ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, November 20, 2014

የሃና ጉዳይ የፖለቲካው ብልሹነት ውጤት ነው።የፖለቲካው ብልሹነት ሌሎች ብዙ ሃናዎች እንዲደፈሩ መንገድ ያመቻቻል። እንዴት? (የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ)


መንደርደርያ 
ከጥቂት ቀናት በፊት በአዲስ አበባ የ17 ዓመት ወጣት በአውሬ ለበስ ወጣቶች ተደፍራ ሕይወቷ ማለፉ መሰማቱ የብዙዎቻችንን ልብ ያደማ ጉዳይ ነበር።ጉዳዩ የአውሬለበስ ግለሰቦች ተግባር መሆኑ ባያከራክርም።ማህበረሰባችን እና የምድሪቱ ሰው ሰራሽ ሕግ በደንብ ልፈተሹ ይገባል።ግለሰቦች በያሉበት ሊብከነከኑ ይችላሉ።ሆኖም ግን እንደ አንድ ሕብረተሰብ ለመንቀሳቀስ እና ለማኅበራዊ ቀውሶች መፍትሄ ለመስጠት ነፃነት የተሞላበት አካባቢ የግድ ይላል።በታፈነ ሕብረተሰብ ውስጥ አፋኙ ስርዓት  ለችግሩ እራሱን ተጠያቂ ሳያደርግ።እንደ ጵላጦስ ''ከደሙ ንፁህ ነኝ'' ማለት አይችልም። ለምን?

በሀገራችን እያንዳንዱ የማኅበራዊ ለውጦች፣አደጋዎች እና ቀውሶችን እያጠና በወቅቱ  በማኅበራዊ ተቋማት አማካይነት እርማት እንዲወሰድ የመገናኛ ብዙሃንም ሆኑ የፖለቲካ አመራሩን የሚዘውረው (ኢህአዲግ/ወያኔ ) አንዳች ነገር አያደርጉም።እነኝህን ተቋማት በማፍረስ ላይ ግን ኢህአዲግ/ወያኔ ቀዳሚ ነው።የሃና ጉዳይ ምን ያህል የፖለቲካ አመራሩ የማኅበራዊ ደህንነት እና የፀጥታ ዋስትና ያለመስጠቱ አይነተኛ አመላካች ነው? ይህንን በምሳሌ እንረዳ-

ምሳሌ - 1/ 

ኢኮኖሚያችን ፖሊሲው፣አቅጣጫው እና ግቡ መጠናት ያለበት ገለልተኛ በሆኑ ምሁራን ነበር።ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ከአስር አመታት በፊት ጥሩ እንቅስቃሴ ያደርግ የነበረ መሆኑ ይታወቃል።ዛሬ እንቅስቃሴው የት ነው? አመታዊ ሪፖርቱን የሀገር ውስጥ የዜና አውታሮች ያሰማሉ? ዛሬ የኢህአዲግ/ወያኔን ሪፖርት ብቻ ነጋ ጠባ ሕዝብ እንዲሰማ ለምን ተገደደ? የሲቪል ተቋማትን የማፈን ተግባር አካል አይደለም?

ምሳሌ 2/ 

የኢትዮጵያ ሴት የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር በርካታ ስራዎችን የሰራ ነበር።በአዲሱ የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አዋጅ ስንት ሚልዮን ብር ነው ፍርድ ቤት አግዶበት አቅሙን ያሽመደመደው? በሌላው ሀገር በአፍሪካም ቢሆን የእዚህ አይነት ሲቪል ተቋማት ሪፖርቶች ፓርላማ ድረስ ቀርበው ጥናታቸውን የማቅረብ፣ሕጎች እንዲስተካከሉ የማሳየት እና የማማከር ሥራ ይሰራሉ።ይሄው ድርጅት በሴት እህቶቻችን ላይ የሚደርሰውን የመደፈር አደጋ ለማጋለጥ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ንቅናቄ ለመፍጠር የጣረ ነበር።
ኢህአዲግ/ወያኔ እርሱ ያልጠረበው እንጨት እንጨት አይደለምና ገንዘቡን በፍርድ ቤት አገደው።ዛሬ ባለስልጣናቱም ሳይቀር የአዞ እንባ ያፈሳሉ።አሰራሩ እነ ሃና ሲደፈሩ ይጮሃል ሌሎች ብዙ ሃናዎች እንዲደፈሩ ግን መንገድ ያመቻቻል።

ባጠቃላይ 

ኢትዮጵያ ውስጥ የማኅበራዊ ቀውስን ቀድመው አጥንተው ተገቢው እርምጃ ሕዝብ እንዲወስድ የሚያደርጉ ድርጅቶች በኢህአዲግ/ወያኔ ተመትተዋል።የእዚህ አይነት ድርጅቶች ቢኖሩ ኖሮ የህዝቡን ማህበራዊ ቀውስ ደረጃ በጥናት እያሳዩ ባስደነገጡን እና ሕዝብ በመረጃ ተመስርቶ ወደ መፍትሄው እንዲሄድ በገፉት ነበር።ይህ ብቻ ሳይሆን በስልጣን ወንበር ላይ የተፈናጠጡትንም መንገድ ባሳዩዋቸው ነበር።ግን አልሆነም።ከእዚህ በከፋ ደረጃ ሕዝብ የሚሰማቸውን የሃይማኖት ተቋማት ሳይቀር በፖለቲካ አጅሎ የሃይማኖታዊ ችግሮችን ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ ጣጣዎችን እንዳይፈቱ ያደረጋቸው አሁንም ፖለቲካውን የሚዘውረው ኢህአዲግ/ወያኔ ነው።

በመቶ ሺህ የሚቆጠር የጎዳና ተዳዳሪ በኢትዮጵያ ከተሞች የተርመሰመሰው ባለፉት 23 አመታት ነው።ሴቶች እህቶቻችን የመደፈራቸው ዜና የሳምንት ክስተት የሆነው ባለፉት 23 አመታት ነው።ጫት መቃምያ በት በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት በር ላይ የተከፈተው ባለፉት 23 አመታት ነው።የሽሻ ቤቶች ትልልቅ ሕንፃዎችን ሁሉ መዳረሻቸው ያደርጉት ባለፉት 23 አመታት ነው።ባጭሩ የማኅበራዊ ቀውሱ መነሻ በስልጣን ላይ የተፈናጠጠው የኢህአዲግ/ወያኔ የአፈና ውጤት ነው።የፖለቲካ አመራሩ እና ፖሊሲው ማኅበራዊ ቀውሱን አፋጥኖታል።መጨረሻው የት እንደሆነ አይታወቅም።

ጉዳያችን 
ህዳር 11/2007 ዓም  (ኖቬምበር 20/2014)

No comments:

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል። በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡  ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?  የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመ...