ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, April 30, 2021

የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶቹ፣የተወሰዱ እርምጃዎች እና መጪው ተስፋ በተመለከተ ባለሙያዎቹ የሰጡት ዝርዝር ማብራርያ (ቪድዮ)

- በኢትዮጵያ የሞባይል ባንክ ተጠቃሚ ከ10.3 ሚልዮን አልፈዋል።
- የባንክ ተደራሽነት ከ57 ሚልዮን ሕዝብ አልፏል።
- የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ ከ730 ቢልዮን ወደ 1 ነጥብ 2 ትሪልዮን ደርሷል።
- የዋጋ ግሽበቱ በመጪው ዓመት ወደ አንድ አሃዝ ይወርዳል።
ቪድዮ ምንጭ - ኢቢሲ 

Wednesday, April 28, 2021

ከከያኒ እስከ ቀዳሽ፣ከወታደር እስከ አካል ጉዳተኛ፣ከመሪ እስከ ተመሪ-ሕዝብ ለኢትዮጵያ የምንቆምበት ጊዜ አሁን ነው።በአጀንዳ ለመጥለፍ የሚሞክሩትን ወደ ጎን ብለን ቁልፉ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ እናተኩር! የህልውና ጉዳይ ነው።



  • በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለማወክ የተነሱትን አራት  ኃይሎች ለማሳፈር ከህዝብ፣ከከያኒው በተለይ ድምፃውያን እና ከመንግስት የሚጠበቁ አፋጣኝ ተግባራት 

ጊዜውን አለመረዳት፣መደነባበር፣የሚያዘውን ትቶ የማይያዘውን ለመያዝ መሞከር፣ቅድምያ የሚሰጠውን ትቶ የማይሰጠው ላይ ማተኮር፣የራስን ሀገር ሳያውቁ ማዋከብ እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች በግልጥ እየታዩ ነው።ኢትዮጵያን ራሳችን ሳናውቅ እንዳናጠፋት፣ ሌሎች ደግሞ አቅደው እና አውቀው እንዳያጠፏት ትኩረታችን ምን ላይ መሆን እንዳለበት እንወቅ! እጅግ ወሳኝ ጊዜ ላይ ነን።በግርግር እና በተደናገረ አስተሳሰብ ውስጥ ዋና አጥፊዎች ሆነን የምንቆመው እራሳችን እንዳንሆን ልብ ማለት አለብን።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለማወክ የተነሱት ኃይሎች  አራት ናቸው።አራቱም በተለያየ መልክ ይምጡ እንጂ ኢትዮጵያን በማተራመስ ሁሉም የሚያገኙት ጥቅም እንዳለ ያስባሉ።እነኝህ ኃይሎች - 1) በኦሮምያ ክልል ውስጥ እና በአማራ ብሔርተኝነት ውስጥ የበቀሉ እጅግ ፅንፍ የያዙ አስተሳሰቦች፣ 2) የህወሓት ዕርዝራዦች፣ 3) የውጭ ኃይሎች ግብፅ፣ሱዳን እና አንዳንድ የመካከለኛውና ምዕራብ ሀገሮች እና 4) በድብቅ የሚንቀሳቀሱ አክራሪ እና ፅንፈኛ አራማጅ የአልቃይዳ ውላጅ ኃይሎች ናቸው።

የመጀመርያው በኦሮምያ እና አማራ ክልል ውስጥ ያሉ የብሔር ፅንፍ ቡድኖች በአንድም ሆነ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የበላይነት ለመያዝ የሚደረግ አደገኛ የሽምያ ፖለቲካ ውስጥ የገቡ ይመስላሉ።እርግጥ ነው በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው የአማራ ንፁሃን ከወለጋ እስከ ሰሜን ሸዋ ጥቃት ተፈፅሞባቸው በከፍተኛ ፈተና ላይ ይገኛሉ።ሆኖም ግን ይህም ሆኖ እያለ በአማራ ክልል ውስጥም ሆነ በውጭ ካሉ አቀንቃኞች ጋር የአንድ ክልል የበላይነት በኢትዮጵያ ካልመጣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የማይረጋጋ አድርገው በማቅረብ ሕዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳ አደገኛ ስብከት የሚያራምዱ አሉ።በሌላ በኩል በኦሮምያም በክልሉ አክራሪ ፖለቲካ ኢትዮጵያን ካልሸበበ መረጋጋት እንደሌለ የሚሰብኩ አሉ።ሁለቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን በጠላትነት ፈርጀው ይንቀሳቀሳሉ፣ የሀገሪቱን ፖለቲካ ለማተራመስ ይሞክራሉ።

የተቀሩት የህወሓት ርዝራዦች፣የውጭ ኃይሎች እና የአልቃይዳ ውላጅ አሸባሪዎች ዓላማቸው ግባቸው እና ተግባራቸው ከእዚህ  በፊት በሰፊው በእዚህ ገፅ ላይ ተወስቷል።ዛሬ ላይ አፅንኦት መስጠት የሚያስፈልገው ሁሉም ጊዜው አሁን ነው ብለው በኢትዮጵያ ላይ የተነሱበት እና ጥምረት ለመፍጠር የሞከሩበት ጊዜ መሆኑ ነው። ሁሉም ኢትዮጵያን በማተራመስ እና አሁን ያለውን የፖለቲካ ስርዓት በአንድ ዓይነት የኃይል መንገድ በማስወገድ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ትርምስ በመፍጠር የቁርስራሹ ተካፋይ ለመሆን አሰፍስፈዋል። 

የአራቱም ኃይሎች የአጭር ጊዜ ግቦች - 

1) መጪው ምርጫ እንዳይሳካ ትርምስ መፍጠር 
2) ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ በትንሽ ሕዝብ ተሳትፎ እንዲደረግ እና ዋጋ እንደሌለው ወሬ ማናፈስ እና ሕጋዊነት ማሳጣት፣
3) ምርጫው ከተደረገ በኃላም የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዳይቀበለው መስራት እና 
4) በመጨረሻም ምርጫው የብሔር ግጭት ምክንያት እንዲሆን መስራት እና ኢትዮጵያን ማተራመስ በመቀጠል ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንድትገባ ማድረግ ነው።

ስለሆነም ከላይ የተጠቀሱትን ኃይሎች ሕልም መና ለማድረግ እና ኢትዮጵያን በሁለት እግሮቿ እንድትቆም ለማድረግ ከመንግስትም ሆነ ከሕዝቡ የሚጠበቁ ተግባራት አሉ።እነርሱም -

መንግስት መስራት ያለበት -
  • ማናቸውም ዓይነት የፅንፍ ማኅበራዊ ሚድያ መገናኛዎችን ለመቆጣጠር  ከግንቦት ወር መጀመርያ ጀምሮ  መዘጋት አለባቸው።
  • የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና ራድዮ በልዮ ሃገራዊ ዝግጅቶች ዝግጅቶቻቸው እና ዜናዎቻቸው ሁሉ መከለስ አለባቸው።
  • አንድ ማዕከላዊ የመረጃ ሰጪ አካል (እንደ ''ፋክት ቼክ'') ያለ መንግስት ማስተዋወቅ እና ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ሀገርም  ብቃት ባለው መልክ የውሸት ዜናዎችን በማስረጃ የሚመልስ ማዕከል ያስፈልጋል።
  • ከጦር ሰራዊት እስከ ፖሊስ በከፍተኛ ደረጃ ዘብ የሚቆሙበት ጊዜ መሆን አለበት።
  • በኢትዮጵያ ላይ የማያቆም የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ላይ የተሰማሩት በተለይ የጦር ኃይሉን መኮንኖች ጨምሮ ምክንያት በሌለው የስም ማጥፋት እና ሕዝብ እና መንግስትን ለማጋጨት ሌት ከቀን የሚሰሩት ላይ የእርምት እርምጃ መወሰድ አለበት።
  • ከውስጡ ያሉትን ሙሰኞች፣ጎሰኞች እና ብቃት የሌላቸውን ባለስልጣናት በተለይ የበታች ሹሞች ገለል ማድረግ።
ሕዝቡ መስራት ያለበት 
  • ኢትዮጵያዊ አሸናፊ ስነ ልቦናውን ከፍ ማድረግ እና በተለያየ መንገድ የስነ ልቦና ጦርነት የከፈቱበትን ከላይ የተጠቀሱትን አራት ኃይሎች ሰለባ እንዳይሆን ከግለሰብ ጀምሮ መዘጋጀት፣
  • ሁል ጊዜ መጥፎ እየነገሩ በሀገሩ እና በመንግስት ላይም የተጋነነ ወሬ የሚያቀብሉትን ሚድያዎች እና ዩቱብ፣ማኅበራዊ ሚድያዎች በሙሉ ውሸት ማጋለጥ እና አለመመልከት፣የእነርሱን ወሬ ይዘው የሚመጡትን ቦታ አለመስጠት።
  • ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተነሱ ኃይሎች ዋነኛ ትኩረት መጀመርያ ኢትዮጵያ ሃገረ መንግስቷን በምርጫ እንዳትመሰረት ማድረግ  መሆኑን አውቆ በብዛት በምርጫው መሳተፍ እና መብቱን ማስከበር።
  • መንግስት ከምርጫ በፊት እናስወግድ የምትል ውስጠ ወይራ ማናቸውም ዓይነት እንቅስቃሴ እና ፕሮፓጋንዳ ቀድሞ አውቆ የእዚህ ዓይነት ሃሳብ አራማጆችን ማሳፈር እና ማጋለጥ።
  • ለማናቸውም ሃገራዊ  አገልግሎት መነሳት እና ወጣቶችም ዝግጁ እንዲሆኑ መምከር።
  • ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚፈልጉ ኃይሎች ብዙ እርቀት እንደሚሄዱ አውቆ እራሱን ማዘጋጀት እና የውስጥ ከሀዲዎችን በእኩል ደረጃ መዋጋት እና 
በውጭም ሆነ በውስጥ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በጎሳ፣በሃይማኖት እና በመሳሰለው ሁሉ ሊከፋፍሉት የሚሞክሩትን ሁሉ በፅናት መዋጋት የሚሉት ናቸው።

 ከኪነ ጥበብ ሰዎች በተለይ ከድምፃውያን የሚጠበቅ -

የኪነ ጥበብ ሰዎች በተለይ ድምፃውያን በእዚህ ሀገር በምትጣራበት ጊዜ እንዳልሰሙ ተሸፋፍነው መተኛት የለባቸው።ለእዚህ ጊዜ ፈጠራቸውን ተጠቅመው ሕዝብ አንድ የሚያደርጉ፣የተናቆሩትን እና የተቃቃሩትን ወደ ህብረት የሚያመጣ፣ሀገር የሚያፈርሱትን የውጭም ሆኑ የውስጥ ባንዳዎች የሚሸነቁጥ ሕዝብን ግን የሚያስተሳስር ስራዎች በአጭር ጊዜ ማድረስ አለባቸው። ለችግር ጊዜ መንገድ የማያሳይ ከያኔ በሰላም ጊዜ ገንዘብ ለመሰብሰብ መምጣት የለባቸውም።ሕዝቡን ተስፋ ማሳየት፣ክፉውን እንዲርቅ መምከር እና በፅናት በኢትዮጵያዊነቱ እንዲቆም የሚያደርጉ ስራዎች በአጭር ጊዜ ከኪነጥበብ ሰዎች ይጠበቃል። 

ኢትዮጵያ ለዘላለም በፈጣሪዋ ጠባቂነት፣በልጆቿ ተጋድሎ ፀንታ ትኖራለች።

Saturday, April 24, 2021

በ1950ዎቹ የነበረውን የኢትዮጵያ ትውልድ የሚያሳይ ቪድዮ።

  • ለአፍሪካ ትንሣኤ መነሻው ኢትዮጵያ ነች - ቪድዮው መግቢያ ላይ ምክንያቱን ያገኙታል።
  • ተማሪዎች ወደ ክፍል ሲገቡ በምን ዓይነት የስነ ምግባር እና የሀገር ፍቅር ስሜት እንደሚገቡ ይመለከታሉ።
  • በቪድዮው አዲስ አበባ፣አስመራ፣ደብረብርሃን፣ጎንደርን ይመለከቱበታል።


ማስታወቂያ /Advertisement 
====================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 

Friday, April 23, 2021

ሕዝብ አስር ጊዜ ቢጠይቅ መንግስት አስር ጊዜ ደጋግሞ የማስረዳት ግዴታ አለበት!



በመንግስት እና በሕዝብ መሃከል ያለው አንዱ የመገናኛ መስመር ሕዝብ ለሚጠይቃቸው ማናቸውም ጥያቄዎች አክብሮ እና ዋጋ ሰጥቶ መመለስ እና ማስረዳት ነው።ሲሆን መንግስት ሳይጠየቅ ቀድሞ እያንዳንዱን ክስተቶች ምን እና እንዴት እንደተፈፀሙ የማስረዳት፣የማሳወቅ እና የሚከተሉትን ችግሮች ሁሉ ቀድሞ ተንትኖ ለሕዝብ ማቅረብ እጅግ አስፈላጊ ነው።መንግስት በሰው ኃይልም አደረጃጀትም፣ ከህዝብ በሚሰበስበው ሀብት እና የመረጃ መዋቅሩ የተሻለ አደረጃጀት እና የላቀ መረጃዎችን ቀድሞ የማወቅ አቅም አለው።

ሰሞኑን በአማራ ክልል እየተካሄዱ ያሉት ሰላማዊ ሰልፎች ጥያቄ በተለይ በኦሮምያ ክልል ዘርን መሰረት አድርገው የሚፈፀሙት ግድያዎች ይቁሙ፣ገዳዮቹ ለፍርድ ይቅረቡ ለወደፊትም ግድያዎቹ እና ጥቃቶቹ እንዳይፈፀሙ መንግስት እርምጃ ይውሰድ ነው።እነኝህ ጥያቄዎች የዜግነት እና የሰብዓዊነት ጥያቄዎችም ጭምር ናቸው።ሕዝብ የመጠየቅ፣መንግስትም የመመለስ መብት እና ግዴታ አለባቸው።ለጥያቀዎቹ ዋና መነሻ ምክንያት የድርጊቱ ዘግናኝ አፈፃፀም እና የሰላም ዋስትና የማጣት መሆናቸው ግልጥ ነው።ከእዚህ ውጪ ነገሮቹን ወደ አላስፈላጊ የእልህ እና ውስብስብ ጉዳዮች መምራቱ እንደሃገርም እንደ ህዝብም አይጠቅምም።

ስለሆነም መንግስት  የመከላከያ ሚኒስትር፣የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፀጥታ ጉዳይ አማካሪ እና የኦርምያ ክልል ፕሬዝዳንት በተገኙበት ስለ ጉዳዩ በቂ ማብራርያ በሚከተሉት ጉዳዮች ዙርያ መስጠት አለበት። እነርሱም -
  • ክስተቱ በእነማን እንደተፈፀመ፣
  • መንግስት ምን እንዳደረገ
  • ወደፊትም ተመሳሳይ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ምን ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ እንደታሰበ 
  • ከሕዝብ ምን እንደሚጠበቅ እና 
  • በደረሱት ሁሉ ከልብ ማዘኑን መግለጥ አለበት 
ሕዝብ አስር ጊዜ ቢጠይቅ መንግስት አስር ጊዜ ደጋግሞ የማስረዳት ግዴታ አለበት! ለጥያቄዎች መልስ አለመስጠት ሕዝብ በተለየ መልክ እንደተናቀ ይሰማዋል።ውጤቱ ደግሞ አደገኛ ነው።ይልቁንም ለአክራሪ ኃይሎች 'ሰርግና ምላሽ' ነው።ሕዝቡን ወደ ፅንፍ ለመውሰድ 'ድሮም ስንል የነበረው ይሄ ነው' እያሉ ሕዝብን ይቀሰቅሱበታል።ስለሆነም በመንግስት እና በሕዝብ መሃል ያለውን የግንኙነት መስመርን በሚገባ አለመጠበቅ ሃገርን ዋጋ ያስከፍላል።በአማራ ክልል ያለው ሕዝብ የመንግስት የክልሉን ተወላጆች ላይ ባነጣጠረ መልኩ እየተፈፀሙ ያሉ ጥቃቶች እንደሚያሳስቡት መግለጡ ምኑ ላይ ነው ወንጀሉ? መንግስት በግንኙነት (communication) ሥራ ላይ ችግር እንዳለበት ማመን አለበት። ለሕዝብ እራስን ዝቅ አድርጎ ማስረዳት ሕዝብን አገለግላለሁ ለሚል መንግስት እንዴት ከበደው? ይህ እንዳይደረግ የሚሞግቱ ካሉ እነኝህ ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ የሚፈልጉ ናቸው።ሕዝብ አስር ጊዜ ቢጠይቅ መንግስት አስር ጊዜ ደጋግሞ የማስረዳት ግዴታ አለበት! ለነገሩ ሕዝብ በሦስት ዓመት አንዴ አሁን ነው የጠየቀው።



ማስታወቂያ /Advertisement 
====================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 

Tuesday, April 20, 2021

ለወቅታዊው የኢትዮጵያ ጉዳይ መፍትሔዎቹ




ነባራዊ ሁኔታ 

በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ አራት ኃይሎች ከወዲህ ወዲያ ሲሉ ይታያሉ።እነርሱም - ለዘብተኛ ጎሰኞች፣አክራሪ ጎሰኞች ፣ዲሞክራሲያዊ ፌድራልስቶች እና ፖለቲካ-ጠል የሰብአዊነት አራማጆች ናቸው

ለዘብተኛ ጎሰኞች

በለዘብተኛ ጎሰኞች ስር የቀድሞ የብአዴን፣ኦህዴድ እና የደቡብ ካድሬዎች ቀዳሚ ናቸው።እነኝህ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሲማሩም ሁኑ ሲመለመሉ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር የብሔር ፖለቲካ በሀገሪቱ አለመስፈኑ ነው እየተባሉ የተመለመሉ ናቸው።በመጀመርያ ቀንደኛ የጎሳ ፖለቲካ ሰባኪ ሆኑ።ቀጥሎ ፖለቲካው፣ኢኮኖሚው እና ምጣኔ ሃብቱ በህወሓት ስር መጠቃለሉን ሲያውቁ አጉረመረሙ።ትንሽ ቆይቶ ህዝቡ በህወሓት/ኢህአዴግ ላይ ሲነሳ የለውጥ ሐዋርያ ሆነው ወጡ እና የነበሩበትን ስርዓት የሚረግሙ ሆኑ።ግማሾቹ በይፋ ይቅርታ ጠየቁ።የተቀሩት ግን በተለይ አሁን ምርጫ እየቀረበ ስመጣ ስልጣን እንደሚያጡ ስለተገነዘቡ ወደ አክራሪ ጎሰኞች በመግባት እና ባለመግባት መሃል እየዋለሉ አሉ።

ዲሞክራሲያዊ ፈድራልስቶች 

እነኝህኞቹ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ችግር በማጥናት ዕድሜያቸውን የፈጁ፣ቀድሞ እንዳይናገሩ የታፈኑ፣አሁን ደግሞ በአክራሪ እና ለዘብተኛ ጎሰኛ ቡድኖች የሚኮረኮሙ ናቸው።ለእነኝህኞቹ ትልቁ እፎይታ የህወሓት መወገድ ቢሆንም በአክራሪ ጎሰኞች ብዙ ፈተና በግልጥም በስውርም እያጋጠማቸው ያሉ ናቸው።ለውጡን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት ከገቡ በኃላ መልካም ተስፋቸው   መጪው ምርጫ ላይ የመሳተፍ ዕድል በማግኘታቸው ነው። ዲሞክራሲያዊ ፌድራልስቶች የኢትዮጵያ ችግር በእውነተኛ ዲሞክራሲ ላይ የተመሰረተ  የፈድራላዊ አስተዳደር ይፈታል  ብለው ያምናሉ።

አክራሪ ጎሰኞች 

አክራሪ ጎሰኞች ዋና መሰረቶቻቸው ሶስት ናቸው። እነርሱም ፍርሃት፣ጥርጣሬ እና የጥላቻ ትርክቶች።አክራሪ ጎሰኞች በዋና ዋና የኢትዮጵያ የወቅቱ ክልሎች ማለትም በአማራ፣ኦሮሞ እና ትግራይ ፖለቲካ ውስጥ እስከ ጉልበታቸው ተነክረውበታል።በፍርሃት አንዱ አንዱን እንዲፈራ አድርገው ይሰብካሉ።ላለመተማመን የሚጠራጠሩት አንዱ የበላይ ሊሆን እየሰራ ነው።ይህንን ታሪካዊ ጊዜ ከተበለጥኩ ጎሳዬን ''አስበላለሁ'' በእዚህም ተወቃሽ እሆናለሁ ብለው ተከታዮቻቸውን ይሰብካሉ።ሕዝቡም ውስጥ በሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ስጋት ማሳደር ችለዋል።በእዚህ ሁሉ መሃል ተግባብተው እንዲሰሩ የጎሳ ፖለቲካን ጥለው ዘመኑን የዋጀ አስተሳሰብ እንዲያራምዱ ሲነገራቸው ደግሞ ያደጉበት የጥላቻ ትርክቶች ከፊታቸው እየተደቀነ አላላውስ ይላቸዋል።በውነቱ ከሆነ አክራሪ ጎሰኞች እውነተኛ አዛኝ ቢያገኙ  ሕክምና ያስፈልጋቸዋል።ችግሩ ሁሉም ድንጋይ ስለሚወረውርባቸው በውስጣቸው ያለውን ፍርሃት፣ጥርጣሪ እና የጥላቻ ትርክት የበለጠ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ያገኙ ያህል ለእሳቢያቸው ማሳመኛ ምክንያት ያገኙ አድርገው ይቆጥሩታል።

ፖለቲካ-ጠል የሰብአዊነት አራማጆች

እነኝህ አሁን ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር እንዴት እንደመጣ፣ወዴት እንደሚሄድ፣ምን ዓይነት መንግስት ይምጣ የሚጨነቁ አይደሉም። በራሳቸው ጉዳይ ተይዘዋል።ነገር ግን ምንም አይነት አስተዳደር መጣ መለኪያቸው የሰብዓዊነት ልኩ ብቻ ነው።ይህ ባብዛኛው ሕዝብ ዘንድ የሚንፀባረቀው ዕይታ መለኪያው ለሁሉም የፖለቲካ ወቀሳዎች መንግስትን ስለሚያጋልጥ የመንግስት ተቃዋሚዎች በቀላሉ የሚያንቀሳቅሱት እና ስሜቱን ኮርኩረው የሚያስነሱት ይህንን የኅብረተሰብ ክፍል ነው።ይህ የኅብረተሰብ ክፍል ፖለቲካዊ ንቃትም ሆነ የመተንተን አቅም ስለሌለው ለሴራ ፖለቲከኞች በቀላሉ የተጋለጠ እና ስሜት የሚኮረኩሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሴረኞቹ በአንድ እጃቸው እራሳቸው ከሰሩ በኃላ በሌላ እጃቸው ይህንኑ የኅብረተሰብ ፍል ቀስቅሰው እንዲጠቃ የፈለጉትን የፖለቲካ ድርጅት ወይንም እራሱን መንግስትን ያሳምፁበታል።

ገመድ ጉተታው 

የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ከተጀመረ ከዛሬ ሶስት ዓመት ወዲህ ትልቁ እና የጎላው የገመድ ጉተታ የነበረው በህወሓት እና በብልጥግና መሃል ዋነኛው ሲሆን ይህንን በመከተል ሌላው የገመድ ጉተታ በኦሮምያ ብልጥግና ውስጥ ያለው የአክራሪ ጎሳ እና ለዘብተኛ (ኢትዮጵያዊነትን በሚያቀነቅነው) መሃከል ያለው ውጥረት ነው።አክራሪው ቡድን ከቢሮክራሲው እስከ የክልሉ ልዩ ኃይል ድረስ የተበተነ እንደሆነ ሲነገር ይሄው ቡድን በዋናነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድን ቤተመንግስቱን ከማደሳቸው ጀምሮ  ኢትዮጵያን ወደቀደመ ክብሯ እንመልሳታለን የሚለው አባባላቸውን ጨምሮ እየጠቀሰ በዙርያው በተኮለኮሉት የፅንፍ አስተሳሰብ አራማጆች ዘንድ ሁሉ  ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከስልጣን እንዲወርዱ የማይጭረው መሬት የለም። 

የፅንፍ ቡድኑ ይህንን የሚያደርገው በቀጥታ በትጥቅ ትግል ከመዋጋት ጀምሮ ከሀገር ውስጥ የተዘጋው የኦኤምኤን ሚድያ በውጭ ሀገር በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በመንግስት ላይ የስም ማጥፋት እና ያልተሳኩ የአመፅ ጥሪዎችን እስከመጥራት ደርሷል። ይህም ሆኖ ግን አሁንም በሌላ ማዶ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሴራ ፖለቲካ ለመክሰስ የሚሞክሩ ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፅንፍ ቡድኑ ጋር እስከ የሕይወት ማጥፋት ሙከራ ተደርጎባቸው፣የኢትዮጵያን አንድነት ማስፈን የጎሳ ፖለቲካን ማጥፋት ዓላማቸው እንደሆነ በግልጥ እየተናገሩም አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚከሱ አሉ።ለእዚህ ዋና ማሳያ የሚያደርጉት በኢትዮጵያ በተለይ የአማራ ሕዝብ ላይ ዓላማ ያደረጉ ጥቃቶች ላይ አፋጣኝ ምላሽ አይሰጡም የሚል ነው።

ከላይ የተጠቀሱት ነባራዊ ሁኔታዎች ባሉበት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ አንፃር በተለይ በፅንፍ ኃይሎች ፋሺሽታዊ በሆነ መልኩ በህፃናት፣ሴቶች እና አረጋውያን ላይ ሳይቀር የተፈፀመው ግድያ እና በሺህ የሚቆጠሩ ''ሀገራችሁ አይደለም'' እየተባሉ ከሁለት ትውልድ በላይ የኖሩ የተሰደዱበት፣የመተከል፣ወለጋ  እና በሌሎች ቦታዎች የተፈፀሙት የግድያ ተግባራት በተጨማሪ በሰሜን ሸዋ አጣዬ ከተማ ላይ እነኝሁ መሰረታቸውን በኦሮምያ ያደረጉ የፅንፍ ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት የከተማዋ መሰረተ ልማት ሙሉ በሙሉ መውደማቸው የአለፈው ሳምንት መጨረሻ አሳዛኝ ድርጊት ነው።ይህንን ተከትሎ  ድርጊቶቹን በመቃወም ዛሬ በባሕርዳር፣ወልዲያ፣ደሴ እና ሌሎች የአማራ ከተሞች ከፍተኛ ሰልፎች ተካሂደዋል።

በኦሮሞ እና የአማራ ብልፅግና መሃል ያሉት ጊዜያዊ የልዩነት ምንጮች

ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ዘጠና ቀናት ውስጥ ወሳኝ የሁኑ ሁለት ተግባራት አሏት።የመጀመርያው የምርጫ ጉዳይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የዓባይ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ነው።ስለሆነም አሁን ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ውጥረት ፈፅሞ አስፈላጊ አይደለም።አሁን በተፈጠረው ሁኔታ በዛሬው ዕለት በግብፅ ሚድያዎች ኢትዮጵያ እንደተከፋፈለች እየተደረገ በሚነዛ ወሬ ፈንጠዝያ ላይ እንደሆኑ ዛሬ ሲደመጥ ነው የዋለው።ስለሆነም ኢትዮጵያ ወቅታዊ ውጥረቶችን መፍታት እና ወደ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ማትኮሩ እጅግ አስፈላጊ ነው። በመሆኑም  አፋጣኝ መፍትሄዎች ከመንግስትም፣ከሁሉም የፖለቲካ አካላትም ይጠበቃል።በቅድምያ ግን በኦሮምያ ብልጥግና እና የአማራ ብልጥግና መሃከል ያሉት ግዝያዊ ልዩነት ሃሳብ ምንጮች ምንድናቸው?

በኦሮሞ እና የአማራ ብልፅግና መሃል ያሉት ጊዜያዊ የልዩነት ምንጮች የሚከተሉት ናቸው። እነርሱም - 
  •    በኦሮምያ ብልፅግና ውስጥ አክራሪ የፅንፍ ኃይሎች በተለየ መንገድ ከቢሮክራሲ እስከ ልዩ ኃይሉ ውስጥ መመሸጋቸው እና አሁንም የሚፈፀሙ ግድያዎች በእነኝሁ ኃይሎች አይዞህ ባይነት መደገፉ፣ 
  •   ሕገ መንግስቱ የአማራን ሕዝብ የማይጨምር መሆኑ እና ሀገር አልባ ሆኖ በኦነግ እና ትህነግ መሃል የተዘጋጀ ሰነድ መሆኑ በአማራ ክልል በኩል በመወሰዱ፣
  •  በሁለቱም ክልሎች ውስጥ ያሉት ህገ-ክልል መንግስታቸው በራሱ የተለያየ መሆኑ።ይሄውም የአማራ ክልል በውስጡ ላሉት ብሔረሰቦች የባለቤትነት መብት ሲሰጥ የኦሮምያ ግን በክልሉ ያሉትን ብሔር ብሔርሰቦች እንደማያውቃቸው የሚገልጥ አረፍተነገር መያዙ እና 
  •  በሁለቱም ክልሎች የሚገኙ የፅንፍ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች ለእየራሳቸው ሕዝብ አንዱ አንዱን ሊውጠው ነው የሚለው የማስደንበርያ አሰቃቂ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎች  የሚሉት ዋና እና መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው። 
ከእዚህ በተጨማሪ ያለፈ ታሪክ ትርክት የተመለከቱ ጉዳዮች ቢነሱም እነኝህ ግን የዋናው ስጋት ማስፈፀምያ መሳርያ ሆነው ቀርበዋል።

ወቅታዊ መፍትሄዎች 

የመፍትሄዎቹ መሰረቶች የነገ መተማመኛ የሚሆኑ አካሄዶችን የብልጥግና ኦሮምያም ሆነ የአማራ ብልጥግና ባለስልጣናት በፍጥነት መሄድ አለባቸው። እነርሱም -

1) ሁለቱም ከምርጫው በኃላ የኢትዮጵያ ህገመንግስት ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ማሻሻያ ማድረግ ላይ እንደ ብልጥግና አንዱ ተግባራቸው እንደሚሆን እና ለእዚህም የራሳቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ መስማማት፣

2) ሁለቱም በእየራሳቸው  ጉያ የሚሰሩ የፕሮፓጋንዳ ስራዎች በፍጥነት እንዲያቆሙ የፈድራል መንግስት ጥብቅ መመርያ እና ቁጥጥር  እንዲያደርግ  ማድረግ፣

3) በኦሮምያ ክልል የሚንቀሳቀሱ እና በወንጀል የተሰማሩ የፅንፍ ኃይሎች ላይ ከቢሮክራሲ እስከ ልዩ ኃይል እርምጃ ክልሉ እንዲወስድ እንዲደረግ ይህንንም ከፌድራል መንግስት እንዲያስፈፅም ክልሉ ሙሉ አዎንታውን እንዲገልጥ፣

4) ከኦሮምያ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ እና የሌሎች ብሔር ተወላጆች ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ እና ይህንንም የፈድራል መንግስት ከሕግ ማስከበሩ ጀምሮ እስከ አስፈላጊው የሎጀስቲክ አቅርቦት ድረስ እንዲከናወን።በቀጣይም ነዋሪዎቹ የሚኖራቸው ዋስትና እራሳቸውን እስከመጠበቅ የማስታጠቅ ተግባር ሁሉ ከዝርዝር ሕግ ጋር ማውጣት፣

5) በአጣዬ፣ሻሸመኔ እና ሌሎች ቦታዎች የተፈፀሙት ግድያዎች በባህላዊ የእርቅ መንገድ እና በካሳ እንዲፈቱ ማድረግ እና የድርጊቱ ፈፃሚዎችንም ለፍርድ ማቅረብ ሂደት በቶሎ መጀመር ፣

6) መንግስት ከቡራዩ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች የተፈፀሙት ግጭቶች እነማን? እንዴት? እንደፈፀሙት ያልተሰሙ አስገራሚ እና ሕዝብ ያልሰማቸው የደህንነት ሪፖርቱን ዝርዝር መረጃዎችን ለሕዝቡ በግልጥ መግለጥ አለበት።ይህ በራሱ በቶሎ መሰራት ከሚገባው ቀዳሚ ተግባር ውስጥ አንዱ መሆን አለበት። ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ዝርዝር ሪፖርት ለሕዝብ ማሳወቅ እና ከሕዝቡ ጋር መተማመንን በቶሎ መፍጠር አለባቸው።

7) በእዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ከጥላቻ ዘመቻዎች መራቅ የሁሉም የመገናኛ ብዙሃን እና የማኅበራዊ ሚድያዎች ቀዳሚ ተግባር እንዲሆን እና ከእዚህ አስተሳሰብ የወጣውን የማኅበራዊ ሚድያው በራሱ የሚያርቅበት እና የሚወቅስበት ስልት መንደፍ እና ተግባራዊ ማድረግ እና 

8) በሁለቱ ክልሎች መሃል የሚነሱ ጉዳዮች ላይ የሌሎች ክልሎች ሚና መጉላት አለበት።የዳር ተመልካች ሳይሆኑ ነገ ኢትዮጵያ ለምትሄድበት የህብረት ጉዞ የሁለቱ ክልሎች ፕሮጀክት ብቻ እንዳይሆን ከአሁኑ ሌሎች ክልሎችም በሁሉም ሂደቶች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ የሚሉት ናቸው።

=================/////=========================

ማስታወቂያ /Advertisement 
====================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 

Saturday, April 17, 2021

በኦሮምያ እና በዓማራ ተወላጆች ሕፃናት እና እናቶች ደም የታጠበው፣ በኦሮምያ የበቀለው ፋሺዝም በኢትዮጵያዊነት መንፈስ መነቀል አለበት።

  • በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ጥቃት የፈፀመውን የህውሓት ጀሌ ጁንታ የሚል ስያሜ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ እናቶችን እና ሕፃናትን በሳንጃ እየወጋ የገደለ እና በመከላከያ ላይ ጥቃት የፈፀመውን ቡድን ፋሽሽት የሚል ስያሜ ሰጥተው ከኢትዮጵያ ምድር ማፅዳት አለባቸው።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ  ካሉት ክልሎች በተለየ መልኩ የኦሮምያ ክልል በሰው አዕምሮ የማይታሰቡ እጅግ አሰቃቂ እልቂቶች ተፈፅመውበታል።በክልሉ የበቀለው ፋሺሽታዊ ስርዓት መጀመርያ በህወሓት/ኢህአዴግ ስር ተወሽቆ በክልሉ የሚገኙ የሌሎች ክልሎች ተወላጆች ላይ የጥፋት ላንቃውን ከመክፈቱ በላይ ክልል ተብሎ በተሰጠው ቦታ በላይ በመጀመርያ ከሱማሌ ክልል ጋር በተፈጠረ ግጭት ከስምንት መቶ ሺህ በላይ የሚሆን ሕዝብ ከኦሮምያም ሆነ ከሱማሌ እንዲፈናቀል ተደረገ።በመቀጠል በጌድዮ ሕዝብ ላይ ተመሳሳይጥቃት ከፈፀመ በኃላ የዓማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ላይ በንፁሃን ላይ ጥቃት እየፈፀመ ነው።በኦሮምያ የበቀለው ፋሺዝም ዋና ኢላማው በክልሉ የሚኖሩ የሌላ ክልል ተወላጆች በተለይ የአማራው ተወላጅ ብቻ አይደለም።በእርግጥ የአማራ ተወላጆች በቀዳሚነት ተገድለዋል፣ተሰደዋል፣በእዚህ ዘመን ይፈፀማል ተብሎ በማይታሰብ ደረጃ ሕፃናት እና እናቶች ሳይቀሩ በአሰቃቂ መንገድ ተገድለዋል።ይህም ሆኖ ግን የኦሮምያ ተወላጆች በወለጋ፣በአርሲ፣በሐረር እና በሰሜን ሸዋ ሳይቀር ነዋሪዎች እና የአካባቢ ባለስልጣናት ሳይቀሩ ተገድለዋል።

ቢቢሲ አማርኛ በዛሬው ዕለት እንደዘገበው የሰሜን ሸዋ ዞን የፀጥታ ጉዳይ ኃላፊ አቶ አበራ መኮንን ለቢቢሲ እንደገለፁት ጥቃቱ የተፈፀመው በዞኑ በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ውስጥ ሲሆን "በጣም ከፍተኛ" ቁጥር ያለው የታጠቀ ኃይል "ወረራ" መፈፀሙን ተናግረዋል።የታጠቀው ኃይል "ቤቶችን ያቃጥላል፤ ሰዎችን ይገድላል" በማለትም ወደ አካባቢው የገባው የፌደራል የጸጥታ መዋቅርና የመከላከያ ሠራዊትም "ከአቅሙ በላይ" መሆኑን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በሌላ በኩል የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን ተቋም እንደተናገሩት በጥቃቱ የደረሰው ጉዳት የከፋ መሆኑን አመልክተዋል።ለጥቃቱም "ኦነግ ሸኔ እና ሌላ ተከታይ" ያሉትን አካል ተጠያቂ አድርገዋል የዞኑ የፀጥታ ጉዳይ ኃላፊ በመቀጠልም በጥቃቱ የጸጥታ አካላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አክለዋል።ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ማታ ጀምሮ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን እና በሰሜን ሸዋ ዞን መካከል በሚገኙ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር መኖሩን ገልጸው፤ ይህ ግን ጋብ ብሎ እንደነበር ኃላፊው አስታውሰዋል።ይሁን እንጂ ትናንት አርብ ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት ጀምሮ ከፍተኛ የታጠቀ ኃይል ወደ አካባቢው በመግባት በአጣዬ፣ በአንጾኪያና በኤፍራታ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተናግረዋል።ከላይ በዘገባው እንደተገለጠው በኦሮምያ ክልል የበቀለው ፋሽሽታዊ ቡድን ኦነግ ሸኔ ነው ወይንም ሌላ ስም እየሰጡ ምክንያት የሚደረደርበት ጊዜ አልፏል።የክልሉ ሀብት ለፋሺሽቱ መንቀሳቀሻ በግልጥ እየዋለ ክልሉ በጉዳዩ ላይ የሌለ ይመስል በተለያየ የቡድን ስሞች እየጠሩ ማሳበቡ አሁን ጊዜው ያለፈበት መሆኑ ግልጥ ሆኗል።

በመጨረሻም በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የሚመጣ ማንም ሆነ ማን በቸልታ ሊታለፍ አይገባውም።በኦሮምያ የበቀለው ፋሺዝም ሱማሌን አፈናቅሎ፣ጌድዮን ለመበተን ሞክሮ፣ደቡብን ተንኩሎ አሁን በአማራ ክልል ላይ ላንቃውን ከፍቷል።የኦሮምያ ክልል፣ሁሉም ክልሎች በተለይ የኢትዮጵያ መከላከያን በዋናነት የሚያዙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮምያ የበቀለውን ፋሺዝም መንቀል ቀዳሚ ተግባራቸው መሆን አለበት።ይህ ፋሺሽታዊ ቡድን በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይም ጥቃት ፈፅሟል።በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ጥቃት የፈፀመውን የህውሓት ጀሌ ጁንታ የሚል ስያሜ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ እናቶችን እና ሕፃናትን በሳንጃ እየወጋ የገደለ እና በመከላከያ ላይ ጥቃት የፈፀመውን ቡድን ፋሽሽት የሚል ስያሜ ሰጥተው ከኢትዮጵያ ምድር ማፅዳት አለባቸው።

================

ማስታወቂያ /Advertisement 
====================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሆሳዕና ከተማ መስተዳድር የፈፀመው ሸፍጥ፣ግፍ እና ወንጀል (አዲስ የወጣ ልዩ ጥናታዊ ፊልም)

ምንጭ = በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ የማ/ቅ ቴሌቭዥን 


ማስታወቂያ /Advertisement 
====================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 

Wednesday, April 14, 2021

ሁለተኛ ዙር ብሔራዊ የጸሎት መርሐግርብ በኢትዮጵያ ከሚያዝያ 8 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ይካሄዳል።ነቅተን እና ተግተን በጋራ ወደ ፈጣሪያችን እንጩኽ!



- የጸሎት መርሐግብሩ መክፈቻ እና መዝጊያ መርሐግርብ ላይ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመንግስት ኃላፊዎች ይገኛሉ።

- በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 3 እስከ 4 ሰዓት ድረስ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በቀጥታ ይተላለፋል።

- ብሔራዊ  ጸሎቱ አራት ጉዳዮችን ዓላማ ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል። እነርሱም - ኢትዮጵያ ምርጫውን  በሰላም እንድታጠናቅቅ፣የዓባይ ውኃ ሙሌቱን በቂ ዝናብ አግኝታ እንድትሞላ፣የእርስ በርስ ስምምነት እንዲጠነክር እና የኢትዮጵያን መጪ ሽግግር ላይ ያለመ ነው።

- በሳምንቱ ውስጥ የሚሰጡት ትምህርቶች ይቅርታ፣ ርህራሄ፣ ተስፋ፣ እምነት፣ ፍቅር እና ምስጋናን መሰረት ያደረጉ ይሆናሉ።

=================


ዜናውን አስመልክቶ ዋልታ ሚያዝያ 5/2013 ዓም ከእዚህ በታች ያለውን ዜና ዘግቧል።

ሁለተኛው ዙር በአይነቱና በይዘቱ ለየት ያለ ሀገር አቀፍ የጸሎትና ምህላ ሳምንት መታወጁን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሀፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፣ ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታ፣ የሰላምና መረጋጋት እጦት እንዲሁም ብሄርና ሃይማኖትን ማዕከል ያደረገ ግድያ መበራከት ሀገራዊ የጸሎትና ምህላ ሳምንት እንዲታወጅ አድርጓል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በጎረቤት ሀገራት ምስራቅ ቀጠና ላይ የሚታየው የድንበር አለመግባባቶችን በሚመለከት የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሀገራዊ ጸሎት ማድረግ ሌላኛው ወሳኝ ጉዳይ ተደርጎ እንዲወሰድ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በዚህ አሳሳቢ ወቅት ስለሆነውና እየሆነ ስላለው ሁሉ በደልና ጥፋት በፈጣሪ ፊት በመቅረብ በንስሃ ከራስና ከፈጣሪ ጋር እርቅ መፈጸም እንደሚገባ ያሳሰቡት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ፣ የጋራ መርሃ ግብሩ ሚያዝያ 7 ከቀኑ 9 ሰዓት እንደሚታወጅ አስታውቀዋል፡፡

መርሃ ግብሩም የሁሉም እምነት ተቋማት፣ በ6ኛው አገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በይፋ እንደሚታወጅ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ከሚያዚያ 8 ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ቀናት የሚቆይ በሁሉም አባል የሃይማኖት ተቋማት በተናጠል የሚዘጋጅ ጸሎትና ትምህርት በመገናኛ ብዙሃን ጣቢያዎች ይተላለፋልም ተብሏል፡፡

በመገናኛ ብዙሃን በሚተላለፍ ፕሮግራም የ1 ሳምንት ቆይታ በሚኖረው የቴሌቪዥን ስርጭት ከምሽት 3 እስከ 4 ሰዓት እንዲተላለፍ የሚደረግ ነው፡፡

ካለፈው ዓመት በተለየ መልኩ ዜጎች ከፈጣሪ ጋር በመቀራረብ በሀገሪቱም ላይ ፍትህ እንዲሰፍን ምርጫውም ሰላማዊ እንዲሆን በምልጃ የሚቀረብበት መሆኑንም ጠቅላይ ፀሐፊው አመልክተዋል፡

ወቅቱ በኦርቶዶክስ አብይ ጾም እና በሙስሊም እምነት ተከታዮች ዘንድ ደግሞ የረመዳን ጾም የሚከናወንበት እንዲሁም ሌሎች እምነት ተቋማት ለመልካም ተግባራት ተባባሪ በመሆናቸው የተወሰነ ስለመሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

ጸሎትና ምህላ የሃይማኖት ተቋማት ችግር መፍቻ እንደሆነ ታምኗል፤ የታመነበት በዚሀም ኢትዮጵያውያን በታሪክ በጋራ ተሻግረው የመጡ በመሆናቸውም ዛሬም የተደቀነባቸውን ፈተናዎች በጋራ እንደሚያልፉ የሚጠበቅ ስለመሆኑ ነው ተብሏል፡፡

በተቀሩት ቀናት ስለ ይቅርታ፣ ርህራሄ፣ ተስፋ፣ እምነት፣ ፍቅር እና ምስጋና በተመረጡ ርዕሶች ተከታታይ ትምህርቶችን ተደራሽ በማድረግ እንደመክፈቻው ሁሉ አርብ ሚያዚያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም  በልዩ ዝግጅት የመዝጊያ መርሃ ግብር እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገልጿል፡፡

*********************************
ማስታወቂያ /Advertisement 
====================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 

Monday, April 5, 2021

በኖርዌይ የዓባይ ግድብ ገቢ የገቢ ማሰባሰብያ መርሐግብር ቅዳሜ ሚያዝያ 2/2013 ዓም  (አፕሪል 10/2021 ዓም)

ለዓባይ ግድብ ገቢ የሚያደርጉበት የባንክ  ሂሳብ ወይንም ቪፕስ ቁጥር 
የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ (ኮምዩኒቲ) የባንክ ሂሳብ ቁጥር  15034313420 ሲሆን በቪፕስ ለመላክ ለምትፈልጉ 647675 በመጠቀም የታሪኩ አካል መሆን ይችላሉ።

ሚያዝያ 2/2013 ዓም (ማርች 10/2021 ዓም) በኖርዌይ ሰዓት አቆጣጠር 15 ሰዓት (3PM) ጀምሮ ለሚኖረው የዙም መርሐግብር መግቢያ ከእዚህ በታች ያለውን ማስፈንጠርያ (ሊንክ) እና መግቢያ ኮድ ይጠቀሙ።

Topic: GERD Norway 
Time: Apr 10, 2021 03:00 PM Oslo 

Join Zoom Meeting 

Meeting ID: 665 4122 0386 
Password: GERD 




*********************************
ማስታወቂያ /Advertisement 
====================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 

Saturday, April 3, 2021

በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በእዚህ ሳምንት ውሃ በጠጡ ቁጥር ለአባይ ግድብ ማዋጣት አለማዋጣታቸውን እራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው።ዶ/ር ስለሺ በቀለ፣የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር በመጪው ቅዳሜ በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ያገኛሉ።

  • በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይህ ዕድል ሊያመልጣቸው ይችላል።ግድቡ ሊጠናቀቅ የቀረው 20% ብቻ ነው።ለራስዎም ለልጆችዎም የታሪኩ አካል ሳይሆኑ ሊያልፍ ነው።

ኢትዮጵያ በክፍለዘመኑ አቅጣጫ ቀያሪ የተባለለትን የዓባይ ግድብ መገንባት ከጀመረች መጋቢት 24/2013 ዓም 10ኛ ዓመቷን ደፈነች።በእነኝህ ዓመታት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ቢያደርጉም አሁንም ግን በውጭ ከሚኖረው ኢትዮጵያዊ አቅም እና ብዛት አንፃር ሲታይ ብዙ እንደሚቀር ይታወቃል።በተለይ ለግድቡ አስተዋፅኦ ከአውሮፓ እና አሜሪካ ይልቅ በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አስተዋፅኦ መብለጡ በአውሮፓ እና አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚያስቆጭ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።

በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባለፈው ስርዓት ወቅት ከመንግስት ጋር በነበሩ ቅራኔዎች እና በዓባይ ፕሮጀክት ግልፅ አሰራር ላይ በነበራቸው ጥያቄ መሰረት ብዙዎች በግድቡ መዋጮ ላይ አልተሳተፉም።ይህ ማለት በከፍተኛ ደረጃ ያዋጡ የሉም ማለት አይደለም። ሆኖም ግን ከነዋሪው ቁጥር አንፃር ሲታይ መዋጣት ባለበት ደረጃ አልተዋጣም ለማለት ነው።አሁን ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ደረጃ ሊያዋጡ የሚችሉበት ዕድል ተከፍቶላቸዋል።ይህ በራስዎ፣በልጆችዎ እና በቤተሰብ ስም ጭምር የአቅምዎትን የሚያዋጡበት ታላቅ ዕድል ነው።ይህ ዕድል ሊያመልጥ ይችላል።በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይህ ዕድል ሊያመልጣቸው ይችላል።ግድቡ ሊጠናቀቅ የቀረው 20% ብቻ ነው።ለራስዎም ለልጆችዎም የታሪኩ አካል ሳይሆኑ ሊያልፍ ነው።

በያዝነው ሳምንት ልዩ የአባይ ግድብ ሳምንት ብለው ለራስዎ ቃል ይግቡ።ውሃ በጠጡ ቁጥር ለአባይ ግድብ ማዋጣት አለማዋጣትዎን እራስዎን ይጠይቁ።ካላዋጡ አሁኑኑ የታሪኩ አካል ይሁኑ።
ይህ በእንዲህ እያለ በሚያዝያ 2/2013 ዓም (ማርች 10/2021 ዓም) በኖርዌይ የሚገኙ የሲቪክ ድርጅቶች በኖርዲክ ሀገሮች የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ከኢትዮጵያ ማኅበረሰብ (ኮሚንቲ) በኖርዌይ ጋር በአንድነት ሆነው ልዩ የዓባይ ግድብ አስተዋፅኦ መርሐግብር በዙም አዘጋጅተዋል።ቀደም ብሎ በኖርዌይ የሚገኙ ሲቪክ እና ኮሚንቲ በአንድነት ለግድቡ ሲያሰባስቡ ነበር የሰነበቱት።በእዚህ በመጪው ሚያዝያ 2/2013 ዓም (ማርች 10/2021 ዓም) በኖርዌይ የሰዓት አቆጣጠር ከ15 ሰዓት ጀምሮ በተዘጋጀው መርሃግብር ላይ ዶ/ር ስለሺ በቀለ፣የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር፣ አምባሳደር ድሪባ ኩማ በኖርዲክ ሀገሮች የኢትዮጵያ አምባሳደር እና ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፤ ደራሲና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና የሥነ ጽሑፍ መምህር ይገኛሉ።

በዕለቱ ከኖርዌይ የተዋጣውን የገንዘብ መጠን ይገልጣል።አሁን የእርስዎ ተራ ነው።ላለፉት ዓመታት በልዩ ልዩ ምክንያቶች ለዓባይ ግድብ አዋጥተው የታሪክ አካል ካልሆኑ።አሁን አያምልጥዎት።

ለዓባይ ግድብ ገቢ የሚያደርጉበት የባንክ  ሂሳብ ወይንም ቪፕስ ቁጥር 
የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ (ኮምዩኒቲ) የባንክ ሂሳብ ቁጥር  15034313420 ሲሆን በቪፕስ ለመላክ ለምትፈልጉ 647675 በመጠቀም የታሪኩ አካል መሆን ይችላሉ።

ሚያዝያ 2/2013 ዓም (ማርች 10/2021 ዓም) በኖርዌይ ሰዓት አቆጣጠር 15 ሰዓት (3PM) ጀምሮ ለሚኖረው የዙም መርሐግብር መግቢያ ከእዚህ በታች ያለውን ማስፈንጠርያ (ሊንክ) እና መግቢያ ኮድ ይጠቀሙ።

Topic: GERD Norway 
Time: Apr 10, 2021 03:00 PM Oslo 

Join Zoom Meeting 

Meeting ID: 665 4122 0386 
Password: GERD 

ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይጠብቅ።
*********************************
ማስታወቂያ /Advertisement 
====================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 





ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።