ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, April 28, 2015

የሰማዕታቱ ሰማዕትነት ለቤተ መንግስቱ እና ቤተ ክህነቱ የመጨረሻው የማስጠንቀቅያ ደወል ነው (የጉዳያችን ልዩ ማስታወሻ)

ለሰማዕታቱ ለቅሶ አዲስ አበባ 

ያለፈው ሳምንት እሁድ ለኢትዮጵያውያን እና ለመላው ዓለም አእምሮ የሚነሳ ግፍ ተፈፀመ። በአክራሪው አይ ኤስ ኤስ ስል ቢላዋ እና የጥይት አረር ሰላሳ ኢትዮያውያን ክርስቲያኖች ሊብያ ውስጥ ሰማዕትነት ተቀበሉ።ይህ መላው ዓለምን ያስደነገጠ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ቀልብ አስቶ ያስለቀሰ ጉዳይ ሌላ ሃዘን ተጨመረበት።ይሄውም ድርጊቱ ለመላው ዓለም የዜና አውታሮች በተለቀቀበት ሚያዝያ  የሰንበት እለት ምሽት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገር ውስጡ ኢቲቪ ዜና ላይ  ስለ ስማዕታቱ ለማየት እና የመንግስት የጉዳዩን አተያይ፣ቀጥሎም ስለሚወሰዱ እርምጃዎች ይናገራል ተብሎ ሲጠበቅ የዕለቱ የመጀመርያ ዜና ሳይሆን ቀረ።ኢቲቪ የቱርክን ውለታ በቀዳሚ ዜናነት በጨርቃ ጨርቅ ምርት እያደረገች ያለችውን፣ቀጥሎ ኮርያ እያለ በሶስተኛ ደረጃ ድርጊቱን  ''አይ ኤስ ኤስ የለቀቀው ዜና'' የሚል ስም ከሰጠው በኃላ ''የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ለመሆናቸው ካይሮ የሚገኘው ኤምባሲያችን እያጣራ ነው'' በሚል ሰማዕታቱ ገና ለሞታቸውም እውቅና እንዳልሰጣቸው ተናገረ።የሚገርመው ይህንኑ ''ኢትዮጵያውያን መሆናቸው እየተጣራ ነው'' የሚለውን አባባል ቤተ ክህነቱም ዘግየት ብሎ ደገመው።ይህ የሆነው የዓለም ታላላቅ የዜና አውታሮች ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ባረጋገጡበት፣ገዳዩ ቡድንም በቪድዮ መልካቸውን እያሳየ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን በገለፀበት እና የሰማዕታቱ ቪድዮ በትትክክል ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን አይደለም እኛ ኢትዮጵያውያን የውጭ ዜጎች በቀላሉ ሊለይ በሚችልበት መንገድ ነበር።

በሚቀጥሉት ቀናት የአዲስ አበባ ሕዝብ ማንም ሳይጠራው በእራሱ ያደረገው ሰልፍ እና ግፈኛውን ፅንፈኛ ቡድን አይ ኤስ ኤስ እና ኢህአዲግ/ወያኔን ያወገዘበት ሰልፍ የገዢዎቻችንን ልብ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሕዝብ ደም መክበራቸውን የዘነጉ የዘመናችን ቅምጥሎች የጥቅም ተጋሪዎችንም ሰውነት አራደ።የሚይዙት የሚጨብጡትን አጡ።የአዲስ አበባ ሕዝብ ''ሉዓላዊነት ማለት በየትኛውም ቦታ የሚገኙ ዜጎችን መብት ማስከበር ማለት ነው!'' የሚል እና ሌሎች መፈክሮችን ይዞ ወደ ቤተ መንግስት ተመመ።ስርዓቱ ሰራዊቱን አሰልፎ ለመግታት ሞከረ።ነገሩ ልመናም ነበረበት።ለተማፅኖ ከቀረበው መባ ውስጥ አንዱ እና ዋናው ''እባካችሁ ነገ ሮብ ሰልፍ ስለምንፈቅድ ያኔ በደንብ መሰልፍ ትችላላችሁ'' የሚል ነበር።ህዝቡ ቤተ መንግስቱን ትቶ ወደ መስቀል አደባባይ እና ዋና ዋና መንገዶች ተመመ።በቀጣዩ ቀን ሮብ ሚያዝያ 14/2007 ዓም አዲስ አበባ ከአስር ዓመት በፊት ሚያዝያ 30፣1997 ዓም ወደነበረችበት የተቃውሞ መልክ ተቀየረች።ያለፈው ሳምንት ግን ከቀድሞው እጅግ በላቀ መልኩ ቁጣ፣ለቅሶ እና እልህ የተቀላቀለበት ነበር።


