ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, November 26, 2014

የግሪክን ብሔራዊ ህልውና የተፈታተነ ''ሶቨሪን ቦንድ'' ለኢትዮጵያ እንዴት ይሰራል?



ኢትዮጵያ ከእዚህ በፊት ከመንግሥታት፣አህጉራዊ ወይም ዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋማት ብድር ወስዳለች።አሁን ያለባት የብድር መጠን ከ20 ቢልዮን ዶላር ወይንም ከ400 ቢልዮን ብር በላይ መሆኑ ይታወቃል።ወደ ''ሶቨሪን ቦንድ'' እንድትገባ በዝግ ምክርቤት ወሰነ የተባለው የብድር አይነት ግን ኢትዮጵያ ከግል አበዳሪዎች ሁሉ በደላሎች ብድር እየፈለገች እንድትበደር የሚያደርግ፣በሙስና ለተሰነገ ሀገር ፈፅሞ የማይመከር ነው።ለመሆኑ የሶቨርን ቦንድ ምን ማለት ነው? ''ኢንቨስቶፕድያ እንዲህ ይገልፀዋል።

''ሶቨሪን ቦንድ'' ማለት በመንግሥታት  በውጭ ምንዛሪ የሚቀርብ የብድር ዋስትና ሲሆን የውጭ ምንዛሪው በጠንካራ አለም አቀፍ ገንዘብ (ሃርድ ከረንሲ) የተደገፈ ነገር ግን ለቦንድ ያዥው የበለጠ አደጋ ያለው '' ይላል 

''DEFINITION OF 'SOVEREIGN BOND'
A debt security issued by a national government within a given country and denominated in a foreign currency. The foreign currency used will most likely be a hard currency, and may represent significantly more risk to the bondholder.'' www.Investopedia.com

ምዕራባውያን እና ሶቨርን ቦንድ 

ብድሩን የምዕራብ ሃገራት ፍላጎት የታዳጊ ሀገሮች ወደገበያው መግባት ነው። ምክንያቱም አበዳሪ ሁል ጊዜ ተበዳሪ  ማግኘት ስራው ነው።ይህ ማለት ተበዳሪ በአዋጭም ይሁን በማያዋጣ መንገድ ላይ ቢሆን ለአበዳሪ ጉዳዩ አይደለም። አበዳሪ ገንዘቤ ባይመለስ በምን ሌላ አስገዳጅ ነገር ውስጥ አስገብቼ ያልታሰበ ሲሳይ ይገኛል? ነው ጥያቄው።ለእዚህ ነው የ''ፋይናንሻል ታይምስ'' ጨምሮ የኢትዮጵያን ወደ እዚህ ብድር መምጣት አሰማምሮ የፃፈው።ኢትዮጵያ ወደ ቻይና ተጠጋች የሚለውን ስጋት ለማራቅ ''በሶቨሪን ቦንድ'' መያዙ ለወደፊት 'ስልታዊ ጥቅም' አለውና።በሌላ በኩል ይህ ብድር የሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ማስፈፀምያ አንዱ ስልት ነው።

ግሪክን ያየህ ተቀጣ

 ግሪክ ባለፉት ሁለት ዓመታት የምጣኔ ሃብቷ ያን ያህል ያሽቆለቆለው ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ ሃገራት ስር በተለይ ጀርመን ስር እንድትንበረከክ የተደረገው በእዚሁ ''ሶቨርን ቦንድ'' አማካይነት ነው።የሀገሪቱ ህዝብም አደባባይ ወጥቶ የገዛ መንግስቱን የተቃወመው በእናንተ ሙስና ምክንያት ሀገሪቱ ከማትችለው ብድር ውስጥ አስገባችሁ በሚል ነበር።ይህንን ለመረዳት ''የሶቨሪን ብድር ቀውስ የዘመናዊዋ ግሪክ አሳዛኝ ሁኔታ''  ''The Sovereign Debt Crisis: A Modern Greek Tragedy'' በሚል ርዕስ የወጣውን ''የሴንት ሉዊስ ባንክ'' ፅሁፍ ያንብቡት።


ሉዓላዊነታችን አደጋ ላይ የመውደቅ እድል አለው 

በኢትዮጵያ ላይ የረጅም ጊዜ ስልታዊ ፍላጎት ያላቸው ሀገሮች በግለሰብ ወይንም በኩባንያ ስም ከአውሮፓ ወይንም ከአሜሪካ ብቅ ቢሉስ? ለምሣሌ የገንዘብ ችግር የሌለባቸው እንደ ሳውዲ አረብያ ያሉ ሀገሮች ገንዘባቸውን በባንክ ከማስቀመጥ በእደዚህ አይነት ብድር ለድሃ ሃገራት  ቢሰጡ ያተርፋሉ።ኢትዮጵያ ላይ በብዛት ብድር ሰጥተው መልሰው የነገር መቆስቆሻ ሊያደርጉት እና እስከ ጦርነት የሚያደርስ ብሎም በሉዓላዊነታችን  ላይ የሚጋረጥ አደጋ ሊያጋጥም ይችላል።በእንደዚህ አይነት መንገድ የሚነሱ ግጭቶች ደግሞ ወደ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሲደርስ ምንም አይነት የዲፕሎማሲ ድጋፍ የማያስገኝ ስለሆነ አበዳሪዎች በዓለም መድረክ የመሰማት እድላቸው ከፍተኛ ነው። ለእዚሁም ምክንያቱ ኩባንያዎቹ በተለያየ ጥቅም ከብዙ ሃገራት ጋር የጀርባ ንግግር ስላላቸው እና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብም ብድሩን መክፈል አለባት የሚሉ ቃላትን እንጂ ሌሎች ሁኔታዎችን የምያገናዝብበት ዕድል ፈፅሞ አይፈጥርለትም።በመሆኑም ሕጋዊ በሚመስል መንገድ ሀገር ለአደጋ ያጋልጣል ማለት ነው።

ባጭሩ የሶቨሪን ብድር በአለማችን የገንዘብ ስርዓት ውስጥ ያለ ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሃገራት ግን የሚገቡበት አግባብ የራሱ የተገደበ መስመር መያዝ ይገባው ነበር። ይህ የተገደበ መስመር ማለት-

 1/ ስለ ብድሩ ምንነት፣አስፈላጊነት እና የመክፈል አቅም በዝርዝር በስሙ ለሚበደሩት የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልፅ መነገር ነበረበት፣
2/ ህዝቡ በጉዳዩ ላይ መወያየት ነበረበት፣
3/ ሙስናው ቅጥ ባጣበት ሀገር እዴት ሊሰራ እንደሚችል መጤን ነበረበት፣
4/ብድሩ ለየትኛው ፕሮጀክት እና  ምን ያህል እንደሚወሰድ ለሕዝብ መታወቅ ነበረበት፣
5/ መንግስት የሚበደረውን የገንዘብ መጠን በሕግ ገድቦ ማስቀመጥ ነበረበት። ለምሳሌ ገንዘብ ባነሰው ቁጥር በደላላ አበዳሪ እየፈለገ የሚበደር ከሆነ መጨረሻው የት ሊሆን ነው?
6/ ኢትዮጵያ ብድሩን ተበድራ ለመክፈል የምታስበው ከየት እና ምንን ታሳቢ አድርጎ ነው? የሚለው  በግልፅ ለሕዝቡ መቅረብ ነበረበት።

እነኝህ ሁሉ ባልተደረጉበት ሁኔታ ኢትዮጵያን አፏን ለጉመው፣የመገናኛ ብዙሃንን ዘግተው፣የግል ጋዜጦችን አሽገው፣ፓርላማውን በዝግ ስብሰባ አስፈራርተው በእኛ እና በልጆቻችን ስም የመበደር መብት እንዴት ያለ ሕዝብን የመናቅ ደረጃ ነው? በትክክል ከላይ ከተባለው አንፃር ስንመለክተው አደጋ ላይ ነን።ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ በተድበሰበሰ መንገድ የሚሰራው ሥራ ''ምን ያህል ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ የያዙ ሰዎች አመራር ላይ አሉ?'' ብሎ የመጠየቂያው ጊዜ ነው።

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ከእራሷ ሀብት አፍርታ፣ወደውጭ የሚላክ ምርት ጨምራ የውጭ ምንዛሪ አግኝታ የመኖር አቅሟን ላለፉት 23 ዓመታትም መፍጠር አለመቻሏ አመላካች አንዱ መንገድ ይህ አሁን በቅርብ ቀናት ውስጥ አውሮፓ ላይ  ''ልንበደር ነው አድገናል'' የሚለው መግለጫ በኢህአዲግ/ወያኔ ባለስልጣናት ሊሰጥ መሆኑ ነው።የእድገታችን መገለጫ መበደር እንዴት ሊሆን ይችላል? ፖለቲካዊ ዝናን ለማግኘት የተገቡባቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ወሳኝ ግን ጠቃሚ የነበሩትን እንደ በምግብ እራስን መቻል፣ወዘተ ፕሮጀክቶች ችላ እንዲባሉ አላደረገም ወይ? ይህ የተሳሳተ የፖሊሲ ውሳኔ ዛሬ ዋጋ እያስከፈለን አይደለም ወይ?  ነገሩን በአንክሮ ለተከታተለው ሰው አሳዛኝ ነው።ጥያቄው ግን አይቆምም የግሪክን ብሔራዊ ህልውና የተፈታተነ ''ሶቨሪን ቦንድ'' ለኢትዮጵያ እንዴት ይሰራል?

ጉዳያችን
ህዳር 18/2007 ዓም (ኖቬምበር 27/2014)

ቅኝ ግዛት እና ሕዝቡን ቢራ እንዲጠጣ ማበረታታ ምን እና ምን ነበሩ? ዳቦ ሳንጠግብ እና የምናነበውን ጋዜጣ ሁሉ ዘግተው አዕምሯችንን እያደነዘዙ የቢራ ፋብሪካ መደርደር ምን ይባላል?








በባዕዳን በቅኝ ግዛት ተይዘው የነበሩ ሀገሮች ሁለት ዋና ዋና ሀብታቸውን አጥተዋል።( በነገራችን ላይ በባዕዳን ቅኝ ግዛት የተያዙቱኑ ነው ያልኩት እንጂ ፕሬዝዳንት መሆን ያማረው ሁሉ ቅኝ ግዛት ነበርኩ እያለ የእራሱን እና የህዝቡን ክብር ገደል የሚጨምረውን አይመለከትም።)
እነኝ በቅኝ ግዛት የተያዙ ሃገራት ካጡት ሀብት መካከል የመጀምርያው ምጣኔ ሀብታቸው የባዕዳን ገዢዎቻቸውን ምጣኔ ሀብት እንዲያገለግል ተደርጎ መዋቀሩ  ሲሆን ሌላው የነበራቸውን ከቀደሙት የወረሱት ባህል እና የአኗኗር ዘይቤ ነው።ሃገራቱ እንዲያመርቱ የተደረጉትም ሆነ ወደውጭ የሚልኩት ምርት የገዢዎቻቸውን የጥሬ ዕቃ ፍላጎት ብቻ ላይ እንዲያተኩር ተደረገ።ዛሬ እነ ኬንያ፣ታንዛንያ እና ዑጋንዳን ብንመለከት ሃገራቱ ለንግድ የሚሆኑ የእርሻ ምርታቸው በወቅቱ እንግሊዝ ትፈልገው ከነበረው ምርት ጋር ብቻ እንዲቆራኝ የተደረገ ነው።

በአንፃሩ ደግሞ አውሮፓውያን በእነርሱ ክህሎት ብቻ የሚሰራውን ምርት ቅኝ ተገዢዎች እንዲቀበሉት አደረጉ።አፍሪካውያን ቡና ከመጠጣት ቢራ እንዲጠጡ እና እንዲለማመዱ ተደረጉ።እንድያውም አንዳንድ ቦታ ቢራ ለመጠጣት ያልደረሱ ታዳጊዎች ሁሉ በሰሩት ሥራ ልክ የሚከፈላቸው ቢራ የነበረበት ወቅት ነበር።የቢራ መጠጥ ከቅኝ ግዛት በኃላም በሰፊው ተለመደ።ብርጭቆ ተጋጨ።በዓል የሚከበረው በቢራ እና በቢራ ብቻ ሆነ። ዛሬ በዑጋንዳ እና በታንዛንያ ቢራ የሚጠጣውን ያክል ቡና አይጠጣም።በአውሮፓ ደግሞ ቡና የሚጠጣውን ያክል ቢራ አይጠጣም።አፍሪካውያን የሚጠጡበት ቢራ በትንሹ ግማሽ ሊትር የሚይዝ ነው።አውሮፓውያን ቡና የሚጠጡበት ስኒ የሻይ ብርጭቆ ያክላል።ቡናው ለንቃት ወደ አውሮፓ ይላካል።

የመንገድ እና ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች ዝርጋታ የቅኝ ገዢዎች የሰሩት አሁንም የሀገራቸውን ምጣኔ ሃብት እንዲገነባ ነው።ለምሳሌ የወደብ ቦታዎች የሚመረጡት የሀገራቱን አንጡራ ሀብት በተገቢ መልክ ለማውጣት ከማመቸቱ አንፃር እንጂ ለሕዝብ ከሚሰጠው ጥቅም አንፃር አይደለም።በምዕራብ አፍሪካ እና በምስራቅ አፍሪካ በቅኝ ገዥዎች የተሰሩትን ወደቦች መመልከት ይቻላል።

ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ካልተገዙ ጥቂት ሃገራት አንዷ ነች።ኢትዮጵያውያንን ቡና አትጠጡ ቢራ ብቻ ጠጡ ብሎ ያስገደዳቸው ቅኝ ገዢ አልነበረባቸውም።እድሜ በደማቸው ሀገራቸውን አስከብረው ለኖሩት አባቶቻችን እና እናቶቻችን።እኛ እንደ ብዙ የአፍሪካ ሃገራት ዋና ከተማችንን የቅኝ ገዢዎች አልመረጡልንም። አለመምረጥ ብቻ አይደለም የከተሞቻችን ህንፃዎች እና መንገዶች በአብዛኛው የተሰሩት በእራሳችን መሀንዲሶች ነው።የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃቤት ፕላን ሲቀርብ አንድ ፈረንሳዊ መሃንዲስ ባለ ብዙ ፎቅ እንዲሆን አድርጎ አቅርቦ ነበር።በኃላ ግን ኢትዮጵያዊው መሃንዲስ (ስማቸውን አላስታውስም) ወደ ንጉሡ ቀርበው ''ይህንን ያህል ፎቅ ብዙ ሕዝብ በእየለቱ በሚወጣበት እና በሚገባበት ህንፃ ላይ አይሆንም።ይህ ማለት ከሀገሩ ሊፍት እንድናስገባ ሊያደርገን ነው።ከእዝያ ይልቅ ወደጎን ነው መለጠጥ ያለበት'' ብለው ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት ማዘጋጃ ቤቱ ወደጎን እንዲሰፋ ተደረገ።በእዚህም ብዙ ሕዝብ ለጉዳዩ በቀላሉ ለመውጣት እና ለመግባት ቻለ።ቅኝ ገዢዎች መሰረተ ልማቱን እንዴት ለሀገራቸው ኢንዱስትሪዎች መጋቢ እንዲሆን አድርገው እንደሚቀርፁ የሚያመላክት አንዱ ማሳያ ነው የማዘጋጃ ቤቱ ህንፃ ጉዳይ።
ቅኝ ግዛት መዘዙ ብዙ ነው።ጉዳቱ የሚታወቀው ትውልድ በተቀያየረ ቁጥር ነው።

ዛሬ ግን ያልገባኝ ጉዳይ በኢትዮጵያ የቢራ ፋብሪካ እንደ አሸን መፍላት ነው።በምግብ እራሷን ያልቻለች ሃገር ለምንድነው የእህል ቀበኛ የቢራ ፋብሪካዎች እንዲበዙላት የተደረገው? ብዙ ተመጣጣኝ ምግብ ማቀናበርያ በምትፈልግ ሀገር ውስጥ ለምን ለቢራ ፋብሪካ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲወጣ ይደረጋል? በኑሮ ውድነት በሚንገላታ ሕዝብ መካከል አማላይ የሆኑ የቢራ ማስታወቅያዎች ምን ይሰሩለታል? ቢራ ከሀገር ይጥፋ አይባልም።ሰው እንደ ምርጫው እና ፍላጎቱ ሊጎነጭ ይችላል።ግን እንደ ፖሊሲ ትኩረት ተሰጥቶት ሊደከምበት አይገባም።የኢህአዲግ የንግድ ድርጅቶች ሳይቀሩ የቢራ ምርት ላይ በከፍተኛ ትኩረት ሲሰሩ ይታያል።የቢራ ፋብሪካ መመስረት ብቻ ሳይሆን የማስፋፋት ሥራ በጣም እየተሰራበት ነው።በቅርቡ ወደ ገበያ ሊመጣ ነው የተባለው የራያ ቢራን ጨምሮ 8 የቢራ ፋብሪካዎች አሉ።እነርሱም አዲስ ቢራ፣በደሌ ቢራ፣ሐረር ቢራ፣ዳሸን ቢራ፣ሜታ  ቢራ፣ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ፣ባቲ ቢራ  እና በቅርቡ ሥራ የሚጀምረው ራያ ቢራ ናቸው።በኢትዮጵያ ያሉት የቢራ ፋብሪካዎች የማስፋፋቱ ሥራ ላይ የተጠመዱት የስርዓቱ የኢኮኖሚ መዋቅሮች ብቻ ሳይሆኑ በቦርድ መሪነት ለምሳሌ የራያ ቢራ ፋብሪካን ብንወስድ የኢህአዲግ/ወያኔ የሰራዊቱ አዛዦች ይገኙበታል።ዛሬ ሕዳር 17/2007 ዓም የወጣው ጋዜጣ የራያ ቢራ ፋብሪካ መከፈትን አስመልክቶ ባወጣው ዜና ላይ እንዲህ የሚል ይገኝበታል።

''አክሲዮን ማኅበሩን በቦርድ ሊቀመንበርነት እየመሩ ያሉት አቶ ኃይሌ አስግዴ ሲሆኑ፣ ምክትላቸው ደግሞ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ ናቸው፡፡ ሁለቱም አመራሮች በራያ ቢራ አመራር ውስጥ ያሉ ሲሆን፣ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኃይሌ ደግሞ የቦርድ አባል መሆናቸው ይታወቃል'' ሪፖርተር ጋዜጣ 

