ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, July 30, 2012

የኢትዮዽያ ጉዳይ በማን እጅ ነው? (አጭር ትረካ)

¨ወቸው ጉድ ሰማዩ እንዴት ጠቁሯል ጃል!¨ አሉ አባ እንጦስ አንገታቸውን ወደ ሰማይ አቅንተው።
¨አዎን አባቴ ክረምት አይደል ወቅቱ ያውም ወርሃ ሃምሌ¨ ራማ መለሰ እርሱም እንደ እሳቸው አንገቱን ቀና አርጎ በ አንድ እጁ ግን የ አባን እጅ እንደያዘ።
¨በል ልጄ ወደ ገዳማችን እንሂድ ተነስ¨ ቀጠሉ አባ እንጦስ በግራ እጃቸው ወተት የመሰለ ጺማቸውን ዳበስ እያደረጉ ¨ለመሆኑ ስንት ሰዓት ነው እንግዶቹ የመጣሉ ያልከኝ?¨
¨ዘጠኝ ሰዓት ነው አባቴ¨ መለሰ ራማ አባ የተቀመጡበትን አጎዛ መጠቅለል ጀመረ።
¨የቀትር ጸሎት እንደፈጸምኩ ታስገባቸዋለህ¨ አሉ አባ አሻግረው ገዳማቸውን እያዩ ከ ራማ ጎን በፍጥነት መራመድ ይዘዋል።

ራማ የ አባ እንጦስ ረድእ (በ እለት እለት ኑሮ የሚያገለግላቸው) ከሆነ እነሆ አምስት አመታት አልፈዋል።እርሱን ለመምከር ወይንም ለማስተማር ካልሆነ ብዙ ሲናገሩ የማያውቃቸው አባ ዛሬ እንግዶች ይመጣሉ ብሎ ከነገራቸው ወዲህ በተለየ መልክ ትኩረት ሰጥተው ሰዓቱን ሲጠይቁት አሁን ሶስተኛ ጊዜ ነው።
¨ ዛሬ ስለሚመጡት እንግዶች የተለየ ነገር መኖሩን አባ ቢያውቁ ነው እንጂ እንደዚህ አበክረው አይጠይቁም ነበር።¨ አለ ለራሱ በሃሳቡ።
አባ ለዋዛ ፈዛዛ ንግግር ፈጽሞ ቦታ የላቸውም።ብዙ ያዳምጣሉ።አስፈላጊ ነው ብለው ካላመኑ በቀር ባብዛኛው ትንሽ ይናገራሉ።
ራማ ይህን ሁሉ የ አባን ባህሪ፣መንፈሳዊነት፣አስተዋይነት ሁሉ ሲያወጣ ሲያወርድ።
¨በመጀመርያ ተግባር ቤት ገብተን ንፍሮውን አይተን እንመለስ¨ ሲሉ አባ እንደመባነን አደረገው እና ¨ደረስን እንዴ?¨ ብሎ ቀና ቢል የገዳማቸው መግቢያ ላይ ያለው ትልቅ የ እንጨት መስቀል ለካ ከፊቱ መሆኑን አስተዋለ።
ቀጠለናም ¨ይተዉ አባቴ እርስዎ ወደ ጸሎት ይግቡ እኔ አይቸው ልመለስ።ወዲያውም እንጨት ከፈለገ ቆስቁሸው እመለሳለሁ¨ አለ።
¨የለም ልጄ አንተ ለእንግዶቹ ውሃው እንዲቀዘቅዝ እንስራው ውስጥ ቀድተህ አዘጋጀው¨ ብለው አባ ወደ ተግባር ቤት መንገድ ጀመሩ።
የ አባ እንጦስ ገዳምን ድፍን ኢትዮዽያ አይደለም ከብዙ የ አለማችን ክፍሎች ብዙ ሰዎች እየመጡ ልመናቸው ተሰምቶ፣ችግራቸው ተቃሎ ተመልሰዋል።
በ ራማ ዘንድ የ ዛሬ እንግዶች ከ እዚህ ቀደም እንደነበሩት እንደሚሆን ቅንጣት ታክል አልተጠራጠረም-ገዳሙን ለመሳለም የሚመጡ አልያም ለመጎብኘት የሚመጡ የባህር ማዶ ሰዎች::

