ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, November 26, 2014

ቅኝ ግዛት እና ሕዝቡን ቢራ እንዲጠጣ ማበረታታ ምን እና ምን ነበሩ? ዳቦ ሳንጠግብ እና የምናነበውን ጋዜጣ ሁሉ ዘግተው አዕምሯችንን እያደነዘዙ የቢራ ፋብሪካ መደርደር ምን ይባላል?
በባዕዳን በቅኝ ግዛት ተይዘው የነበሩ ሀገሮች ሁለት ዋና ዋና ሀብታቸውን አጥተዋል።( በነገራችን ላይ በባዕዳን ቅኝ ግዛት የተያዙቱኑ ነው ያልኩት እንጂ ፕሬዝዳንት መሆን ያማረው ሁሉ ቅኝ ግዛት ነበርኩ እያለ የእራሱን እና የህዝቡን ክብር ገደል የሚጨምረውን አይመለከትም።)
እነኝ በቅኝ ግዛት የተያዙ ሃገራት ካጡት ሀብት መካከል የመጀምርያው ምጣኔ ሀብታቸው የባዕዳን ገዢዎቻቸውን ምጣኔ ሀብት እንዲያገለግል ተደርጎ መዋቀሩ  ሲሆን ሌላው የነበራቸውን ከቀደሙት የወረሱት ባህል እና የአኗኗር ዘይቤ ነው።ሃገራቱ እንዲያመርቱ የተደረጉትም ሆነ ወደውጭ የሚልኩት ምርት የገዢዎቻቸውን የጥሬ ዕቃ ፍላጎት ብቻ ላይ እንዲያተኩር ተደረገ።ዛሬ እነ ኬንያ፣ታንዛንያ እና ዑጋንዳን ብንመለከት ሃገራቱ ለንግድ የሚሆኑ የእርሻ ምርታቸው በወቅቱ እንግሊዝ ትፈልገው ከነበረው ምርት ጋር ብቻ እንዲቆራኝ የተደረገ ነው።

በአንፃሩ ደግሞ አውሮፓውያን በእነርሱ ክህሎት ብቻ የሚሰራውን ምርት ቅኝ ተገዢዎች እንዲቀበሉት አደረጉ።አፍሪካውያን ቡና ከመጠጣት ቢራ እንዲጠጡ እና እንዲለማመዱ ተደረጉ።እንድያውም አንዳንድ ቦታ ቢራ ለመጠጣት ያልደረሱ ታዳጊዎች ሁሉ በሰሩት ሥራ ልክ የሚከፈላቸው ቢራ የነበረበት ወቅት ነበር።የቢራ መጠጥ ከቅኝ ግዛት በኃላም በሰፊው ተለመደ።ብርጭቆ ተጋጨ።በዓል የሚከበረው በቢራ እና በቢራ ብቻ ሆነ። ዛሬ በዑጋንዳ እና በታንዛንያ ቢራ የሚጠጣውን ያክል ቡና አይጠጣም።በአውሮፓ ደግሞ ቡና የሚጠጣውን ያክል ቢራ አይጠጣም።አፍሪካውያን የሚጠጡበት ቢራ በትንሹ ግማሽ ሊትር የሚይዝ ነው።አውሮፓውያን ቡና የሚጠጡበት ስኒ የሻይ ብርጭቆ ያክላል።ቡናው ለንቃት ወደ አውሮፓ ይላካል።

የመንገድ እና ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች ዝርጋታ የቅኝ ገዢዎች የሰሩት አሁንም የሀገራቸውን ምጣኔ ሃብት እንዲገነባ ነው።ለምሳሌ የወደብ ቦታዎች የሚመረጡት የሀገራቱን አንጡራ ሀብት በተገቢ መልክ ለማውጣት ከማመቸቱ አንፃር እንጂ ለሕዝብ ከሚሰጠው ጥቅም አንፃር አይደለም።በምዕራብ አፍሪካ እና በምስራቅ አፍሪካ በቅኝ ገዥዎች የተሰሩትን ወደቦች መመልከት ይቻላል።

ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ካልተገዙ ጥቂት ሃገራት አንዷ ነች።ኢትዮጵያውያንን ቡና አትጠጡ ቢራ ብቻ ጠጡ ብሎ ያስገደዳቸው ቅኝ ገዢ አልነበረባቸውም።እድሜ በደማቸው ሀገራቸውን አስከብረው ለኖሩት አባቶቻችን እና እናቶቻችን።እኛ እንደ ብዙ የአፍሪካ ሃገራት ዋና ከተማችንን የቅኝ ገዢዎች አልመረጡልንም። አለመምረጥ ብቻ አይደለም የከተሞቻችን ህንፃዎች እና መንገዶች በአብዛኛው የተሰሩት በእራሳችን መሀንዲሶች ነው።የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃቤት ፕላን ሲቀርብ አንድ ፈረንሳዊ መሃንዲስ ባለ ብዙ ፎቅ እንዲሆን አድርጎ አቅርቦ ነበር።በኃላ ግን ኢትዮጵያዊው መሃንዲስ (ስማቸውን አላስታውስም) ወደ ንጉሡ ቀርበው ''ይህንን ያህል ፎቅ ብዙ ሕዝብ በእየለቱ በሚወጣበት እና በሚገባበት ህንፃ ላይ አይሆንም።ይህ ማለት ከሀገሩ ሊፍት እንድናስገባ ሊያደርገን ነው።ከእዝያ ይልቅ ወደጎን ነው መለጠጥ ያለበት'' ብለው ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት ማዘጋጃ ቤቱ ወደጎን እንዲሰፋ ተደረገ።በእዚህም ብዙ ሕዝብ ለጉዳዩ በቀላሉ ለመውጣት እና ለመግባት ቻለ።ቅኝ ገዢዎች መሰረተ ልማቱን እንዴት ለሀገራቸው ኢንዱስትሪዎች መጋቢ እንዲሆን አድርገው እንደሚቀርፁ የሚያመላክት አንዱ ማሳያ ነው የማዘጋጃ ቤቱ ህንፃ ጉዳይ።
ቅኝ ግዛት መዘዙ ብዙ ነው።ጉዳቱ የሚታወቀው ትውልድ በተቀያየረ ቁጥር ነው።

ዛሬ ግን ያልገባኝ ጉዳይ በኢትዮጵያ የቢራ ፋብሪካ እንደ አሸን መፍላት ነው።በምግብ እራሷን ያልቻለች ሃገር ለምንድነው የእህል ቀበኛ የቢራ ፋብሪካዎች እንዲበዙላት የተደረገው? ብዙ ተመጣጣኝ ምግብ ማቀናበርያ በምትፈልግ ሀገር ውስጥ ለምን ለቢራ ፋብሪካ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲወጣ ይደረጋል? በኑሮ ውድነት በሚንገላታ ሕዝብ መካከል አማላይ የሆኑ የቢራ ማስታወቅያዎች ምን ይሰሩለታል? ቢራ ከሀገር ይጥፋ አይባልም።ሰው እንደ ምርጫው እና ፍላጎቱ ሊጎነጭ ይችላል።ግን እንደ ፖሊሲ ትኩረት ተሰጥቶት ሊደከምበት አይገባም።የኢህአዲግ የንግድ ድርጅቶች ሳይቀሩ የቢራ ምርት ላይ በከፍተኛ ትኩረት ሲሰሩ ይታያል።የቢራ ፋብሪካ መመስረት ብቻ ሳይሆን የማስፋፋት ሥራ በጣም እየተሰራበት ነው።በቅርቡ ወደ ገበያ ሊመጣ ነው የተባለው የራያ ቢራን ጨምሮ 8 የቢራ ፋብሪካዎች አሉ።እነርሱም አዲስ ቢራ፣በደሌ ቢራ፣ሐረር ቢራ፣ዳሸን ቢራ፣ሜታ  ቢራ፣ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ፣ባቲ ቢራ  እና በቅርቡ ሥራ የሚጀምረው ራያ ቢራ ናቸው።በኢትዮጵያ ያሉት የቢራ ፋብሪካዎች የማስፋፋቱ ሥራ ላይ የተጠመዱት የስርዓቱ የኢኮኖሚ መዋቅሮች ብቻ ሳይሆኑ በቦርድ መሪነት ለምሳሌ የራያ ቢራ ፋብሪካን ብንወስድ የኢህአዲግ/ወያኔ የሰራዊቱ አዛዦች ይገኙበታል።ዛሬ ሕዳር 17/2007 ዓም የወጣው ጋዜጣ የራያ ቢራ ፋብሪካ መከፈትን አስመልክቶ ባወጣው ዜና ላይ እንዲህ የሚል ይገኝበታል።

''አክሲዮን ማኅበሩን በቦርድ ሊቀመንበርነት እየመሩ ያሉት አቶ ኃይሌ አስግዴ ሲሆኑ፣ ምክትላቸው ደግሞ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ ናቸው፡፡ ሁለቱም አመራሮች በራያ ቢራ አመራር ውስጥ ያሉ ሲሆን፣ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኃይሌ ደግሞ የቦርድ አባል መሆናቸው ይታወቃል'' ሪፖርተር ጋዜጣ 

ባጠቃላይ ይህንን ማለት ይቻላል። ፋብሪካዎቹ የስራ ዕድል ይፈጥራሉ።ግን የቢራ ፋብሪካዎች እንደ አሸን መፍላት እህልም ሆነ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ከሚገመተው በላይ ይበላሉ።ፋብሪካ ይኑረን። ግን አዋጪ እና ሌሎች አንገብጋቢ ፋብሪካዎች ለምን አይበልጡብንም? ነው ጥያቄው። ደግሞስ  ቅኝ ገዢዎች ከብዙ ጥቅማቸው አንፃር አደረጉት።እኛ ቅኝ ያልተገዛነውስ? ኢህአዲግ/ወያኔ በወሎ እና በጎንደር ብቻ አዳዲስ የቢራ ፋብሪካዎችን ከፍቷል።አንድ ቢራ ለመጥመቅ ከፍተኛ የምግብ እህል ፍጆታ እና ብዙ ሺህ የተጣራ ንፁህ ውሃ እንደሚፈልግ ይታወቃል።ቅኝ ገዢዎች አፍሪካውያን ቢራ እየጠጡ እንዲናውዙ ማድረግ አንዱ የተሳካላቸው  ስራ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።የኛ ገዢዎች በየመንደሩ የቢራ ፋብሪካ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ እያወጡ የሚከፍቱልን ለምንድን ነው? ዳቦ ሳንጠግብ እና የምናነበውን ጋዜጣ ሁሉ ዘግተው አዕምሯችንን እያደነዘዙ የቢራ ፋብሪካ መደርደር ምን ይባላል? ከየት የተማሯት ''ጥበብ'' ነች?  ለናሙናነት 

ጉዳያችን
ህዳር 18/2007 ዓም (መጋቢት 4/2006 ዓም ወጥቶ የነበረ)

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...