ፖሊሶች ለሀዘን የወጣውን ወጣት ሲደበድቡ 

ቤተ ክህነቱ

ሰማዕታቱ የህዝብን አይን ይበልጥ ገለጡ፣የመሪዎቻችንን የስብዕና ደረጃ አየንባቸው  

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ የሆኑት በሊብያ ሰማዕትነት የተቀበሉ 30 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ጉዳይ በመንፈሳዊ ሚዛን ሲመዘን የቤተ ክርስቲያኒቱ የ21ኛው ክ/ዘመን መንፈሳዊ ተጋድሎ ውስጥ በወርቅ ቀለም የሚፃፍ ታላቅ የሰማዕትነት ተግባር የፈፀሙ ናቸው።ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሰማዕትነት አዲስ ክስተት አይደለም።በዮዲት ጉዲት፣በግራኝ መሐመድ፣በፋሺሽት ጣልያን የአምስት ዓመት ወረራ፣ባለፉት 24 አመታት በ ደቡባዊ፣ምዕራባዊ እና ምስራቃዊ ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ስፍራዎች እና በጅማ በርካታ ክርስቲያኖች ሰማዕትነት ተቀብለዋል።

ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሰማዕትነት ክብር እንጂ ውርደት አይደለም።ጌጥ እንጂ ጉድፍ አይደለም። የፅናት ምልክት እንጂ የድክመት መገለጫ አይደለም።ይልቁንም በእዚህ ዘመን ያውም በወጣት አማኞቿ በእዚያ በበረሃ ከሳሽ እና ወቃሽ በሌለበት  ለእምነታቸው የታመኑ ምዕመናን ዛሬም በፅናት መቆማቸውን የሚያሳይ ልዩ የተስፋ ችቦ ነው።የቅዱስ ጊዮርጊስን፣የቅዱስ ቂርቆስን እና የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን እና የሌሎች አያሌ ሰማዕታትን የምትዘክር ቤተ ክርስቲያን ሰማዕታቱ  አሁንም የክብር ፈርጦቿ ናቸው።በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን በሰማእታቷ ይበልጥ ትነጥራለች እንጂ ፈፅሞ የኃልዮሽ ጉዞ ምልክት አታሳይም።

ሰማዕታት ዓለምን የሚንጡበት ልዩ መንፈሳዊ ኃይል አላቸው።በ1929 ዓም በፋሽሽት ጣልያን በጥይት የተደበደቡት የአቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት መላ ኢትዮጵያን በአዲስ መንፈስ አስተሳሰረ።ከከተማ እስከ ገጠር ኢትዮጵያውያንን አነጋገረ። ፍርሃት ገፈፈ።ለኢትዮጵያ ነፃነት ኢትዮጵያውያንን አንድ ልብ አደረገ።በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ወዳጆችን አስነሳ።የኢትዮጵያ የታሪክ ተመራማሪ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስ እናት እንግሊዛዊቷ  ሲልቭያ ፓንክረስ ኢትዮጵያን ብላ ከሀገር ሀገር ተንከራተተች።በበረሃ ያሉ የኢትዮጵያ አርበኞች እና  የከተማ የውስጥ አርበኞች በአዲስ መልክ ተነሱ።ስማዕታት መላው አለምን የመናጥ ኃይላቸው ልዩ ነው። የቅዱስ እስጢፋኖስ መወገር ከስምንት ሺህ በላይ የሚሆኑ የጉባዔው ታዳሚዎች ይብሱን በየስፍራው ተበትነው ክርስትናን አፀኑ።የቅዱስ እስጢፋኖስ ስማዕትነት ይብሱን አፅናቸው።የቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ ጴጥሮስ ሰማዕትነትም እንዲሁ መላዋ ሮምን ብሎም አውሮፓን በሃይማኖት አፀና  ከእዚህ ሁሉ አልፎ ክርስትና የሮም ቤተ መንግስትን አንዘፍዝፎ ወደ ክርስትና ቀይሯል።

ዛሬም የዘመን ልዩነት ካልሆነ በቀር  የሰማዕታት ክብርም ሆነ የህዝብን አይን የመግለጥ ፀጋቸውን አይተንበታል።የመሪዎቻችንን የግፍ ዳር አየንባቸው፣ኢትዮጵያ ቤተ መንግስቷ ክፍት መሆኑን፣ውሳኔ የመስጠት ብቻ ሳይሆን ብሔራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን የማይድረዱ ሰዎች ስብስብ መሆኑን ከመቸውም ጊዜ በላይ ወደ አጥንታችን እስኪዘልቅ ድረስ ገባን።ከወጣት እስከ ሕፃን፣ ከህፃን እስከ ሽማግሌ በልበ ሙሉነት ኢትዮጵያን በጎሳ የከፋፈላትን ስርዓት በግልፅ በአደባባይ ''ሌባ ነህ'' አሉት።የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ከእረጅም ዓመታት መተኛት በኃላ የዩንቨርስቲውን ኩሩ ታሪክ ከተጣለበት አቧራውን አራግፈው የቤተ መንግስቱን አጥር ''የሀገር አንበሳ የውጭ ሬሳ'' እያሉ እየዘመሩ አለፉ። እርግጥ ነው።በእዚህ ሁሉ መሃል የስርዓቱ ቅልቦች ካለ አንዳች ርኅራኄ በወጣቶቹ ላይ የዱላ ውርጅብኝ አወረዱባቸው።ቂርቆስ የሚገኘው ሃዘንተኞቹ የተሰበሰቡበት ስፍራ በፖሊሶች ተበተነ።የኢትዮጵያ ልጆች በታሪካቸው ከተፈፀሙት አበይት ግፎች ውስጥ የሚዘከሩ ተግባራት በአዲስ አበባ ተደረገ።እናቶች አለቀሱ።ወጣቶች እግራቸው ተሰበረ፣እጃቸው በፖሊስ ዱላ ተቆለመመ።ሰማዕት በሆኑት ያለቀሰው ሕዝብ ዳግም በእራሱ ሀገር ፖሊስ ተደበደበ።በሺህ የሚቆጠሩ ታሰሩ።ወዳልታወቀ ቦታ ተውሰዱ። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክህነት በብዙ የአሰራር ጉድለቶች ሲወቀስ የነበረ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። የአስተዳደር መዋቅር ወጥነት አለመኖር፣ግልፅ የገንዘብ አያያዝ አለመኖር፣ካለ ችሎታችው አገልጋዮችን በማይመጥናቸው ቦታ መመደብ፣የቅዱስ ሲኖዶስ አሰራር እና ደንብ በፓትራሪኩ ጣልቃ ገብነት መበላሸት፣ቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢው ቦታዋን በሁለንተናዊው የሀገሪቱ እንቅስቃሴ አለማግኘት እና ቤተ ክርስቲያን ለተበደሉት፣ፍትህ ላጡት ፣ለታሰሩት እና ለተሰደዱት ድምፅ አልባ መሆኗ ሁሉ የቤተ ክህነቱ ትልቅ የቤት ሥራ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለፈው ሳምንት ያሰማው ድምፅ የመጨረሻ ደወል አይደለም ብሎ የሚከራከር ያለ አይመስለኝም።ቤተ ክህነቱ ከቤተ መንግስቱ ጋር የሚኖረው አግባብነት የሌለው መሞዳሞድ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለብዙ ትችቶች ብቻ ሳይሆን ምመናኗንም ከፍ ወዳለ ቅሬታ መርቶታል።ለችግሩ መፍትሄ ካልተሰጠው ሕዝብ አንድ ቀን በእራሱ ኃይል መፍትሄ እንደሚሰጠው መታወቅ አለበት።የሰማዕታቱ ደም በልቦናው የተቀበረ ምዕመን የኢህአዴግ/ወያኔ ቅልብ ወታደር ይፈራል ማለት ዘበት ነው። አሁንም ግን ቤተ ክህነቱ ይህንን ደውል በውቅቱ ተረድቶ ለማስተካከል መነሳት ካለበት አሁን ነበር።ግን አይመስልም።

