ ከጠየቁ በኃላ ድርጊቱን የፈፀሙ ሁሉ ለፍርድ እንደሚቀርቡ ቃላቸውን ሰጥተዋል ብሏል።
- በሌላ በኩል የናይጀርያው አዲስ ተመራጭ መንግስት ድርጊቱ በ24 ሰዓታት ውስጥ ካልቆመ የደቡብ አፍሪካ የንግድ ማዕከላት በናይጀርያ በሙሉ እንዲዘጉ እንደሚጠይቅ ከወደ ሌጎስ እየተደመጠ ነው።ናይጀርያውያን እና ምስራቅ አፍሪካውያን እንደ ዑጋንዳ ያሉት ሃገራት በቅድምያ ኢላማ ያደርጉታል የሚባለው ታዋቂውን የደቡብ አፍሪካ የሞባይል ስልክ አገልግሎት ሰጪ ''ኤም ቲ ኤን'' መሆኑ እየተሰማ ነው።ኩባንያው አፍሪካ ትልቁ ገበያው ከመሆኗም በላይ በሽርክና የሚሰሩ የአውሮፓ ሃገራት ሌሎቹ ተጎጂዎች የመሆን ዕድል እንዳላቸው እየተነገረ ነው።
እዚህ ላይ የአፍሪካ መንግሥታት ምላሽ ምን ያህል ፈጣን እንደሆነ መመልከት ይቻላል።ኬንያን ብንወስድ የተጎዳ ዜጋ ባይኖርም ዜጎቼን አስወጣለሁ ብላለች።ማላዊ እና ዙምባቤ ባጭር ጊዜ ማስወጣት ጀመሩ።ናይጄርያ አምባሳደሯን ለመጥራት ምክር ቤቷ ወሰነ።ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከመሆኗ አንፃር ጉዳዩን በቀላሉ ማለፍ ማለት ትልቅ ኪሳራ መሆኑ ግልፅ ነው።እስካሁን በሚወጡ መረጃዎች በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አምባሳደር ሙሉጌታ ከሌሎች የኤምባሲው ሰራተኞች ጋር ወደ ደርባን ተጉዘው ኢትዮጵያውያንን ማነጋገራቸውን እና የዙሉ ጎሳ ንጉስ ''ጉድ ዊልን'' ማነጋገራቸውን አፍቃሪ-ኢህአዴግ የሆነው ፋና ራድዮ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ ግን በአፍሪካ ካላት የእረጅም ጊዜ ተፅኖ ፈጣሪነት አንፃር የአምባሳደር ጉብኝት ''አጀብ፣ድንቅ ነው'' የሚባልለት አይደለም።ይህች ለዘመናት በነፃነት የኖረች ሀገር ኢትዮጵያ፣ይህች ለአፍሪካውያን ነፃነት ያላትን ለግሳ ለነፃነት ያበቃች ምድር-ኢትዮጵያ እንደ ሰሞኑ እንደ ደቡብ አፍሪካ ጥቂት ዜጎች ሳይሆኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቿ በሳውዲ አረብያ ሲደበደቡ፣ሲገደሉ እና ሲጋዙ አንዳች አይነት ዲፕሎማሲያዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ሕግን በተከተለ መንገድ እርምጃ አልተወሰደም።ይህ ምን ማለት እንደሆነ እንዴት እንደምንረዳው ያንስብኛል።አፍሪካውያን መንግሥታት በምን አይነት ፍጥነት እንደተንቀሳቀሱ እና እርምጃ እየወሰዱ እንዳሉ ተመልከቱ እና በሳውዲ፣የመን፣ኬንያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እየደረሰባቸው ላለው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምን ያህል የከሸፈ፣ብቃት ያነሰው እና የሃገራዊ ፍቅር ስሜት ቀልብ እንደራቀው መዝኑበት።
ይህ ብቻ አይደለም አዲስ አበባ ወደ ሚገኘው የሳውዲ አረብያ ኤምባሲ ለመቃወም ያመሩትን ወጣቶች የኢህአዲግ/ወያኔ ፖሊስ እንዴት እንደ ባዕድ ዜጋ እንዳባረራቸው አስታውሱ።ሰሞኑን በየመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ለደረሰው አደጋም በብዙ ሺ ኪሎ ሜትሮች እርቀው የሚገኙ ሃገራት ዜጎቻቸውን ሲያስወጡ።የኢህአዲግ/ወያኔ ኢትዮጵያ ግን በቅርብ እርቀት ላይ ሆና ስለ ዜጎቿ አንዳች ሳትትነፍስ ይሄው ቀናት ነጎዱ። አፍሪካውያን በደቡብ አፍሪካ አንፃር የወሰዱትን እርምጃ አይቶ የኢህአዲግ/ወያኔ በሳውዲ፣የመን፣ኬንያ እና ዛሬ ደቡብ አፍሪካ ላይ ለደረሰው የወሰደው እርምጃ ባዶነት መመልከት፣ማን፣እንዴት እና በምን እየመራን እንዳለን በአግባቡ ለማጤን ጥሩ ማሳያ ነው።ኢትዮጵያውያን ለእራሳችን መብት ከእኛ ሌላ ማንም አለመኖሩን ከምር ማወቅ ካለብን አሁን ነው።
ጉዳያችን
ሚያዝያ 9/2007 ዓም (አፕሪል 17/2015)
No comments:
Post a Comment