ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, April 20, 2021

ለወቅታዊው የኢትዮጵያ ጉዳይ መፍትሔዎቹ
ነባራዊ ሁኔታ 

በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ አራት ኃይሎች ከወዲህ ወዲያ ሲሉ ይታያሉ።እነርሱም - ለዘብተኛ ጎሰኞች፣አክራሪ ጎሰኞች ፣ዲሞክራሲያዊ ፌድራልስቶች እና ፖለቲካ-ጠል የሰብአዊነት አራማጆች ናቸው

ለዘብተኛ ጎሰኞች

በለዘብተኛ ጎሰኞች ስር የቀድሞ የብአዴን፣ኦህዴድ እና የደቡብ ካድሬዎች ቀዳሚ ናቸው።እነኝህ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሲማሩም ሁኑ ሲመለመሉ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር የብሔር ፖለቲካ በሀገሪቱ አለመስፈኑ ነው እየተባሉ የተመለመሉ ናቸው።በመጀመርያ ቀንደኛ የጎሳ ፖለቲካ ሰባኪ ሆኑ።ቀጥሎ ፖለቲካው፣ኢኮኖሚው እና ምጣኔ ሃብቱ በህወሓት ስር መጠቃለሉን ሲያውቁ አጉረመረሙ።ትንሽ ቆይቶ ህዝቡ በህወሓት/ኢህአዴግ ላይ ሲነሳ የለውጥ ሐዋርያ ሆነው ወጡ እና የነበሩበትን ስርዓት የሚረግሙ ሆኑ።ግማሾቹ በይፋ ይቅርታ ጠየቁ።የተቀሩት ግን በተለይ አሁን ምርጫ እየቀረበ ስመጣ ስልጣን እንደሚያጡ ስለተገነዘቡ ወደ አክራሪ ጎሰኞች በመግባት እና ባለመግባት መሃል እየዋለሉ አሉ።

ዲሞክራሲያዊ ፈድራልስቶች 

እነኝህኞቹ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ችግር በማጥናት ዕድሜያቸውን የፈጁ፣ቀድሞ እንዳይናገሩ የታፈኑ፣አሁን ደግሞ በአክራሪ እና ለዘብተኛ ጎሰኛ ቡድኖች የሚኮረኮሙ ናቸው።ለእነኝህኞቹ ትልቁ እፎይታ የህወሓት መወገድ ቢሆንም በአክራሪ ጎሰኞች ብዙ ፈተና በግልጥም በስውርም እያጋጠማቸው ያሉ ናቸው።ለውጡን ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት ከገቡ በኃላ መልካም ተስፋቸው   መጪው ምርጫ ላይ የመሳተፍ ዕድል በማግኘታቸው ነው። ዲሞክራሲያዊ ፌድራልስቶች የኢትዮጵያ ችግር በእውነተኛ ዲሞክራሲ ላይ የተመሰረተ  የፈድራላዊ አስተዳደር ይፈታል  ብለው ያምናሉ።

አክራሪ ጎሰኞች 

አክራሪ ጎሰኞች ዋና መሰረቶቻቸው ሶስት ናቸው። እነርሱም ፍርሃት፣ጥርጣሬ እና የጥላቻ ትርክቶች።አክራሪ ጎሰኞች በዋና ዋና የኢትዮጵያ የወቅቱ ክልሎች ማለትም በአማራ፣ኦሮሞ እና ትግራይ ፖለቲካ ውስጥ እስከ ጉልበታቸው ተነክረውበታል።በፍርሃት አንዱ አንዱን እንዲፈራ አድርገው ይሰብካሉ።ላለመተማመን የሚጠራጠሩት አንዱ የበላይ ሊሆን እየሰራ ነው።ይህንን ታሪካዊ ጊዜ ከተበለጥኩ ጎሳዬን ''አስበላለሁ'' በእዚህም ተወቃሽ እሆናለሁ ብለው ተከታዮቻቸውን ይሰብካሉ።ሕዝቡም ውስጥ በሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ስጋት ማሳደር ችለዋል።በእዚህ ሁሉ መሃል ተግባብተው እንዲሰሩ የጎሳ ፖለቲካን ጥለው ዘመኑን የዋጀ አስተሳሰብ እንዲያራምዱ ሲነገራቸው ደግሞ ያደጉበት የጥላቻ ትርክቶች ከፊታቸው እየተደቀነ አላላውስ ይላቸዋል።በውነቱ ከሆነ አክራሪ ጎሰኞች እውነተኛ አዛኝ ቢያገኙ  ሕክምና ያስፈልጋቸዋል።ችግሩ ሁሉም ድንጋይ ስለሚወረውርባቸው በውስጣቸው ያለውን ፍርሃት፣ጥርጣሪ እና የጥላቻ ትርክት የበለጠ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ያገኙ ያህል ለእሳቢያቸው ማሳመኛ ምክንያት ያገኙ አድርገው ይቆጥሩታል።

ፖለቲካ-ጠል የሰብአዊነት አራማጆች

እነኝህ አሁን ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር እንዴት እንደመጣ፣ወዴት እንደሚሄድ፣ምን ዓይነት መንግስት ይምጣ የሚጨነቁ አይደሉም። በራሳቸው ጉዳይ ተይዘዋል።ነገር ግን ምንም አይነት አስተዳደር መጣ መለኪያቸው የሰብዓዊነት ልኩ ብቻ ነው።ይህ ባብዛኛው ሕዝብ ዘንድ የሚንፀባረቀው ዕይታ መለኪያው ለሁሉም የፖለቲካ ወቀሳዎች መንግስትን ስለሚያጋልጥ የመንግስት ተቃዋሚዎች በቀላሉ የሚያንቀሳቅሱት እና ስሜቱን ኮርኩረው የሚያስነሱት ይህንን የኅብረተሰብ ክፍል ነው።ይህ የኅብረተሰብ ክፍል ፖለቲካዊ ንቃትም ሆነ የመተንተን አቅም ስለሌለው ለሴራ ፖለቲከኞች በቀላሉ የተጋለጠ እና ስሜት የሚኮረኩሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሴረኞቹ በአንድ እጃቸው እራሳቸው ከሰሩ በኃላ በሌላ እጃቸው ይህንኑ የኅብረተሰብ ፍል ቀስቅሰው እንዲጠቃ የፈለጉትን የፖለቲካ ድርጅት ወይንም እራሱን መንግስትን ያሳምፁበታል።

ገመድ ጉተታው 

የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ከተጀመረ ከዛሬ ሶስት ዓመት ወዲህ ትልቁ እና የጎላው የገመድ ጉተታ የነበረው በህወሓት እና በብልጥግና መሃል ዋነኛው ሲሆን ይህንን በመከተል ሌላው የገመድ ጉተታ በኦሮምያ ብልጥግና ውስጥ ያለው የአክራሪ ጎሳ እና ለዘብተኛ (ኢትዮጵያዊነትን በሚያቀነቅነው) መሃከል ያለው ውጥረት ነው።አክራሪው ቡድን ከቢሮክራሲው እስከ የክልሉ ልዩ ኃይል ድረስ የተበተነ እንደሆነ ሲነገር ይሄው ቡድን በዋናነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድን ቤተመንግስቱን ከማደሳቸው ጀምሮ  ኢትዮጵያን ወደቀደመ ክብሯ እንመልሳታለን የሚለው አባባላቸውን ጨምሮ እየጠቀሰ በዙርያው በተኮለኮሉት የፅንፍ አስተሳሰብ አራማጆች ዘንድ ሁሉ  ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከስልጣን እንዲወርዱ የማይጭረው መሬት የለም። 

የፅንፍ ቡድኑ ይህንን የሚያደርገው በቀጥታ በትጥቅ ትግል ከመዋጋት ጀምሮ ከሀገር ውስጥ የተዘጋው የኦኤምኤን ሚድያ በውጭ ሀገር በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በመንግስት ላይ የስም ማጥፋት እና ያልተሳኩ የአመፅ ጥሪዎችን እስከመጥራት ደርሷል። ይህም ሆኖ ግን አሁንም በሌላ ማዶ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሴራ ፖለቲካ ለመክሰስ የሚሞክሩ ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፅንፍ ቡድኑ ጋር እስከ የሕይወት ማጥፋት ሙከራ ተደርጎባቸው፣የኢትዮጵያን አንድነት ማስፈን የጎሳ ፖለቲካን ማጥፋት ዓላማቸው እንደሆነ በግልጥ እየተናገሩም አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚከሱ አሉ።ለእዚህ ዋና ማሳያ የሚያደርጉት በኢትዮጵያ በተለይ የአማራ ሕዝብ ላይ ዓላማ ያደረጉ ጥቃቶች ላይ አፋጣኝ ምላሽ አይሰጡም የሚል ነው።

ከላይ የተጠቀሱት ነባራዊ ሁኔታዎች ባሉበት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ አንፃር በተለይ በፅንፍ ኃይሎች ፋሺሽታዊ በሆነ መልኩ በህፃናት፣ሴቶች እና አረጋውያን ላይ ሳይቀር የተፈፀመው ግድያ እና በሺህ የሚቆጠሩ ''ሀገራችሁ አይደለም'' እየተባሉ ከሁለት ትውልድ በላይ የኖሩ የተሰደዱበት፣የመተከል፣ወለጋ  እና በሌሎች ቦታዎች የተፈፀሙት የግድያ ተግባራት በተጨማሪ በሰሜን ሸዋ አጣዬ ከተማ ላይ እነኝሁ መሰረታቸውን በኦሮምያ ያደረጉ የፅንፍ ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት የከተማዋ መሰረተ ልማት ሙሉ በሙሉ መውደማቸው የአለፈው ሳምንት መጨረሻ አሳዛኝ ድርጊት ነው።ይህንን ተከትሎ  ድርጊቶቹን በመቃወም ዛሬ በባሕርዳር፣ወልዲያ፣ደሴ እና ሌሎች የአማራ ከተሞች ከፍተኛ ሰልፎች ተካሂደዋል።

በኦሮሞ እና የአማራ ብልፅግና መሃል ያሉት ጊዜያዊ የልዩነት ምንጮች

ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ዘጠና ቀናት ውስጥ ወሳኝ የሁኑ ሁለት ተግባራት አሏት።የመጀመርያው የምርጫ ጉዳይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የዓባይ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ነው።ስለሆነም አሁን ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ውጥረት ፈፅሞ አስፈላጊ አይደለም።አሁን በተፈጠረው ሁኔታ በዛሬው ዕለት በግብፅ ሚድያዎች ኢትዮጵያ እንደተከፋፈለች እየተደረገ በሚነዛ ወሬ ፈንጠዝያ ላይ እንደሆኑ ዛሬ ሲደመጥ ነው የዋለው።ስለሆነም ኢትዮጵያ ወቅታዊ ውጥረቶችን መፍታት እና ወደ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ማትኮሩ እጅግ አስፈላጊ ነው። በመሆኑም  አፋጣኝ መፍትሄዎች ከመንግስትም፣ከሁሉም የፖለቲካ አካላትም ይጠበቃል።በቅድምያ ግን በኦሮምያ ብልጥግና እና የአማራ ብልጥግና መሃከል ያሉት ግዝያዊ ልዩነት ሃሳብ ምንጮች ምንድናቸው?

በኦሮሞ እና የአማራ ብልፅግና መሃል ያሉት ጊዜያዊ የልዩነት ምንጮች የሚከተሉት ናቸው። እነርሱም - 
  •    በኦሮምያ ብልፅግና ውስጥ አክራሪ የፅንፍ ኃይሎች በተለየ መንገድ ከቢሮክራሲ እስከ ልዩ ኃይሉ ውስጥ መመሸጋቸው እና አሁንም የሚፈፀሙ ግድያዎች በእነኝሁ ኃይሎች አይዞህ ባይነት መደገፉ፣ 
  •   ሕገ መንግስቱ የአማራን ሕዝብ የማይጨምር መሆኑ እና ሀገር አልባ ሆኖ በኦነግ እና ትህነግ መሃል የተዘጋጀ ሰነድ መሆኑ በአማራ ክልል በኩል በመወሰዱ፣
  •  በሁለቱም ክልሎች ውስጥ ያሉት ህገ-ክልል መንግስታቸው በራሱ የተለያየ መሆኑ።ይሄውም የአማራ ክልል በውስጡ ላሉት ብሔረሰቦች የባለቤትነት መብት ሲሰጥ የኦሮምያ ግን በክልሉ ያሉትን ብሔር ብሔርሰቦች እንደማያውቃቸው የሚገልጥ አረፍተነገር መያዙ እና 
  •  በሁለቱም ክልሎች የሚገኙ የፅንፍ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች ለእየራሳቸው ሕዝብ አንዱ አንዱን ሊውጠው ነው የሚለው የማስደንበርያ አሰቃቂ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎች  የሚሉት ዋና እና መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው። 
ከእዚህ በተጨማሪ ያለፈ ታሪክ ትርክት የተመለከቱ ጉዳዮች ቢነሱም እነኝህ ግን የዋናው ስጋት ማስፈፀምያ መሳርያ ሆነው ቀርበዋል።

ወቅታዊ መፍትሄዎች 

የመፍትሄዎቹ መሰረቶች የነገ መተማመኛ የሚሆኑ አካሄዶችን የብልጥግና ኦሮምያም ሆነ የአማራ ብልጥግና ባለስልጣናት በፍጥነት መሄድ አለባቸው። እነርሱም -

1) ሁለቱም ከምርጫው በኃላ የኢትዮጵያ ህገመንግስት ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ማሻሻያ ማድረግ ላይ እንደ ብልጥግና አንዱ ተግባራቸው እንደሚሆን እና ለእዚህም የራሳቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ መስማማት፣

2) ሁለቱም በእየራሳቸው  ጉያ የሚሰሩ የፕሮፓጋንዳ ስራዎች በፍጥነት እንዲያቆሙ የፈድራል መንግስት ጥብቅ መመርያ እና ቁጥጥር  እንዲያደርግ  ማድረግ፣

3) በኦሮምያ ክልል የሚንቀሳቀሱ እና በወንጀል የተሰማሩ የፅንፍ ኃይሎች ላይ ከቢሮክራሲ እስከ ልዩ ኃይል እርምጃ ክልሉ እንዲወስድ እንዲደረግ ይህንንም ከፌድራል መንግስት እንዲያስፈፅም ክልሉ ሙሉ አዎንታውን እንዲገልጥ፣

4) ከኦሮምያ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ እና የሌሎች ብሔር ተወላጆች ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ እና ይህንንም የፈድራል መንግስት ከሕግ ማስከበሩ ጀምሮ እስከ አስፈላጊው የሎጀስቲክ አቅርቦት ድረስ እንዲከናወን።በቀጣይም ነዋሪዎቹ የሚኖራቸው ዋስትና እራሳቸውን እስከመጠበቅ የማስታጠቅ ተግባር ሁሉ ከዝርዝር ሕግ ጋር ማውጣት፣

5) በአጣዬ፣ሻሸመኔ እና ሌሎች ቦታዎች የተፈፀሙት ግድያዎች በባህላዊ የእርቅ መንገድ እና በካሳ እንዲፈቱ ማድረግ እና የድርጊቱ ፈፃሚዎችንም ለፍርድ ማቅረብ ሂደት በቶሎ መጀመር ፣

6) መንግስት ከቡራዩ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች የተፈፀሙት ግጭቶች እነማን? እንዴት? እንደፈፀሙት ያልተሰሙ አስገራሚ እና ሕዝብ ያልሰማቸው የደህንነት ሪፖርቱን ዝርዝር መረጃዎችን ለሕዝቡ በግልጥ መግለጥ አለበት።ይህ በራሱ በቶሎ መሰራት ከሚገባው ቀዳሚ ተግባር ውስጥ አንዱ መሆን አለበት። ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ዝርዝር ሪፖርት ለሕዝብ ማሳወቅ እና ከሕዝቡ ጋር መተማመንን በቶሎ መፍጠር አለባቸው።

7) በእዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ከጥላቻ ዘመቻዎች መራቅ የሁሉም የመገናኛ ብዙሃን እና የማኅበራዊ ሚድያዎች ቀዳሚ ተግባር እንዲሆን እና ከእዚህ አስተሳሰብ የወጣውን የማኅበራዊ ሚድያው በራሱ የሚያርቅበት እና የሚወቅስበት ስልት መንደፍ እና ተግባራዊ ማድረግ እና 

8) በሁለቱ ክልሎች መሃል የሚነሱ ጉዳዮች ላይ የሌሎች ክልሎች ሚና መጉላት አለበት።የዳር ተመልካች ሳይሆኑ ነገ ኢትዮጵያ ለምትሄድበት የህብረት ጉዞ የሁለቱ ክልሎች ፕሮጀክት ብቻ እንዳይሆን ከአሁኑ ሌሎች ክልሎችም በሁሉም ሂደቶች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ የሚሉት ናቸው።

=================/////=========================

ማስታወቂያ /Advertisement 
====================
Click the link below to Top-up your friends or family's mobile air time.
በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሀገር ቤት የሚኖር የቤተሰብ ወይንም የወዳጅዎን ስልክ ሂሳብ ሊሞሉ እንደሚችሉ ያውቃሉ? 
አገልግሎቱን ለማግኘት ከስር ሊንኩን ይጫኑ - 

No comments: