ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, April 28, 2021

ከከያኒ እስከ ቀዳሽ፣ከወታደር እስከ አካል ጉዳተኛ፣ከመሪ እስከ ተመሪ-ሕዝብ ለኢትዮጵያ የምንቆምበት ጊዜ አሁን ነው።በአጀንዳ ለመጥለፍ የሚሞክሩትን ወደ ጎን ብለን ቁልፉ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ እናተኩር! የህልውና ጉዳይ ነው።



  • በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለማወክ የተነሱትን አራት  ኃይሎች ለማሳፈር ከህዝብ፣ከከያኒው በተለይ ድምፃውያን እና ከመንግስት የሚጠበቁ አፋጣኝ ተግባራት 

ጊዜውን አለመረዳት፣መደነባበር፣የሚያዘውን ትቶ የማይያዘውን ለመያዝ መሞከር፣ቅድምያ የሚሰጠውን ትቶ የማይሰጠው ላይ ማተኮር፣የራስን ሀገር ሳያውቁ ማዋከብ እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች በግልጥ እየታዩ ነው።ኢትዮጵያን ራሳችን ሳናውቅ እንዳናጠፋት፣ ሌሎች ደግሞ አቅደው እና አውቀው እንዳያጠፏት ትኩረታችን ምን ላይ መሆን እንዳለበት እንወቅ! እጅግ ወሳኝ ጊዜ ላይ ነን።በግርግር እና በተደናገረ አስተሳሰብ ውስጥ ዋና አጥፊዎች ሆነን የምንቆመው እራሳችን እንዳንሆን ልብ ማለት አለብን።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለማወክ የተነሱት ኃይሎች  አራት ናቸው።አራቱም በተለያየ መልክ ይምጡ እንጂ ኢትዮጵያን በማተራመስ ሁሉም የሚያገኙት ጥቅም እንዳለ ያስባሉ።እነኝህ ኃይሎች - 1) በኦሮምያ ክልል ውስጥ እና በአማራ ብሔርተኝነት ውስጥ የበቀሉ እጅግ ፅንፍ የያዙ አስተሳሰቦች፣ 2) የህወሓት ዕርዝራዦች፣ 3) የውጭ ኃይሎች ግብፅ፣ሱዳን እና አንዳንድ የመካከለኛውና ምዕራብ ሀገሮች እና 4) በድብቅ የሚንቀሳቀሱ አክራሪ እና ፅንፈኛ አራማጅ የአልቃይዳ ውላጅ ኃይሎች ናቸው።

የመጀመርያው በኦሮምያ እና አማራ ክልል ውስጥ ያሉ የብሔር ፅንፍ ቡድኖች በአንድም ሆነ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የበላይነት ለመያዝ የሚደረግ አደገኛ የሽምያ ፖለቲካ ውስጥ የገቡ ይመስላሉ።እርግጥ ነው በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው የአማራ ንፁሃን ከወለጋ እስከ ሰሜን ሸዋ ጥቃት ተፈፅሞባቸው በከፍተኛ ፈተና ላይ ይገኛሉ።ሆኖም ግን ይህም ሆኖ እያለ በአማራ ክልል ውስጥም ሆነ በውጭ ካሉ አቀንቃኞች ጋር የአንድ ክልል የበላይነት በኢትዮጵያ ካልመጣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የማይረጋጋ አድርገው በማቅረብ ሕዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳ አደገኛ ስብከት የሚያራምዱ አሉ።በሌላ በኩል በኦሮምያም በክልሉ አክራሪ ፖለቲካ ኢትዮጵያን ካልሸበበ መረጋጋት እንደሌለ የሚሰብኩ አሉ።ሁለቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን በጠላትነት ፈርጀው ይንቀሳቀሳሉ፣ የሀገሪቱን ፖለቲካ ለማተራመስ ይሞክራሉ።

የተቀሩት የህወሓት ርዝራዦች፣የውጭ ኃይሎች እና የአልቃይዳ ውላጅ አሸባሪዎች ዓላማቸው ግባቸው እና ተግባራቸው ከእዚህ  በፊት በሰፊው በእዚህ ገፅ ላይ ተወስቷል።ዛሬ ላይ አፅንኦት መስጠት የሚያስፈልገው ሁሉም ጊዜው አሁን ነው ብለው በኢትዮጵያ ላይ የተነሱበት እና ጥምረት ለመፍጠር የሞከሩበት ጊዜ መሆኑ ነው። ሁሉም ኢትዮጵያን በማተራመስ እና አሁን ያለውን የፖለቲካ ስርዓት በአንድ ዓይነት የኃይል መንገድ በማስወገድ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ትርምስ በመፍጠር የቁርስራሹ ተካፋይ ለመሆን አሰፍስፈዋል። 

የአራቱም ኃይሎች የአጭር ጊዜ ግቦች - 

1) መጪው ምርጫ እንዳይሳካ ትርምስ መፍጠር 
2) ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ በትንሽ ሕዝብ ተሳትፎ እንዲደረግ እና ዋጋ እንደሌለው ወሬ ማናፈስ እና ሕጋዊነት ማሳጣት፣
3) ምርጫው ከተደረገ በኃላም የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዳይቀበለው መስራት እና 
4) በመጨረሻም ምርጫው የብሔር ግጭት ምክንያት እንዲሆን መስራት እና ኢትዮጵያን ማተራመስ በመቀጠል ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንድትገባ ማድረግ ነው።

ስለሆነም ከላይ የተጠቀሱትን ኃይሎች ሕልም መና ለማድረግ እና ኢትዮጵያን በሁለት እግሮቿ እንድትቆም ለማድረግ ከመንግስትም ሆነ ከሕዝቡ የሚጠበቁ ተግባራት አሉ።እነርሱም -

መንግስት መስራት ያለበት -
  • ማናቸውም ዓይነት የፅንፍ ማኅበራዊ ሚድያ መገናኛዎችን ለመቆጣጠር  ከግንቦት ወር መጀመርያ ጀምሮ  መዘጋት አለባቸው።
  • የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና ራድዮ በልዮ ሃገራዊ ዝግጅቶች ዝግጅቶቻቸው እና ዜናዎቻቸው ሁሉ መከለስ አለባቸው።
  • አንድ ማዕከላዊ የመረጃ ሰጪ አካል (እንደ ''ፋክት ቼክ'') ያለ መንግስት ማስተዋወቅ እና ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ሀገርም  ብቃት ባለው መልክ የውሸት ዜናዎችን በማስረጃ የሚመልስ ማዕከል ያስፈልጋል።
  • ከጦር ሰራዊት እስከ ፖሊስ በከፍተኛ ደረጃ ዘብ የሚቆሙበት ጊዜ መሆን አለበት።
  • በኢትዮጵያ ላይ የማያቆም የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ላይ የተሰማሩት በተለይ የጦር ኃይሉን መኮንኖች ጨምሮ ምክንያት በሌለው የስም ማጥፋት እና ሕዝብ እና መንግስትን ለማጋጨት ሌት ከቀን የሚሰሩት ላይ የእርምት እርምጃ መወሰድ አለበት።
  • ከውስጡ ያሉትን ሙሰኞች፣ጎሰኞች እና ብቃት የሌላቸውን ባለስልጣናት በተለይ የበታች ሹሞች ገለል ማድረግ።
ሕዝቡ መስራት ያለበት 
  • ኢትዮጵያዊ አሸናፊ ስነ ልቦናውን ከፍ ማድረግ እና በተለያየ መንገድ የስነ ልቦና ጦርነት የከፈቱበትን ከላይ የተጠቀሱትን አራት ኃይሎች ሰለባ እንዳይሆን ከግለሰብ ጀምሮ መዘጋጀት፣
  • ሁል ጊዜ መጥፎ እየነገሩ በሀገሩ እና በመንግስት ላይም የተጋነነ ወሬ የሚያቀብሉትን ሚድያዎች እና ዩቱብ፣ማኅበራዊ ሚድያዎች በሙሉ ውሸት ማጋለጥ እና አለመመልከት፣የእነርሱን ወሬ ይዘው የሚመጡትን ቦታ አለመስጠት።
  • ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተነሱ ኃይሎች ዋነኛ ትኩረት መጀመርያ ኢትዮጵያ ሃገረ መንግስቷን በምርጫ እንዳትመሰረት ማድረግ  መሆኑን አውቆ በብዛት በምርጫው መሳተፍ እና መብቱን ማስከበር።
  • መንግስት ከምርጫ በፊት እናስወግድ የምትል ውስጠ ወይራ ማናቸውም ዓይነት እንቅስቃሴ እና ፕሮፓጋንዳ ቀድሞ አውቆ የእዚህ ዓይነት ሃሳብ አራማጆችን ማሳፈር እና ማጋለጥ።
  • ለማናቸውም ሃገራዊ  አገልግሎት መነሳት እና ወጣቶችም ዝግጁ እንዲሆኑ መምከር።
  • ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚፈልጉ ኃይሎች ብዙ እርቀት እንደሚሄዱ አውቆ እራሱን ማዘጋጀት እና የውስጥ ከሀዲዎችን በእኩል ደረጃ መዋጋት እና 
በውጭም ሆነ በውስጥ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በጎሳ፣በሃይማኖት እና በመሳሰለው ሁሉ ሊከፋፍሉት የሚሞክሩትን ሁሉ በፅናት መዋጋት የሚሉት ናቸው።

 ከኪነ ጥበብ ሰዎች በተለይ ከድምፃውያን የሚጠበቅ -

የኪነ ጥበብ ሰዎች በተለይ ድምፃውያን በእዚህ ሀገር በምትጣራበት ጊዜ እንዳልሰሙ ተሸፋፍነው መተኛት የለባቸው።ለእዚህ ጊዜ ፈጠራቸውን ተጠቅመው ሕዝብ አንድ የሚያደርጉ፣የተናቆሩትን እና የተቃቃሩትን ወደ ህብረት የሚያመጣ፣ሀገር የሚያፈርሱትን የውጭም ሆኑ የውስጥ ባንዳዎች የሚሸነቁጥ ሕዝብን ግን የሚያስተሳስር ስራዎች በአጭር ጊዜ ማድረስ አለባቸው። ለችግር ጊዜ መንገድ የማያሳይ ከያኔ በሰላም ጊዜ ገንዘብ ለመሰብሰብ መምጣት የለባቸውም።ሕዝቡን ተስፋ ማሳየት፣ክፉውን እንዲርቅ መምከር እና በፅናት በኢትዮጵያዊነቱ እንዲቆም የሚያደርጉ ስራዎች በአጭር ጊዜ ከኪነጥበብ ሰዎች ይጠበቃል። 

ኢትዮጵያ ለዘላለም በፈጣሪዋ ጠባቂነት፣በልጆቿ ተጋድሎ ፀንታ ትኖራለች።

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።