ቤተ መንግስቱ 

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ በሕዝብ የታወቁ እና ያልታወቁ ሰማዕትነት የተቀበሉ ኢትዮጵያውያን ቢኖሩም ሕዝብ ክፉኛ ያስደነገጠው የዛሬ አርባ ዓመት በደርግ የተገደሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የወቅቱ ፓትሪያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ ነበሩ።ከእዛ ወዲህ የጅማው የፅንፈኞች በቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን ላይ የፈፀሙት ግድያ እና አሁን በሊብያ የተፈፀመው ዋነኞቹ ናቸው።እዚህ ላይ ኢህአዴግ/ወያኔ  ለሊብያው ጉዳይ የሰጠው ቸልተኝነት ብቻ ሳይሆን አሁን በፅንፈኛው አይ ኤስ ኤስ የተከበቡትን ኢትዮጵያውያውን ክርስቲያኖች ለመርዳትም ምንም አይነት እንቅስቃሴ አለማሳየቱ አሁንም ሕዝብ በመንግስቱ ተስፋ ከቆረጠበት አያሌ ጥፋቶች ጋር ተዳምሮ ዛሬም ትኩስ የሆነ ጉዳይ እንደሆነ አለ።

ማንም ሳያስገድዳቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች ሰልፍ ሲወጡ 

የኢህአዴግ/ወያኔ መንግስት ዘግይቶ የሶስት ቀን ሃዘን ማወጁን ይግለፅ እንጂ ይህንን ያደረገው በሕዝብ ተገዶ መሆኑ የድርግቶቹ ሂደት በእራሳቸው በሚገባ አጋልጠውታል።የኢትዮጵያ ሁኔታ በተለይ ለማንኛውም አደጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ መጋለጧ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ግልፅ ሆኗል።በመንግስትነት የተቀመጠው አካል በሁለት መልክ ይገለጣል።የመጀመርያው መገለጫ ለዜጎቹ ምንም የማያደርግ ባጭሩ ሽባነት (Non-functionality) ሲሆን ሁለተኛው መገለጫው ደግሞ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሳይሆን የጎሳ ዜጋ የሚያውቅ መሆኑ ነው። አሁን ጥያቄው ቤተ ክህነቱም ቤተ መንግሥቱም ቤተ ክህነቱም ያለፈው ሳምንት  የህዝብ እንቅስቃሴ የሚያስተምሩት እና ሹክ የሚሉት ጉዳይ አድርገው ወሰዱት። የመጨረሻ ደውል! ከእዚህ በኃላ ''ቀሚሰ አወላከፈኝ'' የለም።ሕዝብ ከተነሳ የሚመልሰው የለምና። 

ሽባነት (Non-functionality)

ኢህአዴግ/ወያኔ የመንግስት መዋቅሩም ሆነ አጠቃላይ እንቅስቃሴው ወደ ሽባነት (Non-functionality) መቀየሩ በግልፅ ታይቷል።አንድ መንግስት ወደ ሽባነት ሲቀየር የሀገር ውስጥ የፖለቲካ፣የምጣኔ ሀብት እና የማህበራዊ ችግሮችን ሁሉ በጉልበት ብቻ እና ብቻ ለመፍታት ይነሳል።እርግጥ ኢህአዴግ/ወያኔ ይህ በሽታ ከጀመረው መቆየቱ ይታወቃል።በእጅጉ የባሰበት ግን  በ1997 ዓም ምርጫ ክፉኛ ከተመታ በኃላ መሆኑ ይታወቃል።ላለፉት አስር አመታት ምንም የማይሰራ የሽባነት በሽታው አድጎ አሁን በመላው ዓለም ኢትዮጵያውያን በባዕዳን መከራ ሲቀበሉ ምንም ማድረግ የማይችል ተመልካች ወደመሆን መቀየሩ በግልፅ ታይቷል።በሳውዲ አረብያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩኢትዮጵያውያኖች በግፍ ሲባረሩ ጠንከር ያለ መግለጫ ማውጣት አልቻለም።በተመሳሳይ መንገድ ሊብያ ለተፈፀመው የግፍ ተግባርም ሆነ በደቡብ አፍሪካ በወገኖቻችን ላይ የተፈፀመውን ሁሉ ከዝምታ ባልተሻለ መልክ ማለፉ ሌላው የሽባ መንግስት መገለጫ ሆነው ቆትይተዋል።