ባጠቃላይ ይህንን ማለት ይቻላል። ፋብሪካዎቹ የስራ ዕድል ይፈጥራሉ።ግን የቢራ ፋብሪካዎች እንደ አሸን መፍላት እህልም ሆነ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ከሚገመተው በላይ ይበላሉ።ፋብሪካ ይኑረን። ግን አዋጪ እና ሌሎች አንገብጋቢ ፋብሪካዎች ለምን አይበልጡብንም? ነው ጥያቄው። ደግሞስ  ቅኝ ገዢዎች ከብዙ ጥቅማቸው አንፃር አደረጉት።እኛ ቅኝ ያልተገዛነውስ? ኢህአዲግ/ወያኔ በወሎ እና በጎንደር ብቻ አዳዲስ የቢራ ፋብሪካዎችን ከፍቷል።አንድ ቢራ ለመጥመቅ ከፍተኛ የምግብ እህል ፍጆታ እና ብዙ ሺህ የተጣራ ንፁህ ውሃ እንደሚፈልግ ይታወቃል።ቅኝ ገዢዎች አፍሪካውያን ቢራ እየጠጡ እንዲናውዙ ማድረግ አንዱ የተሳካላቸው  ስራ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።የኛ ገዢዎች በየመንደሩ የቢራ ፋብሪካ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ እያወጡ የሚከፍቱልን ለምንድን ነው? ዳቦ ሳንጠግብ እና የምናነበውን ጋዜጣ ሁሉ ዘግተው አዕምሯችንን እያደነዘዙ የቢራ ፋብሪካ መደርደር ምን ይባላል? ከየት የተማሯት ''ጥበብ'' ነች?  ለናሙናነት 

ጉዳያችን
ህዳር 18/2007 ዓም (መጋቢት 4/2006 ዓም ወጥቶ የነበረ)

Sunday, November 23, 2014

''ጥቁሩ ቅዳሜ'' በመባል የሚታወቀው ደርግ ስልሳ የካቢኔ ሚኒስትር አባላት ሲቪል እና ወታደራዊ ባለስልጣናትን የረሸነበት ህዳር 14 1967 ዓም ዛሬ ህዳር 14/2007 ዓም 40 ዓመት ሞላው (ስም ዝርዝራቸውን ከቪድዮው ይመልከቱ)

ደርግ ባለሥልጣናቱን በህዳር ወር ላይ ከመረሸኑ በፊት ሰኔ 21/1966 ዓም አፄ ኃይለ ስላሴን ደርግ ስልጣን እንዲለቁ ሲጠይቃቸው የተናገሩት የመጨረሻ ቃል -

''በጠቅላላው የተናገራችሁትን ሰምተናል።የ ኢትዮጵያ ንጉሰ  ነገስት ስንሆን ስም ብቻ አይደለም።ህዝብንም ሀገርንም በሰላም ጊዜ የሚሰራበትን ጥፋትም ሲመጣ የሚመከትበትን በማሰናዳት መሆኑን ይህ በ ጦር ሰራዊታችን ውስጥ የታወቀ ሳይሆን ይቀራል ብለን አንጠረጥርም። ቢሆንም በየጊዜው የሚለዋወጠው ነገር ለሀገር የሚጠቅም ነገር እስካለበት የሀገርን ጥቅም በሌላ ለመለወጥ አይቻልምና ይህን ያነበባችሁትን ሰምተናል በእዚሁ ማቆም ነው።'' ብለዋል።



















ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

የታወቀ የጀርመን የፊልም ኩባንያ ከ20 ሚ. ብር በላይ በሆነ ወጪ “ዘ ኢትዮጵያን” የተሰኘ በኢትዮጵያ ላይ የሚያተኩር ፊልም ሊሰራ ነው።ፊልሙ በአገሪቱ ባህልና የአየር ፀባይ ተማርኮ በኢትዮጵያ በቀረ ጀርመናዊ እውነተኛ ታሪክ ላይ ያጠነጥናል፡፡ታዋቂ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ይሳተፉበታል።

ፎቶ - ሳያት ደምሴ (ይህንኑ ፊልም አስመልክቶ ኢትዮ-ሲኒማ ሪቪው ድረ-ገፅ ላይ ከወጣው ፖስተር የተወሰደ)

ሳያት በኢትዮጵያ ፊልም ታሪክ ከፍተኛ ተከፋይ ትሆናለች  
ፊልሙን የሚቀርፀው የጀርመን የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው
የታወቀ የጀርመን የፊልም ኩባንያ ከ20 ሚ. ብር በላይ በሆነ ወጪ “ዘ ኢትዮጵያን” የተሰኘ በኢትዮጵያ ላይ የሚያተኩር ፊልም ሊሰራ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ዕውቋ ድምፃዊና ተዋናይት ሳያት ደምሴ ከታዋቂ የጀርመን ተዋናይ ጋር በፊልሙ ላይ በመሪነት ትተውናለች፡፡ ሳያት ደምሴ በኢትዮጵያ ፊልም ታሪክ ከፍተኛው ክፍያ እንደሚከፈላት የፊልሙ ዝግጅት አስተባባሪ ዮሐንስ ፈለቀ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ በጀርመናዊው ደራሲ ሄንሪክ ሄዲንት የአጫጭር ልቦለዶች መድበል ውስጥ የተካተተው “The Ethiopian” የተሰኘው ታሪክ ወደ ፊልም እንደሚቀየር የታወቀ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በአገሪቱ ባህልና የአየር ፀባይ ተማርኮ እዚሁ በቀረ ጀርመናዊ እውነተኛ ታሪክ ላይ ያጠነጥናል ተብሏል፡፡
በፊልሙ ላይ ከሳያት ደምሴ በተጨማሪ አንጋፋዋ አርቲስት ሃና ተረፈና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተዋንያን እንዲሁም ሶስት ታዋቂ ጀርመናዊ ተዋንያን ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡ “ሳያት ብቻ ሳትሆን ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ተዋንያን ከፍተኛ ክፍያ ያገኛሉ” ብሏል - አስተባባሪው፡፡ የፊልሙ ዳይሬክተር ታዋቂው ጀርመናዊ ፈርዲናንድ ለኢራች ሲሆን ፊልሙን በመቅረፅ ዕውቁ የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ “ሙቪ ዘ አርት ኦፍ ኢንተርቴይንመንት”፣ በፕሮዱዩሰርነት ደግሞ “ኮንስትሬይን ፊልም ፕሮዳክሽን” እንደሚሳተፉ አስተባባሪው ገልጿል፡፡ 

ኢትዮጵያ የተሟላ መሰረተ ልማት (ኢንተርኔት፣ ደረጃውን የጠበቀ ሆቱል፣ የቀረፃ ቦታና ሌሎች) የሏትም በሚል ፊልሙ በኬንያ ሊሰራ እንደነበር የጠቆመው አስተባባሪው “እንዴት የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያተኮረ ፊልም ኬኒያ ውስጥ ይሰራል” የሚል ከፍተኛ ሙግት ከተካሄደ በኋላ በኢትዮጵያ እንዲሰራ መወሰኑን ገልጿል፡፡ የፊልሙ ቀረፃ ከመጪው ሳምንት ጀምሮ በአዲስ አበባ፣ በድሬደዋና በሃረር እንደሚከናወን አስተባባሪው አክሎ ገልጿል፡፡ 
ምንጭ - ኢትዮ ሲኒማ ሪቪው ድረ ገፅ 
         - አዲስ አድማስ ጋዜጣ  ኅዳር 13/2007 ዓም (22 November, 2014) ዕትም 
  •  

Thursday, November 20, 2014

የሃና ጉዳይ የፖለቲካው ብልሹነት ውጤት ነው።የፖለቲካው ብልሹነት ሌሎች ብዙ ሃናዎች እንዲደፈሩ መንገድ ያመቻቻል። እንዴት? (የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ)


መንደርደርያ 
ከጥቂት ቀናት በፊት በአዲስ አበባ የ17 ዓመት ወጣት በአውሬ ለበስ ወጣቶች ተደፍራ ሕይወቷ ማለፉ መሰማቱ የብዙዎቻችንን ልብ ያደማ ጉዳይ ነበር።ጉዳዩ የአውሬለበስ ግለሰቦች ተግባር መሆኑ ባያከራክርም።ማህበረሰባችን እና የምድሪቱ ሰው ሰራሽ ሕግ በደንብ ልፈተሹ ይገባል።ግለሰቦች በያሉበት ሊብከነከኑ ይችላሉ።ሆኖም ግን እንደ አንድ ሕብረተሰብ ለመንቀሳቀስ እና ለማኅበራዊ ቀውሶች መፍትሄ ለመስጠት ነፃነት የተሞላበት አካባቢ የግድ ይላል።በታፈነ ሕብረተሰብ ውስጥ አፋኙ ስርዓት  ለችግሩ እራሱን ተጠያቂ ሳያደርግ።እንደ ጵላጦስ ''ከደሙ ንፁህ ነኝ'' ማለት አይችልም። ለምን?

በሀገራችን እያንዳንዱ የማኅበራዊ ለውጦች፣አደጋዎች እና ቀውሶችን እያጠና በወቅቱ  በማኅበራዊ ተቋማት አማካይነት እርማት እንዲወሰድ የመገናኛ ብዙሃንም ሆኑ የፖለቲካ አመራሩን የሚዘውረው (ኢህአዲግ/ወያኔ ) አንዳች ነገር አያደርጉም።እነኝህን ተቋማት በማፍረስ ላይ ግን ኢህአዲግ/ወያኔ ቀዳሚ ነው።የሃና ጉዳይ ምን ያህል የፖለቲካ አመራሩ የማኅበራዊ ደህንነት እና የፀጥታ ዋስትና ያለመስጠቱ አይነተኛ አመላካች ነው? ይህንን በምሳሌ እንረዳ-

ምሳሌ - 1/ 

ኢኮኖሚያችን ፖሊሲው፣አቅጣጫው እና ግቡ መጠናት ያለበት ገለልተኛ በሆኑ ምሁራን ነበር።ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ከአስር አመታት በፊት ጥሩ እንቅስቃሴ ያደርግ የነበረ መሆኑ ይታወቃል።ዛሬ እንቅስቃሴው የት ነው? አመታዊ ሪፖርቱን የሀገር ውስጥ የዜና አውታሮች ያሰማሉ? ዛሬ የኢህአዲግ/ወያኔን ሪፖርት ብቻ ነጋ ጠባ ሕዝብ እንዲሰማ ለምን ተገደደ? የሲቪል ተቋማትን የማፈን ተግባር አካል አይደለም?

ምሳሌ 2/ 

የኢትዮጵያ ሴት የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር በርካታ ስራዎችን የሰራ ነበር።በአዲሱ የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አዋጅ ስንት ሚልዮን ብር ነው ፍርድ ቤት አግዶበት አቅሙን ያሽመደመደው? በሌላው ሀገር በአፍሪካም ቢሆን የእዚህ አይነት ሲቪል ተቋማት ሪፖርቶች ፓርላማ ድረስ ቀርበው ጥናታቸውን የማቅረብ፣ሕጎች እንዲስተካከሉ የማሳየት እና የማማከር ሥራ ይሰራሉ።ይሄው ድርጅት በሴት እህቶቻችን ላይ የሚደርሰውን የመደፈር አደጋ ለማጋለጥ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ንቅናቄ ለመፍጠር የጣረ ነበር።
ኢህአዲግ/ወያኔ እርሱ ያልጠረበው እንጨት እንጨት አይደለምና ገንዘቡን በፍርድ ቤት አገደው።ዛሬ ባለስልጣናቱም ሳይቀር የአዞ እንባ ያፈሳሉ።አሰራሩ እነ ሃና ሲደፈሩ ይጮሃል ሌሎች ብዙ ሃናዎች እንዲደፈሩ ግን መንገድ ያመቻቻል።

ባጠቃላይ 

ኢትዮጵያ ውስጥ የማኅበራዊ ቀውስን ቀድመው አጥንተው ተገቢው እርምጃ ሕዝብ እንዲወስድ የሚያደርጉ ድርጅቶች በኢህአዲግ/ወያኔ ተመትተዋል።የእዚህ አይነት ድርጅቶች ቢኖሩ ኖሮ የህዝቡን ማህበራዊ ቀውስ ደረጃ በጥናት እያሳዩ ባስደነገጡን እና ሕዝብ በመረጃ ተመስርቶ ወደ መፍትሄው እንዲሄድ በገፉት ነበር።ይህ ብቻ ሳይሆን በስልጣን ወንበር ላይ የተፈናጠጡትንም መንገድ ባሳዩዋቸው ነበር።ግን አልሆነም።ከእዚህ በከፋ ደረጃ ሕዝብ የሚሰማቸውን የሃይማኖት ተቋማት ሳይቀር በፖለቲካ አጅሎ የሃይማኖታዊ ችግሮችን ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ ጣጣዎችን እንዳይፈቱ ያደረጋቸው አሁንም ፖለቲካውን የሚዘውረው ኢህአዲግ/ወያኔ ነው።

በመቶ ሺህ የሚቆጠር የጎዳና ተዳዳሪ በኢትዮጵያ ከተሞች የተርመሰመሰው ባለፉት 23 አመታት ነው።ሴቶች እህቶቻችን የመደፈራቸው ዜና የሳምንት ክስተት የሆነው ባለፉት 23 አመታት ነው።ጫት መቃምያ በት በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት በር ላይ የተከፈተው ባለፉት 23 አመታት ነው።የሽሻ ቤቶች ትልልቅ ሕንፃዎችን ሁሉ መዳረሻቸው ያደርጉት ባለፉት 23 አመታት ነው።ባጭሩ የማኅበራዊ ቀውሱ መነሻ በስልጣን ላይ የተፈናጠጠው የኢህአዲግ/ወያኔ የአፈና ውጤት ነው።የፖለቲካ አመራሩ እና ፖሊሲው ማኅበራዊ ቀውሱን አፋጥኖታል።መጨረሻው የት እንደሆነ አይታወቅም።

ጉዳያችን 
ህዳር 11/2007 ዓም  (ኖቬምበር 20/2014)

Tuesday, November 18, 2014

ኬንያ፣ቡክናፋሶ እና አዲስ አበባ በእዚህ ሳምንት (ከሶስት ደቂቃ ያነሰ አጭር የቪድዮ ዜና ጋር)

 ኬንያ 

ኬንያ አንዲት ወጣት ሚኒስከርት በመልበሷ በወንዶች የደረሰባት ጥቃት በመቃወም ትናንት ሰኞ  በሺህ የሚቆጠሩ የናይሮቢ ሴቶች፣ተማሪዎች ሰልፍ ወጡ። ሕግ ይስተካከል! አዲስ አበባ ላይ በአውሬ ለበስ  ወንዶች ጥቃት የደረሰባት ሃና ሕይወቷ አልፎ የአዲስ አበባ ወጣት ሕጉ ይሻሻል ብሎ አይጮህም።ነገ በእኔ ነው።

ቡክናፋሶ

የሃያ ሰባት ዓመት አምባገነንነት ለሌላ ተጨማሪ  ዓመታት በስልጣን ላይ ለመቀመጥ ፓርላማው ሕጉን እንዲቀይር ያደረጉት ፕሬዝንዳንትን በሁለት ቀን አብዮት አስወግዶ ዛሬ ወታደራዊ አመራርን በሲቪል አስተዳደር ቀየረ።ሀገሪቱ  በመጪው ዓመት የአሁኑ ጊዚያዊ ፕሬዝዳንት የማይሳተፉበት አዲስ ምርጫ ታደርጋለች።ጊዝያዊ ፕሬዝዳንት ዛሬ ቃለ መሃላ ፈፀሙ።

አዲስ አበባ

በመጪው እሁድ አዲስ አበባ ላይ ከአርባ ሺህ ሕዝብ የማይንስ የሚሳተፍበት ታላቁ እሩጫ መነሻ እና መድረሻውን ጃን ሜዳ አድርጎ ይደረጋል።ገበታው በያይነቱ ነው።ከኬንያው የባሰ ጥቃት እህቶቻችን ላይ ተፈፅሟል።ከቡኪናፋሶ የከፋ በጎሳ ላይ የተመሰረተ አምባገነንነት በኢትዮጵያ አናት ላይ እየጨፈረ ነው።አንድ እንቁላል 3 ብር ከ 50 ሳንቲም በሚሸጥባት አዲስ አበባ አፍ ለጉሞ መሮጥ በራሱ ጤነኝነት አይመስለኝም።ኬንያ እና ቡክናፋሶ ጥለውን ሄዱ። ከእዚህ በታች ያለውን 3 ደቂቃ የማይሞላ ዜና ይመልከቱ።



ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

Monday, November 17, 2014

የአንድ ወቅት የኮሜዲያን ልመነህ ቀልድ ለእዚህ ትውልድ ጥቂት ትምህርት ሳይኖራት አይቀርም። ፅሁፎቻችን፣የድረ-ገፅ ዘመቻዎችን እና ንግግሮቻችን ሕዝብ የሚያቀራርብ እንጂ የሚለያይ እንዳይሆኑ እንጠንቀቅ።(የጉዳያችን ማስታወሻ)

ኮሜድያን ልመነህ ታደሰ 

ልመነህ እና አጭር ኮሜዲው 
ኮመዲያን ልመነህ ታደሰ በአንድ ወቅት የኮሜዲ ሥራ ሲወሳ ቀዳሚ ስሙ የሚጠቀስ አርቲስት ነበር።ዛሬ ላለበት ሁኔታ አርቲስቶቻችን የሚያደርጉትን አንዳንድ ጥረቶች እያሞገስኩ (ድጋፎቹ በበቂ ደረጃ ናቸው ወይ? ለሚለው ጥያቄ መረጃ ባይኖረኝም) ይች በልጅነቴ የቀለዳት ቀልድን ማውሳት ፈለኩ።

 አጭር ኮሜዲ ድራማ - 
ሰውዬው ጎረቤቱን ሊከስ ፈለገ እና የሰፈሩን አንድ ወጣት ወደ ቤቱ ጠራው።ወጣቱን የፈለገበት ምክንያት የክስ ወረቀት እንዲፅፍለት ነበር።በመጀመርያ ያደረሰበትን በደል በቃል ነገረው፣ተረከለት በመጨረሻ ወጣቱ እንዲህ አለ ''ገባኝ እኔ ይህንን በደል በጥሩ ኪነ ጥበባዊ ፅሁፍ ከሽኘ ማመልከቻውን እስክፅፍልህ ግማሽ ሰዓት ስጠኝ'' ብሎ መፃፍ ጀመረ። ከግማሽ ሰዓት በኃላ ወጣቱ ለከሳሹ የፃፈውን ይዞ መጣ ለከሳሽም አነበበለት።

ወጣቱ ፅሁፉን ለከሳሹ ሲያነብለት ከሳሽ እንባው እየወረደ ነበር።በመጨረሻ ከሳሽ ማልቀሱን ማቆም አልቻለም።ወጣቱ ማመልከቻ ፀሐፊ ግራ ገባው።ቅድም ወደ ቤቱ ሲመጣ እንዲህ አልሆነም ነበር።አሁን የእርሱን ፅሁፍ ሲመለከት ይህን ያህል ማልቀሱ ግራ አጋባው።
ወጣቱ ጠየቀ - ''ምን ነካህ? ቅድም ጎረቤትህ ያደረሰብህን በደል ስትነግረኝ፣ያንን ሁሉ ታሪክ ስትተርክልኝ አላለቀስክም። አሁን የእኔን ፅሁፍ ስትሰማ ግን ማልቀስ ጀመርክ ጥላቻህም ባሰበት።ምንድነው ነገሩ?'' 

ከሳሽ መለሰ '' እኔ አሁን አንተ የፃፍከውን በደል ፈፅሞ አላውቀውም ነበር።እኔ በተራ ቃላት የማውቀውን በደል አንተ በከባድ ቃላት እና በስነ-ፅሁፍ ስታቀርበው የማላውቀውን በደል ስትነግረኝ ምንም እንኩአን አንተ ያልካቸው በደሎች ባይኖሩም ቢሆንስ ብዬ ጥላቻዬ ጨመረ።በጣም ነው የማመሰግንህ ያላደረገብኝን እና ያልተፈፀመብኝን ሁሉ ጨምረህ በስነ-ፅሁፍ አስውበህ በማቅረብህ።ቀድሞ በቀላሉ እናደድ የነበረውን ውብ በሆነ የፅሁፍ ችሎታህ የባሰ እንዳለቅስ ስላደረከኝ''

ወጣቱ ፀሐፊ ደነገጠ ማስታረቅ፣ሰላም ማውራት ሲገባው የባሰ ቤንዚን እየጨመረ መሆኑን ቆይቶ አወቀ።አንድነት ከመስበክ ይልቅ በደልን በኪነ-ጥበባዊ ፅሁፍ ከሽኖ ጎረበታሞቹን የባሰ ማጣላቱን አወቀ።የኮሜዲው መጨረሻ።

ወደ ዋናው ነጥብ ልምጣ  
በደል አለ።ማንም አይክደውም የበደሉን መጠን ለመለካት በደሉ የደረሰበትን ሰው ሆኖ መገኘት የግድ አይጠይቅም።ሰው መሆን በቂ ነው።ያለፈው የግማሽ ክ/ዘመን ታሪካችንን ብቻ ብንመለከት ደርግ በመላዋ ኢትዮጵያ ላይ ባደረሰው በደል ሁሉም የተነገረው ከተለያየ የስልጣን ፍላጎቶች አንፃር ነው።

በሰሜን ኤርትራ ለሚኖረው ሻብያ ''አንተ የተበደልከው ኤርትራዊ ስለሆንክ ነው'' አለው።
ህወሓት ለትግራይ ሕዝብ '' አንተ ትግራይ በመወለድህ ነው'' አለው።
ወለጋ ላይ ኦነግ ''አንተ ኦሮሞ በመሆንህ ነው'' አለው።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በደርግ ስርዓት ውስጥ የደህንነት ሚኒስትር ሆነው የሚሰሩት የትግራይ ተወላጅ ነበሩ።እራሳቸው ኮ/ል መንግስቱ የኦሮሞ ተወላጅ ነበሩ።የኮ/ል መንግስቱ የቅርብ አማካሪ የኤርትራ ተወላጅ ነበሩ።እንደ ዘር የተነሱት ጉዳዮች ከአምባገነናዊ ባህሪ እና ከስልጣን ሽምያው ጋር ሲነፃፀሩ የትዬለሌ ነበሩ።መሰረታዊ ችግሮቹ ግን የሕግ የበላይነት አለመከበር እና ሕዝባዊ መሰረት ያለው የእያንዳንዱን ግለሰብ ተሳትፎ ያላገኘ የመንግስት ስርዓት እንጂ የጎሳ ጥያቄዎች አይደሉም።ይህ ማለት የብሔር ጭቆና የለም።ፈፅሞም አልነበረም አሁንም የለም ለማለት አይዳዳኝም። ነገር ግን የችግሮች ሁሉ መፍትሄዎች ወደ ብሔር ፖለቲካ ማራገብ ከወሰድነው ወይንም በይሉኝታ እየተያዝን አንዱን ወገን እናስደስት በሚል ተነሳሽነት ብቻ ጎሳን ካራገብን የማንወጣበት አዘቅት ውስጥ እንዳንገባ ያስፈራል።

የጎሳ ፖለቲካ የችግራችን ሁሉ ምንጭም መፍትሄም አይደለም  
እዚህ ላይ አሁን ያለንበትን የስርዓቱን የጎሳ ፖለቲካ ችግር እና በአንድ ጎሳ የመጠቅለል አባዜ መቃወም እና አጠቃላይ 'የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር የጎሳ ፖለቲካ ነው' ብሎ የመደምደም የመሃይም አስተሳሰብ መዳረሻው የት እንደሆነ አይታወቅም።የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ወደ ስልጣን መወጣጫ እስከመራቸው ድረስ የጎሳ ፖለቲካን ማራገብ እንደ አንድ ስልት ሲጠቀሙበት ይታያል።ይህ በአለማችን የተነሱ ጨካኝ አምባገነኖች የተከተሉት እኩይ መንገድ ነው።አሁን በስልጣን ላይ ያለው ህወሓት እየተከተለው ያለው ይህንኑ መንገድ ነው።ስልጣን ከያዘ ከ23 ዓመት በኃላም ስሙን ''የትግራይ ነፃ አውጪ'' የሚል ነው። በእርሱ መንገድ በመሄድ ስኬት አይገኝም።የተቀናቃኝን ተቃራኒ በመያዝ ግን ስኬት አለ።ጎሳ ለሚያራግበው ህወሓት ሌላ ጎሳን ማራገብ መቃወም ሳይሆን መመሳሰልን ያስከትላል። የሀገራችን ገበሬ ምን ያህል ፊደል ቆጠርኩ ከሚለው መሻሉን እናስብፅሁፎቻችን፣የድረ-ገፅ ዘመቻዎችን እና ንግግሮቻችን ሕዝብ የሚያቀራርብ እንጂ የሚለያይ እንዳይሆን እንጠንቀቅ

ጉዳያችን
ህዳር 8/2007 ዓም (ኖቬምበር17/2014)

''የኦሮሞ ማህበረሰብ ከምንም በላይ ፣ በባሕሉ የሚመቸውና የሚቀበለው የአንድነትን እና የፍቅርን ፖለቲካ ነው። “እገሌ ከዚህ ዘር ስለሆነ፣ ወይንም ይሄ ቋንቋ ስለሚናገር ከአገራችን ይዉጣ፣ ይሄ ምድር የኦሮሞ ብቻ ነው …” የሚባለው አክራሪዎችና ካድሬዎች የሚረጩት እንጂ ከሕዝቡ የሚመጣ አይደለም።'' ግርማ ካሳ

 የኦሮሞ ማኅበረሰብ ባህላዊ አለባበስ ፎቶ ከማኅበራዊ ድረ-ገፅ 


በኦሮሞዉና በአማርኛ ተናገሪው መካከል ጥላቻ እንዲሰርጽ ተብሎ አንድ የተጻፈ መርዛማ መጽሐፍ አለ። የቡርቃ ዝምታ የሚባል መጽሃፍ። የዚህ መጽሀፍ ደራሲ አቶ ተስፋዬ ገበረ አብ ይባላሉ። የሕወሃት/ኢሓአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩ ጊዜ የጻፉት መጽሀፍ ነው። በቅርቡ “በሞጋሳ ኦሮሞ ሆኛለሁ” ሲሉ አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል። ምን ያህል የሞጋሳ ሚስጠር እንደገባቸው ግን አላውቅም።
ከአራት መቶ አመታት በፊት፣ የኦሮሞ ጦረኞች አንድ አካባቢን በሚቆጣጠሩና በሚማርኩ ጊዜ፣ አንድ የሚያደርጉት ሥርዓት ነበር። የጎሳው ሽማግሌዎች ከተማዋ ሲገቡ ከዚያ ጊዜ ጀመሮ ያቺ ክከተማ ኦሮሞ ትሆናለች። በከተማዋም የሚኖረው ህዝብ፣ በሽማግሌዎቹ ፊት ያልፋል። በዘሩ ከሌላ ወገን ቢሆንም፣ በአለቃዉ ያለፈ ሰው ሁሉ ኦሮሞ ይሆናል። ይህ ስርአት ሞጋሳ ይባላል። ኦሮሞነት ከዘር ጋር ግንኙንት እንደሌለው የሚያስተምር የኦሮሞ ባህል !

ሞጋሳ የሚያሠባስብ ነው። አንድ የሚያደርግ ነው። በመሆኑም ኦሮሞነት አንድነት ነው። ኦሮሞነት ሌላውን እንደ እራስ አድርጎ ማቀፍ ነው። ኦሮሞነት ሌላውን ማሳነሳ፣ ሌላውን ማባረር፣ ሌላውን መጥላት አይደለም።
እርግጥ ነው አንዳንድ አክራሪ የኦሮሞ ብሄረተኞች፣ በኦሮሞነት ስም ሌሎችን የመጥላት ፖለቲካ ያራምዳሉ። ከሌሎች የመለየት፣ ሌሎችን የማግለል፣ የመከፋፈል፣ የጥላቻ ፖለቲካ ያራግባሉ። የኦሮሞ ባህል ግን ፣ የሞጋሳ ባህል ግን ፣ አንድ የሚያደርግ ባህል ነው። እነርሱ ከሚናገሩትና ከሚረጩት መርዝ ጋር ግንኙነት የለውም።
ሌላው በአማርኛም ሳይቀር የምንጠቀማት ቃል አለች። ጉዲፈቻ። ጉዲፈቻ ማለት የሌላውን ሰው ልጅ እንደ ራስ አድርጎ ማሳደግ ማለት ነው። ጉዲፋቻ የሚለውን ቃል በአማራኛ መጠቀማችን በራሱ የሚያሳየው፣ የሌላውን ልጅ እንደራስ አድርጎ የማቀፍ ባህል፣ በኦሮሞው ማህበረሰብ ዉስጥ ምንም ያህል ስር የሰደደ ባህል እንደሆነ ነው። የኦሮሞው ማህበረሰብ፣ ትግሬ ይሁኑ አማራ፣ ጉራጌ ይሁኑ ከፊቾ ፣ ከሌላ ዘር የሆኑትን እንደራሱ አድርጉ የሚያሳድግ ማህበረስብ ነው። ከሌላው ጋር የተዛመደ፣ የተዋለደ፣ የዘረኝነት ነገር የሌለበት ማሀብረሰብ ነው።

ላለፉት 23 አመታት ግን በሽታ ገባ። የኦሮሞ ማህበረሰብን ከሌላው ለማጣላት ብዙ ተሞከረ። የባለስልጣናቱ ካድሬዎች ሆን ብለው በኦሮሞው እና ኦሮሞ ባልሆነው ማህብረሰብ መካከል ልዩነቶች እንዲፈጠሩ ቀን እና ሌሊት መስራት ጀመሩ።
ለአማርኛው ተናጋሪዎች “ ኦሮሞዎቹ ዘረኞች ናቸው። አማርኛን ይጠላሉ። ይጨርሷቹሃል። ያርዱዋቹኋል” የሚል እድምታ ያለው መልእክት በጎን ያስተላልፋሉ። ለኦሮሞ ደግሞ ” እነርሱ ነፍጠኞች ናቸው። በቋንቋህ እንዳትናገር ሊያደርጉህ ነው። ሊያጠፉህ ነው። የድሮው የአማራ የበላይነትን ሊያመጡብህ ነው። አሃዳዊ ስርዓት ሊጭኑብህ ነው” ይሉታል። አማርኛ ተናጋሪዎች በአፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች ላይ ፣ አፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች ደግሞ በአማርኛ ተናጋሪዎች ላይ ጥርጥሬ እንዲያድርባቸውና እና እንዳይግባቡ እያደርጓቸው ነው። ኦሮሞዎች አማርኛ እንዳይማሩ፣ አማርኛ ተናጋሪዎች ደግሞ አማርኛ ብቻ እንዲናገሩ ተደርጎ፣ የአንድ አገር ልጆች ሆነን እንዳንግባባ ተደርገናል። መነጋገር ስላልቻልን፣ አንዳንች ስለአንዳንች የሚነጉን የአገዛዙ ካድሬውዎችና ዉጭ ያሉ አንዳንድ አክራሪዎች ናቸው። ነገሮችን እየጠመዘዙ ስለሚነግሩንም እርስ በርስ እየታመስን ነው።

መንቃት ይኖርብናል። እነዚህ የጥፋት ኃይሎች በኛ ላይ የሽረቡትን ወጥመድ ማፈራረስ አለብን። የኦሮሞ ባህል፣ የኦህደድ ካድሬዎች ወይንም ዉጭ ያሉ አንዳንድ ለኦሮሞ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ግን በጥላቻ የተሞሉ አክራሪዎች እንደሚነግሩን አይደለም። ኦሮሞነት ዘረኝነት አይደለም። ኦሮሞነት አንድነት ነው። ኦሮሞነት ሌሎች እንደ ራሱ አድርጎ መቆጠር ነው። ኦሮሞነት የሚለያይ ሳይሆን የሚያሰባስብ ነው። የኦሮሞነት ፖለቲካ የጉዲፈቻና የሞጋሳ ፖለቲካ ነው።

የኦሮሞ ማህበረሰብ ከምንም በላይ ፣ በባሕሉ የሚመቸውና የሚቀበለው የአንድነትን እና የፍቅርን ፖለቲክ ነው። “እገሌ ከዚህ ዘር ስለሆነ፣ ወይንም ይሄ ቋንቋ ስለሚናገር ከአገራችን ይዉጣ። ይሄ ምድር የኦሮሞ ብቻ ነው ….ወዘተረፈ” የሚባለው አክራሪዎችና ካድሬዎች የሚረጩት እንጂ, ከሕዝቡ የሚመጣ አይደለም። የኦሮሞ ማህበረሰብ በባህሉ ሌላውን የሚቀበል፣ እንደራሱ አድርጎ የሚያኖርና የሚያሳድግ ነው። ለዚህም ነው ከጊዜ ወደ ጊዜ የአንድነት ፓርቲ በኦሮሞ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነቱ እየጨመረ የመጣው።

አፋን ኦሮሞ የማናውቅ ካለን፣ እንማር። አማርኛ የማናውቅ ካለን፣ አማርኛ እንማር፡ ብዙ ቋንቋ ማውቅ በረክት ነው። ሌላ ቋንቋ መማር አያሳንሰንም። እንደ ወንድማማቾች፣ ለመግባባት፣ ለመነጋገር፣ አብረን አገራችንን ለማሳደግ ቋንቋ አለማወቃችን እንቃፋት ሊሆንብን አይገባም።

ምንጭ - ሳተናው ድረ-ገፅ http://satenaw.com/amharic/?p=2525 

Tuesday, November 11, 2014

ሰበር ዜና-የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዛግብት እና መፃህፍት ቤት በስሩ ለረጅም ጊዜ የነበሩትን በፈረንሳይኛ፣ስፓኒሽ፣ፖላንድ፣ጀርመንኛ ወዘተ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ የተፃፉትን መፃህፍት ሊሸጣቸው ነው ኢትዮጵያን ያላችሁ መፃሕፍቱን አድኑ!!! ምናለ ኢትዮጵያን መጥላታችሁን በልኩ ብታደርጉልን?


የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዛግብት እና መፃህፍት ቤት መፃሕፍቱን የሚሸጠው  በጨረታ ጭምርም ነው።ዛሬ ህዳር 2/2007 ዓም  ሸገር ራድዮ በምሽቱ ዜና ላይእንደዘገበው ብሔራዊ በተመዛግብት እና መፃህፍት ቤቱ መፃሕፍቱን ለመሸጡ  የተሰጠው ምክንያት ''ቦታ ስለጠበበን ሌሎች ቅጂዎች ማስቀመጫ ስላጣን ለመሸጥ ወስነናል ሌላ ምክንያት  የለም''  ማለታቸውን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመስርያቤቱ ሰራተኛ በቀጥታ ለራድዮ ጣብያው ሲናገሩ አስደምጧል።

ስለኢትዮጵያ ታሪክ  የተጻፉት እነኝህ መፃህፍት በሌላው ዓለም በቀላሉ የማይገኙ እና የተፃፉትም ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ብቻ መሆኑን እያወቁ ''ቦታ አጣበቡ'' ተብለው ሽያጭ ላይ ናቸው። በጣም የሚገርም ነው።ቦታ ጠበበን ተብሎ ለዘመናት የተከማቹ መፃህፍት እንዲሸጡ የወሰነው ኃላፊ  ኢትዮጵያዊ ነው? አሁን በጨረታ ለመግዛት የአንዱ ሀገር ሙዝየም ወይንም መፃህፍት ቤት በጅምላ ሊገዛው እንደሚችል ትልቅ ስጋት ፈጥሯል።ይህ ማለት ነገ ለምርምር ኢትዮጵያውያን ወደ ገዛው ሀገር ብዙ የውጭ ምንዛሪ እየከፈሉ ይሄዳሉ ማለት ነው።ዛሬ የብሔራዊ መዛግብት ሰራተኞች ስፓኒሽ፣ፖላንድኛ፣ጀርመንኛ ባይችሉ ነገ እነኝህን ቋንቋዎች የሚችል ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ አታፈራም?  ወይንም ነገ የሚችል ትውልድ አይነሳም? በምን መለክያ ነው የሀገር እና የህዝብ ሀብት ለጨረታ የሚቀርቡት?

እዚህ አውሮፓ ለምሳሌ ስዊድን እና ኖርዌይ ውስጥ ያሉ ብሔራዊ መዛግብት እና ትልቁ የህዝብ መፃህፍት ቤት በየትኛውም ሀገር የታተሙ መፃህፍት፣መፅሄቶች እና ጋዜጦች በየትኛውም ቋንቋ ቢታተሙ በጀት መድበው ይገዛሉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ የሚታተም ማናቸውም መፅሐፍ እና ጋዜጣ አዲስ ዘመንን ጨምሮ ከወር ወር ተከታትለው ይገዛሉ ያስቀምጣሉ።ያንን ቋንቋ የሚናገር ኖረ፣ አለኖረ የሚል ጥያቄ የለም።

አሁን በተለይ ጋዜጦቹ ዲጂታል ከሆኑ ቀን በቀን እየቀዱ ፋይል ያደርጋሉ።እነኝህ ፅሁፎች ነገ ገንዘብ ብቻ ሳይሆኑ ትልቅ የመመራመርያ መሳርያም ናቸው። ኢትዮጵያ ግን ያውም ስለራሷ የተፃፉትን መፃህፍት ''ቦታ ጠበበኝ'' የሚሉ ከንቱዎች ለጨረታ አቀረቡት።ምናለ ቢያንስ ለዩንቨርስቲዎች በአደራ ቢሰጡ? የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ኢንስቲትዩት እነኝህን መፃህፍት መያዝ አንዱ የስራው አካል አይደለም? ለምን እንዲሸጡ ተወሰነ? 

ምናለ ኢትዮጵያን መጥላታችሁን በልኩ ብታደርጉልን? በነገራችን ላይ መፃሕፍቱን ለረጅም ጊዜ ሲያከማች የነበረው ይሄው ዛሬ ለመሸጥ የሚያስማማው መስርያቤት መሆኑን ይታወቃል።ኢትዮጵያን ያላችሁ መፃሕፍቱን አድኑ!!!

ጉዳያችን
ህዳር 3/2007 ዓም (ኖቬምበር 12/2014)

''አቡነ ዘበሰማያት ሲወጋ እንጂ ሲወረወር አይታይም'' የዘጠኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ለኃይማኖት ተቋማት ያስተላለፉት የፀሎት ተማፅኖን አስመልክቶ የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ


ኢትዮጵያ  በታሪክ ችግሮችን ከምትፈታባቸው  አንዱ እና ዋናው መንገድ  ፀሎት ነው።ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ በተለይ ከፖለቲከኞች ስለ ሀገር እና ሕዝብ ፀሎት ይደረግ ብለው በግልፅ በጋዜጣው መግለጫ በታጀበ መልኩ የሃይማኖት አባቶችን ሲጠይቁ የሰማያዊ ፓርትን ጨምሮ ዘጠኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጀመርያዎቹ ሳይሆኑ አይቀሩም።ኢትዮጵያ መሪዎቿ ሀገራቸውን ከወራሪ ለመከላከል ሲነሱ ገዳማቷን ሳይማፀኑ እግራቸውን የማያነሱባት ሀገር ነበረች።የጥንቱን ትተን በቅርቡ ኢጣልያ ሀገራችንን በወረረ ጊዜ ንጉሡ አሁን ስድስት ኪሎ የሚገኘው ምስካህዙናን መድሃኔ ዓለም ታቦትን ወደ እየሩሳሌም ከዝያም ወደ እንግሊዝ  አብሯቸው መሰደዱ ይታወቃል። በተለይ ይሄው ታቦት  አምስት መነኮሳት አብረው ሌት እና ቀን ሳይለዩ የኢትዮጵያ ነፃነት እንዲመለስ ሲማፀኑ እንደነበር እና በመጨረሻም ንጉሡ በስለታቸው መሰረት በድል የገቡበትን ሚያዝያ 27 ቀን ብቻ ታቦቱ እንዲነግስ ከእዚህ በስተቀር ግን ለጥምቀትም የማይወጣ ብቸኛ ታቦት መሆኑ ይታወቃል።ይህም ነፃነታችን የእግዚአብሔር ኃይል ውጤት ለመሆኑ ምስክር ነው።

ኢጣልያ በአድዋ ዘመቻ ድል ስትሆንም የኢትዮጵያ እና የእግዚአብሔር ግንኙነት በግልፅ የታየበት ነበር።ዛሬ አራዳ የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ታቦተ-ሕግ ከንጉሡ እና ከካህናቱ ጋር አብሮ ዘምቷል።እዚህ ላይ ታቦቱ እና ካህናቱ የዘመቱት ሰው ለመግደል ሳይሆን ሃይማኖት ለዋጭ፣ሀገር አፍራሽ የሆነውን  ወራሪ ኢጣልያን ሲዋጉ ለሚሞቱት የፍትሃት ፀሎት ለማከናወን እና ሰራዊቱን እና ንጉሱን ሃይማኖታዊ አገልግሎት ለመስጠት ነበር። ቤተ ክርስቲያን በደስታም በሀዘንም የመገኘቷን ያህል እልፍ አስከሬን እንደሚከመር በተረጋገጠበት የጦርነት ቦታ ተገኝታ ፀሎት ማድረግ  የቤተ ክርስቲያን ሥራ ካልሆነ የማን ሊሆን ይችላል?

እዚህ ላይ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ ሚና ብትይዝም በስድስተኛው ክ/ዘመን የተነሳው እና ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምስራቅ ቀጥላ አማኞቹን ተቀብላ ያስጠለለችው የእስልምና ሃይማኖትም እንዲሁ በኢትዮጵያ የክፉም ሆነ የደስታ ጊዜ አልተለየም።ለእዚህም ማስረጃው አሁንም የአድዋ ጦርነት ወቅት ዘማቹ ከአዲስ አበባ አራዳ ቤተ ክርስቲያን ሲነሳ በነበረው የፀሎት መርሃ ግብር ላይ ሙስሊም ኢትዮጵያውያንም ፊታቸውን በተቃራኒው አድርገው የእራሳቸውን ፀሎት ማድረጋቸው እና ሳላት መስገዳቸውን የሚያሳዩ  በፎቶ ግራፍ የተደገፉ  ታሪካዊ ማስረጃዎች መገኘታቸው የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው።

ባጠቃላይ ለፖለትካዊው ሆነ ለአጠቃላይ ሃገራዊ ችግራችን ፀሎት ማድረግ ዓለም ሳይጀምረው የጀመርን እና የተጠቀምንበት ሕዝብ ነን።ሆኖም ግን ፀሎትን እንደ ሞኝነት መቁጠር የጀመረ ትውልድ ከታቀፍን ደግሞ አርባ ዓመታትን ማስቆጠራችንን ልንረሳው አይገባም።አሁን በምንኖርበት ዓለም ከሕዝባቸው እስከ 80% የሚሆነው ምንም አይነት እመነት የሌለው ሕዝብ የሚመሩት የምዕራቡ ዓለም መሪዎች ሳይቀሩ  እግዚአብሔርን መጥራት በየንግግራቸው መሃል የለመዱትን ያህል በፀሎት እዚህ የደረሰች ሀገር-የኢትዮጵያ መሪዎች ግን  አባት እና እናቶቻቸው የሚያውቁትን አምላክ እነርሱን ያልፈጠረ ይመስል በመገናኛ ብዙሃን መናገር የሚያፍሩ ናቸው።አንድ ወቅት የኢህአዲግን ምክርቤትን ሲከፍቱ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በንግግራቸው መጨረሻ ላይ ''እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ'' ሲሉ በመስማታችን ደስ ያለን ምስኪኖች መሆናችንን ልብ አላልነው ይሆን? ኢትዮጵያን የሚያህል ሀገር መሪዎቿ እግዚአብሔርን አይጠሩም እና ከአስርተ ዓመታት በኃላ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ''እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ''  የሚል ቃል ስንሰማ ብርቅ ሆነብን።ይህ በራሱ ከእኛነታችን ጋር በተቃረነ የደረሰብንን ስብራት ያሳያል።  

''እግዚአብሔር አሜሪካንን ይባርክ'' እያሉ የሚናገሩ መሪዎች በምንሰማማባት ዓለም ጥንታዊቷ በመፅሐፍ ቅዱስ ''እናንት እስራኤላውያን ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ አይደላችሁምን?'' የተባለልን ሀገር፣ አሁንም በመፅሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ብቻ ከአርባ ጊዜ በላይ ''ኢትዮጵያ'' የሚለው ስማችን የተጠራባት ሀገር፣ በእስልምናውም ዓለም በነቢዩ መሐመድ ''ኢትዮጵያውያንን አትንኩ'' ተብሎ የተነገረላት ሀገር መሪዎች እግዚአበሄርን አይጠሩባትም።ለእዚህ ነው ዛሬ  ለሀገራዊ ምስቅልቅል ችግሯ ከአርባ ዓመት በኃላ  የፖለቲካው ዓለም ተዋናዮች ለሀገራችን ችግር ፀሎት እናድርግ ብለው የሃይማኖት መሪዎችን ሲያሳስቡ ከመስማት የበለጠ ምን ደስታ አለ? የሚያስብለው።

የሃይማኖት መሪዎች ምላሽ 'ታላቅ' የሚሉት በስልጣን ላይ ያለውም አሳሰበ 'ታናሽ' የሚመስሉት ተቃዋሚዎችም አሳሰቡ ከእነርሱ የሚጠበቀው ''እግዚአብሔር አሳሰበን'' ብለው ፀሎት ማድረግ ነው።ፀሎት ፖለቲካዊ መልክ  የለውም። ፀሎቱን የሚሰማው አምላክም የምንም ፓርቲ አባል አይደለም።የእውነት እና የፍቅር ብቻ እንጂ። አዎን ዘመን ተቀይሯል።ትውልድም ተቀይሯል።ፀሎት እንደ አንዱ እና ዋናው  የችግር መፍቻ መንገድ ስትጠቀም የነበረች ሀገር ከፖለቲካ ተዋናዮቿ ፀሎት ለሀገራችን ይደረግ ብለው ለሃይማኖት አባቶች መልዕክት ሲያስተላልፉ መስማት እራሱ የትውልዱ እራሱን እና ማንነቱን የማወቁ ምልክት ነው።''አቡነ ዘበሰማያት ሲወጋ እንጂ ሲወረወር አይታይም'' እንዲል ለሀገራችን መፍትሄ የተባለ ቅንጣት ታህል የመፍትሄ ሃሳብ ልታመልጠን አይገባም እናም ለጥቂት ደቂቃዎች አምላካችን ፊት የሀገራችንን አጀንዳ ማቅረብ አንርሳ!
በመጨረሻም የዘጠኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያደረጉት የፀሎት ጥሪ ይህንን በመጫን ያንብቡ።

ጉዳያችን 
ህዳር 2/2007 ዓም (ኖቬምበር 11/2014)

Sunday, November 9, 2014

Friday, November 7, 2014

አቶ መለስ የሕይወታቸው ፍፃሜ የሆነባት የቤልጅየም ዋና ከተማ ብራስልስ ከመላው አውሮፓ በመጡ ኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ሰልፍ ተናጠች (ቪድዮ)

እስክንድር ይፈታ! በቀለ ገርባ ይፈታ! ርዕዮት ትፈታ! አብርሃ ደስታ ይፈታ! ብሎገሮች ይፈቱ!



ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

Tuesday, November 4, 2014

''ጥበበኛ ሲጎል ከያኒ ሲታጣ፣ሀገር ነው የሚጎል ቀዬ ነው ሚቀጣ ባንዲራ ነው ሚፈዝ መዝሙር ቅጥ የሚያጣ'' የአርቲስት ሜሮን ጌትነት ግጥም የትውልዱን በግፍ መገፋት ያሳያል (ያዳምጡት)

''ጥበበኛ ሲጎል ከያኒ ሲታጣ፣

ሀገር ነው የሚጎል ቀዬ ነው ሚቀጣ፣

ባንዲራ ነው ሚፈዝ መዝሙር ቅጥ የሚያጣ '' የአርቲስት ሜሮን ጌትነት ግጥም የትውልዱን በግፍ መገፋት ያሳያል (ያዳምጡት)



ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

ሰማያዊ ፓርቲን ጨምሮ የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የመጀመሪያ ዙር ህዝባዊ ትግል ፕሮግራሙን ይፋ አደረገ የ24 ሰዓት (የአዳር) የተቃውሞ ሰልፍ ተጠርቷል

 ነፃነት፣ፍትህ እና እኩልነት የሚመጣው  በእያንዳንዱ ግለሰብ ትከሻ ነው።
ፎቶ - ዳሎል ኢትዮጵያ

  •  የ24 ሰዓት (የአዳር) የተቃውሞ ሰልፍ ተጠርቷል
  • ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም 9 ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመሰረቱት ትብብር ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል ለአንድ ወር የሚቆይ የመጀመሪያ ዙር የህዝባዊ ትግል ፕሮግራሙን ዛሬ ጥቅምት 25/2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ይፋ አደረገ፡፡

‹‹ነጻነት በሌለበት ፍትሃዊ ምርጫ የማይታሰብ በመሆኑ የተዘጋውን በር ለመክፈት የ‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ› በሚል የፕሮግራም መርሃ ግብር ለመክፈት ወስኖ የመጀመሪያው ዙር እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ከተማ ለማድረግ›› እንዳዘጋጀ ያሳወቀው ትብብሩ የትግሉ ዓላማ ፍትሃዊ ምርጫ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን ገልጾአል፡፡
‹‹ምርጫ ቦርድ ለገዥው ፓርቲ ያለውን ወገናዊነትና ጉዳይ አስፈጻሚነት ፍንትው አድርጎ አሳይቷል›› ያለው መግለጫው በመጀመሪያ ዙር የአንድ ወር ፕሮግራሙ 6 ዋና ዋና ተግባራትን ለመፈጸም ዝርዝር እቅዶችን አውጥቶ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ በህዳር ወር የሚያከናውናቸው ተግባራትም፡-
1. በቤተ እምነት ጸሎት እንዲደረግና ጥሪ ማቅረብና አማኞች እንደየ እምነታቸው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማድረግ
2. የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማድረግ
3. የተቃውሞ ድምጽ ማሰማት (ሰላማዊ ሰልፍ)
4. ለመንግስት ተቋማት ደብዳቤ ማስገባት
5. በምርጫ ዙሪያ የፓናል ውይይቶችን ማድረግና
6. የህዝብን ተሳትፎ ማበረታታትና ድጋፍ ማሰባሰብ እንደሆኑ በመግለጫው አሳውቋል፡፡
ከእቅዶቹ መካከልም በሶስት ተከታታይ እሁዶች በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች 3 የአደባባይ ስብሰባዎች እንደሚኖሩ፣ በመጨረሻው መርሃ ግብርም ህዳር 27ና 28 በፕሮግራሙ ማጠቃለያነት የ24 ሰዓት (የውሎና የአዳር) የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚደረግ የትብብሩ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ገልጸዋል፡፡
በገዥው ፓርቲና በምርጫ ቦርድ ጥምረት ይፈጸማል ያለውን ህገ ወጥ ተግባር በመታገል ለሰላማዊ ትግሉ አወንታዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት እስከመጨረሻው በፅናት ለመቆም መዘጋጀቱን የገለጸው ትብብሩ በአገር ቤትና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ በትብብሩ ሂደት ቆይተው እስካሁን ያልፈረሙና ሌሎች ፓርቲዎች እና የዓለም አቀፉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ዝርዝሩን ከሰማያዊ ፓርቲ ልሳን ''ነገረ ኢትዮጵያ'' ይመልከቱ 

ጥቅምት 25/2007 ዓም (ኖቬምበር 4/2014)

Saturday, November 1, 2014

አሁን ቡኪናፋሶን ያየ በስልጣን ይቀልዳል? (የጉዳያችን ምጥን)


የቡክናፋሶ ዋና ከተማ ኦጋዱጉ ወጣቶች አምባገነኑን መሪ ካባረሩ በኃላ በድል ስሜት ውስጥ (ፎቶ ኤ ኤፍ ፒ)
Women pose with an armored personnel carrier in Ouagadougou. (Issouf Sanogo/AFP/Getty Images)

በልጅነቴ የሰሞኑ የቡክናፋሶው ''የጥቁር አብዮት'' ሳይነሳ፣ድሮ አክስቴ የነገረችኝን ተረት እንዲህ አስታውሰዋለሁ -

በድሮ ጊዜ አንድ በጣም ሃብታም ሰው ነበር።ይህ ሰው ታድያ ሁል ጊዜ የሞቱ ነገር ያሳስበው ነበር።እናም ለምን ሞትን አግኝቼ ምልክት ሳይሰጥ እንዳይወስደኝ አልነግረውም ብሎ አሰበ። ያሰበው አልቀረም ሞትን 

''ካንተ ጋር ቃል ኪዳን መፈፀም እፈልጋለሁ'' አለው።
''የምን ቃል ኪዳን?'' ሞት ጠየቀ።
''እኔ ሳላውቅ እና ቀድመህ ሳታስጠነቅቀኝ እንዳትወስደኝ'' አለ ሀብታሙ ሰው።
ሞት ''ቃል ለምድር ለሰማይ ሳልነግርህ አልወስድህም'' ማለለት።ሀብታሙ ሰው ተደሰተ።ተዝናና፣በላ፣ ጠጣ፣ደስም አለው።

በዛው ሰሞን የሐብታሙ ሰው አንዲት የታመመች ግልገል በግ መሞቷን ከውጭ ሲገባ ነገሩት።
''አሁን ስንት ከብት የሞላኝ ሰው ቁም ነገር ብላችሁ ስለ አንዲት ግልገል ትነግሩኛላችሁ?'' ብሎ ሳቀ።
ከሳምትን በኃላ ከማዶ ሀገር ያሉ ሽማግሌ መሞታቸው ተሰማ። ከሕዝቡ ጋር ከንፈር እየመጠጠ እጆቹን ወደኃላ አጣምሮ በእርጋታ በመራመድ አስከሬኑን ሸኘ በመጨረሻም ቀበረ።

 ከሶስት ቀን በኃላ ጎረቤቱ ታመው መሞታቸውን ሰማ።አዘነ፣ልጆቻቸው አሳዘኑት፣እየተመላለሰ እናታቸውን አፅናና።።ከስድስት ወር በኃላ የሚወደው አገልጋይ ሞተ።አዘነ ግን ለብዙ ጊዜ ይታመም ስለነበር ህመሙን አማረረ።
ከአመት በኃላ እራሱ ታመመ አልጋ ላይ አንድ ወር ተኛ በመጨረሻ ሞት ሊወስደው መጣ።
ሀብታሙ ሰው ሞትን ''አዝናለሁ ሳልነግርህ አልመጣም ብለህ ቃልህን አጥፈህ መጣህ?'' አለው።

ሞት መለሰ ''ቃሌን አላጠፍኩም።ከአመት በፊት ነግሬሃለሁ'' አለ።
ሀብታሙ ሰው እራሱን ያዘ ''ውሸት! ውሸት!" አለ። 
ሞት እረጋ ብሎ ይዞ የሚሄድበትን ማሰርያ ገመድ እያዘጋጀ እንዲህ አለ ''እኔ አልዋሸሁም።መጀመርያ ግልገልህን በመውሰድ ነገርኩህ፣ቀጥዬ ማዶ የሚኖሩትን ወዳጅህን በመውሰድ አስጠነቀኩህ፣ በመቀጠል ጎረበትህን እና አገልጋይህን አከታተልኩ።በእዚህ ሁሉ መሃል ግን አንተ አልነቃህም።እራስህንም ለማስተካከል አልሞከርክም።እስኪ አሁን የእኔን ጥፋት ንገረኝ'' አለ ሞት ለመውሰድ እግሩን እያሳሰረ።

አሁን የቡክናፋሶን የ27 ዓመት ማስፈራራት በሰዓታት የህዝብ አመፅ መናድ ያየ በስልጣን ይቀልዳል? ከቡክናፋሶ በፊት በቱንስያ፣በአልጀርያ፣በግብፅ የህዝብ ማዕበል ያየ ''አልሰማሁም ነበር'' ማለት ይችላል? እርግጥ ነው ሞትና ስልጣን አንድ አይደሉም።ግን ለአምባገነኖች ከስልጣን መውረድ ከሞት የከበደ ስለሚሆንባቸው አንድ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ።

ጉዳያችን 
ጥቅምት 23/2007 ዓም (ኖቬምበር 2/2014) 

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...