ከ ቀኑ ዘጠኝ ሰዓት እንግዶቹ ወደ ገዳሙ መግባት ጀመሩ። ራማ የ እንግዶቹን ብዛት የገመተው እስከ ሰባት ሰው  ነበር። ሆኖም ግን ቁጥራቸው ከ ሁለት መቶ በላይ ሆነው ስለተገኙ የ አባ እንጦስ ትንሽ ክፍል ፈጽማ የምትበቃ ባለመሆንዋ ከገዳሙ መግብያ በስተቀኝ በኩል ባለው መስክ ላይ እንዲቀመጡ ሆነ።
¨አባቴ ይህን ያህል ህዝብ ይመጣል ብለው ገምተዋል? እኔ እኮ የገመትኩት ቢበዛ አንድ አምስት፣ሰባት ሰው ነበር።¨ አለ ራማ አባ እንግዶቹን መስቀል ሲያሳልሙ ወደ ጆሯቸው ጠጋ ብሎ።
አባ እንግዶቹ መስቀል ከተሳለሙ በሁዋላ ራማ አጎዛ ካነጠፈላቸው ወንበር ላይ ቁጭ አሉ።ጸጥታ ሰፈነ።¨አባም ዝም መጽሃፉም ዝም¨ አለ ራማ በሆዱ ከ አባ ስር ካለችው ድንጋይ ላይ ቁጭ ብሎ ማስተዋል ጀመረ።
ከእንግዶቹ አንድ አዛውንት ተነሱና-
¨እንዴት ነው ነገሩ ያንን ሁሉ ሃገር ተጉዘን የመጣነው ለዝምታ ነው እንዴ?¨ አሉና ንግ ግራቸውን ቀጠሉ።
¨እኔ እስከተረዳሁት ድረስ እዚህ ያለነው ሁላችን አንዳችን ካንዳችን አንተዋወቅም። ሆኖም ግን ሁላችንም አንድ ጥያቄ እየሞገተን ነው። መቸም በ አካል ባንተዋወቅም እዚህ ያለው ህዝብ አባታችን ግማሻችን ኢህአዲጎች፣የቀረነው ሚያዝያ ነው ማን ሰባት ነበር እእእ... ¨ ሲሉ ሽማግለው  ¨ግንቦት ሰባት¨ አለ አንዱ' የ ግንቦት ሰባት' አባል ቆጣ ብሎ የድርጅቱ ስም ቶሎ አለመጠራቱ አናዶታል።¨በነገራችን ላይ ኢህአዴጎች በሉ አባቴ  `ዲ`አይደለም `ዴ` `ዴሞክራሲ` ማለት ነው።¨ አለ አንድ የ ኢህአዲግ አባል ተነስቶ¨
 ¨ድንቄም ዲሞክራሲ¨ አለ አንድ የ 'ኦነግ' አባል በተቀመጠበት። ¨አመድ በዱቄት ይስቃል ሁልሽም ከረፈደ መጥተሽ ደሞ¨ አለ አንድ የ 'ኢህአፓ' አባል ነኝ ያሉ ሸምገል ያሉ ሰው።
የቆሙት ሽማግሌ ቀጠሉ ¨ቆዩ ቆዩ ለስም አጠራሬ ይቅርታ አድርጉልኝ። ታገሱኝ አንድ ጊዜ አይዟችሁ አመት አላወራም¨ ብለው ጋቢያቸውን አስተካከሉ እና ቀጠሉ።
¨....እና በ አካል ባንተዋወቅም በ ቡድን በ ቡድን ግን እንተዋወቃለን።ቀድም ብየ ከ ጠራሁልዎት በተጨማሪ ከ ሃያ በላይ የምንሆን ቡድኖች  አንድ የሚያደርጉን ብዙ ነገሮች አሉ ከ እነዚህም ውስጥ ዲሞክራሲ ይቅርታ ዴሞክራሲ¨ ብለው ወደ ኢህአዲጉ ሰው መልከት አሉና ቀጠሉ
 ¨ አንደኛ ዴሞክራሲን መሽቶ እስኪነጋ የምንሰብክ ነን፥
ሁለተኛ ያለፉት የኢዮዽያ መንግስታት በሙሉ ችግር ነበረባቸው ብለን  እናስባለን ብቻ ሳይሆን ክፉውን ትተን ምን በጎ ነገሮች መያዝ አለብን ብለን አስበን አናውቅም፥
ሶስተኛ ጥርት ያለ ህዝቡ የሚፈልገው ያመነበት ራዕይ የለንም ምናልባት ራዕይ ያለው ገዳም ብቻ ስለሚመስለን ይሁን አይታወቅም¨ ሲሉ ሽማግሌው ተሰብሳቢው ሁሉ ሳቀ አባ እንዳቀረቀሩ በሃዘን ይሰማሉ። ሽማግሌው ሳቁ ሲገታ ቀጠሉና ¨እንደ እዚህ አንዳንዴ በመሳቅም አንድ ነን¨ ሲሉ ሽማግሌው ሌላ ሳቅ ተከተለ።አባ አሁንም እንዳቀረቀሩ ዝም አሉ።
ሽማግሌው ቀጠሉ -

Thursday, July 5, 2012

ሁል ጊዜ የማትረሳኝ ቃል አለች ''ብሔራዊ ጥቅም!'' (National Interest) የምትል::


ሰሞኑን አንድ ግለሰብ በ ባህር ማዶ ካሉት የመገናኛ ብዙሃን በ አንዱ እና በ ዝነኛው ''ኢሳት'' ቀርበው በሃገር ቤት መደረግ ካለበት ትግል ውስጥ አንዱ ''በ ኢትዮዽያ አየር መንገድ ላይ የ ኢኮኖሚ እቀባ ማረግ ይገባል።ሰዎች በ አየር መንገዱ እንዳይጠቀሙ ማድረግ ፤ እኛም መሳፈር የለብንም ወዘተ'' ሲሉ ተደምጠዋል።
 ሆኖም ግን በ ፖለቲካው ዓለም ሁል ጊዜ የማትረሳኝ ቃል አለች ''ብሔራዊ ጥቅም!'' (National Interest)  የምትል:: ብሔራዊ ጥቅም ለድርድር የሚቀርብ አለመሆኑን ነው ሳይንሱ የሚያስተምረን::

 የ ''ያ ትውልድ'' ፖለቲካን (የ መለስ እና የ ኢሳያስ ትውልድ ጨምሮ )  ከምንወቅስበት ምክንያት አንዱ' ብሔራዊ ጥቅምን እና የ ሃገር ገጽታን ደምስሶ ምን አይነት ኢትዮዽያን እየናፈቅን ነው?' ለሚለው ፈታኝ ጥያቄ መመለስ አለመቻሉን ነው።

 በ  'ኢሳት' ጋዜጠኛ ስለ ጉዳዩ ትክክለኛነት ማብራርያ እንዲሰጡ ደጋግመው ሲጠየቁ ''የ ኢትዮዽያን አየር መንገድ በኪሳራ እንጣለው'' ባዩ ሰውዬ አጥጋቢ መልስ መስጠት ሲያቅታቸው ተመልክቻለሁ።

ግለሰቡ ከ እዚህ በፊት ብዙ በጎ ሃሳቦች ሲሰጡ እና የ ሃገር ፍቅራቸውን ሲገልጹ አይቻለሁ፣  ሰምቻለሁ። እዚች ላይ ግን ለእኔ አልገባህ አለኝ ወይም እንዳይገባኝ አርገው ነው የነገሩኝ።
የ ኢትዮዽያን ብሔራዊ ጥቅም የሚነኩ ሂደቶች በሙሉ ሁለት ሶስት ጊዜ መከለስ አለባቸው። እረጅም እድሜ ለ ኢትዮዽያ አየር መንገድ!




ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።