ለጎሳ ዜጋ ቅድምያ የመስጠት አባዜ   

በሊብያ ሰማዕታት ጉዳይ የኢህአዲግ/ወያኔ መንግስት ''ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ላጣራ'' ያለበት ምክንያት እጅግ ታሪካዊ ስህተት የሰራበት ብቻ ሳይሆን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገዛውን ድርጅት ማንነት ለማወቅ የቻለበት ነበር።ምን ያህል ሰብዓዊ አስተሳሰብ የራቃቸው፣ከዓለም አቀፍ መረጃ የራቁ፣እንደመንግስት አይደለም እንደ አንድ የቤተሰብ አስተዳዳሪ በፍጥነት ውሳኔ የመስጠት የአቅም ድህነት ላይ ያሉ እና የሚመሩትን ሕዝብ በጥላቻ እና በቂም የሚመለከቱ መሪዎች ኢትዮጵያ እንደተሸከመች ፍንትው ብሎ ታየ።የሚገርመው መንግስት ''ላጣራ'' እያለ ሲያላግጥ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እና ዋይት ሃውስ ድርጊቱን ኮንነው ማዘናቸውን የሚገልፅ መግለጫ አወጡ።ሰማያዊ ፓርቲ ድርጊቱን ኮንኖ የመንግስትን ቸል ባይነት አስምሮ አወገዘ።ምን ይሄ ብቻ የሁለቱ የሟች ቤተሰቦች  ከቤተ መንግስቱ ዝቅ ብሎ ቂርቆስ ሰፈር እያነቡ፣ሕዝቡም ለቅሶ እየደረሰ ነበር።

ይህ ጉዳይ በጣም አስደንጋጭ ነው።መላው ዓለም ስለእኛ ያለቅሳል፣ሃገራት የሃዘን መግለጫ ይልካሉ፣ሃዘንተኞች ለቅሶ ላይ ናቸው፣መንግስት ግን ''ኢትዮጵያዊነታቸውን ገና እያጣራሁ ነው'' አለ።ይህንን ያለው ቪድዮው ለዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከተለቀቀ ከ 16 ሰዓታት በኃላ መሆኑን ልብ በሉ።ይህ ድርጊት ለመጪው ትውልድ አይደለም አሁን ላለነውስ ማን በትክክል ሊያስረዳን ይቻላል።ለምን አንድ መንግስት ነኝ ያለ አካል ዜጎቹን እና ሀገሪቱን በእንዲህ  ያህል ደረጃ ስልጣጣኑን ወዶ ህዝብን ጠልቶ ይገኛል።ለምን? መልሱን ታሪክ በሚገባ ይመረምረዋል።ለጊዜው ግን አንድ ነገር ማለት ይቻላል።ለኢሕአዴግ/ወያኔ ''ኢትዮጵያዊ ዜጋ'' የሚባለው ማን ነው? የሚለውን ጥያቄ ማንሳቱ ብዙውን ምላሽ ያሰጣል። እንደ ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በጎሳ ካልተጠራን እንደማያውቁን አልጠፋንም።ችግሩ በመንግሥትነት የተቀመጠው አካልም በእራሱ በፈጠረው ዓለም ውስጥም ከጎሳውም ''ዜጋ'' የሚለው ስም የተሰጣቸው ትናንሽ ''ልዑላን'' ሃገሩን እንደሞሉት ያስረዳል።ለህወሓት የኪነት ቡድን ለደረሰበት የመኪና አደጋ ከሰበር ዜና ባላነሰ መደናገጥ ዜናውን ያነበበው ኢቲቪ፣''አንድ የቀድሞ ታጋይ አረፉ'' ለሚል ዜና ቀዳሚ ዜናው የሚያደርገው ኢቲቪ፣ለሰላሳ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል ቀዳሚ ዜና ማድረግ አቃተው።ለዚያውም ኢትዮጵያዊነታቸው  አልተረጋገጠም አለን።

ባጠቃላይ 

በሊብያ ሰማዕትነት የተቀበሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በሶስት ቀናት ውስጥ ብዙ ነገሮችን ቀይረዋል።
  • የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር አስጠብቀዋል፣
  • ከሊቅ እስከደቂቅ ልቡ እየነደደ የቤተ ክህነቱ እና የቤተ መንግስቱን ጥፋት ካለ አንዳች ፍራቻ ከማውገዙም በላይ ለማስተካከል ቃል የገባበት ታሪካዊ ኩነት ሆኗል፣
  • ሕዝብ እርስ በርሱ እንዳይፈራራ ፈር ቀዷል፣
  • የችግሩ ምንጭ ውጫዊ ሳይሆን ውስጣዊ ማለትም የገዢው ኢህአዴግ/ወያኔ የተሳሳተ ፖሊሲ እና ስልጣን እንደ  ከረሜላ የጣማቸው የስርዓቱ መዘውሮች መሆኑን ከእዚህ በፊት የደመደመውን ለመጨረሻ ጊዜ አረጋግጧል፣
  • የኢትዮጵያ ሕዝብ ለህሊና በሚከብድ ደረጃ ለኢትዮጵያውያን ስቃይ እና መከራ ልባቸው የማይደነግጥ በባዕዳን ዘንድም የሌለ የጥላቻ እና የጭካኔ መንፈስ በመሪዎቹ ላይ ተመልክቷል።
  • በባዕድ ሀገር ስደት እና መገፋት ሊገታ የሚችለው ኢትዮጵያ በጎሳ ከፋፍሎ ከሚገዛት የኢህአዲግ/ወያኔ አገዛዝ ነፃ መውጣት ስትችል ብቻ መሆኑን ቀደም ብሎ በለዘብተኛነት የሀገሩን ጉዳይ ስመለከት የነበረው ኢትዮጵያዊ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተረዳበት እና የወሰነበት ጊዜ ነው።ያወቀ እና የወሰነ ሕዝብ ለማታለል መሞከር ደግሞ ብዙ ዋጋ ማስከፈል ብቻ ሳይሆን እንዳይሆኑ ሆኖ መውደቅን ያስከትላላ።
እነኝህ ሁሉ ክስተቶች ሕዝብ የመጨረሻ ጠርዝ ላይ እንደደረሰ በግልፅ አመላክተዋል።ጉዳዩን ኢህአዴግ/ወያኔም ምን ያህል በሕዝብ ታንቅሮ እንደተተፋ በአይኑ አይቷል።በጆሮው ሰምቷል።ይልቁንም በእዚህ ወቅት ብዙዎች ከጎኑ የነበሩ የስርዓቱ አካላት ትተው የሚኮበልሉበት ትክክለኛ ጊዜ መሆኑን ያለፈው ሳምንት ክስተቶች ሁሉ እንዳስተማሯቸው ከግምት በዘለለ መረዳት ይቻላል።አንድ ቀን የቦሌ መንገድም በሕዝብ ይዘጋል።አንድ ቀን ከቤት ሳሉ በሕዝብ ኃይል የመታሰር ዕጣ እንደሚገጥም ደጋፊዎቹ ከግምት የዘለለ እውነታ እየሸተታቸው ነው።ችግሩ ለመፍትሄው እራሳቸውን አንድ አካል ማድረግ እና ወደፊት ከመሄድ ይልቅ በትናንሽ አስተሳሰቦች እየተጠለፉ እራሳቸውን እየደለሉ መገኘታቸው ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ እና ጭላንጭል ማየት የጀመረው አሁን ነው። ያለው አማራጭ አንድ እና አንድ ብቻ መሆኑ በሰማእታቱ ደም ለኢትዮጵያ ሕዝብ  ከመቼውም በበለጠ ተከስቷ።ይሄውም ኢትዮጵያ  ኢትዮጵያዊ መንግስት አሁን በስልጣን ያለውን ስርዓት መቀየር ብቻ ነው።ይህ እንዴት ይሆናል?  የብዙዎች ጥያቄ ነው።መልሱ ብዙም እሩቅ አያስጉዝም በእያንዳንዱ ሰው ኃላፊነት መወጣት የሚል ነው።ሁሉም እንደ ችሎታው ያለበትን ሃገራዊ ኃላፊነት ይወጣ።የእያንዳንዱ ሰው ጠብታ ትልቅ ተራራ ይሰራል።


ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

No comments: